በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሃይማኖት

ሃይማኖት

ፍቺ:- የአምልኮ ዓይነት ነው። ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን፣ እምነቶችንና ልማዶችን ይጨምራል። እነዚህም ግላዊ ወይም ድርጅታዊ አቋም ሊሆኑ ይችላሉ። አብዛኛውን ጊዜ ሃይማኖት በአምላክ ወይም በተለያዩ አማልክት ማመንን ወይም ሰዎችን፣ ዕቃዎችን፣ ፍላጎቶችን ወይም ኃይሎችን ማምለክን ይጨምራል። ብዙዎቹ ሃይማኖቶች የሰዎች ልጆች ተፈጥሮን ከማጥናት የመነጩ ናቸው። በተጨማሪም አምላክ ለሰው የገለጠለት ሃይማኖት አለ። እውነተኛም ሐሰተኛም ሃይማኖት አለ።

ይህን ያህል ብዙ ሃይማኖቶች የኖሩት ለምንድን ነው?

በቅርብ ጊዜ የወጣ ሰንጠረዥ 10 ዋና ዋና ሃይማኖቶችና 10,000 የሚያክሉ ቡድኖች እንዳሉ አመልክቷል። ከእነዚህ መካከል 6,000 የሚያክሉት በአፍሪካ፣ 1,200 የሚያክሉት በዩናይትድ ስቴትስና በመቶ የሚቆጠሩ ደግሞ በሌሎች አገሮች የሚገኙ ናቸው።

አዳዲስ ሃይማኖታዊ ቡድኖች እንዲቋቋሙ ያደረጉ ብዙ ምክንያቶች አሉ። የተለያዩት ሃይማኖቶች ሃይማኖታዊ እውነት የሚገለጥባቸው የተለያዩ መንገዶች ናቸው የሚሉ አሉ። ይሁን እንጂ የእነዚህ ሃይማኖቶች ትምህርቶችና ልማዶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ቢነጻጸሩ ይህን የሚያክሉ የተለያዩ ሃይማኖቶች የኖሩት ሰዎች አምላክን ከማዳመጥ ይልቅ የሰዎች ተከታዮች በመሆናቸው እንደሆነ እንገነዘባለን። እነዚህ ሃይማኖቶች በጋራ የሚያምኑባቸው ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚጻረሩት ትምህርቶች ከጥንቷ ባቢሎን የመነጩ መሆናቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው። (በገጽ 49, 50 ላይ “ታላቂቱ ባቢሎን” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።)

እንዲህ ያለውን ሃይማኖታዊ ዝብርቅ የጠነሰሰው ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ዓለም አምላክ” ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ይናገራል። (2 ቆሮ. 4:4) በተጨማሪም ‘አሕዛብ የሚሠዉት ለአምላክ ሳይሆን ለአጋንንት እንደሆነ’ ያስጠነቅቀናል። (1 ቆሮ. 10:20) ስለዚህ የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነውን እውነተኛ አምላክ የምናመልክ መሆናችንንና አምልኮታችንም እርሱን የሚያስደስተው መሆኑን ማረጋገጥ በጣም አስፈላጊ ነው።

ሃይማኖቶች ሁሉ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አላቸውን?

መሳ. 10:6, 7:- “የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ በኣሊምንና አስታሮትን የሶርያንም አማልክት፣ የሲዶናንም አማልክት፣ የሞዓብንም አማልክት፣ የአሞንንም ልጆች አማልክት፣ የፍልስጥኤማውያንንም አማልክት አመለኩ፤ እግዚአብሔርንም ተዉ፣ አላመለኩትምም። የእግዚአብሔርም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፣ በፍልስጥኤማውያንና በአሞን ልጆች ነደደ፣ በፍልስጥኤማውያንና በአሞን ልጆች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።” (አንድ ሰው የሰማይና የምድር ፈጣሪ ከሆነው እውነተኛ አምላክ ሌላ ማንኛውንም ነገር ወይም አካል ቢያመልክ ይህ ዓይነት አምልኮ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖረው ግልጽ ነው።)

ማር. 7:6, 7:- “እርሱ ግን [ኢየሱስ፣ አይሁዳዊ ፈሪሣውያንና ጸሐፍትን] እንዲህ አላቸው:- ኢሳይያስ ስለ እናንተ ስለ ግብዞች:- ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ።” (አንድ ቡድን አመልከዋለሁ የሚለው ማንንም ቢሆን የሚከተለው በመንፈስ አነሣሽነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ የተገለጸውን ሳይሆን የሰዎችን ትምህርት ከሆነ አምልኮቱ ከንቱ ነው።)

ሮሜ 10:2, 3 የ1980 ትርጉም:- “በትክክለኛ እውቀት አለመሆኑ ነው እንጂ እነርሱ ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ ቅንአት እንዳላቸው እኔ ራሴ እመሰክርላቸዋለሁ። እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያጸድቅበትን መንገድ ባለማወቃቸው የራሳቸውን የጽድቅ መንገድ ተከተሉ እንጂ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አልተከተሉም።” (ሰዎች የአምላክ ቃል በእጃቸው ሊኖር ይችላል። ግን ትክክለኛው ትምህርት ስላልተሰጣቸው ስለ ቃሉ ትክክለኛ እውቀት ላያገኙ ይችላሉ። ለአምላክ እንደሚቀኑ ይሰማቸው ይሆናል። ግን የሚያደርጉት እርሱ የሚፈልገውን ላይሆን ይችላል። አምልኮታቸው አምላክን አያስደስተውም።)

ሁሉም ሃይማኖት የራሱ ጥሩ ጎን አለው የሚባለው እውነት ነውን?

አብዛኞቹ ሃይማኖቶች መዋሸት ወይም መስረቅ ወይም እንዲህ የመሳሰሉትን ነገሮች ማድረግ ጥሩ እንዳልሆነ ያስተምራሉ። ግን ይህ ብቻ ይበቃልን? አንድ ሰው በብርጭቆው ውስጥ ያለው በአብዛኛው ውኃ ነው ስላለህ ብቻ በውስጡ ያለውን የተመረዘ ውኃ ትጠጣለህን?

2 ቆሮ. 11:14, 15:- “ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹም ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም።” (እዚህ ላይ ከሰይጣን የሚመነጭ ሁሉ ከውጭ መጥፎ ሆኖ ላይታይ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል። ሰይጣን ሰዎችን ከሚያስትባቸው ዘዴዎች አንዱ የሐሰት ሃይማኖት ነው። አንዳንዶቹ ሃይማኖቶች የጽድቅ መልክ ያላቸው ሆነው እንዲታዩ ያደርጋል።)

2 ጢሞ. 3:2, 5 የ1980 ትርጉም:- “ሰዎች . . . ሃይማኖት ያላቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን የሃይማኖትን ኀይል ይክዳሉ፤ ከእነዚህም ሰዎች ራቅ።” (የአምልኮ ባልንጀሮችህ ለአምላክ ፍቅር እንዳላቸው ቢናገሩም ቃሉን በሕይወታቸው ላይ የማይሠሩበት ከሆነ እንደነዚህ ካሉት ሰዎች እንድትለይ መጽሐፍ ቅዱስ ይመክርሃል።)

የወላጆችን ሃይማኖት መተው ትክክል ነውን?

ወላጆቻችን ያስተማሩን ከመጽሐፍ ቅዱስ ከሆነ አጥብቀን ልንከተለው ይገባል። የወላጆቻችን ሃይማኖታዊ እምነትና ልማድ ከአምላክ ቃል ጋር የማይስማማ መሆኑን ብናውቅም እንኳን ወላጆቻችንን ማክበር ይገባናል። ይሁን እንጂ ወላጆችህ የነበራቸው አንድ ዓይነት ልማድ ጤንነት የሚጎዳ ወይም ዕድሜ የሚያሳጥር እንደሆነ ብትገነዘብ ምን ታደርጋለህ? ይህን ልማዳቸውን ትከተላለህን? ልጆችህም እንዲከተሉት ታበረታታቸዋለህን? ወይስ የተማርከውን ነገር በአክብሮት ለወላጆችህ ታካፍላለህ? በተመሳሳይም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቅ ኃላፊነት ያስከትላል። የሚቻል ከሆነ የተማርነውን ነገር ለቤተሰባችን ማካፈል ይኖርብናል። ውሳኔ ማድረግ ይገባናል። አምላክን እንወዳለንን? የአምላክን ልጅ ለመታዘዝ ከልብ እንፈልጋለንን? ይህን ማድረግ የወላጆቻችንን ሃይማኖት ትተን እውነተኛውን አምልኮ እንድንይዝ ሊጠይቅብን ይችላል። ለወላጆቻችን ያለን አክብሮት ለአምላክና ለክርስቶስ ካለን ፍቅር ሊበልጥብን አይገባም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።”—ማቴ. 10:37

