በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ድርጅቱን የሚመራው እንዴት ነው?

ይሖዋ ድርጅቱን የሚመራው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 15

ይሖዋ ድርጅቱን የሚመራው እንዴት ነው?

1. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ድርጅት ምን የሚገልጽልን ነገረ አለ? ይህስ ለእኛ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ይሖዋ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት ጽሑፎች ውስጥ ስለ አስደናቂው ሰማያዊ ድርጅቱ ልዩ ልዩ የዕውቀት ጭላንጭል ሰጥቶናል። (ኢሳይያስ 6:2, 3፤ ሕዝቅኤል 1:1, 4–28፤ ዳንኤል 7:9, 10, 13, 14) መንፈሳውያን ፍጡሮችን ለማየት ባንችልም ይሖዋ ቅዱሳን መላእክቱ የሚሠሯቸው ነገሮች እዚህ ምድር ላይ ያሉትን እውነተኛ አምላኪዎቹን በምን በምን መንገድ እንደሚነኩ ጠቁሞልናል። (ዘፍጥረት 28:12, 13፤ 2 ነገሥት 6:15–17፤ መዝሙር 34:7፤ ማቴዎስ 13:41, 42፤ 25:31, 32) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ የሚታየው የይሖዋ ድርጅት እንዴት ያለ እንደሆነ ይገልጻል፤ ይሖዋ እንዴት እንደሚመራው እንድናስተውል ይረዳናል። ስለ እነዚህ ነገሮች እውነተኛ መንፈሳዊ ማስተዋል ማግኘታችን ‘ይሖዋን ሙሉ በሙሉ እንድናስደስትና ለእርሱ እንደሚገባ ሆነን ለመመላለስ’ ይረዳናል። — ቆላስይስ 1:9, 10

በዓይን የሚታየውን የድርጅቱን ክፍል ለይቶ ማወቅ

2. በ33 እዘአ ከዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት ወዲህ የአምላክ ጉባኤ ሆኖ የኖረው የትኛው ነው?

2 የእሥራኤል ሕዝብ ለ1, 545 ዓመታት ያህል የአምላክ ጉባኤ ሆኖ ነበር። ነገር ግን የሕጉን ቃል ኪዳን ሳይፈጽሙ ቀሩ፤ የአምላክንም ልጅ አንቀበልም አሉ። ስለዚህ ይሖዋ አዲስ ጉባኤ አቋቁሞ ከእርሱ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን አደረገ። ቅዱሳን ጽሑፎች ይህንን ጉባኤ የክርስቶስ “ሙሽራ” ብለው የሚጠሩት ሲሆን አምላክ ከልጁ ጋር በሰማይ እንዲተባበሩ የመረጣቸውን 144, 000 አባላት ያቀፈ ጉባኤ ነው። (ኤፌሶን 5:22–32፤ ራእይ 14:1፤ 21:9, 10) በ33 እዘአ በጴንጠቆስጤ ዕለት የመጀመሪያዎቹ አባላት በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተዋል። ይሖዋም ከዚያ በኋላ ዓላማውን ለማስፈጸም የሚጠቀምበት ጉባኤ ይህ መሆኑን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የማያሻማ ማረጋገጫ ሰጥቷል። — ዕብራውያን 2:2–4

3. ዛሬ የሚታየው የይሖዋ ድርጅት የሚባሉት እነማን ናቸው?

3 ዛሬ ከ144, 000 መካከል በምድር ላይ ጥቂት ቀሪዎች ብቻ ይገኛሉ። ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም “የሌሎች በጐች” ክፍል የሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከእነርሱ ጋር በመተባበር ተግተው ይሠራሉ። መልካሙ እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን “ሌሎች በጐች” በመንፈስ ከተቀቡት ቀሪዎች ጋር ቀላቅሎ በእርሱ እረኝነት ሥር የሚመራ “አንድ መንጋ” አድርጓቸዋል። (ዮሐንስ 10:11, 16፤ ራእይ 7:9, 10) እነዚህ ሁሉ አንድ ላይ ተጠቃልለው ኅብረት ያለው አንድ ድርጅት ይኸውም ዛሬ ያለው የሚታየው የይሖዋ ድርጅት ሆነዋል።

ድርጅታዊ መዋቅሩ ቲኦክራቲካዊ ነው

4. ድርጅቱን ማን ይመራዋል? እንዴትስ?

