በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋን ቀን በሐሳብህ ቅርብ አድርገህ ተመልከተው

የይሖዋን ቀን በሐሳብህ ቅርብ አድርገህ ተመልከተው

ምዕራፍ ሃያ

የይሖዋን ቀን በሐሳብህ ቅርብ አድርገህ ተመልከተው

1. ይህ አሮጌ ሥርዓት ካመጣው ሥቃይና መከራ የምትገላገልበት ጊዜ እንደቀረበ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትሰማ ምን ተሰምቶህ ነበር?

ከመጽሐፍ ቅዱስ በቅድሚያ ከተማርካቸው ነገሮች አንዱ ይሖዋ መላዋን ምድር ገነት የማድረግ ዓላማ እንዳለው የሚገልጸው ትምህርት ነው። በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ ጦርነት፣ ወንጀል፣ ድህነት፣ በሽታ፣ ሥቃይና ሞት አይኖሩም። ሙታን እንኳ ሳይቀሩ ዳግመኛ ሕይወት ያገኛሉ። ይህ እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ነው! ክርስቶስ በ1914 በማይታይ ሁኔታ ንጉሥ ሆኖ መግዛት እንደጀመረና ከዚያን ጊዜ አንስቶ የምንኖረው በዚህ ክፉ ዓለም የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ እንደሆነ የሚያሳየው ማስረጃ ይህ ተስፋ የሚፈጸምበት ጊዜ እንደቀረበ በግልጽ ይጠቁማል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ማብቂያ ላይ ይሖዋ ይህን ሥርዓት አጥፍቶ በምትኩ አስቀድሞ የተነገረለትን አዲስ ዓለም ያመጣል!

2. “የእግዚአብሔር ቀን” ምንድን ነው?

2 መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ የሚመጣውን የጥፋት ጊዜ “የጌታ ቀን” ሲል ይጠራዋል። (2 ጴጥሮስ 3:10) በመላው የሰይጣን ዓለም ላይ የሚመጣ ‘የእግዚአብሔር የቊጣ ቀን’ ነው። (ሶፎንያስ 2:3) ይህ የቁጣ ቀን ‘የዓለም ሁሉ ነገሥታት’ በሚጠፉበት ‘በዕብራይስጥ አርማጌዶን ተብሎ በሚጠራው ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ ይደመደማል። (ራእይ 16:14, 16) አኗኗርህ ይህ “የእግዚአብሔር ቀን” ቅርብ መሆኑን በእርግጥ እንደምታምን ያሳያል?—ሶፎንያስ 1:14-18፤ ኤርምያስ 25:33

3. (ሀ) የይሖዋ ቀን የሚመጣው መቼ ነው? (ለ) ይሖዋ ‘ቀኑን ወይም ሰዓቱን’ አለመናገሩ ጠቃሚ ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው?

3 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ በሰይጣን ሥርዓት ላይ የበየነውን ፍርድ ለማስፈጸም ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣበትን ትክክለኛ ቀን ለይቶ አይነግረንም። ኢየሱስ “ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያችም ሰዓት ከአብ በቀር፣ የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን፣ ማንም አያውቅም” ሲል ተናግሯል። (ማርቆስ 13:32) ይሖዋን ከልብ የማይወዱ ሰዎች ቀኑን በሐሳባቸው አርቀው ሊመለከቱትና ቁሳዊ ነገሮችን ወደማሳደድ ሊያዘነብሉ ይችላሉ። ሆኖም ይሖዋን ከልባቸው የሚወዱ ሰዎች የዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ መቼም ይምጣ መቼ ይሖዋን በሙሉ ነፍሳቸው ያገለግሉታል።—መዝሙር 37:4፤ 1 ዮሐንስ 5:3

4. ኢየሱስ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል?

4 ኢየሱስ ይሖዋን ለሚወዱ ሰዎች “ጊዜው መቼ እንደሚሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፣ ጸልዩም” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ማርቆስ 13:33-37) የጊዜውን አጣዳፊነት እስክንዘነጋ ድረስ በመብላትና በመጠጣት ወይም ‘በኑሮ ጭንቀት’ እንዳንዋጥ አጥብቆ አሳስቦናል።—ሉቃስ 21:34-36፤ ማቴዎስ 24:37-42

5. ጴጥሮስ እንደገለጸው የይሖዋ ቀን ምን ያመጣል?

