በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ከእናንተ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን አደርጋለሁ’

‘ከእናንተ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን አደርጋለሁ’

ምዕራፍ 14

‘ከእናንተ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን አደርጋለሁ’

1. ኢየሱስ እንደ ነገው ሊገደል ሲል ማታ ላይ ከሐዋርያቱ ፊት ምን ተስፋ አስቀመጠ?

ኢየሱስ እንደ ነገ ሊገደል ሲል ማታ ላይ ለታማኝ ሐዋርያቱ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትሆኑ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና” ብሏቸዋል። ከዚህም ሌላ “አባቴ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረገ እኔም ከእናንተ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን አደረግጋለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 14:2, 3፤ ሉቃስ 22:29 አዓት) ከፊታቸው እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ አስቀመጠላቸው!

2. በሰማያዊ መንግሥቱ ከክርስቶስ ጋር የሚካፈሉት ስንት ናቸው?

2 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከእርሱ ጋር በሰማያዊ መንግሥት የሚገዙት እነዚያ ሐዋርያት ብቻ ናቸው ማለቱ አልነበረም። ከምድር የተዋጁ 144, 000 ሰዎች ያንን ታላቅ መብት እንደሚያገኙ ቆየት ብሎ በሌላ ጊዜ ተገልጿል። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 4) ዛሬ አንዳንዶች ይህንን ሽልማት ለመጨበጥ እየጣሩ ነውን?

የመንግሥቱን ወራሾች መሰብሰብ

3. ኢየሱስ ለሕዝብ በሚሰብክበት ጊዜ ምን ዕድል የተከፈተ መሆኑን አስታውቋል?

3 ሄሮድስ አንጢጳስ አጥማቂው ዮሐንስን ወኅኒ ካስገባው በኋላ ኢየሱስ ከፍተኛ የስብከት ዘመቻ ጀመረ። ስብከቱ “በመንግሥተ ሰማያት” ላይ የሚያተኩር ነበር። (ማቴዎስ 4:12, 17) አድማጮቹ ወደዚያ መንግሥት የመግባት አጋጣሚ እንዳላቸው አስገነዘባቸው። ደቀመዛሙርቱ ብርቱ ጥረት አድርገው ለዚያ ሽልማት በቅተዋል። — ማቴዎስ 5:3, 10, 20፤ 7:21፤ 11:12

4. (ሀ) የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ለመጀመሪያ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት መቼ ነበር? (ለ) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የመንግሥቱን ወራሾች ለመሰብሰቡ ሥራ ትኩረት እንደተሰጠ የሚያመለክተው ምንድን ነው?

4 በ33 እዘአ በጴንጠቆስጤ ዕለት የመጀመሪያዎቹ ደቀመዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ ተቀቡ። (ሥራ 2:1–4፤ 2 ቆሮንቶስ 1:21, 22) የማይጠፋ ሰማያዊ ሕይወት የሚያስገኘው የአምላክ የመዳን ዝግጅት ታወቀ። ጴጥሮስ “በመንግሥተ ሰማያት ቁልፎች” ተጠቅሞ በመጀመሪያ ለአይሁዶች፣ ቀጥሎ ለሣምራውያን ከዚያም ለአሕዛብ ይህንን ዕውቀት ከፈተላቸው። (ማቴዎስ 16:19) የሰውን ልጆች ለሺህ ዓመት የሚገዛውን መንግሥት አባሎች ለመሰብሰብ ልዩ ትኩረት በመደረግ ላይ ነበር። በክርስቲያን ግሪክኛ ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ደብዳቤዎች የመንግሥቱ ወራሽ ለሆኑት “ቅዱሳን” ወይም “ለሰማያዊ ጥሪ ተካፋዮች” በቀጥታ የተጻፉ ናቸው። *

5. ለሰማያዊ ሕይወት የተጠሩት ከእነርሱ በፊት ከነበሩት የአምላክ አገልጋዮች የተሻሉ ስለሆኑ ነውን?