4 “የሕያው አምላክ ጉባኤ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ አነጋገር ድርጅቱን ማን እንደሚመራው ግልጽ ያደርግልናል። ድርጅቱ ቲኦክራቲካዊ ማለትም አምላክ የሚመራው ነው። ይሖዋ በዓይን የማይታይ የጉባኤው ራስ አድርጐ በሾመው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ አማካኝነት ለሕዝቡ መመሪያ ይሰጣል። — 1 ጢሞቴዎስ 3:14, 15 አዓት፤ ኤፌሶን 1:22, 23፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

5. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤው ሰማያዊ አመራር እንዳለው የታየው እንዴት ነው? (ለ) እስከ ዛሬ ድረስ የጉባኤው ራስ ክርስቶስ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?

5 በ33 እዘአ በጴንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ የመጀመሪያዎቹን የጉባኤው አባላት ለሥራ ባንቀሳቀሳቸው ጊዜ እንደዚህ ያለው ቲኦክራቲካዊ አመራር በጣም ግልጽ ሆኖ ታይቷል። (ሥራ 2:1–4, 32, 33) በተጨማሪም የይሖዋ መልአክ ምሥራቹ ወደ አፍሪካ እንዲስፋፋ ሁኔታዎችን ባቀነባበረ ጊዜ ታይቷል። (ሥራ 8:26–39) ከዚህም ሌላ የጠርሴሱ ሳውል ወደ ክርስትና ሲለወጥ የኢየሱስ ድምጽ መመሪያ በሰጠ ጊዜና በአሕዛብ መካከል ሚስዮናዊ ሥራ በጀመረ ጊዜ በጉባኤው ላይ አምላካዊ አመራር ታይቷል። (ሥራ 9:3–7, 10–17፤ 10:9–16, 19–23፤ 11:12) ይሁን እንጂ አስፈላጊው መመሪያ ሁልገዜ በዚህ መንገድ በተአምራዊ ሁኔታ አልተሰጠም። ከጊዜ በኋላ ከሰማይ ድምጽ መሰማቱ፣ መላእክት ለሰዎች መታየታቸውና ተአምራዊ የመንፈስ ስጦታዎች መሰጠታቸው ቆመ። ሆኖም ኢየሱስ “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ብሎ ለታማኝ ተከታዮቹ ቃል ገብቶ ነበር። ማስረጃዎቹም በእርግጥ ከእነርሱ ጋር እንዳለ ያረጋግጣሉ። (ማቴዎስ 28:20፤ 1 ቆሮንቶስ 13:8) የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ የጉባኤው ራስ መሆኑን ተቀብለው የሚኖሩ ከመሆናቸውም በላይ ያለ እርሱ እርዳታ ይህ ሁሉ ተቃውሞ እያለ የመንግሥቱን መልእክት መስበካቸውን ሊቀጥሉ እንደማይችሉ ያውቃሉ።

6. (ሀ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚባሉት እነማን ናቸው? ለምንስ? (ለ) ኢየሱስ ለዚያ “ባሪያ” ምን ሥራ ሰጥቶታል?

6 ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ራሱ ልዩ ኃላፊነት ስለሚሰጠው “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለደቀመዛሙርቱ ተናግሯል። ኢየሱስ በሰጠው መግለጫ መሠረት ያ “ባሪያ” ጌታው ወደ ሰማይ በሚሄድበት ጊዜም ሆነ ተመልሶ ሲመጣ በሕይወት ይገኛል። ባሪያው አንድ ግለሰብ ቢሆን ኖሮ እንደዚህ ሊባልለት አይችልም ነበር። ነገር ግን ታማኙን የክርስቶስ የቅቡዓን ጉባኤ በአጠቃላይ ስንመለከተው ይህ አነጋገር ለእርሱ የሚስማማ ሆኖ ይገኛል። ኢየሱስ በገዛ ራሱ ደም እንደሚዋጃቸው ያውቅ ነበር። ስለዚህ እነርሱን በጥቅል “ባሪያ” ብሎ መጥራቱ ትክክል ነበር። ኢየሱስ ለእነዚህ ተከታዮቹ ሥራ ሰጥቷቸዋል። ሁሉም ደቀመዛሙርት እንዲያደርጉና ለእነዚህ ደቀመዛሙርት መንፈሳዊ “ምግባቸውን በጊዜው” እያዘጋጁ ደረጃ በደረጃ በመንፈሳዊ እንዲመግቧቸው አዟል። ይህ ሹመታቸው በ33 እዘአ በጴንጠቆስጤ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ ተረጋግጦላቸዋል። — ማቴዎስ 24:45–47፤ 28:19, 20፤ 1 ቆሮንቶስ 6:19, 20፤ ከኢሳይያስ 43:10 ጋር አወዳድር።

7. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ “ባሪያው” ምን ተጨማሪ ኃላፊነቶች አሉት? (ለ) በዚህ መገናኛ መሥመር በኩል የሚመጣልንን መመሪያ ተቀብለን በሥራ ማዋል በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

7 ጌታው ሲመለስ “ባሪያው” ሥራውን በታማኝነት እያከናወነ ከተገኘ ተጨማሪ ኃላፊነቶች እንደሚሰጡት ኢየሱስ ተናግሯል። ከዚያ በኋላ ያሉት ዓመታት ዓለም አቀፍ ምሥክርነት የሚሰጥባቸውና ከመጪው “ታላቅ መከራ” ለመዳን ይሖዋን የሚያመልክ “እጅግ ብዙ ሰዎች” የሚሰበሰቡባቸው ጊዜያት ናቸው። (ማቴዎስ 24:14፤ ራእይ 7:9, 10) እነርሱም መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልጋቸዋል። ምግቡ በጥቅል “ባሪያ” ተብለው በተጠሩት በመንፈስ በተቀቡት የክርስቶስ አገልጋዮች አማካኝነት ይቀርብላቸዋል። ይሖዋን ለማስደሰት ከፈለግን እርሱ በዚህ መገናኛ መሥመር በኩል የሚሰጠንን መመሪያ መቀበልና ሙሉ በሙሉ መፈጸም ያስፈልገናል።

8, 9. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለ መሠረተ ትምህርት የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስና የምሥራቹን ስብከት በሚመለከት አስፈላጊውን አመራር ለመስጠት ምን ዝግጅት ነበረ? (ለ) ዛሬስ ምን ተመሳሳይ ዝግጅት አለ?

8 እርግጥ አልፎ አልፎ መሠረተ ትምህርትንና የአሠራርን ሥርዓት የሚመለከቱ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ምን ይደረጋል? የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ወደ ክርስትና የገቡ አሕዛብ ማሟላት ስለሚኖርባቸው ብቃት የተነሳው ክርክር እንዴት መፍትሔ እንዳገኘ ይነግረናል። አከራካሪው ጥያቄ ማዕከላዊ የአስተዳደር አካል ሆነው ለሚያገለግሉት በኢየሩሳሌም ለነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ተላከ። እነዚያ ሽማግሌዎች ፈጽሞ የማይሳሳቱ ሰዎች አልነበሩም። ከዚያ በፊት አንድም ጊዜ ያልተሳሳቱ ሰዎች አይደሉም። (ከገላትያ 2:11–14 ጋር አስተያይ) ቢሆንም አምላክ ተጠቅሞባቸዋል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች በጉዳዩ ላይ የሚሰጡትን ሐሳብና የአምላክ መንፈስ የአሕዛብን መስክ እንደከፈተ የሚያሳየውን ማረጋገጫ ከመረመሩ በኋላ ውሳኔ አስተላለፉ። አምላክ ያንን ዝግጅት ባርኮታል። (ሥራ 15:1–29፤ 16:4, 5) ጌታ ራሱ ከሰጠው ትእዛዝ ጋር በሚስማማ መንገድ ምሥራቹን በበለጠ ለማስፋፋት በዚያ ማዕከላዊ አካል ግለሰቦች ወደ አንዳንድ ቦታ ይላኩ ነበር። — ሥራ 8:14፤ ገላትያ 2:9

