በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መስቀል

መስቀል

ፍቺ:- በአብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና ተከታዮች ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ የተገደለበት መሣሪያ መስቀል ተብሎ ይጠራል። “ክሮስ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተወሰደው ክሩክስ ከሚለው የላቲን ቃል ነው።

የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ኢየሱስ በተለምዶ በሚታወቀው መስቀል ላይ ሳይሆን እጆቹን ከራሱ በላይ አድርጎ ቀጥ ባለ እን ጨት ላይ እንደተሰቀለ አድርገው የሚያሳዩት ለምንድን ነው?

በብዙ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “መስቀል” (“የመከራ እንጨት” አዓት ) ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል ስታዉሮስ ነው። በጥንቱ የግሪክኛ ቋንቋ ይህ ቃል ቀጥ ያለ እንጨት ወይም ምሰሶ ያመለክት ነበር። ከጊዜ በኋላ ቃሉ ቀጥ ባለው እንጨት ላይ ወደጎን የሚተላለፍ እንጨት የተደረበበትን የመግደያ እንጨት ለማመልከት ማገልገል ጀመረ። ዘ ኢምፔሪያል ባይብል ዲክሽነሪ እንዲህ በማለት ያረጋግጣል:- “መስቀል ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል [ስታዉሮስ ] ማንኛውም ነገር የሚሰቀልበትን ወይም [ለአጥር የሚሆንን] እንጨት ወይም ቀጥ ያለ ምሰሶ ወይም ግንድ ያመለክታል። . . . በሮማውያንም ዘንድ ቢሆን ክሩክስ (ክሮስ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተገኘበት ቃል) በመጀመሪያ ቀጥ ያለ ምሰሶ ማለት የነበረ ይመስላል።”—በፒ ፌርቤርን የተዘጋጀ (ለንደን፣ 1874)፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 376

ታዲያ የአምላክ ልጅ የተገደለው ይህን በመሰለ ቀጥ ባለ ምሰሶ ላይ ነበርን? መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተገደለበትን መሣሪያ ለማመልከት ክሲሎን በሚለው ቃል እንደሚጠቀም ልብ ማለት ይገባል። በሊዴልና ስኮት የተዘጋጀው ግሪክ–ኢንግሊሽ ሌክሲከን (ግሪክኛ–እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት) ክሲሎንን እንዲህ በማለት ተርጉሞታል:- “ተቆርጦ ጥቅም ላይ ለመዋል የተዘጋጀ እንጨት፣ የማገዶ እንጨት፣ ቀጥ ያለ እንጨት ወዘተ . . . ቁራጭ እንጨት፣ ግንድ፣ ምሰሶ፣ አጣና . . . ቆመጥ፣ ዱላ . . . ወንጀለኞች የሚሰቀሉበት ቀጥ ያለ እንጨት . . . እርጥብ እንጨት፣ ዛፍ። ” በተጨማሪ “በአዲስ ኪዳን ውስጥ መስቀል ” የሚል ትርጉም እንደተሰጠው ከገለጸ በኋላ በምሳሌነት ሥራ 5:30⁠ንና 10:39⁠ን ይጠቅሳል። (ኦክስፎርድ፣ 1968፣ ገጽ 1191, 1192) ይሁን እንጂ በእነዚህ ቁጥሮች ላይ ኪጄ፣ ሪስ፣ ጀባ እና ዱዌይ ክሲሎንን “ዛፍ” ብለው ተርጉመውታል። (ይህን አተረጓጎም ከ⁠ገላትያ 3:13⁠ና ከ⁠ዘዳግም 21:22, 23 ጋር አወዳድር።)

ዘ ነን ክርስቲያን ክሮስ (ክርስቲያናዊ ያልሆነው መስቀል) የተባለው የጄ ዲ ፓርሰንስ መጽሐፍ (ለንደን፣ 1896) እንዲህ ይላል:- “ከኢየሱስ አገዳደል ጋር በተያያዘ ሁኔታ የተጠቀሰው ስታዉሮስ የተባለው ቃል በተለምዶ ከሚታወቀው ስታዉሮስ የተለየ ነገርን ወይም በመስቀል መልክ እርስ በርሳቸው የተገናኙ ሁለት እንጨቶችን እንደሚያመለክት የሚያሳይ ቀጥተኛ ያልሆነ መረጃ እንኳን የአዲስ ኪዳን ክፍል በሆኑት የተለያዩ ጽሑፎች ውስጥ አይገኝም። . . . መምህሮቻችን በግሪክኛ የተጻፉትን የቤተ ክርስቲያን መዛግብት ወደ ቋንቋችን በሚተረጉሙበት ጊዜ ስታዉሮስ የሚለውን ቃል ‘መስቀል’ ብለው መተርጐማቸው ተራ የሆነ ቀላል ስህተት አይደለም። ለዚህ ስህተታቸው ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ስታዉሮስ የተባለው ቃል በሐዋርያት ዘመን የነበረው ትርጉም ይህ አለመሆኑን ሳይገልጹ ‘መስቀል’ የሚለው ቃል የስታዉሮስ ተመሳሳይ እንደሆነ አድርገው በቃላት መፍቻ መጻሕፍት ውስጥ አስገብተዋል። ይህም የሆነው በቂ ማስረጃ ተገኝቶ ሳይሆን ኢየሱስ የተገደለበት ያ የተለየ ስታዉሮስ የመስቀል ቅርጽ ነበረው ተብሎ ይታሰብ ስለነበረ ነው።”—ገጽ 23, 24፣ በተጨማሪም ዘ ኮምፓኒየን ባይብል (ለንደን፣ 1885)፣ ተጨማሪ ክፍል (አፔንዲክስ) ቁጥር 162⁠ን ተመልከት።

ስለዚህ ኢየሱስ የሞተው ቀጥ ባለ እንጨት ላይ እንጂ በተለምዶ በሚታወቀው መስቀል ላይ እንዳልነበረ የሚያሳይ በቂ ማስረጃ አለ።

የሕዝበ ክርስትና መስቀል ታሪካዊ አመጣጥ ምን ነበር?

“ከክርስትና ዘመን በፊት ጀምሮ በሁሉም የጥንቱ ዓለም ክፍሎች የተለያየ የመስቀል ቅርጽ ያለባቸው የተለያዩ ዕቃዎች ተገኝተዋል። በሕንድ፣ በሶሪያ፣ በፋርስና በግብፅ ቁጥር ስፍር የሌላቸው መስቀሎች ተገኝተዋል። . . . ከክርስትና በፊት በነበሩት ጊዜያትና ክርስቲያን ባልሆኑት ሕዝቦች መካከል መስቀልን እንደ አንድ ሃይማኖታዊ ምልክት አድርጎ መጠቀም በመላው ዓለም ላይ የተለመደ ልማድ ነበር ማለት ይቻላል። ብዙውን ጊዜም ከአንድ ዓይነት የተፈጥሮ አምልኮት ጋር የተያየዘ ነበር።”—ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ (1946)፣ ጥራዝ 6፣ ገጽ 753

“[ሁለት እንጨቶች የተጋጠሙበት] የመስቀል ቅርጽ የመጣው ከጥንትዋ ከላውዴዎን ሲሆን በዚያ አገርና እንደ ግብጽ በመሳሰሉት የአካባቢው አገሮች ተሙዝ ለተባለው የጣዖት አምላክ (ታው የተባለውን የምሥጢራዊ ስሙን የመጀመሪያ ፊደል ቅርጽ የያዘ ስለሆነ) እንደ ምልክት ሆኖ ያገለግል ነበር። በ3ኛው መቶ ዘመን (ዓ.ም.) አጋማሽ ላይ አብያተ ክርስቲያናት ከአንዳንዶቹ የክርስትና እምነት መሠረተ ትምህርቶች ርቀው ሄደው ወይም የሌሎችን እምነት መቅዳት ጀምረው ነበር። የከሃዲውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ክብር ለመጨመር አረማውያን ምንም የእምነት ለውጥ ሳያደርጉ የቀድሞ እምነቶቻቸውን ከነምልክቶቻቸው እንደያዙ የቤተ ክርስቲያን አባሎች እንዲሆኑ ተፈቀደላቸው። ስለሆነም ታው ወይም ብዙ ጊዜ T ቅርጽ ያለው ሃይማኖታዊ ምልክት የክርስቶስን መስቀል የሚወክል እንዲሆን አግዳሚው ቅርጽ ከላይ ከአናቱ ዝቅ እንዲል ተደረገ።”—አን ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታሜንት ወርድስ (ለንደን፣ 1962)፣ ደብልዩ ኢ ቫይን፣ ገጽ 256

“እንግዳ ሊመስል ቢችልም ክርስቶስ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊትና ከዚያም ወዲህ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ባልተዳረሰባቸው አገሮች መስቀል ቅዱስ ምልክት ሆኖ ሲሠራበት መቆየቱ የማይታበል ሐቅ ነው። . . . የግሪክ ባከስ፣ የጢሮስ ተሙዝ፣ የከለዳውያን ቤልና የኖርስ ኦዲን ሁሉም በአማኞቻቸው ዘንድ የመስቀል ቅርጽ ባለው ምልክት ይመሰሉ ነበር።”—ዘ ክሮስ ኢን ሪችዋል፣ አርክቴክቸር ኤንድ አርት (ለንደን፣ 1900)፣ ጂ ኤስ ታይአክ፣ ገጽ 1

“የግብጽ ካህናትና የሃይማኖት መሪዎች ነን ይሉ የነበሩት ነገሥታት የፀሐይ አምላክ ካህናት ስለነበሩ የሥልጣናቸው ምልክት አድርገው . . . ‘በክሩክስ አንሳታ’ ቅርጽ የተሠራ መስቀል በእጃቸው ይዘው ይዞሩ ነበር። እርሱም ‘የሕይወት ምልክት’ ይባል ነበር።”—ዘ ወርሽፕ ኦቭ ዘ ዴድ (የሙታን አምልኮ)፣ (ለንደን፣ 1904) ኮሎኔል ጄ ጋርኒር፣ ገጽ 226

“በብዙ ቦታዎች ልዩ ልዩ ቅርጽ ያላቸው የመስቀል ሥዕሎች በግብጽ ሐውልቶችና መቃብሮች ላይ ተገኝተዋል። በብዙ ምሁራን ዘንድ እነዚህ የመስቀል ቅርጽ ያላቸው ምስሎች [የወንድን ብልት] ወይም የግብረ ሥጋ ግንኙነትን የሚያመለክቱ ምስሎች እንደሆኑ ይገመታሉ። . . . በግብጽ አገር በሚገኙ መቃብሮች ክሩክስ አንሳታ [ክብ ቅርጽ ያለበት ወይም ከአናቱ ላይ መያዣ ያለው መስቀል] ከወንድ ብልት ቅርጽ ጋር ጐን ለጐን ተገኝቷል።” —ኤ ሾርት ሂስትሪ ኦቭ ሴክስ ወርሽፕ (የወሲብ አምልኮ አጭር ታሪክ) (ለንደን፣ 1940)፣ ኤች ከትነር፣ ገጽ 16, 17፤ በተጨማሪ ዘ ነን ክርስቲያን ክሮስ (ክርስቲያናዊ ያልሆነው መስቀል)፣ ገጽ 183⁠ን ተመልከት።

“እነዚህ መስቀሎች ለባቢሎን የፀሐይ አምላክ ምልክት ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የታዩት ከ100–44 ከክርስቶስ ልደት በፊት በጁሊየስ ቄሣር ዘመነ መንግሥት በተሠሩ ሣንቲሞች ላይ ነው። ከዚያ ቀጥሎ በ20 ከክርስቶስ ልደት በፊት በቄሣሩ ወራሽ (በአውግስጦስ) ዘመን በተሠሩ ሣንቲሞች ላይ ተስሏል። በቆስጠንጢኖስ ዘመን በታተሙ ሣንቲሞች ላይ ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ የታየው ምልክት ነው። ይኸው ተመሳሳይ ምልክት በዙሪያው ያለው ክብ ሳይጨመርበት አራት እኩል ርዝመት ያላቸው ቀጥተኛና አግዳሚ መስመሮች እንዲኖሩት ተደርጐ አገልግሏል። ይህም ‘የፀሐይ መሽከርከሪያ’ ተብሎ በተለይ ይከበር የነበረው ይህ ምልክት ነበር። ቆስጠንጢኖስ የፀሐይ አምላክ የተባለውን ጣዖት ያመልክ እንደነበረና ከሩብ መቶ ዘመን በኋላ ይህን መስቀል በሰማይ አይቻለሁ ብሎ እስከተናገረበት ጊዜ ድረስ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ እንደማያውቅ መግለጽ አስፈላጊ ነው።”—ዘ ኮምፓኒየን ባይብል፣ ተጨማሪ ክፍል (አፔንዲክስ) ቁጥር 162፤ በተጨማሪ ዘ ነን ክርስቲያን ክሮስ (ክርስቲያናዊ ያልሆነው መስቀል)፣ ገጽ 133–141⁠ን ተመልከት።

መስቀልን እንደ ቅዱስ ቆጥሮ ማክበር ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው ተግባር ነውን?

1 ቆሮ. 10:14:- “ወዳጆቼ ሆይ፣ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ።” (ጣዖት በከፍተኛ ደረጃ የሚወደድ፣ የሚከበር ወይም የሚመለክ ቅርጽ ወይም ምስል ነው።)

ዘጸ. 20:4, 5:- “በላይ በሰማይ ካለው፣ በታችም በምድር ካለው፣ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ [“አትሥራ።” አዓት] አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም።” (አምላክ ሕዝቦቹን ሰዎች የሚሰግዱለትን ምስል እንዳይሠሩ እንኳን ከልክሏቸው እንደነበረ ልብ በል።)

ቀጥሎ ያለው ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ ላይ የሠፈረ አስተያየት አስገራሚ ነው:- “ክርስቶስ በጐልጐታ አዳኝ ሆኖ መሞቱን የሚያሳየው ምስል በመጀመሪያዎቹ የክርስትና መቶ ዓመታት በነበረው የምስል ሥነ ጥበብ ሥራ ፈጽሞ አይታወቅም ነበር። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የተቀረጹ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም የሚከለክለውን የብሉይ ኪዳን ትእዛዝ በማክበር ጌታ መከራ የተቀበለበትን እንጨት እንኳ በሥዕል ለማሳየት ፈቃደኞች አልነበሩም።”—(1967)፣ ጥራዝ 4፣ ገጽ 486

ሂስትሪ ኦቭ ዘ ክርስቲያን ቸርች (የክርስትና እምነት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ) የተባለው መጽሐፍ ስለ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሲናገር “በመስቀል መጠቀምና የመስቀል ምስል መሥራት ፈጽሞ አይታወቅም ነበር” ብሏል።—(ኒው ዮርክ፣ 1897)፣ ጄ ኤፍ ሁርስት፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 366

አንድ ሰው እስካላመለከው ድረስ መስቀልን እንደ ክቡር ነገር ቆጥሮ ቢይዝ ስህተት ይሆናልን?

ከምትወዳቸው ጓደኞችህ መካከል አንዱ በሐሰት ቢከሰስና ሞት ተፈርዶበት ቢገደል እንዴት ይሰማሃል? የተገደለበትን መሣሪያ ምስል አሠርተህ ትይዛለህ ወይስ ታስወግደዋለህ?

በጥንት እስራኤላውያን ዘመን ለይሖዋ ታማኝ ያልነበሩት አይሁዶች ተሙዝ የተባለው የሐሰት አምላክ የሞተበትን ቀን በማስታወስ ያለቅሱ ነበር። ይሖዋ ያደርጉት የነበረው “አጸያፊ ነገር” እንደሆነ ተናግሯቸዋል። (ሕዝ. 8:13, 14 የ1980 ትርጉም ) ተሙዝ የባቢሎናውያን የሐሰት አምላክ እንደነበርና ምልክቱም መስቀል እንደነበረ ታሪክ ያስረዳል። ባቢሎን በናምሩድ ዘመን ከተቆረቆረችበት ዘመን ጀምራ የይሖዋ ተቃዋሚና የእውነተኛው አምልኮ ጠላት ሆና ኖራለች። (ዘፍ. 10:8–10፤ ኤር. 50:29) ስለዚህ አንድ ሰው መስቀልን እንደ ክቡር ነገር ቆጥሮ በአክብሮት ቢይዘው የእውነተኛው አምላክ ተቃዋሚ የነበረውን የአምልኮ ምስል ማክበር ይሆንበታል።

በ⁠ሕዝቅኤል 8:17 እንደተገለጸው ከሃዲዎቹ አይሁዳውያን ‘ቅርንጫፉን ወደ ይሖዋ አፍንጫ አቅርበዋል።’ ይሖዋ ይህንን ‘አስጸያፊና’ እርሱን ‘ለማስቆጣት’ የተደረገ ድርጊት አድርጎ ተመልክቶታል። ለምን? አንዳንድ ተመራማሪዎች ይህ ‘ቅርንጫፍ’ የወንድ የፆታ ብልትን የሚያመለክትና ለፆታ አምልኮ ያገለግል እንደነበረ ያስረዳሉ። ከላይ እንዳየነው መስቀል ለፆታ አምልኮ ምስል ሆኖ ያገለግል ነበረ። ታዲያ ይሖዋ በመስቀል መጠቀምን እንዴት ይመለከተዋል?