በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ

ፍቺ:- ለሰው ልጆች ተጽፎ የተሰጠ የይሖዋ አምላክ ቃል ነው። አምላክ ከ16 መቶ ዘመናት በሚበልጥ ጊዜ ውስጥ 40 የሚሆኑ ሰብዓዊ ጸሐፊዎችን በመጠቀም አስጽፎታል። ይሁን እንጂ ሐሳቡን ሲመዝግቡ አምላክ በቀጥታ በመንፈሱ አማካኝነት ይመራቸው ነበር። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተዘጋጀ መጽሐፍ ነው። አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይሖዋ የተናገራቸውንና የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በዝርዝር ያስተማራቸውን ትምህርቶችና ያከናወናቸውን ተግባራት መዝግቦ የያዘ ነው። በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ አምላክ ከአገልጋዮቹ የሚፈልጋቸውን ብቃቶችና ለምድር ያለውን ታላቅ ዓላማ ወደ ፍጻሜ ለማድረስ ምን እንደሚያደርግ የሚገልጹ ሐሳቦች እናገኛለን። ከዚህም በላይ ይሖዋ ስለነዚህ ነገሮች ያለን ግንዛቤ ጥልቅ እንዲሆን ግለሰቦችና ብሔራት አምላክን ሲያዳምጡትና ከዓላማው ጋር ተስማምተው ሲሠሩ ምን እንደሚያገኙ እንዲሁም በራሳቸው ሐሳብ ሲመሩ ምን ውጤት እንደሚከተልባቸው የሚገልጽ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠብቆ እንዲቆይልን አድርጓል። በዚህ ተመዝግቦ በሚገኘው እውነተኛ ታሪክ አማካኝነት ይሖዋ ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነትና የእርሱን አስደናቂ ባሕርያት እንድናውቅ አድርጓል።

መጽሐፍ ቅዱስን እንድንመረምር የሚያደርጉን ምክንያቶች

መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሰው ልጆች ፈጣሪ ከሆነው አምላክ የተገኘ መጽሐፍ እንደሆነ ይናገራል

2 ጢሞ. 3:16, 17 የ1980 ትርጉም:- “ቅዱስ መጽሐፍ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እርሱ እውነትን ለማስተማር፣ የተሳሳቱትን ለመገሠጽ፣ ስሕተትን ለማረምና ለትክክለኛ ኑሮ የሚበጀውን መመሪያ ለመስጠት ይጠቅማል።”

ራእይ 1:1:- “ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው።”

2 ሳሙ. 23:1, 2:- “የእሴይ ልጅ የዳዊት ንግግር፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነበረ።”

ኢሳ. 22:15 አዓት:- “የሠራዊት ጌታ ልዑል ይሖዋ እንዲህ ይላል።”

አምላክ ለሰው ልጆች በሙሉ የሰጠው መልእክት በመላው ምድር በቀላሉ ሊገኝ የሚችል መሆን ይኖርበታል ብለን እናስባለን። መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉም ይሁን በከፊል በ2,000 ያህል ቋንቋዎች ተተርጉሟል። በቢልዮን የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች በሰው እጅ ገብተዋል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ይላል:- “በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዛት የተነበበ መጽሐፍ የለም። ምናልባትም የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል የሰዎችን አስተሳሰብ የለወጠ መጽሐፍ የለም። ከማንኛውም መጽሐፍ በበለጠ ብዛት ተሰራጭቷል። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዙ የተለያዩ ቋንቋዎች የተተረጎመ መጽሐፍ የለም።”—(1984)፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 219

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የዓለም ሁኔታዎችን ትርጉም ይገልጻል

ብዙ የዓለም መሪዎች የሰው ዘር በታላቅ ጥፋት አፋፍ ላይ እንዳለ ይናገራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሁኔታዎች እንደሚመጡ ከረጅም ዘመን በፊት ተናግሮ ነበር። የእነዚህን ሁኔታዎች ትርጉምና ውጤቱ ምን እንደሚሆንም ጨምሮ ገልጿል። (2 ጢሞ. 3:1–5፤ ሉቃስ 21:10, 11, 31) ከመጭው የዓለም ጥፋት ለመዳንና ጽድቅ በሚሰፍንበት ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ምን ማድረግ እንደሚገባን ይናገራል።—ሶፎ. 2:3፤ ዮሐ. 17:3፤ መዝ. 37:10, 11, 29

መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወትን ዓላማ ለመረዳት ያስችለናል

መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተሉትን ለመሳሰሉ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል:- ሕይወት ከየት መጣ? (ሥራ 17:24–26) በምድር ላይ የምንኖረው ለምን ዓላማ ነው? ለጥቂት ዓመታት በሕይወት እንድንኖር፣ ከሕይወት ልናገኝ የምንችለውን አግኝተን በመጨረሻው እንድንሞት ብቻ ነውን?—ዘፍ. 1:27, 28፤ ሮሜ 5:12፤ ዮሐ. 17:3፤ መዝ. 37:11፤ መዝ. 40:8

መጽሐፍ ቅዱስ ጽድቅ ወዳዶች አጥብቀው የሚፈልጓቸውን ነገሮች እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ ይገልጻል

መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሳቸው ከልብ የሚዋደዱ ጥሩ ጓደኞች የት ማግኘት እንደሚቻል (ዮሐ. 13:35)፣ ለራሳችንና ለቤተሰቦቻችን በቂ ምግብ የምናገኝበትን ዋስትና እንዴት ልናገኝ እንደምንችል (ማቴ. 6:31–33፤ ምሳሌ 19:15፤ ኤፌ. 4:28)፣ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የከበቡን ቢሆንም እንዴት ደስተኞች ለመሆን እንደምንችል ይነግረናል።—መዝ. 1:1, 2፤ 34:8፤ ሉቃስ 11:28፤ ሥራ 20:35

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መንግሥት የአሁኑን ክፉ ሥርዓት እንደምታስወግድና (ዳን. 2:44)፣ በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር የሰው ልጆች ፍጹም ጤናና ዘላለማዊ ሕይወት አግኝተው በደስታ ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገልጻል።—ራእይ 21:3, 4፤ ከ⁠ኢሳይያስ 33:24 ጋር አወዳድር።

በአምላክ መንፈስ እንደተጻፈ የሚናገር፣ የዓለም ሁኔታዎችን ትርጉምና የሕይወትን ዓላማ የሚገልጽ፣ ችግሮቻችን እንዴት እንደሚወገዱ የሚያሳይ መጽሐፍ በእርግጥ ሊመረመር የሚገባው መጽሐፍ ነው።

  በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎች

ወደፊት ስለሚፈጸሙት ነገሮች ዝርዝር እውቀት በሚሰጡ ትንቢቶች የተሞላ ነው፤ ሰዎች ይህን የመሰለ እውቀት ሊኖራቸው አይችልም

2 ጴጥ. 1:20, 21:- “በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።”

◼ ትንቢት:- ኢሳ. 44:24, 27, 28፤ 45:1–4:- “እግዚአብሔር . . . ቀላዩንም:- ደረቅ ሁን፣ ፈሳሾችህንም አደርቃለሁ እላለሁ፤ ቂሮስንም:- እርሱ እረኛዬ ነው፤ እርሱም ኢየሩሳሌምን:- ትታነጺያለሽ ቤተ መቅደስም ይመሠረታል ብሎ ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል እላለሁ። እግዚአብሔር ለቀባሁት፣ አሕዛብንም በፊቱ አስገዛ ዘንድ የነገሥታትንም ወገብ እፈታ ዘንድ፣ በሮቹም እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹን በፊቱ እከፍት ዘንድ ቀኝ እጁን ለያዝሁት ለቂሮስ እንዲህ ይላል:- በፊትህ እሄዳለሁ ተራሮችንም ትክክል አደርጋለሁ፣ የናሱንም ደጆች እሰብራለሁ የብረቱንም መወርወሪያዎች እቆርጣለሁ፤ . . . ስለ ባሪያዬ ስለ ያዕቆብ፣ ስለ መረጥሁትም ስለ እስራኤል ብዬ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ በቁልምጫ ስምህ ጠራሁህ።” (ኢሳይያስ ይህን ጽፎ የጨረሰው በ732 ከዘአበ ነበር።)

