በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሐዋርያዊ ተተኪነት

ሐዋርያዊ ተተኪነት

ፍቺ:- አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በመለኮታዊ ሹመት ሥልጣናቸውን የተረከቡ ተተኪዎች አሏቸው የሚል መሠረተ ትምህርት ነው። በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አቡኖች በአጠቃላይ የሐዋርያት ወራሾች ናቸው ሲባሉ ሊቃነ ጳጳሳቱ ደግሞ የጴጥሮስ ወራሽ ናቸው ተብሎ ይታመናል። የሮማ ሊቃነ ጳጳሳት ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ክርስቲያን ሁሉ ላይ የበላይነት ሥልጣን ሰጥቶታል እየተባለ በሚነገርለት በጴጥሮስ መንበር የሚቀመጡ፣ ለጴጥሮስ የተሰጠውን ሥራ የሚሠሩና የጴጥሮስ ቀጥተኛ ተተኪ ናቸው ይባላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም።

ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበት “ዓለት” ጴጥሮስ ነበርን?

ማቴ. 16:18:- “እኔም እልሃለሁ፣ አንተ ጴጥሮስ ነህ፣ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም [“የሔድስ” አዓት ] ደጆችም አይችሉአትም።” (ከጥቅሱ ፊትና ኋላ [ማለትም በቁጥር 13ና 20 ላይ] ያሉትን ሐሳቦች አስተውል። ውይይቱ ያተኮረው ኢየሱስ ማን ነው በሚለው ጥያቄ ላይ ነው።)

ሐዋርያው ጴጥሮስና ሐዋርያው ጳውሎስ “ዓለት” ወይም “የማዕዘን ድንጋይ” የሆነው ማን ነው ብለው ተረድተው ነበር?

ሥራ 4:8–11:- “ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ እንዲህ አላቸው:- እናንተ የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች፣ . . . እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደኅና ሆኖ በፊታችሁ እንደ ቆመ፣ ለእናንተ ለሁላችሁ ለእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን። እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፣ የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው።”

1 ጴጥ. 2:4–8:- “ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ [ወደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ] እየቀረባችሁ፣ እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፣ . . . መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ። በመጽሐፍ:- እነሆ፣ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ፣ በእርሱም የሚያምን አያፍርም ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲህ ክብሩ ለእናንተ ለምታምኑት ነው፤ ለማያምኑ ግን አናጢዎች የጣሉት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ የዕንቅፋትም ድንጋይ የማሰናከያም ዓለት ሆነ።”

ኤፌ. 2:20:- “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፣ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።”

አውጉስቲን (የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንደ ቅዱስ አድርጋ የምትቆጥራቸው ሰው) ምን ብለው ያምኑ ነበር?

“በክህነት ሥራ በቆየሁበት ጊዜ የዶናተስን ደብዳቤ በመቃወም መጽሐፍ ጽፌአለሁ። . . . በዚህ መጽሐፍ በአንደኛው ክፍል ላይ ስለ ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ቤተ ክርስቲያን የተሠራችበት ዓለት እርሱ ነው’ ብዬ ነበር። . . . ይሁን እንጂ በኋላ ላይ ደጋግሜ እንደገለጽኩት ጌታ ‘አንተ ጴጥሮስ ነህ፣ በዚህች ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፣’ በማለት የተናገረው ቃል ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ላይ እንደምትገነባ ያመለክታል። ጴጥሮስም ‘አንተ ክርስቶስ የሕያው አምላክ ልጅ ነህ’ በማለት ቤተ ክርስቲያን የምትሠራበት ዓለት ማን እንደሆነ ተናግሯል። ስለዚህ ከዚህ ዓለት በኋላ የተጠራው ጴጥሮስ በዚህ ዓለት ላይ የተሠራችውን ቤተ ክርስቲያን አካል ይወክል ነበር። ‘የመንግሥተ ሰማያትንም ቁልፎች’ ተቀብሏል። ‘አንተ ጴጥሮስ ነህ’ ተባለ እንጂ ‘አንተ ዓለት ነህ’ አልተባለም። ጴጥሮስ ስምዖን ተብሎ ይጠራ እንደነበረ ቤተ ክርስቲያን እንደምታምን ሁሉ ዓለቱ ክርስቶስ እንደሆነም ታምናለች።”—ዘ ፋዘርስ ኦቭ ዘ ቸርችሴይንት አውጉስቲን፣ ዘ ሪትራክሽንስ (ዋሽንግተን ዲሲ፣ 1968) ትርጉም በሜሪ አይ ቦጋን፣ 1ኛ መጽሐፍ፣ ገጽ 90

ሐዋርያት ጴጥሮስን ዋነኛቸው እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ነበርን?