9 በዘመናችን ያለው የአስተዳደር አካል ከልዩ ልዩ አገሮች ከመጡ በመንፈስ ከተቀቡ ወንድሞች የተውጣጣ ነው። መቀመጫውም በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ነው። የአስተዳደር አካሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ በታች ሆኖ የንጹህ አምልኮን ጉዳዮች ያስፈጽማል። እነዚህ ወንድሞች ሐዋርያው ጳውሎስ እንደነበረው ዓይነት አመለካከት አላቸው። ጳውሎስ ለክርስቲያን ወንድሞቹ መንፈሳዊ ምክር ሲልክ “ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደለንም። በእምነታችሁ ቆማችኋልና” ብሎ ጽፎላቸዋል። — 2 ቆሮንቶስ 1:24

10. (ሀ) ማን ሽማግሌ ወይም ዲያቆን እንደሚሆን የሚወሰነው እንዴት ነው? (ለ) በእነዚህ ቦታዎች እንዲያገለግሉ ከተሾሙት ጋር መተባበር ያለብን እንዴት ነው?

10 ይህንን ቲኦክራቲካዊ ዝግጅት በዓለም ዙሪያ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ይቀበሉታል። በየቦታው ያሉት ጉባኤዎች በሙሉ ከአስተዳደር አካሉ ጋር በቅርቡ እየተባበሩ ይሠራሉ። ጉባኤው በጥሩ ሁኔታ እንዲካሄድ የሚረዱ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት እንዲሾሙላቸው የአስተዳደር አካሉን ይመለከታሉ። ሰዎች ለዚህ ዓይነቱ ሹመት የሚመረጡት በምን መሠረት ነው? ብቃቶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ተዘርዝረዋል። ሰዎቹን ለሹመት እጩ አድርገው የሚያቀርቡት ሽማግሌዎችም ሆኑ ለመሾም ሥልጣን የተሰጣቸው ሁሉ በብቃቶቹ መሠረት እንዲወስኑ በአምላክ ፊት ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1–10, 12, 13፤ 5:22፤ ቲቶ 1:5–9) በጉባኤ ውስጥ በድምጽ ብልጫ ምርጫ አይካሄድም። ከዚህ ይልቅ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሽማግሌዎችና ዲያቆናት በሚሾሙበት ጊዜ ሐዋርያት ያደርጉት የነበረውን በመከተል ወንድሞችን ለሹመት እጩ አድርገው የሚያቀርቡትም ሆኑ ሹመቱን የሚያጸድቁት የበላይ ተመልካቾች የአምላክ መንፈስ እርዳታ እንዲያገኙ ይጸልያሉ፤ በመንፈስ የተጻፈው ቃል የሚሰጠውንም መመሪያ ይመለከታሉ። (ሥራ 6:2–4, 6፤ 14:23፤ ከመዝሙር 75:6, 7 ጋር አወዳድር) የሽማግሌዎችን አመራር በመቀበል ሁላችን ‘ወደ እምነት አንድነት እንድንደርስ’ የሚረዱንን እነዚህን የክርስቶስ ፍቅራዊ “ስጦታዎች” እንደምናደንቅ ልናሳይ እንችላለን። — ኤፌሶን 4:8, 11–16

11. (ሀ) በቲኦክራቲካዊው ዝግጅት ውስጥ ሴቶች ምን ጠቃሚ አገልግሎት ያበረክታሉ? (ለ) ራሳቸውን መሸፈን የሚያስፈልጋቸው መቼ ነው? ለምንስ?