◻ የትንቢቱ ፍጻሜ:- ትንቢቱ በተጻፈበት ጊዜ ቂሮስ ገና አልተወለደም ነበር። አይሁዶች ወደ ባቢሎን ግዞት የተወሰዱት ከ617–607 ከዘአበ በነበረው ጊዜ ነበር። ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ የተደመሰሱት በ607 ከዘአበ ነበር። ትንቢቱ በዝርዝር የተፈጸመው ከ539 ከዘአበ ጀምሮ ሲሆን በመጀመሪያ ቂሮስ የኤፍራጥስ ወንዝ አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ አንድ ሰው ሠራሽ ሐይቅ እንዲገባ አደረገ። የባቢሎን የወንዝ በሮች በከተማዋ ትልቅ ግብዣ ይደረግ በነበረበት ጊዜ በግድየለሽነት ሳይዘጉ ተረስተው ስለነበር ባቢሎን በቂሮስ በሚመሩት በሜዶናውያንና በፋርሳውያን እጅ ወደቀች። ከዚያ በኋላ ቂሮስ በግዞት ይኖሩ የነበሩትን አይሁዳውያን ነፃ በማውጣት በኢየሩሳሌም የነበረውን የይሖዋን ቤተ መቅደስ እንደገና እንዲሠሩ ወደ አገራቸው ላካቸው።—ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና (1956)፤ ጥራዝ 3፣ ገጽ 9፤ ላይት ፍሮም ዘ ኤንሸንት ፓስት (ከጥንቱ ዘመን የተገኘ የእውቀት ብርሃን) (ፕሪንስተን፣ 1959)፣ ጃክ ፊንገን፣ ገጽ 227–229፤ “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው ” (እንግሊዝኛ) (ኒው ዮርክ፣ 1983) ገጽ 282, 284, 295

◼ ትንቢት:- ኤር. 49:17, 18:- “ኤዶምያስም መደነቂያ ትሆናለች፣ የሚያልፍባትም ሁሉ ይደነቃል፣ ስለ መጣባትም መቅሠፍት ሁሉ ያፍዋጭባታል። ሰዶምና ገሞራ በእነርሱም አጠገብ የነበሩት ከተሞች እንደተገለበጡ፣ ይላል እግዚአብሔር፣ እንዲሁ በዚያ ሰው አይቀመጥም።” (ኤርምያስ ትንቢቱን ጽፎ የጨረሰው በ580 ከዘአበ ነበር።)

◻ የትንቢቱ ፍጻሜ:- “እነርሱ [ኤዶማውያን] ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው መቶ ዘመን በመቃባዊው ይሁዳ ከፍልስጥኤም ምድር ተባረሩ። በ109 ከክርስቶስ ልደት በፊት ደግሞ የመቃባውያን መሪ የነበረው ጆን ሒርካኑስ የኤዶማውያንን ምዕራባዊ ክፍል በመጠቅለል የይሁዳን ግዛት አስፋፋ። በአንደኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የሮማውያን አገዛዝ መስፋፋት የኤዶማውያንን የመጨረሻ የነፃነት ጭላንጭል አጥፍቶታል። . . . በ70 ዓ. . ኢየሩሳሌም በሮማውያን ስትጠፋ . . . ኤዱምያ [ኤዶም] የሚለው ስም ፈጽሞ ከታሪክ ጠፋ።” (ዘ ኒው ፋንክ ኤንድ ዋግናልስ ኢንሳይክሎፔድያ፣ 1952፣ ጥራዝ 11፣ ገጽ 4114) የትንቢቱ ፍጻሜ እስከ ዘመናችን ድረስ እንደ ቀጠለ ልብ በሉ። ይህ ትንቢት በምንም ዓይነት መንገድ ድርጊቶቹ ከተፈጸሙ በኋላ የተጻፈ ነው ሊባል አይችልም።

◼ ትንቢት:- ሉቃስ 19:41–44፤ 21:20, 21:- “ሲቀርብም [ኢየሱስ ክርስቶስ] ከተማይቱን [ኢየሩሳሌምን] አይቶ አለቀሰላት፣ እንዲህ እያለ:- . . . ወራት ይመጣብሻልና፣ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኩሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፣ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፣ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።” ከሁለት ቀናት በኋላም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ሲል መከራቸው:- “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ ጥፋትዋ እንደቀረበ እወቁ። በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ።” (ኢየሱስ ይህን ትንቢት የተናገረው በ33 እዘአ ነው።)

