በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትንሣኤ ተስፋ የሚሰጠው ብርታት

የትንሣኤ ተስፋ የሚሰጠው ብርታት

ምዕራፍ ዘጠኝ

የትንሣኤ ተስፋ የሚሰጠው ብርታት

1. የትንሣኤ ተስፋ ባይኖር ኖሮ የሙታን ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን ነበር?

የቅርብ ወዳጅ ወይም ዘመድ ሞቶብሃል? ትንሣኤ ባይኖር ኖሮ በሞት ከተለየህ ሰው ጋር ዳግመኛ የመገናኘት ተስፋ አይኖርህም ነበር። የሞቱ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት በሚገልጸው ሁኔታ ውስጥ ይቀሩ ነበር:- “ሙታን ግን ምንም አያውቁምና፤ . . . ልትሄድበት ባለው መቃብር ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና።”—መክብብ 9:5, 10

2. ትንሣኤ ምን ግሩም አጋጣሚ ከፍቷል?

2 ደግነቱ ይሖዋ በትንሣኤ አማካኝነት ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሙታን ከሞት ተነስተው ለዘላለም መኖር የሚችሉበትን እጅግ ውድ የሆነ አጋጣሚ ከፍቷል። በመሆኑም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ አንድ ቀን በሞት ከተለዩህ ወዳጅ ዘመዶችህ ጋር ዳግመኛ የመገናኘት አስደሳች ተስፋ ይኖርሃል።—ማርቆስ 5:35, 41, 42፤ የሐዋርያት ሥራ 9:36-41

3. (ሀ) ትንሣኤ የይሖዋ ዓላማ ዳር እንዲደርስ በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው በምን መንገዶች ነው? (ለ) የትንሣኤ ተስፋ ይበልጥ የብርታት ምንጭ የሚሆንልን መቼ ነው?

3 የትንሣኤ ተስፋ ስላለ ሞትን ከልክ በላይ የምንፈራበት ምክንያት የለም። ይሖዋ፣ ሰይጣን በአገልጋዮቹ ላይ ዘላቂ ጉዳት እንዲያደርስ ባይፈቅድለትም “ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል” የሚለው ተንኮል ያዘለ ክርክሩ እውነት መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ እስከ መጨረሻው ድረስ እንዲሞክር ሊፈቅድለት ይችላል። (ኢዮብ 2:4) ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ለአምላክ ታማኝ የነበረ ሲሆን አምላክም ከሞት በማስነሳት ሰማያዊ ሕይወት ሰጥቶታል። በመሆኑም ኢየሱስ ሕይወታችንን ሊያድን የሚችለውን ፍጹም የሆነው ሰብዓዊ መሥዋዕቱ የሚያስገኘውን ዋጋ በአባቱ ዙፋን ፊት ማቅረብ ችሏል። ከክርስቶስ ጋር የሚገዙት ‘የታናሹ መንጋ’ አባላት በሰማያዊው መንግሥት ከእርሱ ጋር አብረው የሚሆኑት በትንሣኤ አማካኝነት ነው። (ሉቃስ 12:32 የ1954 ትርጉም) ሌሎች ደግሞ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ትንሣኤ ያገኛሉ። (መዝሙር 37:11, 29) ሁሉም ክርስቲያኖች ከሞት ጋር እንዲፋጠጡ የሚያደርግ ፈተና ሲያጋጥማቸው የትንሣኤ ተስፋ “ታላቅ ኀይል” ይሰጣቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 4:7

ለክርስቲያናዊ እምነት መሠረት የሆነው ለምንድን ነው?

4. (ሀ) ትንሣኤ “የመጀመሪያ ትምህርት” የሆነው በምን መንገድ ነው? (ለ) በጥቅሉ ሲታይ በዓለም ያሉ ሰዎች ስለ ትንሣኤ ምን አመለካከት አላቸው?