ሉቃስ 22:24–26:- “ደግሞም ማናቸው ታላቅ ሆኖ እንዲቆጠር በመካከላቸው [በሐዋርያት መካከል] ጥያቄ ሆነ። እንዲህም አላቸው:- የአሕዛብ ነገሥታት ይገዙአቸዋል፣ በላያቸውም የሚሠለጥኑት ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን።” (“ዓለቱ” ጴጥሮስ ቢሆን ኖሮ ከመካከላቸው ማናቸው “ታላቅ ሆኖ እንዲቆጠር” ክርክር ይነሣ ነበርን?)

የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ነው፤ ታዲያ ተተኪ ያስፈልገዋልን?

ዕብ. 7:23–25:- “እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው [በእስራኤል ውስጥ] ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ [ኢየሱስ ክርስቶስ] ግን ለዘላለም የሚኖር ስለ ሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።”

ሮሜ 6:9:- “ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ፊት እንዳይሞት ሞትም ወደፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና።”

ኤፌሶን 5:23:- “ክርስቶስ . . . የቤተ ክርስቲያን ራስ [ነው።]”

ለጴጥሮስ የተሰጡት “ቁልፎች” ምን ነበሩ?

ማቴ. 16:19:- “የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች [“ቁልፎች” ጀባ ] እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፣ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።”

ኢየሱስ ለሰው ልጆች መብትና ልዩ አጋጣሚ ለመክፈት ራሱ ስለሚጠቀምበት ቁልፍ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ጠቅሷል

ራእይ 3:7, 8:- “የዳዊት መክፈቻ ያለው፤ የሚከፍት፣ የሚዘጋም የሌለ፤ የሚዘጋ የሚከፍትም የሌለ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው እርሱ እንዲህ ይላል:- . . . እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም።”

ጴጥሮስ የተሰጡትን “ቁልፎች” የአምላክን መንፈስ በመቀበል ወደ ሰማያዊት መንግሥት ለመግባት የሚያስችለውን አጋጣሚ (ለአይሁዶች፣ ለሳምራውያንና ለአሕዛብ ) ለመክፈት ተጠቅሞበታል

ሥራ 2:14–39:- “ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፣ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው:- አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፣ . . . ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም [አደረገው።] ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፣ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት:- ወንድሞች ሆይ፣ ምን እናድርግ? አሉአቸው። ጴጥሮስም:- ንስሐ ግቡ፣ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው።”

ሥራ 8:14–17:- “በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰምተው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሰደዱላቸው። እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው፤ በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና። በዚያን ጊዜ እጃቸውን ጫኑባቸው መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ።” (በዚህ ጊዜ ግንባር ቀደም የነበረው ጴጥሮስ እንደሆነ ቁጥር 20 ያመለክታል።)

ሥራ 10:24–48:- “በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ [ያልተገረዘው አሕዛብ] ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር። . . . ጴጥሮስም አፉን ከፍቶ እንዲህ አለ:- . . . ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ።”

ሰማይ የጴጥሮስን ውሣኔ ይጠብቅና አመራሩንም ይከተል ነበርን?

ሥራ 2:4, 14:- “በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፣ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር። . . . [የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ካነሣሣቸው በኋላ] ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፣ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው።” (ቁጥር 33⁠ን ተመልከት።)

ሥራ 10:19, 20:- “መንፈስ [ጴጥሮስን]:- እነሆ፣ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ ውረድ፣ እኔም ልኬአቸዋለሁና [አሕዛብ ወደሆነው ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ለመግባት] ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ አለው።”

ከ⁠ማቴዎስ 18:18, 19 ጋር አወዳድር።

ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ብቃት ያለው ማን እንደሆነና እንዳልሆነ የሚፈርደው ዳኛ ጴጥሮስ ነውን?

