በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈስ

መንፈስ

ፍቺ:- አብዛኛውን ጊዜ “መንፈስ” ተብለው የሚተረጎሙት ሩዋሕ የተባለው የዕብራይስጥ ቃልና ፕነቭማ የተባለው የግሪክኛ ቃል ብዙ ትርጉሞች አሏቸው። ሁሉም የሚያመለክቱት ለሰው ዓይን የማይታይንና በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኝን አንድ ኃይል ነው። የዕብራይስጡና የግሪክኛው ቃላት የሚከተሉትን ነገሮች ለማመልከት ያገለግላሉ:- (1) ነፋስን፣ (2) በምድራዊ ፍጥረታት ውስጥ የሚሠራውን አንቀሳቃሽ የሕይወት ኃይል፣ (3) ከአንድ ሰው ምሳሌያዊ ልብ የሚወጣውንና አንዳንድ ነገሮችን በሆነ መንገድ እንዲሠራ ወይም እንዲናገር የሚያደርገውን አስገዳጅ ኃይል፣ (4) ከማይታይ ቦታ የሚመጡ መግለጫዎችን (5) ሕያው የሆኑ መንፈሳዊ አካላትን (6) አንቀሳቃሽ የሆነውን የአምላክ ኃይል ወይም መንፈስ ቅዱስ ነው። እነዚህ የተለያዩ አጠቃቀሞች በመስክ አገልግሎት ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ርዕሶች ጋር በመዛመድ ተብራርተዋል።

መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?

ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ስናገናዝብ መንፈስ ቅዱስ ሰዎች ‘የሚጠመቁበትና’ ‘የሚቀቡበት’ ሰዎችንም ‘የሚሞላ’ ነገር መሆኑን እንገነዘባለን። (ሉቃስ 1:41፤ ማቴ. 3:11፤ ሥራ 10:38) መንፈስ ቅዱስ የተወሰነ ሕያው አካል ቢሆን ኖሮ እንደነዚህ ያሉ መግለጫዎች ተስማሚ አይሆኑም ነበር።

በተጨማሪም ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ “ረዳት” [በግሪክኛ ጰራቅሊጦስ] እንደሆነና ይህም ረዳት ‘እንደሚያስተምር’፣ ‘እንደሚመሰክር’፣ ‘እንደሚናገርና’ ‘እንደሚሰማ’ ተናግሯል። (ዮሐ. 14:16, 17, 26፤ 15:26፤ 16:13) በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አንድ ነገር ስብዕና እንዳለው ሆኖ መገለጹ እንግዳ ነገር አይደለም። ለምሳሌ ያህል ጥበብ “ልጆች” እንዳሏት ተደርጎ ተነግሯል። (ሉቃስ 7:35) ኃጢአትና ሞት ነገሥታት እንደሆኑ ተነግሯል። (ሮሜ 5:14, 21) አንዳንድ ጥቅሶች መንፈስ ‘እንደ ተናገረ’ ቢገልጹም በሌሎች ቦታዎች ላይ ቃሉ የተነገረው በመላእክት ወይም በሰዎች በኩል መሆኑ ተገልጿል። (ሥራ 4:24, 25፤ 28:25፤ ማቴ. 10:19, 20፤ ከ⁠ሥራ 20:23⁠ንና 21:10, 11 ጋር አወዳድር።) በ⁠1 ዮሐንስ 5:6–8 ላይ መንፈስ ብቻ ሳይሆን “ውኃውና ደሙ” ‘እንደሚመሰክሩ’ ተገልጿል። ስለዚህ ከእነዚህ አነጋገሮች አንዱም ቢሆን መንፈስ ቅዱስ የተወሰነ ሕያው አካል መሆኑን አያረጋግጥም።

ስለ መንፈስ ቅዱስ ምንነት የሚሰጠው ማንኛውም መግለጫ ስለ መንፈስ ቅዱስ ከሚናገሩት ጥቅሶች ሁሉ ጋር መስማማት ይኖርበታል። በዚህ አመለካከት መንፈስ ቅዱስ የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል ነው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው። የተወሰነ ሕያው አካል ሳይሆን አምላክ ቅዱስ ፈቃዱን ለመፈጸም ከራሱ እንዲወጣ የሚያደረገው ብርቱ ኃይል ነው።—መዝ. 104:30፤ 2 ጴጥ. 1:21፤ ሥራ 4:31

በተጨማሪም በገጽ 405, 406 ላይ “ሥላሴ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስ ያለው መሆኑ የሚረጋገጠው በምንድን ነው?

ሉቃስ 4:18, 31–35:- “[ኢየሱስ ከነቢዩ ኢሳይያስ ጥቅል እንዲህ የሚለውን አነበበ:-] የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፣ ለድሆች ወንጌልን እስብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ . . . ወደ ገሊላ ከተማም ወደ ቅፍርናሆም ወረደ። በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር፤ ቃሉ በሥልጣን ነበርና በትምህርቱ ተገረሙ። በምኩራብ የርኩስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፣ በታላቅ ድምፅም [ጮኸ።] . . . ኢየሱስም:- ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም በመካከላቸው ጥሎት ሳይጎዳው ከእርሱ ወጣ።” (ኢየሱስ የአምላክ መንፈስ የነበረው መሆኑን ያረጋገጠው ምን ነበር? ታሪኩ ኢየሱስ ይንቀጠቀጥ ወይም ይጮህ እንደነበረ ወይም በጋለ ስሜት ይወራጭ እንደነበረ አይናገርም። ከዚህ ይልቅ በሥልጣን እንደተናገረ ይገልጻል። ይሁን እንጂ በዚሁ ጊዜ አጋንንታዊ መንፈስ አንድን ሰው እንዲጮህና መሬት ላይ እንዲዘረር እንዳደረገው ማስተዋል ተገቢ ነው።)

ሥራ 1:8 የኢየሱስ ተከታዮች መንፈስ ቅዱስን በተቀበሉ ጊዜ ስለ እርሱ እንደሚመሰክሩ ይናገራል። በሥራ 2:1–11 መሠረት ይህንኑ መንፈስ በተቀበሉ ጊዜ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ድንቅ ስለሆኑት የአምላክ ሥራዎች በዚያ ቦታ ይገኙ በነበሩት የባዕድ አገር ሰዎች ቋንቋ ሲናገሩ በመስማታቸው ተመልካቾች ሁሉ ተደንቀዋል። ይሁን እንጂ መንፈሱን ከተቀበሉት መካከል አንዳቸውም የስሜት ግንፋሎትና ጩኸት እንደታየባቸው አይናገርም።

ኤልሳቤጥ መንፈስ ቅዱስን በተቀበለችና ‘በታላቅ ድምፅ በጮኸች’ ጊዜ ልትጠይቃት ለመጣችው ዘመዷ ሰላምታ ትሰጥ ነበር እንጂ ለአምልኮ በስብሰባ ላይ አልነበረችም። (ሉቃስ 1:41, 42) በ⁠ሥራ 4:31 ላይ ተሰብስበው በነበሩ ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ የተሰበሰቡበት ስፍራ እንደተናወጠ ተገልጿል። ይሁን እንጂ ይህ መንፈስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲንዘፈዘፉ ወይም በመሬት ላይ እንዲንከባለሉ አላደረጋቸውም። ከዚህ ይልቅ ‘የአምላክን ቃል በድፍረት ተናገሩ።’ ዛሬም በተመሳሳይ አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስ ያለው መሆኑን የሚያረጋግጠው የአምላክን ቃል በሚናገርበት ጊዜ የሚኖረው ድፍረትና በምሥክርነቱ ሥራ በቅንዓት መካፈሉ ነው።

ገላ. 5:22, 23:- “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው።” (አንድ ሰው በእውነት የአምላክ መንፈስ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት በሚፈልግበት ጊዜ መመልከት የሚኖርበት እነዚህ ፍሬዎች ያሏቸው መሆኑን እንጂ በሃይማኖታዊ ግለት መጮሃቸውንና መንዘፍዘፋቸውን መሆን የለበትም።)

አንድ ሰው ከዚህ በፊት በማያውቀው ቋንቋ በታላቅ ስሜትና በግለት ለመናገር መቻሉ መንፈስ ቅዱስ ያለው መሆኑን ያረጋግጣልን?

“በልሳናት መናገር” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።

በዘመናችን በአምላክ መንፈስ አማካኝነት ተአምራዊ ፈውስ እየተፈጸመ ነውን?

“ተአምራዊ ፈውስ” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት

በመንፈስ ቅዱስ የሚጠመቁት እነማን ናቸው?

በገጽ 54 ላይ “ጥምቀት” በሚለው ሥር እና “እንደገና መወለድ” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።

አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ከሥጋው ተለይቶ በሕይወት የሚኖር መንፈስ አለን?

ሕዝ. 18:4:- “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።” (ሪስ፣ ኒኢ፣ ኪጄ እና ዱዌይ በዚህ ቁጥር ላይ የሚገኘውን ነፈሽ የተባለ የዕብራይስጥ ቃል “ነፍስ” ብለው ተርጉመውታል። ይህን በማድረጋቸውም ነፍስ የምትሞት መሆኗን አረጋግጠዋል። በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ ነፈሽ የተባለውን ቃል “ነፍስ” እያሉ የተረጎሙ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች በዚህ ቦታ ላይ “ሰውዬው” በሚል ቃል ተጠቅመዋል። ስለዚህ ነፈሽ ወይም “ነፍስ” ሰውዬው ራሱ ነው እንጂ የሰውዬው ክፍል ሆና ሥጋው ሲሞት ተለይታው በሕይወት የምትኖር ረቂቅ ነገር አይደለችም።) (ለተጨማሪ ማብራሪያ “ነፍስ” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።)

መዝ. 146:4 አዓት:- “መንፈሱ ይወጣል፣ ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ በዚያ ቀን ሐሳቡ ሁሉ ይጠፋል።” (እዚህ ላይ “መንፈስ” ተብሎ የተተረጐመው የዕብራይስጥ ቃል ከሩዋሕ የተገኘ ቃል ነው። አንዳንድ ተርጓሚዎች “እስትንፋስ” ብለው ተርጉመውታል። ይህ ሩዋሕ ወይም አንቀሳቃሽ የሕይወት ኃይል ከአካል ሲወጣ የሰውዬው ሐሳብ በሙሉ ይጠፋል። በሌላ ዓለም በሕይወት ውስጥ አይኖርም።)

መክ. 3:19–21:- “የሰው ልጆችና የእንስሳ እድል ፈንታ አንድ ነው፤ ድርሻቸውም ትክክል ነው፤ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ የሁሉም እስትንፋስ አንድ ነው፤ ሁሉም ከንቱ ነውና ሰው ከእንስሳ ብልጫ የለውም። ሁሉ ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፤ ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል። የሰው ልጆች ነፍስ [“መንፈስ” አዓት] ወደ ላይ እንደምትወጣ የእንስሳት ነፍስ [“መንፈስ” አዓት] ወደ ታች ወደ ምድር እንደምትወርድ የሚያውቅ ማን ነው?” (የሰው ልጆች ኃጢአትና ሞትን ከአዳም ስለወረሱ ሁሉም እንደ እንስሳት ይሞታሉ ወደ አፈርም ይመለሳሉ። ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ሰው በአካሉ ውስጥ የነበረውን ሥራ ካቆመ በኋላ በሕይወት የሚኖር፣ ስሜትና ሐሳብ ያለው መንፈስ ይኖረዋልን? አይኖረውም። ቁጥር 19 ሰዎችም ሆኑ አራዊት ‘አንድ ዓይነት መንፈስ እንዳላቸው’ ይናገራል። የሰው ልጆችን የማሰብ ችሎታ በመመርኮዝ በቁጥር 21 ላይ ስለ መንፈስ የተነሣውን ጥያቄ በእርግጠኝነት ሊመልስ የሚችል ሰው የለም። የአምላክ ቃል ግን የሰው ልጆች በሚሞቱበት ጊዜ ሰው ሆነው በመወለዳቸው ምክንያት ከአራዊት የሚበልጡበት ነገር እንደሌላቸው ይገልጻል። ይሁን እንጂ አምላክ በክርስቶስ በኩል ባዘጋጀው የምሕረት ዝግጅት ምክንያት ለዘላለም የመኖር ተስፋ የተከፈተው እምነት ላላቸው የሰው ልጆች ነው እንጂ ለእንስሳት አይደለም። ብዙዎቹ የሰው ልጆች ይህን ተስፋ የሚያገኙት ከአምላክ የሚመጣው አንቀሳቃሽ የሕይወት ኃይል ሕይወት ዘርቶባቸው ከሙታን በሚነሡበት ጊዜ ነው።)

ሉቃስ 23:46:- “ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ:- አባት ሆይ፣ ነፍሴን [“መንፈሴን” አዓት] [በግሪክኛ ፕነቭማ ] በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ [“ሞተ።” አዓት]” (ኢየሱስ ይህን እንደተናገረ መሞቱን ልብ በል። መንፈሱ ከወጣ በኋላ ወደ ሰማይ መጓዝ አልጀመረም። ኢየሱስ ከሙታን የተነሣው ይህ ከሆነ ከሦስት ቀናት በኋላ ነበር። ከዚያም በኋላ ቢሆን ሥራ 1:3, 9 እንደሚያመለክተው ወደ ሰማይ ያረገው ከ40 ቀን በኋላ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ በሞተበት ጊዜ የተናገረው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? በሚሞትበት ጊዜ ተመልሶ ሕያው የመሆኑ ተስፋ ሙሉ በሙሉ በአምላክ እጅ ያለ መሆኑን እንደሚያውቅ መናገሩ ነበር። ‘ወደ አምላክ ስለሚመለሰው መንፈስ’ ተጨማሪ ማብራሪያ ካስፈለገ በገጽ 376, 377 ላይ “ነፍስ” በሚለው ርዕስ ሥር መመልከት ይቻላል።)

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘መንፈስ ቅዱስ ተቀብለሃል?’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘አዎ፣ ዛሬ ወደ እርስዎ ቤት የመጣሁትም ለዚህ ነው። (ሥራ 2:17, 18)’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘በክርስቲያናዊ አገልግሎት ለመካፈል እንድችል ያደረገኝ መንፈስ ቅዱስ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው የአምላክ መንፈስ በትክክል ያለው መሆኑን ስለሚያረጋግጡት ማስረጃዎች ሁሉም ሰዎች ተመሳሳይ ሐሳብ እንደሌላቸው አውቃለሁ። እርስዎ አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስ እንዳለው ለማወቅ ምን ነገሮች ይረዳሉ ብለው ያስባሉ?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (በገጽ 380, 381 ያሉትን ሐሳቦች ተወያይባቸው።)