በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምልኮ አንድነት በዘመናችን ምን ትርጉም አለው?

የአምልኮ አንድነት በዘመናችን ምን ትርጉም አለው?

ምዕራፍ አንድ

የአምልኮ አንድነት በዘመናችን ምን ትርጉም አለው?

1, 2. (ሀ) በዘመናችን ምን ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው? (ለ) ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ምን አስደናቂ ተስፋ ይጠብቃቸዋል?

በምድር ዙሪያ ሰዎችን በአንድ የአምልኮ ጣሪያ ሥር ለማሰባሰብ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ይህ እንቅስቃሴ ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶችና ቋንቋዎች የተውጣጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አንድ እያደረገ ነው። በየዓመቱ በርካታ ሰዎች ወደዚህ የአምልኮ አንድነት ይቀላቀላሉ። እነዚህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የይሖዋ ‘ምስክሮች’ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ተብለው ተጠርተዋል። አምላክን ‘ቀንና ሌሊት ያገለግላሉ።’ (ኢሳይያስ 43:10-12፤ ራእይ 7:9-15) ይህን የሚያደርጉት ለምንድን ነው? እውነተኛው አንድ አምላክ ይሖዋ መሆኑን ስላወቁ ነው። ይህም ከጽድቅ መሥፈርቶቹ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲኖሩ ያነሳሳቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ይህን ክፉ ዓለም አጥፍቶ አስደሳች በሆነ አዲስ ዓለም የሚተካበት ጊዜ በተቃረበበት ‘የመጨረሻ ዘመን’ ውስጥ እንደምንኖር ተገንዝበዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13፤ 2 ጴጥሮስ 3:10-13

2 የአምላክ ቃል የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣል:- “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።” (መዝሙር 37:10, 11) “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:29) “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”—ራእይ 21:4

3. እውነተኛ የአምልኮ አንድነት እውን እየሆነ ያለው እንዴት ነው?

3 በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ነዋሪዎች የሚሆኑት በአሁኑ ጊዜ በእውነተኛ አምልኮ አንድ የሆኑ ሰዎች ናቸው። የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ የተማሩ ሲሆን የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም የተቻላቸውን ያህል ጥረት ያደርጋሉ። ኢየሱስ ይህ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሲያመለክት “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል” ሲል ጽፏል።—1 ዮሐንስ 2:17

የአምልኮ አንድነት ምን ትርጉም አለው?

4. (ሀ) በዘመናችን ብዙ ሰዎች በአንድ አምልኮ ጣሪያ ሥር እየተሰባሰቡ መሆናቸው ምን ትርጉም አለው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ወደ እውነተኛው አምልኮ እንደሚሰባሰቡ የሚገልጸው እንዴት ነው?

4 በዘመናችን ብዙ ሰዎች በአንድ አምልኮ ጣሪያ ሥር እየተሰባሰቡ መሆናቸው ምን ትርጉም አለው? ይህ ክፉ ዓለም ጠፍቶ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም የሚተካበት ጊዜ በጣም እንደቀረበ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው። ሰዎች ወደ እውነተኛው አምልኮ እንደሚሰባሰቡ የሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እየተፈጸሙ እንዳሉ እኛ ራሳችን የዓይን ምሥክሮች ነን። ከእነዚህ ትንቢቶች አንዱ እንዲህ ይላል:- “በመጨረሻው ዘመን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ [ከፍ ያለው የአምላክ እውነተኛ አምልኮ]፣ ከተራሮች [ከማንኛውም ዓይነት ሌላ አምልኮ] ልቆ ይታያል፤ . . . ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ ‘ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንሂድ፤ በመንገዱም እንድንሄድ፣ መንገዱን ያስተምረናል።’”—ሚክያስ 4:1, 2፤ መዝሙር 37:34

5, 6. (ሀ) ብሔራት ወደ ይሖዋ ቤት እየመጡ ያሉት እንዴት ነው? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