◻ የትንቢቱ ፍጻሜ:- ኢየሩሳሌም በሮም መንግሥት ላይ በማመጿ በ66 እዘአ በሴስትየስ ጋለስ የተመራው የሮማ ጦር ሠራዊት በከተማዋ ላይ ጥቃት ሰነዘረ። ነገር ግን ጆሴፈስ የተባለው አይሁዳዊ ታሪክ ጸሐፊ እንደዘገበው ሮማዊው የጦር አዛዥ “ወታደሮቹ ምንም ጥቃት ሳይደርስባቸው ወደኋላ እንዲመለሱ በማድረግ ከተማዋን ለማጥፋት የነበረውን ጥሩ አጋጣሚ ባልታወቀ ምክንያት በመተው ጥሎ ሸሸ።” (ጆሴፈስ፣ ዘ ጁዊሽ ዋር (ጆሴፈስ፣ የአይሁዶች ጦርነት)፣ ፔንጊውን ክላሲክስ፣ 1969፣ ገጽ 167) ይህም ዩሴቢየስ ፓምፊሉስ ኤክሊሲያስቲካል ሂስትሪ በተባለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት ክርስቲያኖች ከተማዋን ለቅቀው ፔላ ወደተባለ ከዮርዳኖስ ማዶ ወደሚገኝ ቦታ እንዲሸሹ አስችሏቸዋል። (ትርጉም በሲ ኤፍ ክሩሴ፣ ለንደን፣ 1894፣ ገጽ 75) ከዚያም በ70 እዘአ በማለፍ በዓል አካባቢ ጄኔራል ቲቶ ከተማዋን ከበበና 7.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው አጥር በሦስት ቀን ውስጥ በከተማዋ ዙሪያ አጠረ። ከአምስት ወር በኋላ ኢየሩሳሌም በሮማውያን እጅ ወደቀች። “ኢየሩሳሌም ፈጽማ ተደመሰሰች፣ ቤተ መቅደሱም የፍርስራሽ ክምር ሆነ። በአይሁድ ምድር የነበሩ ሕንፃዎች ምን ያህል እንደፈራረሱ ከከርሰ ምድር ጥናት (አርኪዮሎጂ) መረዳት ይቻላል።”—ዘ ባይብል ኤንድ አርኪዎሎጂ (መጽሐፍ ቅዱስና የከርሰ ምድር ጥናት) (ግራንድ ራፒድስ፣ ሚቺጋን፣ 1962)፣ ጄ ኤ ቶምሰን፣ ገጽ 299

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ሐሳቦች ተመራማሪዎች በቅርብ ጊዜ ካረጋገጧቸው ሳይንሳዊ ግኝቶች ጋር ይስማማሉ

የጽንፈ ዓለም አጀማመር:- ዘፍ. 1:1:- “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።” የጠፈር ተመራማሪ የሆኑት ሮበርት ጃስትሮው በ1978 እንዲህ ብለው ጽፈው ነበር:- “በአሁኑ ጊዜ ከጠፈር ምርምር የተገኙ መረጃዎች ስለ ዓለም አመጣጥ መጽሐፍ ቅዱስ ወደሚሰጠው ሐሳብ እየመሩን መሆናቸውን ለማየት ችለናል። በዝርዝር ነጥቦች ላይ ይለያዩ እንጂ በዋና ዋና ነገሮች ላይ የጠፈር ምርምርና የዘፍጥረት መጽሐፍ ታሪክ አንድ ናቸው፤ ወደ ሰው መገኘት የሚያመሩት ተከታታይ ሁኔታዎች የተፈጸሙት በድንገት በአጭርና በተወሰነ ጊዜ ውስጥ በብርሃንና በኃይል ብልጭታ ነው።”—ጎድ ኤንድ ዘ አስትሮኖመርስ (አምላክና የከዋክብት ተመራማሪዎች)፣ (ኒው ዮርክ፣ 1978) ገጽ 14

የመሬት ቅርጽ:- ኢሳ. 40:22:- “እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀመጣል።” በጥንት ዘመን መሬት ጠፍጣፋ ናት የሚል አጠቃላይ አስተሳስብ ነበር። የግሪክ ፈላስፎች መሬት ክብ ሳትሆን አትቀርም ብለው የተናገሩት ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ከተጻፈ ከ200 ዓመታት በኋላ ነው። እንዲሁም አንድ የግሪክ የጠፈር ተመራማሪ የምድር ራዲየስ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል በግምታዊ ስሌት የደረሰበት ከሌላ 300 ዓመት በኋላ ነው። ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜም ቢሆን ሰዎች በአጠቃላይ መሬት ክብ ናት የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው። በ20ኛው መቶ ዘመን ሰዎች በአውሮፕላን መጓዝና ከዚያም ወደ ኅዋና ወደ ጨረቃ ሳይቀር መሄድ ስለቻሉ የመሬት ‘ክብነት’ ግልጽ ሊሆን ችሏል።

የእንስሳት አኗኗር:- ዘሌ. 11:6:- “ጥንቸል ያመሰኳል።” ይህን ሐሳብ አንዳንድ ተቺዎች ለረጅም ጊዜ የተቃወሙት ቢሆንም እንግሊዛዊው ዊልያም ኮፐር በ18ኛው መቶ ዘመን እዘአ ጥንቸል ሲያመሰኳ ተመልክተዋል። ያልተለመደው ዓይነት የጥንቸል የማመስኳት ዘዴ በ1940 በወጣው በለንደን ዙኦሎጂ ማኅበር ስብሰባ ሪፖርት ላይ በጥራዝ 110፣ ሴሪ ኤ ገጽ 159–163 ላይ ተገልጿል።

መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ የሚስማማ መሆኑ ያጋጣሚ ጉዳይ ሊሆን አይችልም

የመጽሐፍ ቅዱስን መጻሕፍት የጻፉት 40 የሚያክሉ ሰዎች ከተለያየ የኑሮ ዘርፍ የመጡ፣ ይኸውም ንጉሥ፣ ነቢይ፣ ከብት ጠባቂ፣ ቀረጥ ሰብሳቢና ሐኪም የሚገኙባቸው የተለያየ ሞያ የነበራቸው ሰዎች መሆናቸውን ስንገነዘብ የዚህን አባባል ትክክለኛነት ለመረዳት እንችላለን። ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ለመጻፍ ከ1,610 ዓመት በላይ ፈጅቷል፤ ስለሆነም ተመካክረው ለመጻፍ የሚያስችላቸው ምንም ዓይነት አጋጣሚ አልነበራቸውም። ሆኖም ጽሑፎቻቸው በጥቃቅን ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ስምምነት አላቸው። የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ምን ያህል እርስ በርሳቸው የተያያዙና አንድነት ያላቸው እንደሆኑ አይተህ ለማድነቅ መጽሐፍ ቅዱስን በግልህ ማንበብና ማጥናት ያስፈልግሃል።

መጽሐፍ ቅዱስ እንዳልተለወጠ እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?

“አሁን ለማረጋገጫነት የምንገለገልባቸውን የጥንት የብራና ጽሑፎች ቁጥር፣ እንዲሁም በበኩረ ጽሑፎቹና ለማረጋገጫነት በሚያገለግሉት ጥንታውያን የብራና ጽሑፎች መካከል ያለፉትን ዓመታት ስንመለከት መጽሐፍ ቅዱስ ከክላሲካል ማለትም ከጥንት ሮማውያንና ግሪካውያን ጽሑፎች [የሆሜር፣ የፕላቶና የሌሎች ግሪካውያን ጽሑፎች] ብልጫ አለው። . . . ክላሲካል ጽሑፎች በአንድ ላይ ተሰብስበው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሲወዳደሩ ቁጥራቸው በጣም ጥቂት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በርካታ ማረጋገጫ ያለው ጥንታዊ መጽሐፍ የለም።”—ዘ ባይብል ፍሮም ዘ ቢግኒንግ (ኒው ዮርክ፣ 1929) ፒ ማሪዎን ሲምስ፣ ገጽ 74, 76

በ1971 የታተመ አንድ ሪፖርት እንደገጸው ሁሉንም የዕብራይስጥ መጻሕፍት አጠቃለው ወይም በከፊል የያዙ 6,000 የሚያክሉ የእጅ ጽሑፍ ቅጂዎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ በጣም የቆየ የሚባለው ከዘአበ በሦስተኛው መቶ ዘመን የተጻፈው ነው። ከግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ደግሞ በግሪክኛ የተጻፉ 5,000 ቅጂዎች ሲገኙ በጣም የቆየ የሚባለው እዘአ በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ የተጻፈው ነው። ከዚህም ሌላ በሌሎች ቋንቋዎች የተተረጐሙ ብዙ ቅጂዎች አሉ።

ሰባት ጥራዞች ባሉት ዘ ቸስተር ቤቲ ቢብሊካል ፓፒሪ በተባለው መጽሐፍ መግቢያ ላይ ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን እንዲህ ብለው ጽፈዋል:- “እነዚህን የጥንት መጻሕፍት [በፓፒረስ ላይ የተጻፉ ጽሑፎች] በመመርመር የተደረሰበት የመጀመሪያውና በጣም አስፈላጊው መደምደሚያ እነዚህ ጥንታዊ መጻሕፍት በዛሬው ጊዜ የሚገኙትን መጻሕፍት ትክክለኛነት ያረጋግጣሉ የሚለው ነው። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ይሁን ወይም በአዲስ ኪዳን ውስጥ የጎላ ወይም መሠረታዊ የሆነ ልዩነት አይታይም። በጣም ትልቅ የሆነ ግድፈት ወይም ጭማሪ የለም፤ እንዲሁም ዐበይት ቁም ነገሮችን ወይም መሠረተ ትምህርቶችን የሚያዛቡ ልዩነቶች የሉም። በጽሑፎቹ ውስጥ የሚታዩት ልዩነቶች በጣም አነስተኛ ሲሆኑ የቃላት ቅደም ተከተል ወይም የቃላት ምርጫ ጉዳይ . . . ናቸው። እነዚህ የጥንት ጽሑፎች እስከ አሁን ካሉን ጽሑፎች ረዘም ያለ ዕድሜ ያላቸው በመሆናቸው አሁን በእጃችን ያሉት ጽሑፎች ያልተዛቡ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ስለሚረዱ በጣም አስፈላጊ ናቸው።”—(ለንደን፣ 1933)፣ ገጽ 15

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ከሌሎች ትርጉሞች የበለጠ ከመጀመሪያው ቋንቋ ሐሳብ ጋር የሚቀራረቡ መሆናቸው የታወቀ ነው። በቀላል አተረጓጐም የተዘጋጁ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የመጀመሪያውን ትርጉም እስከ መለወጥ የደረሱበት ጊዜ አለ። ጥቂት ተርጓሚዎች ደግሞ የግል እምነታቸውን በትርጉማቸው ላይ እንዲንጸባረቅ አድርገዋል። ይሁን እንጂ እነዚህን ስህተቶች ከተለያዩ ትርጉሞች ጋር በማስተያየት ማረም ይቻላል።

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘በመጽሐፍ ቅዱስ አላምንም’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘አምላክ እንዳለ ያምናሉ፣ አይደለም? . . . እንግዲያው አንድ ጥያቄ እንድጠይቅዎ የሚፈቅዱልኝ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመቀበል ያስቸገረዎት ነገር ምንድን ነው?’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ከመጀመሪያው ጀምሮ የሚሰማዎት እንዲህ ነበር? . . . አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ሳያጠኑ በመጽሐፍ ቅዱስ አላምንም ብለው ሲናገሩ እሰማለሁ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ከአምላክ የተላከ መልእክት እንደሆነ ብናምንበትና እርሱን ብንከተል የዘላለም ሕይወት እንደምናገኝ በግልጽ ስለሚናገር መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው እውነት መሆኑንና አለመሆኑን መርምረን ማወቅ ጠቃሚ የሚሆን አይመስልዎትም? ( ከገጽ 58–62 ባለው ሐሳብ ተጠቀም።)’

‘መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ይጋጫል’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ሌሎች ሰዎችም እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ። ይሁን እንጂ አንዳቸውም ቢሆኑ እርስ በርስ የሚቃረኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች ሊያሳዩኝ አልቻሉም። እኔ በግሌ መጽሐፍ ቅዱስ በማነብበት ጊዜ አንድም የሚጋጭ ሐሳብ አላገኘሁም። እርስዎ አንድ ምሳሌ ሊሰጡኝ ይችላሉ?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘እርግጥ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በአእምሯቸው ለፈጠረባቸው ጥያቄ መልስ ለማግኘት እንዳልቻሉ ተረድቻለሁ። ለምሳሌ ያህል ቃየን ሚስት ከየት አገኘ? እንደሚለው ያሉት ሊሆኑ ይችላሉ። (በገጽ 301 ላይ ባለው ሐሳብ ተጠቀም።)’

‘መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሰዎች ናቸው’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘እውነት ነው። 40 የሚያክሉ ሰዎች በዚህ ሥራ ተካፍለዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፉ የተጻፈው በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት ነው።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘እንደዚህ ሲባል ምን ማለት ነው? አንድ ሥራ አስኪያጅ ጸሐፊው ደብዳቤ እንድትጽፍለት እንደሚያደርግ ሁሉ አምላክም መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጻፍ በሰዎች ተጠቅሟል ማለት ነው።’ (2) ‘በሰማያት ከሚኖር አንድ ሕያው አካል መልእክት እንዴት ሊመጣ ይችላል ብለን ልንገረም አይገባም። ሰዎች እንኳ ጨረቃ ላይ ሆነው መልእክቶችና ፎቶግራፎች ወደ መሬት ልከዋል። ይህን እንዴት ሊያደርጉ ቻሉ? ከብዙ ዘመን በፊት አምላክ በፈጠራቸው ሕጎች በመጠቀም ነው።’ (3) ‘ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ሐሳብ ከአምላክ የተገኘ ለመሆኑ እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን? ከሰው ሊገኝ የማይችል ሐሳብ ስለያዘ ነው። እንዴት ያሉ ሐሳቦችን ይዟል? ወደፊት የሚፈጸሙ ሁኔታዎችን በዝርዝር ይገልጻል። እነዚህም ሙሉ በሙሉ በትክክል መፈጸማቸው በየጊዜው ተረጋግጧል። (ለምሳሌ  ገጽ 58–60፤ እንዲሁም ከገጽ 234–238 “የመጨረሻ ቀኖች” በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን ተመልከት።)’

‘እያንዳንዱ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዳሻው ይተረጉመዋል’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ቢሆንም ሁሉም አተረጓጐም ትክክለኛ ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘አንድ ሰው ቅዱሳን ጽሑፎች የሚናገሩትን ከራሱ ሐሳብ ጋር ለማስማማት ሲል ማጣመሙ ዘላለማዊ ጉዳት ሊያስከትልበት ይችላል። (2 ጴጥ. 3:15, 16)’ (2) ‘መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል ለመረዳት ሁለት ነገሮች ሊረዱን ይችላሉ። በመጀመሪያ ከጥቅሱ ፊት ኋላ (በዙሪያው) ያለውን ሐሳብ መመርመር። ቀጥሎ ጥቅሱን ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ዝምድና ካላቸው ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር ማወዳደር። ይህን ካደረግን የአምላክ ቃል አስተሳሰባችንን እንዲመራ ፈቀድንለታል ማለት ነው፤ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የምንሰጠው ትርጉሙም የእኛ ሳይሆን የአምላክ ይሆናል። የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች የሚከተሉት ይህንን ዘዴ ነው።’ (ገጽ 205, 206 “የይሖዋ ምሥክሮች” በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን ተመልከት።)

‘ለዘመናችን አያገለግልም’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ሁላችንም በዛሬው ጊዜ ሊሠሩ የሚችሉ ነገሮችን እንወዳለን፤ አይደለም እንዴ?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘ጦርነትን ማጥፋት ጠቃሚ ነገር ነው ቢባል አይስማሙም? . . . ሰዎች ከሌሎች ብሔራት ሕዝቦች ጋር በሰላም አብረው መኖር ቢማሩ መልካም ጅምር የሚሆን አይመስልዎትም? . . . መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት እንዲህ ይሆናል ሲል አስቀድሞ ተናግሯል። (ኢሳ. 2:2, 3) ዛሬ እየተካሄደ ባለው መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ዘመቻ ምክንያት ይህ ሁኔታ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እየተፈጸመ ነው።’ (2) ‘ከዚህም የበለጠ ነገር ያስፈልጋል:- ለጦርነት መንስኤ የሆኑት ሰዎችና ብሔራት በሙሉ መወገድ አለባቸው። ታዲያ ይህ ሊሆን የሚችል ነገር ነው? አዎን ነው፤ ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጽልናል። (ዳን. 2:44፤ መዝ. 37:10, 11)’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ይህ ነገር ለምን እንዳሳሰበዎት ይገባኛል። ለመመሪያነት የተዘጋጀ መጽሐፍ መመሪያዎቹ ምንም የማይሠሩ ከሆነ በዚህ መጽሐፍ መጠቀም ሞኝነት ይሆናል፤ አይደለም እንዴ?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘ደስተኛ የቤተሰብ ኑሮ እንዲኖረን የሚያስችል ጥሩ ምክር የሚሰጥ መጽሐፍ ለጊዜያችን ይሠራል ቢባል አይስማሙም? . . . ደስተኛ የቤተሰብ ኑሮ ያስገኛሉ የሚባሉት ሐሳቦችና ልማዶች በየጊዜው ይለዋወጣሉ። ጥሩ ውጤት አለማስገኘታቸውንም ዛሬ ከምናየው ሁኔታ ለመረዳት እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር የሚያውቁና በሥራ ላይ ለማዋል የሚጥሩ ሰዎች ግን ጽኑና ደስተኛ ቤተሰብ አላቸው። (ቆላ. 3:12–14, 18–21)’

‘መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ መጽሐፍ ነው፤ ግን ሙሉ በሙሉ እውነት ነው የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘እያንዳንዱ ሰው የተለያየ ሐሳብ ሊኖረው የሚችል መሆኑ እውነት ነው። አንድ ሰው አንድን ነገር እንዳወቀ ቢሰማውም ብዙውን ጊዜ ገና ያልመረመረው ቢያንስ አንድ ሌላ ጉዳይ ያገኛል። ነገር ግን እንደዚህ ያለ የእውቀት ውስንነት የሌለበት አንድ አካል አለ። ማን ይሆን? . . . አዎ፣ የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ነው።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘ኢየሱስ ክርስቶስ “ቃልህ እውነት ነው” ያለው ለዚህ ነው። (ዮሐ. 17:17) ይህ እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። (2 ጢሞ. 3:16, 17)’ (2) ‘አምላክ በድንቁርና እንድንደናበር አይፈልግም፤ እርሱ ለእኛ ያለው ፈቃድ የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንድናገኝ መሆኑን ተናግሯል። (1 ጢሞ. 2:3, 4) መጽሐፍ ቅዱስ አጥጋቢ በሆነ መንገድ እንዲህ ለመሰሉት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል:- . . .’ (አንዳንድ ሰዎችን ለመርዳት ሲባል በመጀመሪያ አምላክ እንዳለ ለማመን በሚያስችሉት መረጃዎች ላይ መወያየት ያስፈልግህ ይሆናል። ከገጽ 146–152 “አምላክ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።)