4 በ⁠ዕብራውያን 6:1, 2 ላይ እንደተገለጸው ትንሣኤ “የመጀመሪያ ትምህርት” ነው። የእምነት መሠረት ከሆኑት ትምህርቶች አንዱ ሲሆን አንድ ሰው ያለዚህ ትምህርት የጎለመሰ ክርስቲያን ሊሆን አይችልም። (1 ቆሮንቶስ 15:16-19) ይሁን እንጂ ስለ ትንሣኤ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በዓለም ካለው አስተሳሰብ ጋር አይሄድም። ብዙ ሰዎች መንፈሳዊ አመለካከት ስለሌላቸው ሕይወት ይህ ብቻ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። በመሆኑም ሕይወታቸው ተድላን በማሳደድ ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ነፍስ አትሞትም ብለው የሚያምኑ በሕዝበ ክርስትና ውስጥም ሆነ ከሕዝበ ክርስትና ውጭ ያሉ ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ሰዎች አሉ። ሆኖም ሰዎች የማትሞት ነፍስ ካለቻቸው ትንሣኤ አስፈላጊ ስለማይሆን ይህ እምነት ስለ ትንሣኤ ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር አይጣጣምም። እነዚህን ሁለት ጽንሰ ሐሳቦች ለማስታረቅ መሞከር ይበልጥ ግራ የሚያጋባ እንጂ ተስፋ የሚሰጥ አይሆንም። ትክክለኛውን ነገር ለማወቅ የሚፈልጉ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?

5. (ሀ) አንድ ሰው ስለ ትንሣኤ ከመማሩ በፊት ምን ማወቅ ያስፈልገዋል? (ለ) ስለ ነፍስ ለማስረዳት የትኞቹን ጥቅሶች ትጠቀማለህ? ስለ ሙታን ለማስረዳትስ? (ሐ) አንድ ሰው የሚጠቀምበት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ትክክለኛውን ነገር የሚሰውር ከሆነ ምን ማድረግ ይቻላል?

5 እንዲህ ያሉ ሰዎች አስደናቂ የሆነውን የትንሣኤ ዝግጅት ከመማራቸው በፊት ስለ ነፍስና ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለተጠማ ሰው እነዚህን ጉዳዮች ግልጽ ለማድረግ ብዙውን ጊዜ ጥቂት ጥቅሶችን ብቻ መጥቀስ በቂ ሊሆን ይችላል። (ዘፍጥረት 2:7፤ መዝሙር 146:3, 4፤ ሕዝቅኤል 18:4) ይሁን እንጂ አንዳንድ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችና ቀለል ባለ መንገድ የተዘጋጁ እትሞች ነፍስን በተመለከተ ያለውን እውነታ ሰውረዋል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ውስጥ የሚገኙትን አገላለጾች መመርመሩ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

6. አንድ ሰው ነፍስ ምን እንደሆነች እንዲገነዘብ ልትረዳው የምትችለው እንዴት ነው?

6 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም፣ ነፈሽ የሚለውን የዕብራይስጥ ቃልና ፕስኺ የሚለውን የግሪክኛ ቃል በሁሉም ቦታዎች ላይ “ነፍስ” ብሎ ስለሚተረጉም እንዲህ ያለውን ምርምር ለማድረግ የሚረዳ ጥሩ መሣሪያ ነው። በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ተጨማሪ ክፍል ላይ እነዚህ ቃላት የሚገኙባቸው በርካታ ጥቅሶች ተዘርዝረዋል። ሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እነዚህን ቃላት በትክክል አልተረጎሟቸውም። ቅን የሆነ አንድ ተማሪ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ከአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ጋር በማነጻጸር “ነፍስ” ተብለው የተተረጎሙት በበኩረ ጽሑፉ ላይ የሚገኙት ቃላት ሰዎችንም ሆነ እንስሳትን እንደሚያመለክቱ መገንዘብ ይችላል። ሆኖም እነዚህ ቃላት ነፍስ አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ ከሥጋው ተለይታ በሕይወት የምትቀጥል የማትታይ ረቂቅ ነገር እንደሆነች የሚጠቁም ሐሳብ አያስተላልፉም።

7. መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም በሺኦል፣ በሔዲስና በገሃነም ያሉ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ እንዴት ማስረዳት ትችላለህ?

