በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 10

የእውነተኛው እምነት ጠላት ተጋለጠ

የእውነተኛው እምነት ጠላት ተጋለጠ

ይሖዋ አምላክ ምድርን ከመፍጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት በሰማይ መላእክትን ፈጥሯል። ከጊዜ በኋላ ግን አንድ መልአክ ለአምላክ ብቻ የሚገባውን አምልኮ ለራሱ መመኘት ጀመረ። ይህን ምኞቱን ለማሳካት በወሰደው እርምጃ ራሱን ሰይጣን ማለትም “ተቃዋሚ” አደረገ፤ ይህ ስም የተሰጠው አምላክን በመቃወሙ ነው። ለመሆኑ ሰይጣን አምላክን የተቃወመው እንዴት ነው?

ሰይጣን ሔዋንን (ሐዋን) ለማሳሳት በእባብ ተጠቅሟል

ሰይጣን ሔዋንን (ሐዋን) በማታለል የአምላክን ትእዛዝ እንድትጥስ አደረጋት። ተንኮል የተሞላበት አነጋገር በመጠቀም ይሖዋ አምላክ ከተከለከለው ዛፍ ፍሬ እንዳትበላ ያዘዛት ጥሩ ነገር ሊያስቀርባት ፈልጎ እንደሆነ ነገራት። አምላክ ውሸታም እንደሆነ በድፍረት የተናገረ ከመሆኑም ሌላ ሔዋን የአምላክን አመራር መቀበል እንደሌለባት በተዘዋዋሪ መንገድ ሲገልጽ እንዲህ አለ፦ “አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ ስለሚያውቅ ነው።” (ዘፍጥረት 3:⁠5) ሔዋንም በሰይጣን በመታለል የነገራትን ውሸት አመነች። የአምላክን ሕግ ከመጣሷም ሌላ አዳምም (አደም) እንዲሁ እንዲያደርግ ተጽዕኖ አደረገችበት። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሰይጣን እውነተኛ እምነት ለማዳበር የሚጥሩትን ሁሉ በጠላትነት ሲመለከት ቆይቷል። እንዲሁም እስካሁን ድረስ ሰዎችን ማታለሉን ቀጥሏል። እንዴት?

የሐሰት እምነት ተስፋፋ

ሰይጣን ሰዎችን ለማሳሳት በጣዖት አምልኮና በሰዎች ወግ ተጠቅሟል

ሰይጣን የእስራኤልን ልጆች እምነት ለመበከል የጣዖት አምልኮና የሰው ወጎችን ተጠቅሟል። የሃይማኖት መሪዎቻቸው “የሰውን ሥርዓት” እንደሚያስተምሩና በዚህም የተነሳ አምልኳቸው ከንቱ እንደሆነ መሲሑ ኢየሱስ (ኢሳ) ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 15:⁠9) የእስራኤል ልጆች መሲሑን ባለመቀበላቸው አምላክ ተዋቸው። ኢየሱስ “የአምላክ መንግሥት ከእናንተ ተወስዶ ፍሬውን ለሚያፈራ ሕዝብ ይሰጣል” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 21:​43) በዚህም የተነሳ አምላክ በእነሱ ፈንታ ሕዝቡ እንዲሆኑ የኢየሱስን ተከታዮች መረጠ።

በመቀጠል ሰይጣን የኢየሱስን ተከታዮች እምነት ለመበከል ጥረት ማድረግ ጀመረ። ታዲያ ተሳካለት? ኢየሱስ ወደፊት የሚፈጸመውን ነገር በምሳሌ መልክ በተናገረው ትንቢት ላይ ገልጿል። በምሳሌው ላይ አንድ ሰው በማሳው ላይ ጥሩ ስንዴ እንደዘራ ጠቀሰ። በኋላም አንድ ጠላት በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘራበት። ስንዴውም ሆነ እንክርዳዱ እስከ መከር ድረስ አብረው እንዲያድጉ ተደረገ። የመከር ጊዜ ሲደርስ እንክርዳዱ ከስንዴው እንዲለይ ይደረጋል፤ ከዚያም እንክርዳዱ ይቃጠላል። ስንዴው ግን ተሰብስቦ ጎተራ ውስጥ ይገባል።

ከዚያም ኢየሱስ የምሳሌውን ትርጉም ለደቀ መዛሙርቱ አብራራላቸው። ዘሪው ኢየሱስ ራሱ ነው። “ጥሩው ዘር ደግሞ የመንግሥቱ ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ ግን የክፉው ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱን የዘራው ጠላት፣ ዲያብሎስ ነው። መከሩ የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ሲሆን አጫጆቹ ደግሞ መላእክት ናቸው” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:​38, 39) ኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርቱን በስንዴ መስሏቸዋል። ይሁን እንጂ ሰይጣን፣ በእውነተኞቹ የኢየሱስ ተከታዮች መካከል ልክ እንደ እንክርዳድ ያሉ ሐሰተኛ ደቀ መዛሙርትን ዘራ። በመሆኑም ኢየሱስ እንደተነበየው እሱ ከሞተ ከጥቂት መቶ ዓመታት በኋላ ሐሰተኛ ደቀ መዛሙርት ብቅ አሉ። እነሱም አምላክ አንድም ሦስትም ነው የሚለውን የሥላሴ ትምህርት ጨምሮ በርካታ የክህደት ትምህርቶችን አስፋፉ። በተጨማሪም ሐሰተኞቹ ደቀ መዛሙ​ርት ጣዖት ማምለክና በፖለቲካ ውስጥ መግባት ጀመሩ። የኢየሱስን ትምህርቶች በታማኝነት የተከተሉት ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበሩ።

እውነተኛው እምነት ሳይበከል እንዲቆይ ተደርጓል

ይሁን እንጂ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለውጥ መጣ። የአምላክ መላእክት ሐሰተኞቹን ከእውነተኞቹ በመለየት ለጥፋት እንዲዘጋጁ አደረጉ። በዚህ ጊዜ እውነተኛ እምነት ያላቸውን ሰዎች ለይቶ ማወቅ ቀላል ሆነ። በመጨረሻም የመጀመሪያው የእምነት ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስም ጭምር ይደመሰሳል። አዎ፣ እውነተኛ እምነት ድል ያደርጋል!

ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች እነማን እንደሆኑ ለይተህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

የአምላክ መላእክት እውነተኛውን እምነት ለማግኘት የሚመኙ ሰዎችን በመፈለግ ላይ ናቸው