በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአምላክ ያደርን መሆናችንን በቤታችንም ማሳየት ያስፈልገናል

ለአምላክ ያደርን መሆናችንን በቤታችንም ማሳየት ያስፈልገናል

ምዕራፍ 18

ለአምላክ ያደርን መሆናችንን በቤታችንም ማሳየት ያስፈልገናል

1. (ሀ) ይሖዋ ስለ ጋብቻ ያወጣውን የአቋም ደረጃ ከተማሩ በኋላ ብዙ ሰዎች ምን ለውጥ አድርገዋል? (ለ) ይሁን እንጂ ክርስቲያናዊ የቤተሰብ ኑሮ ምን ሌሎች ነገሮችን ጭምር ይነካል?

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደጀመርን አካባቢ ከተማርናቸው ልብን በደስታ ሞቅ ከሚደርጉት እውነቶች አንዱ ጋብቻንና የቤተሰብን ኑሮ የሚመለከት ነው። የጋብቻ መስራች ይሖዋ መሆኑን ተገንዝበናል። እርሱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለውን የቤተሰብ መመሪያ እንዳስቀመጠልን ተመልክተናል። ብዙ ሰዎች ያንን መመሪያ በመከተል የዘማዊነትን ኑሮ ትተው ጋብቻቸውን በአገባቡ በማስመዝገብ የሚያስመሰግን እርምጃ ወስደዋል። ይሁን እንጂ ክርስቲያናዊው የቤተሰብ ኑሮ በዚህ አያበቃም። የጋብቻውን አንድነት ጽኑ ስለማድረግ፣ በቤተሰብ ውስጥ የየራሳችንን ኃላፊነቶች ስለመፈጸምና ለቤተሰብ አባሎች ስለምናደርገው አያያዝ የነበረንንም ዝንባሌ ይነካል። — ኤፌሶን 5:33 እስከ 6:4

2. (ሀ) ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘውን ዕውቀት ሁሉም ሰው በቤቱ ይሠራበታልን? (ለ) የዚህን አስፈላጊነት ኢየሱስና ጳውሎስ የሚያጐሉት እንዴት ነው?

2 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነዚህ ነገሮች ምን እንደሚል በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያውቃሉ። ሆኖም በቤታቸው ውስጥ ችግሮች ሲነሱ ያንን ዕውቀት አይሠሩበትም። እኛስ ራሳችን እንዴት ነን? አንድ ሰው ሃይማኖተኛ መስሎ ከኖረ “ወላጆችህን አክብር” የሚለውን ትእዛዝ እንዲጠብቅ አይገደድም በማለት የአምላክን ሕግ ያፈረሱትን ሰዎች ኢየሱስ አውግዟቸዋል። አንዳችንም እንደ እነርሱ ለመሆን እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። (ማቴዎስ 15:4–9) ለአምላክ ያደሩ ቢመስሉም ‘ለገዛ ቤተሰቦቻቸው’ በተግባር እንደማያሳዩት ዓይነት ሰዎች ለመሆን አንፈልግም። በዚህ ፋንታ “እጅግ ማትረፊያ” የሆነውን እውነተኛውን ለአምላክ የማደር ጠባይ ለማሳየት መፈለግ አለብን። — 1 ጢሞቴዎስ 5:4፤ 6:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:5

ጋብቻው ለምን ያህል ጊዜ ጸንቶ ይቆያል?

3. (ሀ) ብዙ ጋብቻዎች ምን እየሆኑ ነው? ነገር ግን ምን ቁርጥ ሐሳብ ሊኖረን ይገባል? (ለ) ጋብቻ ቋሚ መሆን እንዳለበት የሚያሳዩትን በአንቀጹ ውስጥ ያሉትን ጥያቄዎች በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት መልሳቸው።

3 የጋብቻ ሰንሰለት በቀላሉ የሚበጠስ እየሆነ መጥቷል። ለ20፣ ለ30ና ለ40 ዓመት አብረው የኖሩ አንዳንድ ሰዎች ከሌላ የትዳር ጓደኛ ጋር “አዲስ ሕይወት” ለመጀመር ወስነዋል። በተጨማሪም ወጣት የትዳር ጓደኞች ከጥቂት ወራት በኋላ ተለያይተዋል የሚለውን ዜና መስማት ባሁኑ ጊዜ እንግዳ አይደለም። ሌሎች የፈለጉትን ቢያደርጉም እኛ ይሖዋን የምናመልክ እንደመሆናችን መጠን አምላክን የማስደሰት ፍላጐት ሊኖረን ይገባል። ታዲያ ቃሉ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሲጋቡ ለምን ያህል ጊዜ አብረን እንኖራለን ብለው ማሰብ አለባቸው? (ሮሜ 7:2, 3፤ ማርቆስ 10:6–9)

በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው ለፍቺ መሠረት የሚሆነው ምን ብቻ ነው? (ማቴዎስ 19:3–9፤ 5:31, 32)

ይሖዋ ቃሉ በሚፈቅደው መሠረት ያልተፈጸመን ፍች ምን ያህል ይጠላዋል? (ሚልክያስ 2:13–16)

መጽሐፍ ቅዱስ ሳይፋቱ ተለያይቶ መኖር የጋብቻን ችግሮች ለመፍታት ይረዳል ይላልን? (1 ቆሮንቶስ 7:10–13)

4. የዘመኑ አዝማሚያ ጋብቻን የሚያዳክም ሆኖ ሳለ አንዳንድ ትዳሮች የሚጸኑት ለምንድን ነው?

4 አንዳንዱ ትዳር ጸንቶ ሲኖር የሌሎች ጋብቻ (ክርስቲያን ነን የሚሉ የአንዳንዶች ጋብቻም ጭምር) የሚፈርሰው ለምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ ሁለቱ ወገኖች እስኪበስሉ ድረስ ሳይጋቡ መቆየታቸው ለትዳሩ መሳካት አንዱ አስፈላጊ ነገር ነው። ተመሳሳይ ፍላጐት ያለውንና ነገሮችን አብሮ በግልጽ ለመወያየት የሚቻለውን የትዳር ጓደኛ ማግኘትም በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ግን ከልቡ ለአምላክ ያደረ ሆኖ ለመኖር የሚፈልግን ሰው ማግኘቱ ነው። አንድ ሰው ይሖዋን በእርግጥ የሚወድና መንገዶቹ ትክክል ናቸው ብሎ የሚያምን ከሆነ በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት ጥሩ መሠረት አለው ማለት ነው። (መዝሙር 119:97, 104፤ ምሳሌ 22:19) የዚህ ዓይነቱ ሰው ጋብቻ “ጥሩ ካልሆነልኝ በፈለግኩት ጊዜ ለመለያየት ወይም ለመፋታት እችላለሁ” በሚል ዝንባሌ የሚቆረቁዝ አይሆንም። በትዳር ጓደኛ ጉድለቶች አሳቦ የራሱን ኃላፊነቶች ገሸሽ አያደርግም። ከዚህ ይልቅ በሕይወት ውስጥ ከሚነሱት ችግሮች ሳይሸሽ እንዴት ተግባራዊ መፍትሔ እንደሚያገኝ ይማራል።

5. (ሀ) ለይሖዋ ታማኝ የመሆኑ ጉዳይ በነገሩ የሚገባው እንዴት ነው? (ለ) በጣም የሚያሰቃይ ሁኔታ በሚደረስበትም ጊዜ ቢሆን የይሖዋን የአቋም ደረጃዎች መጠበቁ ምን ጥቅሞች ሊያመጣ ይችላል?

5 ዲያብሎስ ሰዎች የሚያሰቃይ ችግር ሲደርስባቸው የይሖዋን መንገዶች ይተዋሉ፤ ደግሞም ለራሳቸው ጥሩና መጥፎ ምን እንደሆነ ራሳቸው ቢወስኑ የተሻለ ነው ብለው ይደመድማሉ እያለ እንደሚከራከር በደንብ እናውቃለን። ለይሖዋ በታማኝነት የሚቆሙ ሰዎች ግን እንደዚህ አይሉም። (ኢዮብ 2:4, 5፤ ምሳሌ 27:11) ከማያምን የትዳር ጓደኛ ስደት የደረሰባቸው አብዛኞቹ የይሖዋ ምስክሮች የጋብቻ መሐላቸውን አላፈረሱም። (ማቴዎስ 5:37) እንዲያውም አንዳንዶቹ ከብዙ ዓመታት በኋላ የትዳር ጓደኛቸው አብሮ ይሖዋን ማገልገል በመጀመሩ ደስታ አግኝተዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:16፤ 1 ጴጥሮስ 3:1, 2) ሌሎቹ ግን የትዳር ጓደኛቸው የመለወጥ ዝንባሌ ባያሳይም ወይም በእምነታቸው ስለጸኑ ጥሏቸው ቢሄድም የይሖዋን የአቋም ደረጃዎች በመጠበቃቸው ብዙ እንደተባረኩ ያውቃሉ። የተባረኩት በምን መንገድ ነው? የሚገኙበት ሁኔታ ወደ ይሖዋ የበለጠ መቅረብ እንዳለባቸው አስተምሯቸዋል። በመከራም ጊዜ ጭምር አምላካዊ ጠባዮችን ማሳየት እንዳለባቸው ተምረዋል። አኗኗራቸው ለአምላክ ያደሩ መሆን ምን ዓይነት ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ነው። — መዝሙር 55:22፤ ያዕቆብ 1:2–4፤ 2 ጴጥሮስ 1:5, 6