ኢያሱ 24:14:- “አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፣ በፍጹምም በእውነተኛም ልብ አምልኩት፤ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፣ እግዚአብሔርንም አምልኩ።” (የአባቶቻቸውን ሃይማኖት መለወጥ ነበረባቸው ማለት ነው። አይደለም እንዴ? ይሖዋን ተቀባይነት ባለው ሁኔታ ለማምለክ በቀደመው ሃይማኖታቸው ይገለገሉባቸው የነበሩትን ምስሎች ማስወገድና ለእነዚህ ነገሮች ያላቸውን ፍላጎት ከልባቸው ማውጣት ነበረባቸው።)

1 ጴጥ. 1:18, 19:- “ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፣ ነውርና እድፍ እንደሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ።” (በዚህ ምክንያት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ከአባቶቻቸው ልማዶች ርቀዋል። እነዚህ ልማዶች የዘላለም ሕይወት ሊያስገኙላቸው አይችሉም ነበር። የአባቶቻቸው ልማዶች አምላክን የሚያስከብሩ ስላልነበሩ ለክርስቶስ መሥዋዕት ያላቸው አመስጋኝነት ሕይወታቸውን ፍሬ ቢስና ትርጉም የለሽ ሊያደርግ የሚችለውን ማንኛውም ነገር እንዲያስወግዱ አነሣሥቷቸዋል። እኛስ ይህን የመሰለ አቋም ሊኖረን አይገባምን?)

መጽሐፍ ቅዱስ ሃይማኖቶችን ስለ መቀላቀል ምን አመለካከት አለው?

ኢየሱስ ጻድቃን መስለው እየታዩ ለአምላክ አክብሮት ስላልነበራቸው ሃይማኖታዊ መሪዎች ምን አመለካከት ነበረው? “ኢየሱስም አላቸው:- እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቼአለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና። . . . እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞች ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፣ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። እኔ ግን እውነትን የምናገር ስለ ሆንሁ አታምኑኝም። . . . እናንተ ከእግዚአብሔር አይደላችሁምና ስለዚህ አትሰሙም።”—ዮሐ. 8:42–47

የአምላክ አገልጋዮች አምላክ የሚያወግዛቸውን ነገሮች የሚያደርጉ ወይም አምላክ የሚያወግዛቸውን ልማዶች የሚደግፉ ሰዎችን በሃይማኖታዊ ወንድማማችነት ቢቀበሉ ለአምላክና ለጽድቅ ደረጃዎቹ ታማኝ ሆነው መቆማቸው ነውን? “ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብን የሚመኝ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካር ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ። . . . እንደነዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን አትብሉ። . . . ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖት የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች [ከተፈጥሮ ውጪ የሆኑ ነገሮች የሚሠሩ] ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ [“ስግብግቦች” አዓት ] ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” (1 ቆሮ. 5:11፤ 6:9, 10) “የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።” (ያዕ. 4:4) “እግዚአብሔርን የምትወድዱ ክፋትን ጥሉ፤ እግዚአብሔር የቅዱሳኑን [“የታማኞቹን” አዓት] ነፍሶች ይጠብቃል።”—መዝ. 97:10

2 ቆሮ. 6:14–17:- “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? . . . ስለዚህም ጌታ:- ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኩስንም አትንኩ ይላል፤ . . . እኔም እቀበላችኋለሁ።”

ራእይ 18:4, 5:- “ከሰማይም ሌላ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል:- ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤ ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፣ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ።” (ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት “ታላቂቱ ባቢሎን” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።)

 የአንድ የተደራጀ ሃይማኖት አባል መሆን አስፈላጊ ነውን?

አብዛኞቹ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች መጥፎ ፍሬ አፍርተዋል። መጥፎ የሆነው የሃይማኖቶቹ መደራጀት አይደለም። ብዙዎች የተደራጁ ሃይማኖቶች በሐሰት ትምህርቶች ላይ የተመሠረቱና በአብዛኛው መንፈሳዊ መመሪያ ከመስጠት ይልቅ በአምልኮ ሥርዓቶች ላይ ያተኮሩ የአምልኮ ዓይነቶች ናቸው። የሌሎችን ሕይወት በመቆጣጠር የስስት ግባቸውን ለማሳካት ተገልግለውባቸዋል። እነዚህ ሃይማኖቶች ከመንፈሳዊ ነገሮች ይልቅ ገንዘብ ለመሰብሰብና ያጌጡ የአምልኮ ቤቶችን ለመሥራት የበለጠ ትኩረት ሰጥተዋል። አባሎቻቸውም በአብዛኛው ግብዞች ናቸው። ጽድቅን የሚወድ ማንም ሰው እንደነዚህ ያሉት ድርጅቶች ተባባሪ ለመሆን እንደማይፈልግ ግልጽ ነው። እውነተኛው ሃይማኖት ግን ከእነዚህ ሁሉ የተለየ ነው። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን ብቃቶች ለሟሟላት እውነተኛውም ሃይማኖት ቢሆን የተደራጀ መሆን ይኖርበታል።

