በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ እውነተኛው አምላክ እንደመሆኑ ከፍ ከፍ አድርገው

ይሖዋ እውነተኛው አምላክ እንደመሆኑ ከፍ ከፍ አድርገው

ምዕራፍ 2

ይሖዋ እውነተኛው አምላክ እንደመሆኑ ከፍ ከፍ አድርገው

1. (ሀ) እውነተኛው አምላክ ማን ነው? (ለ) ስለ እርሱ እየተማርን ስንሄድ ሕይወታችን እንዴት ሊነካ ይገባዋል?

ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያን ወንድሞቹ ሲጽፍ:- “አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ ለእኛስ . . . አንድ አምላክ አብ አለን። . . . አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 8:5, 6) ጳውሎስ “አንድ አምላክ” ብሎ የጠራው የሁሉም ነገሮች ፈጣሪ የሆነውን ይሖዋን ነው። (ዘዳግም 6:4፤ ራእይ 4:11) አድናቂ የሆኑ ሰዎች የይሖዋን ጠባዮችና ይሖዋ ለሰው ልጆች ያደረጋቸውን ነገሮች ሲያውቁ ወደ እርሱ የሚስብ ኃይለኛ ውስጣዊ ስሜት ያድርባቸዋል። ውጤቱስ? የጠለቀ አድናቆት ያሳደረባቸውን አምላክ በቃላቸውና በድርጊታቸው ከፍ ከፍ ለማድረግ ይገፋፋሉ። ለአምላክ ያላቸው ፍቅር እያደገ ሲሄድ ስለ እርሱ ለሌሎች እንዲናገሩ ከውስጥ ብርቱ ግፊት ይሰማቸዋል። ሰብዓዊ ሁኔታቸው የፈቀደላቸውንም ያህል እርሱን ለመምሰል ይፈልጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “እንግዲህ እንደተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ (የምትመስሉ) ሁኑ፣ በፍቅር ተመላለሱ” በማለት ሁላችንም እንደዚህ እንድናደርግ ያበረታታናል። (ኤፌሶን 5:1, 2) ይህንን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ይሖዋን በትክክል ማወቅ ያስፈልገናል።

ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ ነው?

2. እርሱን እንድናወድስ ከሚገፋፉን ታላላቅ ጠባዮቹ አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ የይሖዋ ዋና ዋና ጠባዮች በቀጥታ የተገለጹባቸው ብዙ ቦታዎች እናገኛለን። እነዚህን ጥቅሶች ስታነብ ጠባዮቹ ምን እንደሆኑና ለአንተ እንዴት በጣም እንደሚያስፈልጉህ ቆም ብለህ አስብ። ለምሳሌ ቀጥሎ ያሉትን ተመልከት:- “እግዚአብሔር ፍቅር ነው።” (1 ዮሐንስ 4:8) “መንገዱ ሁሉ የቀና ነው” ወይም እንደ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም “መንገዱ ሁሉ ፍትሕ ነው።” (ዘዳግም 32:4) ‘በይሖዋ ዘንድ ጥበብ አለ።’ (ኢዮብ 12:13) ‘የኃይሉ ብዛት ታላቅ ነው።’ (ኢሳይያስ 40:26) ስለ እነዚህ ጠባዮች ቁጭ ብለህ ስታስብ ለአምላክ ባለህ አድናቆት ተገፋፍተህ አታወድሰ⁠ው⁠ምን?

3. በጣም ማራኪ የሆኑት ሌሎቹ የይሖዋ ጠባዮች ምን ምን ናቸው?

3 መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎችም ስፍራዎች ከማራኪ ጠባዮቹ ጋር ሲያስተዋውቀን እንደሚከተሉት እያለ ይናገራል:- “[ይሖዋ (አዓት)] መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት ነው።” (ዘፀአት 34:6) “ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ደግ ነህ፣ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነህ።” (መዝሙር 86:5 አዓት) “[ይሖዋ (አዓት)] ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉ።” (2 ዜና 16:9) ‘እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያደላም . . . ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ የተወደደ ነው።’ (ሥራ 10:34, 35) ይሖዋ “በልግስና ይሰጣል” ደግሞም “ደስተኛ አምላክ ነው።” (ያዕቆብ 1:5፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት) ይህንን ወደር የለሽ አምላክ ማገልገልና ፍቅራዊ ክብካቤውን መቅመስ እንዴት ያነቃቃል!

