በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መናፍስትነት

መናፍስትነት

ፍቺ:- ሰው ሥጋው በሚሞትበት ጊዜ ከአካል ተለይቶ በሕይወት የሚኖር መንፈሳዊ አካል እንዳለና ይህም መንፈሳዊ አካል አብዛኛውን ጊዜ አገናኝ ሆኖ በሚያገለግል ሰው አማካይነት በሕይወት ከሚኖሩት ጋር ሊነጋገር ይችላል የሚል እምነት ነው። አንዳንድ ሰዎች እያንዳንዱ ቁስ አካልና እያንዳንዱ የተፈጥሮ ክስተት ውስጣዊ የሆነ መንፈስ እንዳለው ያምናሉ። ከክፉ መናፍስት ይገኛል ተብሎ በሚታመን ኃይል መጠቀም አስማት ይባላል። መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውንም ዓይነት መናፍስትነት በጥብቅ ያወግዛል።

አንድ ሰው በሞት ከተለየው ወዳጁ “መንፈስ” ጋር ሊነጋገር ይችላልን?

መክ. 9:5, 6, 10 የ1980 ትርጉም:- “በሕይወት ያሉ ሰዎች አንድ ቀን እንደሚሞቱ ያውቃሉ፤ ሙታን ግን አንዳች ነገር አያውቁም። . . . ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸውና ቅንዓታቸው ሁሉ ከእነርሱ ጋር አብሮ ሞቶአል፤ በዚህ ዓለም በሚሆነው ነገር ሁሉ እንደገና እስከ ዘላለም ተካፋይነት አይኖራቸውም። ባለህ ኃይል ሥራህን ሁሉ በትጋት ፈጽም፤ ምክንያቱም ወደ ሙታን ዓለም [ወደ መቃብር] ከወረድህ በኋላ በዚያ ሥራና አሳብ፣ እውቀትና ጥበብ የለም።”

ሕዝ. 18:4, 20:- “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።” (ስለዚህ ነፍስ በሞት ጊዜ ከሥጋ ተለይታ የምትኖርና በሕይወት ያሉ ሰዎች ሊያነጋግሯት የሚችሉ ነገር አይደለችም።)

መዝ. 146:4 አዓት:- “መንፈሱ ይወጣል፣ ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ በዚያ ቀን ሐሳቡ ሁሉ ይጠፋል።” (መንፈስ ከሥጋ ‘ወጣ’ ሲባል የሕይወት ኃይል መሥራት አቆመ ማለት ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ መንፈሱ ከሥጋው ተለይቶ ብቻውን ሊያስብና ዕቅዶቹን ሊፈጽም የሚችል ረቂቅ አካል ሆኖ አይኖርም። አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ከሕያዋን ጋር ሊነጋገር የሚችል ነገር ሆኖ አይኖርም ማለት ነው።)

በተጨማሪም በገጽ 99–101 ላይ “ሞት” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ ሳሙኤል ከሞተ በኋላ ንጉሥ ሳኦል ከነቢዩ ሳሙኤል ጋር እንደተነጋገረ ያመለክት የለምን?

ይህ ታሪክ በ⁠1 ሳሙኤል 28:3–20 ላይ ይገኛል። ቁጥር 13, 14 ንጉሥ ሳኦል ሳሙኤልን እንዳልተመለከተና መናፍስት ጠሪዋ ሴት በሰጠችው መግለጫ መሠረት ሳሙኤል ነው ብሎ እንደገመተ ያመለክታል። ሳኦል ሳሙኤል ነው ብሎ የግድ ለማመን ስለፈለገ ተታለለ። ሳሙኤል እንደሞተና እንደተቀበረ ቁጥር 3 ይናገራል። ቀደም ባለውም ንዑስ ርዕስ ሥር በተጠቀሰው ጥቅስ መሠረት ከሳሙኤል ተለይቶ በሌላ ዓለም የሚኖርና ከሳኦል ጋር ሊነጋገር የሚችል ነገር ሊኖር አይችልም። የሳሙኤልን ድምፅ መስሎ የተሰማው የአንድ አታላይ ድምፅ ነበረ።

ከሙታን ጋር ለመነጋገር የሚሞክሩ ሰዎች በእርግጥ የሚነጋገሩት ከማን ጋር ነው?

ሙታን የሚገኙበት ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ተነግሯል። ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ስለ ሞት የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዲያድርባቸው ለማድረግ የሞከረው ማን ነበር? አለመታዘዝ ሞት እንደሚያመጣ አምላክ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰይጣን አስተባብሎ ነበር። (ዘፍ. 3:4፤ ራእይ 12:9) እርግጥ ከጊዜ በኋላ ሰዎች ልክ አምላክ እንደተናገረው እንደሚሞቱ ግልጽ ሆነ። ስለዚህ ሰዎች በእርግጥ እንደማይሞቱና ሥጋ ከሞተ በኋላ ተለይቶ የሚኖር መንፈስ እንዳለ የሚገልጸውን ሐሳብ የፈለሰፈው ማን መሆን ይኖርበታል? እንዲህ ያለውን የማታለያ ሐሳብ ሊፈለስፍ የሚችለው ኢየሱስ “የሐሰት አባት” ሲል የጠራው ሰይጣን ዲያብሎስ መሆን ይኖርበታል። (ዮሐ. 8:44፤ በተጨማሪም 2 ተሰሎንቄ 2:9, 10⁠ን ተመልከት።) ሙታን በሌላ ዓለም በሕይወት ይኖራሉ፣ ከነርሱም ጋር ልንነጋገር እንችላለን የሚለው እምነት ለሰው ልጆች ያስገኘው ጥቅም የለም። ይልቁንም ራእይ 18:23 ታላቂቱ ባቢሎን በምትፈጽማቸው መናፍስታዊ ሥራዎች ‘አሕዛብ ሁሉ እንደ ተሳሳቱ’ ይናገራል። መናፍስታዊ የሆነው ከሙታን ጋር የመነጋገር ተግባር ሰዎችን ከአጋንንት (በራስ ወዳድነት በአምላክ ላይ ያመፁ መላእክት) ጋር ሊያገናኝ የሚችል የማሳሳቻ ተግባርና አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሰው ያልተፈለጉ ድምፆችን እንዲሰማና በክፉ መናፍስት እንዲጠቃ የሚያደርግ ተግባር ነው።

በመናፍስታዊ ተግባሮች አማካኝነት ፈውስ ወይም ጥበቃ ለማግኘት መሞከር ጉዳት ያስከትላልን?

ገላ. 5:19–21:- “የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው፣ እርሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት [“መናፍስትነት” አዓት ] . . . አስቀድሜም እንዳልሁ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” (አንድ ሰው ከመናፍስታዊ ተግባራት እርዳታ ለማግኘት ቢሞክር ሰይጣን ስለ ሞት የተናገረውን ውሸት አመነ ማለት ነው። ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ኃይል ለማግኘት የሚሞክሩ ሰዎችን ምክር ይፈልጋል ማለት ነው። ስለዚህ እንዲህ ያለው ሰው የይሖዋ አምላክ ጠላቶች ለመሆን ከቆረጡ አካላት ጋር ይሰለፋል። እንዲህ ባለው ተግባር የሚጸና ሰው እውነተኛ እርዳታ ከማግኘት ይልቅ ዘላቂ ጉዳት ይደርስበታል።)

ሉቃስ 9:24:- “ነፍሱን [ወይም ሕይወቱን] ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ [የክርስቶስ ተከታይ በመሆን] ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል።” (የአሁኑን ሕይወቱን ለማትረፍ ወይም ለማቆየት ብሎ የአምላክ ቃል በግልጽ የሚናገረውን ትእዛዝ ሆን ብሎ ቢጥስ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ያጣል። ይህ እንዴት ያለ ትልቅ ሞኝነት ነው!)

2 ቆሮ. 11:14, 15:- “ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች አንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም።” (ስለዚህ በመናፍስታዊ ሥራዎች አማካኝነት የሚፈጸሙ አንዳንድ ነገሮች ጊዜያዊ ጥቅም የሚያስገኙ መስለው ቢታዩ መሳሳት አይገባንም።)

በተጨማሪም በገጽ 157–161 ላይ “ተአምራዊ ፈውስ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ወይም አንድን ዓይነት ዕቅድ ለማሳካት መናፍስትን መጠየቅ ጥሩ ነውን?

