በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 8

መሲሑ መጣ

መሲሑ መጣ

ነቢዩ ዳንኤል ትንቢት ከተናገሩ ከ500 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ መልአኩ ገብርኤል (ጂብሪል) የንጉሥ ዳዊት (ዳውድ) ዝርያ ለሆነች ማርያም (መርየም) የምትባል አንዲት ድንግል ተገለጠላት። ከዚያም “እጅግ የተባረክሽ ሆይ፣ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ይሖዋ ከአንቺ ጋር ነው” አላት። (ሉቃስ 1:​28) ማርያም ግን ፈርታ ነበር። የገብርኤል ሰላምታ ምን ትርጉም ይኖረው ይሆን?

ገብርኤል (ጂብሪል) መሲሑን እንደምትወልድ ለማርያም (ለመርየም) ነግሯታል

ገብርኤል እንዲህ አላት፦ “ማርያም ሆይ፣ በአምላክ ፊት ሞገስ ስላገኘሽ አትፍሪ። እነሆም፣ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። . . . ይሖዋ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ . . . ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” (ሉቃስ 1:​30-33) እንዴት ያለ አስደናቂ ዜና ነው! ማርያም ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የኖረውን “ዘር” ማለትም መሲሑን ልትወልድ ነው!

በቀጣዩ ዓመት ኢየሱስ (ኢሳ) በቤተልሔም ተወለደ። ኢየሱስ በተወለደበት ሌሊት አንድ መልአክ በአካባቢው ለነበሩ እረኞች የሚከተለውን የምሥራች ነገራቸው፦ “እነሆ፣ . . . ታላቅ ደስታ የሚያስገኝ ምሥራች እነግራችኋለሁ፤ በዛሬው ዕለት በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኋልና፤ እሱም . . . ክርስቶስ ነው።” (ሉቃስ 2:​10, 11) ቆየት ብሎም የኢየሱስ ቤተሰብ ወደ ናዝሬት በመሄድ በዚያ መኖር ጀመረ።

ኢየሱስ “30 ዓመት ገደማ” ሲሆነው ማለትም በ29 ዓ.ም. የአምላክ ነቢይ ሆኖ ማገልገል ጀመረ፤ ይህ ጊዜ መሲሑ እንደሚገለጥ ይጠበቅ የነበረበት ዓመት ነው። (ሉቃስ 3:​23) ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ከአምላክ እንደተላከ ተገንዝበው ነበር። “ታላቅ ነቢይ በመካከላችን ተነስቷል” በማለት ተናግረዋል። (ሉቃስ 7:​16, 17) ታዲያ ኢየሱስ ሰዎችን ምን አስተምሯል?

ኢየሱስ፣ ሰዎች አምላክን እንዲወዱና እንዲያመልኩ አስተምሯል፦ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ አምላካችን አንድ ይሖዋ ነው፤ አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።” (ማርቆስ 12:​29, 30) በተጨማሪም “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ” በማለት ተናግሯል።​—⁠ሉቃስ 4:8

ኢየሱስ፣ ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ አጥብቆ መክሯል፦ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ብሏል። (ማርቆስ 12:​31) በተጨማሪም “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው። ሕጉም ሆነ የነቢያት ቃል የሚሉት ይህንኑ ነው” በማለት አስተምሯል።​—⁠ማቴዎስ 7:​12

ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት በትጋት አስተምሯል፦ “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” ብሏል። (ሉቃስ 4:​43) የአምላክ መንግሥት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ቅዱሳን መጻሕፍት፣ የአምላክ መንግሥት ወደፊት መላዋን ምድር የሚገዛ በሰማይ የተቋቋመ መስተዳድር እንደሆነ ያስተምራሉ። አምላክ፣ የዚህ መንግሥት ንጉሥ እንዲሆን የሾመው መሲሑን ኢየሱስን ነው። አምላክ ለመሲሑ “የገዢነት ሥልጣን፣ ክብርና መንግሥት” እንደሚሰጠው ነቢዩ ዳንኤል በራእይ ተመልክተው ነበር። (ዳንኤል 7:​14) ይህ መንግሥት መላዋ ምድር ገነት እንድትሆን እንዲሁም የአምላክ አገልጋዮች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ያደርጋል። ታዲያ ከዚህ የበለጠ ምን አስደሳች ምሥራች አለ?