በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምድር

ምድር

ፍቺ:- “ምድር” የሚለው ቃል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከአንድ በበለጠ ትርጉም ተሠርቶበታል። አብዛኛውን ጊዜ ምድር ሲባል ትዝ የሚለን ይሖዋ ሰውን በሕይወት ለማኖር እንድትችልና በጣም አርኪ የሆነ ሕይወት እንድናሳልፍ በልግስና የሰጠንን ፕላኔት እንደሚያመለክት ነው። ይሁን እንጂ “ምድር” የሚለው ቃል በዚህች ፕላኔት ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ወይም አንዳንድ ባሕርያት ያሉትን ኅብረተሰብ ለማመልከት በምሳሌያዊ አነጋገር እንደሚሠራበትም መገንዘብ ያስፈልጋል።

ፕላኔቷ ምድር በኑክሌር ጦርነት ትጠፋ ይሆን?

መጽሐፍ ቅዱስ ምድርን በተመለከተ የአምላክ ዓላማ ምን መሆኑን ይገልጻል?

ማቴ. 6:10:- “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን። ”—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

መዝ. 37:29:- “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”

በተጨማሪ መክብብ 1:4፤ መዝሙር 104:5⁠ን ተመልከት።

ብሔራት ለአምላክ ዓላማ ደንታ ስለሌላቸው ምድር ለመኖሪያነት የማትመች እስክትሆን ድረስ ፈጽመው ሊያጠፏት ይችሉ ይሆን?

ኢሳ. 55:8–11:- “[ይሖዋ እንዲህ ይላል:-] ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው። . . . ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።”

ኢሳ. 40:15, 26:- “እነሆ፣ አሕዛብ [ከይሖዋ አምላክ አንፃር ሲታዩ] በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፣ በሚዛንም እንዳለ ትንሽ ትቢያ ተቆጥረዋል፤ . . . ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን [ፀሐይን፣ ጨረቃን በቢልዮን የሚቆጠሩትን ከዋክብት] የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።” (ብሔራት የፈጠሩት የኑክሌር ኃይል ለሰው አስፈሪ ነው። ነገር ግን በቢልዮን የሚቆጠሩት ከዋክብት ልንገምት እንኳን የማንችለው ከፍተኛ የኑክሌር ኃይል አላቸው። እነዚህን በሰማይ ያሉ አካላት የፈጠራቸውና የሚቆጣጠራቸው ማን ነው? እርሱስ መንግሥታት ዓላማውን በሚያደናቅፍ መንገድ የኑክሌር ጦር መሣሪያዎቻቸውን እንዳይጠቀሙባቸው ሊያደርግ አይችልምን? አምላክ ይህን ሊያደርግ የሚችል መሆኑ ፈርዖን እስራኤላውያን ከግብፅ እንዳይወጡ ለመከልከል በሞከረበት ጊዜ የግብፅን ወታደራዊ ኃይል በማጥፋቱ ታይቷል።—ዘጸ. 14:5–31)

ራእይ 11:17, 18:- “ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ ትልቁን ኃይልህን ስለ ያዝህ ስለ ነገሥህም እናመሰግንሃለን፤ አሕዛብም ተቆጡ፣ ቁጣህም መጣ፣ . . . ምድርን የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ [“የተቀጠረው” አዓት ] ዘመን መጣ።”

ራሱ አምላክ ምድርን በእሳት ያጠፋት ይሆን?

2 ጴጥሮስ 3:7, 10 ይህን አመለካከት ይደግፋልን? “አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል። . . . የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፣ የሰማይም ፍጥረት [“ንጥረ ነገሮች” አዓት] በትልቅ ትኩሳት ይቀልጣል፣ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። [“ይቃጠላል” ሪስ፣ ጀባ፣ የ1980 ትርጉም፤ “ይጠፋል” ቱኢቨ፤ “ይራቆታል” ኒአባ፤ “እንዲታይ ይገለጣል” ኒኢ፤ “ይገለጣል” አዓት ]” (ማስታወሻ:- ኮዴክስ ሲናይቲክስ እና ቫቲካን ኤም ኤስ 1209 የተባሉት በ4ኛው መቶ ዘመን እዘአ የተጻፉ ሁለት የብራና መጻሕፍት “ይገለጣል” ይላሉ። በኋለኞቹ ዘመናት የተጻፉት የብራና መጻሕፍት ለምሳሌ በ5ኛው መቶ ዘመን የተጻፈው ኮዴክስ አሌክሳንድሪኑስ እና ክሌመንታይን የተባለው በ16ኛው መቶ ዘመን ተሻሽሎ የወጣው የቩልጌት ትርጉም (ወደ ላቲን ቋንቋ የተተረጎመው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትገለገልበት የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ) “ይቃጠላል” ይላሉ።)