4. (ሀ) ይሖዋ እንዴት ያለ አምልኮ ይፈልጋል? የዚህስ አስፈላጊነት የቱን ያህል ነው? (ለ) መዝሙር 34:3 በምን እንድንካፈል ይጋብዘናል?

4 ከጠባዮቹ ጋር አብሮ የሚሄድ አንድ ነገር አለ። ይሖዋ “ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ” እንድንሰጠው ይፈልጋል። (ዘፀአት 20:5 አዓት) እርሱ በሚቀበለው መንገድ ለማገልገል ከፈለግን ሙሉው አምልኮታችን ለእርሱ መሰጠት ይኖርበታል። ይሖዋን እንወዳለን ካልን ሰይጣን አምላክ የሆነለትን ዓለም ጭምር ልንወድ አንችልም። (1 ዮሐንስ 2:15–17፤ 2 ቆሮንቶስ 4:3, 4) የምንፈልገው ጻድቅ መስለን ለመታየት ብቻ ከሆነ ይሖዋ ይህንን ያየዋል። ምን እንደምናደርግ ብቻ ሳይሆን ስለዚያ ነገር ምን እንደሚሰማንና ምን ዓይነት ሰው ለመሆን እየሞከርን እንዳለን በደንብ አድርጐ ያውቃል። ለጽድቅ እውነተኛ ፍቅር ካለን እርሱም ይረዳናል። (ኤርምያስ 17:10፤ ምሳሌ 15:9) በምድር የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ሲያውቁ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙራዊ “[ይሖዋን (አዓት)] ከእኔ ጋር ታላቅ አድርጉት፤ በአንድነትም ስሙን ከፍ ከፍ እናድርግ” ብሎ ያቀረበውን ጥሪ በደስታ ተቀብለዋል። (መዝሙር 34:3) አንተ ከእነዚህ አንዱ ነህን?

5. የይሖዋን አጠቃላይ ባሕርይ ለማጥናት ከምናደርገው ምርምር ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም የሚረዳን ምንድን ነው?

5 አስገራሚ ጠባዮቹን ቀረብ ብለህ ከመረመርካቸው ስለ እርሱ ለመናገር ያለህ ፍላጐት ይበልጥ ጥልቅ እየሆነ ይሄዳል፤ እርሱን ለመምሰል ለምታደርገውም ጥረት የሚረዳህ ኃይል ታገኛለህ። (1) እያንዳንዱ ጠባይ ምን እንደሆነና ከሌሎቹ ጠባዮቹ በምን እንደሚለይ (2) ይሖዋ ያንን ጠባይ እንዴትና ለማን እንዳሳየ (3) አንተም ያንን ጠባይ እንዴት ልታሳይ እንደምትችል ወይም አመለካከትህን እንዴት ሊነካው እንደሚገባ ለማወቅ ሞክር።

6. ፍቅርን እንደ ምሳሌ አድርገህ በመውሰድ የይሖዋን ጠባዮች እንዴት ልትመረምር እንደምትችል አሳይ። ይህንንም በዚህ አንቀጽ መጨረሻ ያሉትን ጥያቄዎች በመመለስ አሳይ፣ ከመልሶችህ ጋር ጥቅሶች ጨምረህ አቅርብ።

6 እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ እንውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ሲል ምን ማለቱ ነው? (1 ዮሐንስ 4:8) የተለያየ ዓይነት ፍቅር አለ። እዚህ ጥቅስ ላይ የገባው ግሪክኛ ቃል አጋፔ  ሲሆን ይሖዋ አምላክ ራሱ የሚያሳየው በደረጃው ከሁሉ የላቀው የፍቅር ዓይነት ነው። ይህን ዓይነቱን ፍቅር ማሳየት ራስ ወዳድነትን ፈጽሞ ማስወገድ ማለት ነው። ይህን በአእምሮህ ይዘህ ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን ጥያቄዎች አውጥተህ እንድታነባቸው በቀረቡት ጥቅሶች አማካይነት ለመመለስ ሞክር:-

