በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 77

ውኃ ልትቀዳ የመጣችው ሳምራዊት ሴት

ውኃ ልትቀዳ የመጣችው ሳምራዊት ሴት

ፋሲካ ከተከበረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ገሊላ ሲመለሱ በሰማርያ በኩል አለፉ። ሰማርያ ውስጥ ሲካር የተባለች ከተማ አቅራቢያ ሲደርሱ ኢየሱስ የያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ አረፍ አለ። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማዋ ሄዱ።

ከዚያም አንዲት ሴት ውኃ ለመቅዳት ወደ ጉድጓዱ መጣች። ኢየሱስም “እባክሽ፣ የምጠጣው ውኃ ስጪኝ” አላት። እሷም እንዲህ አለችው፦ ‘ለምንድን ነው የምታነጋግረኝ? እኔ ሳምራዊት ሴት ነኝ። አይሁዳውያን ደግሞ ከሳምራውያን ጋር አይነጋገሩም።’ ኢየሱስ ግን እንዲህ አላት፦ ‘እኔ ማን እንደሆንኩ ብታውቂ ኖሮ አንቺ ራስሽ ውኃ እንድሰጥሽ ትጠይቂኝ ነበር፤ እኔም ሕይወት የሚያስገኝ ውኃ እሰጥሽ ነበር።’ ሴትየዋም ‘ምን ማለትህ ነው? አንተ የውኃ መቅጃ እንኳ የለህም’ አለችው። ከዚያም ኢየሱስ ‘እኔ የምሰጠውን ውኃ የሚጠጣ ሰው ድጋሚ አይጠማም’ አላት። ሴትየዋም ‘ጌታዬ፣ እባክህ ይህን ውኃ ስጠኝ’ አለችው።

ከዚያም ኢየሱስ ‘ሂጂና ባልሽን ይዘሽ ነይ’ አላት። እሷም ‘ባል የለኝም’ አለችው። እሱም እንዲህ አላት፦ ‘እውነትሽን ነው። አምስት ጊዜ አግብተሽ ነበር፤ አሁን አብሮሽ የሚኖረው ሰው ደግሞ ባልሽ አይደለም።’ ሴትየዋም እንዲህ አለች፦ ‘ጌታዬ፣ አንተ ነቢይ እንደሆንክ አሁን አወቅኩ። እኛ ሳምራውያን በዚህ ተራራ ላይ አምላክን ማምለክ እንደምንችል እናምናለን፤ አይሁዳውያን ግን ማምለክ የምንችለው በኢየሩሳሌም ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ። መሲሑ ሲመጣ አምላክን እንዴት ማምለክ እንዳለብን እንደሚነግረን አምናለሁ።’ ኢየሱስም ‘መሲሑ እኔ ነኝ’ በማለት ከዚያ በፊት ለማንም ሰው ተናግሮ የማያውቀውን ነገር ነገራት።

ሴትየዋ በፍጥነት ወደ ከተማዋ ሄደችና ሳምራውያኑን እንዲህ አለቻቸው፦ ‘መሲሑን ያገኘሁት መሰለኝ። እሱ ስለ እኔ ሁሉንም ነገር ያውቃል። መጥታችሁ ማየት ትችላላችሁ!’ እነሱም እሷን ተከትለው ወደ ጉድጓዱ ሄዱና ኢየሱስ ሲያስተምር ያዳምጡ ጀመር።

ሳምራውያኑ ኢየሱስን በከተማቸው ውስጥ ለተወሰኑ ቀናት እንዲቆይ ጠየቁት። ኢየሱስም ለሁለት ቀናት በዚያ የሚገኙ ሰዎችን አስተማረ፤ ብዙ ሰዎችም በእሱ አመኑ። እነሱም ሳምራዊቷን ሴት ‘አሁን ኢየሱስ የሚያስተምረውን እኛ ራሳችን ስለሰማን እሱ በእርግጥ የዓለም አዳኝ እንደሆነ አውቀናል’ አሏት።

“‘ና!’ . . . የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግ ሁሉ የሕይወትን ውኃ በነፃ ይውሰድ።”—ራእይ 22:17