በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መግቢያ

መግቢያ

‘በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን የምትኮርጁ ሁኑ።’—ዕብራውያን 6:12

1, 2. አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ታማኝ ሰዎች እንዴት ይመለከቷቸው ነበር? እነዚህ ሰዎች ጥሩ ወዳጆች ሊሆኑን ይችላሉ የምንለው ለምንድን ነው?

አንዲት እህት፣ አረጋዊ የሆኑ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ያቀረቡትን ንግግር ካዳመጠች በኋላ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተገለጹት ሰዎች ሲናገሩ እነዚህ ሰዎች የረጅም ጊዜ ወዳጆቻቸው ይመስላሉ” የሚል አስተያየት ሰጥታለች። እኚህ ወንድም ለብዙ አሥርተ ዓመታት የአምላክን ቃል ሲያጠኑና ሌሎችን ለማስተማር ሲጠቀሙበት ስለኖሩ እንዲህ ማለቷ አያስገርምም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ታማኝ ወንዶችና ሴቶች በእርግጥም ለእኚህ ወንድም ለረጅም ጊዜ የሚያውቋቸው ወዳጆቻቸው ናቸው ማለት ይቻላል።

2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት በርካታ ሰዎች ጥሩ ወዳጆቻችን ሊሆኑ ይችላሉ ቢባል አትስማማም? እነዚህ ሰዎች ለአንተስ እውን ሆነውልሃል? እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሩት፣ ኤልያስና አስቴር ካሉ ታማኝ ሰዎች ጋር ይበልጥ ለመተዋወቅ አብረሃቸው እየተጓዝክ ስትጨዋወትና ከእነሱ ጋር ጊዜ ስታሳልፍ ምን ሊሰማህ እንደሚችል አስብ። እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ሊሰጡህ የሚችሉት ግሩም ምክርና ማበረታቻ በሕይወትህ ላይ ምን ያህል በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ገምት!—ምሳሌ 13:20ን አንብብ።

3. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት ታማኝ ሰዎች በመማር ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 እርግጥ ነው፣ ‘ጻድቃን ከሞት በሚነሱበት’ ጊዜ ቃል በቃል ይህን ዓይነቱን ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችል አጋጣሚ ይኖረናል። (ሥራ 24:15) ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት ታማኝ ወንዶችና ሴቶች በመማር ጥቅም ማግኘት እንችላለን። እንዴት? ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን የምትኮርጁ ሁኑ’ በማለት ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ይነግረናል። (ዕብ. 6:12) ታማኝ ስለሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ከመመልከታችን በፊት ጳውሎስ ባነሳው ሐሳብ ላይ ያተኮሩ ጥቂት ጥያቄዎችን ለመመርመር እንሞክር፦ እምነት ምንድን ነው? ይህን ባሕርይ ማዳበር ያለብን ለምንድን ነው? በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩ ታማኝ ሰዎችን መኮረጅ የምንችለውስ እንዴት ነው?

እምነት ምንድን ነው? ይህን ባሕርይ ማዳበር ያለብንስ ለምንድን ነው?

4. ብዙ ሰዎች እምነት ሲባል ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ምንድን ነው? የእነዚህ ሰዎች አመለካከት የተሳሳተ ነው የምንለውስ ለምንድን ነው?

4 እምነት፣ በዚህ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሱት ታማኝ ሰዎች ሁሉ ከፍ አድርገው ይመለከቱት የነበረ ግሩም ባሕርይ ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች እምነት ሲባል አንድን ነገር ያለ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ አምኖ መቀበል እንደሆነ አድርገው ስለሚያስቡ እምነት ማዳበር ያለውን አስፈላጊነት አቅልለው ይመለከታሉ። ይሁን እንጂ የእነዚህ ሰዎች አመለካከት የተሳሳተ ነው። እምነት እንዲሁ በየዋህነት ማመን ወይም በስሜት መነዳት ማለት አይደለም፤ አሊያም አንድን ነገር አምኖ መቀበል ማለት ብቻም አይደለም። አንድን ነገር በየዋህነት አምኖ መቀበል አደገኛ ነው። ስሜታዊነትም ቢሆን ብልጭ ብሎ የሚጠፋ ነገር ሊሆን ይችላል፤ ሌላው ቀርቶ ከአምላክ ጋር በተያያዘ ማመን ብቻውን በቂ አይደለም፤ ምክንያቱም “አጋንንትም ያምናሉ እንዲሁም በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ።”—ያዕ. 2:19

5, 6. (ሀ) እምነት በየትኞቹ ሁለት የማይታዩ ነገሮች ላይ ያተኩራል? (ለ) እምነታችን የተመሠረተበት ማስረጃ ምን ያህል አስተማማኝ መሆን አለበት? በምሳሌ አስረዳ።

