በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሙሴ ሕግ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

የሙሴ ሕግ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

ምዕራፍ 19

የሙሴ ሕግ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

1. (ሀ) ከ36 እዘአ ጀምሮ ይሖዋ ያልተገረዙ አሕዛብን ክርስቲያን አድርጎ መቀበል መጀመሩን ያመለከተው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ሆኖም አንዳንዶቹ የጥንት ክርስቲያኖች በምን ጉዳይ ላይ የጋለ ክርክር አንስተዋል?

ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች የሙሴ ሕግ የሚያዛቸውን ነገሮች እንዲፈጽሙ ግዴታ አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚል የጋለ ክርክር በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን ተነስቶ ነበር። ቀደም ሲል ማለትም በ36 እዘአ ባልተገረዙት አሕዛብ ላይ መንፈስ ቅዱስ መውረዱ እውነት ነው። ሆኖም ከአይሁድ የመጡ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከአሕዛብ የመጡ ደቀ መዛሙርት ሊገረዙና የሙሴን ሕግ እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው ሊማሩ ይገባቸዋል የሚል ኃይለኛ ስሜት ነበራቸው። ታዲያ ያንን ሕግ ወይም ከፊሉን መጠበቅ ያስፈልጋቸው ነበርን? በ49 እዘአ አካባቢ ክርክሩ በኢየሩሳሌም ለሚገኘው የአስተዳደር አካል ቀረበ። — ሥራ 10:44–48፤ 15:1, 2, 5

2. የክርክሩን ውጤት ማወቅ የምንፈልገው ለምንድን ነው?

2 የክርክሩን መጨረሻ ማወቁ በጣም ያስፈልገናል። ለምን? አንዳንድ ጊዜ የሕጉን ክፍሎች፣ ለምሳሌ ሰንበትን አክብሩ የሚለውን ትእዛዝ ክርስቲያኖች መጠበቅ አለባቸው ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ስለሚያጋጥሙን ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ “ሕጉ ቅዱስ ነው፣ ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅ በጎም ናት” ብሎ ስለሚናገር ነው። (ሮሜ 7:12) የሕጉ ቃል ኪዳን መካከለኛ ሙሴ ስለነበረ የሙሴ ሕግ ተብሎ ቢጠራም ሕጉ የመጣው ከይሖዋ አምላክ ነው። — ዘፀአት 24:3, 8

ሕጉ ለምን ተሰጠ?

3. ሕጉ ለእስራኤል ለምን ተሰጠ?

3 ይሖዋ ሕጉን ለእስራኤል ለምን እንደሰጠ መረዳታችን ዛሬ ለሕጉ የሚኖረንን አመለካከት ይለውጠዋል። ቅዱስ ጽሑፉ እንዲህ ይላል:- “ሕጉ ተስፋ የተሰጠበት ዘር እስኪመጣ ድረስ የሰውን ሕግ ተላላፊነት በግልጽ ለማሳየት [በአብርሃም ቃል ኪዳን ላይ] ተጨመረ። . . . ከዚህ የተነሳ ሕጉ በእምነት ጽድቅ እንዲቆጠርልን ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ሞግዚታችን ሆኗል።” (ገላትያ 3:19, 24 አዓት) ሕጉ ይህን ዓላማውን የፈጸመው እንዴት ነው?

4. (ሀ) ሕጉ ‘የሰውን ሕግ ተላላፊነት ግልጽ አድርጎ ያሳየው’ እንዴት ነው? (ለ) ታማኝ ሰዎችንስ ወደ ክርስቶስ የመራቸው እንዴት ነው?

