በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትንሣኤ ተስፋ የሚሰጠው ብርታት

የትንሣኤ ተስፋ የሚሰጠው ብርታት

ምዕራፍ 9

የትንሣኤ ተስፋ የሚሰጠው ብርታት

1. ትንሣኤ ምን አስደናቂ አጋጣሚዎችን ይከፍትልናል?

ትንሣኤ ከሌለ የሞቱት የሰው ልጆች ወደፊት በሕይወት የመኖር ተስፋ አይኖራቸውም። ይሖዋ ግን ይገባናል በማንለው ደግነቱ ተገፋፍቶ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሙታን ዋጋ ሊተመንለት የማይችለውን የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ዕድል ከፍቶላቸዋል። ከዚህ የተነሳ በሞት ካንቀላፉት ውድ ዘመዶቻችን ጋር እንደገና እንደምንገናኝ የሚያረጋግጥ ልብን በደስታ ሞቅ የሚያደርግ ተስፋ አለን። — ከማርቆስ 5:35, 41, 42​ና፤ ከሥራ 9:36–41 ጋር አወዳድር።

2. (ሀ) ትንሣኤ የይሖዋን ዓላማ ለማስፈጸም በጣም አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው በምን መንገዶች ነው? (ለ) የትንሣኤ ተስፋ ትልቅ የብርታት ምንጭ የሚሆንልን በተለይ በምን ጊዜ ነው?

2 የትንሣኤ ተስፋ በመኖሩ ሰይጣን “ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል” የሚለውን ተንኮል ያዘለ ክርክሩን ለማረጋገጥ እስከ መጨረሻው ድረስ እንዲሞክር ይሖዋ ሊፈቅድለት ይችላል። ሆኖም ሰይጣን በታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ላይ ዘላለማዊ ጉዳት ማምጣት አይችልም። (ኢዮብ 2:4) ኢየሱስ ከሞት ስለተነሳ የሰብዓዊ መስዋዕቱን ዋጋ በአባቱ ሰማያዊ ዙፋን ፊት ለማቅረብ ችሏል። ይህም ሕይወት አድን የሆነ ጥቅም አምጥቶልናል። ከክርስቶስ ጋር የሚወርሱት ክርስቲያኖች በትንሣኤ አማካኝነት በሰማያዊ መንግሥት ከእርሱ ጋር ይሆናሉ። በተጨማሪም ከሞት ጋር ፊት ለፊት የሚያገናኙ ፈተናዎች ሲመጡብን እምነት ላለን ሁሉ የትንሣኤ ተስፋ ከወትሮው የበለጠ ብርታት ይሰጠናል።

ለክርስትና እምነት መሠረታዊ ነገር ለምን ሆነ?

3. (ሀ) ትንሣኤ ‘ከመጀመሪያ ትምህርቶች’ አንዱ የሆነው በምን መንገድ ነው? (ለ) ዓለም በአጠቃላይ ለትንሣኤ ምን አመለካከት አለው?

3 በዕብራውያን 6:1, 2 ላይ እንደተገለጸው ትንሣኤ ‘ከመጀመሪያ ትምህርቶች’ ወይም ከእምነት መሠረቶች አንዱ ነው። ማንኛችንም ያለዚህ መሠረት የጎለመስን ክርስቲያኖች ለመሆን አንችልም። ሆኖም ትንሣኤ ከአጠቃላዩ የዓለም ሐሳብ ውጭ የሆነ ነገር ነው። መንፈሳዊነት ስለሚጐድላቸው ደስታን ብቻ እያሳደዱ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እየበዛ ሄዷል። እውን ሆኖ የሚታያቸው የአሁኑ ሕይወት ብቻ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:32) በሕዝበ ክርስትና ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጭ ያሉትን እንደ ባሕል ሆነው የተወረሱ ሃይማኖቶች የሚከተሉ ሰዎች የማትሞት ነፍስ አለችን ብለው ያስባሉ። እንደ አባባላቸው ከሆነ ትንሣኤ አያስፈልግም። እነዚህን ሁለት ሐሳቦች ለማስታረቅ የሚሞክሩ ሁሉ ነገሩ ተስፋ የሚያሳድር ሳይሆን የበለጠ ግራ የሚያጋባ ሆኖ ያገኙታል። ታዲያ ለመስማት ፈቃደኛ የሆኑትን እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን? — ሥራ 17:32

