በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ፈጽሞ የማይፈርስ” መንግሥት

“ፈጽሞ የማይፈርስ” መንግሥት

ምዕራፍ አሥር

“ፈጽሞ የማይፈርስ” መንግሥት

1. በሰው ልጅ የታሪክ ዘመናት ሁሉ በዓለም ላይ የታዩት ክስተቶች የትኛውን ሐቅ ጎላ አድርገው ያሳያሉ?

የሰው ልጆች የይሖዋን ሉዓላዊነት አለመቀበላቸውና ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር መሞከራቸው ደስታ እንዳላስገኘላቸው በየዕለቱ በዓለም ላይ የሚታዩት ክንውኖች ያረጋግጣሉ። ለሰው ዘር በእኩል ደረጃ ጥቅም ያስገኘ አንድም ሰብዓዊ አገዛዝ የለም። ምንም እንኳ የሰው ልጆች በሳይንስ እጅግ የመጠቁ ቢሆንም በሽታን ድል ማድረግም ሆነ ሞትን ማስቀረት ተስኗቸዋል፤ ሌላው ቀርቶ ለአንድ ግለሰብ እንኳ ይህን ማድረግ አልቻሉም። ሰብዓዊ አገዛዝ ጦርነትን፣ ዓመጽን፣ ወንጀልን፣ ሙስናንም ሆነ ድህነትን ማስወገድ አልቻለም። አሁንም ቢሆን በብዙ አገሮች ጨቋኝ የሆኑ መንግሥታት አሉ። (መክብብ 8:9) ቴክኖሎጂ፣ ስግብግብነትና ድንቁርና አንድ ላይ ተጣምረው ምድሩን፣ ውኃውንና አየሩን እየበከሉት ነው። ባለ ሥልጣናት የአገርን ኢኮኖሚ አላግባብ ስለሚጠቀሙበት ብዙዎች ለሕይወት የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮችን እንኳ ማግኘት ተስኗቸዋል። በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት የዘለቀው ሰብዓዊ አገዛዝ የሚከተለውን ሐቅ ያረጋግጣል:- “የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ።”—ኤርምያስ 10:23

2. ለሰው ዘር ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ ምንድን ነው?

2 ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት ነው፤ ኢየሱስ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው ስለዚህ መንግሥት እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት 2 ጴጥሮስ 3:13 ላይ “አዲስ ሰማይ” ተብሎ የተገለጸ ሲሆን ይህ መንግሥት ‘አዲሱን ምድር’ ማለትም ጻድቅ የሆነውን ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ይገዛል። የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ የኢየሱስ ስብከት በዋነኝነት ያተኮረው በዚህ መንግሥት ላይ ነበር። (ማቴዎስ 4:17) “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ” የሚል ማሳሰቢያ በመስጠት የአምላክ መንግሥት በሕይወታችን ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ቦታ አመልክቷል።—ማቴዎስ 6:33

3. በአሁኑ ጊዜ ስለ አምላክ መንግሥት መማር እጅግ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?

3 የአምላክ መንግሥት የምድርን አገዛዝ ለዘላለም ለመለወጥ በቅርቡ እርምጃ ስለሚወስድ በአሁኑ ጊዜ ስለዚህ መንግሥት መማር እጅግ አጣዳፊ ነው። ዳንኤል 2:44 “በነዚያ ነገሥታት [አሁን በመግዛት ላይ ባሉት መንግሥታት] ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት [በሰማይ] ይመሠርታል [የሰው ልጆች ዳግመኛ ምድርን አይገዙም]፤ እነዚያን [አሁን ያሉትን] መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” ሲል ይተነብያል። በመሆኑም የአምላክ መንግሥት መላውን ክፉ ሥርዓት በማጥፋት ይህ የመጨረሻ ዘመን እንዲደመደም ያደርጋል። ከዚያም ሰማያዊው መንግሥት ምድርን ያለምንም ተቀናቃኝ ይገዛል። በዚህ መንገድ እፎይታ የምናገኝበት ጊዜ በመቃረቡ ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል!

4. ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘ በ1914 በሰማይ ምን ተከናውኗል? ይህስ ለእኛ በጣም ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

4 በ1914 ክርስቶስ ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ከመሾሙም በተጨማሪ ‘በጠላቶቹ መካከል ሆኖ እንዲገዛ’ ሥልጣን ተሰጥቶታል። (መዝሙር 110:1, 2) ከዚህም ሌላ የዚህ ክፉ ሥርዓት ‘የመጨረሻው ዘመን’ የጀመረው በዚህ ዓመት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13) ዳንኤል በትንቢታዊው ራእይ የተመለከታቸው ክንውኖችም በሰማይ የተፈጸሙት በዚሁ ጊዜ ነበር። “ጥንታዌ ጥንቱ” ተብሎ የተጠራው ይሖዋ አምላክ ለሰው ልጅ ማለትም ለኢየሱስ ክርስቶስ ‘በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ይሰግዱለት ዘንድ ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ሰጥቶታል።’ ዳንኤል ራእዩን ሲዘግብ “ግዛቱም ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው” በማለት ጽፏል። (ዳንኤል 7:13, 14) አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ወላጆቻችንን በገነት ባስቀመጠበት ወቅት ከነበረው ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ጽድቅ ወዳድ የሆኑ የሰው ልጆች ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን መልካም ነገሮች እንዲያገኙ የሚያደርገው በክርስቶስ ኢየሱስ በሚመራው በዚህ ሰማያዊ መንግሥት አማካኝነት ነው።

5. ስለ አምላክ መንግሥት ምን ዝርዝር ጉዳዮችን ማወቅ እንፈልጋለን? ለምንስ?

5 ለዚህ መንግሥት በታማኝነት ለመገዛት ልባዊ ፍላጎት አለህ? እንዲህ ያለ ፍላጎት ካለህ ስለዚህ ሰማያዊ መንግሥት አወቃቀርና አሠራር ለማወቅ እንደምትጓጓ የታወቀ ነው። ይህ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ምን እያከናወነ እንዳለ፣ ወደፊት ምን እንደሚያከናውንና ምን ብቃቶችን እንድታሟላ እንደሚጠብቅብህ ለማወቅ መጓጓትህ አይቀርም። ስለዚህ መንግሥት በሚገባ ለማወቅ ጥረት ስታደርግ አድናቆትህ እየጨመረ ይሄዳል። ለአምላክ መንግሥት አገዛዝ አዎንታዊ ምላሽ ከሰጠህ ይህ መንግሥት ታዛዥ ለሆኑ የሰው ዘሮች የሚያከናውናቸውን አስደናቂ ነገሮች ለሌሎች ለመንገር በሚገባ የታጠቅክ ትሆናለህ።—መዝሙር 48:12, 13

የአምላክ መንግሥት ገዥዎች

6. (ሀ) ቅዱሳን ጽሑፎች በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት የተገለጸው የማን ሉዓላዊነት እንደሆነ የሚጠቁሙት እንዴት ነው? (ለ) ስለ መንግሥቱ የምናገኘው ትምህርት ምን ስሜት ሊያሳድርብን ይገባል?

6 እንዲህ ያለውን ምርምር ስናደርግ በቅድሚያ ከምንገነዘባቸው ነገሮች አንዱ ይህ መሲሐዊ መንግሥት የራሱ የይሖዋ ሉዓላዊ ገዥነት መገለጫ መሆኑን ነው። ለልጁ “ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል” የሰጠው ይሖዋ ነው። የአምላክ ልጅ ንጉሥ ሆኖ እንዲገዛ ሥልጣን ከተሰጠው በኋላ “የዓለም መንግሥት፣ የጌታችንና [የይሖዋ አምላክና] የእርሱ ክርስቶስ መንግሥት ሆነች፤ እርሱም [ይሖዋ] ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል” የሚሉ ድምፆች በሰማይ መሰማታቸው ተገቢ ነው። (ራእይ 11:15) በመሆኑም ስለዚህ መንግሥትና ስለሚያከናውናቸው ነገሮች የምናገኘው ግንዛቤ ሁሉ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ ያስችለናል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የምንማረው ትምህርት ለይሖዋ ሉዓላዊነት ለዘላለም የመገዛት ፍላጎት በውስጣችን ሊያሳድርብን ይገባል።

7. ኢየሱስ ክርስቶስ የይሖዋ ምክትል ገዥ መሆኑ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

