በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 92

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በድጋሚ ታየ

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በድጋሚ ታየ

ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ከተገለጠ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጴጥሮስ ወደ ገሊላ ባሕር ሄዶ ዓሣ ለማጥመድ አሰበ። ቶማስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና አንዳንድ ሌሎች ደቀ መዛሙርትም አብረውት ሄዱ። ሌሊቱን ሙሉ ዓሣ ለማጥመድ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።

በቀጣዩ ቀን ጠዋት ላይ አንድ ሰው በባሕሩ ዳርቻ ቆሞ አዩ። እሱም ‘ዓሣ ያዛችሁ?’ ብሎ ጠየቃቸው። እነሱም “አልያዝንም!” አሉት። ከዚያም ሰውየው “መረቡን ከጀልባዋ በስተ ቀኝ ጣሉት” አላቸው። ልክ እሱ እንደነገራቸው ሲያደርጉ መረቡ ብዙ ዓሣ ከመያዙ የተነሳ ሊጎትቱት አልቻሉም። በዚህ ጊዜ ዮሐንስ ሰውየው ኢየሱስ መሆኑን አወቀ፤ ከዚያም “ጌታ እኮ ነው!” አለ። ጴጥሮስ ወዲያውኑ ወደ ውኃው ዘሎ በመግባት እየዋኘ ወደ ባሕሩ ዳር ሄደ። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርትም በጀልባ ተከተሉት።

ወደ ባሕሩ ዳርቻ እንደደረሱ ዳቦና በእሳት ላይ እየተጠበሰ ያለ ዓሣ አዩ። ኢየሱስም ከያዙት ዓሣ ላይ የተወሰነውን እንዲያመጡ ነገራቸው። ከዚያም ‘ኑ፣ ቁርስ ብሉ’ አላቸው።

ቁርስ በልተው ከጨረሱ በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን ‘ዓሣ ከማጥመድ ሥራህ የበለጠ ትወደኛለህ?’ አለው። ጴጥሮስም “አዎ፣ ጌታ ሆይ፣ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” አለው። ከዚያም ኢየሱስ “ጠቦቶቼን መግብ” አለው። ኢየሱስ በድጋሚ ‘ጴጥሮስ፣ ትወደኛለህ?’ ብሎ ጠየቀው። ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ፣ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም “ግልገሎቼን ጠብቅ” አለው። ኢየሱስ ጴጥሮስን ለሦስተኛ ጊዜ ጠየቀው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በጣም አዘነ። ከዚያም ‘ጌታ ሆይ፣ አንተ ሁሉንም ነገር ታውቃለህ። በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ’ አለው። ኢየሱስም “ግልገሎቼን መግብ” አለው። ይህን ካለ በኋላም ለጴጥሮስ “እኔን መከተልህን ቀጥል” የሚል ምክር ሰጠው።

“[ኢየሱስም] ‘ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ’ አላቸው። እነሱም ወዲያውኑ መረቦቻቸውን ትተው ተከተሉት።”—ማቴዎስ 4:19, 20