ኢሳ. 8:19 የ1980 ትርጉም:- “በሹክሹክታ የሚንተባተቡትን ሟርተኞችንና የሙታን መናፍስት ጠሪዎችን ጠይቁ እያሉ የሚሰብኩአችሁ ወገኖች አሉ፤ ታዲያ ስለ ሕያዋን ሙታንን ከመጠየቅ ይልቅ፣ ሕዝቡ አምላኩን መጠየቅ አይገባውምን?”

ዘሌ. 19:31:- “ወደ መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች አትሂዱ፤ እንዳትረክሱባቸውም አትፈልጓቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።”

2 ነገ. 21:6:- “[ንጉሥ ምናሴ] ሞራ ገላጭም ሆነ፣ አስማትም አደረገ፣ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም ሰበሰበ፤ ያስቆጣውም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።” (እንደነዚህ ያሉት መናፍስታዊ ልማዶች የሰይጣንንና የአጋንንትን እርዳታ ወደ መፈለግ ያመራሉ። እንደነዚህ ያሉት ተግባራት ‘በይሖዋ ዓይን የተጠሉ’ መሆናቸው አያስደንቅም። ምናሴም ይህን በመፈጸሙ ከባድ ቅጣት ደርሶበታል። ይሁን እንጂ ንስሐ በገባና እነዚህን መጥፎ ተግባራት ባቆመ ጊዜ ይሖዋ ባርኮታል።)

የምዋርት መልክ ያላቸውን ጨዋታዎች መጫወት ወይም የጥሩ ነገር ምልክት የሚመስሉ ነገሮችን ትርጉም ለማወቅ መፈለግ ምን ጉዳት ሊያስከትል ይችላል?

ዘዳ. 18:10–12:- “ምዋርተኛም፣ ሞራ ገላጭም፣ አስማተኛም፣ መተተኛም፣ በድግምት የሚጠነቁልም፣ መናፍስትንም የሚጠራ ጠንቋይም፣ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው።” (ምዋርት ስውር የሆነ እውቀት ወይም ወደ ፊት የሚፈጸምን ሁኔታ በምርምርና በጥናት ሳይሆን የጥንቆላ ምልክቶችን በመተረጎም ወይም ከሰው በላይ በሆኑ ኃይሎች እርዳታ ለማወቅ የሚደረግ ጥረት ነው። ይሖዋ እንደነዚህ ያሉትን ተግባራት አገልጋዮቹ እንዳያደርጉ ከልክሏል። ለምን? ምክንያቱም እነዚህን ተግባራት መፈጸም ርኩሳን መናፍስት ወይም አጋንንት እንዲያነጋግሩን ወይም ሕይወታችንን እንዲቆጣጠሩ መጋበዝ ነው። እንደነዚህ ያሉትን ተግባራት መፈጸም በይሖዋ ላይ የሚፈጸም ከፍተኛ ክህደት ነው።)

ሥራ 16:16–18:- “የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን።” (ጽድቅን የሚወድ ማንም ሰው እንዲህ ካለው ምንጭ በቁም ነገርም ሆነ ለጨዋታ ብሎ መረጃ ለማግኘት እንደማይፈልግ ግልጽ ነው። ጳውሎስ ጩኸቷ አሰልችቶት ነበረ። በዚህም ምክንያት መንፈሱ ከእርሷ እንዲወጣ አዘዘው።)

ክፉ መናፍስት የሰው መልክ ለብሰው ሊታዩ ይችላሉን?

በኖኅ ዘመን ዓመፀኛ የሆኑ መላእክት የሰው መልክ ለብሰው ነበር። እንዲያውም ሚስቶችን አግብተው ልጆች ወልደዋል። (ዘፍ. 6:1–4) ይሁን እንጂ የጥፋት ውኃ በመጣ ጊዜ እነዚህ መላእክት ወደ መንፈሳዊው ዓለም ለመመለስ ተገደዋል። ይሁዳ 6 ስለነዚህ መላእክት እንዲህ ይላል:- “መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል።” አምላክ ከቀድሞው የሰማይ መብታቸው ከማውረድ በተጨማሪ ስለ ይሖዋ ዓላማ በሚኖራቸው እውቀት ረገድ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል። ከዚህም በላይ እስራት የሚል ቃል መጠቀሱ አንድ ዓይነት ገደብ እንዳደረገባቸው ያመለክታል። ገደብ የተደረገባቸው በምን ነገር ላይ ነው? ከጥፋት ውኃ በፊት ያደርጉ እንደነበረው ከሴቶች ጋር ሩካቤ ሥጋ ለመፈጸም ሥጋዊ አካል ከመልበስ እንደታገዱ ግልጽ ነው። ታማኝ መላእክት የአምላክ መልእክተኞች ሆነው በሚላኩበት ጊዜ ግዳጃቸውን ለመፈጸም እስከ መጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ድረስ ሥጋ ለብሰው ይታዩ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። እነዚህ ስጦታቸውን አግባብ ባልሆነ መንገድ የተጠቀሙ መላእክት ግን ከጥፋቱ ውኃ ጀምሮ ሰብዓዊ መልክ የመልበስ ችሎታ ተነፍጓቸዋል።

ይሁን እንጂ አጋንንት የሰው ልጆች ራእይ እንዲመለከቱ ለማድረግ ይችላሉ። ሰዎቹ የሚያዩት ነገር እውነተኛ መስሎ ሊታያቸው ይችላል። ዲያብሎስ ኢየሱስን በፈተነው ጊዜ “የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም” ለኢየሱስ ለማሳየት በዚህ ዘዴ እንደተጠቀመ ግልጽ ነው።—ማቴ. 4:8

አንድ ሰው ከመናፍስታዊ ተጽዕኖ ሊላቀቅ የሚችለው እንዴት ነው?

ምሳሌ 18:10:- “የእግዚአብሔር [“የይሖዋ” አዓት] ስም የጸና ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል [“ጥበቃ ያገኛል።” አዓት]” (ይህ ማለት የአምላክን የተፀውዖ ስም መጥራት ከክፉ ነገር የሚጠብቅ ድግምት ሆኖ ያገለግላል ማለት አይደለም። የይሖዋ “ስም” የይሖዋን ሁለንተናዊ ማንነት ያመለክታል። ይሖዋን ስናውቅና በእርሱ ላይ ሙሉ በሙሉ ስንተማመን፣ ለሥልጣኑ ስንገዛና ትእዛዛቱን ስናከብር፣ ከክፉ ነገር እንጠበቃለን። እንዲህ ካደረግን የተፀውዖ ስሙን በመጥራት እርዳታ እንዲያደርግልን በምንጠይቅበት ጊዜ በቃሉ ውስጥ ቃል የገባልንን ጥበቃ ይሰጠናል።)

ማቴ. 6:9–13:- “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ:- . . . ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።” በተጨማሪም ‘በጸሎት መጽናት’ ያስፈልጋል። (ሮሜ 12:12) (አምላክ እውነትን ለማወቅ ልባዊ ፍላጎት ያላቸውና እርሱን በሚያስደስተው መንገድ ሊያመልኩት የሚፈልጉ ሰዎች የሚያቀርቡለትን ጸሎት ይሰማል።)

1 ቆሮ. 10:21:- “ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም።” (የይሖዋን ወዳጅነት ለማግኘት የሚፈልጉና የእርሱን ጥበቃ የሚሹ ሁሉ የመናፍስትነት ድርጊት በሚፈጸምባቸው ስብሰባዎች ላይ ከመካፈል መራቅ ይኖርባቸዋል። በ⁠ሥራ 19:19 ላይ ከተመዘገበው ምሳሌ ጋር በመስማማት ከመናፍስትነት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ማጥፋት ወይም በተገቢው ሁኔታ ማስወገድ አስፈላጊ ነው።)

ያዕ. 4:7:- “ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል።” (ይህን ለማድረግ የአምላክን ፈቃድ ለመማርና በሕይወትህ ውስጥ በሥራ ለማዋል መትጋት ይኖርብሃል። ለአምላክ ያለህ ፍቅር ሰዎችን እንዳትፈራ ስለሚያጠነክርህ ከመናፍስታዊ እምነት ጋር ዝምድና ባላቸው በማናቸውም ዓይነት ልማዶች ከመካፈል ወይም መናፍስት ሳቢ የሆነ ሰው የሚያወጣውን ማንኛውንም ሕግ ከመታዘዝ ራቅ።)

በ⁠ኤፌሶን 6:10–18 ላይ የተጠቀሰውን ‘የአምላክን ሙሉ የጦር ዕቃ’ ልበስ። እያንዳንዱንም የጦር ዕቃ በጥሩ ሁኔታ ለመጠበቅ በቅንዓት ትጋ።