በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምስሎች

ምስሎች

ፍቺ:- አብዛኛውን ጊዜ አንድን ሰው ወይም ነገር ለማመልከት የሚያገለግሉ ቅርጾች ወይም ሥዕሎች ናቸው። ምስሉ አምልኮ የሚቀርብለት ከሆነ ጣዖት ነው። ብዙ ጊዜ ከምስል ፊት የሚሰግዱ ሰዎች አምልኮ የምንሰጠው በምስሉ ለተወከለው መንፈሳዊ አካል ነው በማለት ይናገራሉ። በምስል መጠቀም ክርስቲያን ባልሆኑ በብዙ ሃይማኖቶች ዘንድ የተለመደ ነው። በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚደረገውን የምስል አምልኮ አስመልክቶ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ (1967፣ ጥራዝ 7፣ ገጽ 372) እንዲህ ይላል:- “ለአንድ ምስል የሚሰጥ አምልኮ ዞሮ ዞሮ ምስሉ ወደሚወክለው አካል ስለሚደርስ ለዚህ ሕያው አካል የሚሰጠው አምልኮ ለምስሉም ሊሰጥ ይችላል።” የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም።

የአምላክ ቃል ለአምልኮ የሚያገለግሉ ምስሎችን ስለ መሥራት ምን ይላል?

ዘጸ. 20:4, 5:- “በላይ በሰማይ ካለው፣ በታችም በምድር ካለው፣ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ [“አትሥራ። ” “አዓት ”] አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም [“አትስገድላቸው ወይም አታገልግላቸው” ጀባ፤ “በፊታቸው አትስገድ ወይም አታምልካቸው” ኒአባ] . . . እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (የተከለከው ነገር ምስሎችን መሥራትና በፊታቸው ወድቆ መስገድ እንደሆነ ልብ ማለት ይገባል።)

ዘሌ. 26:1:- “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለእናንተ ጣዖት አታድርጉ፣ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት [“ቅዱስ ሐውልት” አዓት] አታቁሙ፤ ትሰግዱለት ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ።” (ሰዎች በፊቱ ወድቀው የሚሰግዱለት ምንም ዓይነት ምስል መቆም አልነበረበትም።)

2 ቆሮ. 6:16:- “ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና።”

1 ዮሐ. 5:21:- “ልጆች ሆይ፣ ከጣዖታት [“ከጣዖታት” ዱዌይ፣ ኮክ፤ “ከሐሰት አማልክት” ጀባ ] ራሳችሁን ጠብቁ።”

ምስሎች እውነተኛውን አምላክ ለማምለክ የሚረዱ መሣሪያዎች ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉን?

ዮሐ. 4:23, 24:- “በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል . . . አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።” (ለአምልኮ ይረዱናል በማለት በምስሎች የሚገለገሉ ሁሉ አምላክን “በመንፈስ” ማምለካቸው ሳይሆን በዓይናቸው ሊያዩት በሚችሉት ነገር መታመናቸው ነው።)

2 ቆሮ. 5:7:- “በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና።”

ኢሳ. 40:18:- “እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ?”

ሥራ 17:29:- “የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፣ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም።”

ኢሳ. 42:8:- “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት ] ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች [ዱዌይ፤ “ለጣዖታት” ጀባ ] አልሰጥም።”

“ቅዱሳን” አምላክን ያማልዳሉ ብለን በምስሎቻቸው በመጠቀም ልዩ አክብሮት ልንሰጣቸው ይገባናልን?

ሥራ 10:25, 26:- “ጴጥሮስ በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን:- ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ ብሎ አስነሣው።” (ጴጥሮስ በአካል ሳለ እንዲህ ያለውን አምልኮታዊ ክብር ካልተቀበለ ዛሬ በምስሉ ፊት እንድንበረከክ ይፈልጋልን? በተጨማሪ ራእይ 19:10⁠ን ተመልከት።)

ዮሐ. 14:6, 14:- “ኢየሱስም:- እኔ መንገድ እውነት ሕይወትም ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።” (እዚህ ላይ ኢየሱስ በግልጽ የተናገረው ወደ አብ መቅረብ የምንችለው በኢየሱስ በኩል እንደሆነና ጥያቄዎቻችንም በኢየሱስ ስም መቅረብ እንዳለባቸው ነው።)

1 ጢሞ. 2:5:- “አንድ እግዚአብሔር አለና፣ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፣ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።” (ሌሎች በአምላክና በክርስቶስ ጉባኤ መካከል መካከለኛ ሆነው እንዲያገለግሉ አልተፈቀደላቸውም።)

በተጨማሪ በገጽ 352 ላይ “ቅዱሳን” በሚለው ሥር ተመልከት።

አምላኪዎች ምስሎቹን ሲመለከቱ በአእምሯቸው ውስጥ በመጀመሪያ የሚቀረጸው በምስሉ የተወከለው አካል ነው ወይስ አንዳንድ ምስሎችን ከሌሎች ምስሎች አስበልጠው ይመለከታሉ?