5 ብሔራት እንዳሉ በጅምላ መንፈሳዊ ወደሆነው የይሖዋ የአምልኮ ቤት ባይጎርፉም ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን በማድረግ ላይ ናቸው። የይሖዋ አምላክን ፍቅራዊ ዓላማና ማራኪ የሆኑ ባሕርያቱን ሲማሩ ልባቸው በእጅጉ ይነካል። አምላክ ምን እንደሚጠብቅባቸው ለማወቅ በትሕትና ጥረት ያደርጋሉ። ልክ እንደ መዝሙራዊው “አንተ አምላኬ ነህና፣ ፈቃድህን እንድፈጽም አስተምረኝ” ብለው ይጸልያሉ።—መዝሙር 143:10

6 በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ በአንድ አምልኮ ጣሪያ ሥር እያሰባሰባቸው ካሉት ሰዎች መካከል እንደሆንክ ይሰማሃል? ከአምላክ ቃል ላገኘኸው ትምህርት የምትሰጠው ምላሽ የቃሉ ምንጭ ይሖዋ መሆኑን እንደተገነዘብክ ያሳያል? ‘በመንገዱ ለመሄድ’ ምን ያህል ቆርጠሃል?

የአምልኮ አንድነት የሚገኘው እንዴት ነው?

7. (ሀ) ወደፊት የአምልኮ አንድነት ምን ደረጃ ላይ ይደርሳል? (ለ) በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን ማምለክ አጣዳፊ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው? ሌሎች ይሖዋን እንዲያመልኩ ልንረዳቸው የምንችለውስ እንዴት ነው?

7 የይሖዋ ዓላማ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ በእውነተኛ አምልኮ አንድ እንዲሆኑ ነው። ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ እውነተኛውን አምላክ ብቻ የሚያመልኩበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠባበቃለን! (መዝሙር 103:19-22) ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ይሖዋ ፈቃዱን ለማድረግ አሻፈረኝ የሚሉትን ሁሉ ማጥፋት ይኖርበታል። ይሖዋ በምሕረቱ ተገፋፍቶ በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች አኗኗራቸውን ማስተካከል የሚችሉበት አጋጣሚ እንዲያገኙ ሲል የሚወስደውን እርምጃ በተመለከተ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 55:6, 7) በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ “ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ” የሚከተለው አጣዳፊ ጥሪ እየቀረበ ነው:- “እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል፤ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው ስገዱ።” (ራእይ 14:6, 7) አንተስ ይህን ጥሪ ተቀብለሃል? ከሆነ ሌሎች ሰዎች እውነተኛውን አምላክ እንዲያውቁና እንዲያመልኩ የመጋበዝ መብት አለህ።

8. የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች ከቀሰምን በኋላ ምን ተጨማሪ እድገት ለማድረግ ከልብ መጣር ይኖርብናል?

8 ይሖዋ በእሱ እናምናለን እያሉ የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ ሰዎች እንዲያመልኩት አይፈልግም። አምላክ፣ ሰዎች ትክክለኛውን “የፈቃዱን ዕውቀት” እንዲያገኙና ይህንንም በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ እንዲያደርጉት ይፈልጋል። (ቈላስይስ 1:9, 10) በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች የቀሰሙ አድናቂ ሰዎች ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ለመድረስ ጥረት ያደርጋሉ። ይሖዋን ይበልጥ ማወቅ፣ ስለ ቃሉ ያላቸውን ግንዛቤ ማስፋትና ማሳደግ እንዲሁም ያወቁትን በሕይወታቸው ውስጥ ይበልጥ ተግባራዊ ማድረግ ይፈልጋሉ። በሰማይ ያለውን አባታችንን ባሕርያት ለማንጸባረቅና የእሱን አመለካከት ለመኮረጅ ይጥራሉ። ይህም በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ በምድር ላይ እያሠራ ባለው ሕይወት አድን ሥራ ለመካፈል የሚያስችሉ መንገዶችን እንዲፈልጉ ይገፋፋቸዋል። የአንተስ ፍላጎት ይህ ነው?—ማርቆስ 13:10፤ ዕብራውያን 5:12 እስከ 6:3

9. በአሁኑ ጊዜ እውነተኛ አንድነት ሊገኝ የሚችለው በምን መንገዶች ነው?

