በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነቢያት ሁሉ የመሰከሩለት

ነቢያት ሁሉ የመሰከሩለት

ምዕራፍ 4

ነቢያት ሁሉ የመሰከሩለት

1. ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመምጣቱ በፊት የነበሩት ሁኔታዎች ከይሖዋ ጋር ስለነበረው ዝምድና ምን ያሳያሉ?

ኢየሱስ ከይሖዋ ጋር የነበረውን ሞቅ ያለ ፍቅራዊ ግንኙነት ሲገልጽ “አብ ወልድን ይወዳልና የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳያዋል” ብሏል። (ዮሐንስ 5:​19, 20) ይህ የቅርብ ግንኙነት የጀመረው ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት ብዙ ሺህ ዓመታት ቀደም ብሎ ይኸውም በተፈጠረበት ጊዜ ነው። እርሱ የአምላክ አንድያ ልጅ ነው። ይህም ይሖዋ ብቻውን ሆኖ የፈጠረው እርሱን ብቻ ነው ማለት ነው። በሰማይና በምድር የሚገኙ የቀሩት ነገሮች በሙሉ የተፈጠሩት በዚህ ውድ የአምላክ የበኩር ልጅ አማካይነት ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ የአምላክ ቃል ወይም አፈ ቀላጤ ሆኖ አገልግሏል። መለኮታዊ ፈቃድ ለሌሎች የሚተላለፈው በእርሱ በኩል ነበር። በአምላክ ዘንድ እንደዚህ ያለ ተወዳጅነት የነበረው ልጅ ሰው ሆነና ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ ተጠራ። — ቆላስይስ 1:​15, 16፤ ዮሐንስ 1:​14፤ 12:​49, 50

2. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ስለ ኢየሱስ የሚናገሩት ምን ያህል ብዙ ነው?

2 በተአምር ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት ስለ እርሱ የሚገልጹ በመንፈስ አነሳሽነት የተነገሩ ብዙ ትንቢቶች ተጽፈው ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ በቆርኔሌዎስ ፊት እንደተናገረው “ነቢያት ሁሉ ይመሠክሩለታል።” (ሥራ 10:​43) በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው ንጹሕ አምልኮ ጋር በተያያዘ የኢየሱስ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ አንድ መልአክ ለሐዋርያው ዮሐንስ “ትንቢት የሚነገረው ስለ ኢየሱስ ለመመስከር ሲባል ነው” ብሎታል። (ራእይ 19:​10 አዓት ) እነዚያ ትንቢቶች የኢየሱስን ማንነት በግልጽ ያስረዱ ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ ስለ እርሱ ምን ዓላማ እንደነበረው የሚያሳዩና ዛሬ ያለነው ሁሉ ልናውቃቸው በጣም የሚያስፈልጉንን ሁኔታዎች ገልጸዋል።

ትንቢቶቹ ምን ገልጸው ነበር?

3. (ሀ) በዘፍጥረት 3:​14, 15 በተነገረው ትንቢት ላይ የተጠቀሱት “እባብ” “ሴት” እና “የእባብ ዘር” የምን ምሳሌ ናቸው? (ለ) የይሖዋ አገልጋዮች ‘የእባቡ ራስ እንዲቀጠቀጥ’ በጣም የሚፈልጉት ለምንድን ነው?

