በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን የሚያመልኩ ሁሉ የሚያገኙት አስደሳች ነፃነት

ይሖዋን የሚያመልኩ ሁሉ የሚያገኙት አስደሳች ነፃነት

ምዕራፍ 5

ይሖዋን የሚያመልኩ ሁሉ የሚያገኙት አስደሳች ነፃነት

1, 2. (ሀ) አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ምን ዓይነት ነፃነት ሰጥቷቸው ነበር? (ለ)ተግባሮቻቸውን የሚቆጣጠሩትን አንዳንድ ሕጎች ጥቀስ።

የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት በይሖዋ በተፈጠሩ ጊዜ ዛሬ ማንም ሰው የሌለውን ዓይነት ነፃነት አግኝተው ነበር። መኖሪያቸው ገነት ነበር። በደስታ እንዳይኖሩ የሚያውካቸው ሕመም አልነበረም። ወደፊት ሞት አይጠብቃቸውም ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ዓይነት ነፃነት ለመቀጠል የአምላክን ሕጎች መታዘዛቸው የግድ አስፈላጊ ነበር።

2 ከእነዚህ ሕጎች አንዳንዶቹ በቃል አልተነገሯቸው ይሆናል። ቢሆንም አዳምና ሔዋን እነዚያን ሕጎች እንዲጠብቁ የሚያደርግ የተፈጥሮ ዝንባሌ ነበራቸው። ለምሳሌ ራብ ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ጥምም ውሃ እንደሚያስፈልጋቸው ያሳስባቸዋል። የፀሐይ መጥለቅ አስፈላጊውን እረፍትና ዕንቅልፍ እንዲወስዱ ያበረታታቸዋል። ይሖዋ ያነጋግራቸው ነበር፤ ሥራም ሰጥቷቸዋል። የተሰጣቸው ሥራ የሕግ ያህል ነበር፤ ምክንያቱም ምን እያደረጉ መኖር እንዳለባቸው የሚወስንላቸው ነበር። ሆኖም ሕጉ እንዴት ቀላልና ጠቃሚ ነበር! ሙሉ በሙሉ የሚያረካ ሥራ የሚሰጥና ኃይላቸውን በጥሩ መንገድ እንዲጠቀሙበት የሚያስችል ሕግ ነበር። ልጅ መውለድ፣ የምድርን እንስሳት በበላይነት ማስተዳደርና ገነት ምድርን ከዳር እስከ ዳር እስክትሸፍን ድረስ ማስፋፋት ነበረባቸው። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:15) አምላክ የማያስፈልጉ ዝርዝር ትእዛዞችን በመስጠት ሸክም አልጫነባቸውም። ውሳኔዎችን ለማድረግ በቂ ነፃነት ተሰጥቷቸው ነበር። ማንም ሰው ከዚህ የበለጠ ምን ሊጠይቅ ይችላል?

3. አዳም በነፃነቱ ጥበብ ያለበትን ውሳኔ ለማድረግ ምን ሊረዳው ይችል ነበር?

3 እርግጥ አዳም ውሳኔ የማድረግ መብት ቢሰጠውም የፈለገውን ውሳኔ ቢያደርግ ውጤቱ ሁልጊዜ ጥሩ ይሆናል ማለት አይደለም። ውሳኔ እንዲያደርግ የተሰጠው ነፃነት በኃላፊነትም ያስጠይቀዋል። የሰማይ አባቱን በማዳመጥና ሥራዎቹን በመመልከት ትምህርት ለማግኘት ይችል ነበር። አምላክም የቀሰመውን ትምህርት እንዲጠቀምበት የሚያስችል አእምሮ ሰጥቶታል። አዳም የተፈጠረው “በአምላክ መልክ” ስለነበረ ውሳኔ በሚያደርግበት ጊዜ አምላካዊ ባሕርዮችን ለማንጸባረቅ የተፈጥሮ ዝንባሌ ነበረው። አምላክ ያደረገለትን ከልብ የሚያደንቅና እርሱን ለማስደሰት የሚፈልግ ከሆነ ተጠንቅቆ እንደዚያ ማድረግ ነበረበት። — ዘፍጥረት 1:26, 27፤ ከዮሐንስ 8:29 ጋር አወዳድር።

4. (ሀ) ለአዳም የሚከለክል ትእዛዝ መሰጠቱ ነፃነት የሚያሳጣው ነበርን? (ለ)ትእዛዙ ተገቢ የነበረው ለምንድን ነው?