4. (ሀ) አንድ ሰው የትንሣኤ ተስፋ እንዲገባው ከተፈለገ በመጀመሪያ ምን እንድንገልጽለት ሊያስፈልግ ይችላል? (ለ) ነፍስ ምን እንደሆነችና ሙታን በምን ሁኔታ እንደሚገኙ ለማስረዳት በየትኞቹ ጥቅሶች ትጠቀማለህ? (ሐ) ሰውየው በእነዚያ ጥቅሶች ውስጥ ያለውን ትክክለኛ ሐሳብ በሚሰውር የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ቢጠቀም ምን ታደርጋለህ?

4 እንደነዚህ ያሉት ሰዎች አስደናቂው ትንሣኤ እንዴት ያለ ግሩም ዝግጅት እንደሆነ እንዲገነዘቡ ከተፈለገ በመጀመሪያ ነፍስ ምን እንደሆነችና ሙታን በምን ሁኔታ እንደሚገኙ መረዳት ያስፈልጋቸዋል። እውነትን ለተራበ ሰው እነዚህን ነገሮች ግልጽ ለማድረግ ብዙውን ጊዜ ጥቂት ጥቅሶች ይበቃሉ። (ዘፍጥረት 2:7፤ ሕዝቅኤል 18:4፤ መዝሙር 146:3, 4) ሆኖም አንዳንድ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችና ሰው እንዲገባው ተብሎ በቀላል አባባል የተዘጋጁ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች እነዚህን እውነቶች ይሰውራሉ። ስለዚህ ጥቅሶቹ በበኩረ ጽሑፉ ምን ይሉ እንደነበረ ማስረዳት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

5. እንደዚህ ያለው ሰው ነፍስ ምን እንደሆነች እንዴት ልታስረዳው ትችላለህ?

5 አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ለዚህ ዓላማ በጣም ይረዳል፤ ምክንያቱም ነፈሽ የሚለውን የዕብራይስጥ ቃልና ፕስሂ የሚለውን ተመሳሳዩን ግሪክኛ ቃል በሁሉም ስፍራዎች ላይ “ነፍስ” ብሎ ይተረጉማቸዋል። በመጨረሻው አካባቢ ባለው ቅጣይ ማብራርያ ላይም እነዚህ ቃላት የሚገኙባቸው ጥቅሶች ሁሉ ተዘርዝረዋል። ሌሎቹ ዘመናውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እነዚህን በበኩረ ጽሑፉ ላይ ያሉ ቃላት “ነፍስ” ብቻ ሳይሆን “ፍጡር” “ሰው” እና “ሕይወት” እያሉ ተርጉመዋቸዋል። “የእኔ ነፈሽ ” የሚለውን ሐረግ “እኔ”፤ “የአንተ ነፈሽ ” የሚለውን ደግሞ “አንተ“ ብለው ተርጉመውታል። ቅን ልብ ያለው ተማሪ እነዚህን መጽሐፍ ቅዱሶች ቀደም ብለው ከነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ወይም ከአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ጋር ቢያወዳድር “ነፍስ” ተብለው የተተረጐሙት ዕብራይስጥና ግሪክኛ ቃላት (1) ሰዎችን (2) እንስሳትን (3) የሰውንና የእንስሳትን ሕይወት እንደሚያመለክቱ ይገነዘባል። ቃሎቹ ነፍስ በዓይን የማትታይና የማትጨበጥ እንዲሁም በሞት ጊዜ ከሥጋ ተለይታ በሌላ ስፍራ ሕያው ሆና የምትኖር ነገር ናት የሚል ሐሳብ አያስተላልፉም።

6. (ሀ) አንዳንድ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ሲኦል፣ ሔድስና ገሃነም ምን ስለመሆናቸው አንባቢውን የሚያደናግሩት ለምንድን ነው? (ለ) በሲኦልና በገሃነም ውስጥ ያሉት ሙታን ሁኔታ ምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ልታስረዳ ትችላለህ?