2 ጢሞ. 4:1:- “[ኢየሱስ ክርስቶስ] በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ [አለው።]”

2 ጢሞ. 4:8:- “ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፣ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ [ኢየሱስ ክርስቶስ] ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፣ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።”

ጴጥሮስ ሮም ነበርን?

በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሮም የሚለው ቃል በዘጠኝ ጥቅሶች ላይ ተጽፎ ይገኛል። አንዳቸውም ቢሆኑ ጴጥሮስ በሮም እንደነበረ አይገልጹም። አንደኛ ጴጥሮስ 5:13 ጴጥሮስ በባቢሎን እንደነበረ ይናገራል። ይህስ ሮምን የሚያመለክት ምሥጢራዊ አነጋገር ነበርን? ጴጥሮስ በባቢሎን መገኘቱ (ገላትያ 2:9 እንደሚያመለክተው) ለአይሁዶች እንዲሰብክ ከተሰጠው ሥራ ጋር ይስማማል፤ ምክንያቱም ብዙ አይሁዳውያን በባቢሎን ይኖሩ ነበር። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ (ኢየሩሳሌም፣ 1971፣ ጥራዝ 15፣ ዓምድ 755 ) የአይሁዳውያን የሕግና የሃይማኖት ማስተማሪያ መጽሐፍ የሆነው ታልሙድ በባቢሎን ስለመዘጋጀቱ ሲገልጽ በአንደኛው መቶ ዘመን በባቢሎን “ከፍተኛ የአይሁድ ትምህርት ቤቶች” እንደነበሩ ይገልጻል።

ከጴጥሮስ ጀምሮ አሁን እስካሉት ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ ያልተቋረጠ የተተኪዎች መስመር ነበርን?

ኢየሱሳዊው ጆን መኬንዚ በኖትር ዳም የሃይማኖት ፕሮፌሰር በነበሩበት ጊዜ እንዲህ ብለው ጽፈዋል:- “የቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን ማን ከማን እየተረካከበ እንደመጣ የተሟላ የውርስ ሐረግ ለማቅረብ የሚያስችል ታሪካዊ መረጃ የለም።”—ዘ ሮማን ካቶሊክ ቸርች (የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን)፣ (ኒው ዮርክ፣ 1969)፣ ገጽ 4

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ሲል ሐቁን አምኗል:- “. . . ሰነዶች ተሟልተው ባለመገኘታቸው ምክንያት በጥንት ጊዜ የጳጳሳት አስተዳደር እንዴት እንደተጀመረና እንደተስፋፋ በግልጽ ለማወቅ አልተቻለም። . . . ”—(1967)፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 696

ለአምላክና ለክርስቶስ ታዛዥ እስካልሆኑ ድረስ መለኮታዊ ሹመት ተቀብለናል ብሎ መናገሩ ምንም አይጠቅምም

ማቴ. 7:21–23:- “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች:- ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንት አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም:- ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።”

በተጨማሪ ኤርምያስ 7:9–15⁠ን ተመልከት።

የሐዋርያት ተተኪ ነን ባዮቹ የኢየሱስ ክርስቶስንና የሐዋርያቱን ትምህርትና ተግባር ይከተላሉን?

ኤ ካቶሊክ ዲክሽነሪ (የካቶሊክ መዝገበ ቃላት) እንዲህ ብሏል:- “የሮም ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፤ ምክንያቱም የሃይማኖት ትምህርቷ የተመሠረተው አንድ ጊዜ ለሐዋርያት በተገለጠው እምነት ላይ ነው። በዚህ እምነት ላይ ምንም ሳትጨምርና ከእርሱ ምንም ሳትቀንስ ትጠብቀዋለች።” (ለንደን፣ 1957፣ ደብልዩ ኢ አዲስ እና ቲ አርኖልድ፣ ገጽ 176) ሐቁ ከዚህ ጋር ይስማማልን?

