በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሐሳባችሁ የይሖዋን ቀን ሁልጊዜ ቅርብ አድርጉት

በሐሳባችሁ የይሖዋን ቀን ሁልጊዜ ቅርብ አድርጉት

ምዕራፍ 23

በሐሳባችሁ የይሖዋን ቀን ሁልጊዜ ቅርብ አድርጉት

1. (ሀ) ከአሮጌው ሥርዓት ብስጭት ግልግል የሚመጣበት ጊዜ ቅርብ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትማር እንዴት ተሰማህ? (ለ) ይህንን የሚመለከቱ የትኞቹን ጥያቄዎች በጥሞና ልናስብባቸው ይገባል?

በአሁኑ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ካሉት የኑሮ ብስጭቶች ግልግል የሚገኝበት ጊዜ ቅርብ ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር ከተማርካቸው ነገሮች አንዱ እንደሆነ አያጠራጥርም። (ሉቃስ 21:28) አምላክ መላዋ ምድር ገነት እንድትሆን ዓላማ እንዳለው ማወቅ ችለሃል። ወንጀል፣ ጦርነት፣ ሕመምና ሞት ይጠፋሉ። ሞተው ያሉት የምናፈቅራቸው ሰዎችም እንደገና ሕያው ይሆናሉ። ይህ ሁሉ እንዴት ልብን በደስታ የሚያሞቅ ተስፋ ነው! ክርስቶስ ከ1914 ጀምሮ በዓይን የማይታይ ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ እንዳለና ከዚያን ጊዜ ወዲህ በአሁኑ ክፉ ዓለም መጨረሻ ቀኖች ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳዩት ማስረጃዎች የተስፋዎቹን መቅረብ የበለጠ ያረጋግጣሉ። ይህንን ማወቅህ በሕይወትህ ውስጥ ብዙ ለውጦችን አምጥቷልን? አኗኗርህ “የይሖዋን ቀን” ቅርብ ነው ብለህ በእርግጥ እንደምታምን ያሳያልን?

2. (ሀ) “የይሖዋ ቀን” የሚመጣው መቼ ነው? (ለ) ይሖዋ “ቀኑንና ሰዓቱን” አለመግለጹ ጠቃሚ ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው?

2 የክርስቶስ መገኘት ሲጀምር የተመለከተው “ትውልድ” ዓመጻን የሚያደርጉ ሁሉ በፍርድ የሚደመሰሱበትን “የይሖዋ ታላቅ ቀን” እንደሚያይ ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ ያስረዳሉ። (ማቴዎስ 24:34፤ ሶፎንያስ 1:14 እስከ 2:3) ያ “ትውልድ” አሁን በዕድሜ በጣም ገፍቷል። ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰይጣንን ምድራዊ ሥርዓት ለማጥፋት የይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚ ሆኖ የሚመጣበትን ቀን መጽሐፍ ቅዱስ ለይቶ አይገልጽም። “ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም” ሲል ኢየሱስ ተናግሯል። (ማርቆስ 13:32) ሁኔታው እንደዚህ መሆኑ በጣም ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል። እንዴት ብንል በሰው ልብ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማሳየት ስላስቻለ ነው። ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር የሌላቸው ሰዎች ካሉ በአሳባቸው የእርሱን “ቀን” ሩቅ ያደርጉትና ልባቸው ወዳዘነበለባቸው ሥጋዊ ጉዳዮች ዘወር ይላሉ። ይሖዋ እንደ አገልጋዮቹ አድርጎ የሚቀበለው ለእርሱ እውነተኛ ፍቅር ያላቸውንና የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በፈለገው ጊዜ ይምጣ በሙሉ ነፍሳቸው በማገልገል ይህንን ፍቅር የሚያሳዩትን ብቻ ነው። ለዘብተኞችን ወይም ሁለት ልብ ያላቸውን አምላክና ልጁ አይፈልጓቸውም። — ራእይ 3:16፤ መዝሙር 37:4፤ 1 ዮሐንስ 5:3

3. ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ እኛን ለማስጠንቀቅ ምን አለ?

3 ኢየሱስ ይሖዋን የሚወዱትን ሲያስጠነቅቅ “የተቀጠረው ጊዜ መቼ እንደሆነ አታውቁምና ሁልጊዜ እየጠበቃችሁ ኑሩ፣ ሁልጊዜ ንቁ” ብሏል። (ማርቆስ 13:33–37 አዓት) የጊዜውን አስቸኳይነት እስክንዘነጋ ድረስ በመብላት፣ በመጠጣትና በኑሮ ሐሳቦች እንዳንዋጥ አጥብቆ መክሮናል። — ሉቃስ 21:34–36፤ ማቴዎስ 24:37–42

4. ጴጥሮስ እንደገለጸው “የይሖዋ ቀን” ምን ያመጣል?

4 ከጊዜ በኋላም ሐዋርያው ጴጥሮስ እውነተኛ እምነት ያላቸው ሁሉ ‘ሰማያት በእሳት የሚቃጠሉበትንና ንጥረ ነገሮች በትኩሳት የሚቀልጡበትን የይሖዋን ቀን እንዲጠብቁና በሐሳባቸው ሁልጊዜ ቅርብ እንዲያደርጉት’ መክሯቸዋል። “የይሖዋ ቀን” መቅረቡ አንዳችንም ብንሆን ችላ ልንለው የማይገባን ሐቅ ነው። ሰማያት የተባሉት በዓይን የሚታዩት መንግሥታት ከክፉው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ጋር በቅርቡ ጠፍተው አምላክ በሚያመጣቸው “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” ይተካሉ። በአሁኑ ዓለማዊ ሥርዓት ውስጥ ያሉት “ንጥረ ነገሮችም” ማለትም በራሴ መመራት አለብኝ የሚለው ዝንባሌና የብልግናና የፍቅረ ንዋይ አኗኗር “የይሖዋ ቀን” ትኩሳት ያጠፋቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:10–13) እነዚህ ዓለምን የሚያናጉ ነገሮች በማንኛውም ሰዓት ዱብ ሊሉ እንደሚችሉ በማወቅ ሁልጊዜ ንቁ ሆነን መኖር ያስፈልገናል። — ማቴዎስ 24:44

የምልክቱ ፍጻሜ የሆኑትን ነገሮች ነቅተህ ተከታተል

5. (ሀ) ኢየሱስ በማቴዎስ 24:3 ላይ ለተመዘገበው ጥያቄ የሰጠው መልስ ለአይሁዶች ሥርዓት ፍጻሜ የሚያገለግለው ምን ያህል ነው? (ለ) ከመልሱ ውስጥ የትኞቹ ክፍሎች ናቸው ከ1914 እዘአ ወዲህ በተፈጸሙት ሁኔታዎች ላይ የሚያተኩሩት?

5 በተለይ አሁን ካለንበት ጊዜ አንጻር “በመጨረሻ ቀኖች” ወይም “በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን” እንደምንኖር የሚያሳየውን ብዙ ገጽታ ያጣመረውን ምልክት ዝርዝር ሁኔታ በደንብ ማወቅ አለብን። ምልክቱን በትክክል እንድናስተውል ከተፈለገ በማቴዎስ 24:3 ላይ ለተመዘገበው የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ ኢየሱስ መልስ ሲሰጥ የገለጸው አንዳንዱ ሁኔታ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለመጣው የአይሁድ ሥርዓት ጥፋት የሚያገለግል እንደሆነና የትንቢቱ ዋና ፍጻሜ ግን ከዚያ ዘመን ዘልቆ እንደሚሄድ ማስታወስ ይኖርብናል። ኢየሱስ ከቁጥር 4 እስከ 22 ድረስ የገለጻቸው ነገሮች ከ33 እስከ 70 እዘአ በነበረው ዘመን ውስጥ በትንሹ ተፈጽመዋል። ነገር ግን ትንቢቱ በዘመናችን በትልቁ ተፈጽሟል። ይህ ትንቢት ከ1914 ወዲህ ያለው ዘመን “የክርስቶስ መገኘትና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን” መሆኑን ያመለክታል። (በተጨማሪም ማርቆስ 13:5–20​ና ሉቃስ 21:8–24 ተመልከት) ከ70 እዘአ ጀምሮ ክርስቶስ እስከሚገኝበት ዘመን ድረስና በዚያ ዘመን ውስጥ የሚፈጸሙትን ነገሮች ማቴዎስ 24:23–28 ይዘረዝርልናል። (በተጨማሪም ማርቆስ 13:21–23 ተመልከት) ከማቴዎስ 24:29 ጀምሮ እስከ ምዕራፍ 25 መጨረሻ ድረስ የተገለጹት ነገሮች ግን ከ1914 እዘአ ወዲህ የሚፈጸሙትን ሁኔታዎች ያመለክታሉ። — በተጨማሪም ማርቆስ 13:24–37​ና ሉቃስ 21:25–36 ተመልከት።

6. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ የሚታዩት ሁኔታዎች “ምልክቱን” እንዴት እየፈጸሙ እንዳሉ ነቅተን መከታተል ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) “ምልክቱ” ከ1914 ጀምሮ እንዴት እየተፈጸመ እንዳለ ለማሳየት ከአንቀጹ ቀጥሎ ያሉትን ጥያቄዎች መልስ።

6 በአሁኑ ጊዜ በመከሰት ላይ ያሉትን “የምልክቱ” ፍጻሜ የሆኑ ነገሮች በግል መከታተል ይገባናል። እነዚህን ሁኔታዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጋር ማዛመዳችን የይሖዋን ቀን ‘በሐሳባችን ሁልጊዜ ቅርብ እንድናደርገው’ ይረዳናል። ከዚህም በተጨማሪ “የአምላካችን የበቀል ቀን” ቀርቧል እያልን ሰዎችን ስናስጠነቅቅ ማሳመን እንደምንችል ሆነን ለመናገር ይረዳናል። (ኢሳይያስ 61:1, 2) እነዚህን ዓላማዎች በአእምሮህ ይዘህ ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን “የምልክቱን” ልዩ ልዩ ክፍሎች እንደገና ተመልከት:-

“ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል” የሚለው ትንቢት ከ1914 እዘአ ጀምሮ እንዴት ባለ ልዩ ሁኔታ ሲፈጸም ቆይቷል? ለትንቢቱ መፈጸም ተጨማሪ ማስረጃ የሚሆኑ በቅርቡ ወራት ምን የተደረጉ ነገሮች አሉ?

በ20ኛው መቶ ዘመን የተራቀቀ የሳይንስ ዕውቀት ቢኖርም የምግብ እጥረት ምድርን ምን ያህል አጥቅቷል?

የመሬት መንቀጥቀጥ ከ1914 እዘአ ወዲህ በእርግጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ከድሮ ይበልጥ ቶሎ ቶሎ ደርሷልን?

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ከሞቱት የበለጡ ሰዎችን በ1918 የፈጀው ቸነፈር የትኛው ነው? የሕክምና ዕውቀት ቢጨምርም የትኞቹ በሽታዎች እስከ ዛሬ ድረስ በወረርሽኝ ደረጃ ይስፋፋሉ?

በሉቃስ 21:26 ላይ አስቀድሞ እንደተነገረው ሰዎች ከፍርሐት የተነሳ ልባቸው እንደደከመ የሚያሳይ ምን ማስረጃ ትመለከታለህ?

በ2 ጢሞቴዎስ 3:1–5 ላይ የተዘረዘሩት ሁኔታዎች ከድሮም ጀምሮ የነበሩ ሳይሆን በመጨረሻው ቀኖች ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ በመጨመር ላይ እንዳሉ የሚያሳምንህ ምንድን ነው?

ሰዎችን በየወገኑ መለያየት

7. (ሀ) ኢየሱስ ከሥርዓቱ መደምደሚያ ዘመን ጋር ያዛመደው በማቴዎስ 13:36–43 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የትኛውን ሌላ ሁኔታ ነው? (ለ) የምሳሌውስ ትርጉም ምንድን ነው?

7 ኢየሱስ ከሥርዓቱ መደምደሚያ ዘመን ጋር በከፍተኛ ደረጃ ያዛመዳቸው ሌሎች ነገሮችም አሉ። ከእነዚህ ነገሮች አንዱ “የመንግሥቱን ልጆች” “ከክፉው ልጆች” በየወገናቸው የመለያየቱ ሥራ ነው። ኢየሱስ ይህንን ሲገልጽ ስንዴ በተዘራበት እርሻ ላይ ጠላት እንክርዳዱን እንደዘራ የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሯል። በምሳሌው ውስጥ “ስንዴ” የተባሉት እውነተኞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሲሆኑ “እንክርዳዶቹ” አስመሳይ ክርስቲያኖች ናቸው። “እንክርዳዶቹ” ይኸውም ክርስቲያን ነን እያሉ ሰይጣን ገዥው ከሆነው ዓለም ጋር ሙጥኝ በማለታቸው ምክንያት “የክፉው ልጆች” መሆናቸውን ያሳዩት ሰዎች በፍጻሜው ዘመን ውስጥ ‘ከአምላክ መንግሥት ልጆች’ እንደሚለዩና ለጥፋት ምልክት እንደሚደረግባቸው በትንቢቱ ተገልጿል። (ማቴዎስ 13:36–43) ታዲያ ይህ በእርግጥ ተፈጽሟልን?

8. (ሀ) ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ክርስቲያን ነን የሚሉትን ሁሉ በሁለት ወገን ለመለያየት ምን ታላቅ ሥራ ተካሂዷል? (ለ) እውነተኞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በእርግጥም “የመንግሥት ልጆች” መሆናቸውን ያስመሰከሩት እንዴት ነው?

8 ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ክርስቲያን ነን የሚሉትን ሁሉ በሁለት ወገኖች ለመከፋፈል ከፍተኛ ሥራ ሲካሄድ ቆይቷል። እነርሱም (1) ብሔራዊ ስሜታቸውን ሳይተዉ ለመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር (ዛሬም ላለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት) ብርቱ ድጋፍ የሰጡት ቄሶችና ተከታዮቻቸው (2) በድሕረ ጦርነቱ የነበሩት በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ለመሲሐዊው የአምላክ መንግሥት ሙሉ ድጋፍ የሰጡት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው። በመጀመሪያ የተጠቀሰው ወገን አባሎች የዓለምን መንግሥታት በይፋ በመደገፍና ሰላምና ደኅንነት የሚመጣው በእነርሱ አማካኝነት ነው ብለው በማመን እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዳልሆኑ በግልጽ አሳይተዋል። (ዮሐንስ 17:16) በአንጻሩ ግን የይሖዋ አገልጋዮች የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር በማቴዎስ 24:15 ላይ የተነገረለት ዘመናዊው “የጥፋት ርኩሰት” ነው በማለት በትክክል ገልጸውታል። ‘ይህንን የመንግሥት ምሥራች በመላዋ ምድር በመስበክ’ እውነተኞቹ የአምላክ “መንግሥት ልጆች” መሆናቸውን አስመስክረዋል። (ማቴዎስ 24:14) ምን ውጤቶች ተገኙ?

9. ይህ የመንግሥቱ ስብከት ያስገኘው የመጀመሪያው ውጤት ምን ነበር?

9 በመጀመሪያ “የምርጦቹ” ይኸውም በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ቀሪ አባላት ተሰበሰቡ። “ወደ አራቱ ነፋሳት” እንደተበተኑ ያህል በልዩ ልዩ አገሮች የነበሩ ቢሆንም በመላእክት እርዳታ ወደ ድርጅታዊ አንድነት ተሰባስበዋል። — ማቴዎስ 24:31

10. (ሀ) ሌላ የመለያየት ሥራ የተካሄደው እንዴት ነው? ይህስ በየትኛው ትንቢት መሠረት ነው? (ለ) የእነዚህ ትንቢቶች መፈጸም ምን ትርጉም አለው?