4 ሰው የፈጣሪውና የሕይወት ሰጪው ጥገኛ መሆኑን ለማሳሰብ ይሖዋ የሚከተለውን ሕግ ሰጠው:- “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ።” (ዘፍጥረት 2:16, 17) ያ ሕግ ነፃነት የሚያሳጣ ነበርን? በፍጹም አልነበረም። አዳም ለመታዘዝም ሆነ ላለመታዘዝ ነፃነት ነበረው። የዛፉን ፍሬ እንዳይበላ መከልከሉ ሸክም አልሆነበትም። በቂ ምግብ ስለነበረው ያችን አንዲት ዛፍ መንካት አያስፈልገውም ነበር። ሆኖም የሚኖርባት ምድር የአምላክ ንብረት እንደሆነችና አምላክ የፍጡሮቹ ገዥ ለመሆን መብት እንዳለው መቀበል ነበረበት። — መዝሙር 24:1, 10

5. (ሀ) አዳምና ሔዋን የነበራቸውን ታላቅ ነፃነት እንዴት አጡ? (ለ) ከዚያ ምን ሆነ? እኛስ የተነካነው እንዴት ነው?

5 ነገር ግን ምን ሆነ? በራስ ወዳድነት የሥልጣን ምኞት ያደረበት አንድ መልአክ ሐቀኛ መሪ መስሎ ቀረበና ከአምላክ ፈቃድ ተቃራኒ የሆነ ተስፋ በመስጠት ሔዋንን አታለላት። አዳምም አባቱን በመታዘዝ ፋንታ ሕግ በመጣሱ ተግባር ሔዋንን ተባበራት። አዳምና ሔዋን የራሳቸው ያልሆነውን በመውሰድ በፊት የነበራቸውን ታላቅ ነፃነት አጡ። ኃጢአት ጌታቸው ሆነ። አምላክ እንዳስጠነቀቃቸውም ሞት ያለ ጥርጥር ይጠብቃቸው ጀመር። እንግዲያው ለዘሮቻቸው ምንን አወረሱ? ኃጢአትን ነው። ይህ ኃጢአት ወደ መጥፎ የሚገፋፋ ውስጣዊ ዝንባሌ ሆኖ ይሠራል፤ እንዲሁም ለሕመም በቀላሉ እንድንጋለጥና በመጨረሻም አርጅተን እንድንጃጃ በሚያደርጉ ድክመቶች መልክ ይታያል። አዳምና ሔዋን ሞትንም አውርሰውናል። ወደ መጥፎ ድርጊት የሚገፋፋው የተፈጥሮ ዝንባሌ ሁኔታውን የሚያባብስ ሰይጣናዊ ግፊት ተጨምሮበት ለሰው ሕይወት አደገኛ የሆነ ኅብረተሰብ አፍርቷል። ይህ ሁሉ አምላክ በመጀመሪያ ላይ ለሰው ከሰጠው ነፃነት እንዴት የተለየ ነው! — ሮሜ 5:12፤ ኢዮብ 14:1 ራእይ 12:9

ነፃነት የሚገኘው የት ነው?

6. (ሀ) እውነተኛ ነፃነት ሊገኝ የሚችለው የት ነው? (ለ)ኢየሱስ በዮሐንስ 8:31, 32 ላይ የተናገረው ስለ ምን ዓይነት ነፃነት ነው?

