በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥምቀትህ ትርጉም

የጥምቀትህ ትርጉም

ምዕራፍ 12

የጥምቀትህ ትርጉም

1, 2. (ሀ) የውኃ ጥምቀት ሁላችን በግል ልናስብበት የሚገባን ለምንድን ነው? (ለ) በ2ኛው አንቀጽ ያሉትን ጥያቄዎች በአጭሩ እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?

በ29 እዘአ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። ይህ ሲሆን ይሖዋ ይመለከት ነበር። በአድራጎቱ የተደሰተ መሆኑንም አስታወቀ። (ማቴዎስ 3:16, 17) ከዚያ ሦስት ዓመት ተኩል ያህል ቆይቶ ኢየሱስ ከሞት ተነሳና ለደቀመዛሙርቱ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . እያጠመቃችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው” የሚል መመሪያ ሰጣቸው። (ማቴዎስ 28:19, 20) ኢየሱስ እዚህ ላይ በሰጠው መመሪያ መሠረት ተጠምቀሃልን? ወይስ ይህን እርምጃ ለመውሰድ ገና በመዘጋጅት ላይ ነህ?

2 ያም ሆነ ይህ የጥምቀት ትርጉም ግልጽ ሆኖ እንዲገባህ ያስፈልጋል። ሊታሰብባቸው ከሚገቡት ጥያቄዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:- ዛሬ የሚደረገው የክርስቲያኖች ጥምቀት ከኢየሱስ ጥምቀት ጋር አንድ ትርጉም አለውን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥምቀት የሚናገረው ሁሉ አንተን ይመለከታልን? የክርስቲያኖች የውኃ ጥምቀት ከያዘው ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ምን ማድረግን ይጠይቃል?

በዮሐንስ የተከናወኑ ጥምቀቶች

3. የዮሐንስ ጥምቀት ለእነማን የተወሰነ ነበር?

3 ኢየሱስ ሳይጠመቅ ስድስት ወራት ያህል ቀደም ብሎ መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ ምድረበዳ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ መስበክ ጀመረ። (ማቴዎስ 3:1, 2) በዚያ አካባቢ የነበሩት ሰዎች ዮሐንስ የተናገረውን ሰሙ፣ ኃጢአታቸውን በግልጽ ተናዘዙ፣ በዮርዳኖስም ወንዝ በእርሱ ተጠመቁ። ያ ጥምቀት ለአይሁዶች ብቻ የተወሰነ ነበር። — ሥራ 13:23, 24፤ ሉቃስ 1:13–16

4. (ሀ) አይሁዶች በአስቸኳይ ንስሐ መግባት ያስፈለጋቸው ለምን ነበር? (ለ) በእሳት ከመጠመቅ ለመዳን ምን ማድረግ ነበረባቸው?

4 እነዚያ አይሁዶች በአስቸኳይ ንስሐ መግባት አስፈልጓቸው ነበር። ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት በ1513 አባቶቻቸው ከይሖዋ አምላክ ጋር ብሔራዊ ቃል ኪዳን ገብተው ነበር። ይሁን እንጂ ያ ቃል ኪዳን የሚጠይቅባቸውን ኃላፊነት ሳይፈጽሙ ስለቀሩ ቃል ኪዳኑ ኃጢአተኞች አድርጎ ኰነናቸው። ስለዚህ በአደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኙ ነበር። በሚልክያስ ትንቢት የተነገረው “ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን” ቅርብ ነበር። እርሱም በ70 እዘአ መጣና በኢየሩሳሌም ላይ ፈጣን ጥፋት አስከተለ። መጥምቁ ዮሐንስ ለእውነተኛ አምልኮ እንደ ኤልያስ ያለ ቅንአት ይዞ ከዚያ ጥፋት በፊት ለይሖዋ አንድ ሕዝብ እንዲያዘጋጅ ተላከ። ሕዝቡ በሕጉ ቃል ኪዳን ላይ ስለፈጸሙት ኃጢአት ንስሐ መግባትና ይሖዋ የሚልክላቸውን ልጁን ለመቀበል በልብና በአእምሮ ዝግጁ መሆን አስፈልጓቸው ነበር። (ሚልክያስ 4:4–6፤ ሉቃስ 1:17፤ ሥራ 19:4) የአምላክ ልጅ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት እንደሚያጠምቅ ዮሐንስ ተናገረ። (ታማኝ ደቀመዛሙርት ይህን ጥምቀት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠመቁት በ33 እዘአ በጴንጠቆስጤ ዕለት ነበር።) ንስሐ ያልገቡት እስራኤላውያን ግን በ70 እዘአ ሲጠፉ በእሳት ተጠምቀዋል። (ሉቃስ 3:16) እነዚያ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዶች በግለሰብ ደረጃ ከእሳቱ ጥምቀት ለማምለጥ ከፈለጉ በውኃ በመጠመቅ ንስሐ መግባታቸውን ማሳየትና አጋጣሚው ሲከፈትላቸው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት መሆን ነበረባቸው።