ዕብ. 10:24, 25:- “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶች ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” (ይህንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዝ ለመፈጸም አዘውትረን የምንገኝበት ክርስቲያናዊ ስብሰባ መኖር አለበት። እንዲህ ያለው ዝግጅት ስለ ራሳችን ብቻ ከማሰብ ይልቅ ለሌሎች ያለንን ፍቅር እንድናሳይ ያበረታታናል።)

1 ቆሮ. 1:10:- “ወንድሞች ሆይ፣ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።” (ግለሰቦች አንድ ላይ ካልተሰበሰቡ፣ ከአንድ ዓይነት መንፈሳዊ የመመገቢያ ፕሮግራም ካልተጠቀሙና ይህን መንፈሣዊ ትምህርት እያዘጋጀ እንዲያቀርብ የተመደበውን አካል ካላከበሩ እንዲህ ያለውን አንድነት ማግኘት አይቻልም። በተጨማሪ ዮሐንስ 17:20, 21⁠ን ተመልከት።)

1 ጴጥ. 2:17 አዓት:- “ለመላው የወንድሞች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ።” (ይህ የሚናገረው በአንድ የተወሰነ የግል ቤት ውስጥ ለአምልኮ ስለሚሰበሰቡ ሰዎች ብቻ ነውን? በፍጹም አይደለም። በ⁠ገላትያ 2:8, 9 እና በ⁠1 ቆሮንቶስ 16:19 ላይ እንደተመለከተው ዓለም አቀፍ የወንድማማችነት ማኅበር ነው።)

ማቴ. 24:14:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (አሕዛብ ሁሉ ይህን ምሥራች የመስማት አጋጣሚ እንዲያገኙ ከተፈለገ የስብከቱ ሥራ በተቀነባበረ መልክና ተገቢ የበላይ አመራር ባለው ሁኔታ መከናወን ይኖርበታል። በዓለም በሙሉ የሚኖሩ ሰዎች ለአምላክና ለሰዎች ባላቸው ፍቅር ተነሣሥተው ይህን ሥራ ለመሥራት ጥረታቸውን አስተባብረዋል።)

በተጨማሪም “ድርጅት” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።

 የሚያስፈልገው ሌላውን ሰው መውደድ ብቻ ነውን?

እንዲህ ያለው ፍቅር አስፈላጊነቱ ከፍተኛ ለመሆኑ ምንም አያጠራጥርም። (ሮሜ 13:8–10) ይሁን እንጂ ክርስቲያን መሆን ለሰው ደግ በመሆን ብቻ የሚወሰን አይደለም። ኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ አንዳቸው ለሌላው ማለትም ለእምነት ባልንጀሮቻቸው በሚያሳዩት ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል። (ዮሐ. 13:35) የዚህ አስፈላጊነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተደጋግሞ ተገልጿል። (ገላ. 6:10፤ 1 ጴጥ. 4:8፤ 1 ዮሐ. 3:14, 16, 17) ይሁን እንጂ ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ለአምላክ ያለን ፍቅር እንደሆነ ኢየሱስ አመልክቷል። ይህ ፍቅር የሚገለጸው የአምላክን ትእዛዞች በመፈጸም ነው። (ማቴ. 22:35–38፤ 1 ዮሐ. 5:3) እንዲህ ያለውን ፍቅር በተግባር ለማሳየት የአምላክን ቃል ማጥናትና በሥራ ላይ ማዋል እንዲሁም ከአምላክ አገልጋዮች ጋር ለአምልኮ አንድ ላይ መሰብሰብ ያስፈልገናል።

ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና ማበጀት የግድ አስፈላጊ ነገር ነውን?