6 ዛሬ ያሉትን ሁኔታዎች ስንመለከት ሰዎች አሁን ካላቸው የበለጠ ነፃነት ለማግኘት መጓጓታቸው አያስደንቀንም። ይሁን እንጂ እውነተኛ ነፃነት ሊገኝ የሚችለው የት ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ “በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናቸሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሏል። (ዮሐንስ 8:31, 32) ይህ ነፃነት ሰዎች የመሪ ወይም የመንግሥት ለውጥ ተደርጎ ለማየት የሚጓጉለት ዓይነት ውስን ነፃነት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሰውን ልጆች ችግር ከሥሩ የሚነቅል ነው። ኢየሱስ የተናገረው ከኃጢአት ባርነት ነፃ ስለመሆን ነው። (ዮሐንስ 8:24, 34-36 ተመልከት) በዚህ ምክንያት አንድ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዝሙር ሲሆን በሕይወቱ ላይ ጉልህ ለውጥ ይታይበታል፤ ነፃነት ያገኛል።

7. (ሀ) እንግዲያው አሁን ከኃጢአት ነፃ ለመሆን የምንችለው በምን መንገድ ነው? (ለ)ይህን ነፃነት ለማግኘት ምን ማድረግ አለብን?

7 ይህም ሲባል እውነተኛ ክርስቲያኖች በአሁኑ ጊዜ ወደ ኃጢአት ድርጊት የሚገፋፋ የተፈጥሮ ዝንባሌ አይሰማቸውም ማለት አይደለም። እንዲያውም በዚህ ምክንያት ትግል አለባቸው። (ሮሜ 7:21-25) ነገር ግን አንድ ሰው ከኢየሱስ ትምህርት ጋር የሚስማማ ተግባር እየሠራ ቢኖር ለኃጢአት የሚገዛ ባሪያ አይሆንም። ከዚያ በኋላ ኃጢአት እንደ ንጉሥ ሆኖ የሚገዛው፣ እርሱም የሚታዘዝለት መሆኑ ያቆማል። ዓላማ በሌለውና ሕሊናውን በሚረብሽ የአኗኗር ወጥመድ አይያዝም። በፊት የሠራቸው ኃጢአቶች በክርስቶስ መስዋዕት ላይ ባለው እምነት መሠረት ይቅር ስለተባሉለት በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይኖረዋል። የኃጢአት ዝንባሌዎች ሊታገሉት ይሞክሩ ይሆናል። ነገር ግን የክርስቶስን ንጹሕ ትምህርቶች አስታውሶ በግፊቶቹ ለመሸነፍ እምቢ ካለ ኃጢአት የእርሱ ጌታ እንዳልሆነ አሳየ ማለት ነው። — ሮሜ 6:12-17

8. (ሀ) እውነተኛው የክርስትና እምነት ምን ሌላ ነፃነት ይሰጠናል? (ለ) ይህስ ለዓለማዊ ባለ ሥልጣኖች ያለንን አመለካከት እንዴት ሊነካው ይገባል?

8 በክርስቲያንነታችን ትልቅ ነፃነት አግኝተን በደስታ እንኖራለን። የሐሰት ትምህርት ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች፣ ለአጉል እምነት ባርያ ከመሆንና ለኃጢአት ከመንበርከክ ተገላግለናል። ስለ ሙታን ሁኔታና ስለ ትንሳኤ የሚገልጹት ታላላቅ እውነቶች የሰውን ሕሊና ከሚያፍነው ጭፍን ከሆነው የመገደል ፍርሐት ነፃ አውጥቶናል። ፍጽምና የሌላቸው ሰብዓዊ መንግሥታት ጠፍተው በምትካቸው ጽድቅ የሚሰፍንበት የአምላክ መንግሥት እንደሚመጣ ማወቃችን ተስፋ ቆርጦ ከመቃተት ነፃ ያደርገናል። ይሁን እንጂ ይህ ነፃነት በቅርቡ ይህ አሮጌ ሥርዓት ይጠፋል በሚል ሰበብ ሕግን ለማፍረስና የመንግሥት ባለ ሥልጣኖችን ላለማክበር ፈቃድ አይሰጠንም። — 1 ጴጥሮስ 2:16, 17፤ ቲቶ 3:1, 2

9. (ሀ) ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ሰው ማግኘት የሚችለውን የመጨረሻውን ሰፊ ነፃነት እንድናገኝ በፍቅር የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ)ውሳኔ ስናደርግ አዳም ነፃነቱን በአግባቡ ሳይጠቀምበት በመቅረቱ የደረሰበት ውጤት በግልጽ እንደገባን እንዴት ልናሳይ እንችላለን?