5 እውነተኛ እምነት ከዚህ ሁሉ የላቀ ትርጉም አለው። መጽሐፍ ቅዱስ እምነትን ምን ብሎ እንደሚፈታው ልብ በል። (ዕብራውያን 11:1ን አንብብ።) ጳውሎስ እምነት በዓይናችን ልናያቸው በማንችላቸው ሁለት ነገሮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጿል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ “ባይታዩም እንኳ” መኖራቸው በተረጋገጠ እውነታዎች ላይ ያተኩራል። ለምሳሌ ይሖዋ አምላክን፣ ልጁን ወይም በሰማይ እየገዛ ያለውን መንግሥት የመሳሰሉትን በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ያሉ ነገሮችን በሰብዓዊ ዓይናችን ማየት አንችልም። በሁለተኛ ደረጃ፣ እምነት ‘ተስፋ በሚደረጉ ነገሮች’ ማለትም ገና ባልተፈጸሙ ክንውኖች ላይ ያተኩራል። የአምላክ መንግሥት በቅርቡ የሚያመጣውን አዲስ ዓለም አሁን ልናየው አንችልም። ታዲያ ይህ ሲባል እንዲህ ባሉ እውነታዎችና ተስፋ በምናደርጋቸው ነገሮች ላይ እምነት ለማሳደር የሚያስችል ተጨባጭ ማስረጃ የለንም ማለት ነው?

6 በፍጹም! ጳውሎስ እውነተኛ እምነት በጽኑ መሠረት ላይ የተገነባ እንደሆነ ተናግሯል። እምነት “በእርግጠኝነት መጠበቅ” ማለት እንደሆነ ሲናገር የተጠቀመበት አገላለጽ “የንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። አንድ ሰው ቤት ሊሰጥህ አሰበ እንበል። በዚህ ጊዜ የንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነዱን እየሰጠህ “ይኸው፣ አዲሱ ቤትህ” ይልህ ይሆናል። ይህን ሲል በዚያ ሰነድ ላይ ትኖራለህ ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ከዚህ ይልቅ ሰነዱ ቤቱን እንድትረከብ የሚያስችልህ ሕጋዊ ማስረጃ ስለሆነ ሰነዱ ራሱ ቤቱ እንደሆነ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። በተመሳሳይም እምነታችን የተመሠረተበት ማስረጃ በጣም አሳማኝና ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ማስረጃው ራሱ እምነታችን ነው ሊባል ይችላል።

7. እውነተኛ እምነት ምን ነገሮችን ይጨምራል?

7 በመሆኑም እውነተኛ እምነት በጽኑ መሠረት ላይ የተገነባ የመተማመን ስሜትንና ይሖዋ አምላክን አለኝታ ከማድረግ የሚመነጭ የማይናወጥ አቋምን አጣምሮ የያዘ ነው። እምነታችን ይሖዋን እንደ አፍቃሪ አባታችን እንድናየውና የሰጠን ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ እንድንተማመን ያደርገናል። ይሁንና እውነተኛ እምነት ከዚህ ያለፈ ነገርንም ይጨምራል። ልክ እንደ አንድ ሕይወት ያለው ነገር ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል ከተፈለገ ልንመግበው ይገባል። እምነታችን በሥራ መገለጽ ይኖርበታል፤ ካልሆነ ግን ይሞታል።—ያዕ. 2:26

8. እምነት ማዳበር ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

8 እምነት ማዳበር ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ጳውሎስ ይህን ማድረግ የግድ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ገልጿል። (ዕብራውያን 11:6ን አንብብ።) እምነት ከሌለን ወደ ይሖዋ መቅረብም ሆነ እሱን ማስደሰት አንችልም። በመሆኑም የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ ከተፈጠሩበት እጅግ ታላቅና የተከበረ ዓላማ ጋር ተስማምተን እንድንኖር ይኸውም በሰማይ ከሚኖረው አባታችን ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንድንመሠርትና እሱን እንድናወድስ ከተፈለገ እምነት ማዳበራችን ወሳኝ ነገር ነው።

9. ይሖዋ እምነት ማዳበራችን አስፈላጊ መሆኑን እንደሚያውቅ ያሳየው እንዴት ነው?