9 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎች አንድነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ይገልጻል። (ኤፌሶን 4:1-3) ምንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ የምንኖርና ካለብን አለፍጽምና ጋር የምንታገል ቢሆንም ይህ አንድነት ሊኖረን ይገባል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ እውነተኛ አንድነት እንዲኖራቸው አጥብቆ ጸልዮአል። ይህ ምን ማለት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ከይሖዋና ከልጁ ጋር ጥሩ ዝምድና ይኖራቸዋል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እርስ በርስ አንድነት አላቸው። (ዮሐንስ 17:20, 21) ይህ አንድነት ይኖር ዘንድ ይሖዋ ሕዝቦቹን ለማስተማር የክርስቲያን ጉባኤን መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምበታል።

ለአንድነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ነገሮች ምንድን ናቸው?

10. (ሀ) እኛን በቀጥታ ለሚመለከቱ ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም በግለሰብ ደረጃ መልስ ለማግኘት በምንሞክርበት ጊዜ የትኞቹን ባሕርያት እናዳብራለን? (ለ) በዚህ አንቀጽ ውስጥ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ለክርስቲያናዊ አንድነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን ነጥቦች በጥሞና መርምር።

10 ለአምልኮ አንድነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሰባት ቁልፍ ነጥቦች ከዚህ ቀጥሎ ተዘርዝረዋል። ተያይዘው ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ በምትሰጥበት ጊዜ እያንዳንዱ ነጥብ ከይሖዋና ከክርስቲያን ባልንጀሮችህ ጋር ያለህን ዝምድና እንዴት እንደሚነካው ለማሰብ ሞክር። በእነዚህ ነጥቦች ላይ ማሰላሰልህና ምዕራፋቸውና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ጥቅሶች አውጥተህ ማንበብህ ሁላችንም የሚያስፈልጉንን ባሕርያት ማለትም አምላካዊ ጥበብን፣ የማሰብ ችሎታንና ማስተዋልን እንድታዳብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክትልሃል። (ምሳሌ 5:1, 2፤ ፊልጵስዩስ 1:9-11) እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ መርምር።

(1) ይሖዋ መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር ለመወሰን የሚያስችል መሥፈርት የማውጣት መብት እንዳለው አምነን እንቀበላለን። “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።”—ምሳሌ 3:5, 6

ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ የይሖዋን ምክርና መመሪያ ለማግኘት መጣር ያለብን ለምንድን ነው? (መዝሙር 146:3-5፤ ኢሳይያስ 48:17)

(2) የአምላክ ቃል መመሪያ ሆኖ ያገለግለናል። “ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ፣ በእናንተ በምታምኑት ዘንድ በእርግጥ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ [አልተቀበላችሁትም]።”—1 ተሰሎንቄ 2:13

እንዲሁ ትክክል መስሎ “የተሰማንን” ማድረጋችን ምን አደጋ አለው? (ምሳሌ 14:12፤ ኤርምያስ 10:23, 24፤ 17:9)

መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ጉዳይ በተመለከተ ምን ምክር እንደሚሰጥ ካላወቅን ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ምሳሌ 2:3-5፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17)

(3) ሁላችንም ከአንድ መንፈሳዊ ገበታ እንመገባለን። “ወንዶች ልጆችሽ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ።” (ኢሳይያስ 54:13) “እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።”—ዕብራውያን 10:24, 25