7 በተጨማሪም የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም፣ ሔዲስ የተባለው የግሪክኛ ቃል አቻ ትርጉም የሆነውን ሺኦል የተባለውን የዕብራይስጥ ቃልም ሆነ ጊዬና የተባለውን የግሪክኛ ቃል የሚተረጉምበት መንገድ ወጥነት ያለው ነው። (መዝሙር 16:10፤ የሐዋርያት ሥራ 2:27) የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም፣ ሺኦል እና ሔዲስ የተባሉት ሁለቱም ቃላት የሰውን ዘር መቃብር እንደሚያመለክቱና ከሞት ጋር እንጂ ከሕይወት ጋር ተያይዘው እንደማይጠቀሱ ግልጽ ያደርግልናል። (መዝሙር 89:48፤ ራእይ 20:13) ከዚህም ሌላ ቅዱሳን ጽሑፎች ሙታን በትንሣኤ አማካኝነት ከዚህ መቃብር የመውጣት ተስፋ እንዳላቸው ይገልጻሉ። (ኢዮብ 14:13፤ የሐዋርያት ሥራ 2:31) በአንጻሩ ግን ገሃነም ውስጥ የገቡ ወደፊት ሕይወት የማግኘት ተስፋ የሌላቸው ከመሆኑም በላይ ነፍስ በገሃነም ውስጥ ሕያው ሆና እንደምትቀጥል የሚጠቁም ምንም የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ የለም።—ማቴዎስ 10:28

8. አንድ ሰው ስለ ትንሣኤ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘቱ በአመለካከቱና በድርጊቱ ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው እንዴት ነው?

8 አንድ ሰው በቅድሚያ እነዚህ ነገሮች በደንብ ግልጽ ከሆኑለት ትንሣኤ ለእሱ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝለት በቀላሉ ማስረዳት ይቻላል። ይሖዋ እንዲህ ያለ አስደናቂ ዝግጅት በማድረግ ያሳየውን ፍቅር ማድነቅ ሊጀምር ይችላል። የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ያጡ ግለሰቦች በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ እንደገና ሊያገኟቸው እንደሚችሉ ሲያስቡ ሐዘናቸው ቀለል ይልላቸዋል። በተጨማሪም አንድ ሰው የክርስቶስ ሞት ያስገኘውን ጥቅም ለመረዳት በቅድሚያ እነዚህን ነገሮች መገንዘቡ ወሳኝ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ሌሎች ትንሣኤ ማግኘት የሚችሉበትን አጋጣሚ የከፈተ በመሆኑ ለክርስቲያናዊ እምነት መሠረት እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። ስለ ኢየሱስ ትንሣኤና ይህ ትንሣኤ ስላስገኘው ተስፋ በቅንዓት ሰብከዋል። ስለሆነም በዛሬው ጊዜ የትንሣኤን ተስፋ በሚገባ የተረዱና የሚያደንቁ ሁሉ ይህን ውድ እውነት ለሌሎች ለማካፈል ከፍተኛ ጉጉት አላቸው።—የሐዋርያት ሥራ 5:30-32፤ 10:42, 43

‘የሲኦልን መክፈቻ’ መጠቀም

9. ኢየሱስ ‘የሞትንና የሲኦልን መክፈቻ’ በቅድሚያ የሚጠቀምበት እንዴት ነው?

9 በሰማያዊው መንግሥት ከክርስቶስ ጋር የመግዛት ተስፋ ያላቸው ሁሉ ውሎ አድሮ የግድ መሞት ይኖርባቸዋል። ሆኖም “ሞቼ ነበር፤ እነሆ አሁን ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦል መክፈቻም በእጄ ነው” በማለት የሰጣቸውን ዋስትና በሚገባ ያውቃሉ። (ራእይ 1:18) ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነው? በእሱ ላይ የደረሰውን ሁኔታ መጥቀሱ ነው። እሱም ሞቶ ነበር። ሆኖም አምላክ በሔዲስ ወይም በሲኦል አልተወውም። በሦስተኛው ቀን ይሖዋ ራሱ ከሞት ያስነሳው ሲሆን የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት ሰጥቶታል። (የሐዋርያት ሥራ 2:32, 33፤ 10:40) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ሌሎችን ከሰው ዘር መቃብርና የአዳም ኃጢአት ካስከተላቸው ውጤቶች ነፃ እንዲያወጣ ‘የሞትንና የሲኦልን መክፈቻ’ ሰጥቶታል። ኢየሱስ ይህ መክፈቻ የተሰጠው በመሆኑ ታማኝ ተከታዮቹን ከሞት ማስነሳት ይችላል። በቅድሚያ የሚያስነሳው በመንፈስ የተቀቡ የጉባኤውን አባላት ሲሆን አባቱ ለእሱ የማይሞት ሕይወት እንደሰጠው ሁሉ እሱም ለቅቡዓን ተከታዮቹ የማይሞት ውድ ሰማያዊ ሕይወት ይሰጣቸዋል።—ሮሜ 6:5፤ ፊልጵስዩስ 3:20, 21

10. የታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ትንሣኤ የሚከናወነው መቼ ነው?