9 ይሖዋ እምነት ማዳበራችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያውቃል፤ ስለሆነም እምነት መገንባትና ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንድንማር የሚያስችሉ ምሳሌዎችን ሰጥቶናል። ግንባር ቀደም ሆነው የሚመሩ ታማኝ ወንዶችን ምሳሌ አድርጎ በመስጠት ክርስቲያን ጉባኤን ባርኮታል። ቃሉ “እምነታቸውን ኮርጁ” የሚል ማበረታቻ ይሰጠናል። (ዕብ. 13:7) ይሖዋ ተጨማሪም ነገር ሰጥቶናል። ጳውሎስ “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” በማለት ስለጠራቸው እምነት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ስለሚሆኑ በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ጽፏል። (ዕብ. 12:1) በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ የሚገኘው ጳውሎስ የጻፈው የታማኝ ሰዎች ስም ዝርዝር ሁሉንም አካቷል ሊባል አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ እምነት በጠፋበት በዚህ ዘመን ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑን የሚችሉ የተለያየ ዕድሜ፣ የኑሮ ደረጃና አስተዳደግ ያላቸው እንዲሁም ጠንካራ እምነት ይዘው ሲመላለሱ የነበሩ የበርካታ ታማኝ ወንዶችና ሴቶችን ታሪክ ይዟል።

የሌሎችን እምነት መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

10. የግል ጥናት ማድረጋችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ታማኝ ሰዎች እንድንመስላቸው ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

10 አንድን ሰው በደንብ የማታውቀው ከሆነ እሱን ልትመስለው አትችልም። ይህን መጽሐፍ ስታነብ እነዚህን የእምነት ሰዎች ይበልጥ እንድታውቃቸው ለመርዳት ሲባል ጥልቀት የተሞላበት ምርምር መደረጉን ሳትገነዘብ አትቀርም። ታዲያ አንተስ በግልህ ለምን ተጨማሪ ምርምር አታደርግም? የግል ጥናት በምታደርግበት ወቅት ባሉህ የምርምር መሣሪያዎች ተጠቅመህ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ለማጥናት ጥረት አድርግ። ባጠናኸው ነገር ላይ ስታሰላስል ያነበብከውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መቼትና የኋላ ታሪክ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። በሌላ አነጋገር በአካባቢው የነበረውን ሁኔታ ለማየት፣ ድምፆቹን ለመስማትና መዓዛውን ለማሽተት ጣር። ከዚህም በላይ በዘገባው ላይ የተጠቀሱትን ሰዎች ስሜት ለመረዳት ሞክር። ራስህን በእነሱ ቦታ የምታስቀምጥ ከሆነ እነዚህ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ይበልጥ እውን ይሆኑልሃል፤ አልፎ ተርፎም አንዳንዶቹ ለረጅም ጊዜ የምታውቃቸው ወዳጆችህ እንደሆኑ ሊሰማህ ይችላል።

11, 12. (ሀ) አብራምንና ሦራን በቅርብ እንደምታውቃቸው ሆኖ እንዲሰማህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) ሐና፣ ኤልያስ ወይም ሳሙኤል ከተዉት ምሳሌ ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

11 እነዚህን የእምነት ሰዎች ይበልጥ እያወቅካቸው ስትሄድ የእነሱን ምሳሌ ለመከተል መነሳሳትህ አይቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ አዲስ ኃላፊነት የመቀበል አጋጣሚ ተከፍቶልሃል እንበል። የይሖዋ ድርጅት አገልግሎትህን ማስፋት የምትችልበት ግብዣ አቅርቦልሃል። ምናልባትም የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረህ እንድታገለግል ወይም ከዚህ በፊት ሞክረህ በማታውቀው አሊያም የግል ምቾትህን መሥዋዕት ማድረግ በሚጠይቅብህ አንድ ዓይነት የአገልግሎት ዘርፍ እንድትሰማራ ተጠይቀህ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ጉዳይ ስታውጠነጥንና ስትጸልይ አብራም በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰልህ ሊጠቅምህ ይችል ይሆን? አብራምና ሦራ በዑር የነበራቸውን የተመቻቸ ኑሮ ትተው ለመሄድ ፈቃደኞች መሆናቸው ብዙ በረከት አስገኝቶላቸዋል። አንተም የእነሱን አርዓያ ከተከተልክ እነዚህን የአምላክ አገልጋዮች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንዳወቅካቸው ሆኖ እንደሚሰማህ ጥርጥር የለውም።

