በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 70

መላእክት ኢየሱስ መወለዱን ተናገሩ

መላእክት ኢየሱስ መወለዱን ተናገሩ

የሮም ንጉሠ ነገሥት የነበረው አውግስጦስ ቄሳር ሁሉም አይሁዳውያን ወደተወለዱበት ከተማ ሄደው እንዲመዘገቡ አዘዘ። ስለዚህ ዮሴፍና ማርያም የዮሴፍ ቤተሰቦች ይኖሩባት ወደነበረችው ወደ ቤተልሔም ሄዱ። በዚህ ጊዜ ማርያም ልትወልድ ተቃርባ ነበር።

ቤተልሔም ሲደርሱ ያገኙት የማረፊያ ቦታ የከብቶች በረት ብቻ ነበር። በዚያም ማርያም ኢየሱስን ወለደች። ከዚያም በጨርቅ ጠቅልላ ግርግም ውስጥ አስተኛችው።

በቤተልሔም አቅራቢያ ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። በድንገት አንድ መልአክ በፊታቸው ቆመ፤ የይሖዋም ክብር በዙሪያቸው አንጸባረቀ። በዚህ ጊዜ እረኞቹ በጣም ፈሩ፤ መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ ‘አትፍሩ። አንድ ደስ የሚል ዜና እነግራችኋለሁ። መሲሑ ዛሬ በቤተልሔም ተወልዷል።’ ወዲያውኑም በሰማይ ላይ ብዙ መላእክት ታይተው ‘በሰማይ ለአምላክ ክብር ይሁን፤ በምድርም ላይ ሰላም ይሁን’ አሉ። ከዚያም መላእክቱ ተሰወሩ። በዚህ ጊዜ እረኞቹ ምን አደረጉ?

እረኞቹ እርስ በርሳቸው ‘አሁኑኑ ወደ ቤተልሔም እንሂድ’ ተባባሉ። ከዚያም በፍጥነት ወደ ቤተልሔም ሄዱ፤ ዮሴፍንና ማርያምንም ከአዲሱ ልጃቸው ጋር በረት ውስጥ አገኟቸው።

መልአኩ ለእረኞቹ የተናገረውን ነገር የሰሙ ሰዎች በሙሉ በጣም ተደነቁ። ማርያም መልአኩ የተናገረውን ነገር በደንብ አሰበችበት፤ ከዚያ በኋላም ጨርሶ አልረሳችውም። እረኞቹ ስላዩትና ስለሰሙት ነገር ይሖዋን እያመሰገኑ ወደ መንጎቻቸው ተመለሱ።

“እኔ ወደዚህ የመጣሁት ከእሱ ዘንድ [ነው]። እሱ ላከኝ እንጂ እኔ በራሴ ተነሳስቼ አልመጣሁም።”—ዮሐንስ 8:42