የአማኞችን አስተሳሰብ ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም በ“ምስል” እና በ“ጣዖት” መካከል ያለው ዋና ልዩነት ምስሉ ጥቅም ላይ የዋለበት ዓላማ ነው።

አንድ አማኝ አንድን አካል ለሚወክሉ የተለያዩ ምስሎች የተለያየ ዋጋና ክብር ይሰጣልን? የሚሰጥ ከሆነ አማኙ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ለምስሉ ነው እንጂ ምስሉ ለተሠራለት አካል አይደለም። ሰዎች ለመሳለም ሲሉ ሩቅ መንገድ የሚሄዱት ለምንድን ነው? “ተአምራዊ” ኃይል እንዳለው የሚታመነው ምስሉ ራሱ አይደለምን? ለምሳሌ በካኖን ኢቭ ዴላፓርት የተጻፈው ሌ ትሯ ኖትር– ዳም ደ ላ ካቴድራል ደ ሻርትር የተባለው መጽሐፍ በፈረንሳይ አገር ሻርትር ውስጥ በሚገኘው ካቴድራል ስለተሠሩት የማርያም ምስሎች እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “እነዚህ የተቀረጹ ምስሎች፣ የቀለም ቅቦች ወይም ልዩ ልዩ ቀለሞች ባላቸው መስተዋቶች ምስሎች ላይ የሚታዩት ምስሎች ሁሉም እኩል ክብር አይሰጣቸውም። . . . ከእነዚህ ውስጥ የሚሰገድላቸው ሦስቱ ብቻ ናቸው። እነርሱም:- የክሪፕት እመቤታችን፣ የፒላር እመቤታችንና ‘በቤል ቨርየር’ የምትገኘው እመቤታችን ናቸው።” አማኞች ትልቅ ቦታ የሚሰጡትና በመጀመሪያ ደረጃ የሚያስቡት ምስሉን ሳይሆን ምስሉ የተሠራለትን አካል ቢሆን ኖሮ አንደኛውን ምስል ከሌላው ምስል ጋር እኩል እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩት አልነበረምን?

የሚሰገድላቸውን ምስሎች አምላክ እንዴት ይመለከታቸዋል?

ኤር. 10:14, 15:- “አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፣ እስትንፋስም የላቸውምና። እነርሱ ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው።”

ኢሳ. 44:13–19 የ1980 ትርጉም:- “አናጢው እንጨት ቆርጦ ይለካዋል፤ በእርሳስም ነድፎ በላዩ ላይ ቅርጽ ያወጣል፤ በመላጊያና በሌሎችም መሣሪያዎች ቀርጾ ውበት ያለው የሰው ምስል በማበጀት በቤቱ ያኖረዋል። ይህንንም ለማድረግ ዝግባ ይቆርጣል፤ የሾላ ዛፍ ወይም ጥድ ከጫካ ይመርጣል፤ አለበለዚያም የኮምቦል ዛፍ ተክሎ ዝናም እስኪያሳድገው ድረስ ይጠባበቃል። ሰው ከአንድ ዛፍ ግማሹን ለማገዶ፣ ግማሹንም ጣዖት ለመሥራት ይጠቀምበታል፤ ግማሹን እሳት አንድዶ ለመሞቅና እንጀራ ለመጋገር ይጠቀምበታል፤ በሌላው ጉማጅ ጣዖት ሠርቶ በፊቱ እየሰገደ ያመልከዋል። ግማሹን እሳት አንድዶ ምግቡን ያዘጋጅበታል፤ ሥጋም ጠብሶ እስከሚጠግብ ይመገባል፤ ከሞቀውም በኋላ “ግሩም እሳት ነው፤ እንዴት ይሞቃል!” ይላል። የቀረውንም ጉማጅ ጣዖት አድርጎ ይሠራና በፈቱ ተደፍቶ በመስገድ ያመልከዋል፤ “አንተ አምላኬ ነህ አድነኝ” እያለ ወደ እርሱ ይጸልያል። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ምንም ነገር የማያውቁና ማስተዋል የተሣናቸው ናቸው፤ እውነትን ላለማወቅ ዓይናቸውን በመጨፈን አእምሮአቸውን ዘግተዋል። ጣዖት የሚሠራ ሰው “እንጨት ቆርጬ ግማሹን አነደድሁት፤ በፍሙም እንጀራ ጋገርሁበት፤ ሥጋም ጠብሼ በላሁ፤ ታዲያ ግማሹን ጠርቤ ጣዖት አድርጌ ለሠራሁት ለእንጨት ጉማጅ የምሰግደው ለምንድን ነው?” ብሎ እንኳ አያመዛዝንም።”

