በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የማይፈርስ መንግሥት”

“የማይፈርስ መንግሥት”

ምዕራፍ 10

“የማይፈርስ መንግሥት”

1, 2. (ሀ) በየዕለቱ በዓለም የሚፈጸሙ ሁኔታዎች የትኛውን እውነት አጉልተው ያሳያሉ? እንዴትስ? (ለ) መፍትሔው ምን ብቻ ነው?

የሰው ልጆች የይሖዋን ሉዓላዊነት አንቀበልም ብለው ራሳችውን በራሳቸው ለማስተዳደር መሞከራቸው ደስታን እንዳላመጣላቸው በየቀኑ የሚፈጸሙ የዓለም ሁኔታዎች በጉልህ ያረጋግጣሉ። ያለ አድልዎ ለሁሉም ሰው ጥቅም የሚሰጥ አንድም ሰብዓዊ የአስተዳደር ሥርዓት የለም። ሰዎች በሳይንስ ተራቀው ከአሁን በፊት ወዳልደረሱበት ደረጃ ቢደርሱም ኃጢአትን ከሥሩ ለመንቀል፣ በሽታን አሸንፈው ለማጥፋት ወይም ሞትን ለማቆም አልቻሉም። ከዜጎቻቸው ለአንዱም እንኳን ይህንን አላደረጉለትም። እንዲያውም በተቃራኒው ብሔራት እጅግ አስፈሪ የሆኑ አዳዲስ መሣሪያዎችን መፈልሰፋቸውን ቀጥለዋል። የወንጀል ድርጊት እየተስፋፋ ነው። ቴክኖሎጂ፣ ስግብግብነትና ድንቁርና አንድ ላይ ተዳምረው መሬቱን፣ ውኃውንና አየሩን ይበክላሉ። እየባሰበት በሄደው የኑሮ ውድነትና በሥራ አጥነት ምክንያት ብዙ ሰዎች ለመኖር የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማግኘት ተስኗቸዋል። ሰዎች ከዚህ ሁሉ ውስብስብ ሁኔታ እንዴት እንደሚወጡ ጨንቋቸዋል። — መክብብ 8:9

2 ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹ ይህ መንግሥት ይምጣ ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) መንግሥቱ የሚያመጣው እፎይታ በጣም ቅርብ በመሆኑ እንዴት አመስጋኝ መሆን ይገባናል!

3. (ሀ) ይህንን መንግሥት በሚመለከት በ1914 በሰማይ ምን ሆነ? (ለ) ይህስ ለእኛ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?

3 በኢየሱስ ክርስቶስ መሪነት የሚገዛው የአምላክ መንግሥት ከ1914 ጀምሮ በሥልጣን ላይ ነው። * ዳንኤል በትንቢታዊ ራእይ ላይ የተመለከታቸው ነገሮች በዚያ ዓመት በሰማይ ተፈጽመዋል። “በዘመናት የሸመገለው” ይሖዋ አምላክ ለሰው ልጅ ይኸውም ለኢየሱስ ክርስቶስ “ወገኖችና አሕዛብ፣ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም” ሰጥቶታል። ዳንኤል በራእይ ያየውን ሲገልጽ “ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው” ሲል ጽፎአል። (ዳንኤል 7:13, 14) ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችን በገነት ባስቀመጠ ጊዜ ለሰው ልጆች አስቧቸው የነበሩትን ስፍር ቁጥር የሌላቸው መልካም ነገሮች ጽድቅ ወዳድ ለሆኑት ሰዎች የሚሰጠው በዚህ መንግሥት አማካኝነት ይሆናል።

4. መንግሥቱን በሚመለከት የትኞቹን ዝርዝር ሁኔታዎች ለማወቅ እንጓጓለን? ለምንስ?

4 የመንግሥቱ ታማኝ ተገዥዎች ስለ መንግሥቱ አደረጃጀትና የአስተዳደር ሁኔታ ለማወቅ በጣም ይፈልጋሉ። መንግሥቱ በአሁኑ ጊዜ ምን እያደረገ እንዳለ፣ ወደፊት ምን እንደሚያከናውንና ከእነርሱ ምን እንደሚጠብቅባቸው ለማወቅ ይፈልጋሉ። የመንግሥቱን ሁኔታ አጥብቀው ይመረምራሉ። ይህንንም ሲያደርጉ ለመንግሥቱ ያላቸው አድናቆት ይጨምራል። እንዲሁም ስለ መንግሥቱ ለሌሎች ለመናገር የተሻለ ብቃት ያገኛሉ። — መዝሙር 48:12, 13

ልብን የሚቀሰቅስ ምርመራ

5. (ሀ) መሲሐዊው መንግሥት የማን ሉዓላዊነት መግለጫ እንደሆነ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) እንግዲያው ስለ መንግሥቱ የምንማረው ሁሉ እንዴት ይነካናል?

5 አንድ ሰው እነዚህን ነገሮች ለማወቅ ሲመራመር በመጀመሪያ ከሚገነዘባቸው ነገሮች አንዱ ይህ መንግሥት የይሖዋ ሉዓላዊነት መግለጫ መሆኑን ነው። ለልጁ “ግዛትና ክብር መንግሥትም” የሰጠው እርሱ ነው። ስለሆነም ይህ መንግሥት መግዛት ከጀመረ በኋላ በሰማይ “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና [ለይሖዋ አምላክና] ለክርስቶስ ሆነች፣ [ይሖዋም (አዓት)] ለዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል” የሚል አዋጅ መሰማቱ ተገቢ ነበር። (ራእይ 11:15) እንግዲያው ይህን መንግሥት ቀረብ ብለን ስንመለከተው የምናየውና መንግሥቱ የሚያከናውነው ነገር ሁሉ ወደ ይሖዋ የበለጠ እንድንጠጋ ያደርገናል። ለይሖዋ ሉዓላዊነት ራሳችንን ለዘላለም እንድናስገዛ ፍላጎት ያሳድርብናል።

6. ኢየሱስ ክርስቶስ የይሖዋ ምክትል ገዥ መሆኑን በጣም የምንፈልገው ነገር የሆነው ለምንድን ነው?

6 ይሖዋ ኢየሱስ ክርስቶስን ምክትል ገዥ አድርጎ በዙፋን ላይ ማስቀመጡ እንዴት ጥሩ ነው! ኢየሱስ ምድርንና ሰውን ለመሥራት አምላክ የተጠቀመበት ዋና ሠራተኛ እንደመሆኑ መጠን ሰው ምን እንደሚያስፈልገው ከማንኛችንም ይበልጥ የሚያውቅ እርሱ ነው። ከዚህም በላይ የሰው ታሪክ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር አሳይቷል። (ምሳሌ 8:30, 31፤ ቆላስይስ 1:15–17) ይህ ፍቅሩ ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ ራሱ ወደ ምድር ወርዶ ሕይወቱን ለሰዎች ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። በዚህ መንገድ ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የምንሆንበትና የዘላለም ሕይወት የምናገኝበት አጋጣሚ ከፍቶልናል። — ማቴዎስ 20:28

7. (ሀ) ከሰብዓዊ መንግሥታት አንጻር ሲታይ ይህ መንግሥት ለሁልጊዜ ጸንቶ የሚኖረው ለምንድን ነው? (ለ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከሰማያዊው መንግሥት ጋር ምን ዝምድና አለው?

7 መንግሥቱ የተረጋጋ፣ ለሁልጊዜው ጸንቶ የሚኖር መንግሥት ነው። ይሖዋ የማይሞት መሆኑ ለመንግሥቱ ዘላለማዊነት ዋስትና ይሆናል። (ዕንባቆም 1:12 አዓት፤ መዝሙር 146:3–5, 10) ይሖዋ ንጉሥ አድርጎ የሾመው ኢየሱስ ክርስቶስም ያለመሞትን ባሕርይ ስለለበሰ ከሰብዓዊ ነገሥታት የተለየ ነው። (ሮሜ 6:9፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:15, 16) በሰማያዊ ዙፋኖች ከክርስቶስ ጋር የሚቀመጡ ሌሎች 144, 000 ነገሥታት ይኖራሉ። እነርሱም “ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ” የተወሰዱ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ሲሆኑ ከቶ ሊጠፋ የማይችል ሕይወት ይሰጣቸዋል። (ራእይ 5:9, 10፤ 1 ቆሮንቶስ 15:42–44, 53) በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ በሰማይ ይገኛሉ፤ ገና በምድር ያሉት ቀሪዎች ደግሞ “ታማኝና ልባም ባሪያ” በመሆን የዚያን መንግሥት ጉዳዮች እዚህ ምድር ላይ በታማኝነት ያካሄዳሉ። — ማቴዎስ 24:45–47

