በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምክርን ስማ፣ ተግሣጽን ተቀበል

ምክርን ስማ፣ ተግሣጽን ተቀበል

ምዕራፍ 16

ምክርን ስማ፣ ተግሣጽን ተቀበል

1. (ሀ) ከመካከላችን ምክርና ተግሳጽ የማያስፈልገው ሰው አለን? (ለ) ነገር ግን የትኞቹን ጥያቄዎች ብናስብባቸው ጥሩ ነው?

“ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን” በሚለው ጥቅስ አብዛኞቻችን ያለ ምንም ማመንታት እንስማማለን። (ያዕቆብ 3:2 አዓት) የአምላክ ቃል እንድንሆን እንደሚያሳስበን፣ እኛም መሆን እንደምንፈልገው ዓይነት ሰው ሳንሆን የቀረንበትን ጊዜ ማስታወስ አያስቸግረንም። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስ “ምክርን ስማ፣ ተገሣጽንም ተቀበል፣ በፍጻሜህ ጠቢብ ትሆን ዘንድ” ሲል የሚናገረው ቃል ትክክል መሆኑን እናምናለን። (ምሳሌ 19:20) ይህ ዓይነቱ እርዳታ እንደሚያስፈልገን እናውቃለን። አኗኗራችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ከተማርነው ትምህርት ጋር እንዲስማማ አንዳንድ ማስተካከያዎችን እንዳደረግን አያጠራጥርም። ነገር ግን አንድ ክርስቲያን ወንድማችን እኛ ያደረግነውን ጥበብ የጐደለው አድራጎት ለይቶ በመጥቀስ ግልጽ ምክር ቢሰጠን እንዴት ይሰማናል? ወይም በአንዱ ዓይነት ሥራ እንዴት ማሻሻል እንደምንችል ሐሳብ ቢሰጠንስ?

2. (ሀ) በግል ምክር ሲሰጠን አመስጋኝ መሆን ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ምን ማድረግ የለብንም?

2 በሰብዓዊ አለፍጽምና የተነሳ ለጊዜው በውስጣችን አንዳንድ የማንገራገር ስሜት ቢሰማንም ስለ ምክሩ ከልብ አመስግነን በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ማድረግ አለብን። እንደዚህ ማድረጋችን ጠቃሚ ውጤት ሊያመጣ ይችላል። (ዕብራውያን 12:11) ሆኖም ምክር ሲሰጠን የሠራሁት ትክክል ነው ብለን ለመከራከር ወይም ስህተቱን ለማቃለል ወይም በሌላው ሰው ለማመካኘት ሞክረን ይሆናል። እንደዚህ አድርገህ ታውቃለህን? ነገሩ እንደገና ትዝ ሲለን ምክሩን በሰጠን ላይ ቅሬታ ይሰማናልን? ከተወቃሽነት የሚያድነን ይመስል ምክር የሰጠንን ሰው ስህተቶች የመልቀም ወይም የምክር አሰጣጡን ዘዴ የመንቀፍ ዝንባሌ ያድርብናልን? አንድ ሰው እንደነዚህ ያሉትን ዝንባሌዎች ከራሱ እንዲያስወግድ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳው ይችል ይሆን?

እኛን ለመምከር የተመዘገቡ ምሳሌዎች

3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ለምክርና ለተግሣጽ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዱንን ምን ነገሮች ይዞአል? (ለ) ከላይ ባሉት ጥያቄዎች ተጠቅመህ ሳዖልና ኦዝያን ለምክር ያሳዩትን ዝንባሌ ግለጽ።

3 የአምላክ ቃል ስለዚሁ ጉዳይ በቀጥታ ብዙ ምክር ከመስጠቱም በላይ ምክር ስለተሰጣቸው ግለሰቦች የሚገልጹ እውነተኛ ታሪኮችንም ይዟል። ለሰዎቹ የተሰጠው ምክር ብዙ ጊዜ እንደ ተግሳጽም ጭምር ነበር፤ ምክንያቱም ሰዎቹ አመለካከታቸውን ወይም ጠባያቸውን እንዲለውጡ የሚጠይቅባቸው ምክር ነበር። ከእነዚህ ምሳሌዎች መካከል አንደንዶቹን በሚከተሉት ጥያቄዎች አማካኝነት ስትመረምራቸው ለሁላችንም ጠቃሚ የሆነ ብዙ ትምህርት እንዳለ ትረዳለህ።