6 በተመሳሳይም አዲሲቱ ዓለም ትርጉም በሁሉም ስፍራ ላይ ሺኦል የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል በቀጥታ ሲኦል ብሎ ይተረጉመዋል፣ ሔድስ እና ጊኤና የሚሉትን ግሪክኛ ቃላት ደግሞ ሔድስ እና ጊሄና (ገሃነም) በማለት በቀጥታ ያስቀምጣቸዋል። ሌሎቹ ዘመናውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችና ሰው እንዲገባው ተብሎ በቀላል አነጋገር የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶች ግን ሔድስ እና ጊኤና የሚሉትን ሁለቱንም ቃላት ሲኦል (ወይም በእንግሊዝኛ ሄል) ብለው ይተረጉሟቸዋል። አንዳንድ ጊዜም ሺኦል እና ሔድስን “መቃብር” “የሙታን ዓለም” እያሉ ይተረጉሟቸዋል። አስፈላጊ ከሆነ ልዩ ልዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን በማስተያየት ሺኦልና ሔድስ ትርጉማቸው አንድ መሆኑን ማስረዳት ይቻላል። (መዝሙር 16:10፤ ሥራ 2:27) የሰው ልጆች ተራ መቃብር የሆነው ሲኦል ወይም ሔድስ የሙታን እንጂ የሕያዋን ስፍራ እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። (መዝሙር 89:48፤ ራእይ 20:13) ከዚህም ሌላ በትንሣኤ አማካኝነት ከሲኦል የመውጣት ተስፋ መኖሩን ይገልጽልናል። (ኢዮብ 14:13፤ ሥራ 2:31) ወደ ገሃነም ለሚሄዱት ግን እንደዚህ ያለ ወደፊት የመኖር ተስፋ አልተሰጠም። ከዚህም ሌላ በዚያ ውስጥ ነፍስ ሕያው ሆና ትኖራለች የሚል ጥቅስ የለም። — ማቴዎስ 18:9፤ 10:28

7. አንድ ሰው የትንሣኤ ተስፋ በትክክል ከገባው አስተሳሰቡና ድርጊቶቹ እንዴት ይለወጣሉ?

7 እነዚህን ነገሮች በዚህ መንገድ ግልጽ ካደረግንላቸው የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ለሰዎች ትርጉም ያላቸው ይሆኑላቸዋል። ከዚያ በኋላ የትንሣኤ ተስፋ ለራሳቸው ምን ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል ልናስረዳቸው እንችላለን። እነርሱም ይሖዋ እንደዚህ ያለ አስደናቂ ዝግጅት በማድረግ ያሳየውን ፍቅር ማድነቅ ሊጀምሩ ይችላሉ። በጣም የሚወዱት የቅርብ ዘመድ የሞተባቸው ሰዎች ከዚህ በኋላ ኀዘናቸው ጠፍቶ ከሟቹ ጋር በአዲሱ የአምላክ ሥርዓት ውስጥ እንደገና የሚገናኙበትን ጊዜ በደስታ መጠባበቅ ሊጀምሩ ይችላሉ። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የኢየሱስ ትንሣኤ ለክርስትና እምነት እንደ ማዕዘን ድንጋይ ያህል መሆኑን ተገንዝበው ነበር። ስለዚሁ ትንሣኤና እርሱ ምን ሊያመጣላቸው እንደሚችል ለሌሎች በቅንዓት መስክረዋል። ዛሬም ይህንን ውድ እውነት የሚያደንቁ ሁሉ ለሌሎች ሊያካፍሉት ይጓጓሉ። — ሥራ 5:30–32፤ 10:40–43፤ 13:32–39፤ 17:31

‘በሔድስ መክፈቻዎች’ መጠቀም

8. ኢየሱስ ‘በሞትና በሔድስ መክፈቻዎች’ መጠቀሙ በመንፈስ ለተቀቡት ተከታዮቹ ምን ትርጉም ይኖረዋል?

8 የሰማያዊው መንግሥት አባላት በመሆን ከክርስቶስ ጋር የሚኖሩት ሁሉ ወደ ሰማይ ከመሄዳቸው በፊት መሞት አለባቸው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለሐዋርያው ዮሐንስ “ሞቼም ነበርሁ እነሆም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፣ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ” ሲል የሰጠውን አስተማማኝ ተስፋ ያውቃሉ። (ራእይ 1:18) ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? በራሱ ላይ የደረሰውን ሁኔታ መጥቀሱ ነበር። እርሱም ሞቶ ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ በሔድስ ወስጥ አልተወውም። በሦስተኛው ቀን ይሖዋ ራሱ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት አስነስቶ ያለመሞትን ባሕርይ አለበሰው። ይህ ብቻ አይደለም። የሰውን ልጆች ከጋራ መቃብራቸው ለማስለቀቅና የአዳም ኃጢአት ካመጣባቸው ውጤቶች ለማዳን እንዲጠቀምባቸው ይሖዋ “የሞትና የሲኦል መክፈቻ” ሰጥቶታል። ኢየሱስ እነዚያን መክፈቻዎች ስለያዘ ታማኝ ተከታዮቹን ከሞት ሊያስነሳቸው ይችላል። ይህንን በሚያደርግበት ጊዜ አባቱ ለእርሱ እንዳደረገለት እርሱም በመንፈስ ለተቀቡት የጉባኤው አባሎች ውድ ስጦታ የሆነውን፣ ሊጠፋም ከቶ የማይችለውን ሰማያዊ ሕይወት ይሰጣቸዋል። — ሮሜ 6:5፤ ፊልጵስዩስ 3:20, 21

9. የታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ትንሣኤ መጀመር ያለበት መቼ ነው?

9 ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይህንን ትንሣኤ የሚያገኙት መቼ ነው? ትንሣኤያቸው አሁንም ጀምሯል። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በክርስቶስ መገኘት’ ወቅት እንደሚነሱ ተናግሮ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:23) መገኘቱ የጀመረው በ1914 ነው። በአሁኑ ጊዜ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምድራዊ ጉዞአቸውን ሲጨርሱ ጌታቸው እስኪመለስ ድረስ ሞተው መጠበቅ አያስፈልጋቸውም። ሲሞቱ “በድንገት በቅጽበተ ዓይን” ተለውጠው ወዲያው መንፈሳውያን ሆነው ይነሳሉ። ‘ሥራቸው ተከትሏቸው ስለሚሄድ’ እንዴት ደስ ይላቸዋል! — 1 ቆሮንቶስ 15:51, 52፤ ራእይ 14:13

10. ምን ሌላ ትንሣኤ ይኖራል? እርሱስ መቼ ይጀምራል?

10 ይሁን እንጂ ትንሣኤ የሚያገኙት እነርሱ ብቻ አይደሉም። ትንሣኤያቸው “የመጀመሪያው ትንሣኤ” ተብሎ መጠራቱ ከእርሱ ቀጥሎ ሌላ ትንሣኤ እንደሚከናወን ያመለክታል። (ራእይ 20:6) ሁለተኛውን ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ አስደሳቹን የዘላለም ሕይወት የማግኘት ዕድል አላቸው። ታዲያ ይህ ትንሣኤ የሚከናወነው መቼ ነው? የአሁኑ ክፉ ሥርዓት ክፍል የሆኑት “ምድርና ሰማይ” ከጠፉ በኋላ መሆኑን የራእይ መጽሐፍ ያስረዳል። ይህ አሮጌ ሥርዓት የሚጠፋበት ጊዜ በጣም ቅርብ ነው። ከዚያ በኋላ አምላክ በወሰነው ጊዜ ምድራዊው ትንሣኤ ይጀምራል። — ራእይ 20:11, 12

11. በምድር ላይ ለሚኖረው ሕይወት ከሚነሱት ታማኝ ሰዎች መካከል እነማን ይገኛሉ? ያ ጊዜ በጣም አስደሳች የሚሆነው ለምንድን ነው?