3 ከእነዚህ ትንቢቶች መካከል የመጀመሪያው በዔደን አመጽ ከተካሄደ በኋላ የተነገረው ነው። ትንቢቱ ይሖዋ ለእባቡ በተናገረው የፍርድ ቃል ውስጥ ተጠቅሷል። ይሖዋ እንዲህ አለ:​-“በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፣ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍጥረት 3:​14, 15) የዚህ አባባል ትርጉም ምንድን ነው? አምላክ በወሰነው ጊዜ ሌሎች ትንቢቶች ይህንን ትንቢት አብራርተውታል፤ እንዲሁም ሌላ ሐሳብ እየጨመሩ አስፋፍተውታል። በዚህ ምክንያት በእባቡ የተመሰለው ሰይጣን ዲያብሎስ መሆኑን ለማወቅ ችለናል። በ“ሴቲቱ” የተመሰለው ለይሖዋ በታማኝነት የሚቆመው ሰማያዊ ድርጅቱ ሲሆን ለእርሱ እንደ ታማኝ ሚስት ነው። ‘የእባቡ ዘር’ የዲያብሎስን መንፈስ የሚያንጸባርቁትንና ይሖዋንና ሕዝቡን የሚቃወሙትን መላእክትና ሰዎች ሁሉ ይጨምራል። ዲያብሎስ በዔደን ውስጥ እባብን እንደ መሣሪያ አድርጐ ስለተጠቀመበት በትንቢቱ ላይ የተገለጸው የእባቡ ራስ መቀጥቀጥ ይህ ይሖዋን የተሳደበና በሰው ልጆች ላይ ታላቅ መከራ ያመጣው ዐመጸኛ የአምላክ ልጅ በመጨረሻው የሚጠፋ መሆኑን እንደሚያመለክት ለመረዳት እንችላለን። የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው “ዘር” ማን እንደሆነ ግን ለረጅም ዘመን ምሥጢር ሆኖ ነበር። — ሮሜ 16:​25, 26

4. የኢየሱስ የትውልድ መሥመር ተስፋ የተደረገበት ዘር እርሱ መሆኑን ለይቶ ለማወቅ የረዳው እንዴት ነው?

4 ከ2,000 ዓመታት የሰው ልጅ ታሪክ በኋላ ይሖዋ ተጨማሪ መግለጫዎች ሰጠ። ዘሩ ከአብርሃም የትውልድ መሥመር እንደሚመጣ አመለከተ። (ዘፍጥረት 22:​15-18) ሆኖም ወደ ዘሩ የሚያደርሰው ይህ የትውልድ መሥመር በአምላክ ምርጫ እንጂ በሥጋዊ የትውልድ ሐረግ ላይ ብቻ የተመካ አልነበረም። አብርሃም አጋር ከተባለችው ባሪያው ለወለደው ልጅ ለእስማኤል ከፍተኛ ፍቅር ቢኖረውም ይሖዋ “ቃል ኪዳኔን . . . ሣራ ከምትወልድልህ ከይስሐቅ ጋር አቆማለሁ” ሲል በግልጽ ነግሮታል። (ዘፍጥረት 17:​18-21፣ 21:​8-12) በኋላም ይህ ቃል ኪዳን ለይስሐቅ የበኩር ልጅ ለኤሳው ሳይሆን አሥራ ሁለቱን ነገዶች ላስገኘው ለያዕቆብ ተላልፏል። (ዘፍጥረት 28:​10-14) ከጊዜ በኋላም ዘሩ ከይሁዳ ነገድ ከዳዊት ቤት እንደሚወለድ ተገለጸ። — ዘፍጥረት 49:​10፣ 1 ዜና 17:​3, 4, 11–14

5. ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ገና ሲጀምር መሲሕ መሆኑን የሚያሳዩ ምን ግልጽ ነገሮች ነበሩ?

5 ዘሩ ሰው ሆኖ የሚወለድበት ሥፍራ ቤተልሔም እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ 700 ዓመታት ቀደም ብሎ ተናግሮ ነበር። በተጨማሪም እርሱ “ከቀድሞ ጀምሮ” ይኸውም በሰማይ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በሕይወት እንደኖረ ትንቢቱ ገለጸ። (ሚክያስ 5:​2) በይሖዋ የተቀባ ወይም መሲሕ ሆኖ ወደ ምድር የሚመጣበትን ጊዜ ነቢዩ ዳንኤል አስቀድሞ አመለከተ። (ዳንኤል 9:​24-26) በመንፈስ ቅዱስ በተቀባበትም ወቅት ከሰማይ የመጣ ድምጽ ማንነቱን አስታውቋል። (ማቴዎስ 3:​16, 17) ስለሆነም ፊልጶስ የኢየሱስ ተከታይ ከሆነ በኋላ “ሙሴ በሕግ፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ [ይኸውም በአሳዳጊነቱ] የናዝሬቱን ኢየሱስ አግኝተነዋል” ብሎ በሙሉ እምነት ለመናገር ችሏል። — ዮሐንስ 1:​45 (በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ 1:46)