4 ሕጉ በልዩ ልዩ የሕይወት ዘርፎች ፍጹም የሆነውን አኗኗር በግልጽ በማስቀመጥ አይሁዶች ኃጢአተኞች መሆናቸውን አሳይቷል። የልባቸው ዓላማ ጥሩ ቢሆንና ተግተው ቢጥሩም ሕጉን አሟልተው ሊፈጽሙ እንደማይችሉ በግልጽ ታየ። ሕጉ ፍጽምና ለሌለው ሰብዓዊ ቤተሰብ አይሁዶችን እንደ ናሙና አድርጎ በመውሰድ ዓለም በሙሉ፤ እኛም ጭምር፤ ኃጢአተኞችና የአምላክ ቅጣት የሚገባን መሆናችንን አጋለጠ። (ሮሜ 3:19, 20 አዓት) በዚህ መንገድ ሕጉ የሰው ልጆች አዳኝ እንደሚያስፈልጋቸው አጉልቶ አሳየ። ታማኝ የሆኑትንም ሰዎች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ አድርሶ ያ አዳኝ እርሱ መሆኑን አመልክቷቸዋል። እንዴት ቢባል ኢየሱስ ሕጉን ሙሉ በሙሉ እንደፈጸመ፣ በዚህም ምክንያት ኃጢአት የሌለበት ሰው እርሱ ብቻ መሆኑን ሕጉ ስላረጋገጠ ነው። በሕጉ ሥር ይቀርቡ የነበሩት የእንስሳት መስዋዕት ጥቅማቸው የተወሰነ ነበር። ኢየሱስ ግን ፍጹም ሰው ስለነበረ ሕይወቱን ኃጢአትን በእርግጥ አስወግዶ ለማያምኑት ሁሉ የዘላለም ሕይወትን መንገድ የሚከፍት መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ችሏል። — ዮሐንስ 1:29፤ 3:16፤ 1 ጴጥሮስ 1:18, 19

5. በዚህ አንቀጽ ውስጥ ያሉትን ጥያቄዎች በተሰጡት ጥቅሶች አማካኝነት መልሳቸው።

5 ይህንን መሠረታዊ ዕውቀት በአእምሮህ ይዘህ ለሚቀጥሉት ጥያቄዎች ምን መልስ ትሰጣለህ?

የሙሴ ሕግ ወደፊት በሁሉም የሰው ዘሮች ላይ እንዲሠራ ታስቦ ነበርን? (መዝሙር 147:19, 20፤ ዘፀአት 31:12, 13)

የሕጉ ቃል ኪዳን አንድ ቀን እንደሚያበቃ ይሖዋ ለእስራኤላውያን ጠቁሞላቸው ነበርን? (ኤርምያስ 31:31–33፤ ዕብራውያን 8:13)

ሕጉ ከተሻረ በኋላ አሥሩ ትእዛዛት፣ ስለ ሣምንታዊ ሰንበት የሚናገረው ትእዛዝ ጭምር፣ ሳይሻሩ ቀርተዋልን? (ቆላስይስ 2:13, 14, 16፤ 2 ቆሮንቶስ 3:7–11 [የዚህኛውን ጥቅስ ትርጉም ዘፀአት 34:28–30 ግልጽ ያደርገዋል]፤ ሮሜ 7:6, 7)

ይሖዋ የሕጉን ቃል ኪዳን ወደ ፍጻሜው ያመጣው በምን አማካኝነት ነው? (ቆላስይስ 2:13–17፤ ማቴዎስ 5:17, 18፤ ሮሜ 10:4)

6. የሙሴ ሕግ አሁንም ይሠራል የሚለው ክርክር ምን ያመለክታል?

6 ታዲያ ይህ ሁሉ ማስረጃ እያለ የሙሴ ሕግ አሁንም ይሠራል ብሎ መከራከሩ ምን ያመለክታል? በተዘዋዋሪ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ዋጋ የለውም ብሎ እንደመናገር ያህል ነው። ለምን እንደዚህ እንላለን? ምክንያቱም ይህ አመለካከት ኢየሱስ ሕጉን አልፈጸመውም፣ ስለዚህ አምላክ እንዲሽረው መንገድ አልተከፈተለትም ብሎ እንደማሰብ ያህል ስለሚቆጠር ነው። ክርስቲያን ነን እያሉ ሕጉን በሙሉ ወይም ከፊሉን መጠበቅ ያስፈልጋል በሚለው ክርክር ለተሳቡ ለአንዳንዶች ሐዋርያው ጳውሎስ “በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል” በማለት ኃይለኛ ቃል ጽፎላቸዋል። — ገላትያ 5:4፤ በተጨማሪም ሮሜ 10:2–4ን ተመልከት።

7. (ሀ) በሕጉ ውስጥ የነበሩት አንዳንድ ነገሮች አሁንም ይሠራሉ ብለው የሚከራከሩት ሙሉ በሙሉ ያልገባቸው ነገር ምንድን ነው? (ለ) የክርስቲያን ሥራዎች ምን ያህል አስፈላጊ ናቸው? እነርሱስ የዘላለም ሕይወት ስጦታ ከማግኘታችን ጋር ምን ግንኙነት አላቸው?