9 ይሖዋ ይህንንም ያንንም እየሞከሩ ከሁሉ የተሻለውን የአኗኗር መንገድ ማግኘቱን ለእኛው አልተወውም። የተፈጥሮአችን ሁኔታ፣ እውነተኛ እርካታ የሚያመጣልን፣ ሰብዓዊ ክብር እንዲሰማን የሚያደርገውና ለዘለቄታው የሚጠቅመን ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል። ከዚህም በላይ የራሱን ዓላማ የሚያስፈጽምበትን የጊዜ ፕሮግራም ስለሚያውቅ ዛሬ ጊዜያችንን በምን ሥራ ላይ ብናውለው እንደሚሻል ያውቃል። በተጨማሪም የአንድን ሰው ክብር ዝቅ የሚያደርጉትን ወይም ከሌሎች ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያሻክሩበትን ወይም ወደ አምላክ መንግሥት በረከቶች ከመግባት የሚያግዱትን አስተሳሰቦችና ጠባዮች ያውቃል። እነዚህ ነገሮች ምን እንደሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስና በሚታየው ድርጅቱ አማካይነት በፍቅሩ ገልጾልናል። (ገላትያ 5:19-23፤ ማርቆስ 13:10፤ ከ1 ጢሞቴዎስ 1:12, 13 ጋር አወዳድር) ከዚያ በኋላ ግን አምላክ በሰጠን የመምረጥ ነፃነት ተጠቅመን ምን እንደምናደርግ መወሰኑ የራሳችን ነው። ለሰው ልጅ በመጀመሪያ ተሰጥቶ የነበረውን ነፃነት አዳም እንዴት እንዳጣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው ቁም ነገር ወደ ልባችን ገብቶ ከሆነ በጥንቃቄ እንወስናለን። በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ በላይ የሚያሳስበን ጉዳይ ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና መሆኑን እናሳያለን።

ሌላ ዓይነት ነፃነት መመኘት

10. ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንዶች ምን ዓይነት ነፃነት ለማግኘት ሞክረዋል?

10 የይሖዋ ምሥክር ሆነው ያደጉ ወጣቶች ወይም ወጣት ያልሆኑ ሌሎች ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ሌላ ዓይነት ነፃነት ያምራቸዋል። ዓለም ግሩም መስላ ትታያቸው ይሆናል። ነገሩን ብዙ ባሰቡበት መጠን የዓለማውያንን መንገድ ለመከተል ያደረባቸው ምኞት እየጠነከረ ይሄዳል። አደንዛዥ ዕፅ ወስደው የደስታ ስሜት ለመቀስቀስ ወይም ከመጠን በላይ ለመጠጣት ወይም ዝሙት ለመፈጸም አቅደው አልተነሱ ይሆናል። ነገር ግን ከትምህርት ወይም ከሥራ በኋላ ያሉትን ሰዓታት ከዓለማውያን ጋር ማሳለፍ ይጀምራሉ። በእነዚህ አዲስ ጓደኞች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ስላለባቸው በአነጋገራቸውና በፀባያቸው እነርሱን መምሰል ይጀምራሉ።— 3ዮሐንስ 11

11. አንዳንድ ጊዜ ወደዚህ የሚመራው ግፊት ከየት ይመጣል?

11 አንዳንድ ጊዜ ዓለማዊ ድርጊት እንድንፈጽም የሚያደፋፍረን ይሖዋን አገለግላለሁ የሚል ሰው ሊሆን ይችላል። በዔደን ውስጥ ሰይጣን ሔዋንን ሲያስታት፣ ሔዋንም አዳም እንዲተባበራት ስታግባባው የተፈጸመው ይኸው ነበር። በመጀመሪያዎቹ እውነተኛ ክርስቲያኖች ዘንድ እንደዚህ ያለ ነገር ደርሷል፤ ዛሬም ይደርሳል። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ስሜትን የሚቀሰቅሱና ከፍተኛ ደስታ እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ነገሮች ያምሯቸዋል። “ትንሽ እንደሰት” እያሉ ሌሎችን ለማግባባት ይጥራሉ። “ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው [ሳሉ] አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ” ይሰጣሉ። — 2 ጴጥሮስ 2:18, 19

12. (ሀ) የዓለማዊ ድርጊቶች አሳዛኝ ውጤቶች ምንድን ናቸው? (ለ) ድርጊቶቹን የሚፈጽሙት ሰዎች ውጤቱን እያወቁት በዚያው የሚቀጥሉት ለምንድን ነው?

