በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንጽሔ

መንጽሔ

ፍቺ:- “መንጽሔ [የሮማ ካቶሊክ] ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረው በጸጋ የሞቱ ግን ገና ካለፍጽምናቸው ሙሉ በሙሉ ያልነጹ ነፍሳት ይቅርታ ላላገኙባቸው ቀላል ኃጢአቶች ንስሐ የሚገቡበት ወይም ለሠሯቸው ቀላል ግን ሞት የሚገባቸው ኃጢአቶች ጊዜአዊ ቅጣት የሚቀበሉበትና ወደ ሰማይ ከመግባታቸው በፊት የሚነጹበት በወዲያኛው ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሁኔታ ወይም ቦታ ነው።” (ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ፣ 1967፣ ጥራዝ 11፣ ገጽ 1034) የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም።

የመንጽሔ ትምህርት የተመሠረተው በምን ላይ ነው?

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ (1967፣ ጥራዝ 11፣ ገጽ 1034) ካቶሊካውያን ጸሐፊዎች እንደ 2 መቃብያን 12:39–45፣ ማቴዎስ 12:32​ና 1 ቆሮንቶስ 3:10–15 ስላሉት ጥቅሶች የጻፏቸውን ከመረመረ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “ይህንን ሁሉ ከመረመርን በኋላ የምንገነዘበው የካቶሊክ የመንጽሔ መሠረተ ትምህርት በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ሳይሆን በወግ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ነው።”

“ቤተ ክርስቲያን በሰማይና በሲኦል መካከል መሸጋገሪያ ቦታ አለ ብላ ስታስተምር ድጋፍ ያደረገችው ወግን ነው።”—ዩ ኤስ ካቶሊክ፣ መጋቢት 1981፣ ገጽ 7

የካቶሊክ ቃል አቀባዮች ስለ መንጽሔ ምን ብለዋል?

“ብዙዎች ጠቅላላው የመንጽሔ ሥቃይ የብጽአት ራእይ ለጊዜው የተላለፈ መሆኑን ከመንገዘብ የሚመጣ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። በጣም የተለመደው አስተሳሰብ ግን ከዚህ ተጨማሪ የሆነ ሥቃይ እንደሚደርስ ነው። . . . ይህ ሥቃይ ቃል በቃል በእሳት ከመቃጠል የሚመጣ እንደሆነ የላቲን ቤተ ክርስቲያን ታምናለች። ይሁን እንጂ ይህ በመንጽሔ ለማመን ዋና ነገር አይደለም። እንዲያውም የተረጋገጠ ነገር እንኳን አይደለም። . . . አንድ ሰው ከምሥራቃውያን ሃይማኖተኞች ጋር ተስማምቶ በእሳት የመቃጠል ሥቃይ መኖሩን ላለመቀበል ቢመርጥ እንኳ በመንጽሔ ውስጥ እውነተኛ የሆነ ሥቃይ የለም ብሎ እንዳያምን መጠንቀቅ ይኖርበታል። በመንጽሔ ውስጥ እውነተኛ ስቃይ ሊያስከትሉ የሚችሉ እንደ ትካዜ፣ ኀዘን፣ ጸጸት፣ ብስጭት፣ የሕሊና ኃፍረት እና ሌሎች መንፈሳዊ ሥቃዮች ሊኖሩ ይችላሉ። . . . ያም ሆነ ይህ እነዚህ ነፍሳት ይህን ሁሉ መከራ በሚቀበሉበት ጊዜ መዳናቸው የተረጋገጠ መሆኑን እያስታወሱ ትልቅ ደስታ እንደሚሰማቸው መታወስ ይኖርበታል።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ (1967)፣ ጥራዝ 11፣ ገጽ 1036, 1037

“በመንጽሔ ውስጥ ስለሚሆነው ነገር ከግምት በስተቀር የተረጋገጠ ነገር የለም።”— ዩ ኤስ ካቶሊክ፣ መጋቢት 1981፣ ገጽ 9

ሥጋ ከሞተ በኋላ ነፍስ ተለይታ በሕይወት ትኖራለችን?

ሕዝ. 18:4:- “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ [በዕብራይስጥ ነፈሽ፤ “ሰው” ጀባ፤ “ነፍስ” ኖክስ ] እርስዋ ትሞታለች።”

ያዕ. 5:20:- “ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፣ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ይህ ጥቅስ ነፍስ ሟች መሆኗን እንደሚናገር ልብ በል።)

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት “ሞት” እና “ነፍስ” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።

አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ድሮ ለሠራቸው ኃጢአቶች ተጨማሪ ቅጣት ይቀበላልን?

ሮሜ 6:7:- “የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቆአልና።” (ኒአባ:- “የሞተ ሰው ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷል”፤ ኖክስ:- “በሞተ ሰው ላይ በደል አይታሰብበትም።”)

ሙታን መዳን እንደሚያገኙ እርግጠኛ በመሆን ሊደሰቱ ይችላሉን?

መክ. 9:5:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም።”

ኢሳ. 38:18:- “ሲኦል አያመሰግንህምና፣ ሞትም አያከብርህምና፤ ወደ ጉድጓድ የሚወርዱ እውነትህን ተስፋ አያደርጉም።” (ታዲያ እንዲህ ከሆነ ‘መዳናቸው የተረጋገጠ መሆኑን እያስታወሱ ታላቅ ደስታ ሊሰማቸው የሚችለው’ እንዴት ነው?)

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ከኃጢአት መንጻት የሚቻለው እንዴት ነው?

1 ዮሐ. 1:7, 9:- “ነገር ግን እርሱ [አምላክ] በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፣ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። . . . በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።”

ራእይ 1:5:- “ኢየሱስ ክርስቶስ . . . [ወደደን፣] ከኃጢአታችንም በደሙ [አጠበን።]”