10 ታማኝ የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለሰማያዊ ሕይወት ትንሣኤ የሚያገኙት መቼ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ትንሣኤ እንደጀመረ ይጠቁማል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ከሞት የሚነሱት ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ በሚገኝበት ጊዜ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ የተገኘው ደግሞ ከ1914 ጀምሮ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:23 NW) ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ በተገኘበት በዚህ ዘመን የሚሞቱ ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሞተው መቆየት አያስፈልጋቸውም። እንደሞቱ ወዲያውኑ “ድንገት በቅጽበተ ዐይን” በመለወጥ መንፈሳዊ አካል ይዘው ይነሳሉ። ያከናወኑት መልካም ሥራ “ስለሚከተላቸው” ታላቅ ደስታ ያገኛሉ!—1 ቆሮንቶስ 15:51, 52፤ ራእይ 14:13

11. አብዛኞቹ የሰው ልጆች ምን ዓይነት ትንሣኤ ያገኛሉ? ይህ ትንሣኤ የሚጀምረውስ መቼ ነው?

11 ይሁን እንጂ ትንሣኤ የሚያገኙት ሰማያዊ ሕይወት የሚጎናጸፉት የመንግሥቱ ወራሾች ብቻ አይደሉም። በራእይ 20:6 ላይ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ትንሣኤ ‘የመጀመሪያው ትንሣኤ’ ተብሎ መጠራቱ ሌላ ትንሣኤ መኖር እንዳለበት ያመለክታል። ይህን ቀጣይ ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አስደሳች ተስፋ አላቸው። ይህ ትንሣኤ የሚከናወነው መቼ ነው? የራእይ መጽሐፍ ይህ የሚሆነው “ምድርና ሰማይ” ማለትም በአሁኑ ጊዜ ያለው ክፉ ሥርዓት ከነገዥዎቹ ተጠራርጎ ከጠፋ በኋላ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ አሮጌ ሥርዓት የሚጠፋበት ጊዜ በጣም ቀርቧል። ከዚያ በኋላ አምላክ በወሰነው ጊዜ ምድራዊው ትንሣኤ ይጀምራል።—ራእይ 20:11, 12

12. በምድር ላይ ለመኖር ትንሣኤ ከሚያገኙት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች መካከል እነማን ይገኙበታል? ይህስ አስደሳች ተስፋ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ይህን ምድራዊ ትንሣኤ ከሚያገኙት መካከል እነማን ይገኙበታል? በጥንት ዘመን የነበሩ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ይኸውም በትንሣኤ ላይ በነበራቸው ጠንካራ እምነት የተነሳ ‘ነፃ ለመውጣት ያልፈለጉ’ ወንዶችና ሴቶች ይገኙበታል። እነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉ ለአምላክ ታማኝ በመሆን የያዙትን የጸና አቋም ለማላላት ፈቃደኞች አልሆኑም። እነዚህን ሰዎች በአካል ማግኘትና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአጭሩ የተገለጸውን ታሪካቸውን ከራሳቸው አንደበት በዝርዝር መስማት መቻል ምንኛ የሚያስደስት ነው! ከዚህም በተጨማሪ ከሞት ተነስተው በምድር ላይ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል የመጀመሪያው የይሖዋ ታማኝ ምሥክር የሆነው አቤል፣ ከጥፋት ውኃ በፊት የአምላክን የማስጠንቀቂያ መልእክት በድፍረት ያወጁት ሄኖክና ኖኅ፣ መላእክትን ያስተናገዱት አብርሃምና ሣራ፣ በሲና ተራራ ሕጉን የተቀበለው ሙሴ እንዲሁም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢየሩሳሌም ስትጠፋ የተመለከተውን ኤርምያስን የመሳሰሉ ደፋር ነቢያትና ኢየሱስ ልጁ መሆኑን አምላክ ራሱ ሲናገር የሰማው አጥማቂው ዮሐንስ ይገኙበታል። በተጨማሪም በዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የሞቱ በርካታ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ትንሣኤ ያገኛሉ።—ዕብራውያን 11:4-38፤ ማቴዎስ 11:11

13, 14. (ሀ) ሔዲስም ሆነ በውስጡ ያሉት ሙታን ወደፊት ምን ይሆናሉ? (ለ) ትንሣኤ ከሚያገኙት መካከል እነማን ይገኙበታል? ለምንስ?