10 ከዚያ ቀጥሎ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው “እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ” እርሱም አሕዛብን ሁሉ በየወገኑ መለያየት ጀመረ። ኢየሱስ በሰማያዊ ዙፋኑ ተቀምጦ የሚመራው ይህ ሥራ እስከ አሁን ድረስ ቀጥሏል። አንተንም ጭምር ነክቷል። አብዛኞቹ የሰው ልጆች የአምላክን መንግሥትና በመንፈስ የተቀቡትን “የመንግሥት ልጆች” ስለሚንቁ ‘የዘላለም የሞት ቅጣት’ ይፈጸምባቸዋል። ለሌሎቹ ግን ጌታ ከዘላለም ሕይወት ተስፋ ጋር የመንግሥቱን ምድራዊ ክፍል እንዲወርሱ ጥሪ ያቀርብላቸዋል። የተቀቡት “የመንግሥት ልጆች” ጭካኔ ያለበት ስደት ቢደርስባቸውም እነዚህ በግ መሰል ሰዎች ከእነርሱ ጋር በመቀራረብ ተባባሪዎቻቸው ሆነዋል። (ማቴዎስ 25:31–46) በጣም አስፈላጊ የሆነውን የመንግሥቱን መልዕክት ለሕዝብ ለማሳወቅ በሚደረገው ሥራ በታማኝነት ይረዷቸዋል። ባሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ “እጅግ ብዙ ሰዎች” በዚህ ሥራ እየተሳተፉ ነው። የመንግሥቱ መልዕክት በምድር ላይ ከዳር እስከ ዳር እየተሰማ ነው። እነዚህ ክንዋኔዎች ምን ትርጉም አላቸው? “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ማለቂያ ላይ እንደምንገኝና “የይሖዋ ቀን” እንደደረሰ ያሳያሉ።

ከፊታችን ምን ነገሮች አሉ?

11. “የይሖዋ ቀን” ከመምጣቱ በፊት ገና የምናከናውነው የምስክርነት ሥራ ይኖራልን?

11 ታላቁና አስፈሪው የይሖዋ ቀን ከመጀመሩ በፊት መፈጸም ያለባቸው ገና ሌሎች ትንቢቶች አሉን? አዎን፣ አሉ። ሰዎች የመንግሥቱ ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ በመሆን በሁለት ወገን መለያየታቸው ገና አላበቃም። ከዚህ በፊት ለብዙ ዓመታት ከባድ ስደት የነበረባቸው አንዳንድ ቦታዎች በአሁኑ ጊዜ ብዙ አዳዲስ ደቀመዛሙርት አፍርተዋል። ምሥራቹን በማይቀበሉበት አካባቢም ቢሆን ምሥክርነት መስጠታችን የይሖዋ ፍትሕና ምሕረት እንዲረጋገጡ ያደርጋል። እንግዲያው በሥራው ወደፊት ግፉ! ሥራው ሲያበቃ ‘ፍጻሜው እንደሚመጣ’ ኢየሱስ አረጋግጦልናል። — ማቴዎስ 24:14

12. (ሀ) በ1 ተሰሎንቄ 5:2, 3 ላይ እንደተገለጸው ምን ትልቅ ሁኔታ ገና ይፈጸማል? (ለ) እርሱስ ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል?

12 ከፍተኛ ትርጉም ያለው ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል፣ ከቶም አያመልጡም” ይላል። (1 ተሰሎንቄ 5:2, 3) “ሰላምና ደኅንነት” የሚለው አዋጅ በምን መልክ እንደሚቀርብ ገና ወደፊት የሚታይ ነገር ነው። ይሁን እንጂ የዓለም መሪዎች የሰውን ልጆች ችግሮች በእርግጥ መፍትሄ አግኝተውላቸዋል ማለት አይሆንም። የይሖዋን ቀን በሐሳባቸው ቅርብ የሚያደርጉ ሁሉ በዚያ አዋጅ አይወናበዱም። ከዚያ ቀጥሎ ወዲያው ድንገተኛ ጥፋት እንደሚመጣ ያውቃሉ።

13. “ሰላምና ደኅንነት” ከታወጀ በኋላ ወዲያው ምን ነገሮች ይከተላሉ? ቅደም ተከተላቸውስ እንዴት ይሆናል?

