በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 7

አምላክ በነቢያቱ በኩል የሰጠው ተስፋ

አምላክ በነቢያቱ በኩል የሰጠው ተስፋ

የጥንቶቹ ነቢያት በአምላክ ላይ እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል። እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ ሕይወታቸው ይህንን የሚያሳይ ነበር። እነዚህ ተስፋዎች ምንድን ናቸው?

አዳምና ሔዋን (አደምና ሐዋ) በኤደን ገነት ውስጥ ካመፁ በኋላ አምላክ፣ ‘የእባቡን’ ራስ በመጨፍለቅ ለዘላለም የሚያጠፋው “ዘር” እንደሚያስነሳ ወዲያውኑ ተስፋ ሰጠ፤ እንደሚጨፈለቅ የተገለጸው “ታላቁ ዘንዶ . . . ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የጥንቱ እባብ” ነው። (ዘፍጥረት 3:​14, 15፤ ራእይ 12:​9, 12) ታዲያ ይመጣል ተብሎ ተስፋ የተደረገበት ይህ ዘር ማን ሆኖ ተገኘ?

ይሖዋ ይህንን የመጀመሪያ ትንቢት ከተናገረ ከ2,000 ዓመታት ገደማ በኋላ ለነቢዩ አብርሃም (ኢብራሂም) ይመጣል ተብሎ ተስፋ የተደረገበት ሰው ከእሳቸው ዝርያ እንደሚወለድ ቃል ገባላቸው። አምላክ ለአብርሃም እንዲህ አላቸው፦ “ቃሌን ስለሰማህ የምድር ብሔራት ሁሉ በዘርህ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ።”​—⁠ዘፍጥረት 22:​18

በ1473 ዓ.ዓ. አምላክ ይህንን “ዘር” አስመልክቶ ለነቢዩ ሙሴ (ሙሳ) ተጨማሪ መረጃ ሰጣቸው። ሙሴ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ አሏቸው፦ “አምላክህ ይሖዋ ከወንድሞችህ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳልሃል። እናንተም እሱን ማዳመጥ ይኖርባችኋል።” (ዘዳግም 18:​15) ስለዚህ ይመጣል ተብሎ ተስፋ የተደረገበት ነቢይ ልክ እንደ ሙሴ ከአብርሃም ልጆች መካከል ይወለዳል ማለት ነው።

በተጨማሪም ይህ ነቢይ ከንጉሥ ዳዊት (ዳውድ) የዘር ሐረግ የሚወለድ ሲሆን እሱ ራሱም ታላቅ ንጉሥ ይሆናል። አምላክ ለንጉሥ ዳዊት “ከአንተ በኋላ ከአብራክህ የሚወጣውን ዘርህን አስነሳለሁ፤ . . . የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ” የሚል ቃል ገብቶላቸዋል። (2 ሳሙኤል 7:​12, 13) በተጨማሪም አምላክ ይህ የዳዊት ዝርያ “የሰላም መስፍን” ተብሎ እንደሚጠራ የገለጸ ሲሆን አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ ይቀመጣል፤ እየተጠናከረ የሚሄደው አገዛዙም ሆነ ሰላሙ ፍጻሜ አይኖረውም። ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም በማይናወጥ ሁኔታ ይመሠረታል፤ በፍትሕና በጽድቅም ጸንቶ ይኖራል።” (ኢሳይያስ 9:​6, 7) አዎ፣ ይህ ጻድቅ መሪ በምድር ላይ ሰላምና ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል። ታዲያ የሚመጣው መቼ ይሆን?

ተስፋ የተደረገበት “ዘር” . . . የሚወለደው ከአብርሃም (ከኢብራሂም) ዘር ነው፣ እንደ ሙሴ (ሙሳ) ያለ ነቢይ ይሆናል፣ የሚመጣው ከዳዊት (ከዳውድ) የዘር ሐረግ ነው፣ የሚመጣው በ29 ዓ.ም. ነው፣ እባቡን ማለትም ሰይጣንን ይጨፈልቃል

ከጊዜ በኋላ መልአኩ ገብርኤል (ጂብሪል) ለነቢዩ ዳንኤል እንዲህ አላቸው፦ “ኢየሩሳሌምን ለማደስና መልሶ ለመገንባት ትእዛዝ ከሚወጣበት ጊዜ አንስቶ መሪ የሆነው መሲሕ እስከሚገለጥበት ጊዜ ድረስ 7 ሳምንታትና 62 ሳምንታት እንደሚሆን እወቅ፤ አስተውልም።” (ዳንኤል 9:​25) እያንዳንዳቸው የ7 ዓመት ርዝማኔ ያላቸው እነዚህ 69 ሳምንታት በድምሩ 483 ዓመታት ይሆናሉ። እነዚህ ዓመታት ከ455 ዓ.ዓ. እስከ 29 ዓ.ም. ያሉትን ጊዜያት ያመለክታሉ። a

ታዲያ መሲሑ ማለት እንደ ሙሴ ያለው ነቢይና ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየው “ዘር” በ29 ዓ.ም. መጥቷል? ይህን በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንመለከታለን።