በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ምን ጊዜም አስቀድመህ መንግሥቱን ፈልግ’

‘ምን ጊዜም አስቀድመህ መንግሥቱን ፈልግ’

ምዕራፍ 11

‘ምን ጊዜም አስቀድመህ መንግሥቱን ፈልግ’

1. (ሀ) ኢየሱስ ከ1, 900 ዓመታት በፊት ከሁሉ አስቀድማችሁ መንግሥቱን ፈልጉ ብሎ የተናገረው ለምንድን ነው? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ አለብን?

ከ1,900 ዓመታት በፊት ኢየሱስ በገሊላ ተሰብስቦ ለነበረ ሕዝብ በሰጠው ንግግር ላይ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ” ሲል አድማጮቹን አሳስቧል። ለምን ይህን ምክር ሰጠ? ክርስቶስ በዙፋኑ ለመቀመጥ ገና ብዙ መቶ ዓመታት ቀርተውት አልነበረምን? አዎን፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ ቅዱስ ስሙን ለማስከበርና ለምድር ያለውን ዓላማ ለማስፈጸም መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀምበት ይህ መሲሐዊ መንግሥት ነው። የዚህን አስፈላጊነት በትክክል የተገነዘበ ማንኛውም ሰው በሕይወቱ ውስጥ ለመንግሥቱ የመጀመሪያውን ቦታ ይሰጣል። በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሆነ መንግሥቱ በሚገዛበት በአሁኑ ጊዜ ሁኔታው እንደዚሁ ነው። ታዲያ ከሁሉ በፊት የአምላክን መንግሥት እንደምትፈልግ አኗኗርህ ያሳያልን? — ማቴዎስ 6:33

2. ሰዎች በአጠቃላይ በጉጉት የሚፈልጓቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

2 ሕዝቦች በአጠቃላይ ፍላጎታቸው ያረፈው በሌሎች ነገሮች ላይ ነው። ሀብትን በጦፈ ስሜት ያሳድዳሉ፣ ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችሉትን ልብስ፣ ምግብና ሌሎች ሥጋዊ ንብረቶችና ተድላዎች ለማግኘት ይጓጓሉ። (ማቴዎስ 6:31, 32) አኗኗራቸው በግል ጥቅምና ተድላዎች የተጠመዱ መሆናቸውን ያሳያል። በሕይወታቸው ውስጥ ለአምላክ ሁለተኛ ቦታ ይሰጣሉ፤ ያውም ካመኑበት።

3. (ሀ) ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ ምን ዓይነት ሀብቶችን እንዲፈልጉ አበረታታቸው? ለምንስ? (ለ) ስለሚያስፈልጉን ሥጋዊ ነገሮች ከመጠን በላይ ማሰብ የማያስፈልገን ለምንድን ነው?

3 ኢየሱስ ግን ለደቀመዛሙርቱ “በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ” የሚል ምክር ሰጥቷል፤ ምክንያቱም ከእነዚህ ንብረቶች አንዱም እንኳ ቢሆን ለዘላለም አይኖርም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን በማገልገል “በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ” ሲል ኢየሱስ መክሮናል። ተከታዮቹ ዓይናቸው “ጤናማ” እንዲሆን (ወይም እንደ አዓት ‘ዓይናቸው በትክክል የሚያይ እንዲሆን’) ይኸውም የአምላክን ፈቃድ በማድረጉ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አሳስቧቸዋል። “ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም” ሲል ነገራቸው። እንደ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ የመሳሰሉት አስፈላጊ ሥጋዊ ነገሮችስ? ኢየሱስ “አትጨነቁ” የሚል ምክር ሰጥቷል። ተከታዮቹ ወፎችን እንዲመለከቱ አሳሰባቸው። ወፎችን አምላክ ይመግባቸዋል። ከአበቦችም እንዲማሩ አበረታታቸው። አበቦችን አምላክ ውብ አድርጎ አልብሷቸዋል። የማሰብ ችሎታ ያላቸው የይሖዋ ሰብዓዊ አገልጋዮች ከእነዚህ ሁሉ አይበልጡምን? ስለዚህ ኢየሱስ “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሐርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ [ማለትም አስፈላጊ የሆነው ነገር ሁሉ] ይጨመርላችኋል” አለ። (ማቴዎስ 6:19–34) በዚህ ታምናለህን? የምታደርጋቸው ነገሮች ይህ እምነት እንዳለህ ያሳያሉን?