የአምላክ ማንነት

“ሥላሴ የሚለው ቃል የክርስትናን ሃይማኖት ዋነኛ ትምህርት ለማመልከት የሚሠራበት ቃል ነው።”—ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ (1912)፣ ጥራዝ 15፣ ገጽ 47

“ሥላሴ የሚለው ቃልም ሆነ የሥላሴ ትምህርት በአዲስ ኪዳን ውስጥ አይገኝም። . . . ይህ ትምህርት ቀስ በቀስ እየተስፋፋ የሄደው በብዙ መቶ ዘመናትና በብዙ ክርክር ነው።”—ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ (1976)፣ ማይክሮፔድያ፣ ጥራዝ 10፣ ገጽ 126

“በጽሑፍ ሥራዎች ላይ ገለጻና ትርጉም የሚሰጡ ሰዎችና የመንፈሣዊ ኮሌጅ ሊቃውንት፣ ቁጥራቸው ያለማቋረጥ እያደገ የሄደ የሮም ካቶሊኮች ጭምር፣ ትልልቅ ለውጦች ካልተደረጉ በስተቀር በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሥላሴ ትምህርት ተገልጿል ብሎ ማንም ሊናገር እንደማይችል ይገነዘባሉ። በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን ቀኖናዎችን ታሪክ ያጠኑ ታሪክ ጸሐፊዎችና ሥርዓት ተከታይ የሆኑ የሃይማኖት ሊቃውንት ምንም ዓይነት ማስተካከያ ባልተደረገበት የሥላሴ ትምህርት የሚያምን ሰው ራሱን ክርስትና ከመነጨበት ዘመን አርቆ ወደ አራተኛው መቶ ዘመን የመጨረሻ ሩብ ማምጣቱ እንደሆነ ያምናሉ።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ (1967)፣ ጥራዝ 14፣ ገጽ 295

ብሕትውና (የቀሳውስት ሳያገቡ መኖር)

ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ ለጳጳሳት በጻፉት ሳክርዶታሊስ ሴሊባቱስ (የካህናት ብሕትውና፣ 1967) በተባለው ደብዳቤ ብሕትውና አንደኛው የካህናት ብቃት ነው ሲሉ አጽድቀውታል። ይሁን እንጂ “የክርስቶስንና የሐዋርያትን ትምህርት ጠብቆ ያቆየው አዲስ ኪዳን . . . ቅዱሳን አገልጋዮች በብሕትውና እንዲኖሩ አያዝም። . . . ኢየሱስ ራሱ አሥራ ሁለቱን ሲመርጥም ሆነ ሐዋርያት ለመጀመሪያዎቹ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ኃላፊዎች የሚሆኑትን ሲመርጡ ብሕትውናን መሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታ አድርገው አልተመለከቱም” በማለት ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።—ዘ ፓፓል ኢንሳይክሊካልስ 1958–1981 (ፎልስ ቸርች፣ ቨርጂኒያ፣ 1981)፣ ገጽ 204

1 ቆሮ. 9:5 ኒአባ :- “እንደ ሌሎች ሐዋርያት፣ እንደ ጌታ ወንድሞችና እንደ ኬፋ የምታምን ሚስት ለማግባት መብት የለንምን?” (“ኬፋ” በአረማይስጥ ቋንቋ ለጴጥሮስ የተሰጠ ስም ነው፤ ዮሐንስ 1:42⁠ን (በ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ቁጥር 43⁠ን) ተመልከት። በተጨማሪም የስምዖን ወይም የጴጥሮስ አማት ተብሎ የተነገረበትን ማርቆስ 1:29–31⁠ን ተመልከት።)

1 ጢሞ. 3:2 ዱዌይ:- “ስለዚህ ጳጳስ . . . የአንዲት ሚስት ባል [“አንድ ጊዜ ብቻ ያገባ” ኒአባ] ሊሆን ይገባዋል።”