የቂስ ልጅ ሳዖል:- ከአማሌቅ ጋር በተዋጋ ጊዜ ንጉሡንና ጥሩ ጥሩዎቹን እንስሳት ባለመግደሉ ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ሳይታዘዝ ቀርቷል። (1 ሳሙኤል 15:1–11)

ሳሙኤል እየወቀሰ ሲያርመው ሳዖል በደሉን ትንሽ ለማስመሰል ይሞክር እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው? (ቁጥር 20ን ተመልከት) በማን ለማሳበብ ሞከረ? (ቁጥር 21) በመጨረሻው ስህተቱን ሲያምን ምን ብሎ አመካኘ? (ቁጥር 24) እዚህ ነጥብ ላይ ከደረሰ በኋላም ቢሆን ከሁሉ በላይ ያሳሰበው ነገር ምን ይመስላል? (ቁጥር 25, 30)

ዖዝያን:- በይሖዋ ቤተመቅደስ ውስጥ ዕጣን ለማጠን የተፈቀደላቸው ካህናት ብቻ ቢሆኑም እርሱ እንደዚያ ለማድረግ ወደ ቤተ መቅደሱ ገብቷል። (2 ዜና. 26:16–20)

ዋናው ካህን ንጉሥ ዖዝያንን ለስማቆም ሲሞክር ንጉሡ በጣም የተናደደው ለምንድን ነው? (ቁጥር 16ን ተመልከት) ውጤቱ ምን ሆነ? (ቁጥር 19–21)

4. (ሀ) ሳዖልና ዖዝያን ምክርን መቀበል ከባድ የሆነባቸው ለምን ነበር? (ለ) ዛሬም ይህ ከባድ ችግር ያለው ለምንድን ነው?

4 ከላይ በተጠቀሱት ምሳሌዎች ግለሰቦቹ ምክር የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ለመቀበል የተቸገሩት ለምንድን ነው? መሠረታዊ ችግራቸው ኩራት ነበር። ራሳቸውን ከመጠን በላይ ከፍ አድርገው ተመለከቱ። ዛሬም ብዙ ሰዎች በዚህ ጠባይ ምክንያት በራሳቸው ላይ ብዙ መከራ ያመጣሉ። በዕድሜአቸው ወይም በሥልጣናቸው ምክንያት ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደደረሱ ስለሚሰማቸው በግል ምክር ሲቀርብላቸው አይቀበሉም። ምክሩ ጉድለት ያለባቸው መሆኑን እንደሚያመለክት ወይም ስማቸውን እንደሚያጐድፍ ሆኖ ይሰማቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ደካማነትን የሚያመለክተው ኩራት ነው። ኩራት በብዙዎች ላይ የሚታይ መሆኑ ምክንያት ሊሆነን አይችልም። ሰይጣን አንድ ሰው ይሖዋ በቃሉና በሚታየው ድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠውን ፍቅራዊ እርዳታ እንዳይቀበል አስተሳሰቡን ለማጨለም የሚጠቀምበት አንዱ ወጥመድ ይህ ነው። ይሖዋ “ትዕቢት ጥፋትን፣ ኩሩ መንፈስ ውድቀትን ይቀድማል” ሲል ያስጠነቅቀናል። — ምሳሌ 16:18፤ በተጨማሪም ሮሜ 12:3ንና ምሳሌ 16:5ን ተመልከት።

5. የዚህ አንቀጽ ክፍል በሆኑት ጥያቄዎች ተጠቅመህ ስለ ሙሴና ስለ ዳዊት ከሚናገሩት ታሪኮች ምን ትምህርት ማግኘት እንደምትችል አስረዳ።

5 በሌላው በኩል ግን ቅዱሳን ጽሑፎች ምክርን በመቀበል ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑንን ሰዎች ታሪክ ይዘዋል። ከእነርሱም ጠቃሚ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን። ለምሳሌ የሚከተሉትን ተመልከት:-

