በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ከሁሉ አስቀድመህ መንግሥቱን ፈልግ’

‘ከሁሉ አስቀድመህ መንግሥቱን ፈልግ’

ምዕራፍ አሥራ አንድ

‘ከሁሉ አስቀድመህ መንግሥቱን ፈልግ’

1. (ሀ) ኢየሱስ አድማጮቹ በሕይወታቸው ውስጥ መንግሥቱን አስቀድመው እንዲፈልጉ አጥብቆ ያሳሰባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

ከ1,900 ዓመታት በፊት ኢየሱስ በገሊላ በሰጠው ንግግር ላይ አድማጮቹን “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ” ሲል አጥብቆ አሳስቧቸው ነበር። ይሁንና ክርስቶስ ንጉሣዊ ሥልጣኑን የሚረከበው ገና ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ሆኖ ሳለ እንዲህ ያለ አጣዳፊ ማሳሰቢያ የሰጠው ለምንድን ነው? ይሖዋ ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥና ለምድር ያለውን ታላቅ ዓላማ ለመፈጸም መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀመው በዚህ መሲሐዊ መንግሥት አማካኝነት ነው። የእነዚህን ነገሮች አስፈላጊነት በሚገባ የተገነዘበ ማንኛውም ሰው በሕይወቱ ውስጥ ለመንግሥቱ ቅድሚያውን ቦታ ይሰጣል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይህን ማድረግ አስፈላጊ ከነበረ ክርስቶስ ንጉሣዊ ሥልጣኑን በያዘበት በአሁኑ ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ እንደሚሆን ምንም አያጠያይቅም! እንግዲያው አኗኗሬ የአምላክን መንግሥት እንደማስቀድም ያሳያል? ብሎ ራስን መጠየቁ ተገቢ ነው።—ማቴዎስ 6:33

2. ሰዎች በአብዛኛው የሚያሳድዷቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

2 በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ መንግሥቱን በማስቀደም ላይ ናቸው። ራሳቸውን ለይሖዋ በመወሰንና ሕይወታቸው የእሱን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ያተኮረ እንዲሆን በማድረግ የዚህን መንግሥት አገዛዝ እንደሚደግፉ ያሳያሉ። በሌላ በኩል ግን አብዛኛው የሰው ዘር ፍላጎቱ በዓለማዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው። ሰዎች ገንዘብን እንዲሁም ገንዘብ ሊያስገኛቸው የሚችላቸውን ቁሳዊ ነገሮችና ተድላዎች ያሳድዳሉ። ወይም ደግሞ በሥራው ዓለም ስኬት ለማግኘት ብዙ ይደክማሉ። ብዙውን ጊዜ የሚያስቡት ስለ ራሳቸው፣ ስለ ቁሳዊ ነገሮችና ስለ ተድላ እንደሆነ አኗኗራቸው በግልጽ ያሳያል። በሕይወታቸው ውስጥ ለአምላክ ሁለተኛ ቦታ ይሰጣሉ፤ ያውም ካመኑበት።—ማቴዎስ 6:31, 32

3. (ሀ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ምን ዓይነት ሀብት እንዲፈልጉ አበረታቷቸዋል? ለምንስ? (ለ) ስለ ቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ መጨነቅ የማያስፈልገው ለምንድን ነው?

3 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ” የሚል ምክር ሰጥቷቸው ነበር። ምክንያቱም እንዲህ ያለው ሀብት ዘለቄታ የለውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን በማገልገል ‘በሰማይ ለራሳቸው ሀብት እንዲያከማቹ’ መክሯቸዋል። ትኩረታቸውንም ሆነ ሙሉ ኃይላቸውን የአምላክን ፈቃድ በማድረጉ ሥራ ላይ በማዋል “ጤናማ” ወይም ቀና የሆነ ዓይን ይዘው እንዲኖሩ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። “እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም” ሲል ነግሯቸዋል። ይሁንና አስፈላጊ የሆኑ ቁሳዊ ነገሮችን ማለትም ምግብን፣ ልብስንና መጠለያን በተመለከተስ? ኢየሱስ “አትጨነቁ” የሚል ምክር ሰጥቷል። ተከታዮቹ ወፎችን እንዲመለከቱ አሳሰባቸው፤ ወፎችን አምላክ ይመግባቸዋል። ከአበቦችም እንዲማሩ አበረታታቸው፤ አበቦችን አምላክ ውብ አድርጎ አልብሷቸዋል። የማሰብ ችሎታ ያላቸው የይሖዋ ሰብዓዊ አገልጋዮች ከእነዚህ አይበልጡም? ስለዚህ ኢየሱስ “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ [አስፈላጊ ነገሮች] ይጨመሩላችኋል” ብሏል። (ማቴዎስ 6:19-34) የምታደርጋቸው ነገሮች እንዲህ ያለ እምነት እንዳለህ ያሳያሉ?