ይህ ጠባይ በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ የታየው እንዴት ነው? (ሥራ 14:16, 17)

ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ያሳየበት ከሁሉ የሚበልጠው ምሳሌ ምንድን ነው? (ዮሐንስ 3:16) ይሖዋ ይህንን ያደረገው ሰው ጥሩ ስለሆነ ነውን? (ሮሜ 5:8)

ይሖዋ በልጁ በኩል ያደረገልን ሁሉ ሕይወታችንን እንዴት እንድንጠቀምበት ሊያደርገን ይገባል? (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15, 18, 19)

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን ይህንን ዓይነት ፍቅር ለሌሎች ክርስቲያኖች በምን መንገዶች ልናሳይ እንችላለን? (1 ቆሮንቶስ 13:4–7፤ 1 ዮሐንስ 4:10, 11፤ 3:16–18)

ለሌላ ለማን ጭምር ፍቅር ማሳየት አለብን? እንዴትስ? (ማቴዎስ 5:43–48፤ 28:19, 20፤ ገላትያ 6:10)

7. የግል ጥናት ስታደርግ ስለ ሌሎቹ የይሖዋ ጠባዮች ተመሳሳይ ማብራሪያ ለማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

7 ሌሎቹንም የይሖዋ ጠባዮች መርምረህ ለማወቅ ትፈልጋለህን? የግል ጥናት ስታደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ “ፍትሕ” እና “ጥበብ” የሚሉትን ጠባዮች መርምር። በኋላም “ፍቅራዊ ደግነት” እና “ምሕረት” በሚል አርዕስት ልትመራመር ትችላለህ። በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች የአርዕስት ማውጫ (ኢንዴክስ) እና በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ማውጫ (ኮንኮርዳንስ) ተጠቅመህ ብትመረምር ሰፊ ዕውቀት ልታገኝ ትችላለህ።

ሌሎች ስለ አምላክ እውነቱን እንዲማሩ እርዳቸው

8. (ሀ) የዓለም ሕዝቦች የትኞቹን አማልክት አምልከዋል? (ለ) ከዚህ ሁሉ ዝብርቅ በስተኋላ ያለው ማን ነው? ለምንስ እንደዚያ ትላለህ?

8 የእውነተኛውን አምላክ አምልኮ በመቃረን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች አማልክት በሰዎች ይመለካሉ። ሕዝበ ክርስትና ከእርሷ በፊት ባቢሎናውያን፣ ግብፃውያን፣ ሂንዱዎችና ቡድሂስቶች ሲያስተምሩት የነበረውን የሥላሴን ትምህርት በአራተኛው መቶ ዘመን ተቀብላለች። ስለ አምላክ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ከመኖሩም ሌላ ኃይለኛ መሪዎች፣ ታዋቂ ስፖርተኞችና ዝነኛ ዘፋኞች እንደ ጣዖት ተመልከዋል። ሰዎች ገንዘብን፣ ራሳቸውንና ፆታን በጋለ ስሜት አምልከዋል። ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ ያለው ማን ነው? “የዚህ ዓለም አምላክ” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 1 ቆሮንቶስ 10:20) እርሱም ባለ በሌለ የተንኮል ዘዴ ሁሉ እየተጠቀመ ሰዎችን ከይሖዋ ለማራቅ አለዚያም አምልኮአቸውን ለመከፋፈል ይሞክራል።

9. ማንኛውንም ሰው ስለ አምላክ እውነቱን እንዲያውቅ የምንረዳበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው?

9 ክርስቲያን ነን ባዮች ወይም የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች የሆኑትን እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ስለ አምላክ እውነቱን እንዲያውቁ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን? እጅግ በጣም ጥሩ ከሆኑት መንገዶች አንዱ እውነተኛው አምላክ ማንና ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ማብራሪያ ሰዎቹን ሊረዳ በሚችል መንገድ ማሳየቱ ነው። ከዚያም በሕይወታችን ውስጥ አምላካዊ ጠባዮችን በማንፀባረቅ የሰጠነውን ትምህርት በተግባር መደገፍ ያስፈልገናል። — 1 ጴጥሮስ 2:12

10. አንድን የሥላሴ አማኝ ስናነጋግር ምን ብሎ እንደሚያምን በትክክል እንደምናውቅ አድርገን ማሰብ የሌለብን ለምንድን ነው?