የመንግሥቱን እውነት ሌሎች ነገሮች ገፍትረው እንዲያስወጡት አትፍቀድ

4. አንድ ሰው ለሥጋዊ ነገሮች ከመጠን በላይ ትኩረት ከሰጠ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? በምሳሌ አስረዳ።

4 አንድ ሰው ስለ ሥጋዊ ነገሮች ከመጠን በላይ የሚያስብ ከሆነ አስከፊ ውድቀት ሊመጣበት ይችላል። መንግሥቱን እፈልጋለሁ ቢልም በልቡ ሌሎች ነገሮቸን የሚያስቀድም ከሆነ የመንግሥቱ እውነት በነዚያ ነገሮች ተገፍትሮ ይወጣል። (ማቴዎስ 13:18, 19, 22) ለምሳሌ አንድ ጊዜ የሕዝብ አለቃ የሆነ አንድ ሀብታም ወጣት ኢየሱስን “የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?” ብሎ ጠየቀው። ሰውየው ንጹሕ ሥነ ምግባር እንዳለውና ለሌሎች ጥሩ ያደርግ እንደነበረ ለኢየሱስ ከሰጠው መልስ መረዳት ይቻላል። ሆኖም ከሥጋዊ ንብረቶች ጋር ከመጠን በላይ ተጣብቆ ነበር። ከእነርሱ ተለይቶ የክርስቶስ ተከታይ ለመሆን አልቻለም። በዚህ ምክንያት ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ መንግሥት ገዥ የመሆን አጋጣሚ አመለጠው። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንደተናገረው “ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል!” — ማርቆስ 10:17–23

5. (ሀ) ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በምን ነገሮች እንዲረካ መከረው? ለምንስ? (ለ) ሰይጣን “የገንዘብን ፍቅር” እንደ አጥፊ ወጥመድ አድርጎ የሚጠቀምበት እንዴት ነው?

5 ከዚያ ብዙ ዓመታት ቆይቶ ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ ሀብታም የንግድ መናኸሪያ በነበረችው በኤፌሶን ከተማ ለነበረው ለጢሞቴዎስ ደብዳቤ ጻፈለት። ጳውሎስ “ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና አንዳችም ልንወስድ አይቻለንም። ምግብና ልብስ ከኖረን ግን እርሱ ይበቃናል” ሲል አሳስቦታል። ለራስና ለቤተሰብ የሚያስፈልገውን ተስማሚ “ምግብና ልብስ” ለማግኘት ሲባል መሥራት ትክክል ነው። ሆኖም ጳውሎስ “ባለጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ” ሲል አስጠንቅቋል። የሰይጣን አቀራረብ የረቀቀ ነው። በመጀመሪያ ማራኪ ነገር አቅርቦ አንድን ሰው በትንንሽ መንገዶች ያስተው ይሆናል። ከዚያ በኋላ ብዙውን ጊዜ ጠንከር ያሉ ተጽዕኖዎች ይከተላሉ። ምናልባት በመሥሪያ ቤት የደመወዝ ጭማሪ ያለው የሥራ ዕድገት ያገኝ ይሆናል። ነገር ግን አዲሱ ሥራ በፊት ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ተመድቦ የነበረውን ጊዜ ይሻማበታል። ካልተጠነቀቅን “ገንዘብን መውደድ” በጣም አስፈላጊ የሆኑትን የመንግሥቱን ፍላጎቶች ከልባችን ገፍትሮ ሊያወጣቸው ይችላል። ጳውሎስ እንደገለጸው “አንዳንዶችም ይህን [ገንዘብን] ሲመኙ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ስቃይ ራሳቸውን ወጉ።” — 1 ጢሞቴዎስ 6:7–10

6. (ሀ) ከወጥመድ ለመዳን ምን ማድረግ አለብን? (ለ) ዛሬ ያለው የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ ሲታይ እንደዚያ ማድረግ ይቻላልን?