7 አንዳንዱ የሕጉ ክፍል መሥራቱን ቀጥሏል ብለው የሚከራከሩት ሰዎች በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም የሚገኘው ሕጉን በሥራ ላይ በማዋል ሳይሆን በኢየሱስ መስዋዕት በማመን መሆኑን ሙሉ በሙሉ አልገባቸውም። (ገላትያ 3:11, 12) አንድ ሰው እንደነዚህ ባሉት ሥራዎች ጻድቅ መሆኑን ማስመስከር አለበት ብለው ያስባሉ። ለኃጢአተኛ ሰዎች ደግሞ ይህ የማይቻል ነገር ነው። እርግጥ አምላክና ክርስቶስ ለክርስቲያኖች የሰጧቸውን ሥራዎች በመፈጸም ታዛዥ መሆን አስፈላጊ ነው። (ያዕቆብ 2:15–17፤ ማቴዎስ 28:19, 20) እነዚህ ሥራዎች የፍቅራችንና የእምነታችን መግለጫ ናቸው። የእነርሱ አለመኖር እምነታችን የሞተ መሆኑን ያመለክታል። ሆኖም የፈለገውን ያህል ብንሠራ መዳን የድካማችን ደመወዝ ሆኖ ሊከፈለን አይችልም። ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕት ከኃጢአትና ከሞት መዳን ፈጽሞ አይቻልም። ስለሆነም የዘላለም ሕይወት አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያዘጋጀልን ስጦታ ነው። የድካማችን ደመወዝ ሳይሆን ልዩ የሆነና ይገባናል የማንለው የአምላክ ደግነት መግለጫ ነው። — ኤፌሶን 2:8, 9፤ ሮሜ 3:23, 24፤ 6:23

8  የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአስተዳደር አካል የሙሴ ሕግ ከአሕዛብ በመጡ ክርስቲያኖች ላይ ይሠራል ወይስ አይሠራም በሚለው ክርክር ላይ ምን ውሳኔ አስተላለፈ?

8 የሙሴ ሕግ ከአሕዛብ በመጡት ክርስቲያኖች ላይ ይሠራል ወይስ አይሠራም የሚለው ጥያቄ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌም ለነበረው የአስተዳደር አካል በቀረበ ጊዜ የአካሉ ውሳኔ ከእነዚህ ቁም ነገሮች ጋር የሚስማማ ነበር። የአስተዳደር አካሉ ከአሕዛብ የመጡት አማኞች የሙሴን ሕግ ሳያከብሩ ይሖዋ መንፈስ ቅዱስ እንዳፈሰሰላቸው ተገነዘበ። ውሳኔው በሙሴ ሕግ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ‘አስፈላጊ’ ዕገዳዎችንም ይጨምራል። ይሁን እንጂ የአስተዳደር አካሉ እነዚህን ዕገዳዎች የጨመረው ከሕጉ በፊት በተፈጸሙና በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግበው በነበሩ ታሪኮች ላይ ተመርኩዞ ነው። ስለዚህ ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ ወይም ከፊሉን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዲሸከሙ መደረጉ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ዕገዳዎቹ የተጠቀሱት ከሙሴ በፊት የነበሩትን የአቋም ደረጃዎች ለማጽናት ነው። — ሥራ 15:28, 29፤ ከዘፍጥረት 9:3, 4፤ 34:2–7፤ 35:2–5 ጋር አወዳድር።

9 . (ሀ) አምላክ አይሁዶች አሁንም የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ይፈልግባቸዋልን? (ለ) የክርስቶስ አሟሟት ምን ልዩ ነገር አስገኝቶላቸዋል?

