በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 6

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

አምላክ ምድርን የፈጠራት ለሰው ልጆች ተስማሚ መኖሪያ እንድትሆን ነው። ቃሉ “ሰማያት የይሖዋ ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” በማለት ይናገራል።​—⁠መዝሙር 115:​16

አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ከመፍጠሩ በፊት ምድር ላይ ኤደን ተብሎ የሚጠራ አንድ ትንሽ ቦታ መርጦ ስፍራውን ውብ የአትክልት ቦታ አደረገው። ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ከኤደን የሚመነጩ አራት ወንዞች እንደነበሩ ይናገራሉ። a የኤደን የአትክልት ሥፍራ ይገኝ የነበረው በአሁኗ ቱርክ ምሥራቃዊ ግዛት ውስጥ እንደሆነ ይታሰባል። ኤደን ገነት በእርግጥም በምድር ላይ ነበረ!

አምላክ አዳምን (አደምን) ከፈጠረ በኋላ “እንዲያለማውና እንዲንከባከበው በኤደን የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው።” (ዘፍጥረት 2:​15) ቆየት ብሎም አምላክ ለአዳም ሚስት እንድትሆነው ሔዋንን ፈጠረለት። አምላክ ባልና ሚስቱን “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም” በማለት አዘዛቸው። (ዘፍጥረት 1:​28) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አምላክ ‘ምድርን መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ አልፈጠራትም።’​—⁠ኢሳይያስ 45:​18

አዳምና ሔዋን ግን ሆን ብለው ሕጉን በመጣስ በአምላክ ላይ ዓመፁ። በመሆኑም አምላክ ከኤደን ገነት አስወጣቸው። የሰው ልጆች በገነት ውስጥ የመኖር አጋጣሚያቸውን አጡ። የአዳም ኃጢአት ያስከተለው መዘዝ በዚህ ብቻ አላበቃም። ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ ይላሉ፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።”​—⁠ሮም 5:​12

ታዲያ ይሖዋ፣ ምድር ገነት ሆና ደስተኛ በሆኑ ሰዎች እንድትሞላ ለማድረግ የነበረውን ዓላማ ትቶታል ማለት ነው? በፍጹም! አምላክ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ ‘ከአፌ የሚወጣው ቃሌ ደስ የሚያሰኘኝን ነገር ያደርጋል፤ የተላከበትንም ዓላማ በእርግጥ ይፈጽማል እንጂ ያላንዳች ውጤት ወደ እኔ አይመለስም።’ (ኢሳይያስ 55:​11) በእርግጥም ምድር እንደገና ገነት ትሆናለች!

በገነት ውስጥ የሚኖረን ሕይወት ምን ይመስል ይሆን? በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተገለጹትን ተስፋዎች በቀጣዮቹ ሁለት ገጾች ላይ ተመልከት።

a ዘፍጥረት 2:​10-14 እንዲህ ይላል፦ “የአትክልቱን ስፍራ የሚያጠጣ ወንዝ ከኤደን ወጥቶ ይፈስ ነበር፤ ከዚያም ተከፋፍሎ አራት ወንዝ ሆነ። የመጀመሪያው ወንዝ ስም ፊሶን ነው፤ . . . የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ . . . የሦስተኛው ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው፤ ይህ ወንዝ ከአሦር በስተ ምሥራቅ የሚፈስ ነው። አራተኛው ወንዝ ደግሞ ኤፍራጥስ ነው።”