5. (ሀ) ኢየሱስ ለመጠመቅ ሲመጣ የእሱ መጠመቅ አስፈላጊ ስለመሆኑ ዮሐንስ ጥያቄ ያስነሳው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በውኃ መጠመቁ ምንን የሚያመለክት ነበር? (ሐ) ኢየሱስ አምላክ ለእርሱ የነበረውን ፈቃድ የመፈጸሙን ጉዳይ የቱን ያህል ክብደት ሰጥቶታል?

5 ለመጠመቅ ወደ ዮሐንስ ከመጡት አንዱ ኢየሱስ ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ለምን መጠመቅ አስፈለገው? ኢየሱስ የሚናዘዝበት አንድም ኃጢአት እንደሌለው ዮሐንስ ያውቅ ስለነበር “እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል፣ አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን?” አለው። ነገር ግን የኢየሱስ ጥምቀት ሌላ ነገር የሚያመለክት ነበር። ስለሆነም “አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” ብሎ መለሰለት። (ማቴዎስ 3:13–15) የኢየሱስ ጥምቀት ለኃጢአት ንስሐ መግባቱን ሊያመለክት አይችልም። ራሱንም ለአምላክ መወሰን አያስፈልገውም ነበር፤ ምክንያቱም ቀደም ሲል ለይሖዋ የተወሰነው ሕዝብ አባል ነበር። ከዚህ ይልቅ እንደ አይሁዶች አመለካከት በ30 ዓመቱ ለአካለ መጠን ሲደርስ መጠመቁ የሰማያዊ አባቱን ተጨማሪ ፈቃድ ለማድረግ ራሱን ለእርሱ ማቅረቡን የሚያመለክት ነበር። አምላክ ለክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ፈቃድ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዘ ሥራ ማከናወንንና ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ሰውቶ ቤዛና የአዲስ ኪዳን መሠረት ማድረግን የሚጨምር ነበር። (ሉቃስ 8:1፤ 17:20, 21፤ ዕብራውያን 10:5–10፤ ማቴዎስ 20:28፤ 26:28፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6) ኢየሱስ የውኃ ጥምቀቱ የሚያመለክተውን ነገር ከፍተኛ ክብደት ሰጥቶታል። ሐሳቡ ወደ ሌሎች ጉዳዮች ዘወር እንዲል አልፈቀደም። እስከ ምድራዊ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ የአባቱን ፈቃድ ከማድረግ ፈቀቅ አላለም። — ዮሐንስ 4:34

ወደ ሞት ውስጥ መጠመቅ

6. ኢየሱስ ምን ሌላ ጥምቀት ተጠምቋል? ይህስ የተከናወነው ከመቼ እስከ መቼ ድረስ ነው?

6 ኢየሱስ የውኃ ጥምቀቱ ከሚያመለክተው ነገር ጋር የሚስማማ ሌላ ዓይነት ጥምቀትም ተጠምቋል። አባቱ ከፊቱ ያስቀመጠለት ሥራ ሰብዓዊ ሕይወቱን እስከ መሰዋት እንደሚያደርሰውና በሦስተኛው ቀን መንፈሣዊ አካል ሆኖ እንደሚነሳ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ይህ እንደ ጥምቀት እንደሆነ ተናግሯል። ይህ ጥምቀት የጀመረው በ29 እዘአ ሲሆን እርሱ ሞቶ እስከተነሳበት ጊዜ ድረስ ሙሉ በሙሉ አልተፈጸመም ነበር። ስለዚህ በውኃ ከተጠመቀ ከሦስት ዓመት በኋላ “የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፣ እስክትፈጸምም ድረስ እንዴት እጨነቃለሁ?” ብሎ በትክክል ለመናገር ችሏል። — ሉቃስ 12:50

7. (ሀ) ወደ ሞት ውስጥ የሚጠመቁት ሌሎች ሰዎች እነማን ናቸው? (ለ) ይህንን ጥምቀት የሚያከናውነው ማን ነው?