6 ጳውሎስ ለክርስቲያን ወንድሙ ለጢሞቴዎስ በነበረው እውነተኛ ፍቅር ተገፋፍቶ “ከዚህ ሽሽ . . . መልካሙን የእምነት ገደል ተጋደል” ብሎታል። (1 ጢሞቴዎስ 6:11, 12) በዙሪያችን ባለው ዓለም የፍቅረ ንዋይ መንገድ ጭልጥ ብለን እንዳንወሰድ ከፈለግን ከልብ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ነገር ግን ከእምነታችን ጋር በሚስማማ መንገድ በርትተን ብንሠራ ይሖዋ አይተወንም። የዕቃዎች ዋጋ ቢንርና ሥራ አጥነት በጣም ቢስፋፋም የሚያስፈልገንን እንድናገኝ ያደርጋል። ዕብራውያን 13:5, 6

የመጀመሪያዎቹ ደቀመዛሙርት ምሳሌ ይሆኑናል

7. ኢየሱስ ሐዋርያቱ በእሥራኤል እንዲሰብኩ ሲልካቸው ምን መመሪያዎች ሰጣቸው? መመሪያዎቹስ ትክክል የነበሩት ለምንድን ነው?

7 ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ተስማሚ ማሰልጠኛ ከሰጣቸው በኋላ በእሥራኤል ውስጥ ምሥራቹን እንዲሰብኩ ላካቸው። “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” የሚለው መልዕክታቸው እንዴት አስደናቂ ነበር! መሲሐዊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሐከላቸው ነበር። ሐዋርያቱ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በአምላክ አገልግሎት ላይ ስለሚያውሉት ይሖዋ አስፈላጊውን እንክብካቤ ያደርግልናል ብለው እንዲተማመኑ ኢየሱስ አሳሰባቸው። “በትርም ቢሆን፣ ከረጢትም ቢሆን፣ እንጀራም ቢሆን፣ ወርቅም ቢሆን፣ ብርም ቢሆን፣ ለመንገድ አትያዙ፤ ሁለት እጀ ጠባብም አይሁንላችሁ፤ በማናቸውም በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ ከዚያም ውጡ” አላቸው። (ማቴዎስ 10:5–10፤ ሉቃስ 9:1–6፤ 10:4–7) ይሖዋ እንግዳን ማስተናገድ ባሕላቸው በነበረው ሌሎች እሥራኤላውያን አማካኝነት የሚያስፈልጋቸው ሁሉ እንዲሟላላቸው አድርጓል።

8. (ሀ) ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ከፊተኛው ለየት ያለ መመሪያ ለምን ሰጠ? (ለ) ነገር ግን አሁንም ቢሆን በሕይወታቸው ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ መያዝ የነበረበት ምንድን ነው?

8 በኋላ ግን ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ሐዋርያቱ ከበፊቱ ለየት ባለ ሁኔታ ሥር እንደሚሠሩ ገለጸላቸው። ከባለ ሥልጣኖች ተቃውሞ ስለሚኖር በእሥራኤል ውስጥ እንደ ቀድሞው እንግድነት ላይቀበሏቸው ይችላሉ። ከዚህም በላይ የመንግሥቱን መልዕክት ወደ አሕዛብ የሚወስዱበት ጊዜ ሩቅ አልነበረም። ስለዚህ ከዚያ በኋላ የገንዘብ “ከረጢት” እና ስንቅ መያዝ አስፈለጋቸው። ይሁን እንጂ አስፈላጊውን ምግብና ልብስ ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት አምላክ እንደሚባርክላቸው ተማምነው ከሁሉ በፊት የይሖዋን መንግሥትና ጽድቁን መፈለጋቸውን መቀጠል ነበረባቸው። — ሉቃስ 22:35–37

9. (ሀ) ጳውሎስ መንግሥቱን በአንደኛ ቦታ ማስቀመጡን የቀጠለው እንዴት ነው? (ለ) የሚያስፈልጉትን ሥጋዊ ነገሮች እንዴት ያገኝ ነበር? (ሐ) በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ለሌሎች ምን ምክር ሰጠ?