8, 9. (ሀ) መንግሥቱ የትኞቹን የሚከፋፍሉና የሚያበላሹ ኃይሎች ያስወግዳል? (ለ) እንግዲያው የአምላክ መንግሥት ጠላቶች እንዳንሆን ከፈለግን ከየትኞቹ ድርጅቶችና ድርጊቶች መራቅ አለብን?

8 ይሖዋ የወሰነው ጊዜ በቅርቡ ሲመጣ አጥፊ ኃይሎቹ ምድርን ለማጽዳት እርምጃ ይወስዳሉ። እነርሱም የአምላክን ሉዓላዊነት ለመቀበል አሻፈረን በማለት በራሳቸው ምርጫ አምላክን ያላወቁትንና ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ያደረገልንን ፍቅራዊ ዝግጅቶች የናቁትን ሁሉ ለዘላለም ያጠፋሉ። (2 ተሰሎንቄ 1:6–9) ያ ቀን የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበት ለረጅም ዘመን ሲጠበቅ የኖረው የይሖዋ ቀን ነው።

9 በዓይን የማይታየው ክፉው የዚህ ዓለም ገዥ በፈለገው መንገድ የሚያሽከረክራቸው የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ፣ ሰብዓዊ መንግሥታትና ሠራዊታቸው በሙሉ ለዘላለም ይወድማሉ። ራስ ወዳድነት፣ ውሸትና ስነ ምግባር የጎደለው ኑሮ በመከተል የዓለም ክፍል መሆናቸውን የሚያሳዩ ሁሉ ከምድር ገጽ ይጠረጋሉ። ሰይጣንና አጋንንቱ ለአንድ ሺህ ዓመት በጽኑ ታሥረው ከምድር ነዋሪዎች ጋር እንዳይገናኙ ይደረጋል። ይህ ለውጥ ጽድቅን ለሚያፈቅሩ ሁሉ እንዴት ያለ ግልግል ይሆንላቸዋል! — ራእይ 18:21, 24፤ 19:11–16, 19–21፤ 20:1, 2

መንግሥቱ ዓላማዎቹን የሚፈጽመው እንዴት ነው?

10. (ሀ) መሲሐዊው መንግሥት ይሖዋ ለምድር ያለውን ዓላማ የሚፈጽመው እንዴት ነው? (ለ) ይህስ በዚያን ጊዜ በምድር ለሚኖሩት ምን ትርጉም ይኖረዋል?

10 ይህ መሲሐዊ መንግሥት አምላክ ለምድር የነበረውን የመጀመሪያውን ዓላማ ሙሉ በሙሉ ይፈጽማል። (ዘፍጥረት 2:8, 9, 15፤ 1:28) እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ሰው ይህንን ዓላማ ለማከናወን አልቻለም። ወደፊት የምትኖረው በሰዎች የተሞላች ምድር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር የምትገዛ ትሆናለች። ይሖዋ ይህንን አሮጌ ሥርዓት ሲደመስሰው ከጥፋቱ የሚተርፉት በሙሉ በኅብረት ክርስቶስን እንደ ንጉሣቸው አድርገው በመቀበል መመሪያውን በደስታ እየተከተሉ ምድርን ከዳር እስከ ዳር ገነት ያደርጓታል። (ዕብራውያን 2:5–9) የሰው ልጆች በሙሉ በእጃቸው ሥራ ይደሰታሉ፤ ከተትረፈረፈው የምድር ፍሬ ሁሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ። — መዝሙር 72:1, 7, 8, 16–19፤ ከኢሳይያስ 65:21, 22 ጋር አወዳድር።

11. (ሀ) ለመንግሥቱ ተገዥዎች የአእምሮና የአካል ፍጽምና የሚመጣላቸው እንዴት ነው? (ለ) ይህስ ምን ምን ለውጦችን ይጨምራል?

