በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ”

“እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ”

ምዕራፍ 17

“እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ”

1, 2. (ሀ) ወደ ይሖዋ ምስክሮች ስብሰባ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚመጡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ምን ያስደንቃቸዋል? (ለ) ሰዎቹ በትልልቆቹ ስብሰባዎቻችን ለዚህ ጠባይ ማስረጃ የሚሆኑ ምን ነገሮች ይመለከታሉ?

ሰዎች ወደ ይሖዋ ምስክሮች ስብሰባ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጡ ብዙውን ጊዜ በዚያ በሚያዩት ፍቅር በጣም ይደነቃሉ። ይህንን ፍቅር በጉባኤው ውስጥ ባለው የሞቀ የጓደኝነት መንፈስና ለራሳቸው በሚደረገላቸው ጥሩ አቀባበል ላይ ያዩታል።

2 ትልልቅ ስብሰባዎቻችንን የሚጎበኙ ሰዎች አብዛኞቹ ተሰብሳቢዎች የታረመ ፀባይ እንዳላቸው ይመለከታሉ። ስለዚህ ዓይነቱ ስብሰባ አንድ ጋዜጠኛ እንዲህ ብሏል:- “አደንዛዥ ዕፅ የወሰደ ወይም መጠጥ የጠጣ አልነበረባቸውም፣ በስፖርት ሜዳ እንደሚታየው ዓይነት ጩኸት የለም፣ መጋፋት ወይም ሰውን ገፍትሮ ማለፍ የለም፣ ስድብ ወይም የእርግማን ቃል አይሰማባቸውም፣ አስቀያሚ ቀልድ ወይም ቀፋፊ ቃል አይናገሩም፣ አየሩ በሲጋራ ጭስ የተሞላ አይደለም፣ ስርቆት የለም፣ ለስላሳ መጠጥ የጠጡበትን ቆርቆሮ ሜዳ ላይ አይጥሉትም። በእውነቱ ሁኔታው በሌላ ጊዜ ከምናየው የተለየ ነበር።” ይህ ሁሉ ‘ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፣ የራሱንም ጥቅም ብቻ አይፈልግም’ የተባለለቱ ዓይነት ፍቅር መኖሩን ያሳያል። — 1 ቆሮንቶስ 13:4–8

3. (ሀ) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ፍቅር በማሳየት በኩል ሁኔታችን እንዴት መሆን አለበት? (ለ) ክርስቶስን ለመምሰል ምን ዓይነት ፍቅር መኰትኰት ያስፈልገ⁠ናል?

3 ፍቅር እያንዳንዱ እውነተኛ ክርስቲያን ተለይቶ የሚታወቅበት ጠባይ ነው። (ዮሐንስ 13:35) በመንፈሳዊነት እያደግን ስንሄድ ይህንን ፍቅር የበለጠ ማሳየት አለብን። ሐዋርያው ጳውሎስ የወንድሞቹ ፍቅር “ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ” ጸልዮአል። (ፊልጵስዩስ 1:9፤ 1 ተሰሎንቄ 3:12) ሐዋርያው ጴጥሮስም ክርስቲያን ወንድሞቹ ‘ፍቅራቸው መላውን የወንድማማች ማኅበር’ ያቀፈ እንዲሆን አሳስቧቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:17 አዓት) ፍቅራችን በግል እንድናውቃቸው ከማንጥርላቸው ሰዎች ጋር እንድንሰበሰብ ብቻ የሚገፋፋን መሆን የለበትም። በየጊዜው ስናገኛቸው “ሰላም” ብቻ ብለን ከማለፍ የበለጠ እንድናደርግላቸው የሚገፋፋን መሆን አለበት። ሐዋርያው ዮሐንስ ፍቅራችን ራስን መስዋዕት ለማድረግ የሚገፋፋን መሆን እንዳለበት አመልክቷል። ዮሐንስ “[የአምላክ ልጅ] ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፣ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል።” ብሎ ጽፎአል። (1 ዮሐንስ 3:16፤ ዮሐንስ 15:12, 13) ይህን ገና አላደረግንም። ይሁን እንጂ ቢያጋጥመን ሕይወታችንን ለወንድሞቻችን በእውነት እንሰጥ ነበርን? ታዲያ አሁንስ የራሳችንን ጉዳይ ትተን አመቺ በማይሆንበትም ጊዜ ጭመር ምን ያህል ልንረዳቸው እንሞክራለን?