እያንዳንዱ የበኩሉን ድርሻ ይፈጽም

6. የተሳካ ትዳር እንዲኖር የትኛው ዝግጅት መከበር ይኖርበታል?

6 የተሳካ ትዳር ለማግኘት አብሮ መኖር ብቻ አይበቃም። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ማድረግ የሚኖርበት አንዱ መሠረታዊ ነገር ይሖዋ ያቋቋመውን የራስነት ሥርዓት ማክበር ነው። ይህን ማድረጉ ቤቱ ጥሩ ሥርዓትና የመተማመን መንፈስ የሰፈነበት እንዲሆን ይረዳል። — 1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ቲቶ 2:4, 5፤ ምሳሌ 1:8, 9፤ 31:10, 28

7. በቤተሰብ ውስጥ የራስነት ሥልጣን እንዴት ሊሠራበት ይገባል?

7 ይህ የራስነት ሥልጣን እንዴት ሊሠራበት ይገባል? የኢየሱስ ክርስቶስን ጠባዮች በሚያንፀባርቅ መንገድ መሆን ይኖርበታል። ኢየሱስ የይሖዋን መንገዶች በማስጠበቅ በኩል ጥብቅ ነው፤ ጽድቅን ይወዳል አመጻን ግን ይጠላል። (ዕብራውያን 1:8, 9) ጉባኤውንም በጥልቅ ይወደዋል። ለጉባኤው አስፈላጊውን መመሪያ ይሰጣል፣ እንክብካቤም ያደርግለታል። ‘የዋህ፣ በልቡም ትሑት ነው’ እንጂ ኩራት የሚሰማውና ለሌሎች ደንታ የሌለው አይደለም። ኢየሱስ ራሳቸው የሚሆንላቸው ሰዎች ‘ለነፍሳቸው ዕረፍትን ያገኛሉ።’ (ማቴዎስ 11:28, 29፤ ኤፌሶን 5:25–33) ባልና አባት የሆነው ሰው ቤተሰቡን እንደዚያ አድርጐ ሲይዝ ለአምላክ ያደረ በመሆን በኩል ፍጹም ምሳሌ ለተወለት ለክርስቶስ እየተገዛ እንደሆነ ግልጽ ነው። ክርስቲያን እናቶችም ልጆቻቸውን በዚሁ መንገድ መያዝ ይኖርባቸዋል።

8. (ሀ) በአንዳንድ ቤቶች ክርስቲያናዊ መንገዶች የተፈለገውን ውጤት ያላመጡ መስሎ የሚታየው ለምንድን ነው? (ለ) እንደዚህ ያለ ሁኔታ ቢደርስብን ምን ማድረግ አለብን?

8 ይሁን እንጂ በሰብዓዊ አለፍጽምና ምክንያት ችግሮች ይነሱ ይሆናል። በቤተሰባቸው ውስጥ አንዳቸውም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማክበር ከመጀመራቸው በፊት በሌላ መመራትን አጥብቀው ይጠሉት ኖረው ይሆናል። በለዘበ አንደበት ጥያቄ ማቅረብና ፍቅራዊ መንፈስ ማሳየት ምንም ውጤት አላመጣ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ንዴት፣ ቁጣም፣ ጩኸትም፣ መሳደብም ሁሉ . . . ከእናንተ ዘንድ ይወገድ” እንደሚል እናውቃለን። (ኤፌሶን 4:31) ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ቁጣና ጩኸት እንጂ ሌላ ነገር የማይገባቸው ቢሆኑ ምን መደረግ አለበት? ኢየሱስ ከባድ ተጽዕኖ በደረሰበት ጊዜ ምን አደረገ? የጠላቶቹን መንገድ በመከተል ለዛቻውና ለስድቡ አጸፌታውን በመመለስ ፈንታ ትምክሕቱን በአባቱ ላይ ጥሎ ራሱን ለሱ አደራ ሰጥቷል። (1 ጴጥሮስ 2:22, 23) እኛም በተመሳሳይ እቤታችን ውስጥ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢደርሱብን የዓለምን መንገድ በመከተል ፈንታ ወደ ይሖዋ ዘወር ብለን እንዲረዳን ብንጸልይ ለእርሱ ያደርን መሆናችንን እናሳያለን። — ምሳሌ 3:5–7