12 ፍሬው ግን ጣፋጭ አይደለም። የዝሙት ድርጊት የስሜት ስቃይን ያስከትላል። ከዚህም ሌላ በሽታ፣ ዲቃላና የትዳር መፍረስ ሊያመጣ ይችላል። (ምሳሌ 6:32-35፤ 1 ቆሮንቶስ 6:18፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3-8) አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ በትንሽ ነገር መበሳጨትን፣ ሲናገሩ መንተባተብን፣ ብዥ የሚል እይታን፣ መፍዘዝን፣ የመተንፈስ ችግርን፣ ቅዠት እያዩ መኖርን ወይም ሞትን ሊያስከትል ይችላል። (ምሳሌ 23:29-35 ጋር አወዳድር።) ሱስ ሊያስይዝ ይችላል። ይህም የዕፅ መግዣ ለማግኘት ሲባል ወንጀል ወደ መፈጸም ሊመራ ይችላል። በዚህ ዓይነቱ አድራጎት የሚጠመዱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ውጤቱን ያውቁታል። ይሁን እንጂ ለደስታና ለፈንጠዝያ ያላቸው ኃይለኛ አምሮት ውጤቶቹን ይሸፍንባቸዋል። ይህ እኮ ነፃነት ነው እያሉ ያስባሉ፤ ነገር ግን ምንም ማድረግ በማይችሉበት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ወደኋላ መለስ ይሉና የኃጢአት ባሪያዎች እንደነበሩ ይገነዘቡታል። ኃጢአት ደግሞ እንዴት ያለ ጨካኝ ጌታ ነው! አሁንኑ ስለ ነገሩ አውጥተን አውርደን ማሰባችን ከዚህ ዓይነቱ ውድቀት ለመዳን ይረዳናል። — ገላትያ 6:7, 8

ችግሮቹ የሚነሱት ከየት ነው?

13. (ሀ) ወደ እነዚህ ችግሮች የሚመሩት ምኞቶች ብዙውን ጊዜ እንዴት ይቀሰቀሳሉ? (ለ) መጥፎ ባልንጀርነት ምን እንደሆነ እንዲገባን የማንን አመለካከት መያዝ አለብን? (ሐ) በአንቀጹ መጨረሻ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች ስትመልስ የይሖዋን አመለካከት ጐላ አድርግ። ጥያቄዎቹን አንድ በአንድ ሐሳብ ስጥባቸው።

13 እስቲ ቆም በልና እነዚህ ችግሮች ከየት እንደሚነሱ አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጠአትን ትወልዳለች፣ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች” ሲል መንስዔውን ይገልጽልናል። (ያዕቆብ 1:14, 15) ነገር ግን እነዚያ ምኞቶች የሚፋፋሙት እንዴት ነው? ወደ አእምሮ በሚገቡት ሐሳቦች አማካይነት ነው። ሐሳቦቹም የሚመጡት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ከማይከተሉ ሰዎች ጋር በመዋል ነው። እርግጥ ሁላችንም “ከመጥፎ ባልንጀርነት” መራቅ እንዳለብን እናውቃለን። ጥያቄው ግን ‘መጥፎ የሚባለው የእነማን ባልንጀርነት ነው?’ የሚል ነው። ይሖዋ ነገሩን እንዴት ይመለከተዋል? ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን ጥያቄዎችና ጥቅሶች ብናስብባቸው ወደ ትክክለኛ መደምደሚያ ለመድረስ እንችላለን:-