የመንግሥቱ እውነት በሌሎች ነገሮች እንዲታነቅ አትፍቀድ

4. አንድ ሰው ለቁሳዊ ነገሮች ከፍተኛ ግምት የሚሰጥ ከሆነ ውጤቱ ምን ይሆናል?

4 አንድ ሰው ለራሱም ሆነ ለቤተሰቡ የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት መጨነቁ ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ስለ ቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ የሚጨነቅ ከሆነ አስከፊ ውድቀት ሊደርስበት ይችላል። በአምላክ መንግሥት አምናለሁ ቢልም እንኳ በልቡ ሌሎች ነገሮችን የሚያስቀድም ከሆነ የመንግሥቱ እውነት ይታነቃል። (ማቴዎስ 13:18-22) ለምሳሌ አንድ ጊዜ የሕዝብ አለቃ የሆነ አንድ ሀብታም ወጣት ኢየሱስን “የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል?” ሲል ጠይቆት ነበር። ሰውየው ንጹሕ ሥነ ምግባር ያለውና ለሌሎች መልካም ያደርግ የነበረ ቢሆንም ለቁሳዊ ሀብት ከፍተኛ ፍቅር ነበረው። ስለሆነም ቁሳዊ ሀብቱን ትቶ የክርስቶስ ተከታይ መሆን አልቻለም። በዚህ ምክንያት ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ መንግሥት ገዥ የመሆን አጋጣሚ አመለጠው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው!” ሲል ተናገረ።—ማርቆስ 10:17-23

5. (ሀ) ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን በምን ነገሮች እንዲረካ አበረታቶታል? ለምንስ? (ለ) ሰይጣን ‘የገንዘብን ፍቅር’ አደገኛ ወጥመድ አድርጎ የሚጠቀምበት እንዴት ነው?

5 ከዚያ ብዙ ዓመታት ቆይቶ ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ ሀብታም የንግድ መናኸሪያ በነበረችው በኤፌሶን ከተማ ለነበረው ለጢሞቴዎስ ደብዳቤ ጻፈለት። ጳውሎስ “ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለም፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም። ነገር ግን ምግብና ልብስ ካለን፣ ያ ይበቃናል” ሲል አሳስቦታል። ለራስም ሆነ ለቤተሰብ “ምግብና ልብስ” ለማግኘት ሲባል መሥራት ምንም ስህተት የለውም። ሆኖም ጳውሎስ “ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ግን ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ፣ እንዲሁም ሰዎችን ወደ መፍረስና ወደ ጥፋት ወደሚያዘቅጠው ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት ይወድቃሉ” ሲል አስጠንቅቋል። ሰይጣን የሚጠቀምበት ዘዴ የረቀቀ ነው። መጀመሪያ ላይ አንድን ሰው ቀላል በሆኑ መንገዶች ለማታለል ይሞክር ይሆናል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ከበድ ያሉ ተጽዕኖዎች ሊያመጣበት ይችላል። ምናልባትም ግለሰቡ የሥራ እድገት ወይም ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝ የተሻለ ሥራ ያገኝ ይሆናል። ነገር ግን አዲሱ ሥራ በፊት ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ያውለው የነበረውን ጊዜ ሊሻማበት ይችላል። ካልተጠነቀቅን “የገንዘብ ፍቅር” ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ከመንግሥቱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ጉዳዮች ሊያንቅብን ይችላል። ጳውሎስ ይህን ሁኔታ “አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጕጕት የተነሣ ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል” ሲል ገልጾታል።—1 ጢሞቴዎስ 6:7-10

6. (ሀ) በፍቅረ ንዋይ እንዳንጠመድ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) ዛሬ ካለው የኢኮኖሚ ሁኔታ አንጻርም እንኳ ቢሆን ምን ትምክህት ሊያድርብን ይችላል?