ሕዝ. 14:6:- “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ንስሐ ግቡ ከጣዖቶቻችሁም [“አስጠሊ ጣዖቶቻችሁ” አዓት ] ተመለሱ፣ ፊታችሁንም ከርኩሰታቸው ሁሉ መልሱ።”

ሕዝ. 7:20:- “የክብሩንም ጌጥ ወደ ትዕቢት ለወጡ፣ የርኩሰታቸውንም ምስሎች አደረጉባት፤ ስለዚህ እኔ በእነርሱ ዘንድ ርኩስ [“ርኩስ” ዱዌይ፤ “ቆሻሻ” ኒአባ ] አድርጌአታለሁ።”

በፊት እንደ ቅዱስ አድርገን እናያቸው ስለነበሩት ምስሎች ምን ሊሰማን ይገባል?

ዘዳ. 7:25, 26:- “የተቀረጸውንም የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ የተሠራባቸውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትጠመድበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ። እንደ እርሱም ርጉም እንዳትሆን ርኩስን ነገር ወደ ቤትህ አታግባ፤ ርጉም ነውና ተጸየፈው፣ ጥላውም። [“በፍጹም ጥላቸው። በፍጹም ተጸየፋቸው።” አዓት ]” (ዛሬ የይሖዋ ሕዝቦች የሌሎች ሰዎች ንብረት የሆኑትን ምስሎች ሰባብረው የማስወገድ ሥልጣን ባይኖራቸውም አክብሮት ይሰጧቸው የነበሩ በእጃቸው የሚገኙ ምስሎችን ምን ሊያደርጓቸው እንደሚገባ ይህ ለእስራኤላውያን የተሰጠው ትእዛዝ ምሳሌ ይሆናቸዋል። ከሥራ 19:19 ጋር አወዳድር።)

1 ዮሐ. 5:21:- “ልጆች ሆይ፣ ከጣዖታት [“ከሐሰት አማልክት” ጀባ] ራሳችሁን ጠብቁ።”

ሕዝ. 37:23 የ1980 ትርጉም:- “ከዚያም በኋላ አስጸያፊ በሆኑ ጣዖቶች ራሳቸውን አያረክሱም፤ . . . እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።”

ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም በወደፊት ሕይወታችን ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?

ዘዳ. 4:25, 26:- “በማናቸውም ቅርጽ የተቀረጸውን ምስል [“ጣዖት” ኖክስ፤ “የማናቸውንም ነገር አምሳያ” ዱዌይ፤ “ማናቸውም ዐይነት ምስል” የ1980 ትርጉም] ባደረጋችሁ ጊዜ፣ ታስቆጡትም ዘንድ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር በሠራችሁ ጊዜ፣ . . . እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በእናንተ አስመሰክራለሁ፤ ፈጽሞም ትጠፋላችሁ።” (የአምላክ አመለካከት አሁንም አልተለወጠም። ሚልክያስ 3:5, 6⁠ን ተመልከት።)

1 ቆሮ. 10:14, 20:- “ወዳጆቼ ሆይ፣ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። . . . አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ፤ ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም።”

ራእይ 21:8:- “የሚፈሩና የማያምኑ የርኩሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይህም ሁለተኛ ሞት [የግርጌ ማስታወሻ “ዘላለማዊ ሞት”] ነው።”

መዝ. 115:4–8:- “የአሕዛብ ጣዖቶች የወርቅና የብር፣ የሰው እጅ ሥራ ናቸው። አፍ አላቸው አይናገሩምም፤ ዓይን አላቸው አያዩምም፤ ጆሮ አላቸው አይሰሙምም፤ አፍንጫ አላቸው አያሸትቱምም፤ እጅ አላቸው አይዳስሱምም፤ እግር አላቸው አይሄዱምም፤ በጉሮሮአቸውም አይናገሩም። የሚሠሩአቸውም የሚያምኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ።”