5 ጴጥሮስም በተመሳሳይ ‘ሰማያት በእሳት ተቃጥለው የሚጠፉበትንና የሰማይም ፍጥረት [“ሰማያትና ምድር የተሠሩባቸው ንጥረ ነገሮች፣” NW] በታላቅ ትኩሳት የሚቀልጡበትን የይሖዋን ቀን መምጣት’ በሐሳባችን አቅርበን እንድንመለከተው ምክር ሰጥቶናል። “ሰማያት” ማለትም ሰብዓዊ መንግሥታት በሙሉ እንዲሁም “ምድር” ማለትም መላው ክፉ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ይጠፋሉ። ከዚህም በተጨማሪ ‘ምድር የተሠራችባቸው ንጥረ ነገሮች’ ይኸውም በአምላክ ከመመራት ይልቅ በራስ የመመራት ዝንባሌን እንዲሁም ሥነ ምግባር የጎደለውንና ፍቅረ ንዋይ የሚንጸባረቅበትን አኗኗር ጨምሮ የዚህ ክፉ ዓለም አስተሳሰቦችና ድርጊቶች በሙሉ ይወገዳሉ። እነዚህ ነገሮች ‘ጽድቅ በሚኖርበት አዲስ ሰማይ [የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት] እና አዲስ ምድር [አዲስ ምድራዊ ኅብረተሰብ]’ ይተካሉ። (2 ጴጥሮስ 3:10-13) እነዚህ ዓለምን የሚያናጉ ክስተቶች ባልተጠበቀ ቀንና ሰዓት ድንገት ዱብ ይላሉ።—ማቴዎስ 24:44

ምልክቶቹን በንቃት ተከታተል

6. (ሀ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ላቀረቡለት ጥያቄ የሰጠው መልስ በአይሁድ ሥርዓት ማብቂያ ላይ ፍጻሜውን ያገኘው እስከ ምን ድረስ ነው? (ለ) ኢየሱስ ከሰጠው መልስ ውስጥ ከ1914 ወዲህ ባሉት ሁኔታዎችና የሰዎች አመለካከት ላይ የሚያተኩረው ክፍል የትኛው ነው?

6 ከምንኖርበት ዘመን አንጻር የመጨረሻዎቹን ቀኖች ማለትም ‘የሥርዓቱን መደምደሚያ’ ለይቶ የሚያሳውቀውን ብዙ ገጽታ ያለውን ምልክት አንድ በአንድ ጠንቅቀን መረዳታችን አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ በ⁠ማቴዎስ 24:3 [NW] ላይ ተመዝግቦ ለሚገኘው ደቀ መዛሙርቱ ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ በሰጠበት ወቅት ከ4 እስከ 22 ባሉት ቁጥሮች ላይ ከዘረዘራቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ከ33 እስከ 70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በነበረው ጊዜ በአይሁድ ሥርዓት ላይ በተወሰነ ደረጃ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ አስታውስ። ይሁንና ትንቢቱ ዋነኛ ፍጻሜውን ያገኘው ከ1914 አንስቶ ባለው፣ ክርስቶስ ‘በሥልጣኑ ላይ በተገኘበትና የሥርዓቱ መደምደሚያ’ በሆነው ዘመን ውስጥ ነው። ማቴዎስ 24:23-28 ከ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አንስቶ ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ እስከሚገኝበት ጊዜ ድረስ ባለው ዘመን ውስጥ ምን ሁኔታ እንደሚከሰት ይናገራል። ከ⁠ማቴዎስ 24:29 እስከ 25:46 ድረስ የተገለጹት ክንውኖች በመጨረሻው ዘመን የሚፈጸሙ ናቸው።

7. (ሀ) እያንዳንዳችን በአሁኑ ጊዜ ያሉት ሁኔታዎች ምልክቱ ፍጻሜውን እንዲያገኝ እያደረጉ ያሉት እንዴት እንደሆነ በንቃት መከታተላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ምልክቱ ከ1914 አንስቶ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት እንደሆነ በመግለጽ ከዚህ አንቀጽ በታች ያሉትን ጥያቄዎች መልስ።

