በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 94

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስ ተቀበሉ

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስ ተቀበሉ

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ ከአሥር ቀን በኋላ ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስ ተቀበሉ። በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ ዕለት ብዙ ሰዎች በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ነበር። በዚያ ቀን 120 ገደማ የሚሆኑ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሰገነት ላይ በሚገኝ ክፍል ውስጥ ተሰብስበው ነበር። ድንገት አንድ አስደናቂ ነገር ተፈጸመ። እሳት የሚመስል ነገር በእያንዳንዱ ደቀ መዝሙር ራስ ላይ ታየ፤ ከዚያም ሁሉም በተለያዩ ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ። እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ድምፅ ተሰብስበውበት የነበረውን ቤት ሞላው።

ከተለያዩ አገሮች ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሰዎች ይህን ድምፅ ሲሰሙ ምን እንደተፈጠረ ለማየት ደቀ መዛሙርቱ ወደተሰበሰቡበት ቤት ሄዱ። እነሱም ደቀ መዛሙርቱ በተለያዩ ቋንቋዎች ሲናገሩ ሲሰሙ በጣም ተደነቁ። እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ ‘እነዚህ ሰዎች የገሊላ ሰዎች አይደሉም እንዴ? ታዲያ በእኛ ቋንቋ መናገር የቻሉት እንዴት ነው?’

ከዚያም ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ቆሙ። ጴጥሮስም ኢየሱስ የተገደለውና ይሖዋ ከሞት ያስነሳው እንዴት እንደሆነ ለሕዝቡ ተናገረ። እንዲህ አለ፦ ‘አሁን ኢየሱስ በሰማይ ላይ በአምላክ ቀኝ ተቀምጦ ይገኛል፤ እሱም ቃል በገባው መሠረት መንፈስ ቅዱስን አፈሰሰ። እናንተ ያያችሁትና የሰማችሁት ተአምር የተፈጸመው ለዚህ ነው።’

ሰዎቹም ጴጥሮስ የተናገረውን ሲሰሙ ልባቸው ተነክቶ “ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” በማለት ጠየቁ። ጴጥሮስም ‘ከኃጢአታችሁ ንስሐ ግቡ፤ እንዲሁም በኢየሱስ ስም ተጠመቁ። የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ትቀበላላችሁ’ አላቸው። በዚያ ቀን 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተጠመቁ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በኢየሩሳሌም የሚገኙት ደቀ መዛሙርት ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ማደግ ጀመረ። ሐዋርያቱም ኢየሱስ ያዘዛቸውን ነገር በሙሉ ለደቀ መዛሙርቱ ለማስተማር ሲሉ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ተጨማሪ ጉባኤዎችን አቋቋሙ።

“ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ በይፋ ብትናገር እንዲሁም አምላክ ከሞት እንዳስነሳው በልብህ ብታምን ትድናለህ።”—ሮም 10:9