9 አይሁዶች ራሳቸው በ33 እዘአ ከዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት በኋላ የሙሴን ሕግ እንዲያከብሩ የነበረባቸውን ግዴታ አምላክ አንስቶላቸዋል። ያመኑት አይሁዶች በዚህ የሚደሰቱበት ልዩ ምክንያት እንዳላቸው ተገንዝበዋል። ለምን ይሆን? አሕዛብ እንደ እነርሱ ኃጢአተኞች ቢሆኑና በዚህ ምክንያት ቢሞቱም የሕጉን ቃል ኪዳን አፍራሽ በመሆን በአምላክ እርግማን ሥር የወደቁት አይሁዶች ብቻ ነበሩ። ነገር ግን ኢየሱስ እንደተረገመ ወንጀለኛ ሆኖ በእንጨት ላይ ስለተሰቀለ በሚያምኑበት አይሁዶች ቦታ ገብቶ ሕጉን ባለመታዘዛቸው ምክንያት ሊመጣባቸው ከሚችለው ቅጣት አድኗቸዋል። (ገላትያ 3:10–13) በዚህ መንገድ በሙሴ ሕግ ሥር ሳሉ ሊያገኙት ያልቻሉትን የኃጢአት ይቅርታ አስገኝቶላቸዋል። — ሥራ 13:38, 39

10. የሕጉ መወገድ የአምልኮ አንድነት ያስገኘው በምን መንገድ ነው?

10 እንዲያውም ሕጉ በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል እንደ አጥር ሆኖ ነበር። አይሁዶች ለአሕዛብ ያልተሰጡ ትዕዛዞችን ተቀብለዋል። ከዚህም ሌላ ያልተገረዙ አሕዛብ ከአይሁድ ጋር በአምልኮ ሙሉ በሙሉ እንዳይሳተፉ ተከልክለው ነበር። (ከዘፀዓት 12:48 እና ከሥራ 10:28 ጋር አወዳድር) ነገር ግን ሕጉ ዓላማውን አከናውኖ ከተወገደ በኋላ አይሁዶችና ያልተገረዙ አሕዛብ እውነተኛውን አንድ አምላክ በክርስቶስ በኩል በአንድነት ለማምለክ ችለዋል። — ኤፌሶን 2:11–18

ስለ ሕጉ የምናገኘው ዕውቀት ይጠቅመናል

11. ስለ ሕጉ የምናገኘው እውቀት ክርስቶስ ያስተማራቸው ትምህርቶች እንዲገቡን የሚረዳን እንዴት ነው?

11 እኛ ዛሬ በሕጉ ሥር ባንሆንም ስለ ሕጉ እውቀት ማግኘታችን ለእያንዳንዳችን ትልቅ ጥቅም ያመጣልናል። በምን መንገድ? ኢየሱስ አይሁዳዊት እናት እንደወለደችውና በዚህ ምክንያት በሙሴ ሕግ ሥር ለመሆን እንደቻለ አስታውስ። ኢየሱስ ያደረጋቸውን አንዳንድ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ለመረዳት የምንችለው ስለ ሕጉ ትዕዛዞች እወቀት ካለን ብቻ ነው። (ገላትያ 4:4፤ በተጨማሪም ሉቃስ 22:7, 8ን ተመልከት) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ አገልግሎቱን ያከናውን የነበረው በሕጉ ሥር በነበሩት ሕዝብ መካከል ነው። ስለዚህ ትምህርቶቹ ብዙውን ጊዜ ከሕጉ ጋር ዝምድና ባላቸው ነገሮች ላይ የተመሠረቱ ነበሩ። — ከማቴዎስ 5:23, 24 ጋር አወዳድር።

12. (ሀ) ኢየሱስ የራሱን ሕይወትና የሙሴን ሕግ ያዛመደው እንዴት ነው? (ለ) ሕጉን ማወቅ ስለሚሰጠው ጥቅም ሐዋርያው ጳውሎስ ያመለከተው እንዴት ነው? (ሐ) ሕጉ የሚያዛቸውን ነገሮች መንፈሳዊ ትርጉም መረዳታችን ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል?