9. ብዙ ክርስቲያን ባሎች ጥፋትን ከመከታተል ይልቅ ምን የተሻለ ዘዴ አግኝተዋል?

9 የተፈለጉት ለውጦች ሁልጊዜ ቶሎ አይመጡም። ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በእርግጥ ይሠራል። ስለ ሚስቶቻቸው ጉድለቶች አምርረው ይናገሩ የነበሩ ብዙ ባሎች ክርስቶስ ጉባኤውን እንዴት እንደሚይዝ የበለጠ ሲረዱ ሁኔታው መሻሻል ጀምሮላቸዋል። ጉባኤው ከፍጹማን ሰዎች የተውጣጣ አይደለም። ቢሆንም ኢየሱስ ይወደዋል። ትክክለኛውን ምሳሌ ትቶለታል። ሕይወቱንም ሰውቶለታል። ጉባኤው በሁሉም ነገር እርሱን የሚያስደስት ሆኖ እንዲገኝ በቅዱሳን ጽሑፎች አማካይነት እንዲያሻሽል ይረዳዋል። (ኤፌሶን 5:25–27፤ 1 ጴጥሮስ 2:21) የእርሱ ምሳሌ ብዙ ክርስቲያን ባሎች ጥሩ አርዓያ ለመሆን እንዲጥሩና ለማሻሻል የሚረዳ ፍቅራዊ እርዳታ እንዲሰጡ አበረታቷቸዋል። ስለተሠራው ስሕተት አምርሮ ከመናገርና ከማኩረፍ ይልቅ እንደነዚህ ያሉት ዘዴዎች የተሻለ ውጤት ያስገኛሉ።

10. (ሀ) አባትና ባል የሆነ ሰው (ክርስቲያን ነኝ የሚል አባትና ባል ጭምር) በቤት ውስጥ የሌሎችን ሕይወት አስጨናቂ ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ሁኔታውን ለማሻሻል ምን ሊደረግ ይችላል?

10 በሌላው በኩል ግን በቤት ውስጥ ችግር የሚነሳው በባልየውና በአባትየው ጉድለቶች ምክንያት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ለቤተሰቡ ስሜታዊ ፍላጐቶች የማያስብ ቢሆንስ? ወይም የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይትና ሌሎች ነገሮች በማዘጋጀት ቤቱን በደንብ ባይመራስ? አንዳንድ ቤተሰቦች ችግሩን አክብሮት በተሞላበት መንገድ በግልጽ ሲወያዩበት ጥሩ ውጤት አግኝተዋል። (ምሳሌ 15:22፤ 16:23፤ 31:26) ውጤቱ ተስፋ ያደረግነውን ያህል ባይሆንም እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በግሉ የመንፈስ ፍሬዎችን በመኰትኰትና ለሌሎች የቤተሰቡ አባሎች ፍቅራዊ አሳቢነት በማሳየት የቤቱ መንፈስ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ ለማድረግ ይቻላል። መሻሻል የሚመጣው ሌላው ለውጥ እንዲያደርግ በመጠበቅ ሳይሆን የበኩላችንን ድርሻ እያከናወንን እኛ ራሳችን በቤታችን ውስጥ ለአምላክ ያደርን መሆናችንን በማሳየት ነው። — ቆላስይስ 3:18–20, 23, 24

መልስ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

11, 12. (ሀ) ይሖዋ በቤተሰብ ኑሮ ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመወጣት የሚረዱ ምን ዝግጅቶች አድርጎልናል? (ለ) የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ምን ብናደርግ ጥሩ ነው?