ራእይ 21:1 ፕላኔታችን እንደምትጠፋ ያመለክታልን? “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፣ ባሕርም ወደ ፊት የለም።”

ለእነዚህ ቁጥሮች የሚሰጠው ትርጉም ትክክል እንዲሆን በጥቅሶቹ ዙርያ ካለው ሐሳብና ከቀሪው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጋር መስማማት ይኖርበታል

የእነዚህ ጥቅሶች (2 ጴጥሮስ 3:7, 10 እና ራእይ 21:1) ሐሳብ ቃል በቃል ፕላኔቷ ምድራችን በእሳት ትጋያለች የሚል ትርጉም ከተሰጠው ግዑዛን ሰማያትም (ከዋክብትና ሌሎች በሰማይ ያሉ አካሎች) እንዲሁ ቃል በቃል በእሳት ተቃጥለው ይጠፋሉ ማለት ይሆናል። ጥቅሱን ቃል በቃል ወስዶ በዚህ መንገድ መረዳት እንደ ማቴዎስ 6:10፣ መዝሙር 37:29 እና 104:5እንዲሁም ምሳሌ 2:21, 22 ባሉት ጥቅሶች ውስጥ ከተሰጠው ማስረጃ ጋር ይቃረናል። ከዚህም በላይ እሳት ቀድሞውኑም እጅግ ከፍተኛ ግለት ባላት ፀሐይና በከዋክብት ላይ ምን ውጤት ሊኖረው ይችላል? ስለዚህ ከላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች ላይ “ምድር” የሚለው ቃል የተሠራበት ለየት ባለ መንገድ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

በ⁠ዘፍጥረት 11:1፣ አንደኛ ነገሥት 2:1, 2፣ አንደኛ ዜና መዋዕል 16:31፤ መዝሙር 96:1 ወዘተ ላይ “ምድር” የሚለው ቃል የሰው ልጆችን፣ ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል። በ⁠2 ጴጥሮስ 3:7, 10 እና ራእይ 21:1 ላይም የተሠራበት በዚሁ መንገድ ሊሆን አይችልምን?

በ⁠2 ጴጥሮስ 3:5, 6 (እንዲሁም 2:5, 9) ዙሪያ ያለው ሐሳብ ክፉ የነበረው ኅብረተሰብ በኖኅ ዘመን በደረሰው የጥፋት ውኃ ሲጠፋ ኖኅና ቤተሰቡ፣ መሬትም ጭምር መትረፋቸው ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ሆኖ እንደቀረበ ልብ በል። በተመሳሳይ በ⁠2 ጴጥሮስ 3:7 ላይ የጠፉት “እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች” ናቸው ይላል። ከላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች ላይ እንደተብራራው በዚህ ጥቅስ ላይ “ምድር” ክፉውን ኅብረተሰብ ያመለክታል የሚለው አመለካከት ከቀሪው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማል። ‘የተገለጠው’ [አዓት ] ይህ ምሳሌያዊ “ምድር” ወይም ክፉ ኅብረተሰብ ነው። ይህም ሲባል ይሖዋ ተሰውሮ የነበረውን ነገር ሁሉ ማለትም አምላክን የማያመልከውን ኅብረተሰብ ክፋት በመግለጥና ፈጽሞ መጥፋት እንደሚገባው በማሳየት በእሳት እንደሚነድ ያህል ጠራርጎ ያስወግደዋል ማለት ነው። ይህ ክፉ ኅብረተሰብ በ⁠ራእይ 21:1 ላይ “ፊተኛው ምድር” ተብሎ የተጠቀሰው ነው።

በዚሁ መንገድ በ⁠ሉቃስ 21:33 ላይ የሚገኘው (“ሰማይና ምድር ያልፋሉ . . . ግን . . .”) የሚለው የኢየሱስ አገላለጽ በ⁠ሉቃስ 16:17 (“ከ . . . ሰማይና ምድር ሊያልፍ ይቀላል ” ) ተብሎ ከተጠቀሰው ተመሳሳይ አነጋገር ጋር በአንድ ዓይነት መልክ መታየት አለበት። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ሁለቱም የሚያጐሉት በዚያ ላይ የቀረቡት ነገሮች የማይቻሉ መሆናቸውን ብቻ ነው።—በተጨማሪ ማቴዎስ 5:18⁠ን ተመልከት።

ጻድቃን ወደ ሰማይ ተወስደው፣ ክፉዎች ከጠፉ በኋላ ወደ ምድር ይመለሳሉን?