12 ኢየሱስ ሰው ሆኖ ባሳለፈው ሕይወቱ በሕጉ፣ በነቢያትና በመዝሙሮች ስለ እርሱ የተጻፉትን ነገሮች እንደፈጸመ ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ገልጾላቸዋል። (ሉቃስ 24:44) ሐዋርያው ጳውሎስም ከሕጉ ቃል ኪዳን ጋር የተያያዙ አንዳንድ ሁኔታዎች “ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ” መሆናቸውን ተናግሯል። በተጨማሪም “ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር ጥላ አለው” ብሏል። (ዕብራውያን 8:4, 5፤ 10:1) በኢየሱስ ክርስቶስ ክህነትና መስዋዕት በሆነልን ሰብዓዊ ሕይወቱ ላይ የተፈጸሙ አስደናቂ ዝርዝሮች በሙሴ ሕግ ውስጥ ይገኙ ነበር። እነዚህን ነገሮች መረዳታችን የክህነቱንና የመስዋዕቱን ትርጉም የበለጠ ግልጽ ያደርግልናል። ከትንቢታዊ ጥላዎቹ መካከል ዛሬ በታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሆኖ ስለ ማምለክ የሚገልጹ ዝርዝሮች ይገኙበታል። እነዚህ ነገሮች የበለጠ ሲገቡን በመንፈስ ለተቀባው ጉባኤና ጉባኤው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር ከአምልኰታችን ጋር በተያያዘ መንገድ ለሚሠራቸው ነገሮች ያለን አድናቆት ይጨምራል።

13. በሕጉ ላይ ስለተንፀባረቁት መሠረታዊ ሥርዓቶች ማሰላሰል ለምን ይጠቅማል?

13 የሙሴ ሕግ “ለትምህርት፣ ለተግሣጽ፣ ነገሮችንም ለማቅናት” ይጠቅማሉ የተባለላቸው በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ጽሑፎች ክፍል ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16 አዓት) ሕጉ የተመሠረተባቸውን ቋሚ መሠረታዊ ሥርዓቶች ስንመረምርና ስናሰላስልባቸው አምላክን ደስ የሚያሰኙትን ነገሮች ለማድረግ ልባዊ ፍላጎት ያድርብናል። የሕጉ መንፈስ ወዴት አቅጣጫ እንደሚመራ ካስተዋልንና ያንን መንፈስ በሕይወታችን ውስጥ ካንፀባረቅን እንዴት ብዙ እንጠቀማለን!

14. (ሀ) የሕጉ መንፈስ ወዴት እንደሚመራ የማስተዋልን ጥቅም ኢየሱስ በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው? (ለ) በገጽ 152 ላይ ባለው ሠንጠረዥ መሠረት ሕጉ የያዛቸውን ሌሎች ጥሩ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥቀስ? (ሐ) እነዚህን ነገሮች መረዳታችን አምላክን የበለጠ ለማስደሰት የሚረዳን እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ይህን ሁኔታ በምሳሌ ጥሩ አድርጎ አብራርቶታል። በዚያን ጊዜ በሕጉ ሥር ለነበሩት ሰዎች ሲናገር ሰውን ከመግደል መቆጠብ ብቻ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ተቆጥቶ የመቆየትን አዝማሚያ ሁሉ ከሥሩ ነቅለው መጣልና በምላሳቸው ወንድማቸውን ከማንቋሸሽ መራቅ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጾላቸዋል። ዝሙትን ፈጽሜ አላውቅም በማለት በዚህ ብቻ በመርካት ፋንታ ሴትን በምኞት እንዳይመለከቱ ነገራቸው። እኛም እንደ እነርሱ የሰውነታችንን ክፍሎች በሙሉ ከይሖዋ የጽድቅ መንገዶች ጋር በሚስማማ መንገድ እንድንጠቀምባቸው ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (ማቴዎስ 5:21, 22, 27–30፤ በተጨማሪም ሮሜ 13:8–10ን ተመልከት) ይህንን የምናደርግ ከሆነ “ይሖዋ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም አእምሮህም ውደድ” የሚለው ከሁሉ የሚበልጠው ሕግ እንደገባን እናሳያለን። (ማቴዎስ 22:36, 37 አዓት) ይህ ወደ ይሖዋ አምላክ የበለጠ እንደሚያቀርበን የተረጋገጠ ነው። እንግዲህ ምንም እንኳ ዛሬ በሙሴ ሕግ ሥር ባንሆንም ሕጉ የተመሠረተባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶችና በሕጉ ውስጥ ያሉትን ትንቢታዊ ምሳሌዎች በትክክል ብናውቅ ብዙ ጥቅም ማግኘታችን አያጠራጥርም።

የክለሣ ውይይት

● የሙሴን ሕግ ማክበር አለብን ብለው የሚከራከሩት ሰዎች ክርስቶስን አልተቀበሉትም የምንለው ለምንድን ነው?

● ስለ ሕጉ የምናገኘው ዕውቀት ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ያለውን ሚና ለመረዳት የሚያስችለን እንዴት ነው?