11 ሰዎች ስለቤተሰብ ጉዳዮች ምክር ለማግኘት የሚሄዱባቸው ምንጮች ብዙ ናቸው። እኛ ግን የአምላክ ቃል ከሁሉ የሚበልጠውን ምክር እንደያዘ እናውቃለን። ይሖዋ በሚታየው ድርጅቱ አማካኝነት ምክሩን እንድንሠራበት ስለሚረዳን እናመሰግነዋለን። ታዲያ ይህንን እርዳታ ሙሉ በሙሉ እየተጠቀምክበት ነውን? — መዝሙር 119:129, 130፤ ሚክያስ 4:2

12 ወደ ጉባኤ ስብሰባ ከመሄዳችሁ በተጨማሪ ፕሮግራም አውጥታችሁ ዘወትር የቤተሰብ ጥናት ታደርጋላችሁን? በየሣምንቱ ይህን የሚያደርጉ ቤተሰቦች በአምልኰአቸው አንድ ይሆናሉ። የአምላክ ቃል ለራሳቸው ሁኔታ እንዴት እንደሚሰራ ሲወያዩበት የቤተሰባቸው ኑሮ የተባረከ ይሆናል። — ከዘዳግም 11:18–21 ጋር አወዳድር።

13. (ሀ) ስለ ጋብቻ ወይም ስለ ቤተሰብ ጉዳይ ጥያቄ ካለን መልሱን ለማግኘት ምን ይረዳናል? (ለ) የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ ምን ማንፀባረቅ አለባቸው?

13 ምናልባት አንተን የሚያሳስቡ ጋብቻን ወይም የቤተስብን ጉዳዮች የሚመለከቱ ጥያቄዎች ይኖሩህ ይሆናል። ለምሳሌ የወሊድ ቁጥጥር እንዴት ነው? በሕክምና አማካኝነት መኻን መሆን ለክርስቲያኖች ተገቢ ነውን? ሕፃኑ አካለ ጐደሎ ሆኖ የሚወለድ ከመሰለ ጽንሱን ማስወረድ ይቻላልን? በባልና በሚስት መካከል የሚደረገው የሩካቤ ሥጋ ዓይነት ወሰን አለውን? የጐረመሰ ልጅ ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጐት ከሌለው ከቤተሰቡ ጋር በአምልኰ መካፈል አለብህ ሊባል የሚችለው እስከምን ድረስ ነው? ስለ እነዚህ ነገሮች የራስህ ሐሳብ እንደሚኖርህ አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተመርኩዘህ ልትመልሳቸው ትችላለህን? እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች በመጠበቂያ ግንብ ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። በኢንዴክስ ተጠቅመህ እንደዚህ ዓይነቱን ማብራሪያ እንዴት ማግኘት እንደምትችል ተማር። ኢንዴክሱ የሚጠቅሳቸው የቆዩ ጽሑፎች ከሌሉህ በመንግሥት አዳራሹ ያሉትን መጻሕፍት ተመልከት። ለእያንዳንዱ ጥያቄ “ይቻላል” ወይም “አይቻልም” የሚል ቀጥተኛ መልስ ለማግኘት አትጠብቅ። አንዳንድ ጊዜ በግልህ ወይም ከሚስትህ ጋር ተወያይታችሁ መወሰን ይኖርባችኋል። ሆኖም ለይሖዋና ለቤተሰብህ ፍቅር እንዳለህ የሚያሳዩ ውሳኔዎችን አድርግ። አምላክን ለማስደሰት ቅን ፍላጐት እንዳለህ የሚያሳዩ ውሳኔዎች አድርግ። እንደዚህ የምታደርግ ከሆነ በውጭ ብቻ ሳይሆን በቤትህም ጭምር ለምላክ ያደርህ መሆንህን ለይሖዋና በደንብ ለሚያውቁህ ሁሉ ግልጽ ይሆናል። — ኤፌሶን 5:10፤ ሮሜ 14:19

የክለሣ ውይይት

● ለጋብቻ መሐላ ታማኝ መሆን ለይሖዋ ታማኝ መሆን ማለት የሆነው እንዴት ነው?

● ከቤተሰባችን አንድ ዓይነት ተጽዕኖ ሲመጣብን አምላክን የሚያስደስተውን ለማድረግ የሚረዳን ምንድን ነው?

● የቤተሰብ አባሎች ጉድለት ቢኖርባቸውም ሁኔታውን ለማሻሻል ምን ልናደርግ እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]