12 ወይም ደግሞ አንድ የምትቀርበው ሰው ሆን ብሎ አንተን የሚያዋርድ ድርጊት ቢፈጽምና ሁኔታው ስሜትህን ክፉኛ ቢጎዳው አልፎ ተርፎም ከጉባኤ ስብስባዎች ለመቅረት ብትፈተን ምን ታደርጋለህ? ሐና በተወችው ምሳሌ ላይ ማሰላሰልህና ፍናና ትፈጽምባት የነበረውን የተንኮል ድርጊት እንዴት እንደተቋቋመች ማስታወስህ ትክክለኛ ውሳኔ እንድታደርግ ይረዳሃል፤ አልፎ ተርፎም ሐና የቅርብ ወዳጅህ እንደሆነች እንዲሰማህ ሊያደርግህ ይችላል። ከከንቱነት ስሜት ጋር የምትታገል ከሆነ ደግሞ ኤልያስ ሸሽቶ በሄደበት ወቅት ይሖዋ እንዴት እንዳጽናናው የሚገልጸውን ዘገባ ማጥናትህ ወደ ኤልያስ ይበልጥ እንደቀረብክ ሆኖ እንዲሰማህ ያደርግ ይሆናል። አብረዋቸው የሚማሩ ብልሹ ሥነ ምግባር ያላቸው ልጆች ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩባቸው ወጣቶች ሳሙኤል የኤሊ ልጆች በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ያሳድሩበት የነበረውን መጥፎ ተጽዕኖ እንዴት መቋቋም እንደቻለ የሚገልጸውን ዘገባ ሲያጠኑ ይበልጥ ወደ ሳሙኤል እንደቀረቡ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል።

13. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ሰዎች እምነት ለመኮረጅ በመጣርህ ይሖዋ ከእነሱ ያነሰ እምነት እንዳለህ አድርጎ ይመለከትህ ይሆን? አብራራ።

13 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት እነዚህ ሰዎች ያሳዩትን እምነት ለመኮረጅ በመጣርህ ይሖዋ ከእነሱ ያነሰ እምነት እንዳለህ አድርጎ ይመለከትህ ይሆን? በፍጹም! የይሖዋ ቃል በእምነታቸው ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን እንድንኮርጅ እንደሚያበረታታን አስታውስ። (1 ቆሮ. 4:16፤ 11:1፤ 2 ተሰ. 3:7, 9) በተጨማሪም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ሰዎች ራሳቸው ከእነሱ በፊት የነበሩ ታማኝ አገልጋዮችን ምሳሌ ተከትለዋል። ለምሳሌ ያህል በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 17 ላይ የሰፈረው ማርያም የተናገረችው ሐሳብ ሐና ከተናገረችው ላይ የተወሰደ እንደነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ ይህም ማርያም ሐናን ምሳሌ አድርጋ እንደተመለከተቻት በግልጽ ያሳያል። ታዲያ ይህ ማርያም ከሐና ያነሰ እምነት እንደነበራት የሚያሳይ ነው? በጭራሽ! ከዚህ ይልቅ ሐና የተወችው ምሳሌ ማርያም ጠንካራ እምነት እንድትገነባና በይሖዋ አምላክ ዘንድ ልዩ የሆነ ስም እንድታተርፍ ረድቷታል።

14, 15. የዚህ መጽሐፍ አንዳንድ ገጽታዎች ምንድን ናቸው? በጥሩ ሁኔታ ልንጠቀምበት የምንችለውስ እንዴት ነው?

14 ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀው እምነትህን እንድታጠናክር ለመርዳት ታስቦ ነው። ቀጥሎ ያሉት ምዕራፎች ከ2008 እስከ 2013 ባሉት ጊዜያት “በእምነታቸው ምሰሏቸው” በሚል ርዕስ በመጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡትን ርዕሰ ትምህርቶች የያዙ ናቸው። ይሁንና አንዳንድ አዳዲስ ሐሳቦችም ተጨምረውባቸዋል። ለውይይት የሚረዱና ነጥቡን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል የሚጠቁሙ ጥያቄዎችም ተዘጋጅተዋል። ነጥቡን የሚያስጨብጡ አዳዲስ የሆኑ ማራኪ ስዕሎችም በመጽሐፉ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን ቀደም ሲል የነበሩትም ቢሆኑ መጠናቸውና ውበታቸው ይበልጥ እንዲጨምር ተደርጓል። መጽሐፉ የጊዜ ሰሌዳና ካርታዎችን ጨምሮ ሌሎች ጠቃሚ የሆኑ ገጽታዎችም አሉት። በእምነታቸው ምሰሏቸው የተባለው ይህ መጽሐፍ በግል፣ በቤተሰብና በጉባኤ ደረጃ እንዲጠና ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ቤተሰቦች በዚህ መጽሐፍ ላይ የሰፈሩትን ታሪኮች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በማንበብ ብቻ እንኳ ጥቅም ማግኘት ይችላሉ።

15 ይህ መጽሐፍ በጥንት ዘመን የነበሩ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እምነት በማሳየት ረገድ የተዉትን ምሳሌ እንድትከተል ይረዳህ ዘንድ ምኞታችን ነው። በተጨማሪም እምነትህ እያደገ እንዲሄድና በሰማይ ወደሚኖረው አባትህ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ እንደሚረዳህ ተስፋ እናደርጋለን!