5 እነርሱ ለሰማያዊ ሕይወት የተጠሩት በ33 እዘአ ከዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት በፊት ከሞቱት የአምላክ አገልጋዮች ሁሉ የተሻሉ ስለሆኑ አይደለም። (ማቴዎስ 11:11) ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚገዙትን በዚያን ጊዜ መምረጥ ስለጀመረ ነው። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ለ19 መቶ ዓመታት ያህል አንድ ጥሪ ብቻ ነበር፤ እርሱም ሰማያዊ ጥሪ ነው። ይሖዋ ጥበብና ፍቅር የተሞላውን የራሱን ዓላማ ለማከናወን ሲል የተወሰነ ቁጥር ላላቸው ሰዎች ይገባናል የማይባል ደግነቱን አሳይቷል። — ኤፌሶን 2:8–10

6. (ሀ) ሰማያዊ ጥሪ የሚያበቃበት ጊዜ መኖር ያለበት ለምንድን ነው? (ለ) “እጅግ ብዙ ሰዎች” እንደሚመጡ የሚናገረው ትንቢት እንዲፈጸም ነገሮችን ወደዚያ አቅጣጫ የመራቸው ማን ነው? ታዲያ ምን ሆኖአል?

6 የተወሰነው የ144, 000 ቁጥር ከጊዜ በኋላ የሚሞላበትና ይሖዋ መንፈሳዊ እሥራኤላውያንን እንደተቀበላቸው የሚያረጋግጥበት የመጨረሻውን ማህተም የሚያደርግበት ጊዜ ቅርብ የሚሆንበት ዘመን መምጣት ነበረበት። (ራእይ 7:1–8) ያ ዘመን ሲደርስ ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነትና የሚታየው ድርጅቱ ቃሉን እንዲረዳ በማድረግ ነገሮችን በራእይ 7:​9–17 ያለው ሌላው የዓላማው ክፍል ወደሚፈጸምበት አቅጣጫ እንዲያመሩ ያደርጋል ማለት ነው። “ከታላቁ መከራ” ተርፎ በምድራዊት ገነት ውስጥ በፍጽምና ለዘላለም መኖርን የመሰለ አስደናቂ ተስፋ ያላቸው “እጅግ ብዙ ሰዎች” በመሰብሰብ ላይ ናቸው። ከተፈጸሙት ሁኔታዎች አንጻር ስንገመግም የሰማይ ጥሪ ባጠቃላይ በ1935 አካባቢ የተፈጸመ ይመስላል። በዚያ ዓመት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ምድራዊ ተስፋ እንዳላቸው በግልጽ ለመረዳት ተችሏል። ከዚያን ጊዜ በኋላ በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ከጥቂቶቹ የሰማይ ክፍል ቀሪዎች ጎን ተሰልፈዋል።

7. ዛሬም ቢሆን አንዳንዶች ሰማያዊ ጥሪ ሊያገኙ ይችላሉን? ለምን እንደዚያ ብለህ ትመልሳለህ?

7 ታዲያ እንደዚህ ሲባል አሁን አምላክ ለሰማያዊ ሕይወት የሚጠራቸው ምንም ሰዎች የሉም ማለት ነውን? የመጨረሻው ማኅተም እስኪደረግ ድረስ ይህ ተስፋ ካላቸው መካከል አንዳንዶች ታማኝ ሳይሆኑ ቀርተው በቦታቸው ሌሎች ሊመረጡ ይችላሉ። ሆኖም እነዚህ በጣም ጥቂት ይሆናሉ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይመስላል።

መንፈሳዊ ልጆች መሆናቸውን እንዴት ያውቃሉ?

8. በመንፈስ ቅዱስ የተወለዱ ሁሉ ይህ ሁኔታ እንደሚታወቃቸው ለማሳየት ጳውሎስ ምን ማብራሪያ ሰጥቷል?