ይሖዋ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ለመመገብ ባደረገው ዝግጅት ሙሉ በሙሉ የሚጠቀሙ ሁሉ ምን በረከት ያገኛሉ? (ኢሳይያስ 65:13, 14)

(4) መሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ ሌላ ማንም ሰው አይደለም። “‘መምህር’ ተብላችሁ አትጠሩ፤ አስተማሪያችሁ አንድ ብቻ ሲሆን፣ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁና። በሰማይ ያለ አንድ አባት ስላላችሁ፣ በምድር ማንንም ‘አባት’ ብላችሁ አትጥሩ። መምህራችሁ አንዱ ክርስቶስ ስለሆነ፣ ‘መምህር’ ተብላችሁ አትጠሩ።”—ማቴዎስ 23:8-10

ማንኛችንም ብንሆን ከሌሎች እንደምንልቅ ሆኖ ሊሰማን ይገባል? (ሮሜ 3:23, 24፤ 12:3)

(5) የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ እናምናለን። “እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን።’ ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ።”—ማቴዎስ 6:9, 10, 33

‘መንግሥቱን ማስቀደማችን’ አንድነታችንን እንድንጠብቅ የሚረዳን እንዴት ነው? (ሚክያስ 4:3፤ 1 ዮሐንስ 3:10-12)

(6) መንፈስ ቅዱስ የይሖዋ አምላኪዎች ለክርስቲያናዊ አንድነት አስፈላጊ የሆኑ ባሕርያትን እንዲያፈሩ ይረዳቸዋል። “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው።”—ገላትያ 5:22, 23

የአምላክ መንፈስ በእኛ ላይ ፍሬ እንዲያፈራ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (የሐዋርያት ሥራ 5:32)

የአምላክን መንፈስ ማግኘታችን ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ምን በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል? (ዮሐንስ 13:35፤ 1 ዮሐንስ 4:8, 20, 21)

(7) እውነተኛ የአምላክ አምላኪዎች በሙሉ የመንግሥቱን ምሥራች ይሰብካሉ። “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:14

በዚህ የስብከት ሥራ ሙሉ ተሳትፎ እንድናደርግ ሊገፋፋን የሚገባው ነገር ምንድን ነው? (ማቴዎስ 22:37-39፤ ሮሜ 10:10)

11. የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረጋችን ምን ውጤት ያስገኛል?

11 አንድ ሆነን ይሖዋን ማምለካችን ይበልጥ ወደ እሱ እንድንቀርብ የሚያስችለን ከመሆኑም በላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንዲኖረን ይረዳናል። መዝሙር 133:1 “ወንድሞች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ፣ እንዴት መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” ይላል። በራስ ወዳድነት፣ በጾታ ብልግናና በዓመጽ ከሚታወቀው ዓለም ወጥቶ ይሖዋን ከልባቸው ከሚወዱና ሕጉን ከሚጠብቁ ሰዎች ጋር መሰብሰብ እንዴት ደስ ያሰኛል!

ከሚከፋፍሉ ነገሮች ራቅ

12. በራስ የመመራት መንፈስ እንዳያድርብን መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው?

12 ውድ የሆነው ዓለም አቀፋዊ አንድነታችን እንዳይናጋ ከሚከፋፍሉ ነገሮች መራቅ ይኖርብናል። ከእነዚህ መካከል አንዱ አምላክንም ሆነ ሕጎቹን ቸል በማለት በራስ የመመራት መንፈስ ነው። ይሖዋ የዚህ መንፈስ ምንጭ ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ በመግለጽ ከዚህ ዓይነቱ መንፈስ እንድንርቅ ያበረታታናል። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ራእይ 12:9) አዳምና ሔዋን አምላክ የነገራቸውን ቃል ቸል እንዲሉና የአምላክን ፈቃድ የሚጻረር ውሳኔ እንዲያደርጉ የገፋፋቸው ሰይጣን ነው። ይህም በእነሱም ሆነ በእኛ ላይ ትልቅ ኪሳራ አስከትሏል። (ዘፍጥረት 3:1-6, 17-19) ይህ ዓለም በአምላክም ሆነ በሕጎቹ ከመመራት ይልቅ በራስ የመመራት መንፈስ ተጠናውቶታል። በመሆኑም ይህ መንፈስ እንዳይጠናወተን መጠንቀቅ ያስፈልገናል።

13. አምላክ በሚያመጣው ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ከወዲሁ እየተዘጋጀን መሆን አለመሆናችንን የሚያሳየው ምንድን ነው?