10 ነገር ግን የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አባል የሆኑ አንዳንድ ሰዎች የሥላሴ እምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው ብለው ቢከራከሩህስ? በመጀመሪያ አብያተ ክርስቲያናት ስለ ሥላሴ የሚሰጡት ማብራሪያ ቢኖርም ብዙ ሰዎች የራሳቸው የሆነ አስተሳሰብ እንዳላቸው መገንዘብ አለብህ። ስለዚህ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ጋብዛቸው። ከዚያ በኋላ እምነታቸውን ከራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንዲያስተያዩ እርዳቸው። ከጊዜ በኋላ የቤተክርስቲያኑን ትምህርት የአምላክ ቃል ከሚሰጠው ትምህርት ጋር እንዲያወዳድሩ አበረታታቸው።

11. በአንቀጹ ያሉትን አምስት ነጥቦች አንድ በአንድ በማንሳት የሥላሴ ትምህርት ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ እንደሌለው ለማስረዳት በአንቀጹ ውስጥ ባሉት ጥያቄዎችና ጥቅሶች ተጠቀም።

11 ቅን ሰዎችን የመርዳት ፍላጐት በአእምሮህ በመያዝ ከዚህ በታች ባሉት ጥቅሶች ተጠቅመህ ጥቅሶቹ ያሉባቸውን ነጥቦች እንዴት ማስረዳት እንደምትችል ተመራመር:-

() አንዳንድ የሥላሴ አማኞች ሦስት መለኮታዊ አካሎች (ይኸውም አባት፣ ልጅና መንፈስ ቅዱስ ) አሉ፤ ሆኖም አምላክ አንድ ብቻ ነው የሚለውን ሐሳብ አጥብቀው ይደግፋሉ።

ነገር ግን ሥራ 2:4, 17 “መንፈስ ቅዱስ” ራሱን የቻለ አንድ ሕያው አካል መሆኑን ያሳያልን?

ቀጥሎ ባሉት ጥቅሶች ውስጥ ስንት አካሎች እንደተጠቀሱ ማስተዋል የሚረዳው ለምንድን ነው? (ዮሐንስ 17:20–22፤ ሥራ 7:56፤ ራእይ 7:10)

() አንዳንድ ሰዎች “የሥላሴ” ክፍል የሆኑት አካሎች በክብር እኩል ናቸው፣ አንዱ ከሌላው አይበልጥም፤ አያንስም፤ እኩል ስልጣን አላቸው፤ እኩል ዘላለማውያን ናቸው ብለው ያምናሉ።

ቅዱሳን ጽሑፎች በዚህ አባባል ይስማማሉን? (ለመልሱ ዮሐንስ 14:28፤ ማቴዎስ 24:36፤ ራእይ 3:14 ተመልከት)

() አንዳንድ ሰዎች “የሥላሴ” እምነት ማስረጃ ነው ብለው ዮሐንስ 1:1ን ይጠቅሳሉ። በግሪክኛው ምንባብ እዚህ ላይ “አምላክ ” ከሚለው ቃል በፊት ልክ እንደ እንግሊዝኛ “a ” የሚል ምንነትን ወይም ማንነትን የማይወስን ቃል ስላልገባ ጥቅሱ “ቃልም እግዚአብሔር ነበር ” ተብሎ እንጂ “ቃልም አምላክ ነበር ” ተብሎ መነበብ የለበትም ብለው ይከራከራሉ

ነገር ግን ዮሐንስ 1:1 የሚናገረው ስለ ስንት አካሎች ነው? ስለ ሦስት ወይስ ስለ ሁለት? ዮሐንስ 1:18 ከሥላሴ ትምህርት ጋር የሚጋጨው እንዴት ነው?