● በሕጉ ሥር ባንሆንም ሕጉን በማጥናት ምን ጠቃሚ ነገሮችን ለመረዳት እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 152 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሙሴ ሕግ የታቀፉ አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶች

አምላክን በሚመለከት መሟላት የሚገቡ ኃላፊነቶች

ይሖዋን ብቻ አምልክ ዘፀ 20:3፤ 22:20

ስሙን በክብር ያዝ ዘፀ 20:7፤ ዘሌ 24:16

በፍጹም ልብህ፣ ነፍስህና ኃይልህ ውደደው፣ ዘዳ 6:5፤ 10:12፤ 30:16

አገልግለው

ይሖዋን ራሱንና እሱን አለመታዘዝን ፍራ ዘዳ 5:29፤ 6:24

እርሱ በሚፈቅደው መንገድ ብቻ ዘሌ 1:1–5፤ ዘኁ 16:1–50

ቅረበው ዘዳ 12:5–14

ምርጥህን ስጠው፤ የመጣው ከእርሱ ነውና ዘፀ 23:19፤ 34:26

አምላኪዎቹ በአካል ዘፀ 19:10, 11፤ 30:20

ንጹሕ መሆን አለባቸው

ለሥጋዊ ነገሮች ሲባል ቅዱሳን ነገሮችን ዘፀ 20:8–10፤ 34:21

ወደ ጎን ማድረግ አይገባም ዘኁ 15:32–36

የተከለከሉ ሃይማኖታዊ ድርጊቶች

ጣዖት ማምለክ ዘፀ 20:4–6፤ ዘዳ 7:25

ቅልቅል ሃይማኖት መያዝ ዘፀ 23:13፤ 34:12–15

ዘዳ 6:14, 15፤ 13:1–5

መናፍስትነት፣ መተተኛነት፣ ጥንቆላ፣ ዘፀ 22:18፤ ዘሌ 20:27

ምዋርት፣ አስማት፣ በሰው ላይ ማስደገም ዘዳ 18:10–12

ጋብቻና የቤተሰብ ኑሮ

ምንዝር ክልክል ነበር ዘፀ 20:14፤ ዘሌ 20:10

ይሖዋን ከማያመልኩ ጋር መጋባት ክልክል ነበር ዘዳ 7:1–4

የቅርብ ዘመዳሞች ጋብቻ ክልክል ነበር ዘሌ 18:6–16፤ 20:11

ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ግብረ ሥጋ አይፈቀድም ዘሌ 18:23፤ 20:13

ላልተወለደ ሕፃን ሕይወት አክብሮት ማሳየት ዘጸአት 21:22, 23

ወላጆችህን አክብር ዘፀ 20:12፤ 21:15, 17

ዘዳ 21:18–21

ለልጆች የይሖዋን መንገዶች አስተምሩ ዘዳ 6:4–9፤ 11:18–21

ሌሎች ሰዎችን የሚመለከቱ ተግባራት

የሰውን ሕይወት እንደ ቅዱስ ነገር መያዝ ዘፀ 20:13፤ ዘኁ 35:9–34

ባልንጀራህን ውደድ፤ ቂም አትያዝ ዘሌ 19:17, 18

ለአረጋውያን እዘኑ ዘሌ 19:32

የኢኮኖሚ ችግር ላለባቸው፣ አባት ለሌላቸውና ዘሌ 25:35–37

ለመበለቶች ፍቅራዊ አሳቢነት አሳዩ ዘዳ 15:7–11፤ 24:19–21

በደንቆሮና ዓይነ ስውር ላይ ክፉ መሥራት አይገባም ዘሌ 19:14፤ ዘዳ 27:18

በንግድ ሥራ ሐቀኞች ሁኑ ዘሌ 19:35, 36፤ 25:14

የሰውን ንብረት አክብሩ ዘፀ 20:15፤ 22:1, 6፤ 23:4

ዘዳ 22:1–3

የሌላውን ሀብት አትመኝ ዘፀ 20:17

ከባድ ኃጢአት የሚሠሩትን አጋልጥ ዘሌ 5:1፤ ዘዳ 13:6–11

እውነት ተናገሩ፣ በውሸት አትመስክር ዘፀ 20:16፤ 23:1, 2

ሥልጣን አይተህ አታድላ ዘፀ 23:3, 6፤ ዘሌ 19:15