13 ለምሳሌ ያህል ይሖዋ አሁን ያለውን ክፉ ዓለም ‘ጽድቅ በሚኖርበት’ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደሚተካ በመግለጽ የሰጠውን አስደሳች ተስፋ አስብ። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይህ ተስፋ ጽድቅ በሚሰፍንበት በዚያ ዘመን ለመኖር ራሳችንን ከወዲሁ እንድናዘጋጅ ሊገፋፋን አይገባም? ይህም “ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ፣ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም” የሚለውን ግልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቃል። (1 ዮሐንስ 2:15) በመሆኑም በዚህ ዓለም ላይ ገኖ ከሚታየው መንፈስ ማለትም በራስ ከመመራት ዝንባሌ፣ ከራስ ወዳድነት፣ ከጾታ ብልግናና ከዓመጽ እንርቃለን። ምንም እንኳ ፍጽምና የጎደለው ሥጋችን ተቃራኒ የሆነ ነገር እንድናደርግ ሊገፋፋን ቢችልም ምንጊዜም ይሖዋን ለመስማትና ከልብ ለመታዘዝ እንጥራለን። አስተሳሰባችንም ሆነ ውስጣዊ ዝንባሌያችን የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ያተኮረ መሆኑን መላው አኗኗራችን በግልጽ ያሳያል።—መዝሙር 40:8

14. (ሀ) የይሖዋን መንገዶች ለመማርና በሕይወታችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለንን አሁን ያለንን አጋጣሚ መጠቀማችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በአንቀጹ ውስጥ የተጠቀሱት ጥቅሶች በግለሰብ ደረጃ ለእኛ ምን መልእክት ያስተላልፋሉ?

14 ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓትም ሆነ የዚህን ሥርዓት የአኗኗር መንገድ የመረጡትን ሁሉ ለማጥፋት የቆረጠው ቀን አይዘገይም። አምላክ ፈቃዱን በሙሉ ልባቸው ለመማርም ሆነ ተግባራዊ ለማድረግ ያልቆረጡትንና ይህን ዓለም ገና የሙጥኝ ብለው የያዙትን ሰዎች ለማስተናገድ ሲል የወሰነውን ቀን አያራዝምም ወይም መሥፈርቶቹን አይለውጥም። እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን ነው! (ሉቃስ 13:23, 24፤ 17:32፤ 21:34-36) እጅግ ብዙ ሕዝብ ይሖዋ በቃሉም ሆነ በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠውን ትምህርት ከልብ በመቀበልና ወደ አዲሱ ዓለም በሚወስደው ጎዳና ላይ በአንድነት በመጓዝ ይህን ውድ አጋጣሚ ሲጠቀሙበት ማየት ምንኛ የሚያስደስት ነው! ስለ ይሖዋ ይበልጥ በተማርን መጠን ለእሱ ያለን ፍቅርና እሱን ለማገልገል ያለን ፍላጎት የዚያኑ ያህል ይጨምራል።

የክለሳ ውይይት

• ከአምልኮ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ዓላማ ምንድን ነው?

• መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ከተማርን በኋላ ምን ተጨማሪ እድገት ለማድረግ ከልብ መጣር ይኖርብናል?

• ከሌሎች የይሖዋ አምላኪዎች ጋር አንድነት እንዲኖረን በግለሰብ ደረጃ ምን ማድረግ እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ገሮች ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ’