በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን የሚያመልኩ ሁሉ ያገኙት ነፃነት

ይሖዋን የሚያመልኩ ሁሉ ያገኙት ነፃነት

ምዕራፍ አምስት

ይሖዋን የሚያመልኩ ሁሉ ያገኙት ነፃነት

1, 2. (ሀ) አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ምን ዓይነት ነፃነት ሰጥቷቸው ነበር? (ለ) የአዳምንና የሔዋንን እንቅስቃሴ ይቆጣጠሩ የነበሩትን አንዳንድ ሕግጋት ጥቀስ።

ይሖዋ የፈጠራቸው የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ዛሬ ማንም ሰው የሌለው ዓይነት ነፃነት ነበራቸው። የሚኖሩት ውብ በሆነችው ኤደን ገነት ውስጥ ነበር። ፍጹም የሆነ አእምሮና አካል ስለነበራቸው ደስታቸውን የሚሰርቅ ምንም ዓይነት ሕመም አልነበረባቸውም። እንደ ሌሎች ሰዎች ሞት የሚጠብቃቸው አልነበሩም። ከዚህም በተጨማሪ የተሰጣቸውን መመሪያ ብቻ ተከትለው እንደሚሠሩ ሮቦቶች ወይም ማሽኖች አልነበሩም፤ ከዚህ ይልቅ የራሳቸውን ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችል ልዩ የሆነ የመምረጥ ነፃነት ተሰጥቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ነፃነታቸውን እንዳያጡ የአምላክን ሕግጋት ማክበር ነበረባቸው።

2 ለምሳሌ ያህል አምላክ ያወጣቸውን የተፈጥሮ ሕጎች እንመልከት። አምላክ እነዚህን ሕጎች ለአዳምና ለሔዋን በጽሑፍ አስፍሮ ባይሰጣቸውም አፈጣጠራቸው ራሱ እነዚህን ሕግጋት እንዲታዘዙ ያደርጋቸው ነበር። ምግብ ሲያሰኛቸው መብላት፣ ሲጠሙ መጠጣትና ፀሐይ ስትጠልቅ ሲያዩ መተኛት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። ከዚህም ሌላ ይሖዋ ሥራ ሰጥቷቸው ነበር። የተሰጣቸው ሥራ ምን እያደረጉ መኖር እንዳለባቸው የሚያስገነዝባቸው በመሆኑ እንደ ሕግ ሊቆጠር ይችላል። ልጆችን መውለድ፣ በምድር ላይ ያሉትን የተለያዩ ሕያዋን ፍጥረታት መግዛትና መላዋን ምድር እስክትሸፍን ድረስ ገነትን ማስፋት ይጠበቅባቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:15) ይህ እንዴት ያለ ጠቃሚ ሕግ ነው! የማሰብ ችሎታቸውን ጠቃሚ በሆነ መንገድና በተሟላ ደረጃ ለመጠቀም የሚያስችል እጅግ አስደሳች የሆነ ሥራ የመሥራት አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። በተጨማሪም ሥራቸውን በመረጡት መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ነፃነት ነበራቸው። አንድ ሰው ከዚህ የበለጠ ምን ይፈልጋል?

3. አዳምና ሔዋን ውሳኔ የማድረግ ነፃነታቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙ ይችሉ የነበረው እንዴት ነው?

3 እርግጥ ነው፣ አዳምና ሔዋን ውሳኔ የማድረግ መብት ተሰጥቷቸዋል ሲባል የሚያደርጉት ማንኛውም ውሳኔ ጥሩ ውጤት ያስገኛል ማለት አይደለም። ውሳኔ የማድረግ ነፃነታቸውን ሊጠቀሙበት የሚገባው ከአምላክ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ሳይወጡ ነበር። የአምላክን ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች መማር የሚችሉት እንዴት ነው? ፈጣሪያቸውን በማዳመጥና ሥራዎቹን በማስተዋል ነው። አምላክ የተማሩትን በሥራ ለመተርጎም የሚያስችል የማሰብ ችሎታ ሰጥቷቸዋል። ፍጹማን ሆነው የተፈጠሩ በመሆናቸው ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ የአምላክን ባሕርያት የማንጸባረቅ ተፈጥሯዊ ዝንባሌ ነበራቸው። አምላክ ላደረገላቸው ነገሮች ልባዊ አድናቆት ካላቸውና እሱን ማስደሰት የሚፈልጉ ከሆነ የአምላክን ባሕርያት ለማንጸባረቅ መጣር ይጠበቅባቸው ነበር።—ዘፍጥረት 1:26, 27፤ ዮሐንስ 8:29

4. (ሀ) አዳምና ሔዋን ከአንድ ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ የተሰጣቸው ትእዛዝ ነፃነታቸውን የሚነፍግ ነበር? (ለ) አምላክ ይህን ትእዛዝ መስጠቱ ተገቢ የነበረው ለምንድን ነው?

4 አምላክ ሕይወት ሰጪያቸው እንደመሆኑ መጠን ምን ያህል ለእሱ ያደሩ እንደሆኑና እሱ ካወጣው ገደብ ላለማለፍ ምን ያህል ፈቃደኞች እንደሆኑ ለማየት መፈለጉ ተገቢ ነው። ይሖዋ ለአዳም የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቶት ነበር:- “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።” (ዘፍጥረት 2:16, 17) ሔዋን ከተፈጠረች በኋላም ይህ ሕግ ተነግሯት ነበር። (ዘፍጥረት 3:2, 3) ይህ ትእዛዝ ነፃነት የሚያሳጣቸው ነበር? በፍጹም። ከዚያ ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ ቢከለከሉም እንኳ ብዙ ዓይነት አስደሳች ምግብ ተትረፍርፎላቸው ነበር። (ዘፍጥረት 2:8, 9) ምድርን የፈጠራት አምላክ እንደመሆኑ መጠን ምድር የእሱ ንብረት መሆኗን እንዲገነዘቡ ማድረግ ተገቢ እርምጃ ነበር። በመሆኑም ከዓላማው ጋር የሚጣጣሙና የሰውን ዘር የሚጠቅሙ ሕጎችን የማውጣት መብት አለው።—መዝሙር 24:1, 10

5. (ሀ) አዳምና ሔዋን የነበራቸውን አስደሳች ነፃነት ያጡት እንዴት ነው? (ለ) አዳምና ሔዋን የነበራቸው ነፃነት በምን ተተካ? ይህስ እኛን የነካን እንዴት ነው?

5 ይሁንና የተፈጸመው ሁኔታ ምን ነበር? አንድ መልአክ ከራስ ወዳድነት በመነጨ የሥልጣን ጥም በመገፋፋት የመምረጥ ነፃነቱን አላግባብ የተጠቀመበት ሲሆን በዚህም ሳቢያ ሰይጣን ማለትም “ተቃዋሚ” ሆነ። ከአምላክ ፈቃድ ተቃራኒ የሆነ ተስፋ በመስጠት ሔዋንን አታለላት። (ዘፍጥረት 3:4, 5) አዳምም የአምላክን ሕግ በመጣስ ከሔዋን ጋር ተባበረ። የራሳቸው ያልሆነውን ነገር በመውሰዳቸው የነበራቸውን አስደሳች ነፃነት አጥተዋል። በኃጢአት ባርነት ሥር የወደቁ ከመሆናቸውም በላይ አምላክ በሰጣቸው ማስጠንቀቂያ መሠረት ከጊዜ በኋላ ለሞት ተዳረጉ። ለዘሮቻቸው ኃጢአትን ያወረሱ ሲሆን ይህም ዘሮቻቸው መጥፎ ነገር የመሥራት ዝንባሌ በውስጣቸው እንዲያድር አድርጓል። በተጨማሪም ኃጢአት የሰው ዘሮችን ለበሽታ፣ ለእርጅናና ለሞት አጋልጧቸዋል። ይህ መጥፎ ነገር የመሥራት ዝንባሌ የሰይጣን ተጽዕኖ ታክሎበት በጥላቻ፣ በወንጀል፣ በጭቆናና የብዙ ሰዎችን ሕይወት በቀጠፉ ጦርነቶች የተሞላ ታሪክ ያለው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ እንዲፈጠር አድርጓል። ይህ ሁሉ አምላክ በመጀመሪያ ለሰው ዘር ከሰጠው ነፃነት ፍጹም ተቃራኒ ነው!—ዘዳግም 32:4, 5፤ ኢዮብ 14:1, 2፤ ሮሜ 5:12፤ ራእይ 12:9

ነፃነት ሊገኝ የሚችለው ከየት ነው?

6. (ሀ) እውነተኛ ነፃነት ሊገኝ የሚችለው ከየት ነው? (ለ) ኢየሱስ የተናገረው ስለምን ዓይነት ነፃነት ነው?

6 በአሁኑ ጊዜ በየትኛውም የምድር ክፍል ካለው መጥፎ ሁኔታ አንጻር ሲታይ ሰዎች የተሻለ ነፃነት ለማግኘት መናፈቃቸው ምንም አያስደንቅም። ሆኖም እውነተኛ ነፃነት ሊገኝ የሚችለው ከየት ነው? ኢየሱስ “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:31, 32) ይህ ነፃነት ሰዎች የመሪ ወይም የመስተዳድር ለውጥ ተደርጎ ለማየት የሚጓጉለት ዓይነት ነፃነት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህ ነፃነት የሰውን ልጅ ችግር ከሥረ መሠረቱ የሚያስወግድ ነው። ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው ከኃጢአት ባርነት ነፃ ስለመውጣት ነው። (ዮሐንስ 8:24, 34-36) ስለዚህ አንድ ሰው እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሲሆን በሕይወቱ ላይ ጉልህ ለውጥ ያደርጋል ብሎም ነፃነት ያገኛል!

7. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ ከኃጢአት ነፃ ልንሆን የምንችለው ከምን አንጻር ነው? (ለ) ይህን ነፃነት ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

7 እንዲህ ሲባል ግን በአሁኑ ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች መጥፎ ድርጊት እንዲፈጽሙ የሚገፋፋቸው ውስጣዊ ዝንባሌ ከሚያሳድርባቸው ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ተላቅቀዋል ማለት አይደለም። ኃጢአትን የወረሱ በመሆናቸው ምንጊዜም ቢሆን ከዚህ የኃጢአት ዝንባሌ ጋር ይታገላሉ። (ሮሜ 7:21-25) ይሁን እንጂ አንድ ሰው ከኢየሱስ ትምህርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ የሚኖር ከሆነ የኃጢአት ባሪያ አይሆንም። በመሆኑም ኃጢአት እንደፈለገ የሚቆጣጠረውና የሚያዘው ዓይነት ሰው አይሆንም። ዓላማ በሌለውና ለሕሊና ወቀሳ በሚዳርግ የአኗኗር ዘይቤ አይጠመድም። ቀድሞ የሠራው ኃጢአት በክርስቶስ መሥዋዕት ላይ በሚኖረው እምነት አማካኝነት ይቅር ስለሚባልለት በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይኖረዋል። የኃጢአት ዝንባሌዎች ሊቆጣጠሩት ይሞክሩ ይሆናል፤ ሆኖም የክርስቶስን ንጹሕ ትምህርቶች በማስታወስ ለእነዚህ ዝንባሌዎች እጅ ስለማይሰጥ ኃጢአት ጌታው አይሆንም።—ሮሜ 6:12-17

8. (ሀ) እውነተኛ ክርስትና ምን ነፃነት አስገኝቶልናል? (ለ) ለዓለማዊ ባለ ሥልጣናት ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

8 ክርስቲያኖች በመሆናችን ያገኘነውን ነፃነት እስቲ እንመልከት። ከሐሰት ትምህርቶች፣ ከአጉል እምነትና ከኃጢአት ባርነት ነፃ ወጥተናል። ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታና ስለ ትንሣኤ የሚገልጸውን እውነት ማወቃችን አግባብ ካልሆነ የሞት ፍርሃት አላቅቆናል። ፍጽምና የጎደላቸው ሰብዓዊ መስተዳድሮች በቅርቡ ጻድቅ በሆነው የአምላክ መንግሥት እንደሚተኩ ማወቃችን ተስፋ ቢስ ከመሆን አድኖናል። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:10) ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ነፃነት ለመንግሥት ባለ ሥልጣናትና ለሚያወጧቸው ሕጎች አክብሮት እንዳናሳይ ምክንያት አይሆነንም።—ቲቶ 3:1, 2፤ 1 ጴጥሮስ 2:16, 17

9. (ሀ) ይሖዋ አሁን ባለንበት ዘመን የሰው ልጆች ሊኖራቸው የሚችለውን ከሁሉ የተሻለ ነፃነት እንድናገኝ የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

9 ይሖዋ ይህንንም ያንንም ሞክረን እኛ ራሳችን የተሻለውን የሕይወት መንገድ እንድናገኝ አላደረገም። አፈጣጠራችንንም ሆነ እውነተኛ ደስታና ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝልንን ነገር ያውቃል። በተጨማሪም ከእሱም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያበላሽብን አልፎ ተርፎም ወደ አዲሱ ዓለም እንዳንገባ ሊያደርገን የሚችለው አስተሳሰብም ሆነ ምግባር ምን እንደሆነ ያውቃል። ይሖዋ በፍቅር በመገፋፋት እነዚህን ሁሉ ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስና በሚታየው ድርጅቱ አማካኝነት አሳውቆናል። (ማርቆስ 13:10፤ ገላትያ 5:19-23፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:12, 13) በመሆኑም አምላክ የሰጠንን የመምረጥ ነፃነት ተጠቅመን ምን ማድረግ እንዳለብን መወሰን የእኛ ኃላፊነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠንን ምክር የምንከተል ከሆነ ከአዳም በተለየ ሁኔታ ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ እናደርጋለን። በሕይወታችን ውስጥ ይበልጥ የሚያሳስበን ነገር ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና እንደሆነም እናሳያለን።

ሌላ ዓይነት ነፃነት መመኘት

10. የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ አንዳንዶች ምን ዓይነት ነፃነት ለማግኘት ሊጥሩ ይችላሉ?

10 የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ አንዳንድ ወጣቶች ብሎም አዋቂዎች አንዳንድ ጊዜ ሌላ ዓይነት ነፃነት ሊያምራቸው ይችላል። ይህ ዓለም በጣም ማራኪ መስሎ ሊታያቸው ይችላል፤ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ባሰቡ መጠን በዓለም ውስጥ ተወዳጅ የሆኑትን ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ድርጊቶች ለመፈጸም ያላቸው ፍላጎት እያየለ ይሄዳል። እነዚህ ሰዎች ዕፆችን ለመውሰድ፣ ከልክ በላይ ለመጠጣት ወይም ዝሙት ለመፈጸም አያስቡ ይሆናል። ሆኖም እውነተኛ ክርስቲያኖች ካልሆኑ ሰዎች ጋር ሊወዳጁና በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሊጥሩ ይችላሉ። አልፎ ተርፎም የእነሱን አነጋገርና ምግባር ሊኮርጁ ይችላሉ።—3 ዮሐንስ 11

11. አንዳንድ ጊዜ መጥፎ ነገር እንድንሠራ የሚያባብሉን እነማን ሊሆኑ ይችላሉ?

11 አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያናዊ ያልሆነ ድርጊት እንድንፈጽም የሚያባብለን ይሖዋን አገለግላለሁ የሚል ሰው ሊሆን ይችላል። ይህ ሁኔታ በአንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች ላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን ዛሬም እኛን ሊያጋጥመን ይችላል። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉ ሰዎች ደስታ ያስገኙልናል ብለው የሚያስቧቸውን ነገሮች ማድረግ ይፈልጋሉ፤ ሆኖም እነዚህ ነገሮች የአምላክን ሕግ የሚጻረሩ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ሌሎችም “ራሳቸውን እንዲያስደስቱ” ለመገፋፋት ይሞክራሉ። “እነርሱ ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው ሳሉ፣ ሌሎችን ነጻ ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል።”—2 ጴጥሮስ 2:19

12. የአምላክን ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚጻረር ድርጊት ምን አሳዛኝ ውጤቶች ያስከትላል?

12 ይህ ዓይነቱ ነፃነት የአምላክን ሕግጋት የሚያስጥስ በመሆኑ ምንጊዜም ፍሬው መራራ ነው። ለምሳሌ ያህል ሕገ ወጥ የጾታ ግንኙነት የስሜት መረበሽ፣ በሽታ፣ ሞት፣ ያልተፈለገ እርግዝናና ምናልባትም የትዳር መፍረስ ሊያስከትል ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 6:18፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3-8) አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ ብስጩነትን፣ ሲናገሩ መንተባተብን፣ ብዥታን፣ መፍዘዝን፣ የመተንፈስ ችግርን፣ የቁም ቅዠትንና ሞትን ሊያስከትል ይችላል። በተጨማሪም ሱስ የሚያስይዝ ከመሆኑም በላይ ይህን ሱስ ለማርካት ሲባል ደግሞ ወንጀል ወደ መፈጸም ሊኬድ ይችላል። አልኮል ከልክ በላይ መጠጣትም ተመሳሳይ ችግሮች ያስከትላል። (ምሳሌ 23:29-35) እነዚህን ድርጊቶች የሚፈጽሙ ሰዎች ነፃነት እንዳላቸው ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል፤ ሆኖም ምንም ማድረግ የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ከገቡ በኋላ የኃጢአት ባሪያዎች እንደሆኑ ይገነዘባሉ። ኃጢአት ደግሞ ጨካኝ ጌታ ነው! ከወዲሁ ጉዳዩን ቆም ብለን ማጤናችን እንዲህ ያለ ሁኔታ ላይ እንዳንወድቅ ይጠብቀናል።—ገላትያ 6:7, 8

የችግሮቹ መነሻ

13. (ሀ) ችግር ውስጥ እንድንገባ የሚያደርጉ ምኞቶች ብዙውን ጊዜ የሚቀሰቀሱት እንዴት ነው? (ለ) “መጥፎ ጓደኝነት” ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት የማንን አመለካከት ማወቅ ያስፈልገናል? (ሐ) በአንቀጽ 13 ላይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች መልስ በምትሰጥበት ጊዜ የይሖዋን አመለካከት ጎላ አድርገህ ግለጽ።

13 እስቲ ቆም በልና ብዙውን ጊዜ የችግሮቹ መነሻ ምን እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞትም ከፀነሰች በኋላ ኀጢአትን ትወልዳለች፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች” ሲል ይገልጻል። (ያዕቆብ 1:14, 15) ምኞት የሚቀሰቀሰው እንዴት ነው? ወደ አእምሮ በሚገቡ ነገሮች ነው። ብዙውን ጊዜ ይህ ሁኔታ የሚከሰተው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ከማይከተሉ ሰዎች ጋር በመዋል ነው። እርግጥ ነው፣ ሁላችንም ‘ከመጥፎ ጓደኝነት’ መራቅ እንዳለብን እናውቃለን። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ይሁን እንጂ መጥፎ ጓደኝነት ሲባል ምን ማለት ነው? ይሖዋስ ይህን ጉዳይ የሚመለከተው እንዴት ነው? ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች ማጤናችንና ጥቅሶቹን አውጥተን ማንበባችን ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ሊረዳን ይገባል።

አንዳንድ ሰዎች የተከበሩ መስለው መታየታቸው ጥሩ ጓደኞች ሊያሰኛቸው ይችላል? (ዘፍጥረት 34:1, 2, 18, 19)

ወሬያቸው ብሎም ቀልዳቸው ልንቀርባቸው የሚገቡ ሰዎች መሆናቸውን ያሳያል? (ኤፌሶን 5:3, 4)

ይሖዋ እሱን ከማይወዱ ሰዎች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ብንመሠርት ምን ይሰማዋል? (2 ዜና መዋዕል 19:1, 2)

እምነታችንን ከማይጋሩ ሰዎች ጋር ልንሠራ ወይም ልንማር ብንችልም እንኳ ጠንቃቆች መሆናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (1 ጴጥሮስ 4:3, 4)

ቴሌቪዥንና ፊልም መመልከት፣ ኢንተርኔት መጠቀም እንዲሁም መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና ጋዜጦች ማንበብ ከሌሎች ጋር ጊዜያችንን የምናሳልፍበት ሌላው መንገድ ነው። በእነዚህ ምንጮች አማካኝነት የሚቀርቡ ልንርቃቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ምሳሌ 3:31፤ ኢሳይያስ 8:19፤ ኤፌሶን 4:17-19)

የጓደኛ ምርጫችን፣ ማንነታችንን በተመለከተ ለይሖዋ ምን መልእክት ያስተላልፋል? (መዝሙር 26:1, 4, 5፤ 97:10)

14. በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ቃል የሚሰጠውን ምክር በታማኝነት ሥራ ላይ የሚያውሉ ሁሉ ምን ዓይነት ታላቅ ነፃነት ይጠብቃቸዋል?

14 አምላክ የሚያመጣው አዲስ ዓለም ከፊታችን ይጠብቀናል። የሰው ዘር በሰማይ ሆኖ በሚገዛው የአምላክ መንግሥት አማካኝነት ከሰይጣንም ሆነ በእሱ ቁጥጥር ሥር ካለው ክፉ ሥርዓት ተጽዕኖ ይላቀቃል። ታዛዥ የሆኑ የሰው ዘሮች ቀስ በቀስ ከኃጢአት ውጤቶች ሙሉ በሙሉ ስለሚላቀቁና በአእምሮም ሆነ በአካል ፍጹም ስለሚሆኑ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ በደስታ ለዘላለም ይኖራሉ። በመጨረሻ ሁሉም ፍጥረት ‘ከይሖዋ መንፈስ’ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ነፃነት ያገኛል። (2 ቆሮንቶስ 3:17) በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ቃል የሚሰጠውን ምክር ቸል በማለት ይህን ሁሉ በረከት ማጣት አሳዛኝ አይሆንም? ዛሬ ሁላችንም ክርስቲያናዊ ነፃነታችንን በአግባቡ በመጠቀም ‘ለእግዚአብሔር ልጆች የሆነውን የከበረውን ነጻነት’ ማግኘት እንደምንፈልግ እናሳይ።—ሮሜ 8:21

የክለሳ ውይይት

• የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ምን ዓይነት ነፃነት ነበራቸው? በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጆች ያሉበት ሁኔታ በዚያን ጊዜ ከነበረው ነፃነት ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል?

• እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ነፃነት አላቸው? ይህስ ዓለም አለኝ ከሚለው ነፃነት ጋር ሲነጻጸር ምን ልዩነት አለው?

• ከመጥፎ ጓደኝነት መራቅ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ከአዳም በተለየ ሁኔታ መጥፎ የሆነውን ነገር በተመለከተ ማን የሚሰጠውን ውሳኔ እንቀበላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 46 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የአምላክ ቃል “አትሳቱ፤ ‘መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል’” ሲል ያስጠነቅቃል