11 የጉባኤውን የኃላፊነት ቦታዎች ወንዶች እንዲይዙ ቅዱሳን ጽሑፎች መመሪያ ይሰጣሉ። ይህ ሥርዓት ሴቶችን ዝቅ አያደርግም፤ ምክንያቱም የሰማያዊ መንግሥት ወራሽ ከሆኑት መካከል ብዙ ሴቶች ይገኛሉ። ክርስቲያን ሴቶች በትሕትናቸው፣ በንጹሕ ምግባራቸውና ተግተው ቤተሰባቸውን በደንብ በመያዛቸው ለጉባኤው መልካም ስም አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ። (ቲቶ 2:3–5) ፍላጐት ያሳዩ አዲሶችን ፈልጐ ከድርጅቱ ጋር እንዲገናኙ በሚደረገው ጥረት አብዛኛውን ሥራ የሚሠሩት እነርሱ ናቸው። (መዝሙር 68:11 አዓት) ጉባኤውን ማስተማሩ ግን በተሾሙ ወንዶች የሚከናወን ተግባር ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:12, 13) ጉባኤው የሚያዘጋጀውን ስብሰባ ለመምራት የሚበቁ ወንዶች ባለመኖራቸው አንዷ ሴት ስብሰባውን ብትመራ ስትጸልይ ይሁን ስብሰባውን ስትመራ የራስ መሸፈኛ ታደርጋለች። * በዚህ መንገድ ኢየሱስ ለአባቱ በመገዛት ለሁላችን ያሳየውን ምሳሌ በመከተል ለይሖዋ ዝግጅት ያላትን አክብሮት ታሳያለች። — 1 ቆሮንቶስ 11:3–16፤ ዮሐንስ 8:28, 29

12. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ሽማግሌዎች ስለቦታቸው እንዴት ያለ አመለካከት እንዲኖራቸው ይመክራቸዋል? (ለ) ሁላችን በየትኛው አስደናቂ መብት ልንካፈል እንችላለን?

12 በዓለም ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ የያዘ ሰው በጣም ተፈላጊ እንደሆነ ሰው ተደርጎ ይታያል። በአምላክ ድርጅት ውስጥ ያለው ሥርዓት ግን “ከመካከላችሁ ትልቁ እንደ በታች ሆኖ የሚመላለሰው ነው” ይላል። (ሉቃስ 9:46–48 አዓት፤ 22:24–26) ስለሆነም ሽማግሌዎች ለመንጋው ምሳሌ እንዲሆኑ እንጂ የአምላክ ውርሻ የሆኑትን እንደ ጌታ እንዳይሆኑባቸው እንዲጠነቀቁ ቅዱሳን ጽሑፎች ይመክሯቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) የጽንፈ ዓለሙን የበላይ ገዥ በመወከል በትህትና በይሖዋ ስም የመናገሩና በየትም ሥፍራ ለሚገኙ ሰዎች ስለ መንግሥቱ የመስበኩ አስደናቂ መብት ግን ወንድ ሴት ሳይባል ለሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች የተሰጠ እንጂ ለጥቂት ምርጦች የተወሰነ አይደለም።

13. በተጠቀሱት ጥቅሶች እየተጠቀምህ በዚህ አንቀጽ መጨረሻ ባሉት ጥያቄዎች ላይ ሐሳብ ስጥ።

13 ራሳችንን “ይሖዋ የሚታየውን ድርጅቱ እንዴት እየመራ እንዳለ በእርግጥ ተረድቻለሁን? ዝንባሌዬ፣ ንግግሬና አድራጐቴ ይህንን ያንጸባርቃሉን?” እያልን ብንጠይቅ ጥሩ ነው። እያንዳንዳችን የሚከተሉትን ነጥቦች ብናሰላስልባቸው ራሳችንን በዚያ መንገድ ለመመርመር እንችላለን:-

ክርስቶስ የጉባኤው ራስ መሆኑን ተቀብለን ከልብ የምንገዛለት ከሆነ የሚከተሉት ጥቅሶች በሚያመለክቱት መሠረት ምን እያደረግን መሆን አለብን? (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ሉቃስ 21:34–36፤ ዮሐንስ 13:34, 35)

የድርጅቱ ክፍል የሆኑ በሙሉ ፍሬያማ ክርስቲያን ለመሆን በሚያደርጉት ጥረት የአምላክና የክርስቶስ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ምን ያህል ሊሰማቸው ይገባል? (ዮሐንስ 15:5፤ 1 ቆሮንቶስ 3:5–7)

ነገሮችን ጠቅላላው የወንድሞች ማኅበር በሚመለከታቸው መንገድ እንድናይ ብለው ሽማግሌዎች አስተሳሰባችንን ለማስተካከል ምክር ሲሰጡ ማን በደግነት እያሰበልን መሆኑን ማስተዋል አለብን? (ኤፌሶን 4:7, 8, 11–13፤ 2 ቆሮንቶስ 13:11)

“በባሪያው” ክፍልና በአስተዳደር አካሉ በኩል የሚቀርቡልንን መንፈሳዊ ስጦታዎች በአድናቆት ስንቀበል ለማን አክብሮት እያሳየን ነው? ስጦታዎቹን የሚያንቋሽሽ ቃል ብንናገርስ? (ሉቃስ 10:16፤ ከ3 ዮሐንስ 9, 10 ጋር አወዳድር)

የተሾሙ ሽማግሌዎችን በክፉ ቃል መንቀፍ የሌለብን ለምንድን ነው? (ሥራ 20:28፤ ሮሜ 12:10)

14. (ሀ) ለቲኦክራቲካዊው ድርጅት ባለን ዝንባሌ ምን እናሳያለን? (ለ) በዚህ ረገድ ዲያብሎስን ውሸታም ለማድረግና የይሖዋን ልብ ለማስደሰት ምን አጋጣሚዎች አሉን?

14 ይሖዋ ዛሬ ከእኛ ጋር ማንኛውንም ግንኙነት የሚያደርገው ክርስቶስ ራስ ሆኖ በተሾመበት በሚታየው ድርጅቱ በኩል ነው። ስለዚህ ለድርጅቱ ያለን ዝንባሌ ስለ ሉዓላዊነት በተነሳው አከራካሪ ጥያቄ በየትኛው ወገን እንደቆምን በተግባራዊ መንገድ ያሳያል። (ዕብራውያን 13:17) ሰይጣን ሁላችንም የምንሮጠው ለግል ጥቅም ነው ብሎ ይከራከራል። ከሁሉ በላይ የምናስበው ስለራሳችን ነው ባይ ነው። እንግዲያው የሰውን ትኩረት ወደ ራሳችን የሚስብ አንድም ነገር ከመናገር ወይም ከማድረግ እየተቆጠብን አስፈላጊ በሆነበት በማንኛውም መንገድ ለማገልገል ራሳችንን በደስታ ካቀረብን ዲያብሎስን ሐሰተኛ እናደርጋለን። ‘ለገዛ ጥቅማቸው ሲሉ ሌሎችን እንደሚክቡት’ ሰዎች እንዳንሆን እየተጠነቀቅን የሚመሩንን ወንድሞች የምናፈቅርና የምናከብር፤ እምነታቸውንም የምንከተል ከሆንን የይሖዋን ልብ ደስ እናሰኛለን። (ዕብራውያን 13:7፤ ይሁዳ 16) ለይሖዋ ድርጅት ተገቢ አክብሮት በመኮትኮትና እርሱ ያዘዘንን ሥራ በሙሉ ልባችን በመፈጸም አምላካችን በእርግጥ ይሖዋ እንደሆነ፤ በእርሱ አምልኮም አንድ እንደሆንን እናስመሠክራለን። — 1 ቆሮንቶስ 15:58

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 ይሁን እንጂ ከቤት ወደቤት እየሄደች በምትሰብክበት ጊዜ ራሷን መሸፈን አያስፈልጋትም ምክንያቱም ምሥራቹን የመስበኩ ኃላፊነት ለሁሉም ክርስቲያኖች የተሰጠ ነው። ነገር ግን ባሏ በተገኘበት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድትመራ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢያጋጥማት እርሱ ክርስቲያን እንኳን ባይሆን ራስዋ ስለሆነ ራሷን መሸፈን አለባት። በተጨማሪም ቀደም ብሎ የተቋቋመውን የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምትመራበት ጊዜ የግድ አስፈላጊ ሆኖ አንድ ራሱን የወሰነ የጉባኤ አባል ቢገኝ ራሷን ትሸፈናለች፤ ጸሎቱን ግን እርሱ ማድረግ አለበት።

ክለሳ ውይይት

● ዛሬ የሚታየው የይሖዋ ድርጅት የትኛው ነው? የድርጅቱስ ዓላማ ምንድን ነው?

● የጉባኤው ራስ ሆኖ የተሾመው ማን ነው? እርሱስ ፍቅራዊ አመራር የሚያደርግልን በየትኞቹ በዓይን በሚታዩ ዝግጅቶች አማካኝነት ነው?

● በድርጅቱ ውስጥ ላሉት ኃላፊነቶችና ሰዎች እንዴት ያለ ጤናማ ዝንባሌ መኮትኮት ይኖርብናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]