ከክርስትና ዘመን በፊት የቡድሃ ሃይማኖት ቀሳውስትና ካህናት ሳያገቡ እንዲኖሩ ያዝ ነበር። (ሂስትሪ ኦቭ ሳክርዶታል ሴሊባሲ ኢን ዘ ክርስቲያን ቸርች (በቤተ ክርስቲያን የካህናት ብሕትውና ታሪክ)፣ ለንደን፣ 1932፣ አራተኛ እትም፣ እንደገና የተሻሻለ፣ ሄነሪ ሲ ሌ፣ ገጽ 6) ከዚህ ቀደም ብሎ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው የባቢሎን ካህናት ብሕትውና ይፈለግባቸው እንደነበር ኤ ሂሲሎፕ የተባሉት ሰው ዘ ቱ ባቢሎንስ (ሁለቱ ባቢሎኖች) በተባለው መጽሐፋቸው ገልጸዋል።—(ኒው ዮርክ፣ 1943)፣ ገጽ 219

1 ጢሞ. 4:1–3:- “መንፈስ . . . በግልጥ:- በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና . . . የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፣ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ . . . እነዚህ . . . መጋባትን ይከለክላሉ።”

ከዓለም መለየት

ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ በ1965 ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባሰሙት ንግግር እንዲህ ብለው ነበር:- “የምድር ሕዝቦች የመጨረሻው የስምምነትና የሰላም ተስፋ አድርገው በማሰብ ፊታቸውን ወደ ተባበሩት መንግሥታት አዙረዋል። የእነዚህን ሕዝቦችና የራሳችንን የአክብሮትና የተስፋ መግለጫ ለማቅረብ እንወዳለን።”—ዘ ፖፕስ ቪዚት (የሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት) (ኒው ዮርክ፣ 1965)፣ ታይም– ላይፍ ልዩ ሪፖርት፣ ገጽ 26

ዮሐ. 15:19 ጀባ:- “[ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ አለ:-] የዓለም ብትሆኑ ኖሮ ዓለም የራሱ እንደሆናችሁ አድርጎ ይወዳችሁ ነበር፤ ነገር ግን የዓለም ስላልሆናችሁና የእኔም ምርጫ ከዓለም ለይቶ ስላወጣችሁ ዓለም ይጠላችኋል።”

ያዕ. 4:4 ጀባ:- “ዓለምን ወዳጅ ማድረግ አምላክን ጠላታችሁ ማድረግ እንደሆነ አትገነዘቡምን?”

በጦር መሣሪያዎች መጠቀም

ካቶሊካዊው የታሪክ ምሁር ኢ አይ ዋትኪን እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ጳጳሳት በሀገራቸው መንግሥታት የተደረጉትን ጦርነቶች ያለማቋረጥ እንደደገፉ መናገር የሚዘገንን ቢሆንም ሞራልን ይጐዳል ወይም ታማኝነት የጐደለው ድርጊት ነው በሚል የተሳሳተ ምክንያት ታሪካዊ ሐቅ የሆነውን መካድ ወይም ችላ ማለት አንችልም። ብሔራዊ የቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣናት የትኛውንም ዓይነት ጦርነት ትክክለኛ ያልሆነ ጦርነት ነው ብለው ያወገዙበት፣ እኔ እንደማውቀው፣ አንድም ጊዜ የለም። . . . የካቶሊክ ጳጳሳት የቤተ ክርስቲያን ኦፊሴላዊ ንድፈ ሐሳብ ምንም ይሁን ምን በጦርነት ጊዜ በተግባራቸው ‘አገሬ ሁልጊዜ ትክክለኛ ናት’ የሚለውን መርሆ ይከተላሉ።”—ሞራልስ ኤንድ ሚሳይልስ (ለንደን፣ 1959) በቻርልስ ኤስ ቶምሰን የተዘጋጀ፣ ገጽ 57, 58

ማቴ. 26:52:- “በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው:- ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ።”

1 ዮሐ. 3:10–12:- “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። . . . እርስ በርሳችን እንዋደድ፤ . . . ከክፉው እንደነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም።”

ከዚህ በላይ በተገለጹት ሐሳቦች መሠረት የሐዋርያት ተተኪዎች ነን ባዮቹ ትምህርታቸው እና ተግባራቸው ክርስቶስ እና የእርሱ ሐዋርያት ካደረጉት ጋር በእርግጥ ይስማማልን?