አንዳንድ ሰዎች ጨዋ መስለው መታየታቸው ጥሩ ጓደኞች ይሆናሉ ማለት ነውን? (ከዘፍጥረት 34:1, 2, 18, 19 ጋር አወዳድር)

ወሬያቸው፣ ለምሳሌ የሚናገሩት ቀልድ ሊጠጓቸው የሚገቡ መሆናቸውን ያሳያልን? (ኤፌሶን 5:3, 4)

ስለ አምላክ ዓላማ የእኛው ዓይነት እምነት ከሌላቸው ነገሩ ሊያሳስበን ይገባልን? (ከ1 ቆሮንቶስ 15:12, 32, 33 ጋር አወዳድር።)

ይሖዋ እርሱን ከማይወዱት ጋር ጊዜያችንን ለማሳለፍ ብንመርጥ እንዴት ይሰማዋል? (ከ2 ዜና 19:1, 2 ጋር አወዳድር።)

ከማያምኑ ጋር ብንሠራ ወይም ብንማርም ለጓደኝነት እንደማንመርጣቸው እንዴት ልናሳይ እንችላለን? (1 ጴጥሮስ 4:3, 4)

ቴሌቪዥን ማየት፣ መጽሐፍ፣ መጽሔት ወይም ጋዜጣ ማንበብ ከሌሎች ጋር ጊዜያችንን የምናሳልፍበት ሌላው መንገድ ነው። በዛሬው ጊዜ በእነዚህ ምንጮች አማካይነት ከሚመጡ በተለይ ከምን ነገሮች ነው ራሳችንን መጠበቅ ያለብን? (ምሳሌ 3:31፤ ኢሳይያስ 8:19፤ ኤፌሶን 4:17-19)

በምናደርገው የጓደኛ ምርጫ ለይሖዋ ምን ዓይነት ሰዎች መሆናችንን እያሳየነው ነው? (መዝሙር 26:1, 4, 5፤ 97:10)

14. የአምላክን ቃል ምክር አሁን በታማኝነት የሚሠሩበት ሁሉ እንዴት ያለ ታላቅ ነፃነት ይጠብቃቸዋል?

14 አዲሱ የአምላክ ሥርዓት ከፊታችን ተደቅኗል። የሰው ዘር ባሪያ አድርጎ ከሚገዛው የሰይጣን እጅና ክፉ ከሆነው ጠቅላላ ሥርዓቱ ተጽዕኖ በአምላክ መንግሥት አማካይነት ይላቀቃል። በሰው ልጆች ውስጥ ያለው የኃጢአት ኃይል ቀስ እያለ እየከሰመ ይሄዳል። በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ዕድል ከፊታቸው ይዘረጋል። በመጨረሻው ፍጥረታት ሁሉ “ከይሖዋ መንፈስ” ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማውን አስደሳች ነፃነት ይቀዳጃሉ። (2 ቆሮንቶስ 3:17) ታዲያ በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ቃል ምክር አቃልለን በማየታችን የተነሳ ይህን ሁሉ ማጣቱ ምክንያታዊ ነውን? እንግዲያው በእርግጥ የምንፈልገው “የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት” መሆኑን ሁላችንም ዛሬ ክርስቲያናዊ ነፃነታችንን በምንጠቀምበት ሁኔታ እናሳይ። — ሮሜ 8:21

የክለሳ ወይይት

● የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ምን ዓይነት ነፃነት አግኝተው በደስታ ይኖሩ ነበር? ይህንንስ በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጆች ካሉበት ሁኔታ ጋር እንዴት ማወዳደር ይቻላል?

● እውነተኛ ክርስቲያኖች ዓለም ያላገኘውን ምን ነፃነት አግኝተዋል? ይህስ እንዴት ሊገኝ ቻለ?

● ዓለም ያላትን ዓይነት ነፃነት የሚፈልጉ ምን ይደርስባቸዋል?

● ከመጥፎ ባልንጀርነት መራቅ በጣም የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? የአዳምን ምሳሌ ባለመከተል መጥፎ የሚባለው ምን ስለመሆኑ የማንን ውሳኔ እንቀበላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]