በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መናዘዝ/ማሳወቅ

መናዘዝ/ማሳወቅ

ፍቺ:- አንድ ሰው (1) እምነቱን ወይም (2) የሠራውን ኃጢአት በሕዝብ ፊት ወይም በምሥጢር መናገሩ ወይም ማሳወቁ በእንግሊዝኛ “ኮንፌሽን” ይባላል። ይህም መናዘዝ ወይም ማሳወቅ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው (ለአንድ ቄስ በምሥጢር የሚነገር) ምሥጢራዊ ኑዛዜን የሚጨምረው የማስታረቅ ሥርዓት ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ አለውን?

ኑዛዜው ለቄሱ የሚነገርበት ሥርዓት

የተለመደውና እስከ ዛሬ ድረስ የሚሠራበት ሥርዓት:- “አባቴ ይፍቱኝ፣ ኃጢአት ሠርቻለሁ። ኃጢአቴን ከተናዘዝሁ [ይህን ያህል ጊዜ] ሆኖኛል” የሚል ነው።—ዩ ኤስ ካቶሊክ መጽሔት፣ ጥቅምት 1982፣ ገጽ 6

ማቴ. 23:1, 9:- “ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነገራቸው:- . . . አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም:- አባት ብላችሁ አትጥሩ።”

ይቅር ሊባሉ የሚችሉ ኃጢአቶች

“ማንኛውም ኃጢአት ምንም ያህል ከባድ ቢሆን ይቅር ሊባል እንደሚችል ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ ስታስተምር ቆይታለች።”—ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ (የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የማትቀበለውን እምነትና ጽሑፎችን ለማሳተም የምትሰጠውን ፈቃድ የያዘ)፣ አር ሲ ብሮደሪክ (ናሽቪል፣ ቴነሲ፣ 1976)፣ ገጽ 554

ዕብ. 10:26:- “የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና።”

ማር. 3:29:- “በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘላለም ኃጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም።”

ንስሐ መግባት የሚገለጸው እንዴት ነው?

ብዙውን ጊዜ የንስሐ አባቱ ኃጢአቱን የሚናዘዘው ሰው ንሥሐ መግባቱን ለማሳየት ይህን ያህል ጊዜ “አባታችን ሆይ” ወይም “እመቤቴ ሆይ” ብለህ ድገም ይለዋል።

ማቴ. 6:7:- “አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ። [ማለትም ትርጉም በማይሰጥ መንገድ አትደጋግሙ።]”

ማቴ. 6:9–12:- “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ:- በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ . . . በደላችንን ይቀር በለን።” (በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በየትም ቦታ ላይ ለማርያም ወይም በማርያም በኩል እንድንጸልይ አልታዘዝንም። ፊልጵስዩስ 4:6⁠ን እንዲሁም ገጽ 258 ላይ “ማርያም” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።)

ሮሜ 12:9:- “ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ።”

ሐዋርያቱ ኃጢአትን ይቅር እንዲሉ ኢየሱስ ሥልጣን ሰጥቷቸው የለም እንዴ?

ዮሐ. 20:21–23:- “አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና:- መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።”

ሐዋርያት ይህንን የተረዱትና በሥራ ላይ ያዋሉት እንዴት ነበር? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ሐዋርያ የግል ኑዛዜ እንዳዳመጠና ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል ብሎ እንደተናገረ የሚገልጽ አንድም ማስረጃ የለም። ይሁን እንጂ ከአምላክ ይቅርታ የሚያስገኙ ብቃቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጸዋል። ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ ግለሰቦች እነዚህን ብቃቶች አሟልተው እንደሆነ ማየትና በዚህ መሠረት አምላክ ይቅር ብሏቸው ወይም አላላቸው እንደሆነ መናገር ይችሉ ነበር። ለምሳሌ ሥራ 5:1–11⁠ን እንዲሁም 1 ቆሮንቶስ 5:1–5⁠ን እና 2 ቆሮንቶስ 2:6–8⁠ን ተመልከት።

በተጨማሪ “ሐዋርያዊ ተተኪዎች” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።

ምሁራን በምሥጢር ለቄስ መናዘዝ እንዴት ተጀመረ በሚለው ጥያቄ ላይ የተለያየ አመለካከት አላቸው

በአር ሲ ብሮደሪክ የተዘጋጀው ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ይላል:- “ከአራተኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ኃጢአትን በምሥጢር ለቄስ መናዘዝ የተለመደ ሥርዓት ሆኖ ቆይቷል።”—ገጽ 58