7 በተጨማሪም ይሖዋ ኢየሱስ ክርስቶስን ዙፋን ላይ በማስቀመጥ የእሱ ምክትል ገዥ አድርጎ እንደሾመው ልብ በል። ኢየሱስ፣ አምላክ ምድርንና የሰው ልጆችን በፈጠረበት ጊዜ ዋና ሠራተኛ የነበረ እንደመሆኑ መጠን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ከማንኛችንም በላይ ያውቃል። ከዚህም በላይ ከመጀመሪያው የሰው ዘር ታሪክ አንስቶ ‘ለሰው ልጆች ፍቅር’ እንደነበረው አሳይቷል። (ምሳሌ 8:30, 31 NW፤ ቈላስይስ 1:15-17) ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ወደ ምድር በመምጣት ሕይወቱን ለእኛ ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 3:16) በዚህ መንገድ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት በመላቀቅ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችልበትን አጋጣሚ ከፍቶልናል።—ማቴዎስ 20:28

8. (ሀ) የአምላክ መንግሥት ከሰብዓዊ መንግሥታት በተለየ ሁኔታ ጸንቶ የሚኖረው ለምንድን ነው? (ለ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከሰማያዊው መንግሥት ጋር ምን ግንኙነት አለው?

8 የአምላክ መንግሥት የማይናወጥና ለሁልጊዜው ጸንቶ የሚኖር መንግሥት ነው። ይሖዋ የማይሞት መሆኑ ለመንግሥቱ ዘላለማዊነት ዋስትና ይሆናል። (መዝሙር 146:3-5, 10) ይሖዋ ንጉሥ አድርጎ የሾመው ኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ሰብዓዊ ነገሥታት ሟች አይደለም። (ሮሜ 6:9፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:15, 16) በሰማያዊ ዙፋኖች ከክርስቶስ ጋር የሚነግሡ ሌሎች 144,000 ነገሥታት ይኖራሉ። እነዚህ ነገሥታት “ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ” የተውጣጡ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ሲሆኑ እነሱም ከቶ ሊጠፋ የማይችል ሕይወት ይሰጣቸዋል። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1-4፤ 1 ቆሮንቶስ 15:42-44, 53) በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ በሰማይ ይገኛሉ፤ ገና በምድር ያሉት ቀሪዎች ደግሞ “ታማኝና ልባም ባሪያ” በመሆን ከዚህ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ጉዳዮች እዚህ ምድር ላይ በታማኝነት ያከናውናሉ።—ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም

9, 10. (ሀ) የአምላክ መንግሥት የሚከፋፍልና የሚበክል ተጽዕኖ የሚያሳድሩትን የትኞቹን ነገሮች ያስወግዳል? (ለ) የአምላክ መንግሥት ጠላቶች እንዳንሆን ከፈለግን በየትኞቹ ነገሮች እንዳንጠላለፍ መጠንቀቅ ይኖርብናል?

9 በቅርቡ ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ምድርን ከክፋት ለማጽዳት ፍርድ አስፈጻሚ ኃይሎቹን ይልካል። እነዚህ ኃይሎች ሆን ብለው የአምላክን ሉዓላዊነት ለመቀበል አሻፈረን ያሉትንና ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ያደረገልንን ፍቅራዊ ዝግጅቶች የናቁትን ሁሉ ለዘላለም ያጠፋሉ። (2 ተሰሎንቄ 1:6-9) ያ ቀን የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበት ለረጅም ዘመን ሲጠበቅ የኖረው የይሖዋ ቀን ይሆናል። “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ቀን ጨካኝ ነው፤ . . . በውስጧም [በምድር ውስጥ] ያሉትን ኀጢአተኞች ሊያጠፋ፣ ከመዓትና ከብርቱ ቍጣ ጋር ይመጣል።” (ኢሳይያስ 13:9) “ያ ቀን የመዓት ቀን፣ የመከራና የጭንቀት ቀን፣ የሁከትና የጥፋት ቀን፣ የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ይሆናል።”—ሶፎንያስ 1:15

10 በዓይን የማይታየው ክፉው የዚህ ዓለም ገዥ በፈለገው መንገድ የሚያሽከረክራቸው የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ እንዲሁም ሰብዓዊ መንግሥታትና ሠራዊታቸው በጠቅላላ ለዘላለም ይጠፋሉ። ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት እንዲሁም ውሸትና ብልሹ ሥነ ምግባር የተሞላ የአኗኗር መንገድ በመከተል የዓለም ክፍል መሆናቸውን የሚያሳዩ ሁሉ ከምድር ገጽ ይወገዳሉ። ሰይጣንና አጋንንቱ ለአንድ ሺህ ዓመት ታሥረው ከምድር ነዋሪዎች ጋር እንዳይገናኙ ይደረጋል። በዚያን ጊዜ የአምላክ መንግሥት የምድርን ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል። ይህ ጽድቅን ለሚያፈቅሩ ሁሉ እንዴት ያለ ግልግል ይሆንላቸዋል!—ራእይ 18:21, 24፤ 19:11-16, 19-21፤ 20:1, 2

መንግሥቱ ዓላማዎቹን የሚፈጽመው እንዴት ነው?

11. (ሀ) መሲሐዊው መንግሥት ይሖዋ ለምድር ያለውን ዓላማ የሚያስፈጽመው እንዴት ነው? (ለ) የዚህ መንግሥት አገዛዝ በዚያን ጊዜ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል?

11 መሲሐዊው መንግሥት አምላክ ለምድር የነበረውን የመጀመሪያውን ዓላማ ሙሉ በሙሉ ይፈጽማል። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:8, 9, 15) እስካሁንም ድረስ የሰው ዘር ይህን ዓላማ የሚደግፍ ሆኖ አልተገኘም። ይሁንና ‘መጪው ዓለም’ ለሰው ልጅ ማለትም ለኢየሱስ ክርስቶስ ይገዛል። ይሖዋ ይህን አሮጌ ሥርዓት ሲደመስሰው ከጥፋቱ የሚተርፉት በሙሉ በንጉሡ በክርስቶስ አመራር ሥር ሆነው የሚሰጣቸውን መመሪያ ሁሉ በደስታ በመቀበል መላዋን ምድር ገነት ለማድረግ በኅብረት ይሠራሉ። (ዕብራውያን 2:5-9) የሰው ልጆች በሙሉ በእጃቸው ሥራ ይደሰታሉ፤ እንዲሁም ምድር ከምትሰጠው የተትረፈረፈ ምርት ሙሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ።—መዝሙር 72:1, 7, 8, 16-19፤ ኢሳይያስ 65:21, 22

12. የመንግሥቱ ተገዥዎች በአእምሮም ሆነ በአካል ወደ ፍጽምና ደረጃ የሚደርሱት እንዴት ነው?

12 አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ ፍጹማን ነበሩ። ምድር በአእምሮም ሆነ በአካል ፍጹም በሆኑ ዘሮቻቸው እንድትሞላ የአምላክ ዓላማ ነበር። በመንግሥቱ ግዛት ውስጥ ይህ ዓላማ አስደናቂ ፍጻሜውን ያገኛል። ይህ እንዲሆን ግን የኃጢአት ውጤቶች በሙሉ መደምሰስ ይኖርባቸዋል። ለዚህ ሲባል ክርስቶስ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ሊቀ ካህንም ጭምር ሆኖ ያገለግላል። ታዛዥ ተገዥዎቹ ኃጢአትን ከሚያስተሰርየው የሰብዓዊ ሕይወቱ መሥዋዕት እንዲጠቀሙ ኢየሱስ በትዕግሥት ይረዳቸዋል።

13. በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የምድር ነዋሪዎች ምን ዓይነት አካላዊ ፈውስ ያገኛሉ?

13 በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የሚኖሩ የምድር ነዋሪዎች አስደናቂ የሆነ አካላዊ ፈውስ ያገኛሉ። “በዚያን ጊዜም የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ፤ የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ። አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል።” (ኢሳይያስ 35:5, 6) በእርጅና ወይም በሕመም ምክንያት የተጎዳ ሰውነት ከሕፃን ገላ ይበልጥ ይታደሳል። አሁን ፈውስ የሌላቸው አካላዊ ችግሮች ተወግደው የሰው ልጆች የተሟላ ጤንነት ያገኛሉ። “[በዚያን] ጊዜ ሥጋው እንደ ሕፃን ልጅ ገላ ይታደሳል፤ ወደ ወጣትነቱም ዘመን ይመለሳል።” (ኢዮብ 33:25) ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች በሙሉ ከኃጢአትና አስከፊ ከሆኑ የኃጢአት ውጤቶች ስለሚላቀቁ ማንም ሰው “ታምሜአለሁ” ብሎ የማያማርርበት ጊዜ ይመጣል። (ኢሳይያስ 33:24፤ ሉቃስ 13:11-13) አዎን፣ አምላክ “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”—ራእይ 21:4

14. ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና መድረስ ምን ነገርን ይጨምራል?