6. (ሀ) ከኢየሱስ ሞት በኋላ ተከታዮቹ ምን ተገነዘቡ? (ለ) ዋነኛው ‘የሴቲቱ ዘር’ ማን ነው? እርሱ የእባቡን ራስ መቀጥቀጡስ ምን ትርጉም አለው?

6 ከዚያ በኋላ የኢየሱስ ተከታዮች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለ ኢየሱስ የሚናገሩ ብዙ ትንቢቶች እንዳሉ ለመረዳት ቻሉ። ኢየሱስም ከሞት ከተነሳ በኋላ “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው።” (ሉቃስ 24:​27) ‘የእባቡን ራስ ቀጥቅጦ’ በመጨረሻው የሰይጣንን ኅልውና የሚያጠፋው ዋነኛው ‘የሴቲቱ ዘር’ ኢየሱስ መሆኑ በዚህ ጊዜ ግልጽ ሆነ። አምላክ ለሰው ልጆች የሰጣቸውና እኛ በጉጉት የምንጠብቃቸው ተስፋዎች ሁሉ በኢየሱስ አማካይነት ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። — 2 ቆሮንቶስ 1:20

7. በእነዚህ ትንቢቶች የተገለጸው ማን መሆኑን ብቻ ሳይሆን ምን ሌላ ነገር ጭምር ብንመረምር እንጠቀማለን?

7 ከእነዚህ ትንቢቶች አንዳንዶቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ስታነብ ምናልባት እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ “ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል?” ብለህ ጠይቀህ ይሆናል። ጃንደረባው መልስ ባገኘ ጊዜ ነገሩን በዚያው አልተወውም። የፊልጶስን ማብራሪያ በጥንቃቄ ካዳመጠ በኋላ ኢየሱስ ትንቢቱን እንዴት እንደፈጸመ ማወቁ በእርሱ በኩል ርምጃ መውሰድን ይኸውም መጠመቅን እንደሚጠይቅ ተገነዘበ። (ሥራ 8:​32-38፣ ኢሳይያስ 53:3-9) እኛስ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እንነሳሳለንን? አንዳንድ ጊዜ በጥልቅ የሚነካን አንድ ትንቢት እንዴት ሆኖ እንደቀረበ ማየታችን ይሆናል፤ ወይም ልባችንን በጣም የሚነካው መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ትንቢት እንዴት እንደተፈጸመ ከገለጸ በኋላ የሚሰጠው የመደምደሚያ ሐሳብ ሊሆን ይችላል።

8. እዚህ ላይ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገሩ አራት ትንቢታዊ ምሳሌዎች ተገልጸዋል። በጥያቄዎቹና በጥቅሶቹ አማካይነት እየተመራመርህ እነዚህ ትንቢቶች እንዴት እንደሚነኩህ አንድ በአንድ አስረዳ።

8 ይህንን ሁኔታ ከዚህ ቀጥሎ ባሉት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚናገሩት ትንቢታዊ ተስፋዎችና ምሳሌዎች ላይ ተመልከት። አውጥተህ እንድትመለከታቸው በቀረቡት ጥቅሶች እየተረዳህ የምትመልሳቸው ጥያቄዎች ከዚህ በታች ቀርበውልሃል:-

(1) አብርሃም ይስሐቅን መስዋዕት አድርጐ ለማቅረብ እንደሞከረ የሚገልጸው ታሪክ ይሖዋ የራሱን ልጅ ቤዛ አድርጐ ሲያቀረብ ያሳየንን ፍቅር ለማድነቅ የሚረዳን እንዴት ነው? (ዮሐንስ 3:​16፤ ዘፍጥረት 22:​1-18 [በተለይ በቁጥር 2 ላይ ይስሐቅ እንዴት ሆኖ እንደተገለጸ አስተውል])