9 ሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሱስን ምክር እንዴት በሥራ ላይ ማዋል እንደሚቻል የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ጳውሎስ ሕይወቱ የተገነባው በአገልግሎቱ ዙሪያ ነበር። (ሥራ 20:24, 25) ለመስበክ ወደ አንድ አካባቢ ሲሄድ ድንኳን በመስፋት የሚያስፈልጉትን ሥጋዊ ነገሮች ራሱ ይችል ነበር። ሌሎች ወጪውን እንዲሸፍኑለት አልጠበቀም። (ሥራ 18:1–4፣ 1 ተሰሎንቄ 2:9፤ 1 ቆሮንቶስ 9:18) ይሁን እንጂ አንዳንዶች ፍቅራቸውንና አድናቆታቸውን በዚህ መንገድ ለመግለጽ ከፈለጉ እንግዳ ተቀባይነታቸውንና ስጦታቸውን በምሥጋና ይቀበል ነበር። (ሥራ 16:15, 34፤ ፊልጵስዩስ 4:15–17) ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ለመስበክ ብለው የቤተሰብ ግዴታቸውን ችላ እንዲሉ አላበረታታም። ከዚህ ይልቅ የተለያዩ ኃላፊነቶቻቸውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማከናወን ነበረባቸው። በገዛ እጃቸው እየሠሩ ቤተሰቦቻቸውን እንዲወዱና ለጋስ ሆነው ለሌሎች እንዲያካፍሉ መከራቸው። (ኤፌሶን 4:28፤ 2 ተሰሎንቄ 3:7–12፤ ቲቶ 2:3–5) ከዚህም በላይ ትምክህታቸውን በሥጋዊ ንብረቶች ሳይሆን በአምላክ ላይ እንዲጥሉና በሕይወት ውስጥ ትልልቆቹ ነገሮች ምን እንደሆኑ መረዳታቸውን በሚያሳይ መንገድ እንዲኖሩ አጠንክሮ መከራቸው። ይህ ማለት መንግሥቱንና ጽድቁን አስቀድማችሁ ፈልጉ ማለት ስለሆነ ከኢየሱስ ትምህርት ጋር የሚስማማ ነው። — ፊልጵስዩስ 1:9–11

በሕይወትህ ውስጥ ለመንግሥቱ አንደኛ ቦታ መስጠትህን ቀጥል

10. (ሀ) ‘ከሁሉ በፊት መንግሥቱን መፈለግ’ ምን ማለት ነው? (ለ) ይሁን እንጂ ምንን ቸል ማለት አይገባንም?

10 የመንግሥቱን ምሥራች ለሌሎች በማካፈሉ ሥራ የቱን ያህል እንሳተፋለን? ይህ በትንሹ በሁኔታዎቻችን ላይ፣ በአብዛኛው ግን በአድናቆታችን ጥልቀት ላይ የተመካ ነው። ኢየሱስ ‘ሌላ ሥራ ካጣችሁ መንግሥቱን ፈልጉ’ እንዳላለ አስታውስ። ወይም ደግሞ አልፎ አልፎ ስለ መንግሥቱ ከተናገራችሁ የሚፈለግባችሁን ሁሉ ፈጽማችኋል አላለም። ወይም ‘የመንግሥቱን ጉዳዮች በቅንዓት መሥራት ጀምሩና አዲሱ ሥርዓት የሚዘገይ መስሎ ከታያችሁ በአምላክ አገልግሎት ትንሽ እየተሳተፋችሁ እንደሌላው ሕዝብ ኑሩ’ አላለም። ከዚህ ይልቅ የመንግሥቱን አስፈላጊነት ያውቅ ስለነበር “ሳታቋርጡ መንግሥቱን ፈልጉ” በማለት በጉዳዩ ላይ የአባቱን ፈቃድ ገልጿል። ወይም ሐዋርያው ማቴዎስ ቃሉን እንደመዘገበው “እንግዲህ መንግሥቱንና ጽድቁን ሁልጊዜ ፈልጉ” ብሏል። (ሉቃስ 12:31፤ ማቴዎስ 6:33 አዓት) ምንም እንኳን አብዛኞቻችን ለራሳችንና ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን ሥጋዊ ነገሮች ለማግኘት አንድ ዓይነት ሥራ መሥራት አስፈላጊ ሆኖ ብናገኘውም በእርግጥ እምነት ካለን በሕይወታችን ውስጥ ትልቁ ነገር አምላክ የሰጠን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዘው ሥራ ይሆናል። ይህንንም እያደረግን የቤተሰብ ኃላፊነታችንን ቸል አንልም። — 1 ጢሞቴዎስ 5:8፤ ምሳሌ 29:15