ራእይ 21:2, 3 ይህን አመለካከት ይደግፋልን? ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ቅድስቲቱ ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፣ ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፣ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ:- እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር [ይሆናል።]” (እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር “ያድራል”፣ ‘ከእነርሱ ጋር ይሆናል’ ማለት ሥጋ ይለብሳል ማለት ነውን? ይህ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ይሖዋ ለሙሴ:- “ሰው አይቶኝ አይድንም” ብሎታል። [ዘጸ. 33:20] ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አባሎች ሥጋዊ አካል የለበሱ ሰዎች በመሆን ወደ ምድር አይመለሱም። ታዲያ አምላክ ከሰዎች ጋር ‘የሚሆነው’ እና አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ‘ከሰማይ የምትወርደው’ በምን መንገድ ነው? በዘፍጥረት 21:1 [አዓት ] ላይ አምላክ ሣራን ‘እንደጐበኘ’ እና በእርጅና ዕድሜዋ ልጅን እንደሰጣት የሚገልጸው ሐሳብ ለዚህ ጥያቄ መልሱን እንደሚጠቁመን ምንም አያጠራጥርም። ዘፀአት 4:31 አምላክ ሙሴን እንደ ነፃ አውጭ አድርጎ በመላክ እስራኤልን “እንደ ጐበኘ” ይናገራል። ሉቃስ 7:16 አምላክ በኢየሱስ አገልግሎት አማካኝነት ሕዝቦቹን ‘እንደጎበኛቸው’ ይናገራል። ሌሎች ትርጉሞች አምላክ ወደ ሕዝቦቹ “ትኩረቱን መለሰ” [አዓት ] ወይም ‘ለእነርሱ እንደሚያስብ አሳየ’ [ኒኢ ] በሚሉ አገላለጾችን ተጠቅመዋል። ስለዚህ ራእይ 21:2, 3 የሚገልጸው አምላክ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች በረከት በምታመጣው በአዲሲቱ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በኩል የሰውን ልጅ ‘እንደሚጎበኝ’ ወይም ከሰዎች ጋር እንደሚሆን ነው።)

ምሳሌ 2:21, 22:- “ቅኖች በምድር ላይ [“ምድር ላይ” ኒኢ] ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም [“ነቀፋ የሌለባቸው ሰዎች” ኒኢ] በእርስዋ ይኖራሉና፤ [“ይቀራሉ።” “አዓት”] ኀጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ነቀፋ የሌለባቸው ወደ ምድር ይመለሳሉ ሳይሆን “በምድር ላይ ይቀራሉ” [አዓት] እንደሚል ልብ ማለት ይገባል።)

አምላክ ለምድር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማው ተለውጧልን?

ዘፍ. 1:27, 28:- “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም ባረካቸው፣ እንዲህም አላቸው:- ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።” (አምላክ ዓለምን በሞላ ገነት የማድረግ ኃላፊነት በሰጣቸው በአዳምና ሔዋን ልጆች ምድርን ለመሙላት ያለውን ዓላማ ያሳወቀው በዚህ መንገድ ነበር። ሰዎች በቴሌስኮፖችና (አቅርበው በሚያሳዩ መሣሪያዎችና) በጠፈር መንኩራኩሮች ከመረመሯቸው ሌሎች ፕላኔቶች ሁሉ ልዩ የሆነችውን ይህችን ምድር አምላክ ለሰው ልጆች መኖሪያ እንድትሆን ውብ አድርጎ ከሠራት በኋላ በአዳም ኃጢአት ምክንያት ለምድር የነበረውን ዓላማ ለዘላለም ሳይፈጽመው ይቀራልን?)

ኢሳ. 45:18:- “ሰማያትን የፈጠረ እግዚአብሔር፣ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፣ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፣ እንዲህ ይላል:- እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።” (በተጨማሪ ኢሳይያስ 55:10, 11⁠ን ተመልከት።)

በአዲሱ የአምላክ ሥርዓት ውስጥ ሞት ከሌለ ምድር ለዚያ ሁሉ ሰው እንዴት ትበቃለች?

አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማውን በገለጸ ጊዜ “ብዙ፣ ተባዙምድርንም ሙሉአት ” በማለት የተናገረውን አስታውስ። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ዘፍ. 1:28) አምላክ ለሰው የመራባት ችሎታ ሰጥቷል። ይህ ዓላማው ከተፈጸመ በኋላ ደግሞ በምድር ላይ መዋለድ እንዲቆም ማድረግ ይችላል።

አምላክ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት የሚሰጣቸው እንዴት ያሉ ሰዎች ናቸው?

ሶፎ. 2:3:- “እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፤ ትሕትናንም ፈልጉ፣ ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።”

መዝ. 37:9, 11:- “ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ . . . እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። . . . ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”