እርግጥ ነው፤ ግሪክኛ ቋንቋ ልክ እንደ እንግሊዝኛ ከቃላት በፊት የሚገባ “a” የሚል ምንነትን ወይም ማንነትን የማይወስን ቃል የለውም። ሆኖም ብዙ ቋንቋዎች ይህ ቃል አላቸው። ሐሳቦችን በትክክል ለመግለጽ ቃሉ በእነዚያ ቋንቋዎች ይሠራበታል። እንግዲያው ዮሐንስ 1:1 በሚተረጐምበት ጊዜ “a” የሚል ቃል ማስገባቱ ስሕተት እንደሆነ የሚሰማው ሰው ቢኖር በኪንግ ጄምስ እና በሌሎች ትርጉሞች በሥራ 28:6 ላይ እንዳይገባ ይፈልግ ይሆን? (አን አሜሪካን ትራንስሌሽን የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው ዮሐንስ 1:1ን “ቃልም መለኰታዊ ነበር” (ማለትም አምላክ ያሉት ዓይነት መለኰታዊ ባሕርዮች አሉት) በማለት በሌላም መንገድ ማስቀመጥ ይቻላል።

(የሥላሴ አማኞች በዘፍጥረት 1:1, 26 ላይ “እግዚአብሔር ” ተብሎ የተተረጐመው የዕብራይስጥ ቃል ኤሎሂም ሲሆን ቃሉ ብዙ ቁጥር ነው። ስለዚህ “እግዚአብሔሮች” ማለት ነው ብለው ይከራከራሉ።

ይህስ “በአንድ አምላክ ሦስት መለኮታዊ አካሎች አሉ ” የሚለውን ትምህርት የማይደግፈው ለምንድን ነው?

ቃሉ በዘፍጥረት 1:1 ላይ “ሥላሴን” የሚያመለክት ከሆነ በመሳፍንት 16:23 ላይ ምን ያመለክታል? እዚህ ላይ ኤሎሂም አንድን አምላክ ለማመልከት ገብቷል። ከቃሉ ጋር የገባው የዕብራይስጥ ግሥም ነጠላ ቁጥር እንጂ ብዙ ቁጥር አይደለም።

ታዲያ የዕብራይስጡ ጽሑፍ በእነዚህ ጥቅሶች ላይ አምላኮች የሚለውን ቃል የተጠቀመበት ለምንድን ነው? ምክንያቱም የዕብራይስጥ ቋንቋ ከፍ ያለ ማዕረግን ወይም አክብሮትን የሚገልጽበት አንዱ መንገድ ይህ ስለሆነ ነው። ቃሉ የሚያመለክተው ከአንድ አካል በላይ ቢሆን ኖሮ አብረው ያሉት ግሦችም የብዙ ቁጥር ይሆኑ ነበር። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ግን ግሦቹ ነጠላ ቁጥር ናቸው።

() አብያተ ክርስቲያናት ለኢየሱስ ከፍተኛ ትኩረት ስለሚሰጡት (እንዲሁም ከብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይሖዋ የሚለው ስም እንዲወጣ ስለተደረገ ) አንዳንድ ሰዎች አምላክ ወይም እግዚአብሔር የሚለው ቃል ሲጠራ ወደ አእምሮአቸው የሚመጣው ኢየሱስ ብቻ ነው።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ በአምልኮ ረገድ ልንከተለው የሚገባንን ምን ምሳሌ ትቶልናል? (ሉቃስ 4:8)

12. ኢየሱስ አባቱን “አንተ ብቻ አምላክ የሆንህ” ወይም “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ” ብሎ መጥራቱ ትክክል የሆነው ለምንድን ነው?

12 ቅዱሳን ጽሑፎች ኢየሱስን “አምላክ” እንዲሁም “ኃያል አምላክ” ብለው ቢጠሩትም እርሱ አባቱን “አምላኬና አምላካችሁ” ብሎ በመጥራት ከሁሉ በላይ መሆኑን አስታውቋል። (ዮሐንስ 1:1፤ 20:17፤ ኢሳይያስ 9:6) ሙሴ ቀደም ብሎ “እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ነው፣ ከእርሱ በቀር ሌላ የለም” ሲል በተናገረው ቃል መስማማቱን ኢየሱስ አሳይቷል። (ዘዳግም 4:35 አዓት) ይሖዋ በሰዎች ዘንድ ከሚመለኩት ጣዖታት፣ እንደ አምላክ ተደርገው ከሚታዩት ሰዎችና ከሰይጣን ዲያብሎስ ፈጽሞ የተለየ አምላክ ነው። እርሱ “እውነተኛው አንድ አምላክ” ብሎ ኢየሱስ እንደጠራው ስለሆነ ከእነዚያ ሁሉ የተለየ ነው። — ዮሐንስ 17:3

‘በይሖዋ ስም መሄድ’

13, 14. ይሖዋን ማወቅና በስሙ መሄድ ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?