ይህ ምን ትምክህት እንዲሰማን ሊያደርግ ይገባል? (ሮሜ 8:​32, 38, 39)

ይሁን እንጂ በበኩላችን ምን ማድረግ ይፈለግብናል? (ዘፍጥረት 22:​18 አዓት፤ ዮሐንስ 3:36)

(2) መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ መሆኑን ሲገልጽ ምን ከባድ ኃላፊነት እንዳለብን ያሳስበናል? (ሥራ 3:​22, 23፤ ዘዳግም 18:​15-19)

ኢየሱስ ለእኛ የተናገራቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ለአሁኑ ጊዜ አስፈላጊ የሆኑትስ ለምንድን ነው? (ማቴዎስ 28:​18-20፤ 19:​4-9፤ 18:3-6)

(3) መጽሐፍ ቅዱስ የአሮን ክህነት የምን ጥላ እንደሆነ በሚገልጽበት ጊዜ ኢየሱስ በሊቀ ካህንነቱ የሚያሳያቸውን የትኞቹን ማራኪ ጠባዮች በቀጥታ ይጠቅሳል? (ዕብራውያን 4:15 እስከ 5:3፤ 7:​26-28)

እንግዲያው አምላክ ድክመቶቻችንን ለማሸነፍ እንዲረዳን በክርስቶስ በኩል በጸሎት ወደ እርሱ ስለመቅረብ እንዴት ሊሰማን ይገባል?

(4) በሙሴ ሕግ የሚቀርቡትን መስዋዕቶች በሙሉ የሚተካው የኢየሱስ መስዋዕት ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው ስንመለከት አምላክን የሚያስከፋ ነገር የማድረግ ልማድ እንዳንጀምር በጣም መጠንቅቅ ያለብን ለምንድን ነው? (ዕብራውያን 10:​26, 27)

የኢየሱስ መስዋዕት ያስገኘውን የሕይወት ተስፋ ከልብ የምናደንቅ ከሆነ ምን ነገሮችን ለማድረግ እንተጋለን? (ዕብራውያን 10:​19-25)

በክርስቶስ እንደምናምን እንዴት ልናሳይ እንችላለን?

9. በኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ በሌላ በማንም መዳን የማይቻለው ለምንድን ነው?

9 ሐዋርያው ጴጥሮስ ትንቢት በኢየሱስ ላይ እንዴት እንደተፈጸመ በኢየሩሳሌም ለሚገኘው የአይሁዶች ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከገለጸ በኋላ በመደምደሚያው ላይ “መዳንም በሌላ በማንም የለም፣ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” የሚል ቁርጥ ያለ ሐሳብ ተናግሯል። (ሥራ 4:​11, 12፤ መዝሙር 118:​22) የአዳም ልጆች በሙሉ ኃጢአተኞች ናቸው። እንዲያውም የሚሞቱት የኃጠአትን ዋጋ ለመክፈል ስለሆነ ሞታቸው ለማንም ቤዛ ለመሆን አይበቃም። ኢየሱስ ግን ፍጹም ስለነበረ ሞቱ መስዋዕታዊ ዋጋ አለው። (መዝሙር 49:​6-9፤ ዕብራውያን 2:​9) ኢየሱስ አዳም ለዘሮቹ ካጠፋባቸው ነገር ጋር የሚመጣጠን ቤዛ ለአምላክ አቅርቧል። ይህ እኛን የጠቀመው እንዴት ነው? — 1 ጢሞቴዎስ 2:​5, 6 አዓት