4. (ሀ) ፍቅራችንን በምን ሌላ መንገድ የበለጠ ማሳየት እንችላለን? (ለ) እርስ በርሳችን የጋለ ፍቅር እንዲኖረን የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

4 ራስን የመሰዋት መንፈስ እንዳለን ከሚያንጸባርቁት ሥራዎች በተጨማሪ ለወንድሞቻችን ከውስጥ የሞቀ የመውደድ ስሜት እንዲኖረን ያስፈልጋል። የአምላክ ቃል “በወንድምነት ፍቅር አንዳችሁ ሌላውን ከልብ ይውደደው” ሲል ያሳስበናል። (ሮሜ 12:10 አዓት) ሁላችንም ለአንዳንድ ሰዎች እንደዚህ ያለ ስሜት አለን። ነገር ግን እንደዚህ አድርገን የምንወዳቸውን ሰዎች ቁጠር ልንጨምር እንችላለንን? የአሮጌው ሥርዓት መጨረሻ እየቀረበ ሲመጣ ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር የበለጠ መቀራረብ ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን አስፈላጊነት ሲያስታውሰን “የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። . . . ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ” ይላል። — 1 ጴጥሮስ 4:7, 8

5. በጉባኤ አባላት መካከል ምንም ችግር አይነሳም ብሎ ማሰብ ስሕተት የሚሆነው ለምንድን ነው?

5 እርግጥ አለፍጽምና እስካለን ድረስ አንዳንድ ጊዜ ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ነገር ማድረጋችን አይቀርም። እነርሱም በበኩላቸው በልዩ ልዩ መንገድ ይበድሉናል። (1 ዮሐንስ 1:8) ይህ ሁኔታ ቢደርስብህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ችግሮች ሲነሱ ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

6. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ከዝንባሌያችን ጋር ሁልጊዜ ላይስማማ የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ሆኖም ምክሩን ከሠራንበት ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል?

6 ቅዱሳን ጽሑፎች አስፈላጊውን መመሪያ ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ የቅዱሳን ጽሑፎች ምክር ፍጽምና የሌለን ሰዎች ካለን ዝንባሌ ጋር አንድ ላይሆን ይችላል። (ሮሜ 7:21–23) ቢሆንም ምክሩን በሥራ ላይ ለማዋል ከልብ ጥረት ማድረጋችን ይሖዋን ለማስደሰት እንደምንፈልግ ያሳያል። ለሌሎች የምናሳየው ፍቅርም የበለጠ ጥራት ይኖረዋል።

7. (ሀ) አንድ ሰው ቢበድለን ብድር መመለስ የሌለብን ለምንድን ነው? (ለ)ቅር ያሰኘንን ወንድም ርቀነው ዝም ማለት የማይገባን ለምንድን ነው?

7 አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሲበደሉ አጸፋውን እንዴት እንደሚመልሱ ያስባሉ። ሆኖም ይህ ነገሩን ያባብሰዋል። በቀል የሚያስፈልግ ከሆነ ለአምላክ ልንተውለት ይገባናል። (ምሳሌ 24:29፤ ሮሜ 12:17–21) በደል የፈጸመባቸውን ሰው ለመገናኘትም ሆነ ለማየት ፈጽሞ የማይፈልጉ ሰዎች አሉ። አብረውን ይሖዋን በሚያመልኩት ላይ ግን እንደዚህ ያለ አቋም ለመውሰድ አንችልም። አምልኰታችን ተቀባይነት የሚያገኝበት አንዱ መንገድ ለውንድሞቻችን በምናሳየው ፍቅር ነው። (1 ዮሐንስ 4:20) አንድን ሰው ማነጋገር የማንፈልግ ከሆነ ወይም አጠገባችን ሲሆን ደስ የማይለን ከሆነ እንወደዋለን በማለት ሳንዋሽ መናገር እንችላለንን? ከችግሩ ሳንሸሽ አንድ መፍትሄ ልንፈልግለት ይገባል። እንዴት?

8, 9. (ሀ) በአንድ ወንድም ላይ ቅሬታ ቢኖረን ማድረግ ያለብን ትክክለኛው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ነገር ግን ደጋግሞ በእኛ ላይ ኃጢአት ሠርቶ ቢሆንስ? (ሐ) ነገሩን በዚህ መንገድ መያዝ ያለብን ለምንድን ነው? ይህንንስ ለማድረግ ምን ይረዳናል?