11. (ሀ) የመንግሥቱን መልዕክት በማሰራጨቱ በኩል ሁሉም የሚሠሩት መጠን አንድ ዓይነት እንደማይሆን ኢየሱስ በምሳሌ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) መጠኑን የሚነኩት ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

11 አንዳንዶቻችን በመስክ አገልግሎት ላይ ከሌሎች የበለጠ ጊዜ ለማሳለፍ እንችላለን። ኢየሱስ ስለተለያዩ የአፈር ዓይነቶች በተናገረው ምሳሌ ላይ ልባቸው እንደ መልካሙ አፈር የሆኑት በሙሉ ፍሬ እንደሚያፈሩ ተናግሯል። ነገር ግን ምን ያህል ያፈራሉ? የግለሰቦች ሁኔታዎች ይለያያሉ። ዕድሜ፣ ጤንነትና የቤተሰብ ኃላፊነት የፍሬውን መጠን ይነካሉ። ሆኖም ልባዊ አድናቆት ካለን ብዙ መሥራት እንችላለን። — ማቴዎስ 13:19, 23

12. በተለይ ወጣቶች የትኛውን ጥሩ መንፈሣዊ ግብ እንዲያስቡበት እናበረታታቸዋለን?

12 በመንግሥቱ አገልግሎት ተሳትፎአችንን ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ግቦች ብናወጣ ጥሩ ነው። ቀናተኛው ወጣት ክርስቲያን ጢሞቴዎስ ያሳየውን እጅግ በጣም ጥሩ አርዓያ ወጣቶች ሁሉ አጥብቀው ሊያስቡበት ይገባል። (ፊልጵስዩስ 2:19–22) ትምህርታቸውን ሲጨርሱ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ከመሆን የበለጠ ምን ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ? ትልልቆችም ቢሆኑ ጥሩ መንፈሳዊ ግቦች ቢኖሩአቸው ሊጠቀሙ ይችላሉ።

13. (ሀ) በመንግሥቱ አገልግሎት ምን ያህል መሥራት እንደምትችል የሚወስንልህ ማን ነው? (ለ) በእርግጥ ከሁሉ በፊት መንግሥቱን የምንፈልግ ከሆነ ይህ የምን ማረጋገጫ ነው?

13 የበለጠ መሥራት ይችሉ ነበር ብለን የምናስባቸውን ሰዎች ከመንቀፍ ይልቅ የራሳችን ሁኔታዎች በሚፈቅዱልን አጋጣሚ ሁሉ አምላክን እንድናገለግል በእምነት ተገፋፍተን ራሳችንን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (ሮሜ 14:10–12፤ ገላትያ 6:4) በኢዮብ ላይ እንደታየው ሁሉ ሰይጣን ሰዎች በተለይ የሚያሳስባቸው ሥጋዊ ንብረታቸው፣ የግል ምቾታቸውና ደኅንነታቸው ነው፤ አምላክን የሚያገለግሉትም ለጥቅም ብለው ነው ባይ ነው። ነገር ግን ከሁሉ አስቀድመን መንግሥቱን በእርግጥ እየፈለግን ከሆነ ሰይጣን ትልቅ ውሸታም መሆኑን ከሚያሳዩት መካከል እንሆናለን። በሕይወታችን ውስጥ አንደኛውን ቦታ የያዘው ሥጋዊ ሀብት ወይም የግል ምቾት ሳይሆን የአምላክ አገልግሎት መሆኑን እናስመሰክራለን። በዚህ መንገድ በቃላችንም ሆነ በድርጊታችን ለይሖዋ የጠለቀ ፍቅር እንዳለን፣ ሉዓላዊነቱን በመደገፍ በታማኝነት እንደምንቆምና ሰውን እንደምንወድ እናረጋግጣለን። — ምሳሌ 27:11፤ ኢዮብ 1:9–11፤ 2:4, 5