7 እያንዳንዳችን የምልክቱ ፍጻሜ የሆኑትን ክንውኖችና የሰዎችን አመለካከት በንቃት መከታተል ይኖርብናል። እነዚህን ነገሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጋር ማዛመዳችን የይሖዋን ቀን በሐሳባችን አቅርበን እንድንመለከተው ይረዳናል። በተጨማሪም ይህ ቀን መቅረቡን በመግለጽ ሌሎችን በምናስጠነቅቅበት ጊዜ በሚያሳምን መንገድ ለመናገር ያስችለናል። (ኢሳይያስ 61:1, 2) እነዚህን ግቦች በአእምሯችን ይዘን በ⁠ማቴዎስ 24:7 እና በ⁠ሉቃስ 21:10, 11 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን የምልክቱን ክፍሎች ጎላ አድርገው የሚያሳዩትን የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመርምር።

“ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል” የሚለው ትንቢት ከ1914 ጀምሮ ለየት ባለ ሁኔታ የተፈጸመው እንዴት ነው? ከጦርነት ጋር በተያያዘ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ምን ሁኔታዎች ተከስተዋል?

በ1918፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ከሞቱት ይበልጥ በርካታ ሰዎችን የፈጀው ቸነፈር የትኛው ነው? ሰዎች በሕክምና እውቀት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርሱም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እየቀጠፉ ያሉት በሽታዎች የትኞቹ ናቸው?

ባለፈው መቶ ዘመን በሳይንስ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ መድረስ የተቻለ ቢሆንም የምግብ እጥረት ምድርን ምን ያህል አጥቅቷል?

በ⁠2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13 ላይ የተዘረዘሩት ሁኔታዎች ከድሮ ጀምሮ የነበሩ ሳይሆኑ ወደ መጨረሻው ዘመን ፍጻሜ እየተቃረብን ስንሄድ ይበልጥ እየተባባሱ የመጡ መጥፎ ሁኔታዎች እንደሆኑ የሚያሳምንህ ምንድን ነው?

ሰዎችን የመለየት ሥራ

8. (ሀ) ኢየሱስ ከሥርዓቱ መደምደሚያ ጋር አያይዞ የጠቀሰውና በ⁠ማቴዎስ 13:24-30, 36-43 ላይ የተገለጸው ተጨማሪ ነገር ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው?

8 ኢየሱስ ከሥርዓቱ መደምደሚያ ጋር አያይዞ የገለጻቸው ጉልህ ሥፍራ የሚሰጣቸው ሌሎች ክንውኖችም አሉ። ከእነዚህ ክንውኖች አንዱ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ልጆች” ‘ከክፉው ልጆች’ የመለየት ሥራ ነው። ኢየሱስ ጠላት መጥቶ በስንዴ መካከል እንክርዳድ እንደዘራ የሚገልጸውን ምሳሌ በተናገረበት ወቅት ይህን ጠቅሷል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው “ስንዴ” እውነተኛ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያመለክታል። “እንክርዳዱ” ደግሞ ክርስቲያን ነን ቢሉም ዲያብሎስ የሚገዛውን ዓለም የሙጥኝ ብለው በመያዛቸው “የክፉው ልጆች” መሆናቸውን ያሳዩትን ሰዎች ያመለክታል። እነዚህ ሰዎች ‘ከእግዚአብሔር መንግሥት ልጆች’ የተለዩ ሲሆን ለጥፋት ምልክት ተደርጎባቸዋል። (ማቴዎስ 13:24-30, 36-43) ይህ ሁኔታ በእርግጥ ፍጻሜውን አግኝቷል?

9. (ሀ) ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ክርስቲያን ነን ከሚሉ ሰዎች ጋር በተያያዘ ምን ታላቅ የመለየት ሥራ ተካሂዷል? (ለ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች እውነተኛ የመንግሥቱ አገልጋዮች መሆናቸውን ያስመሠከሩት እንዴት ነው?

