በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 58

ኢየሩሳሌም ጠፋች

ኢየሩሳሌም ጠፋች

የይሁዳ ሰዎች በተደጋጋሚ ይሖዋን ትተው የሐሰት አማልክትን ያመልኩ ነበር። ለብዙ ዓመታት ይሖዋ እነሱን ለመርዳት ሞክሮ ነበር። አይሁዳውያንን እንዲያስጠነቅቋቸው በርካታ ነቢያትን ልኮ የነበረ ቢሆንም እነሱ ግን ነቢያቱ የነገሯቸውን አልሰሙም። እንዲያውም በነቢያቱ ላይ ያሾፉባቸው ነበር። ታዲያ ይሖዋ የይሁዳ ሰዎች ጣዖት ማምለካቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ምን እርምጃ ወስዶ ይሆን?

የባቢሎን ንጉሥ የሆነው ናቡከደነጾር ብዙ አገሮችን ድል አድርጎ ነበር። ኢየሩሳሌምን ለመጀመሪያ ጊዜ ድል ባደረገበት ወቅት ንጉሥ ዮአኪንን፣ መኳንንቱን፣ ተዋጊዎቹንና የእጅ ጥበብ ባለሙያዎቹን በሙሉ ይዞ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚገኙትንም ውድ ዕቃዎች በሙሉ ወሰደ። ከዚያም ናቡከደነጾር ሴዴቅያስን የይሁዳ ንጉሥ አደረገው።

ሴዴቅያስ መጀመሪያ ላይ ናቡከደነጾርን ይታዘዝ ነበር። ሆኖም በአካባቢው የሚኖሩ ሕዝቦችና ሐሰተኛ ነቢያቱ ሴዴቅያስን በባቢሎን ላይ እንዲያምፅ መከሩት። ኤርምያስ ግን ‘በባቢሎን ላይ ካመፅክ በይሁዳ ውስጥ ግድያ፣ ረሃብና በሽታ ይኖራል’ በማለት አስጠነቀቀው።

ሴዴቅያስ ለስምንት ዓመት ያህል ንጉሥ ሆኖ ከገዛ በኋላ በባቢሎን ላይ ዓመፀ። የግብፅ ንጉሥ እንዲረዳው ጠየቀ። ከዚያም ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ ወታደሮቹን ላከ፤ ወታደሮቹም ኢየሩሳሌምን ከበቧት። ኤርምያስም ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፦ ‘ይሖዋ “ለባቢሎን እጅህን ከሰጠህ አንተም ሆንክ ከተማዋ ትተርፋላችሁ” ብሏል። እጅ ካልሰጠህ ግን ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ያቃጥሏታል፤ አንተንም ይወስዱሃል።’ ሴዴቅያስ ግን እጅ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።

ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ የባቢሎን ወታደሮች የኢየሩሳሌምን አጥር አፍርሰው በመግባት ከተማዋን በእሳት አቃጠሏት። ቤተ መቅደሱን አቃጠሉ፤ ብዙ ሰዎችን ገደሉ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እስረኛ አድርገው ወሰዱ።

ሴዴቅያስ ከኢየሩሳሌም አመለጠ፤ ሆኖም ባቢሎናውያን አሳደዱት። ኢያሪኮ አካባቢ ሲደርስ ያዙትና ወደ ናቡከደነጾር አመጡት። የባቢሎን ንጉሥ፣ ሴዴቅያስ ዓይኑ እያየ ልጆቹ እንዲገደሉ አደረገ። ከዚያም ናቡከደነጾር የሴዴቅያስን ዓይኖች አሳወረና እስር ቤት አስገባው፤ ሴዴቅያስም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እስር ቤት ውስጥ ሞተ። ይሖዋ ግን ለይሁዳ ሰዎች ‘ከ70 ዓመት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም እንድትመለሱ አደርጋለሁ’ በማለት ቃል ገባላቸው።

ታዲያ ወደ ባቢሎን የተወሰዱት ወጣቶች ምን ይገጥማቸው ይሆን? ይሖዋን በታማኝነት ማምለካቸውን ይቀጥሉ ይሆን?

“ሁሉን ቻይ የሆንከው ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ፍርድህ ሁሉ እውነትና ጽድቅ ነው።”—ራእይ 16:7