7 ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ መንግሥት የሚገዙትም ልክ እንደ እርሱ ወደ ሞት ውስጥ መጠመቅ አለባቸው። (ማርቆስ 10:37–40፤ ቆላስይስ 2:12) ሲሞቱ ልክ እንደ ኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወታቸውን ለዘላለም ጥለው ይሄዳሉ። ከሞት ሲነሱም በሰማያዊ መንግሥት ከእርሱ ጋር ይሆናሉ። ይህ ጥምቀት አምላክ በሰማያዊ ልጁ በኩል የሚያከናውነው እንጂ በሰው የሚፈጸም አይደለም።

8. ‘ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ ይጠመቃሉ’ ሲባል ምን ማለት ነው?

8 ወደ ኢየሱስ ሞት የሚጠመቁት ሁሉ ወደ ክርስቶስ ኢየሱስም ጭምር እንደሚጠመቁ ተገልጿል። በክርስቶስ በኩል በሚያገኙት መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት “የአካሉ” ማለትም በመንፈስ የተቀባው ጉባኤ አባላት በመሆን ራሳቸው ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ አካል ይሆናሉ። ይህ መንፈስ በዓይነቱ ከፍ ያለውን የኢየሱስ ጠባይ እንዲያሳዩ ስለሚረዳቸው “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ ሰው ይሆናሉ” ብሎ ለመናገር ይቻላል። — ሮሜ 6:3–5 አዓት፤ 1 ቆሮንቶስ 12:13፤ ገላትያ 3:27, 28፤ ሥራ 2:32, 33

የክርስቲያን ደቀመዛሙርት የውኃ ጥምቀት

9. (ሀ) በማቴዎስ 28:19 ላይ ያለውን መመሪያ የተከተለ ጥምቀት በመጀመሪያ የተፈጸመው መቼ ነው? (ለ) በዚህ አንቀጽ ውስጥ ባሉት ጥቅሶችና ጥያቄዎች ተጠቅመህ ኢየሱስ የጥምቀት እጩዎች ምን ማመንና መቀበል አለባቸው ብሎ እንዳመለከተ ግለጽ።

9 የኢየሱስ ደቀመዛሙርት በመጀመሪያ በዮሐንስ በውኃ ተጠምቀው ነበር። ከዚያም የኢየሱስ መንፈሳዊ ሙሽራ እጩ አባላት በመሆን ወደ እርሱ እንዲሄዱ ተነገራቸው። (ዮሐንስ 3:25–30) እነርሱም ኢየሱስ በሰጣቸው መመሪያ አንዳንድ ሰዎችን አጥምቀዋል። ይህ ጥምቀት ከዮሐንስ ጥምቀት ጋር አንድ ትርጉም ነበረው። (ዮሐንስ 4:1–3) ነገር ግን በ33 እዘአ ከዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” እንዲያጠምቁ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ መፈጸም ጀመሩ። (ማቴዎስ 28:19) ከዚህ ቀጥሎ ባሉት ጥቅሶችና ጥያቄዎች አማካኝነት የዚህን ትእዛዝ ትርጉም እንደገና መመልከቱ በጣም ጠቃሚ ሆኖ ታገኘዋለህ:-

አንድ ሰው “በአብ ስም” መጠመቅ አለበት ሲባል ስለ አባት ምን ማወቅና መቀበል ይኖርበታል ማለት ነው? (2 ነገሥት 19:15፤ መዝሙር 3:8፤ 73:28፤ ኢሳይያስ 6:3፤ ሮሜ 15:6፤ ዕብራውያን 12:9፤ ያዕቆብ 1:17)

“በወልድ” ወይም “በልጅ ስም” መጠመቅ ምን መቀበልንና ማመንን ይጠይቃል? (ማቴዎስ 16:16, 24፤ ፊልጵስዩስ 2:9–11፤ ዕብራውያን 5:9, 10)

አንድ ሰው “በመንፈስ ቅዱስ ስም” የሚጠመቀው ምንን በማመን ነው? (ሉቃስ 11:13፤ ዮሐንስ 14:16, 17፤ ሥራ 1:8፤ 10:38፤ ገላትያ 5:22, 23፤ 2 ጴጥሮስ 1:21)

10. (ሀ) ዛሬ የክርስቲያኖች የውኃ ጥምቀት ምን ያመለክታል? (ለ) ይህስ ኢየሱስ ከተጠመቀው የውኃ ጥምቀት የሚለየው እንዴት ነው? (ሐ) ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን ያሟሉ ሰዎች ሲጠመቁ ምን ይሆናሉ?