9 ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ክርስቲያን ነን የሚሉትን ሁሉ በሁለት ወገን የመለየት ሥራ ሲካሄድ ቆይቷል። እነርሱም (1) ብሔራዊ ስሜታቸው እንዳለ ሆኖ ለመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር (አሁን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሚባለው) ብርቱ ድጋፍ የሰጡት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትና ተከታዮቻቸው እንዲሁም (2) ለዓለም ብሔራት ሳይሆን ለመሲሐዊው የአምላክ መንግሥት ሙሉ ድጋፍ የሰጡትና ጦርነቱ ካበቃ በኋላ በነበረው ዘመን ውስጥ የኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች ናቸው። (ዮሐንስ 17:16) እነዚህ ክርስቲያኖች ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ በምድር ዙሪያ በመስበክ የአምላክ መንግሥት እውነተኛ አገልጋዮች መሆናቸውን አስመሥክረዋል። (ማቴዎስ 24:14) ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?

10. የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ያስገኘው የመጀመሪያው ውጤት ምንድን ነው?

10 በመጀመሪያ ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊው መንግሥት የመግዛት ተስፋ ያላቸውን በአምላክ መንፈስ የተቀቡትን ቀሪዎች የመሰብሰቡ ሥራ ተከናውኗል። እነዚህ ሰዎች በተለያዩ ብሔራት ውስጥ ተበታትነው የሚገኙ ቢሆኑም በአንድ ድርጅት ሥር ታቅፈዋል። እነዚህን ቅቡዓን የማተሙ ሥራ ወደ መጠናቀቁ ደርሷል።—ራእይ 7:3, 4

11. በአሁኑ ጊዜ የትኛው የመሰብሰብ ሥራ ቀጥሏል? ይህስ ከየትኛው ትንቢት ጋር ይስማማል?

11 ከዚያ በኋላ ደግሞ በክርስቶስ አመራር በመታገዝ “ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ” መሰብሰብ ተጀመረ። እነዚህ ሰዎች “ከታላቁ መከራ” ተርፈው አምላክ የሚያመጣውን አዲስ ዓለም የሚወርሱ “ሌሎች በጎች” ናቸው። (ራእይ 7:9, 14፤ ዮሐንስ 10:16) መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የሚከናወነው ይህ የአምላክን መንግሥት የመስበኩ ሥራ እስከ ዘመናችን ድረስ ቀጥሏል። በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩት የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑ እጅግ ብዙ ሕዝብ በጣም አስፈላጊ የሆነውን የመንግሥቱን መልእክት በማወጁ ሥራ ቅቡዓን ቀሪዎችን በታማኝነት በመደገፍ ላይ ናቸው። ይህ መልእክት በሁሉም አገሮች በመሰበክ ላይ ነው።

ወደፊት ምን ነገሮች ይከናወናሉ?

12. የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት የስብከቱ ሥራ ምን ያህል መከናወን አለበት?

12 ከላይ ያሉት ማስረጃዎች በሙሉ ወደ መጨረሻዎቹ ቀናት ፍጻሜ እንደተቃረብንና የይሖዋ ቀን በደጅ እንደቀረበ ያመለክታሉ። ሆኖም ይህ አስፈሪ ቀን ከመምጣቱ በፊት መፈጸም ያለባቸው ሌሎች ትንቢቶች አሉ? አዎን፣ አሉ። አንደኛ ነገር፣ ከአምላክ መንግሥት ጉዳይ ጋር በተያያዘ እየተከናወነ ያለው ሰዎችን የመለየት ሥራ ገና አልተጠናቀቀም። ለብዙ ዓመታት ከፍተኛ ተቃውሞ በነበረባቸው አንዳንድ ቦታዎች በአሁኑ ጊዜ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት እየተገኙ ነው። ሰዎች ምሥራቹን ለመቀበል ፈቃደኛ ባልሆኑባቸው ቦታዎችም እንኳ የምንሰጠው ምሥክርነት የይሖዋን ምሕረት በግልጽ ያንጸባርቃል። እንግዲያው በዚህ ሥራ ግፋበት! ኢየሱስ ሥራው ሲጠናቀቅ መጨረሻው እንደሚመጣ አረጋግጦልናል።

13. በ⁠1 ተሰሎንቄ 5:2, 3 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ወደፊት ምን ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ትንቢት ይፈጸማል? ይህስ ለእኛ ምን መልእክት ይኖረዋል?