ሙሴ:- አማቱ ጤንነቱን ሳይጐዳ ከባድ ኃላፊነቱን እንዴት ማከናወን እንደሚችል ተግባራዊ ምክር ሰጠው። ሙሴ ምክሩን ሰማና ወዲያው በሥራ ላይ አዋለው። (ዘፀአት 18:13–24)

ሙሴ ከፍተኛ ሥልጣን ቢኖረውም ጥሩ ምክርን ለመቀበል ይህን ያህል ዝግጁ የነበረው ለምንድን ነው? (ከዘኁልቁ 12:3 ጋር አወዳድር) ይህ ጠባይ ለእኛ ምን ያህል እስፈላጊ ነው? (ሶፎንያስ 2:3)

ዳዊት:- ምንዝር ከፈጸመ በኋላ ሴትዮዋን አግብቶ ኃጢአቱን ለመሸፈን ሲል ባልዋ የሚገደልበትን መንገድ ቀይሷል። ይሖዋ ለዳዊት ጥፋቱን ለመንገር ናታንን ከመላኩ በፊት አያሌ ወራት አለፉ። (2 ሳሙኤል 11:2 እስከ 12:12)

ዳዊት ሲወቀስ ለመቆጣት፣ በደሉን ለማቃለል ወይም በሌላ ሰው ለማሳበብ ሞክሯልን? (2 ሳሙኤል 12:13፤ መዝሙር ምዕራፍ 51 ምዕራፉ ከመጀመሩ በፊት ያለውን መግለጫና ከቁጥር 1–3) አምላክ የዳዊትን ንስሐ መቀበሉ ዳዊትና ቤተሰቡ የተፈጸመው ኃጢአት ከሚያስከትለው መዘዝ ነፃ ሆኑ ማለት ነበርን? (2 ሳሙኤል 12:10, 11, 14፤ ዘፀአት 34:6, 7)

6. (ሀ) ዳዊት ጥሩ ምክር ስለሰጡት ሰዎች እንዴት ተሰማው? (ለ) እኛም እንደዚህ ዓይነቱን ምክር ሳናንገራግር ከተቀበልን እንዴት እንጠቀማለን? (ሐ) ከባድ ተግሣጽ ቢሰጠን ምን መርሳት የለብንም?

6 ንጉሥ ዳዊት መልካም ምክርን መስማት የሚያመጣውን ጥቅም ያውቅ ነበር። አንድ ጊዜ እርሱን ለማረም ስለተላከችለት ሴት አምላክን አመስግኖታል። (1 ሳሙኤል 25:32–35፤ በተጨማሪም ምሳሌ 9:8 ተመልከት) እኛስ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ነንን? ከሆንን ፀፀትን የሚያስከትሉ ብዙ ነገሮች ከመናገርና ከማድረግ እንድናለን። ነገር ግን ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ እንደተገሠጸ ሁሉ እኛም ብርቱ ተግሳጽ ወደሚያስፈልገው ነገር ብንገባ ተግሳጹ ለዘላለማዊ ደኅንነታችን ሲባል የመጣ የይሖዋ የፍቅሩ መግለጫ መሆኑን አንርሳ። — ምሳሌ 3:11, 12፤ 4:13

ዋጋ ሊተመንላቸው የማይችሉ ጠባዮችን መኰትኰት

7. ኢየሱስ ሰዎች ወደ መንግሥቱ ለመግባት የትኛው ጠባይ ሊኖራቸው ያስፈልጋል አለ?

7 ከይሖዋና ከወንድሞቻችን ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን አንዳንድ የግል ጠባዮችን መኰትኰት ያስፈልገናል። ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ መካከል አንድ ትንሽ ልጅ አቁሞ የሚከተለውን በተናገረ ጊዜ ከእነዚህ ጠባዮች አንዱን ጐላ አድርጐ አሳይቷል:- “ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው።” (ማቴዎስ 18:3, 4) እነዚያ ደቀ መዛሙርት ለውጥ ማድረግ አስፈልጓቸዋል። ኩራታቸውን አስወግደው ትህትናን መኰትኰት ነበረባ⁠ቸው።

8. (ሀ) በማን ፊት ትሑቶች መሆን ያስፈልገናል? ለምንስ? (ለ) ትሑቶች ከሆንን ምክር ሲሰጠን ምን እናደርጋለን?