8 ሰማያዊ ጥሪ ያገኙ የተጠመቁ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ልጆች ሆነው እንደተወለዱ የአምላክ መንፈስ አስተማማኝ ማረጋገጫ ይሰጣቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበሩት “ቅዱሳን” ሲጽፍ ይህን አመልክቷል። በዚያን ጊዜ የነበረውን የሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነት መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔት ወራሾች ነን፤ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።” — ሮሜ 1:7፤ 8:14–17

9. “መንፈሱ ራሱ” በእውነት የአምላክ ልጆች ከሆኑት ሰዎች መንፈስ ጋር ሆኖ ‘የሚመሠክረው’ እንዴት ነው?

9 እዚህ ላይ “መንፈስ” የሚለው ቃል “መንፈሱ ራሱ” እና “መንፈሳችን” በሚል በሁለት መንገድ ተሠርቶበታል። “መንፈሱ ራሱ” ሲል በዓይን የማይታየው አንቀሳቃሹ የአምላክ ኃይል ነው። ይህ መንፈስ የአምላክን መንፈሣዊ ልጆች “ነፃ የአምላክ ልጆች ሆነን ተወልደናል” የሚል እምነት ያሳድርባቸዋል። በተጨማሪም በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ይመሰክርላቸዋል። ቃሉ ለመንፈሳዊ ልጆቹ ለግል የተጻፈላቸው ደብዳቤ ያህል ነው። (1 ጴጥሮስ 1:10–12) በመንፈስ ቅዱስ የተወለዱት ልጆች ስለ አምላክ መንፈሳዊ ልጆች የሚናገሩ ጥቅሶች ሲያነቡ ‘ይህ እኔን የሚመለከት ነው’ የሚል ትክክለኛ ስሜት ይቀሰቀስባቸዋል። በዚህ መንገድ የአምላክ መንፈስ ከራሳቸው መንፈስ ይኸውም ከአእምሮአቸውና ከልባቸው ግፊት ጋር ሆኖ የአምላክ ልጆች መሆናቸውን በተለያዩ መንገዶች ይመሰክርላቸዋል። የአምላክ መንፈስ በዚህ መንገድ ከሚያመለክታቸው አቅጣጫ ጋር በመስማማት ልባቸውና አእምሮአቸው ከክርስቶስ ጋር ወራሽ በመሆኑ ተስፋ ላይ ያተኩራል። እነርሱም ለአምላክ መንፈሣዊ ልጆች የተሰጡትን ኃላፊነቶች ይቀበላሉ። — ፊልጵስዩስ 3:13, 14

10. (ሀ) አንድ ሰው እንዴት ያሉ ሁኔታዎች ብቻ የተቀባ ክርስቲያን አያደርጉትም? (ለ) “ሌሎች በጎች” በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስለተሰጣቸው ቦታ እንዴት ያለ አመለካከት አላቸው?

10 ያንተ ሁኔታ እንደዚህ ነውን? ከሆነ አስደናቂ መብት አለህ። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ጥልቅ የሆኑ መንፈሣዊ ነገሮች ስለሚገቡት ወይም በመስክ አገልግሎት ቀናተኛ ስለሆነ ወይም ለወንድሞቹ የጋለ ፍቅር ስላለው በመንፈስ የተቀባ ክርስቲያን መሆን አለበት ብሎ መደምደም ስህተት ነው። ብዙዎቹ “ሌሎች በጎች” እነዚህ ጠባዮች አሏቸው። ከክርስቶስ ጋር ወራሽ ስለሆኑት የሚናገሩትን ጥቅሶች ሲያነቡ እነርሱም ልባቸው በነገሩ ይነካል፤ ይሁን እንጂ አምላክ ያልሰጣቸውን መብት በድፍረት የእኔ ነው አይሉም። (ከዘኁልቁ 16:1–40 ጋር አወዳድር) አምላክ በመጀመሪያ ለምድር የነበረውን ዓላማ ያውቃሉ፣ ያ ዓላማ ሲፈጸም ተካፋይ ለመሆን በአድናቆት ይጥራሉ።

እንደሚገባው ሆኖ መካፈል

11. በየዓመቱ በሚከበረው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል እነማን ይገኛሉ? ለምንስ?