13 ትልቅ ትርጉም ያለው አንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲህ ይላል:- “ሰዎች፣ ‘ሰላምና ደኅንነት ነው’ ሲሉ፣ ምጥ እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት እንዲሁ ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል፤ ከቶም አያመልጡም።” (1 ተሰሎንቄ 5:2, 3) “ሰላምና ደኅንነት ነው” የሚለው አዋጅ በምን መልኩ እንደሚፈጸም ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ይሁንና ይህ አዋጅ መታወጁ የዓለም መሪዎች ለሰው ዘር ችግሮች ትክክለኛ መፍትሔ አገኙ ማለት እንደማይሆን የተረጋገጠ ነው። የይሖዋን ቀን በሐሳባቸው አቅርበው የሚመለከቱ ሁሉ በዚህ አዋጅ አይታለሉም። ከዚያ በኋላ በድንገት ጥፋት እንደሚመጣ ያውቃሉ።

14. በታላቁ መከራ ወቅት ምን ነገሮች ይከናወናሉ? የሚፈጸሙበት ቅደም ተከተልስ ምን ይመስላል?

14 በታላቁ መከራ መጀመሪያ ላይ ገዥዎች የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ተነስተው ያጠፏታል። (ማቴዎስ 24:21፤ ራእይ 17:15, 16) ከዚያ በኋላ ብሔራት የይሖዋን ሉዓላዊነት በሚደግፉ ሁሉ ላይ የሚነሱ ሲሆን ይህም ይሖዋ በፖለቲካ መንግሥታትና በደጋፊዎቻቸው ላይ እንዲቆጣና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያጠፋቸው ያነሳሳዋል። ታላቁ መከራ በዚህ መንገድ በአርማጌዶን ይደመደማል። ከዚያም ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ጥልቁ ስለሚጣሉ በሰው ዘር ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አይችሉም። በዚህ ሁኔታ የይሖዋ ቀን ይደመደማል፤ ይህም የይሖዋ ስም በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀደስ ያደርጋል።—ሕዝቅኤል 38:18, 22, 23፤ ራእይ 19:11 እስከ 20:3

15. የይሖዋ ቀን ገና ሩቅ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ሞኝነት የሆነው ለምንድን ነው?

15 የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ አምላክ ባወጣው ፕሮግራም መሠረት ጊዜውን ጠብቆ ይመጣል። ፈጽሞ አይዘገይም። (ዕንባቆም 2:3) በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ጥፋት አይሁዳውያን አስጊው ሁኔታ አልፏል ብለው ያስቡ በነበረበት ወቅት ምንም ሳይጠብቁት በድንገት እንደመጣ አስታውስ። ስለ ጥንቷ ባቢሎን ጥፋትስ ምን ለማለት ይቻላል? የጥንቷ ባቢሎን ኃያል፣ በራሷ የምትተማመንና ግዙፍ በሆኑ ግንቦች የታጠረች ነበረች። ሆኖም በአንድ ሌሊት ወድቃለች። ልክ እንደዚሁ አሁን ባለው ክፉ ሥርዓት ላይም ድንገተኛ ጥፋት ይመጣል። የይሖዋን ቀን በሐሳባችን ሁልጊዜ ቅርብ አድርገን በመመልከት ይህ ጥፋት በሚመጣበት ጊዜ በእውነተኛው አምልኮ የተሳሰርን ሰዎች ሆነን ለመገኘት ያብቃን።

የክለሳ ውይይት

• የይሖዋን ቀን በሐሳባችን ቅርብ አድርገን መመልከታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

• በአሁኑ ጊዜ እየተከናወነ ያለው ሰዎችን የመለየት ሥራ እኛን በግለሰብ ደረጃ የሚነካን እንዴት ነው?

• የይሖዋ ቀን ከመጀመሩ በፊት መፈጸም ያለባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ስለሆነም በግለሰብ ደረጃ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 180 እና 181 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የመጨረሻዎቹ ቀናት በቅርቡ በሰይጣን ሥርዓት ላይ በሚደርሰው ጥፋት ይደመደማሉ