6 ጳውሎስ ለክርስቲያን ወንድሙ ለጢሞቴዎስ ካለው ልባዊ ፍቅር የተነሳ “ከዚህ ሁሉ ሽሽ” እንዲሁም “መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል” ሲል አሳስቦታል። (1 ጢሞቴዎስ 6:11, 12) በዙሪያችን ባለው ዓለም የፍቅረ ንዋይ አኗኗር ተታልለን እንዳንወሰድ ከፈለግን ከልብ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። ነገር ግን ከእምነታችን ጋር በሚስማማ መንገድ ለመመላለስ የተቻለንን ሁሉ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ አይተወንም። የቱንም ያህል ኑሮ ቢወደድና ሥራ አጥነት ቢስፋፋም የሚያስፈልገንን እንድናገኝ ያደርጋል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ ‘ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም’ ብሎአል። ስለዚህ በሙሉ ልብ፣ ‘ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?’ እንላለን።” (ዕብራውያን 13:5, 6) ንጉሥ ዳዊትም “ጐልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤ ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም” ሲል ጽፏል።—መዝሙር 37:25

የጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት ምሳሌ ይሆኑናል

7. ኢየሱስ ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ለደቀ መዛሙርቱ ምን መመሪያዎች ሰጥቷል? እነዚህ መመሪያዎች ተገቢ የነበሩትስ ለምንድን ነው?

7 ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ተስማሚ ማሠልጠኛ ከሰጣቸው በኋላ በእስራኤል ውስጥ ምሥራቹን እንዲሰብኩና “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” ብለው እንዲያውጁ ልኳቸው ነበር። ይህ እንዴት ያለ አስደሳች መልእክት ነበር! መሲሐዊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላቸው ነበር። ሐዋርያቱ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ለአምላክ አገልግሎት እያዋሉ ስለነበር አምላክ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው ሙሉ በሙሉ እንዲተማመኑ ኢየሱስ አሳስቧቸዋል። በመሆኑም “ለመንገዳችሁ በትር ቢሆን፣ ከረጢትም ቢሆን፣ እንጀራም ቢሆን፣ ገንዘብም ቢሆን፣ ሁለት ሁለት እጀ ጠባብም መያዝ አያስፈልጋችሁም። ከዚያ ከተማ እስከምትወጡ ድረስ መጀመሪያ በገባችሁበት በማንኛውም ቤት ቈዩ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 10:5-10፤ ሉቃስ 9:1-6) ይሖዋ እንግዳን ማስተናገድ ባሕላቸው በነበረው እስራኤላውያን አማካኝነት የሚያስፈልጋቸው ሁሉ እንዲሟላላቸው ያደርግ ነበር።

8. (ሀ) ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ለየት ያለ መመሪያ የሰጠው ለምንድን ነው? (ለ) ያም ሆኖ የኢየሱስ ተከታዮች በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባው ነገር ምን ነበር?

8 በኋላ ግን ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ሐዋርያቱ ከበፊቱ ለየት ያለ ሁኔታ እንደሚገጥማቸው አሳሰባቸው። ሥራቸውን በይፋ የሚቃወሙ ሰዎች ስለሚነሱ እስራኤላውያን እንደ ቀድሞው ተቀብለው ላያስተናግዷቸው ይችላሉ። ከዚህም በላይ የመንግሥቱን መልእክት ለአሕዛብ የሚናገሩበት ጊዜ ሩቅ አልነበረም። ስለዚህ በዚህ ወቅት “ኰረጆ” እና “ከረጢት” መያዝ ያስፈልጋቸው ነበር። ይሁን እንጂ አስፈላጊውን ምግብና ልብስ ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት አምላክ እንደሚባርክላቸው ተማምነው ከሁሉ በፊት የይሖዋን መንግሥትና ጽድቁን መፈለጋቸውን መቀጠል ነበረባቸው።—ሉቃስ 22:35-37

9. ጳውሎስ የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት ጥረት እያደረገም በሕይወቱ ውስጥ መንግሥቱን ያስቀደመው እንዴት ነው? ይህን ጉዳይ በተመለከተስ ምን ምክር ሰጥቷል?

9 ሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሱስን ምክር ሥራ ላይ በማዋል ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ጳውሎስ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ ይሰጥ የነበረው ለአገልግሎቱ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:24, 25) ለመስበክ ወደ አንድ አካባቢ ሲሄድ ድንኳን በመስፋት የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት ይጥራል። ሌሎች እንዲንከባከቡት አይጠብቅም ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 18:1-4፤ 1 ተሰሎንቄ 2:9) ይሁን እንጂ አንዳንዶች እሱን በእንግድነት ተቀብለው በማስተናገድና አንዳንድ ስጦታዎችን በመስጠት ፍቅራቸውን መግለጽ በሚፈልጉበት ጊዜ ይህን በምሥጋና ይቀበላል። (የሐዋርያት ሥራ 16:15, 34፤ ፊልጵስዩስ 4:15-17) ጳውሎስ ክርስቲያኖች ለመስበክ ብለው የቤተሰብ ኃላፊነቶቻቸውን ቸል ከማለት ይልቅ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንዲያከናውኑ አበረታቷቸዋል። በገዛ እጃቸው እንዲሠሩ፣ ቤተሰቦቻቸውን እንዲወዱና ለሌሎች እንዲያካፍሉ መክሯቸዋል። (ኤፌሶን 4:28፤ 2 ተሰሎንቄ 3:7-12) ከዚህም በላይ ትምክህታቸውን በቁሳዊ ሀብት ሳይሆን በአምላክ ላይ እንዲጥሉና በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች በሚገባ እንደተገነዘቡ በሚያሳይ መንገድ እንዲኖሩ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። ይህም ከኢየሱስ ትምህርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መንግሥቱንና ጽድቁን ማስቀደም ማለት ነው።—ፊልጵስዩስ 1:9-11

በሕይወትህ ውስጥ መንግሥቱን አስቀድም

10. መንግሥቱን ማስቀደም ሲባል ምን ማለት ነው?

10 የመንግሥቱን ምሥራች ለሌሎች ለመንገር በግለሰብ ደረጃ ምን ያህል ጥረት እናደርጋለን? ይህ በከፊል በሁኔታዎቻችን ላይ፣ በይበልጥ ግን በአድናቆታችን ጥልቀት ላይ የተመካ ነው። ኢየሱስ ‘ሌላ ምንም የምትሠሩት ነገር ከሌላችሁ መንግሥቱን ፈልጉ’ እንዳላለ አስታውስ። የመንግሥቱን አስፈላጊነት ያውቅ ስለነበር “ምንጊዜም መንግሥቱን ፈልጉ” በማለት የአባቱን ፈቃድ ገልጿል። (ሉቃስ 12:31 NW) ምንም እንኳን አብዛኞቻችን ለራሳችንና ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት መሥራታችን አስፈላጊ ቢሆንም እምነት ካለን በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው አምላክ የሰጠን የመንግሥቱ ሥራ ይሆናል። ይህንንም እያደረግን የቤተሰብ ኃላፊነታችንን ቸል አንልም።—1 ጢሞቴዎስ 5:8

11. (ሀ) ኢየሱስ የመንግሥቱን መልእክት በማዳረሱ ሥራ ሁሉም ሰው እኩል ተሳትፎ ሊኖረው እንደማይችል በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ሰው በሚያፈራው ፍሬ መጠን ላይ ለውጥ ሊያስከትሉ የሚችሉት ነገሮች ምንድን ናቸው?

11 አንዳንዶቻችን የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ ከሌሎች የበለጠ ጊዜ ማሳለፍ እንችል ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስ ስለተለያዩ የአፈር ዓይነቶች በተናገረው ምሳሌ ላይ ልባቸው እንደ መልካሙ አፈር የሆነ ሁሉ ፍሬ እንደሚያፈሩ ተናግሯል። ፍሬ የሚያፈሩት ምን ያህል ነው? የሰዎች ሁኔታ ይለያያል። በዚህ ረገድ ለውጥ ከሚያስከትሉት ነገሮች መካከል ዕድሜ፣ ጤንነትና የቤተሰብ ኃላፊነት ይገኙበታል። ሆኖም ልባዊ አድናቆት ካለን ብዙ መሥራት እንችላለን።—ማቴዎስ 13:23

12. በተለይ ወጣቶች ምን ጥሩ መንፈሳዊ ግብ እንዲያወጡ ይበረታታሉ?

12 በመንግሥቱ አገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ከፍ ማድረግ እንድንችል የሚረዱ ግቦች ማውጣት ጠቃሚ ነው። ወጣቶች ሁሉ ቀናተኛ ክርስቲያን የነበረው ወጣቱ ጢሞቴዎስ የተወውን ግሩም ምሳሌ አጥብቀው ሊያስቡበት ይገባል። (ፊልጵስዩስ 2:19-22) ትምህርታቸውን ሲጨርሱ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ከመሆን የተሻለ ምን ጥሩ ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ? ትልልቆችም ቢሆኑ ጥሩ መንፈሳዊ ግቦች ቢኖሯቸው ሊጠቀሙ ይችላሉ።

13. (ሀ) በግለሰብ ደረጃ በመንግሥቱ አገልግሎት ምን ያህል መካፈል እንደምንችል የሚወስነው ማን ነው? (ለ) አስቀድመን መንግሥቱን የምንፈልግ ከሆነ ምን ነገር እናረጋግጣለን?