ይህ በእርግጥ አስፈላጊ ነው። በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ መገኘት ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና ለማበጀት ምትክ ሊሆን አይችልም። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ መጠንቀቅ ያስፈልገናል። ለምን? በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዳላቸው ያምኑ የነበሩ ኢየሱስ ግን በጣም የተሳሳቱ እንደሆኑ የገለጻቸው ሰዎች ነበሩ። (ዮሐ. 8:41–44) ሐዋርያው ጳውሎስም በእርግጥ ስለ እምነታቸው ቀናተኞች ስለሆኑና ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዳላቸው ያስቡ ስለነበሩ ሰዎች ጽፏል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚፈለግባቸው አልተገነዘቡም ነበር።—ሮሜ 10:2–4

የአምላክን ትእዛዛት እንደ ቀላል ነገር አድርገን ብንመለከት ከአምላክ ጋር ጥሩ የግል ዝምድና ሊኖረን ይችላልን? ከእነዚህ ትእዛዞች አንዱ ከእምነት ባልደረቦቻችን ጋር አዘውትረን መሰብሰብ ነው።—ዕብ. 10:24, 25

 መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን ብናነብ ይህ ብቻ በቂ ይሆናልን?

ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለብቻቸው ቢያነቡ ብዙ እውቀት ሊያገኙ እንደሚችሉ አይካድም። ዓላማቸው የአምላክን እውነትና ዓላማዎቹን ለማወቅ ከሆነ ይህ በጣም የሚያስመሰግን ዓላማ ነው። (ሥራ 17:11) ይሁን እንጂ ነገሩን በሐቀኝነት ከተመለከትን አለማንም እርዳታ መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ ለመረዳት እንችላለንን? መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች ለመረዳት የሌላ ሰው እርዳታ እንደሚያስፈልገው ስለተናገረ ከፍተኛ ሹመት የነበረው ሰው ይናገራል። ይህንንም እርዳታ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ከነበረ ሰው አገኘ።—ሥራ 8:26–38፤ በ⁠ሥራ 6:1–6፤ 8:5–17 ላይ ስለ ፊሊጶስ ከተነገረው ጋር አወዳድር።

እርግጥ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ቢያነብና በሥራ ላይ ግን ባያውለው ምንም ጥቅም አያስገኝለትም። መጽሐፍ ቅዱስን ቢያምንና በሥራ ላይ ቢያውለው ደግሞ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በጉባኤ ስብሰባቸው አዘውትሮ ይገኛል። (ዕብ. 10:24, 25) በተጨማሪም ከእነርሱ ጋር በመተባበር “ምሥራቹን” ለሌሎች ሰዎች ያካፍላል።—1 ቆሮ. 9:16፤ ማር. 13:10፤ ማቴ. 28:19, 20

  አንድ ሰው ትክክለኛው ሃይማኖት የትኛው እንደሆነ እንዴት ሊያውቅ ይችላል?

(1) የሃይማኖቱ ትምህርቶች በምን ላይ የተመሠረቱ መሆን አለባቸው? ትምህርቶቹ በአብዛኛው ከሰው የመነጩ ናቸው ወይስ ከአምላክ? (2 ጢሞ. 3:16፤ ማር. 7:7) ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሥላሴ እንደሆነ የሚያስተምረው የት ላይ ነው? የሰው ነፍስ የማትሞት እንደሆነች የሚያስተምረው የት ላይ ነው? ብለህ ጠይቅ።

(2) የአምላክን ስም የሚያሳውቅ መሆኑንና አለመሆኑን ተመልከት። ኢየሱስ ሲጸልይ “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥኩላቸው” ብሎ ነበር። (ዮሐ. 17:6) “ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና” ብሏል። (ማቴ. 4:10) ታዲያ የአንተ ሃይማኖት ይሖዋን ብቻ ማምለክ እንደሚገባ አስተምሮሃልን? ይሖዋ በተባለው ስም የሚታወቀውን አምላክም ዓላማዎቹን፣ ሥራዎቹንና ባሕርያቱን ባጠቃላይ የቅርብ ወዳጅህ እንደሆነ እስኪሰማህ ድረስ አውቀኸዋልን?

