በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 13

እውነተኛ እምነት ለዘላለም ደስታ ያስገኝልሃል

እውነተኛ እምነት ለዘላለም ደስታ ያስገኝልሃል

ቅዱሳን መጻሕፍት “ጻድቅ . . . በእምነት ይኖራል” በማለት ይናገራሉ። (ሮም 1:​17) እነዚህ ቃላት ወደፊት የምታገኘውን አስደናቂ ተስፋ ይዘዋል። ይህ ጥቅስ አንተን የሚመለከትህ እንዴት ነው?

መሲሑ ኢየሱስ (ኢሳ) በምድር ላይ የነበረውን ሥራ ካጠናቀቀ በኋላ ከአምላክ ጋር ለመሆን ወደ ሰማይ አረገ። ደቀ መዛሙርቱ እየተመለከቱት “ወደ ላይ ወጣ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰወረው።” (የሐዋርያት ሥራ 1:⁠9) አምላክ ኢየሱስን በሰማይ ኃያል ንጉሥ አድርጎ ሾመው። በቅርቡ ኢየሱስ “ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል። ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሁሉ እሱም ሰዎችን አንዱን ከሌላው ይለያል።” (ማቴዎስ 25:​31, 32) ይህ የሚሆነው መቼ ነው?

በመላው ዓለም የመከራ ዘመን እንደሚመጣ ቅዱሳን መጻሕፍት ትንቢት ተናግረዋል፤ ይህም መሲሑ በሕዝቦች ላይ የሚፈርድበት ጊዜ መቅረቡን የሚጠቁም ምልክት ይሆናል። ኢየሱስ፣ ምልክቱ ምን ነገሮችን እንደሚያጠቃልል ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል። ታላላቅ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ፤ በተለያየ ስፍራም የምግብ እጥረትና ቸነፈር ይሆናል፤ ደግሞም የሚያስፈሩ ነገሮች . . . ይታያሉ።”​—⁠ሉቃስ 21:​7, 10, 11

በዛሬው ጊዜ ችግሮች እየበዙ መሄዳቸው መሲሑ በሕዝቦች ላይ የሚፈርድበት ጊዜ እንደቀረበ ያሳያል

ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት በዛሬው ጊዜ እየተፈጸመ መሆኑን በግልጽ ማየት እንችላለን። በቅርቡ ኢየሱስ ክፉዎችን ለማጥፋት ይመጣል። በመጨረሻም ሰይጣን ራሱ ይጠፋል! መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች። ሁሉም ሰዎች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከእንስሳት ጋር በሰላም ይኖራሉ። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር የሚቀመጥበት ጊዜ ይኖራል፤ ነብርም ከፍየል ግልገል ጋር ይተኛል፤ ጥጃ፣ አንበሳና የሰባ ከብት አብረው ይሆናሉ፤ ትንሽ ልጅም ይመራቸዋል። . . . ምንም ዓይነት ጉዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም።” (ኢሳይያስ 11:​6, 9) “በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም። . . . በዚያን ጊዜ የዓይነ ስውራን ዓይን ይገለጣል፤ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ጆሮም ይከፈታል።” (ኢሳይያስ 33:​24፤ 35:⁠5) የሞቱ ሰዎችም እንኳ ትንሣኤ ያገኛሉ። “ይሖዋ ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል”፤ እንዲሁም “ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።” (ኢሳይያስ 25:8፤ ራእይ 21:⁠4) አምላክ ለምድር የነበረው ዓላማ ይፈጸማል። እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው!

እምነትህ እያደገ እንዲሄድ አድርግ

አምላክ በገነት ውስጥ እንዲኖሩ የሚፈቅድላቸው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው? እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎችን ነው!

እውነተኛ እምነት በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው ትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አስታውስ። በመሆኑም ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ ይበልጥ ለማወቅ የምታደርገውን ጥረት ግፋበት!

እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች በገነት ውስጥ ለዘላለም ይኖራሉ!

እውነተኛ እምነት በጽድቅ ሥራዎች መደገፍ አለበት። የአምላክ ቃል ‘እምነት ያለ ሥራ የሞተ ነው’ ይላል። (ያዕቆብ 2:​26) እንዲህ ያሉትን መልካም ሥራዎች በመሥራት የአምላክን ድንቅ ባሕርያት ማለትም ኃይሉን፣ ፍትሑን፣ ጥበቡንና ፍቅሩን ማንጸባረቅ ትችላለህ። አምላክ የሚወዳቸውን እነዚህን ባሕርያት ለማዳበር ጥረት ማድረግህን ቀጥል!

እውነተኛ እምነት ማዳበር ብዙ በረከቶችን ያስገኝልሃል። በእርግጥም እውነተኛ እምነት አሁንም ሆነ ለዘላለም አስደሳች ሕይወት የሚያስገኝልህ ቁልፍ ነው!