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ይላል:- “ብዙዎች የካቶሊክና የፕሮቴስታንት ዘመናዊ የታሪክ ምሁራን በምሥጢር መናዘዝ የተለመደ ሥርዓት ሆኖ የተጀመረው ብዙ ጊዜ የንሥሐ ሥርዓትን የሚጨምሩ የቁርባን ሥርዓቶች በገዳማት አበምነቶችና በመነኮሳት ይከናወኑ በነበሩበት በአየርላንድ፣ በዌልስና በብሪታንያ አብያተ ክርስቲያናት እንደሆነ ያመለክታሉ። ምዕመናንም በገዳማት ውስጥ የሚፈጸመውን የኑዛዜና የመንፈሳዊ አመራር ሥርዓት እንደ ምሳሌ በመውሰድ ተደጋጋሚ የኃጢአት ኑዛዜና የአምልኮ ሥርዓት መከተል ጀመሩ። . . . ይሁን እንጂ በምሥጢር የተሠሩ ኃጢአቶችን በኑዛዜው ጊዜና ለንሥሐ የሚያበቃው ቅጣት ከመፈጸሙ በፊት ማስተሰረይ የተጀመረው ከ11ኛው መቶ ዘመን በኋላ ነው።”—(1967) ጥራዝ 11፣ ገጽ 75

የታሪክ ምሁር የሆኑት ኤ ኤች ሴይስ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ባቢሎናውያን ኃጢአታቸውን በግልጽና በምሥጢር የመናዘዝ ልማድ እንደነበራቸው ስለ አምልኮ ሥርአቶች የሚገልጹ ጽሑፎች ያመለክታሉ። በእርግጥም የምሥጢር ኑዛዜ የተለመደና ብዙ ዘመን የቆየ የጥንት ልማድ ነው።”—ዘ ሪሊጅንስ ኦቭ ኤንሸንት ኢጅፕት ኤንድ ባቢሎንያ (የጥንት ግብጽና ባቢሎን ሃይማኖቶች) (ኤድንበርግ፣ 1902)፣ ገጽ 497

መናዘዝን ወይም ማሳወቅን በተመለከተ የይሖዋ ምሥክሮች እምነት ምንድን ነው?

እምነትን በሰዎች ፊት ማሳወቅ

ሮሜ 10:9, 10:- “ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና።”

ማቴ. 10:32, 33:- “በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ [ለኢየሱስ ክርስቶስ] ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፣ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።”

አንድ ሰው በአምላክ ላይ ኃጢአት በሚሠራበት ጊዜ

ማቴ. 6:6–12:- “አንተ ግን ስትጸልይ፣ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ . . . በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ . . . እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን።”

መዝ. 32:5:- “ኃጢአቴን ለአንተ [ለአምላክ] አስታወቅሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር [“ለይሖዋ ” “አዓት ” ] መተላለፌን አልሁ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ።”— ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

1 ዮሐ. 2:1:- “ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።”

አንድ ሰው ባልንጀራውን በሚበድልበት ወይም በራሱ ላይ በደል በሚፈጸምበት ጊዜ

ማቴ. 5:23, 24:- “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፣ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፣ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፣ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፣ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።”

ማቴ. 18:15:- “ወንድምህ ቢበድልህ፣ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው።”

ሉቃስ 17:3:- “ወንድምህ ቢበድልህ፣ ገሥጸው ቢጸጸትም ይቅር በለው።”

ኤፌ. 4:32:- “እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ እግዚአብሔር ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።”

አንድ ሰው ከባድ ስሕተት ፈጽሞ መንፈሳዊ እርዳታ በሚፈልግበት ጊዜ

ያዕ. 5:14–16:- “ከእናንተ [በመንፈሳዊ] የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን [የጉባኤን] ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነት ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ [በአምላክ] ይሰረይለታል። እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ፣ ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ።”

ምሳሌ 28:13:- “ኃጢአቱን የሚሠውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል።”

ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎች እርዳታ የማይፈልጉ ቢሆንስ?

ገላ. 6:1 አዓት :- “ወንድሞች ሆይ፣ አንድ ሰው በመዘንጋት የተሳሳተ እርምጃ ቢወስድ መንፈሳዊ ብቃት ያላችሁ እናንተ እንደነዚህ ያለውን ሰው በየዋህነት መንፈስ ለማስተካከል ሞክሩ፤ እናንተም ደግሞ መጥፎ ለመሥራት እንዳትፈተኑ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ።”

1 ጢሞ. 5:20:- “ሌሎቹ ደግሞ እንዲፈሩ፣ ኃጢአት የሚሠሩትን በሁሉ ፊት [ይኸውም ጉዳዩን በግል በሚያውቁት ፊት] ገሥጻቸው።”

1 ቆሮ. 5:11–13:- “ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብን የሚመኝ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካር ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ እጽፍላችኋለሁ፤ እንደነዚህ ካለው ጋር መብል እንኳ አትብሉ። . . . ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት።”