በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 11

የአብርሃም እምነት ተፈተነ

የአብርሃም እምነት ተፈተነ

አብርሃም፣ ልጁ ይስሐቅ ይሖዋን እንዲወድና እሱ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዲኖረው አስተምሮታል። ሆኖም ይስሐቅ 25 ዓመት አካባቢ ሲሆነው ይሖዋ አብርሃምን አንድ በጣም ከባድ ነገር እንዲያደርግ ጠየቀው። ይሖዋ ለአብርሃም ያቀረበው ጥያቄ ምን ነበር?

አምላክ አብርሃምን ‘እባክህ አንድ ልጅህን ወስደህ በሞሪያ ምድር በሚገኝ ተራራ ላይ መሥዋዕት አድርገህ አቅርበው’ አለው። አብርሃም፣ ይሖዋ እንዲህ እንዲያደርግ የጠየቀው ለምን እንደሆነ አላወቀም ነበር። ቢሆንም ይሖዋን ታዟል።

በማግስቱ ጠዋት አብርሃም ይስሐቅንና ሁለት አገልጋዮቹን ይዞ ወደ ሞሪያ ሄደ። ለሦስት ቀን ከተጓዙ በኋላ ከርቀት ተራራው ታያቸው። አብርሃም፣ እሱና ይስሐቅ መሥዋዕት አቅርበው እስኪመለሱ ድረስ አገልጋዮቹ እዚያው እንዲቆዩ ነገራቸው። አብርሃም ለእሳት ማንደጃ የሚሆነውን እንጨት ይስሐቅ እንዲሸከም አደረገ፤ እሱ ደግሞ ቢላውን ያዘ። ይስሐቅ አባቱን ‘መሥዋዕት የምናደርገው በግ የት አለ?’ ብሎ ጠየቀው። አብርሃምም ‘ልጄ፣ በጉን ይሖዋ ያዘጋጃል’ ብሎ መለሰለት።

በመጨረሻም ተራራው ጋ ሲደርሱ መሠዊያ ሠሩ። ከዚያም አብርሃም የይስሐቅን እጆችና እግሮች አስሮ መሠዊያው ላይ አስተኛው።

አብርሃም ቢላውን አነሳ። በዚህ ጊዜ የይሖዋ መልአክ ከሰማይ እንዲህ አለው፦ ‘አብርሃም፣ ልጁን እንዳትነካው! ልጅህን እንኳ መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ስለሆንክ በአምላክ ላይ እምነት እንዳለህ አሁን አወቅኩ።’ ከዚያም አብርሃም አንድ አውራ በግ ቀንዶቹ በዛፍ ቅርንጫፎች ተይዘው አየ። ወዲያውኑ ይስሐቅን ፈታውና በጉን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ።.

ከዚያ ቀን አንስቶ ይሖዋ አብርሃምን ‘ወዳጄ’ በማለት ይጠራው ጀመር። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? አብርሃም፣ ይሖዋ አንድ ነገር እንዲያደርግ ያዘዘው ለምን እንደሆነ ቢገባውም ባይገባውም ምንጊዜም ይታዘዝ ነበር።

ከዚያም ይሖዋ ለአብርሃም ‘እባርክሃለሁ፤ ዘርህን ወይም ልጆችህን አበዛልሃለሁ’ በማለት በድጋሚ ቃል ገባለት። በተጨማሪም ይሖዋ ጥሩ ሰዎችን በሙሉ በአብርሃም ቤተሰብ በኩል እንደሚባርክ ቃል ገባ።

“አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐንስ 3:16