13 ብዙ ሰዎች ስለ አምላክ ማንነት ለብዙ ዓመታት ግራ ገብቷቸው ከኖሩ በኋላ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ የግል ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲያዩ በጣም ይደሰታሉ። (ዘፀአት 6:3 የ1879 እትም) ይሁን እንጂ ይህ ዕውቀት ለዘለቄታው የሚጠቅማቸው ‘በይሖዋ ስም ለዘላላም ከሄዱ’ ብቻ ነው። (ሚክያስ 4:5) ይህም የይሖዋን ስም ማወቅ ወይም የይሖዋ ምሥክር ተብሎ መጠራት ማለት ብቻ አይደለም።

14 መዝሙር 9:10 የአምላክ ስም ለእኛ ሊኖረው የሚገባውን ትርጉም ሲገልጽ “ስምህን የሚያውቁ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ” ይላል። ይህ ምን ማለት ነው? ይሖዋ የሚለውን ስም ያወቀ ሁሉ ወዲያው በይሖዋ ይታመናል ማለት ስላልሆነ ቃሉ ከዚያ የበለጠ ትርጉም አለው። እዚህ ላይ የአምላክን ስም ‘ማወቅ’ ማለት ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ አንደሆነ መረዳትን፣ ሥልጣኑን ማክበርንና ትእዛዛቱን መጠበቅን ያጠቃልላል። በተመሳሳይም ‘በይሖዋ ስም መሄድ’ ሲባል ራስን ለእርሱ መወሰንን፣ ይሖዋን እያመለኩ እርሱን በሚወክል መንገድ መኖርንና ሕይወትን ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ በትክክል መጠቀምን ያጠቃልላል። (ሉቃስ 10:27) ታዲያ እንደዚህ እያደረግህ ነውን?

15. ይሖዋን ለዘላለም እንድናገለግለው ከተፈለገ ይህን ማድረጉ ግዴታችን እንደሆነ ከማወቃቸን በተጨማሪ ምን ያስፈልገናል?

15 ይሖዋን ለዘላለም እንድናገለግለው ከተፈለገ ይህን ማድረጉ ግዴታችን መሆኑን ማወቃችን ብቻ በቂ ግፊት አይሆንም። ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋን ለብዙ ዓመታት ሲያገለግል የነበረውን ጢሞቴዎስን “ለአምላክ ያደሩ መሆንን ዓላማህ አድርገህ ራስህን አሰልጥን” ብሎ አጥብቆ አሳስቦታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:7 አዓት) ለአምላክ ያደሩ መሆን ለእርሱ ያለን አድናቆት የሚቀሰቅስብን ከልብ የሚመነጭ ነገር ነው። “ለአምላክ ያደሩ መሆን” ይሖዋን ራሱን በጥልቅ ማክበር ማለት ሲሆን ለእርሱና ለመንገዶቹ ካለን አድናቆት የተነሳ ከእርሱ ጋር በፍቅር መጣበቃችንን ያመለክታል። ይህ ጠባይ ሁሉም ሰው ስሙን በከፍተኛ ክብር ይዞ ለማየት እንድንመኝ ያደርገናል። በእውነተኛው አምላክ በይሖዋ ስም ለዘላለም እንድንሄድ ከተፈለገ “ለአምላክ ያደሩ መሆንን” የሕይወታችን ግብ ወይም ዓላማ ማድረግ ይኖርብናል። — መዝሙር 37:4፤ 2 ጴጥሮስ 3:11

የክለሳ ውይይት

● ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ ነው? እያንዳንዱ ጠባዩ ግልጽ ሆኖ ሲገባን እንዴት እንጠቀማለን?

● ሌሎች ሰዎች ስለ አምላክ እውነቱን እንዲያውቁ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?

● ይሖዋን ‘ማወቅ’ እና ‘በስሙ መሄድ’ ምን ማለት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]