11 አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ ፍጹማን ነበሩ። ምድር የአእምሮና የአካል ፍጽምና ባላቸው ዘሮቻቸው እንድትሞላ የአምላክ ዓላማ ነበር። በመንግሥቱ ግዛት ውስጥ ይህ ዓላማ ክብራማ ፍጻሜውን ያገኛል። ይህ እንዲሆን ግን የኃጢአት ውጤቶች በሙሉ መደምሰስ ይኖርባቸዋል። ለዚህ ሲባል ኢየሱስ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ሊቀ ካህንም ጭምር ሆኖ ያገለግላል። ታዛዥ ተገዢዎቹ ኃጢአትን ከሚያስተሰርየው የሰብዓዊ ሕይወቱ መስዋዕትነት እንዲጠቀሙ ኢየሱስ በትዕግሥት ይረዳቸዋል። የታወሩ ዓይኖች ይገለጣሉ፣ የማይሰሙ ጆሮዎች ይከፈታሉ፣ በእርጅና ወይም በሕመም ምክንያት ቅርጹን የለወጠ አካል ከሕፃን አካል የበለጠ ለጋ ይሆናል። አሁን ፈውስ የሌላቸው የአካል ጉድለቶች ቦታውን ለተሟላ ጤንነት ይለቃሉ። ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች በሙሉ ከኃጢአትና ኀዘንን ከሚያመጡ ውጤቶቹ ስለሚላቀቁ ማንም ሰው ታምሜአለሁ ለማለት ምክንያት አያገኝም። — ከኢሳይያስ 33:22, 24፤ 35:5, 6፤ ከኢዮብ 33:25​ና ከሉቃስ 13:11–13 ጋር አወዳድር።

12. (ሀ) ሰብዓዊ ፍጽምና ላይ ለመድርስ የሚያስፈልገው ሌላው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ይህስ የሚገኘው እንዴት ነው? ከእርሱስ ምን ውጤት ይገኛል?

12 ይሁን እንጂ ወደ ፍጽምና መድረስ ሲባል ጤናማ አካልና አእምሮ ማግኘት ማለት ብቻ አይደለም። የይሖዋን ባሕርያት በትክክል ማንጸባረቅንም ይጨምራል፤ ምክንያቱም ሰው የተፈጠረው ‘በአምላክ መልክ እንደ ምሳሌው’ ነው። (ዘፍጥረት 1:26) ይህም ከፍተኛ የትምህርት ዘመቻ ማካሄድን የሚጠይቅ ይሆናል። ጊዜው “ጽድቅ የሚኖርበት” የአዲስ ሥርዓት ጊዜ ይሆናል። በዚህ ምክንያት ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው “በዓለም የሚኖሩ ጽድቅን ይማራሉ።” (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ኢሳይያስ 26:9) ይህ የጽድቅ ባሕርይ ወደ ሰላም የሚመራ ስለሆነ በሁሉም ሕዝቦች፣ አብረው በሚኖሩና በሚውሉ፣ በቤተሰብ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአምላክና በሰው መካከል ሰላም ይኖራል። (ኢሳይያስ 32:17፤ መዝሙር 85:10–13) ጽድቅን የሚማሩ ሁሉ አምላክ ለእነርሱ ያለውን ፈቃድ እንዲያውቁ ደረጃ በደረጃ ትምህርት ይሰጣቸዋል። ለአምላክ መንግሥት ያላቸው ፍቅር ወደ ልባቸው ጠልቆ ሲገባ በማንኛውም አኗኗራቸው እነዚህን መንገዶች ይከተላሉ። ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ‘አባቴ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁ’ ብሏል። (ዮሐንስ 8:29) የሰው ልጆች በሙሉ እንደዚያ ለማለት የሚበቁበት ጊዜ ሲመጣ ሕይወት እንዴት አስደሳች ይሆናል!