8 በዚህ ጉዳይ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ጽፎአል:- “ማንም በሌላው ላይ ቅሬታ ካለው እርስ በርሳችሁ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም እንዲሁ አድርጉ” (ቆላስይስ 3:13 አዓት) እንደዚህ ማድረግ ትችላለህን? ሰውየው በልዩ ልዩ መንገድ ደጋግሞ ቢበድልህስ?

9 ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህንን ጥያቄ ጠይቋል። ‘ወንድሜን ሰባት ጊዜ ይቅር ለማለት ብሞክር ጥሩ ነውን?’ የሚል ሃሳብ አቀረበ። ኢየሱስ ግን “ሰባት ጊዜ ሳይሆን ሰባ ሰባት ጊዜ እልሃለሁ” ብሎ መለሰለት። ነገር ግን ለምን? ኢየሱስ ማንም ሰው ለእኛ ካለበት ዕዳ ጋር ሲወዳደር እኛ ለአምላክ ያለብን ዕዳ እጅግ በጣም የበዛ መሆኑን የሚያጐላ ምሳሌ በመናገር ምክንያቱን ገልጿል። (ማቴዎስ 18:21–35 አዓት) በየቀኑ በአምላክ ላይ በብዙ መንገዶች ኃጢአት እንሠራለን። አንዳንድ ጊዜ የራስ ወዳድነት ድርጊት እንፈጽማለን፣ ብዙ ጊዜም በንግግራችን ወይም በሐሳባችን እንሳሳታለን። በተጨማሪም የሚገባንን ባለማድረግ ኃጢአት እንሠራለን። እንዲያውም የሠራናቸው ነገሮች ኃጢአት እንደሆኑ ላይታወቀን ይችላል ወይም ለኑሮ በሚደረገው ሩጫ ለነገሩ በቂ ክብደት ሰጥተን አላሰብንበት ይሆናል። ለምንሠራቸው ኃጢአቶች አምላክ ሕይወታችንን እንድንከፍል ሊጠይቀን ይችል ነበር (ሮሜ 6:23) ይሁን እንጂ ለእኛ ምሕረት ማድረጉን ቀጥሏል። (መዝሙር 103:10–14) ስለዚህ እርስ በርሳችን ይህንን ጠባይ እንድናሳይ መጠየቁ ምክንያታዊ ነው። (ማቴዎስ 6:14, 15፤ ኤፌሶን 4:1–3) ቂም በመያዝ ፈንታ እንደዚያ የምናደርግ ከሆነ “በደልን አይቆጥርም” ወደተባለለት ዓይነት ፍቅር ደርሰናል ማለት ነው። — 1 ቆሮንቶስ 13:4, 5፤ 1 ጴጥሮስ 3:8, 9

10. አንድ ወንድም በእኛ ላይ ቅሬታ ቢኖረው ምን ማድረግ አለብን?

10 አንዳንድ ጊዜ በወንድማችን ላይ ቅሬታ ባይኖረንም እርሱ በእኛ ላይ ቅሬታ እንዳለው ይሰማን ይሆናል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ አለብን? ሳንዘገይ ልናነጋግረውና ሰላማዊ ግንኙነታችንን ለማደስ መሞከር ይኖርብናል። ነገሩን ራሳችን ቀዳሚ ሆነን እንድንጀምር መጽሐፍ ቅዱስ ያሳስበናል። (ማቴዎስ 5:23, 24) እንደዚያ ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል። ፍቅርና ትሕትና ይጠይቃል። በውስጥህ ያለው ፍቅርና ትሕትና የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር እንድትከተል ለመገፋፋት የሚያስችል ጥንካሬ አለውን? ይህ በጣም አስፈላጊ ግብ ስለሆነ ወደዚያ ለመድረስ ጥረት ማድረግ አለብን።

11. አንድ ወንድም እኛን የሚረብሽ ነገር ቢሠራ ምን ማድረግ አለብን?

11 በሌላው በኩል ግን አንተን፣ ምናልባትም ሌሎችን ጭምር የሚረብሽ ነገር የሚያደርግ ሰው ይኖር ይሆናል። ታዲያ አንድ ሰው ሄዶ ቢያነጋግረው አይሻልምን? ምናልባት ይሻል ይሆናል። አንተ ራስህ ቀስ ብለህ ችግሩን ብትገልጽለት ጥሩ ውጤት ሊገኝ ይችል ይሆናል። ሆኖም በመጀመሪያ ‘ሰውየው የሚያደርገው ነገር በእርግጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጋጫልን? ወይስ ነገሩ ስሕተት መስሎ የታየኝ አስተዳደጌ የተለየ ስለሆነ ነው?’ እያልህ ራስህን ጠይቅ። ሁኔታው እንደዚህ ከሆነ የራስህን የሚዛን ደረጃ ፈጥረህ ሌሎችን በዚያ እንዳትገምት ተጠንቀቅ። (ያዕቆብ 4:11, 12) ይሖዋ የተለያየ አስተዳደግ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ ያለ አድልዎ ይቀበላል። በመንፈሣዊ እያደጉ ሲሄዱም ይታገሣቸዋል።

12. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ከባድ ኃጢአት ተፈጽሞ ከሆነ ጉዳዩን የሚከታተለው ማን ነው? (ለ) ነገር ግን በመጀመሪያ ተበዳዩ ችግሩን ለመፍታት የመሞከር ኃላፊነት የሚኖረው በምን ጊዜ ነው? ምን ዓላማስ ሊኖረው ይገባል?

12 ይሁን እንጂ በጉባኤ ውስጥ የሚገኝ ግለሰብ ከባድ ኃጢአት ከሠራ ነገሩ ወዲያው ትኩረት እንዲሰጠው ያስፈልጋል። በማን? ብዙውን ጊዜ በሽማግሌዎች ነው። ነገሩ ገንዘብ ነክ ከሆነ ወይም በምላስ ሌላውን መጉዳትን የሚመለከት ከሆነ በመጀመሪያ ተበዳዩ በግል አነጋግሮ ሊረዳው ጥረት ማድረግ አለበት። እንደዚህ ማድረጉ ለአንዳንዶች ከባድ መስሎ ይታይ ይሆናል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በማቴዎስ 18:15–17 ላይ የሰጠው ምክር ይኸው ነው። ለወንድማችን ያለን ፍቅርና እርሱ ወንድም ሆኖ እንዲቀጥል ያለን ቅን ፍላጐት ልቡን መንካት በምንችልበት መንገድ እንድናነጋግረው ይረዳናል። — ምሳሌ 16:23

13. በእኛና በሌላ ወንድም መካከል ችግር ቢፈጠር ነገሩን በትክክል ለማየት የሚረዳን ምንድን ነው?

13 ትልቅ ይሁን ትንሽ፣ አንድ ዓይነት ችግር ሲፈጠር ነገሩን በይሖዋ አመለካከት ለማየት መሞከራችን ይረዳናል። ይሖዋ በምንም ዓይነት መልኩ ኃጢአትን ይቃወማል፤ ሆኖም በሁላችንም ላይ ኃጢአት ያገኛል። ንስሐ የማይገቡ ኃጢአት አድራጊዎች በጊዜው ከድርጅቱ ይበጠራሉ። ሌሎቻችንስ? ሁላችንም ትዕግስቱንና ምሕረቱን ፈላጊዎች ነን። ይሖዋ ልንከተለው የሚገባንን ምሳሌ አሳይቶናል። እርሱን ከመሰልን ፍቅርን እያንጸባረቅን ነው ማለት ነው። — ኤፌሶን 5:1, 2

ፍቅርህን ‘ለማስፋት’ የሚያስችሉ መንገዶች ፈልግ

14. (ሀ) ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ‘ልባቸውን እንዲያሰፉት’ ያበረታታቸው ለምንድን ነው? (ለ) በአንቀጹ ውስጥ ያሉት ጥቅሶች ነገሩን ሁላችንም ልናስብበት እንደሚገባ የሚያመለክቱት እንዴት ነው?

14 ሐዋርያው ጳውሎስ በግሪክ የነበረውን የቆሮንቶስ ጉባኤ በማነጽ ብዙ ወራት አሳልፎ ነበር። እዚያ የነበሩትን ወንድሞች ለመርዳት ብዙ ደከመ። ይወዳቸውም ነበር። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ለእርሱ ሞቅ ያለ የፍቅር ስሜት አልነበራቸውም። በጣም ይነቅፉት ነበር። ጳውሎስ ፍቅራቸውን ‘እንዲያሰፉት’ አጥብቆ መከራቸው። (2 ቆሮንቶስ 6:11–13፤ 12:15) ሁላችን ለሌሎች እስከምን ድረስ ፍቅር እያሳየን እንደሆነ ብንመረምርና ‘ፍቅራችንን ማስፋት’ የምንችልባቸውን መንገዶች ብንፈልግ ጥሩ ነው። — 1 ዮሐንስ 3:14፤ 1 ቆሮንቶስ 13:3

15. ለመቅረብ እምብዛም የማይማርኩን ቢኖሩ ለእነርሱ ያለንን ፍቅር ለማሳደግ ምን ሊረዳን ይችላል?

