በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምልኮ አንድነት ለአንተ ምን ትርጉም ሊኖረው ይገባል?

የአምልኮ አንድነት ለአንተ ምን ትርጉም ሊኖረው ይገባል?

ምዕራፍ 1

የአምልኮ አንድነት ለአንተ ምን ትርጉም ሊኖረው ይገባል?

1, 2. (ሀ) በዘመናችን እውነተኛ የአምልኮ አንድነት እየመጣ ያለው በምን መሠረት ነው? (ለ) በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ያለውን ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል?

በምድር ዙሪያ ወደ አምልኮ አንድነት ለመድረስ የሚደረግ አንድ አስደሳች እንቅስቃሴ አለ። እንቅስቃሴው ከሁሉም ብሔራት፣ ጐሳዎችና ቋንቋዎች ብዙ ሰዎችን እያሰባሰበ ነው። ይህ አንድነት ለስምምነት ተብሎ የልዩ ልዩ እምነቶችን አቋም በማላላት የተገኘ አይደለም። ከአምላክ ቃል ጋር የሚጋጨውን አኗኗር ከመንቀፍ በመቆጠባቸው የተነሳ የመጣ አይደለም። ታዲያ አንድነቱ የምን ውጤት ነው? በፊት የተለያየ አስተሳሰብ የነበራቸው ሰዎች ይሖዋን እንደ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ አድርገው በመቀበላቸውና አኗኗራቸውን ከጽድቅ መንገዶቹ ጋር ለማስማማት ፈቃደኛ በመሆናቸው የተገኘ አንድነት ነው። — ከራእይ 15:3, 4 ጋር አወዳድር።

2 ይህ ሁኔታ የዛሬ 2,700 ዓመት በነቢዩ ሚክያስ የተመዘገበውን ትንቢት ይፈጽማል። ሚክያስ:- “በመጨረሻው ዘመን” የሚሆነውን በማስመልከት “ብዙዎች አሕዛብ ሄደው ኑ፣ ወደ [ይሖዋ (አዓት)] ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፣ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በፍለጋውም እንሄዳለን ይላሉ” በማለት ጽፎ ነበር። (ሚክያስ 4:1, 2) ይህ ነገር ሲፈጸም ትመለከታለህን?

3, 4. (ሀ) “አሕዛብ” ወደ ይሖዋ ቤት እየጐረፉ ያሉት እንዴት ነው? (ለ) ራሳችንን ምን ምን እያልን መጠየቅ አለብን?

3 የአንድ ብሔር “አሕዛብ” በጅምላ ወደ መንፈሣዊው የይሖዋ ቤት በመምጣት ራሳቸውን ለአምልኮ ሲያቀርቡ አናይም። ሆኖም በእነዚህ ብሔራት ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች ወደ ይሖዋ ቤት እየጐረፉ ነው። እነዚህ ሰዎች ስለ ፍቅራዊው የይሖዋ ዓላማና ማራኪ ስለሆኑት ጠባዮቹ ሲማሩ ልባቸው በጥልቅ ይነካል። ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ይሖዋ ምን እንደሚፈልግባቸው ለማወቅ ይጥራሉ። የእምነት ሰው የነበረው ዳዊት:- “አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ” ብሎ ያቀረበውን ዓይነት ጸሎት እነርሱም ያቀርባሉ። — መዝሙር 143:10

4 ይሖዋን በሚያመልከው በዚህ ታላቅ ሕዝብ መሐል ትገኛለህን? ለሚቀርብልህ ትምህርት የምትሰጠው ምላሽ ትምህርቱ የመጣው ከይሖዋ መሆኑን በእርግጥ እንደምታምን ይመሰክራልን? ‘በይሖዋ መንገዶች የምትሄደው’ እስከ ምን ድረስ ነው?

አንድነቱ የሚገኘው እንዴት ነው?

5. (ሀ) የአምልኮ አንድነት በመጨረሻው ወደ ምን ደረጃ ይደርሳል? (ለ) በአሁኑ ጊዜ አንድ ሰው በአስቸኳይ ይሖዋን ማምለክ መጀመር ያለበት ለምንድን ነው? ሌሎችም እንደዚሁ እንዲያደርጉ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?

5 ይሖዋ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡሮች በሙሉ በአምልኮ አንድ እንዲሆኑ፤ አንዳቸውም በሐሰት መንገድ ተሳስተው እንዳይሄዱና የመኖር ትርጉም ጠፍቷቸው እንዳይደናበሩ ለማድረግ ዓላማ አለው። ሕይወት ያለው ሁሉ ብቸኛውን እውነተኛ አምላክ የሚባርክበትን ቀን እንዴት በናፍቆት እንጠብቃለን! (መዝሙር 103:19–22) ነገር ግን ይህ ከመሆኑ በፊት ይሖዋ ከፍጥረታት መካከል አገዛዙን የሚንቁትንና የሌሎችን ሕይወት ከማበላሸት የማይመለሱትን ሁሉ ለይቶ በማጥፋት ፍጥረቱን ማጥራት ይኖርበታል። ሆኖም ወደፊት የሚወስደውን እርምጃ በምሕረቱ አስቀድሞ አስታውቋል። በየትም ስፍራ የሚኖሩ ሰዎች አካሄዳቸውን ለመለወጥ አጋጣሚ አላቸው። ለዚህም ሲባል በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ “የፍርዱ ሰዓት ደርሷልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፣ ሰማይንና ምድርን ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት” የሚል አስቸኳይ ጥሪ እየቀረበ ነው። (ራእይ 14:6, 7) ይህንን ጥሪ ተቀብለሃልን? ተቀብለህ ከሆነ ከይሖዋ ድርጅት ጋር በመተባበር ጥሪውን ሌሎችም እንዲቀበሉት የመርዳት መብት አግኝተሃል ማለት ነው።

6. የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች ከቀሰምን በኋላ ወደ ምን የዕድገት ደረጃ ለመድረስ ከልብ ልንጥር ይገባናል?

6 ‘በይሖዋ እናምናለን፣ በገነትም ለመኖር እንፈልጋለን’ እያሉ የግል ጥቅማቸውን ማሳደድ የሚቀጥሉትን ወደ ድርጅቱ ለማምጣት ይሖዋ ዓላማ የለውም። ይሖዋ ሰዎች ስለ ፈቃዱ ‘ትክክለኛ ዕውቀት’ እንዲያገኙ ይፈልጋል። ይህም በአኗኗራቸው መንፀባረቅ ይኖርበታል። (ቆላስይስ 1:9, 10) አድናቂ የሆኑ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች ከቀሰሙ በኋላ ወደፊት መራመዳቸውን በመቀጠል ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ለመድረስ ይፈልጋሉ። ይሖዋን እንደ ቅርብ ጓደኛ በደንብ ለማወቅ፣ ቃሉን ሰፋና ጠለቅ ባለ መንገድ ለመረዳትና በሕይወታቸው ውስጥ በይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ሊሠሩበት ይፈልጋሉ። ጠባዮቹን በማንፀባረቅና ነገሮችን በእርሱ አመለካከት በማየት እንደ ሰማዩ አባታቸው ለመሆን ይጥራሉ። ይህም ይሖዋ በምድር ላይ ዛሬ በሚያካሄደው ሥራ ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ የሚሳተፉበትን መንገድ ፈልገው እንዲያገኙ ያነሳሳቸዋል። አንተስ እንደዚህ እያደረግህ ነውን? — ኤፌሶን 5:1፤ ዕብራውያን 5:12 እስከ 6:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:15

7. በአሁኑ ጊዜ እውነተኛ አንድነት ያለው እንዴት ነው? ይህስ አንድነት እንዴት ሊመጣ ቻለ?

7 ይሖዋን የሚያገለግሉት ሁሉ አንድነት ያለው ሕዝብ መሆን እንዳለባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። (ኤፌሶን 4:1–3) በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ብንኖርና ከአለፍጽምናችን ጋር ገና እየታገልን ብንሆንም እንደዚህ ያለው አንድነት በዛሬው ጊዜ የግድ መገኘት አለበት። ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ በሙሉ አንድ እንዲሆኑ ወይም እውነተኛ አንድነት ኖሮአቸው እንዲደሰቱ አጥብቆ ጸልዮአል። ይህ ምን ማለት ነው? በመጀመሪያ ከይሖዋና ከልጁ ጋር ጥሩ ዝምድና ይኖራቸዋል ማለት ነው። በተጨማሪም እርስ በርሳቸው ኅብረት ወይም አንድነት ይኖራቸዋል ማለት ነው። (ዮሐንስ 17:20, 21) በይሖዋ “ቤት” ውስጥ የሚሰጣቸውን ትምህርት ስለሚሠሩበት ዛሬ ይህ አንድነት እውን ሊሆን ችሏል።

ምን ነገሮች ለአንድነቱ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ?

8. (ሀ) በግላችን በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመን እኛን የሚነኩንን ጥያቄዎች መልስ ለማወቅ በምንመራመርበት ጊዜ ምን ለማፍራት እንቸላለን? (ለ) ከላይ የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች በመመለስ ለክርስቲያን አንድነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን ነገሮች ግለጽ?

8 ለዚህ አንድነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ አንዳንድ ቁልፍ ሁኔታዎች ከዚህ በታች አንድ በአንድ ተዘርዝረዋል። ከነጥቦቹ በታች ያሉትን ጥያቄዎች ስትመልስ እያንዳንዱ ነጥብ ከይሖዋና ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ያለህን ግንኙነት እንዴት እንደሚነካ ቆም እያልክ አስብ። አውጥተህ እንድታያቸው ከቀረቡት ጥቅሶች ጋር እያገናዘብህ እነዚህን ነጥቦች ጥሩ አድርገህ ብታስብባቸው ወደ አምላክ ያዘነበለ የማሰብ ችሎታና ነገሮችን የማስተዋል ጠባይ ለማፍራት አስተዋጽኦ ያደርግልሃል። እነዚህ የምታፈራቸው ጠባዮች ደግሞ ለሁላችንም የሚያስፈልጉ ናቸው። (ምሳሌ 5:1, 2፤ ፊልጵስዩስ 1:9–11) እንግዲያው እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ መርምራቸው:-

(ሁላችንም ይሖዋን እናመልካለን፤ ምን ነገር ጥሩ ወይም መጥፎ እንደሆነ የሚለካበት የአቋም ደረጃ ለማውጣት ያለውንም መብት እንቀበ⁠ላ⁠ለን።

ቀላል መስሎ ስለሚታየን ስለ አንድ ነገር ይሖዋ የሰጠውን ምክር ሆነ ብለን ብንጥስ ይሖዋ አድራጎቱን እንዴት ይመለከተዋል? (ሉቃስ 16:10፤ ከሚልክያስ 1:6–8 ጋር አወዳድር)

ሁልጊዜ የይሖዋን ትዕዛዞች ባናከብር አድራጐታችን ሌሎችን ይነካልን? (ከሮሜ 5:12፤ ከኢያሱ 7:20–26፤ ከ1 ነገሥት 14:16 ጋር አወዳድር)

(በዓለም ላይ በየትኛውም ስፍራ ብንገኝ የምንመራው በአምላክ ቃል ነው።

ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ እንዲሁ ትክክል መስሎ “የተሰማንን” ማድረጋችን ምን አደጋ አለው? (ኤርምያስ 17:9፤ ምሳሌ 14:12)

ስለ አንዱ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ምን እንደሆነ ካላወቅን ምን ማድረግ አለብን? (ምሳሌ 2:3–5)

(ሁላችንም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ገበታ ይቀርብልናል፤ ከዚህም እንጠቀማለን።

ይሖዋ እኛን በመንፈሣዊ ለመመገብ የሚጠቀምበትን ዝግጅት በአድናቆት የማይቀበሉት እንዴት ባለ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? (ከኢሳይያስ 1:3፤ 9:16፤ 65:14 ጋር አወዳድር)

(መሪያችንና በአምልኮ ወደ ይሖዋ አቅራቢያቸን ኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ ማንም ሌላ ሰው አይደለም።

ማናችንም ብንሆን ከሌሎች እበልጣለሁ ብለን ለማመን በቂ ምክንያት ይኖረናልን? (ሮሜ 3:23, 24፤ 12:3፤ ማቴዎስ 23:8–10)

(በየትም ስፍራ ብንኖር ብቸኛው የሰው ልጆች ተስፋ የአምላክ መንግሥት ነው ብለን እናምናለን።

ይህ አቋም ሰዎችን ከሚከፋፍሉት ኃይሎች የሚጠብቀን እንዴት ነው? (ማቴዎስ 6:9, 10 ሚክያስ 4:3)

(መንፈስ ቅዱስ ይሖዋን በሚያመልኩት ሰዎች ውስጥ ለክርስቲያን አንድነት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ጠባዮችን ያፈራል።

የአምላክ መንፈስ ፍሬውን በእኛ ውስጥ እንዲያፈራ መንገድ የምንከፍትለት እንዴት ነው? (መዝሙር 1:2፤ ምሳሌ 22:4፤ ራእይ 3:6፤ ሥራ 5:32)

የመንፈስ ፍሬዎችን ማፍራታችን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና እንዴት ይነካዋል? ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን ግንኙነትስ? (ገላትያ 5:22, 23)

(ሁላችንም የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበክ ኃላፊነት ተጥሎብናል።

በዚህ የስብከት ሥራ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር አዘውትረን መሳተፋችን ለእነርሱ ያለንን ስሜት እንዴት ይለውጠዋል? (ከቆላስይስ 4:7, 11 ጋር አወዳድር)

9. እነዚህን እውነቶች በሕይወታችን ስንሠራባቸው ውጤቱ ምን ይሆናል?

9 የእነዚህን ነገሮች ትክክለኛነት መቀበል አንድ ነገር ነው። ከእነርሱ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ግን የበለጠ ጥረትን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ እንደዚህ ማድረጋችን ወደ ይሖዋ የበለጠ እንድንቀርብ ይረዳናል። ከዚህም ሌላ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር የምናሳልፈው ጊዜ መንፈሳችንን ያድሰዋል። መዝሙር 133:1 እንደሚለው “ወንድሞች በኅብረት (በአንድነት) ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው፣ እነሆም ያማረ ነው።” በራስ ወዳድነት ከተጥለቀለቀው ዓለም ወጥቶ ይሖዋን ከልብ የሚወዱ ሰዎች በተሰበሰቡበት ስፍራ መገኘቱ ምን ያህል መንፈስን እንደሚያድስ ራስህ ቀምሰኸው የ⁠ለ⁠ምን?

ከሚከፋፍሉ ነገሮች ራቅ

10. በራሴ እመራለሁ የሚለው መንፈስ እንዳያድርብን መጠንቀቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

10 ይህ ውድ አንድነት እንዳይበላሽብን መከፋፈልን ከሚያመጡ ነገሮች መራቅ ይኖርብናል። ከዋና ዋናዎቹ ነገሮች አንዱ በራሴ እመራለሁ የሚለው መንፈስ ነው። ይሖዋ እንደዚህ ያለውን መንፈስ በመጀመሪያ ያመጣው ሰይጣን ዲያብሎስ መሆኑን በማጋለጥ ከዚህ ጠባይ እንድንርቅ ይረዳናል። ሔዋን አምላክ የነገራትን ወደ ጐን ትታ የራሷን ጉዳይ ራሷ ብትወስን እንደሚጠቅማት አድርጋ እንድታስብ ያታለላት ሰይጣን ነው። በዚህ የዓመጽ ጐዳና አዳምም ተባበራት። ይህም በእነርሱና በእኛ ላይ ይህ ነው የማይባል ጣጣ አምጥቷል። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:1–6, 17–19) ዛሬ የምንኖረው በራሴ መመራት እፈልጋለሁ የሚል መንፈስ በገነነበት ዓለም ውስጥ ነው። ስለሆነም ይህንን መንፈስ ከራሳችን እንድናስወጣ አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝ ሊያስደንቀን አይገባም። ይህን እርምጃ እንድንወስድ ይሖዋ በድርጅቱ በኩል በፍቅር ይመክረናል።

11. ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ የአምላክ ሥርዓት ውስጥ ለሚገኘው ሕይወት ከልብ እየተዘጋጀን መሆናችንን የሚመሰክረው ምንድን ነው?

11 ይሖዋ አሁን ያለውን ሥርዓት አስወግዶ በምትኩ “ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ለማምጣት ስላለው ታላቅ ዓላማ በዚህ ድርጅት አማካኝነት አውቀናል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይህ ክፉ ዓለም በቅርቡ እንደሚጠፋና ምድር ወደ ገነትነት እንደምትለወጥ ማወቃችን በደስታ እንድንፍለቀለቅ ያደርገናል። ይሁን እንጂ ጽድቅ በሚያይልበት ዓለም ውስጥ ለሚገኘው ሕይወት ከልብ እየተዘጋጀን መሆናችንን አኗኗራችን ያሳያልን? መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ . . . ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም” ብሎ በግልጽ ይነግረናል። (1 ዮሐንስ 2:15) እርግጥ፣ ማንኛችንም ብንሆን በዓለም ውስጥ የማንወዳቸው ነገሮች አሉ። ይሁን እንጂ በተለይ የምንጠላው የጊዜውን ደስታችንን የሚነካብንን ነገር ብቻ ነውን? ወይስ የዓለምን መንፈስ ይኸውም በራሴ እመራለሁ የሚለውንና ስለ ራስ ከልክ በላይ የመጨነቅን ጠባይ ጭምር እንጠላለን? የሥጋችን ዝንባሌ ተቃራኒ ቢሆንም ይሖዋን ማዳመጥንና ከልብ መታዘዝን ልምድ አድርገነዋልን? የትም ቦታ እንኑር፤ ምንም ሥራ እንሥራ፤ አስተሳሰባችንና ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሚያነሳሳን ዓላማ ወደ አምላክ ያዘነበለ መሆኑን መላው አኗኗራችን መመስከር ይኖርበታል። — ምሳሌ 3:5, 6

12. (ሀ) አሁን ያለንን አጋጣሚ የይሖዋን መንገዶች ለመማርና ለመከተል ልንጠቀምበት የሚገባን ለምንድን ነው? (ለ) በአንቀጹ ውስጥ ያሉት አውጥተን እንድናነባቸው የተሰጡት ጥቅሶች ለእያንዳንዳችን ምን ትርጉም አላቸው?

12 ይሖዋ ይህንን ክፉ የነገሮች ሥርዓትና የሥርዓቱን መንገዶች የሚወዱትን ሁሉ ለማጥፋት የቀጠረው ጊዜ አይዘገይም። ይሖዋ ቀጠሮውን ለሌላ ጊዜ አያስተላልፈውም፤ ወይም ደግሞ እስካሁን ከዓለም ጋር ተጣብቀው ለመኖር የሚሞክሩትን፤ ማለትም የአምላክን ፈቃድ ለመማርና ለማድረግ ልባቸው ሙሉ ያልሆነውን ሰዎች ለማስተናገድ ሲል የአቋም ደረጃውን አይለውጥም። እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን ነው። (ሉቃስ 13:23, 24፤ 17:32፤ 21:34–36) እንግዲያው ይህንን ውድ አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ያሉት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ይሖዋ በፍቅራዊ ድርጅቱ በኩል የሚሰጠውን ትምህርት በጉጉት ሲከታተሉና አንድነታቸውን ጠብቀው በጐዳናዎቹ ሲጓዙ ማየቱ እንዴት ደስ ይላል!

የክለሳ ውይይት

● አምልኮን በሚመለከት የይሖዋ ዓላማ ምንድን ነው?

● መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ከቀሰምን በኋላ ምን ተጨማሪ ዕድገት ለማድረግ ከልብ መጣጣር አለብን?

● የተወያየንባቸው አንድነትን የሚያመጡ ነገሮች እንደሚገባው ያህል ሕይወታችንን እንዲለውጡ በግለሰብ ደረጃ ምን ለማድረግ እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]