‘መጽሐፍ ቅዱስ የነጮች መጽሐፍ ነው’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ነጮች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ማሳተማቸው እውነት ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ዘር ከሌላው ዘር የተሻለ ነው አይልም።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የመጣ ነው፣ አምላክ ደግሞ ለማንም አያዳላም። (ሥራ 10:34, 35)’ (2) ‘የአምላክ ቃል የሁሉም አገር ሕዝቦችና ነገዶች በዚህች ምድር ላይ በአምላክ መንግሥት ሥር ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንዳላቸው ይናገራል። (ራእይ 7:9, 10, 17)’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘በፍጹም አይደለም! ስድሳ ስድስቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በመንፈስ አነሣሽነት የጻፉትን ሰዎች የመረጠው የሰው ልጆች ፈጣሪ ነው። ነጭ የቆዳ ቀለም ባላቸው ሰዎች ለመጠቀም ከመረጠ ይህ የእርሱ ኃላፊነት ነው። ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለነጮች ብቻ የተወሰነ አይደለም።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘ኢየሱስ የተናገረውን ልብ ይበሉ . . . (ዮሐ. 3:16) “ሁሉ” የሚለው አባባል የትኛውንም ዓይነት የቆዳ ቀለም ያላቸውን ሰዎች ይጨምራል። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ የሚል የመሰነባበቻ ንግግር አድርጎላቸው ነበር:- . . . (ማቴ. 28:19)’ (2) ‘እንዲያውም የሐዋርያት ሥራ 13:1 ኔጌር ስለተባለ አንድ ሰው ይናገራል። የዚህ ሰው ስም ትርጉም “ጥቁር” ማለት ነው። እሱም በሦሪያ ግዛት የአንጾኪያ ጉባኤ ውስጥ ነቢያትና አስተማሪዎች ከነበሩት አንዱ ነበር።’

‘እኔ የማምነው የኪንግ ጄምስን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ብቻ ነው’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘የራስዎ መጽሐፍ ቅዱስ በቅርብ ካለ ከእርሱ ውስጥ ያገኘሁትን አንድ በጣም የሚያበረታታ ነገር ብነግርዎት ደስ ይለኛል።’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ብዙ ሰዎች በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይጠቀማሉ። እኔም በግሌ ይህ ትርጉም አለኝ።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተጻፈው በዕብራይስጥ፣ በአረማይክና በግሪክኛ ቋንቋዎች እንደነበረ ያውቁ ነበር? . . . በእነዚህ ቋንቋዎች የተጻፉትን ማንበብ ይችላሉ? . . . ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አማርኛ ቋንቋ በመተርጎሙ አመስጋኞች ነን።’ (2) ‘ይህ ሰንጠረዥ (በአዓት ላይ ያለው “የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የተዘረዘሩበት ሰንጠረዥ”) የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የዘፍጥረት መጽሐፍ ተጽፎ ያለቀው በ1513 ከዘአበ እንደነበረ ያሳያል። የዘፍጥረት መጽሐፍ ከተጻፈ በኋላ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ እስከሚተረጐም 2, 900 ዓመታት እንዳለፉ ያውቁ ነበር? የኪንግ ጄምስ ትርጉም የተጠናቀቀው ተጨማሪ 200 ዓመታት ካለፉ በኋላ ነው። (በ1611 እዘአ)’ (3) ‘ከ17ኛው መቶ ዘመን ወዲህ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ብዙ ለውጦችን አድርጓል። በዘመናችንም እንኳ ይህን ለማየት ችለናል። አይደለም እንዴ? . . . ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን እውነቶች ዛሬ በምንናገረው ቋንቋ የሚያቀርቡልንን ዘመናዊ ትርጉሞች በደስታ እንቀበላቸዋለን።’

‘እናንተ የራሳችሁ መጽሐፍ ቅዱስ አላችሁ’

“የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።