14. (ሀ) ለመስክ አገልግሎት ፕሮግራም ማውጣት ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ብዙዎች የይሖዋ ምሥክሮች በመስክ አገልግሎት ምን ያህል ሰዓት ያጠፋሉ? ለምንስ?

14 ያለ ፕሮግራም ከመሥራት ይልቅ በፕሮግራም መሥራቱ የበለጠ እንድናከናውን ይረዳናል። ይሖዋ ራሱ ዓላማውን የሚፈጽምበት ‘የተሰወነ ጊዜ’ አለው። ምሳሌውን ብንከተል ጥሩ ነው። (ዘፀአት 9:5፤ ማርቆስ 1:15፤ ገላትያ 4:4) የምንችል ከሆነ በመስክ አገልግሎት በየሣምንቱ አንድ ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ ብንካፈል ጥሩ ነው። በዓለም ዙሪያ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ረዳት አቅኚ በመሆን ምሥራቹን በመስበክ በየቀኑ ሁለት ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ያሳልፋሉ። አንዳንዶች ያለማቋረጥ ዓመቱን በሙሉ ሌሎች ደግሞ በዓመቱ ውስጥ አልፎ አልፎ ረዳት አቅኚ ይሆናሉ። በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች አስፋፊዎች ደግሞ የዘወትር አቅኚ በመሆን በየቀኑ ቢያንስ ሦስት ሰዓት የመንግሥቱን መልዕክት በማወጅ ያጠፋሉ። ልዩ አቅኚዎችና ሚስዮናውያን ግን ከዚያ በላይ ሰዓት በመንግሥቱ አገልግሎት ላይ ያውላሉ። ሁላችንም በመስክ አገልግሎት ላይ በምንሠማራበት ጊዜም ሆነ በሌላ ጊዜ አጋጣሚ ፈልገን ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑት ሁሉ የመንግሥቱን ተስፋ ለመንገር እንችላለን። (ከዮሐንስ 4:7–15 ጋር አወዳድር) ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ሲል የተናገረው ትንቢት ምን ማድረግን እንደሚጠቁም አጥብቀን ብናስብበት ጥሩ ነው። ሁኔታዎቻችን በሚፈቅዱልን ሁሉ በዚህ ሥራ መሳተፍ ፍላጎታችን መሆን አለበት። — ማቴዎስ 24:14፤ ኤፌሶን 5:15–17

15. አገልግሎታችንን በሚመለከት የ1 ቆሮንቶስ 15:58 ምክር ለዚህ ጊዜ የሚስማማ መስሎ የሚታይህ ለምንድን ነው?

15 በሁሉም የምድር ክፍሎች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የየትኛውም አገር ነዋሪዎች ቢሆኑ በአንድነት በዚህ ታላቅ የአገልግሎት መብት ይሳተፋሉ። “ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፣ የማትነቃነቁም፣ የጌታም ሥራ ሁል ጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ” የሚለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር ይሠሩበታል። — 1 ቆሮንቶስ 15:58

የክለሳ ውይይት

● ኢየሱስ ዘወትር አስቀድማችሁ መንግሥቱን ፈልጉ ሲል ምን ነገር ሁለተኛ ቦታ መያዝ እንዳለበት ማመልከቱ ነበር?

● ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን ሥጋዊ ነገሮች ለማግኘት ስለ መሥራት እንዴት ያለ አመለካከት ሊኖረን ይገባል? አምላክስ ምን እርዳታ ይሰጠናል?

● በመንግሥቱ አገልግሎት ተሳትፎ እስካደረግን ድረስ የተሳትፎአችን መጠን የቱንም ያህል ቢሆን ለውጥ ያመጣልን? ለምንስ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]