11 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች እርሱ ለሐዋርያቱ የሰጠውን መመሪያ በመከተል በየዓመቱ ኒሳን 14 ላይ ፀሐይ ከገባች በኋላ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ያከብራሉ። (ሉቃስ 22:19, 20) “ሌሎች በጎችም” በበዓሉ ይገኛሉ፤ ሆኖም በዓሉን በአክብሮት ለመከታተል እንጂ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ለመካፈል አይደለም።

12. በቆሮንቶስ የነበሩት አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች ለጌታ እራት ተገቢ አድናቆት ሳያሳዩ የቀሩት እንዴት ነው?

12 በዓሉ ከፍተኛ ትርጉም ያለው እንጂ ከንቱ ሃይማኖታዊ ስነ ሥርዓት አይደለም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ቆሮንቶስ በተባለች የግሪክ ከተማ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ለበዓሉ ተገቢውን አድናቆት ሳያሳዩ ቀርተው ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት” በማለት ከባድ ምክር ጽፎላቸዋል። መካፈል ‘የማይገባቸው’ ሆነው የተገኙት ለምን ነበር? በአእምሮና በልብ ተገቢ ዝግጅት አላደረጉም ነበር። ጉባኤው ተከፋፍሎ ነበር። ከዚህም ሌላ አንዳንዶቹ ከመጠን በላይ በልተውና ጠጥተው ወደ ስብሰባው ይመጡ ነበር። ለጌታ እራት የግድ የለሽነት መንፈስ አሳዩ። የቂጣውንና የወይን ጠጁን ትልቅ ትርጉም ለማስተዋል በሚያስችል ሁኔታ አልተገኙም። — 1 ቆሮንቶስ 11:17–34

13. በመታሰቢያው በዓል የሚቀርቡት ቂጣና ወይን ጠጅ ትርጉማቸው ምንድን ነው?

13 ታዲያ የቂጣውና የወይን ጠጁ ትርጉም ምንድን ነው? አንዳንዶች እንደሚያስቡት እነዚህ ነገሮች በተአምር የክርስቶስ ሥጋና ደም ሆነው አይለወጡም። ክርስቶስ በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ላይ በምንም ዓይነት መልኩ እንደገና አይሰዋም። ቅዱሳን ጽሑፎች “ክርስቶስ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ” እንደተሰዋ ይናገራሉ። (ዕብራውያን 9:28፤ 10:10፤ ሮሜ 6:9) ያልቦካው ቂጣና ቀዩ ወይን ጠጅ ኢየሱስ ለሰዋው ሥጋና ላፈሰሰው ደም የቆሙ ምሳሌዎች ናቸው። ሆኖም እንዴት ክቡር ነገሮች ናቸው! የሰው ልጆች ዓለም ለዘላለም የመኖር ዕድል እንዲያገኝ ኃጢአት የሌለበት የኢየሱስ ሰብአዊ አካል ተሰውቷል። (ዮሐንስ 6:51) የፈሰሰው ደሙም ለሁለት ዓላማ ያገለግላል። የሚያምኑበትን ሁሉ ከኃጢአት ያነጻቸዋል። በተጨማሪም በአምላክና በመንፈሳዊ እሥራኤል ጉባኤ መካካል አዲስ ቃል ኪዳን እንዲመሠረት አድርጓል። (1 ዮሐንስ 1:7፤ 1 ቆሮንቶስ 11:25፤ ገላትያ 6:14–16) አምላክ “የታናሹ መንጋ” አባሎች በአሁኑ ጊዜ ጻድቃን ሆናችኋል ብሎ የሚያስታውቅላቸው ወይም ሰብዓዊ ፍጽምና እንዳላቸው አድርጎ የሚቆጥርላቸው በእነዚህ ውድ ስጦታዎች ምክንያት ነው። (ሉቃስ 12:32) ይህ የሚደረግበት ምክንያት በመንፈስ ቅዱስ የአምላክ ልጆች ሆነው እንዲወለዱ ለማስቻል ነው። የአምላክ ልጆች ከሆኑ ደግሞ በሰማያዊው መንግሥት ከክርስቶስ ጋር የመግዛት ተስፋ ይኖራቸዋል። በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን ጠጅ በመካፈል ሰማያዊ ተስፋ እንዳላቸው ይመሠክራሉ። ይህንንም ሲያደርጉ በክርስቶስ መካከለኛነት በተመሠረተው “አዲስ ቃል ኪዳን” ውስጥ ስለመሆናቸው ያላቸው አድናቆት ይታደሳል፤ ጥልቀትም እያገኘ ይሄዳል። — ዕብራውያን 8:6–12

