በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 9

መሪ እንዲሆን ከተሾመው መሲሕ መማር

መሪ እንዲሆን ከተሾመው መሲሕ መማር

አምላክ፣ የሰው ልጆችን የመምራት ሥልጣን ለመሲሑ እንደሚሰጠው ትንቢት ተናግሮ ነበር። አምላክ ምን ዓይነት መሪ እንደሚያስፈልገን ስለሚያውቅ ከሁሉ የተሻለውን መሪ መርጦልናል። ታዲያ መሲሑ ምን ዓይነት መሪ ነበር? ኃያል የጦር መሪ? የተዋጣለት ፖለቲከኛ? ታላቅ ፈላስፋ? ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚናገሩት ከሆነ መሲሑ በጣም ልዩ የሆነ ነቢይ ነበር፤ ይህ ነቢይ ኢየሱስ ክርስቶስ (ኢሳ) ነው።​—⁠ማቴዎስ 23:​10

አምላክ፣ ኢየሱስ ፍጹምና ቅዱስ ሆኖ እንዲወለድ አድርጓል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ፣ ኃጢአት እንዲሠራ ሰይጣን ያሳደረበትን ተጽዕኖ ተቋቁሟል። ኢየሱስ የአምላክን ኃይል፣ ፍትሕ፣ ጥበብና ፍቅር በትምህርቱም ሆነ በድርጊቱ ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። እስቲ ከኢየሱስ ምሳሌ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመልከት።

ኢየሱስ (ኢሳ) ራሱን ሳይቆጥብ ሌሎችን ረድቷል

ኢየሱስ ከአምላክ ያገኘውን ኃይል ሌሎችን ለመርዳት ተጠቅሞበታል። ኢየሱስ ለሰዎች ከልብ ያስብ ስለነበር ኃይሉን የተጠቀመበት እነሱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት ነበር። በአንድ ወቅት “እነዚህ ሰዎች . . . የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ” በማለት ተናግሮ ነበር። (ማርቆስ 8:⁠2) ከዚያም ኢየሱስ ከእሱ ለመማር የተሰበሰቡትን ብዙ ሰዎች በተአምር መገባቸው።

በተጨማሪም ኢየሱስ እያስተማረና “በሕዝቡ መካከል ያለውን ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እየፈወሰ” በየቦታው ይዘዋወር ነበር። (ማቴዎስ 4:​23) ከዚህ አንጻር ብዙ ሕዝብ ይከተለው የነበረ መሆኑ ምንም አያስገርምም፤ ደግሞም “ኃይል ከእሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለነበር ሕዝቡ ሁሉ ሊነካው ይፈልግ ነበር።” (ሉቃስ 6:​19) በእርግጥም ኢየሱስ የመጣው “ለማገልገልና በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል አይደለም።” (ማቴዎስ 20:​28) a የትኞቹ መሪዎች ናቸው ልክ እንደ ኢየሱስ ለሌሎች ሲሉ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉት?

ኢየሱስ ልጆችን ይወድ ነበር

ኢየሱስ የአምላክን ፍትሕ አንጸባርቋል። ኢየሱስ የአምላክን ሕግ በጥብቅ የተከተለ ከመሆኑም ሌላ ሕጉ የተሰጠበትን ዓላማ በሚገባ እንደተረዳ አሳይቷል። በሌላ አባባል ኢየሱስ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ አስቀድሞ እንደተገለጸው “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው” ብሎ የተናገረ ያህል ነው። (መዝሙር 40:⁠8) ኢየሱስ ሀብታም ድሃ፣ ወንድ ሴት ወይም ልጅ አዋቂ ሳይል ልክ እንደ አምላክ ሁሉንም ሰው በአክብሮትና ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ ይይዝ ነበር። በአንድ ወቅት ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ኢየሱስ ሲያመጡ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ገሥጸዋቸው ነበር። ኢየሱስ ግን “ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የአምላክ መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ነውና” አለ።​—⁠ማርቆስ 10:​14

ኢየሱስ በአምላክ ጥበብ እንደሚመራ አሳይቷል። ኢየሱስ ሰዎችን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ‘በሰው ውስጥ ያለውን ሐሳብ ያውቅ ነበር።’ (ዮሐንስ 2:​25) የኢየሱስ ጠላቶች እሱን አስረው ይዘው እንዲመጡ ሰዎችን በላኩ ጊዜ፣ የተላኩት ሰዎች እንኳ “ማንም ሰው እንደዚህ ተናግሮ አያውቅም” በማለት ተናግረው ነበር። ለመሆኑ ኢየሱስ ይህን ሁሉ ጥበብ ያገኘው ከየት ነበር? “የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው” በማለት ገልጿል።​—⁠ዮሐንስ 7:​16, 46

ኢየሱስ በርኅራኄ ተገፋፍቶ የታመሙትን ፈውሷል

ኢየሱስ የአምላክን ፍቅር አንጸባርቋል። ኢየሱስ ለሰዎች ከልብ ይራራ ነበር። “መላ ሰውነቱን የሥጋ ደዌ የወረሰው” አንድ ሰው “ጌታ ሆይ፣ ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ለምኖት ነበር። ኢየሱስም ለሰውየው በጣም ከማዘኑ የተነሳ “እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና ‘እፈልጋለሁ! ንጻ’ አለው። ወዲያውኑ የሥጋ ደዌው ለቀቀው።” (ሉቃስ 5:​12, 13፤ ማርቆስ 1:​41, 42) በእርግጥም ኢየሱስ ይህንን ምስኪን ሰው ከሥቃዩ ለመገላገል ልባዊ ፍላጎት እንዳለው አሳይቷል።

ኢየሱስ ለአንተም ያስብልሃል? ኢየሱስ ራሱ ለዚህ ጥያቄ መልሱን ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ።”​—⁠ማቴዎስ 11:​28, 29

ከኢየሱስ የተሻለ መሪ ልናገኝ አንችልም። ‘ከእኔ ተማሩ’ በማለት የመከረን ለዚህ ነው። ታዲያ ይህን አስደሳች ግብዣ ትቀበል ይሆን? ይህን ግብዣ መቀበልህ ሕይወትህን አስደሳች ያደርግልሃል።

a ስለ ቤዛው ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 27 ተመልከት።