15 በጉባኤ ውስጥ ልንቀርባቸው እምብዛም ደስ የማይሉን ሰዎች አሉን? የራሳችንን ጥቃቅን ጉድለቶች እንዲያልፉልን እንደምንፈልግ ሁሉ እኛም የእነርሱን ጥቃቅን ጉድለቶች ብናልፍላቸው በመካከላችን ሞቅ ያለ ግንኙነት ሊፈጠር ይችላል። (ምሳሌ 17:9፤ 19:11) በተጨማሪም ጥሩ ጥሩ ጠባዮቻቸውን ለማስታወስ ብንሞክርና በእነዚያ ላይ ብናተኩር ለእነርሱ ያለን ስሜት ሊሻሻል ይችላል። ይሖዋ እነዚህን ወንድሞች እንዴት እየተጠቀመባቸው እንዳለ በእርግጥ አስበንበታልን? ይህንን መገንዘባችን ለእነርሱ ያለንን ፍቅር ከፍ ሊያደርገው ይችላል። — ሉቃስ 6:32, 33, 36

16. ሁኔታው በሚፈቅደው መሠረት በጉባኤ ውስጥ ላሉት ፍቅራችንን ልናሰፋው የምንችለው እንዴት ነው?

16 ለሌሎች ማድረግ የምንችለው ነገር ውስን መሆኑ አይካድም። ስብሰባ ባለ ቁጥር ሁሉንም መጨበጥ አንችል ይሆናል። ጓደኞቻችንን ምግብ ስንጋብዝ ሁሉንም መጥራት አንችል ይሆናል። ከሌሎች ይልቅ በጣም ከምንቀርባቸው ጋር የበለጠ ጊዜ እናጠፋለን። ይሁንና ‘ፍቅራችንን ሰፋ ልናደርገው’ እንችላለንን? በጉባኤያችን ውስጥ ካለ የቅርብ ጓደኛችን ካልሆነ ሰው ጋር የበለጠ ለመተዋወቅ በየሣምንቱ ጥቂት ደቂቃዎች ልናጠፋ እንችላለንን? አንዳንድ ጊዜ ከእኛ ጋር በመስክ አገልግሎት እንዲሠሩ ልንጋብዛቸው እንችል ይሆን? እርስ በርሳችን አጥብቀን የምንዋደድ ከሆነ ይህንን ለማሳየት የሚያስችሉ መንገዶች በእርግጥ እናገኛለን።

17. ከአሁን በፊት አግኝተናቸው በማናውቅ ወንድሞች መካከል ስንሆን እነርሱን አጥብቀን እንደምንወድ የምናሳየው እንዴት ነው?

17 ትልልቅ የክርስቲያን ስብሰባዎች ፍቅራችንን ለማስፋት ጥሩ አጋጣሚ ይሰጡናል። በስብሰባው በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኙ ይሆናል። ሁሉንም ዞረን ልናነጋግራቸው አንችልም። ሆኖም ከዚያ በፊት አግኝተናቸው ባናውቅም ከራሳችን ምቾት የእነርሱን ደኅንነት የሚያስቀድም ፀባይ ልናሳይ እንችላለን። በእረፍት ጊዜ አጠገባችን ወዳሉት ሄደን ልናነጋግራቸውና ስለ ሁኔታቸው ልንጠያይቃቸው እንችላለን። በምድር የሚኖሩ በሙሉ የሁሉም አምላክና አባት በሆነው በይሖዋ አምላክ የተባበሩ ወንድማማቾችና እህትማማቾች የሚሆኑበት ቀን ይመጣል። በዚያን ጊዜም ሁሉንም ከተለያየው ጠባያቸው ጋር ስናውቃቸው እንዴት እንደሰት ይሆን! ለእነርሱ የሚኖረን የጋለ ፍቅር እንደዚያ እንድናደርግ ይገፋፋናል። ታዲያ ለምን ከአሁኑ አንጀምረውም?

የክለሳ ውይይት

● በወንድሞች ወይም በእህቶች መካከል ችግር ሲነሳ እንዴት ሊፈታ ይገባዋል? ለምንስ?

● በመንፈሳዊ እያደግን ስንሄድ ፍቅራችንስ በምን መንገዶች ማደግ አለበት?

● ከቅርብ ጓደኞቻችን ክልል ውጭ የጋለ ፍቅር ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]