14 ይሁን እንጂ ወደ ፍጽምና መድረስ ሲባል ጤናማ አካልና አእምሮ ማግኘት ማለት ብቻ አይደለም። የይሖዋን ባሕርያት በትክክል ማንጸባረቅንም ይጨምራል፤ ምክንያቱም የተፈጠርነው ‘በአምላክ መልክና አምሳል’ ነው። (ዘፍጥረት 1:26) ይህም ከፍተኛ የትምህርት ዘመቻ ማካሄድን የሚጠይቅ ይሆናል። በአዲሱ ዓለም ‘ጽድቅ የሚሰፍን’ በመሆኑ ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው “የዓለም ሕዝቦች ጽድቅን ይማራሉ።” (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ኢሳይያስ 26:9) ይህ የጽድቅ ባሕርይ በሁሉም ዘሮች፣ በቅርብ ጓደኛሞች፣ በቤተሰብ አባላትና ከሁሉም በላይ ደግሞ በአምላክና በሰዎች መካከል ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል። (መዝሙር 85:10-13፤ ኢሳይያስ 32:17) ጽድቅን የሚማሩ ሁሉ አምላክ ለእነርሱ ያለውን ፈቃድ እንዲያውቁ ደረጃ በደረጃ ትምህርት ይሰጣቸዋል። ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር ወደ ልባቸው ጠልቆ ሲገባ በማንኛውም የሕይወታቸው ዘርፍ እሱ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ይከተላሉ። ልክ እንደ ኢየሱስ ‘ምንጊዜም አባቴ የሚያስደስተውን አደርጋለሁ’ ብለው መናገር ይችላሉ። (ዮሐንስ 8:29) የሰው ልጆች በሙሉ እንደዚያ ለማለት የሚበቁበት ጊዜ ሲመጣ ሕይወት እንዴት አስደሳች ይሆናል!

አሁንም ቢሆን በግልጽ የሚታዩ ክንውኖች

15. በዚህ አንቀጽ ውስጥ የቀረቡትን ጥያቄዎች በመጠቀም የአምላክ መንግሥት እያከናወናቸው ያሉትን ነገሮች ጎላ አድርገህ ግለጽ፤ እንዲሁም እኛ በአሁኑ ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚጠበቅብን ተናገር።

15 በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መንግሥትም ሆነ ተገዥዎቹ እያከናወኗቸው ያሉትን ድንቅ ነገሮች በግልጽ ማየት ይቻላል። ከዚህ ቀጥሎ ያሉት ጥያቄዎችና ጥቅሶች ከእነዚህ ክንውኖች መካከል አንዳንዶቹን እንዲሁም የመንግሥቱ ተገዥዎች በሙሉ ሊያከናውኗቸው የሚችሏቸውንና ሊያደርጓቸው የሚገቡትን ነገሮች እንድታስተውል ያደርጉሃል።

መንግሥቱ መጀመሪያ እርምጃ የወሰደው በማን ላይ ነው? ይህስ ምን ውጤት አስከተለ? (ራእይ 12:7-10, 12)

ክርስቶስ ዙፋን ላይ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ ትኩረት የተሰጠው የየትኛውን ቡድን ቀሪ አባላት ለመሰብሰቡ ሥራ ነው? (ራእይ 14:1-3)

ማቴዎስ 25:31-33 ላይ በተገለጸው መሠረት ኢየሱስ ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ ምን ሥራ እንደሚያከናውን ትንቢት ተናግሯል?

ይህ ከመሆኑ በፊት በዛሬው ጊዜ የትኛው ሥራ እየተከናወነ ነው? በዚህ ሥራ እየተካፈሉ ያሉትስ እነማን ናቸው? (መዝሙር 110:3፤ ማቴዎስ 24:14፤ ራእይ 14:6, 7)

ፖለቲካዊም ሆኑ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎች የስብከቱን ሥራ ማስቆም ያልቻሉት ለምንድን ነው? (ዘካርያስ 4:6፤ የሐዋርያት ሥራ 5:38, 39)

ራሳቸውን ለአምላክ መንግሥት ያስገዙ ሰዎች በሕይወታቸው ላይ ምን ለውጦች አድርገዋል? (ኢሳይያስ 2:4፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9-11)

ለአንድ ሺህ ዓመት የሚገዛ መንግሥት

16. (ሀ) ክርስቶስ ለምን ያህል ጊዜ ይገዛል? (ለ) በዚያን ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ ምን አስደናቂ ነገሮች ይከናወናሉ?

16 ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ጥልቁ ከተጣሉ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስና 144,000ዎቹ ተባባሪ ገዥዎች ነገሥታትና ካህናት ሆነው ለአንድ ሺህ ዓመት ይገዛሉ። (ራእይ 20:6) በዚያን ጊዜ ኃጢአትም ሆነ በአዳም ምክንያት የመጣው ሞት ለዘላለም ተወግዶ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ ይደረጋል። ኢየሱስ መሲሐዊ ንጉሥና ካህን ሆኖ እንዲያከናውን የተሰጠውን ተልእኮ በተሳካ ሁኔታ በመፈጸም በሺው ዓመት የግዛት ዘመን ማብቂያ ላይ “እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን” ‘መንግሥቱን ለአባቱ ያስረክባል።’ (1 ቆሮንቶስ 15:24-28) በዚህ ጊዜ ሰይጣን፣ አምላክ የተቤዣቸው የሰው ዘሮች የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ይደግፉ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመፈተን ለተወሰነ ጊዜ ከእስር ይፈታል። ይህ የመጨረሻ ፈተና ካበቃ በኋላ ይሖዋ ሰይጣንንና ከእሱ ጎን የተሰለፉትን ዓመጸኞች በሙሉ ያጠፋቸዋል። (ራእይ 20:7-10) የይሖዋን ሉዓላዊነት ማለትም የመግዛት መብቱን የሚደግፉ ሁሉ ፈጽሞ የማይናወጥ የታማኝነት አቋም ያሳያሉ። ከዚያ በኋላ ይሖዋ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ አድርጎ ስለሚቀበላቸው ከእሱ ጋር ትክክለኛ የሆነ ዝምድና የሚመሠርቱ ከመሆኑም በላይ ለዘላለም ሕይወት የሚያበቃ መለኮታዊ ተቀባይነት ያገኛሉ።—ሮሜ 8:21

17. (ሀ) በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ መንግሥቱ ምን ይሆናል? (ለ) ‘መንግሥቱ ፈጽሞ አይጠፋም’ ሲባል ምን ማለት ነው?

17 ስለዚህ ኢየሱስና 144,000ዎቹ ከምድር ጋር በተያያዘ የሚጫወቱት ሚና ይለወጣል። ከዚያ በኋላ የሚያከናውኑት ሥራ ምን ይሆናል? ይህን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም የይሖዋን ሉዓላዊነት በታማኝነት ከደገፍን በሕይወት ቆይተን ይሖዋ በሺው ዓመት የግዛት ዘመን ማብቂያ ላይ ለእነሱም ሆነ ዕጹብ ድንቅ ለሆነው አጽናፈ ዓለም ያለው ዓላማ ምን እንደሆነ ማወቅ እንችላለን። ይሁንና የክርስቶስ የሺህ ዓመት አገዛዝ “ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው።” (ዳንኤል 7:14) ይህ ምን ማለት ነው? አንደኛ ነገር ገዥው ይሖዋ ስለሚሆን የመግዛቱ ሥልጣን የተለየ ዓላማ ላላቸው ለሌሎች አይሰጥም። እንዲሁም ይህ መንግሥት የሚያከናውናቸው ነገሮች ለዘላለም ጸንተው ስለሚኖሩ መንግሥቱ “ፈጽሞ የማይፈርስ” ይሆናል። (ዳንኤል 2:44) በተጨማሪም መሲሐዊው ንጉሥና ካህን እንዲሁም ተባባሪ ነገሥታቱና ካህናቱ ለይሖዋ በሚያቀርቡት የታማኝነት አገልግሎት ለዘላለም ተከብረው ይኖራሉ።

የክለሳ ውይይት

• ለሰው ዘር ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ የአምላክ መንግሥት የሆነው ለምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት ንጉሥ መግዛት የጀመረው መቼ ነው?

• ከአምላክ መንግሥትም ሆነ ይህ መንግሥት ከሚያከናውናቸው ነገሮች ጋር በተያያዘ የአንተን ትኩረት ይበልጥ የሚስበው ነገር ምንድን ነው?

• የአምላክ መንግሥት እያከናወናቸው ያሉ በአሁኑ ጊዜም እንኳ በግልጽ ልናያቸው የምንችላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? እኛስ በዚህ ረገድ ምን ድርሻ እናበረክታለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 92 እና 93 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ሰዎች ሁሉ ጽድቅን ይማራሉ