13 በጊዜ ሂደት ከአምላክ ታማኝ አገልጋዮች በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችም ከሞት ስለሚነሱ የሰው ዘር መቃብር ባዶ ይሆናል። ኢየሱስ ሙታንን ለማስነሳት ‘የሲኦልን መክፈቻ’ የሚጠቀምበት መንገድ ይህ መቃብር ምን ያህል ባዶ እንደሚሆን ያሳያል። ሲኦል ወይም ሔዲስ ‘ወደ እሳት ባሕር እንደተጣለ’ የሚገልጸው ሐዋርያው ዮሐንስ ያየው ራእይ ይህን ሁኔታ የሚያመለክት ነው። (ራእይ 20:14) ሔዲስ ወደ እሳት ባሕር መጣሉ ምን ትርጉም አለው? የሰው ዘር መቃብር የሆነው ሔዲስ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠፋ ያሳያል። ኢየሱስ የይሖዋን ታማኝ አምላኪዎች ብቻ ሳይሆን ኃጥአንንም ከሞት በማስነሳት ሔዲስን ሙሉ በሙሉ ባዶ የሚያደርገው በመሆኑ ከዚያ በኋላ ሔዲስ የሚባል ነገር አይኖርም። የአምላክ ቃል “ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን [ይነሣሉ]” በማለት ዋስትና ይሰጠናል።—የሐዋርያት ሥራ 24:15

14 እነዚህ ኃጥአን የሚነሱት እንዲሁ ዳግመኛ ሞት እንዲፈረድባቸው አይደለም። በአምላክ መንግሥት በሚተዳደረው ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ሕይወታቸውን ከአምላክ መመሪያዎች ጋር ማስማማት እንዲችሉ አስፈላጊው እርዳታ ይደረግላቸዋል። ዮሐንስ ያየው ራእይ “የሕይወት መጽሐፍ” እንደሚከፈት ይገልጻል። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች በዚህ መጽሐፍ ላይ የመጻፍ አጋጣሚ ያገኛሉ። እያንዳንዳቸው ከሞት ከተነሡ በኋላ በሚያከናውኑት ‘ሥራ መሠረት ይፈረድባቸዋል።’ (ራእይ 20:12, 13) ስለዚህ መጨረሻ ላይ ከሚኖረው ውጤት አንጻር ሲታይ ትንሣኤያቸው የግድ ‘የፍርድ ትንሣኤ’ ብቻ ሳይሆን ‘የሕይወት ትንሣኤም’ ሊሆን ይችላል።—ዮሐንስ 5:28, 29

15. (ሀ) ትንሣኤ የማያገኙት እነማን ናቸው? (ለ) ስለ ትንሣኤ ትክክለኛውን ነገር ማወቃችን አኗኗራችንን እንዴት ሊነካው ይገባል?

15 ይሁን እንጂ የሞቱ ሁሉ ትንሣኤ ያገኛሉ ማለት አይደለም። አንዳንዶች ይቅር ሊባል የማይችል ኃጢአት ሠርተዋል። እነዚህ ሰዎች ያሉት በሔዲስ ሳይሆን በገሃነም ውስጥ ነው፤ ይህ ደግሞ ዘላለማዊ ጥፋት እንደደረሰባቸው ያመለክታል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል በቅርቡ በሚመጣው “ታላቅ መከራ” ወቅት የሚጠፉት ሰዎችም ይገኙበታል። (ማቴዎስ 12:31, 32፤ 23:33፤ 24:21, 22፤ 25:41, 46፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-9) እንግዲያው ይሖዋ በሔዲስ ያሉት ሙታን ሁሉ እንዲነሱ ልዩ ምሕረት የሚያደርግ ቢሆንም የትንሣኤ ተስፋ በአሁኑ ጊዜ እንደፈለግነው ለመኖር ምክንያት ሊሆነን አይችልም። ሆን ብለው በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የሚያምጹ ሁሉ ትንሣኤ አያገኙም። ይህን ማወቃችን ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር ይገባናል ለማንለው የይሖዋ ደግነት የጠለቀ አድናቆት እንድናሳይ ሊገፋፋን ይገባል።

የትንሣኤ ተስፋ የሚሰጠው ብርታት

16. የትንሣኤ ተስፋ ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ሊሆንልን የሚችለው እንዴት ነው?

16 በትንሣኤ ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት ካለን ይህ ተስፋ ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ይሆንልናል። በአሁኑ ጊዜ እያረጀን ስንሄድ ምንም ዓይነት ሕክምና ብናደርግ ለዘለቄታው ሞትን ማስቀረት አንችልም። (መክብብ 8:8) ከድርጅቱ ጋር ተባብረን ይሖዋን በታማኝነት የምናገለግል ከሆነ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ እንችላለን። ብንሞት እንኳ አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በትንሣኤ አማካኝነት ዳግመኛ ሕይወትን እንደምናጣጥም እናውቃለን። በዚያን ጊዜ የምናገኘው ሕይወት እጅግ አስደሳች ይሆናል! ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሕይወት ‘እውነተኛ የሆነ ሕይወት’ ሲል ጠርቶታል።—1 ጢሞቴዎስ 6:19፤ ዕብራውያን 6:10-12

17. ለይሖዋ ታማኞች ሆነን እንድንጸና ምን ሊረዳን ይችላል?

17 ትንሣኤ እንዳለና የዚህ ዝግጅት ምንጭ ማን እንደሆነ ማወቃችን ጠንካራ እምነት እንዲኖረን ያደርገናል። ጨካኝ የሆኑ አሳዳጆች እንደሚገድሉን ቢዝቱብን እንኳ ለአምላክ ታማኞች ሆነን እንድንጸና ይረዳናል። ሰይጣን ከረጅም ዘመናት አንስቶ ሞትን እንደ ማስፈራሪያ አድርጎ በመጠቀም በርካታ ሰዎችን በባርነት ቀንበር ይዟቸዋል። ኢየሱስ ግን ለእንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት አልተንበረከከም። እስከ ሞት ድረስ ለይሖዋ ታማኝ ከመሆኑም ሌላ በቤዛዊ መሥዋዕቱ አማካኝነት ሌሎች ሰዎችም ከእንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት መላቀቅ የሚችሉበትን መንገድ ከፍቷል።—ዕብራውያን 2:14, 15

18. የይሖዋ አገልጋዮች በአቋም ጽናት ረገድ አስደናቂ ታሪክ እንዲያስመዘግቡ የረዳቸው ምንድን ነው?

18 የይሖዋ አገልጋዮች በክርስቶስ መሥዋዕትና በትንሣኤ ላይ ባላቸው እምነት የተነሳ በአቋም ጽናት ረገድ አስደናቂ ታሪክ አስመዝግበዋል። ከፍተኛ ተጽዕኖ በሚደረግባቸው ጊዜ ለይሖዋ ካላቸው ፍቅር የተነሳ “እስከ ሞት ድረስ እንኳ፣ ለነፍሳቸው አልሳሱም።” (ራእይ 12:11) ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን አይጥሱም። (ሉቃስ 9:24, 25) የይሖዋን ሉዓላዊነት በታማኝነት በመደገፋቸው ምክንያት ሕይወታቸውን ቢያጡ እንኳ በትንሣኤ አማካኝነት ዳግመኛ ሕይወት እንደሚሰጣቸው ያውቃሉ። ታዲያ አንተ እንዲህ ያለ እምነት አለህ? ይሖዋን ከልብ የምትወድና የትንሣኤን ተስፋ ከፍ አድርገህ የምትመለከት ከሆነ እንዲህ ያለ እምነት ይኖርሃል።

የክለሳ ውይይት

• አንድ ሰው የትንሣኤን ተስፋ መረዳትና ማድነቅ እንዲችል በቅድሚያ ስለ ነፍስና ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

• ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው? ይህን ማወቃችንስ በአኗኗራችን ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይገባል?

• የትንሣኤ ተስፋ የብርታት ምንጭ የሚሆንልን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 84 እና 85 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ጻድቃንም ሆኑ ኃጥአን ከሞት እንደሚነሱ ቃል ገብቷል