(3) ሃይማኖቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እውነተኛ እምነት እንዳለው በተግባር ያሳያልን? ይህን ማድረግ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው የኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወት ያለውን ዋጋ ማድነቅንና በአሁኑ ጊዜ ሰማያዊ ንጉሥ በመሆን ያገኘውን ቦታ መቀበልን ይጨምራል። (ዮሐ. 3:36፤ መዝ. 2:6–8) ይህ ዓይነቱ አድናቆትና ግንዛቤ የሚገለጸው ኢየሱስ ለተከታዮቹ በሰጠው ሥራ በቅንዓት በመካፈል ነው። እውነተኛው ሃይማኖት እንዲህ ያለ እምነት ስላለው እምነቱ በሥራ የተደገፈ ነው።—ያዕ. 2:26

(4) በአብዛኛው ውጫዊ የአምልኮ ሥርዓቶች የበዙበት ነው ወይስ የሕይወት መንገድ? አምላክ በታይታ ሥርዓቶች ላይ ብቻ የተመሠረቱ ሃይማኖቶችን አይቀበልም። (ኢሳ. 1:15–17) እውነተኛው ሃይማኖት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትክክለኛ ሥነ ምግባርና ንጹሕ አነጋገር ያወጣውን ደረጃ ያስከብራል እንጂ በደካማነት አብዛኛው ሰው የሚደግፈውን ዝንባሌ መከተልን አያበረታታም። (1 ቆሮ. 5:9–13፤ ኤፌ. 5:3–5) አባሎቹ በሕይወታቸው ውስጥ የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች ያሳያሉ። (ገላ. 5:22, 23) ስለዚህ እውነተኛውን አምልኮ የሚከተሉ ሰዎች በመሰብሰቢያ ቦታቸው ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ ኑሯቸው፣ በመሥሪያ ቤታቸው፣ በትምህርት ቤታቸውና በመዝናኛ ቦታዎች የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደረጃዎች ለመጠበቅ የሚጥሩ በመሆናቸው ተለይተው ይታወቃሉ።

(5) አባሎቹ በእውነት ይዋደዳሉን? ኢየሱስ “እርስ በእርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐ. 13:35) ይህ ዓይነቱ ፍቅር የዘር፣ የማኅበራዊ ኑሮና የብሔር ድንበሮችን ተሻግሮ የተለያዩ ሰዎችን በእውነተኛ ወንድማማችነት የሚያቀራርብ ነው። ይህ ፍቅራቸው በጣም ጠንካራ በመሆኑ የተለዩ ሰዎች መሆናቸው በቀላሉ ይታወቃል። ብሔራት ለጦርነት በሚዘምቱበት ጊዜ በሌሎች አገሮች ላሉ ወንድሞቻቸው ከፍተኛ ፍቅር ስላላቸው መሣሪያ አንሥተው እነርሱን ለመግደል ፈቃደኛ አይሆኑም። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የወሰዱት አቋም ይኸው ነበር።

(6) በእውነት ከዓለም የተለየ ነውን? ኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮቹ ‘ከዓለም እንዳይደሉ’ ተናግሯል። (ዮሐ. 15:19) አምላክ በሚፈልገው መንገድ እርሱን ለማምለክ ራሳችንን ‘ከዓለም እድፍ መጠበቅ’ ይፈለግብናል። (ያዕ. 1:27) ታዲያ ቀሳውስቶቻቸውና ሌሎች አባሎቻቸው በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ስለሚገቡ ወይም ሕይወታቸው በአብዛኛው ቁሳዊና ሥጋዊ ፍላጎቶችን በማሳደድ ላይ ስለተመሠረቱ ሃይማኖቶች እንዲህ ለማለት ይቻላልን?—1 ዮሐ. 2:15–17

(7) የሃይማኖቱ አባሎች ስለ አምላክ መንግሥት በትጋት ይመሠክራሉን? ኢየሱስ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴ. 24:14) ሰዎች ችግሮቻቸውን ለመፍታት ሰብዓዊ መስተዳድሮችን ተስፋ እንዲያደርጉ ከማበረታታት ይልቅ የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነች የሚያውጅ ሃይማኖት የትኛው ነው? ሃይማኖትህ በዚህ እንቅስቃሴ እንድትካፈልና ኢየሱስ ሐዋርያቱን አድርጉት ብሎ እንዳስተማረው ከቤት ወደ ቤት እየሄድክ እንድትሰብክ አስታጥቆሃልን?—ማቴ. 10:7, 11–13፤ ሥራ 5:42፤ 20:20

የይሖዋ ምሥክሮች ትክክለኛው ሃይማኖት የእነርሱ ሃይማኖት ብቻ እንደሆነ ያምናሉን?

ገጽ 204, 205 ላይ “የይሖዋ ምሥክሮች” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

አንዳንድ ሰዎች እምነት ሲኖራቸው ሌሎቹ የማይኖራቸው ለምንድን ነው?