13 የበለጠ መሥራት ይችሉ ነበር ብለን የምናስባቸውን ሰዎች ከመንቀፍ ይልቅ ሁኔታችን በሚፈቅደው መጠን አምላክን በተሟላ መንገድ ማገልገል እንድንችል በእምነት ተገፋፍተን ራሳችንን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (ሮሜ 14:10-12፤ ገላትያ 6:4, 5) በኢዮብ ላይ እንደታየው፣ ሰይጣን በዋነኝነት የሚያሳስበን ቁሳዊ ሀብት፣ የግል ምቾትና ደኅንነት እንደሆነ እንዲሁም አምላክን የምናገለግለው ለግል ጥቅማችን ስንል እንደሆነ አድርጎ ይከራከራል። ነገር ግን ከሁሉ አስቀድመን መንግሥቱን የምንፈልግ ከሆነ የሰይጣንን ውሸታምነት በማጋለጥ የበኩላችንን ድርሻ እናበረክታለን። እንዲህ በማድረግ በሕይወታችን ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ የያዘው የአምላክ አገልግሎት መሆኑን በተግባር እናስመሠክራለን። በዚህ መንገድ በቃላችንም ሆነ በድርጊታችን ለይሖዋ የጠለቀ ፍቅር እንዳለን፣ ሉዓላዊነቱን በመደገፍ በታማኝነት ከጎኑ እንደምንቆምና ሰዎችን እንደምንወድ እናረጋግጣለን።—ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4, 5፤ ምሳሌ 27:11

14. (ሀ) ለመስክ አገልግሎት ፕሮግራም ማውጣት ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በመስክ አገልግሎት ምን ያህል ተሳትፎ ያደርጋሉ?

14 በፕሮግራም መሥራት የበለጠ እንድናከናውን ሊረዳን ይችላል። ይሖዋ ራሱ ዓላማውን የሚፈጽምበት የተወሰነ ጊዜ አለው። (ዘፀአት 9:5፤ ማርቆስ 1:15) የምንችል ከሆነ በመስክ አገልግሎት በሳምንት ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ መካፈል የምንችልበት ፕሮግራም ብናወጣ ጥሩ ነው። በዓለም ዙሪያ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ረዳት አቅኚ ሆነው ምሥራቹን በመስበክ በየቀኑ ሁለት ሰዓት ገደማ ያሳልፋሉ። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች ደግሞ የዘወትር አቅኚ በመሆን በየቀኑ የመንግሥቱን መልእክት በማወጅ ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ ያሳልፋሉ። ልዩ አቅኚዎችና ሚስዮናውያን ለመንግሥቱ አገልግሎት ከዚህ የበለጠ ሰዓት ያውላሉ። በተጨማሪም ሁላችንም በማንኛውም አጋጣሚ ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሁሉ የመንግሥቱን ተስፋ መንገር እንችላለን። (ዮሐንስ 4:7-15) ኢየሱስ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት አስቀድሞ የተናገረ በመሆኑ ሁኔታችን በሚፈቅድልን መጠን በዚህ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ መጓጓት ይኖርብናል።—ማቴዎስ 24:14፤ ኤፌሶን 5:15-17

15. ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ 1 ቆሮንቶስ 15:58 ላይ የሚገኘው ምክር ወቅታዊ እንደሆነ የሚሰማህ ለምንድን ነው?

15 በሁሉም የምድር ክፍሎች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የየትኛውም አገር ነዋሪዎች ቢሆኑ በአንድነት በዚህ የአገልግሎት መብት ይሳተፋሉ። “ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ” የሚለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይሠሩበታል።—1 ቆሮንቶስ 15:58

የክለሳ ውይይት

• ኢየሱስ ‘ከሁሉ አስቀድማችሁ መንግሥቱን ፈልጉ’ ሲል ምን ነገር ሁለተኛ ቦታ መያዝ እንዳለበት ማመልከቱ ነበር?

• ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች ስለማሟላት ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው? አምላክስ ምን እርዳታ ያደርግልናል?

• በየትኞቹ የመንግሥቱ አገልግሎት ዘርፎች መካፈል እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 107 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ በየትኛውም አገር የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ምሥራቹን በመስበክ ላይ ናቸው