11 ከሚነሱት መካከል እነማን ይገኛሉ? ከጥንት ጀምሮ የነበሩት ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ይነሳሉ። ከመካከላቸውም በትንሣኤ ላይ በነበራቸው ጽኑ እምነት የተነሳ “መዳንን ሳይቀበሉ” ማለትም መገደልን ለማስቀረት ሲሉ ተስማምተው በመኖር ፋንታ አቋማችንን አንለቅም ብለው የጸኑት ሰዎች ይገኙበታል። (ዕብራውያን 11:35) ከእነርሱ ጋር በግል መተዋወቅና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባጭሩ ብቻ የተወሳውን ታሪካቸው በዝርዝር ከራሳቸው አፍ መስማት እንዴት ደስ ይላል! ከእነርሱ መካከል የመጀመሪያው ታማኝ የይሖዋ ምሥክር አቤል ይገኝበታል። ከጥፋት ውሃ በፊት የአምላክን ማስጠንቀቂያ ያለ ፍርሐት ያወጁት ሔኖክና ኖህም አሉ። መላእክትን ያስተናገደው አብርሃምም አለ። ሕጉን በሲና ተራራ ተቀብሎ ለእሥራኤላውያን ያስተላለፈው ሙሴም አንዱ ነው። ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት በ607 ኢየሩሳሌም ስትጠፋ በዓይኑ እንደተመለከተው እንደ ኤርምያስ ያሉ ደፋር ነቢያትም ይነሳሉ። አምላክ ራሱ ኢየሱስ ልጄ ነው ብሎ ሲናገር የሰማው መጥምቁ ዮሐንስም ሌላው ነው። በአሁኑ ሥርዓት መጨረሻ ቀኖች ውስጥ የሞቱት ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም አሉ። — ዕብራውያን 11:4–38፤ ማቴዎስ 11:11

12. (ሀ) በሲኦል ካሉት ሙታን መካከል ስንቶቹ ይነሳሉ? (ለ) እንግዲያው እነማን ጭምር ይነሣሉ ማለት ነው? ለምንስ?

12 ከጊዜ በኋላ ሌሎችም ይነሳሉ። ኢየሱስ የሰውን ልጆች ለማስነሳት “የሲኦልን መክፈቻዎች” እስከ ምን ድረስ እንደሚጠቀምባቸው ለሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ተገለጾለታል። ዮሐንስ ሔድስ ወደ እሳት ባሕር ሲጣል ተመልክቷል። ይህ ምን ማለት ነው? ባዶ ስለሚሆን ጨርሶ ይጠፋል ወይም አይኖርም ማለት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ከታማኝ የይሖዋ አምላኪዎች በተጨማሪ ኃጢአተኞችንም ከሔድስ ወይም ከሲኦል በምሕረት ያወጣቸዋል። እነዚህ ሰዎች የሚነሱት እንዲፈረድባቸውና እንዲሞቱ አይደለም። በአምላክ መንግሥት አማካኝነት በሚሰፍነው አዲስና ጻድቅ ሥርዓት ውስጥ አኗኗራቸውን ከይሖዋ መንገዶች ጋር እንዲያስማሙ እርዳታ ይደረግላቸዋል። ራእዩ “የሕይወት መጽሐፍ” ሲከፈት አሳይቷል። እንግዲህ የእነርሱም ስም በመጽሐፉ ላይ እንዲመዘገብ አጋጣሚ ይኖራቸዋል። እያንዳንዳቸው ከትንሣኤያቸው በኋላ በሚያደርጉት መሠረት ፍርድ ያገኛሉ። (ራእይ 20:12–14፤ ሥራ 24:15) ከመጨረሻው ውጤቱ አንጻር ሲታይ ትንሣኤያቸው “የሕይወት ትንሣኤ” ሊሆንላቸው ይችላል። አማራጭ የሌለው የጥፋት ፍርድ የሚያመጣ ትንሣኤ አይሆንባቸውም። — ዮሐንስ 5:28, 29

13. (ሀ) እነማን አይነሱም? (ለ) ስለ ትንሣኤ እውነቱን ማወቃችን ሕይወታችንን እንዴት ሊነካው ይገባል?

13 ይሁን እንጂ በሕይወት የኖሩ በሙሉ ይነሣሉ ማለት አይደለም። አንዳንዶች ይቅርታ የማይደረግለት ኃጢአት ሠርተዋል። በቅርቡ በሚመጣው “ታላቅ መከራ” ወቅት እንዲጠፉ የሚፈረድባቸው ሁሉ ለዘላለም ሞተው ከሚቀሩት መካከል ይሆናሉ። (ማቴዎስ 12:31, 32፤ 23:33፤ 24:21, 22፤ 25:41, 46፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6–9) እንግዲያው ምንም እንኳን በሔድስ ያሉት በሙሉ ከዚያ እንዲወጡ ልዩ ምሕረት ቢደረግም ትንሣኤ በአሁኑ ጊዜ እንደፈለግነው ለመኖር ያስችለናል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ላደረገልን ለዚህ የማይገባ ደግነት የጠለቀ አድናቆት እንድናሳይ ሊገፋፋን ይገባል።

በትንሣኤ ተስፋ መበርታት

14. ወደ አሁኑ ሕይወት ፍጻሜ ለቀረበ ሰው ትንሣኤ ትልቅ የብርታት ምንጭ የሚሆንለት እንዴት ነው?

14 የትንሣኤን ተስፋ ተቀብለው የተማመኑበት ሁሉ ትልቅ ብርታት ይሰጣቸዋል። ወደ ሕይወታቸው ፍጻሜ ሲደርሱ ምንም ዓይነት ሕክምና ቢደረግላቸው ሞትን ለሌላ ጊዜ እያስተላለፉት መቀጠል እንደማይችሉ ያውቃሉ። (መክብብ 8:8) በጌታ ሥራ በትጋት ሲሳተፉና ከይሖዋ ድርጅት ጋር በታማኝነት ሲያገለግሉ ከነበረ የወደፊቱን ጊዜ በሙሉ ዋስትና ሊጠብቁት ይችላሉ። አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በትንሣኤ አማካኝነት እንደገና ሕያው እንደሚሆኑ ያውቃሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “እውነተኛ ሕይወት” ብሎ የሚጠራው የዚያን ጊዜው ሕይወት እንዴት አስደናቂ ይሆናል! — 1 ጢሞቴዎስ 6:19፤ 1 ቆሮንቶስ 15:58፤ ዕብራውያን 6:10–12

15. ኃይል ተጠቅመው ለመጉዳት የሚፈልጉ አሳዳጆች እንገድላችኋለን ብለው ቢዝቱ ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት እንድንጠብቅ ምን ሊረዳን ይችላል?

15 ሊያበረታን የሚችለው ትንሣኤ እንደሚኖር መገንዘባችን ብቻ ሳይሆን በተለይ የዚህ ዝግጅት ምንጭ የሆነውን አምላክ ማወቃችን ነው። ይህ እውቀት ኃይል ተጠቅመው ለመጉዳት የሚፈልጉ አሳዳጆች እኛን ለመግደል ሲዝቱ ለአምላክ ታማኝ ሆነን እንድንቆም ያበረታናል። ሰይጣን አለጊዜው የመሞትን ፍርሃት ሰዎችን በባርነት ቀንበር ለመያዝ እንደ መሣሪያው አድርጎ ለብዙ ዘመናት ሲጠቀምበት ቆይቷል። ኢየሱስ ግን ለዚህ ዓይነቱ ፍርሃት አልተንበረከከም። እስከ ሞት ድረስ ለይሖዋ በታማኝነት ቆሟል። የእርሱ ሞት ያስገኘው ውጤት ሰዎችን ከእንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት ነፃ ሊያወጣቸው ችሏል። (ዕብራውያን 2:14, 15) እውነተኛ ተከታዮቹ በዚያ ዝግጅት ላይ ባላቸው እምነት ምክንያት አስደናቂ የአቋም ጽኑነት በማሳየት ጥሩ ታሪክ አስመዝግበዋል። ተጽዕኖ ሲመጣባቸው ‘ነፍሳቸውን ከይሖዋ አስበልጠው እንደማይወዱ’ አስመስክረዋል። (ራእይ 12:11) የክርስትናን መሠረታዊ ሥርዓቶች ትተው የአሁኑን ሕይወታቸውን ለማዳን አይሞክሩም። እንደዚያ ማድረግ ማለት የዘላለም ሕይወትን ተስፋ ማጣት ማለት ነው። (ሉቃስ 9:24, 25) ታዲያ አንተስ ይህ ዓይነት እምነት አለህን? ይሖዋን በእውነት የምትወድና የትንሣኤን ተስፋ ከልብ ተቀብለህ የምትኖር ከሆነ ይህ እምነት ይኖርሃል።

የክለሳ ውይይት

● አንድ ሰው የትንሣኤ ተስፋ እንዲገባው ከተፈለገ በመጀመሪያ ነፍስ ምን እንደሆነችና ሙታን በምን ሁኔታ እንደሚገኙ ማወቅ ያለበት ለምንድን ነው?

● ከሞት የሚመለሱት እነማን ናቸው? ይህ ዕውቀት እንዴት ሊነካን ይገባል?

● የትንሣኤ ተስፋ የሚያበረታን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]