እምነት” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘እኔ ስለ ሃይማኖት ግድ የለኝም’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ይህን ማለትዎ አያስደንቀኝም። ብዙ ሰዎች የእርስዎን የመሰለ አስተሳሰብ አላቸው። ግን እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበረዎት ነው?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘በጣም ካስደነቁኝ ነገሮች አንዱ አብያተ ክርስቲያናት የሚያስተምሯቸው ዋነኛ መሠረተ ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኙ መሆናቸው ነው። (በገጽ 204, 205 ላይ “የይሖዋ ምሥክሮች” በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን በተለይም ለመንግሥቲቱ የተለየ ትኩረት በመስጠት መጠቀም ትችላለህ። ለማነጻጸር ያህል የይሖዋ ምሥክሮች የሚያምኑትን በገጽ 199–201 እንደተገለጸው ለማብራራት ትችላለህ።)’

በተጨማሪም ገጽ 16, 17⁠ን ተመልከት።

‘በሃይማኖት ውስጥ ብዙ ግብዝነት ይታያል’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘አዎ፣ ከእርስዎ ጋር እስማማለሁ። ብዙዎች የሚሰብኩት ቃልና አኗኗራቸው አይጣጣምም። ስለ መጽሐፍ ቅዱስስ ምን ይሰማዎታል? (መዝ. 19:7–10)’

‘ጥሩ እየሠራሁ እኖራለሁ። በሰው ላይ መጥፎ ነገር አልሠራም። ይህ ለእኔ በቂ ሃይማኖት ነው’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ጥሩ እየሠሩ እንደሚኖሩ ስለነገሩኝ በደስታ ይኖራሉ ማለት ነው፤ አይደለም? . . . በዚህ በ⁠ራእይ 21:4 ላይ የተገለጸው ዓይነት ሁኔታ በሚሰፍንበት ዓለም ውስጥ ቢኖሩ ምን ይሰማዎታል? . . . እንዲህ ባለው ሁኔታ ለመኖር የሚያስፈልገው ነገር ምን እንደሆነ ዮሐንስ 17:3 የሚናገረውን ልብ ይበሉ።’

በተጨማሪም  ገጽ 326⁠ን ተመልከት።

‘የተደራጀ ሃይማኖት ውስጥ መግባት አልፈልግም። አስፈላጊው ነገር ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና መፍጠር እንደሆነ አምናለሁ’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ስለተናገሩት ነገር ብንወያይ ደስ ይለኛል። ከመጀመሪያ ጀምሮ እንዲህ ይሰማዎት ነበር? . . . ድሮ የአንድ ሃይማኖት አባል ነበሩ? . . . (ከዚያም  በገጽ 325–327 ላይ ያለውን ሐሳብ ተጠቀምበት።)’

‘የራሴ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውን በጠቅላላ አምንበታለሁ ለማለት አልችልም። ሃይማኖት የመለወጡ አስፈላጊነት ግን አይታየኝም። እዚያው ባለሁበት አንዳንድ ነገሮች እንዲሻሻሉ ባደርግ ሳይሻል አይቀርም’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ይህንን ስለነገሩኝ አመሰግናለሁ። ለሁላችንም አስፈላጊ የሆነው ነገር የአምላክን ድጋፍ ማግኘት ነው ብል እንደሚስማሙ እርግጠኛ ነኝ። ይህ እውነት አይደለም?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘አምላክ በ⁠ራእይ 18:4, 5 ላይ ሁላችንም እንድናስብበት የሚገባ አንድ አሳሳቢ ጉዳይ ገልጾልናል። . . . ስህተት የሆኑትን ነገሮች በግል ባንፈጽምም እነዚህን ድርጅቶች የምንደግፍ ከሆነ ከወንጀሉ ተካፋዮች እንደምንሆን መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። (በተጨማሪ “ታላቂቱ ባቢሎን” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት)’ (2) (በተጨማሪ  በገጽ 327–329 ያለውን ሐሳብ ተጠቀምበት።) (3) ‘አምላክ እውነትን የሚያፈቅሩ ሰዎችን እየፈለገ ነው፤ እነርሱንም አንድነት ላለው አምልኮ እየሰበሰባቸው ነው። (ዮሐ. 4:23, 24)’

‘ሁሉም ሃይማኖቶች ጥሩ ናቸው፤ አንተም የራስህ የሆነ ሃይማኖት አለህ፣ እኔም የራሴ አለኝ’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘እርስዎ አእምሮዎን ለውይይት ክፍት ያደረጉ ሰው የመስሉኛል። ነገር ግን ሁላችንም የአምላክ ቃል የሚሰጠን መመሪያ ያስፈልገናል ቢባል ይቀበላሉ። ሃይማኖት የያዙትም በዚህ ምክንያት ነው፤ እውነት አይደለም እንዴ?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘መጽሐፍ ቅዱስ በ⁠ማቴዎስ 7:13, 14 ላይ ኢየሱስ የተናገረውን በጣም ጠቃሚ መመሪያ ይሰጠናል። (አንብበው) . . . ይህ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው?’

በተጨማሪ  ገጽ 321, 322 ተመልከት።

‘በኢየሱስ እስካመንህ ድረስ የየትኛውም ቤተ ክርስቲያን አባል ብትሆን ለውጥ የለውም’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘በኢየሱስ ማመን አስፈላጊ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። እንደዚህ ብለው ሲናገሩ ኢየሱስ ያስተማረውን ሁሉ መቀበል ያስፈልጋል ማለትዎ እንደሆነ እገምታለሁ። ብዙዎቹ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ይህ ስም የሚወክለውን ነገር እንደማያሟሉ እኔም ሆንኩ እርስዎ የታዘብን መሆናችን ጥርጥር የለውም።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘እስቲ ኢየሱስ በ⁠ማቴዎስ 7:21–23 ላይ የተናገረውን ልብ ይበሉ።’ (2) ‘የአምላክ ፈቃድ ምን መሆኑን ለማወቅና ለማድረግ ለሚፈልጉት ሰዎች ወደፊት አስደናቂ ጊዜ ይጠብቃቸዋል። (መዝ. 37:10, 11፤ ራእይ 21:4)’

‘ትክክለኛ የሆነ አንድ ሃይማኖት ብቻ አለ ለማለት የሚያበቃችሁ ምንድን ነው?’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ ቅን የሆኑ ሰዎች መኖራቸው አያጠራጥርም። ነገር ግን ዋጋ ያለው የአምላክ ቃል የሚናገረው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስንት እውነተኛ ሃይማኖቶች አሉ ይላል? በ⁠ኤፌሶን 4:4, 5 ላይ የተጻፈውን እስቲ ይመልከቱ።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘ይህ አባባል ሌሎች ጥቅሶች ከሚገልጹት ሐሳብ ጋር ይስማማል። (ማቴ. 7:13, 14, 21፤ ዮሐ. 10:16፤ 17:20, 21)’ (2) ‘ስለዚህ እኛ ልንወጣው የሚገባው ፈተና ይህንን ሃይማኖት ለይቶ ማወቅ ነው። ይህን ሃይማኖት እንዴት ልናውቀው እንችላለን? (ምናልባት  በገጽ 327–329 ላይ ያለውን ሐሳብ ልትጠቀምበት ትችል ይሆናል።)’ (3) (በተጨማሪ በገጽ 199–201 ላይ “የይሖዋ ምሥክሮች” በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን ተመልከት።)

‘እቤቴ መጽሐፍ ቅዱስን አነባለሁ፤ እንዲገባኝም ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር አንብበው ጨርሰውታል?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘በሚያነቡበት ጊዜ በ⁠ማቴዎስ 28:19, 20 ላይ አንድ ጥሩ ነገር ያገኛሉ። . . . ይህ የሚታሰብበት ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ እውነተኛ ክርስቲያን ለመሆን የሚያስፈልገውን ነገር ለማወቅ እንድንችል እኛን ለመርዳት በሌሎች ሰዎች እንደሚጠቀም ያሳያል። የይሖዋ ምሥክሮችም ከዚህ ጋር በመስማማት በየሳምንቱ ለአንድ ሰዓት ያህል በነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት በቤታቸው ውስጥ ለማድረግ ሰዎችን ይጋብዛሉ። ይህን ውይይት እንዴት እንደምናደርግ ለጥቂት ደቂቃዎች ባሳይዎትስ?’

በተጨማሪ  ገጽ 327⁠ን ተመልከት።

‘ሃይማኖት የግል ጉዳይ እንደሆነ ይሰማኛል’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ይህ አመለካከት በአሁኑ ጊዜ የተለመደ ሆኗል። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመስማት ካልፈለጉ ወደ ሌሎች ቤቶች እንሄዳለን። ነገር ግን እርስዎን ለማነጋገር የመጣሁበት ምክንያት ኢየሱስ ተከታዮቹ ይህን እንዲያደርጉ በማዘዙ ምክንያት መሆኑን ያውቃሉ? . . . (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20፤ 10:40)’