“ከእናንተ ጋር እንሂድ”

14. (ሀ) “ሌሎች በጎች” ከምሳሌለያዊው ቂጣና ወይን ጠጅ ለምን አይካፈሉም? ይሁን እንጂ በጉጉት የሚጠብቁት ምንድን ነው? (ለ) የመንግሥቱ ወራሾች ከሆኑት ቀሪዎች ጋር አብረው መሥራታቸውን እንዴት አድርገው ይመለከቱታል?

14 “ሌሎቸ በጎች” ይሖዋ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ያደረጋቸውን ነገሮች ያስተውላሉ። “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ” እያሉም ይተባበሯቸዋል። (ዘካርያስ 8:20–23) አብረው ከመሰብሰባቸውም ሌላ በምድር ዙሪያ የመንግሥቱን ምሥራች በማወጁ ሥራ አብረው ይሳተፋሉ። ሆኖም ይሖዋ “ሌሎችን በጎች” ከመንፈሣዊ እሥራኤል ጋር ወደ “አዲስ ቃል ኪዳን” አላስገባቸውም። በተጨማሪም ከኢየሱስ ጋር ሰማያዊ ሕይወት እንዲካፈሉ ለተመረጡት በተደረገው “የመንግሥት ቃል ኪዳን” ውስጥ አልገቡም። (ሉቃስ 22:20, 29) ስለዚህ በመታሰቢያው በዓል ከሚቀርቡት ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን ጠጅ አይካፈሉም፣ አድራጎታቸውም ተገቢ ነው። “አዲሱ ቃል ኪዳን” የታናሹን መንጋ የመጨረሻ አባላት ወደ ሰማያዊ መንግሥት የመሰብሰብ ዓላማውን ሲያጠናቅቅ ይህ ሁኔታ ያ መንግሥት በምድር ላይ በረከት የሚያዘንብበት ጊዜ መቅረቡን እንደሚያመለክት “ሌሎቹ በጎች” ይገነዘባሉ። በእነዚህ “መጨረሻ ቀኖች” ከታማኞቹ የመንግሥቱ ወራሾች ጐን ቆመው በአንድነት ማገልገሉን እንደ መብት ይቆጥሩታል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 የሮሜን፣ የ1ኛና የ2ኛ ቆሮንቶስን፣ የኤፌሶንን፣ የፊልጵስዮስን፣ የቆላስይስን፣ የቲቶንና የ1ኛንና የ2ኛጴጥሮስን መክፈቻ ቃላት ተመልከት። በተጨማሪም ገላትያ 3:26–29፣ 1 ተሰሎንቄ 2:12፤ 2 ተሰሎንቄ 2:14፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:8፤ ዕብራውያን 3:1፤ ያዕቆብ 1:18፤ 1 ዮሐንስ 3:1, 2ንና ይሁዳ 1ን ተመልከት

የክለሳ ውይይት

● በክርስቲያን ግሪክኛ ጽሑፎች ያለው አብዛኛው ሐሳብ ስለ ሰማያዊ ተስፋ የሚናገረው ለምንድን ነው?

● የአምላክ ልጆች ሆነው የተወለዱት ይህንን እንዴት ያውቃሉ? እነርሱ የሚካፈሉአቸው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን ጠጅ ትርጉማቸው ምንድን ነው?

● “ሌሎች በጎች” ከታናሹ መንጋ ጋር እውነተኛ አንድነት እንዳላቸው የሚያሳዩት እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]