10. ከኢየሱስ መስዋዕት ትልቅ ጥቅም የምናገኝበትን አንዱን መንገድ ግለጽ።

10 በቤዛው የኃጢአት ይቅርታ ስለምናገኝ ንጹህ ሕሊና እንዲኖረን አስችሎናል። በሙሴ ሕግ የሚቀርቡት የእንስሳት መስዋዕት ለእሥራኤላውያን እንደዚህ ሊያደርጉላቸው አልቻሉም። (ሥራ 13:​38, 39፤ ዕብራውያን 9:​13, 14) እርግጥ ይህንን ንጹሕ ሕሊና ለማግኘት ራሳችንን ከማታለል መራቅና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እውነተኛ እምነት መጣል ይኖርብናል። የክርስቶስ መስዋዕት ምን ያህል እንደሚያስፈልገን እኛ ራሳችን በጥልቅ ይሰማናልን? “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመጻም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።” — 1 ዮሐንስ 1:8, 9

11. በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና ለማግኘት የውሃ ጥምቀት ለምን ያስፈልጋል?

11 ‘ኃጢአተኞች መሆናችንን እናውቃለን፣ በክርስቶስም እናምናለን’ የሚሉ፤ ምናልባትም ኢየሱስ እንዳደረገው ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች በመጠኑ የሚናገሩ አንዳንዶች በኢየሱስ ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ያላሳዩበት አንድ ሁኔታ አለ። ምን ይሆን? መልሱን ለማወቅ ‘በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሰዎች አማኝ ሲሆኑ እምነታቸውን በሕዝብ ፊት እንዴት ያሳዩ ነበር?’ ብለን እንጠይቃለን። ሰዎቹ ይጠመቁ ነበር። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ እንዲጠመቁ አዟል። (ማቴዎስ 28:​19, 20፤ ሥራ 8:​12፤ 18:​8) የአንድ ሰው ልብ ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ባደረገው ፍቅራዊ ዝግጅት በእርግጥ ከተነካ ይህንን ከማድረግ ወደኋላ አይልም። በሕይወቱ ውስጥ ማንኛውንም አስፈላጊ ማስተካከያ ያደርጋል፣ ራሱን ለአምላክ ይወስናል፣ በኋላም ይህንን በውሃ ጥምቀት ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳው ሰውየው ‘ጥሩ ሕሊና ስጠኝ’ ብሎ አምላክን ለመጠየቅ የሚችለው እምነቱን በዚህ መንገድ በማሳየት ነው። — 1 ጴጥሮስ 3: 21

12. ኃጢአት እንደሠራን ካወቅን ምን ማድረግ አለብን? ለምንስ?

12 ይሁን እንጂ ከዚያም በኋላ ቢሆን አንዳንድ የኃጢአት ጠባዮች ብቅ ማለታቸው አይቀርም። ታዲያ ምን ማድረግ አለብን? “ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ” ሲል ሐዋርያው ዮሐንስ ተናግሯል። ስለዚህ በድርጊት ወይም በንግግር ወይም በሐሳብ የምንፈጽመውን ኃጢአት እንደ ቀላል ነገር ቆጥረን ማለፍ አይገባንም። ሆኖም “ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተሰሪያ ነው፤ ለኃጢአታችን ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።” (1 ዮሐንስ 2:​1, 2) ታዲያ እንደዚህ ሲባል ማንኛውንም ኃጢአት ብንሠራና አምላክ ይቅር እንዲለን ብንጠይቀው ነገሩ በዚህ ያልቃል ማለት ነውን? አይደለም። ይቅርታ ለማግኘት ቁልፉ እውነተኛ ንስሐ ነው። በተጨማሪም በክርስቲያን ጉባኤ ያሉት ሽማግሌዎች እንዲረዱን ሊያስፈልግ ይችላል። የተፈጸመው ድርጊት መጥፎ መሆኑን መቀበልና በአድራጐታችን ተጸጽተን ያንን በድጋሚ እንዳንፈጽም ከልብ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። (ሥራ 3:​19፣ ያዕቆብ 5:​13-16) ይህንን ካደረግን ኢየሱስ እንደሚረዳን እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን። የኢየሱስ መስዋዕት ኃጢአትን የማስተሰረይ ኃይል እንዳለው በማመን የይሖዋን ሞገስ መልሰን ለማግኘት እንችላለን። አምልኮታችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ከተፈለገ ይህን ሞገስ ማግኘቱ አስፈላጊ ነው።

13. (ሀ) ከኢየሱስ መስዋዕት ጥቅም ያገኘንበትን ሌላውን መንገድ ግለጽ። (ለ) ይህስ ለአምላክ ለምናቀርበው አገልግሎት እንደ ደመወዝ ሆኖ ሊከፈለን የማይችለው ለምንድን ነው? (ሐ) በእርግጥ እምነት ካለን ምን እናደርጋለን?