8 ከብዙ ጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ ለክርስቲያን ወንድሞቹ “ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትህትናን እንደልብስ ታጠቁ፣ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና ለትሁታን ግን ፀጋን ይሰጣል” ብሎ ጽፎላቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:5) በአምላክ ፊት ትሑት መሆን እንደሚያስፈልገን እናውቃለን። ነገር ግን ይህ ጥቅስ በእምነት ወንድሞቻችን ፊት ትሑት መሆን ወይም ራሳችንን ዝቅ ማደረግ እንደሚያስፈልገን ያሳስበናል። ትህትና ካለን ማሻሻያ ሐሳብ ሲቀርብልን ሞኞች ሆነን በነገሩ ቅር አንሰኝም። አንዳችን ከሌላው ለመማር ፈቃደኛ እንሆናለን። (ምሳሌ 12:15) ወንድሞቻችን እርማት አዘል ምክር ሲያቀርቡልንም ይሖዋ ምክሩን እኛን ለማስተካከል በፍቅሩ እየተጠቀመበት እንዳለ ስለምናውቅ ምክሩን እምቢ አንልም። — መዝሙር 141:5

9. (ሀ) ከትህትና ጋር በጣም የሚቀራረበው የትኛው አስፈላጊ የሆነ ጠባይ ነው? (ለ) የምናደርገው ነገር ሌሎችን እንዴት እንደሚነካ ማሰብ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

9 ከትሕትና ጋር በጣም የሚቀራረበው ሌላው ጠባይ ስለሌሎች ደህንነት ከልብ ማሰብ ነው። የምናደርገው ነገር ሌሎችን ይነካል። ከዚህ ሐቅ ልንሸሽ አንችልም። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስና በሮም የነበሩት የጥንት ክርስቲያኖች ስለ ሌሎች ኅሊና እንዲያስቡ መክሯቸዋል። እርግጥ የግል ምርጫቸውን ሁሉ መተው አለባቸው ማለቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ሌላ ሰው ኅሊናው የከለከለውን ነገር እንዲያደርግ የሚያደፋፍረውን አንድም ነገር ማድረግ የለባቸውም ማለቱ ነው። ያ ወንድም ኅሊናውን መጣሱ ወደ መንፈሳዊ ውድቀት ሊመራው ይችላል። ጳውሎስ ግልጽ የሆነ አጠቃላይ መሠረታዊ ሥርዓት ሲሰጥ እንዲህ ብሏል:- “እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ እንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ . . . እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። . . . ለአይሁድም ለግሪክም ሰዎች ለእግዚአብሔር [ጉባኤም] ማሰናከያ አትሁኑ።” — 1 ቆሮንቶስ 10:24–33፤ 8:4–13፤ ሮሜ 14:13–23

10. ያንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በሥራ ላይ የማዋል ልማድ እንዳለንና እንደሌለን ምን ነገር ሊያሳይ ይችላል?

10 የሌሎችን ደህንነት ከግል ምርጫ የማስቀደም ልማድ ያለህ ሰው ነህን? ይህን ማድረግ የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ፤ ነገር ግን አንድ ምሳሌ እንውሰድ:- ልከኛና ንጹህ እስከሆንን ድረስ የልብስና የፀጉር ስታይል አብዛኛውን ጊዜ የግል ምርጫ ጉዳይ ነው። ነገር ግን የአካባቢያችን ሰዎች በነበራቸው አስተዳደግ የተነሳ የልብሳችን ወይም የፀጉራችን ሁኔታ የመንግሥቱን መልዕክት እንዳያዳምጡ መሰናክል እንደሆነባቸው ብናውቅ ለውጥ እናደርጋለንን? የሌላው ሰው ሕይወት ራስህን ከማስደሰት ይበልጥብ⁠ሃ⁠ልን?

11. በእርግጥ ክርስቲያን ለመሆን ከፈለግን እነዚህን ጠባዮች መኰትኰት እንደሚያስፈልገን የሚያሳየው ምንድን ነው?