13 ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚያሳዩት በመጀመሪያ የፖለቲካ መሪዎች ዓለም አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ድርጅት በሆነችው በታላቋ ባቢሎን ላይ ተነስተው ይደመስሷታል። (ራእይ 17:15, 16) በአሁኑም ጊዜ ቢሆን በተለይ ክርስቲያን ነን በሚሉት ሃይማኖቶች ላይ የጥላቻ አዝማሚያ በመታየት ላይ ነው። በአሁኑ ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ያሉ ፀረ ሃይማኖት አቋም ያላቸው መንግሥታት ከፍተኛ ተደማጭነት አላቸው። ለብዙ ዘመናት ሰዎች ሃይማኖተኛ ሆነው በኖሩባቸው አገሮች የሚገኙ ብዙ ሕዝቦችም የአያቶቻቸውን ሃይማኖት ትተው እየወጡ ነው። ይህ ሁሉ ምን ማለት ነው? ሁሉም ሃይማኖት የሚወድምበት ጊዜ ቀርቧል ማለት ነው። ያ ከሆነ በኋላ ብሔራት በማን አለብኝነት የይሖዋን ሉዓላዊነት በሚደግፉት ላይ በሙሉ ኃይላቸው ሲነሱ በፖለቲካዊ መንግሥታትና በደጋፊዎቻቸው ላይ የመለኮታዊ ቁጣ ረመጥ ይነሰነሳል፤ ሁሉም እንዳልነበሩ ይሆናሉ። በመጨረሻም ሰይጣን ራሱ ከአጋንንቱ ጋር የሰውን ልጆች ማሳት ወደማይችልበት ጥልቅ ይጣላል። ያ ቀን የይሖዋ ስም ከፍ ከፍ የሚልበት “የይሖዋ ቀን” ይሆናል። — ሕዝቅኤል 38:18, 22, 23፤ ራእይ 19:11 እስከ 20:3

14. የይሖዋ ቀን ገና ነው ብሎ ማሰብ አስተዋይነት ያልሆነው ለምንድን ነው?

14 ቀኑ የአምላክን ፕሮግራም ጠብቆ ልክ በሰዓቱ ከተፍ ይላል። አይዘገይም። (ዕንባቆም 2:3) በ70 እዘአ የወረደው የኢየሩሳሌም ጥፋት አይሁዶች ባልጠበቁት ወቅት፣ አደገኛው ጊዜ አልፎአል በሚሉበት ሰዓት በድንገት እንደመጣ አስታውስ። የጥንቷ ባቢሎንስ እንዴት ነበረች? በረጃጅም ግንቦች የታጠረች፣ ብርቱ ኃይል ያላት ተማምና የምትኖር አገር ነበረች። ይሁን እንጂ በአንድ ሌሊት ወድቃለች። አሁን ባለው ክፉ ሥርዓት ላይም “ጥፋት በድንገት ይመጣል።” ያ ጊዜ ሲመጣ ‘የይሖዋን ቀን በሐሳባችን ሁልጊዜ ቅርብ እያደረግን’ በእውነተኛ አምልኮ ውስጥ በአንድነት ተሰባስበን የምንገኝ ያድርገን።

የክለሣ ውይይት

● የይሖዋን ቀን ‘በሐሳባችን ሁልጊዜ ቅርብ ማድረጉ’ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እንደዚያ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

● በአሁኑ ጊዜ ሰዎችን በሁለት ወገን ለመለያየት የሚካሄደው ሥራ አንተን በግል እንዴት ይነካሃል?

● የይሖዋ ቀን ከመጀመሩ በፊት መፈጸም ያለባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ስለዚህ በግላችን ምን እያደረግን መሆን አለብን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]