10 ከላይ በተጠቀሰው የኢየሱስ መመሪያ መሠረት የተጠመቁት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አይሁዶች (እና ወደ ይሁዲነት ሃይማኖት የተለወጡ ሰዎች) ነበሩ። አይሁዶች በብሔር ደረጃ ለይሖዋ የተወሰኑ ሕዝብ ነበሩ፤ ይሖዋም እስከ 36 እዘአ ድረስ ልዩ አስተያየት አድርጎላቸው ነበር። ሣምራውያንና አሕዛብ ግን ክርስቲያን ደቀመዛሙርት የመሆን መብት በተከፈተላቸው ጊዜ ከመጠመቃቸው በፊት በየግላቸው የልጁ ደቀ መዛሙርት በመሆን ይሖዋን ለማገልገል ያለ ምንም ገደብ ራሳቸውን ለእርሱ መወሰን አስፈለጋቸው። ከዚያ በኋላ ሁሉም ደቀመዛሙርት (ከአይሁድ የመጡትም ጭምር) ክርስቲያናዊ የውኃ ጥምቀታቸው ትርጉሙ ይኸው ሆኖ ቆይቷል። ይህን “አንድ ጥምቀት” እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ሊጠመቁት ይገባል። በዚህ መንገድ ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች ወይም በአምላክ የተሾሙ አገልጋዮች ይሆናሉ። — ኤፌሶን 4:5፤ 2 ቆሮንቶስ 6:3, 4

11. (ሀ) የክርስቲያን የውኃ ጥምቀት ከምን ጋር ይመሳሰላል? እንዴትስ? (ለ) አንድ ክርስቲያን በዚህ መንገድ ከምን ይድናል?

11 ይህ ዓይነቱ ጥምቀት በአምላክ ፊት ትልቅ ዋጋ አለው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ኖኅ ራሱና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃ የዳኑበትን መርከብ እንደሠራ ከገለጸ በኋላ ይህንን ቁም ነገር ጠቅሷል። እንዲህ ብሎ ጻፈ:- “ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፣ የሰውነት ዕድፍ ማስወገድ አይደለም፣ ለእግዚአብሔር የበጎ ህሊና ልመና ነው እንጂ፤ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ነው።” (1 ጴጥሮስ 3:21) መርከቡ ኖኅ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን ለመወሰኑና አምላክ የሰጠውን ሥራ በታማኝነት ለመፈጸሙ ተጨባጭ ማስረጃ ነበር። ይህንንም በማድረጉ ከጥፋቱ ለመዳን ችሏል። በተመሳሳይም ከሙታን በተነሳው በክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት መሠረት ራሳቸውን ለይሖዋ የሚወስኑት፣ ይህንን ውስንነታቸውን በጥምቀት የሚያሳዩትና ከዚያ በኋላ አምላክ በዚህ ዘመን ላሉት አገልጋዮቹ ያለውን ፈቃድ የሚፈጽሙት ሁሉ ከዚህ ክፉ ዓለም ይድናሉ። (ገላትያ 1:3, 4) ከዓለም ጋር ወደ ጥፋት መጓዛቸውን አቁመዋል። ከዚህ ድነዋል፤ አምላክም ንጹሕ ሕሊና ሰጥቷቸዋል።

ኃላፊነቶቻችንን መፈጸም

12. አንድ ሰው መጠመቁ ብቻ ለመዳን ዋስትና የማይሆነው ለምንድን ነው?

12 መጠመቅ ብቻውን የመዳን ዋስትና ነው ብሎ መደምደም ስህተት ነው። ጥምቀት ዋጋ የሚኖረው አንድ ሰው በእርግጥ ራሱን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለይሖዋ ከወሰነና ከዚያ በኋላ እስከ መጨረሻው ድረስ የአምላክን ፈቃድ ካደረገ ብቻ ነው። — ማቴዎስ 24:13

13. (ሀ) አንድ የተጠመቀ ክርስቲያን ሕይወቱን እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚገባ የአምላክ ፈቃድ ምንድን ነው? (ለ) በሕይወታችን ውስጥ ክርስቲያን ደቀመዝሙርነት ምን ቦታ መያዝ አለበት?

13 አምላክ ለኢየሱስ የነበረው ፈቃድ የሰብዓዊ ሕይወቱን አጠቃቀም የሚመለከት ነበር። ሕይወቱ በሞት መስዋዕት ሆኖ መቅረብ ነበረበት። እኛ ደግሞ ሰውነታችንን ለአምላክ በማቅረብ የመስዋዕትነት ሕይወት መኖር ይገባናል። ሰውነታችንን የአምላክን ፈቃድ ብቻ ለማድረግ እንድንጠቀምበት ያስፈልጋል። (ሮሜ 12:1, 2) ነገር ግን አልፎ አልፎ ብቻም ቢሆን በዙሪያችን ያለው ዓለም የሚያደርጋቸውን ነገሮች ሆን ብለን ብናደርግ ወይም አምላክን ለይስሙላ ያህል ብቻ እያገለገልን የግል ጥቅማችንን በማሳደድ ብንኖር ሕይወታችንን በዚያ መንገድ ተጠቅመንበታል ለማለት አንችልም። (1 ጴጥሮስ 4:1–3፤ 1 ዮሐንስ 2:15–17) አንድ አይሁዳዊ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ አለብኝ ብሎ ኢየሱስን በጠየቀው ጊዜ ኢየሱስ ንጹሕ ሥነ ምግባር አስፈላጊ እንደሆነ ካሳሰበው በኋላ የእርሱ ተከታይ መሆንን ወይም ክርስቲያን ደቀ መዝሙር መሆንን የሕይወቱ ዋና ዓላማ ማድረግ እንዳለበት ገልጾለታል። ይህንን ከሥጋዊ ነገሮች በስተኋላ ማስቀመጥ አይቻልም። — ማቴዎስ 19:16–21

14. (ሀ) ክርስቲያኖች በሙሉ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዘ ምን ኃላፊነት አለባቸው? (ለ) በገጽ 101 ላይ በሥዕል በተገለጸው መሠረት ይህንን ሥራ የምናከናውንባቸው አንዳንድ ውጤታማ መንገዶች ምን ምን ናቸው? (ሐ) በዚህ ሥራ በእርግጥ በሙሉ ልባችን ከተሳተፍን ይህ የምን ማረጋገጫ ይሆናል?

14 አምላክ ለኢየሱስ የነበረው ፈቃድ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዘ ትልቅ ሥራ መሥራትን እንደሚጨምር ማስታወስ ይኖርብናል። ኢየሱስ ራሱ ንጉሥ እንዲሆን ተቀብቶ ነበር። ይሁን እንጂ እዚህ ምድር ሳለ ለመንግሥቱ ቀናተኛ ምሥክር ሆኖ ይሰራ ነበር። እኛም ተመሳሳይ የምሥክርነት ሥራ አለን። በዚህ ሥራ በሙሉ ልባችን የምንሳተፍበት በቂ ምክንያት አለን። እንደዚህ በማድረግ የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደምንወድና ለሰዎች ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። ከዚህም በላይ በመንግሥቱ ግዛት ውስጥ ወደሚገኘው የዘላለም ሕይወት ግብ በመጓዝ በዓለም ዙሪያ ካሉት የይሖዋ አምላኪዎችና የመንግሥቱ ምሥክሮች ጋር አንድነት እንዳለን እናሳያለን።

የክለሳ ውይይት

● በኢየሱስ ጥምቀትና ዛሬ በሚከናወነው የውኃ ጥምቀት መካከል ምን ተመሳሳይነትና ልዩነት አለ?

● የዮሐንስ ጥምቀት ለእነማን የመጣ ነበር? ወደ ሞት ውስጥ የሚጠመቁት እነማን ናቸው? ‘ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ የሚጠመቁትስ?’

● የክርስቲያን የውኃ ጥምቀት የሚያስከትላቸው ኃላፊነቶች ምን ነገሮችን ይጨምራሉ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 101 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

መንግሥቱን የምታውጀው በምን በምን መንገዶች ነው?

ከበር ወደ በር በመሄድ

ፍላጎት ያላቸውን ተመላልሶ በመጠየቅ

በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

በየመንገዱ

አብረውህ ለሚማሩት

አብረውህ ለሚሠሩት