11 እስካሁን የተወያየንባቸው ጠባዮች የጠቅላላው ባሕርያችን ክፍል ከሆኑ የክርስቶስን አስተሳሰብ መያዝ ጀምረናል ማለት ነው። ትሑት በመሆን በኩል ኢየሱስ ፍጹም አርአያ ትቶልናል። (ዮሐንስ 13:12–15፤ ፊልጵስዩስ 2:5–8) ራሴን ብቻ ላስደስት ሳይል ለሌሎች አሳቢ በመሆን ረገድ ልንከተለው የሚገባንን ምሳሌ አሳይቶናል። — ሮሜ 15:2, 3

የይሖዋን ተግሳጽ ለመቀበል እምቢ አትበል

12. (ሀ) አምላክን የሚያስደስት ጠባይ እንዲኖረን ሁላችንም ምን ለውጦች ማድረግ ያስፈልገናል? (ለ) ለዚህስ የሚረዱን ምን ነገሮች አሉን?

12 ሁላችንም ኃጢአተኞች ስለሆንን የአምላካችንን ባሕርያት ለማንጸባረቅ በዝንባሌያችን፣ በአነጋገራችንና በፀባያችን ብዙ ለውጦችን ማድረግ ይፈለግብናል። “አዲሱን ሰው” መልበስ ያስፈልገናል። (ቆላስይስ 3:5–14፤ ቲቶ 2:11–14) ምክርና ተግሳጽ የትኞቹን ነገሮች ማስተካከል እንደሚያስፈልገንና እንዴት ልናስተካክላቸው እንደምንችል ለይተን ለማወቅ ይረዱናል።

13. (ሀ)ይሖዋ ለሁላችንም ምክርና ተግሣጽ የሰጠው በምን አማካኝነት ነው? (ለ) ምክሩንስ ምን ማድረግ አለብን?

13 በመሠረቱ የምክሩና የተግሳጹ ምንጭ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) በተጨማሪም ይሖዋ በሚታየው ድርጅቱ አማካኝነት ጽሑፎችና ስብሰባዎች እያዘጋጀ ትምህርቱን እንዴት ልንሠራበት እንደምንችል ለማስተዋል ይረዳናል። ያንን ትምህርት ከአሁን በፊት ሰምተነው ሊሆን ቢችልም ለእኛ በግል እንደሚያስፈልገን በትሕትና አምነንና ተቀብለን ዘወትር ለማሻሻል እንጥራለንን?

14. ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ምን ተጨማሪ እርዳታ ይሰጠናል?

14 በጣም የተቸገርንበት ነገር ቢኖር ይሖዋ ራሳችሁ ታግላችሁ ተወጡት ብሎ አይተወንም። በፍቅራዊ አሳቢነቱ የተነሳ በግል እርዳታ የምናገኝበትን ዝግጅት አድርጐልናል። ከእነዚህ የእርዳታ መንገዶች አንዱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚጠቀሙበት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነው። ወላጆችም ልጆቻቸው የኋላ ኋላ ብዙ ኀዘን ከሚያመጣ ጠባይ እንዲርቁ ለመገሰጽ ልዩ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። (ምሳሌ 6:20–35፤ 15:5) በጉባኤው ውስጥ ደግሞ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንድሞች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በቅዱስ ጽሑፉ እየተጠቀሙ ሌሎችን የማስተካከል ኃላፊነት ተሸክመዋል። ይህንንም በየዋህነት መንፈስ ያደርጋሉ። (ገላትያ 6:1, 2) ይሖዋ አንድነት ያለን ሕዝብ ሆነን እንድናገለግለው በእነዚህ መንገዶች ምክርና ተግሳጽ ይሰጠናል።

የክለሳ ውይይት

● በግላችን በምን በኩል ለውጥ ማድረግ እንዳለብን ይሖዋ በፍቅር የሚያስገነዝበን እንዴት ነው?

● ብዙ ሰዎች ምክር ለመቀበል የሚቸገሩት ለምንድን ነው? ይህስ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ ያልሆነው እንዴት ነው?

● ዋጋ ሊተማንላቸው የማይችሉት ምክር ተቀባይ ለመሆን የሚረዱን ጠባዮች የትኞቹ ናቸው? በእነዚህ ነገሮች በኩል ኢየሱስ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]