አሁንም ቢሆን የሚታዩ ክንዋኔዎች

13. ከላይ ባሉት ጥያቄዎች ተጠቅመህ የመንግሥቱን ክንዋኔዎችና እኛም በዚያ ምክንያት ምን ማድረግ እንዳለብን ጎላ አድርገህ ግለጽ።

13 የእምነት ዓይኖች ላሏቸው ሁሉ የመንግሥቱ ታላላቅ ክንዋኔዎች አሁንም በግልጽ ይታያሉ። ከዚህ ቀጥሎ ያሉት ጥያቄዎችና ጥቅሶች ከእነርሱ መሀል አንዳንዶቹን ያስታውሱሃል። በተጨማሪም የመንግሥቱ ተገዥዎች በሙሉ በአሁኑ ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚችሉና እንደሚገባቸው ያስገነዝቡሃል:-

ንጉሡ በመጀመሪያ እርምጃ የወሰደው በማን ላይ ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ? (ራእይ 12:7–10, 12)

ክርስቶስ በዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ ወዲያው ትኩረት የተሰጠው የየትኛውን ቡድን የመጨሻ አባላት ለመሰብሰቡ ሥራ ነው? (ማቴዎስ 24:31፤ ራእይ 7:1–4)

ኢየሱስ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠ በኋላ፣ ነገር ግን ክፉዎችን ከማጥፋቱ በፊት ምን ሌላ ሥራ እንደሚያከናውን ነው በማቴዎስ 25:31–33 ላይ የተናገረው?

ይህ ሥራ የሚከናወነው እንዴት ነው? በሥራው የሚሳተፉትስ እነማን ናቸው? (ማቴዎስ 24:14፤ መዝሙር 110:3 አዓት፤ ራእይ 14:6, 7)

ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎች ሥራውን ለማቆም ያልቻሉት ለምንድን ነው? (ሥራ 5:38, 39፤ ዘካርያስ 4:6)

የአምላክን መንግሥት አገዛዝ የተቀበሉ ሰዎች አሁን እየተሰጠ ባለው ትምህርት ምክንያት በሕይወታቸው ውስጥ ምን ምን ለውጦች አድርገዋል? (ኢሳይያስ 2:4፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9–11)

የመንግሥቱ ጥንካሬ

14. (ሀ) ክርስቶስ ለምን ያህል ጊዜ ይገዛል? (ለ) በዚያ ጊዜ ውስጥ ምን ይከናወናል?

14 ሰይጣንና አጋንንቱ ከታሠሩ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስና 144, 000ዎቹ ለአንድ ሺህ ዓመት ይገዛሉ። (ራእይ 20:6) በዚያን ጊዜ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ ይደረጋል። ይሖዋን የሚቃወም መንግሥትም ሆነ ሥልጣን ወይም ኃይል ሁሉ ይወገዳል። ይህ ከተከናወነ በኋላ “እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ” ኢየሱስ መንግሥቱን ለአባቱ መልሶ ይሰጣል። — 1 ቆሮንቶስ 15:24, 28

15. ይህ መንግሥት ፈጽሞ አይፈርስም የሚለው አባባል ትክክል የሚሆነው እንዴት ነው?

15 ስለዚህ ኢየሱስ ከምድር ጋር በተያያዘ ሁኔታ የነበረው ቦታ ወይም ሥልጣን ይለወጣል። ሆኖም “ግዛቱ ለዘላለም” “መንግሥቱም የማይፈርስ” ይሆናል። (ዳንኤል 7:14) ይህ ምን ማለት ነው? ከዚያ በኋላ የመግዛቱ ሥልጣን የተለየ ዓላማ ላላቸው ለሌሎች አይሰጥም። መንግሥቱ የሚያከናውናቸው ነገሮች ለዘላለም አይፈርሱም። መንግሥቱ የይሖዋን ስም ከስድብ ሁሉ ነጻ አድርጎ ይሖዋ ለምድር የነበረውን ዓላማ ለማስፈጸም ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

የክለሳ ውይይት

● ለሰው ልጆች ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ የአምላክ መንግሥት የሆነው ለምንድን ነው? መንግሥቱስ መቼ መግዛት ጀመረ?

● የአምላክን መንግሥትና ይህ መንግሥት የሚያከናውነውን በሚመለከት በተለይ አንተን የሚማርክህ ምንድን ነው? ለምንስ

● አሁንም ቢሆን የትኞቹን የመንግሥቱን ክንውኖች ለማየት እንችላለን? እኛስ በእነርሱ ረገድ ምን ድርሻ እናበረክታለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 84, 85 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕዝቦች ጽድቅን ይማራሉ