13 ከዚህም ሌላ የኢየሱስ መስዋዕት የዘላለም ሕይወት ዕድል ከፍቶልናል። “ታናሹ መንጋ” በሰማይ፣ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች የሰው ልጆች ደግሞ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ አስችሏል። (ሉቃስ 12:​32፣ ራእይ 20:​11, 12፤ 21:​3, 4) ይህ የሥራችን ዋጋ ሆኖ የሚከፈለን ደመወዝ አይደለም። በይሖዋ አገልግሎት የቱንም ያህል ብንደክም አምላክ ለእኛ ሕይወትን የመስጠት ዕዳ ሊኖርበት አይችልም። የዘላለም ሕይወት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የሚገኝ “የእግዚአብሔር የፀጋ ስጦታ” ነው። (ሮሜ 6:​23፤ ኤፌሶን 2:​8-10) ነገር ግን በዚህ ስጦታ ላይ እምነት ካለንና ስጦታው ሊገኝ የቻለበትን መንገድ የምናደንቅ ከሆነ ይህ አቋማችን በግልጽ ይታያል። ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈፀም ኢየሱስን እንዴት አስደናቂ በሆነ መንገድ እንደተጠቀመበት መረዳታችንና ሁላችንም የኢየሱስን ኮቴ መከተል ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘባችን በሕይወታችን ውስጥ ለክርስቲያን አገልግሎት ትልቁን ቦታ እንድንሰጥ ይረዳናል። ስለ አስደናቂው የአምላክ ስጦታ በእርግጠኝነት መንፈስ ለሌሎች ስንናገር እምነታችን ግልጽ ሆኖ ይታያል። — ከሥራ 20:​24 ጋር አወዳድር።

14. በኢየሱስ ክርስቶስ ያለን ይህ ዓይነቱ እምነት ለአንድነት የሚረዳ ትልቅ ኃይል ያለው ለምንድን ነው?

14 ይህ ዓይነቱ እምነት አንድነትን በማምጣት በኩል እንዴት ያለ አስደናቂ ኃይል አለው! በዚህ አማካይነት ከይሖዋ፣ ከልጁና ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር በጣም እንቀራረባለን። (1 ዮሐንስ 3:​23, 24) ይህ እምነት “በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሠክር ዘንድ” ይሖዋ ከራሱ ስም በስተቀር “ከስም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም” በደግነት ለልጁ በመስጠቱ እንድንደሰት ያደርገናል። — ፊልጵስዩስ 2:​9-11

የክለሳ ውይይት

● መሲሑ በመጣ ጊዜ የአምላክን ቃል ከልብ ለሚያምኑት ሁሉ ማንነቱ ግልጽ የሆነላቸው ለምንድን ነው?

● በገጽ 34 ላይ በሥዕል የተገለጹት በኢየሱስ ላይ የተፈጸሙ ትንቢታዊ ምሳሌዎች እንዴት ሊነኩን ይገባል?

● አሁንም ቢሆን የኢየሱስ መስዋዕት በምን መንገዶች ጠቅሞናል? ለዚህስ ያለንን አድናቆት እንዴት ልናሳይ እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 34 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ወደ ኢየሱስ የሚያመለክቱ ትንቢታዊ ምሳሌዎች—እንዴት ሊነኩህ ይገባል?

አብርሃም ይስሐቅን መስዋዕት አድርጎ ማቅረቡ

ሙሴ አምላክን ወክሎ መናገሩ

አሮን እንደ ሊቀ ካህናት ሆኖ መሥራቱ

የእንስሳት መስዋዕት