በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሞት

ሞት

ፍቺ:- የሁሉም የሕይወት እንቅስቃሴዎች መቆም ሞት ይባላል። ትንፋሽ፣ የልብ ምት፣ የአእምሮ ሥራ ከቆመ በኋላ በሰውነት ሴሎች ውስጥ የነበረው የሕይወት ኃይል እየከሰመ ይሄዳል። ሞት የሕይወት ተቃራኒ ነው።

አምላክ ሰውን የፈጠረው እንዲሞት ነበርን?

አምላክ ሰውን የፈጠረው እንዲሞት ሳይሆን ለዘላለም እንዲኖር ስለነበረ አዳም ሞት ከሚያስከትልበት ያለመታዘዝ ድርጊት እንዲርቅ ይሖዋ አስጠንቅቆት ነበር። (ዘፍ. 2:17) ከጊዜ በኋላ አምላክ እስራኤላውያንን ያለ ዕድሜአቸው እንዲቀጠፉ ከሚያደርጋቸው ተግባር እንዲርቁ አስጠንቅቋቸዋል። (ሕዝ. 18:31) አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስም በርሱ ዝግጅት የሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ልጁን ስለ ሰው ልጆች እንዲሞት ላከው።—ዮሐ. 3:16, 36

መዝሙር 90:10 የሰው ዕድሜ አብዛኛውን ጊዜ 70 ወይም 80 ዓመት እንደሚደርስ ይናገራል። ይህ ሁኔታ ሙሴ በጻፈበት ዘመን እውነት ቢሆንም ከመጀመሪያ ጀምሮ ግን እንዲህ አልነበረም። (ከዘፍጥረት 5:3–32 ጋር አወዳድር።) ዕብራውያን 9:27 “ሰዎች አንዴና ለሁልጊዜ እንዲሞቱ ተመድቦባቸዋል” ይላል። [አዓት ] ይህም ቢሆን እውነት የሆነው በተጻፈበት ጊዜ ነበር። አምላክ በኃጢአተኛው አዳም ላይ የሞት ፍርድ ከመፍረዱ በፊት ግን ሁኔታው እንደዚህ አልነበረም።

የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው?

ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ለዘላለም ለመኖር የሚችሉ ፍጹማን አድርጎ ፈጥሯቸው ነበር። የፈቀዱትን የማድረግ ነፃነትም ተሰጥቷቸው ነበር። ፈጣሪያቸው ያደረገላቸውን ነገር ሁሉ በማሰብ በፍቅርና በአድናቆት ተነሳስተው ይታዘዙት ይሆን? ይህን ለማድረግ የተሟላ ብቃት ነበራቸው። አምላክ ለአዳም እንዲህ ብሎት ነበር:- “መልካሙንና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።” ሰይጣን እባብን እንደ ቃል አቀባይ አድርጎ በመጠቀም ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ እንድታፈርስ አታለላት። አዳምም ሔዋንን በመገሠጽ ፈንታ የተከለከለውን ፍሬ በመብላት ተባበራት። ይሖዋ በተናገረው ማስጠንቀቂያ መሠረት በአዳም ላይ የሞት ፍርድ በየነበት። ይሁን እንጂ ኃጢአት የሠሩት ባልና ሚስት ከመሞታቸው በፊት ይሖዋ በምሕረቱ ልጆች እንዲወልዱ ፈቀደላቸው።—ዘፍ. 2:17፤ 3:1–19፤ 5:3–5፤ ከ⁠ዘዳግም 32:4 እና ራእይ 12:9 ጋር አወዳድር።

ሮሜ 5:12, 17, 19:- “ኃጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] ወደ ዓለም ገባ፣ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤ . . . በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል [ነገሠ።] . . . በአንድ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች [ሆኑ።]”

1 ቆሮ. 15:22:- “ሁሉ በአዳም [ይሞታሉ።]”

በተጨማሪ “ዕድል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ሕፃናት ለምን ይሞታሉ?

መዝ. 51:5 የ1980 ትርጉም:- “ኃጢአተኛ ሆኜ እንደተወለድሁ ታውቃለህ፣ ከተፀነስሁበት ጊዜ ጀምሮ ኃጢአተኛ ነኝ።” (በተጨማሪ ኢዮብ 14:4፤ ዘፍጥረት 8:21⁠ን ተመልከት።)

ሮሜ 3:23፤ 6:23:- “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል፤ . . . የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው።”—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

አንዳንዶች አምላክ ልጆችን ከወላጆቻቸው ነጥቆ በሞት “ይወስዳቸዋል” ተብሎ ተነግሯቸዋል። ይህ ትክክል አይደለም። መሬት በቂ ምግብ ለመስጠት የምትችል ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ስግብግብ የሆኑ የፖለቲካና የንግድ ሰዎች ምግብ ለተቸገሩ ሰዎች እንዳይደርስ እንቅፋት በመሆናቸው በምግብ እጥረት የተነሣ ሰዎች ይሞታሉ። ሕፃናትም አዋቂዎችም በአደጋ ይሞታሉ። ሁላችንም ኃጢአትን ወርሰናል። ሁላችንም ፍጽምና የጐደለን ሰዎች ነን። ሁላችንም ሰው ሁሉ፣ ጥሩም ሆነ መጥፎ፣ በሚሞቱበት ሥርዓት ውስጥ የተወለድን ነን። (መክ. 9:5) ሆኖም ይሖዋ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር በትንሣኤ እንዲገናኙ የሚያደርግበትን ጊዜ ‘በናፍቆት’ ይጠባበቃል። ለዚህም የሚያስፈልገውን ፍቅራዊ ዝግጅት አድርጓል።—ዮሐ. 5:28, 29፤ ኢዮብ 14:14, 15፤ ከ⁠ኤርምያስ 31:15, 16 ጋር አወዳድር፤ ማር. 5:40–42

ሙታን የት ናቸው?

ዘፍ. 3:19:- “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራ ትበላለህ፤ አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህና።”

መክ. 9:10:- “አንተ በምትሄድበት በሲኦል [“መቃብር” ኪጄ፣ ኖክስ፤ “የሙታን ዓለም” የ1980 ትርጉም፣ ቱኢቨ ] ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።”

ሙታን በምን ሁኔታ ይገኛሉ?

መክ. 9:5:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና።”

መዝ. 146:4 አዓት:- “መንፈሱ ይወጣል፤ ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ በዚያ ጊዜ ሐሳቡ [“ሐሳቡ” ኪጄ፣ 145:4 በዱዌይ፤ “ያሰበው” ኒኢ፤ “ዕቅዱ” ሪስ፣ ኒአባ፤ “ምክሩ” የ1954 ትርጉም ] ሁሉ ይጠፋል።”

ዮሐ. 11:11–14:- “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ . . . ኢየሱስም በግልጥ:- አልዓዛር ሞተ፤ . . . አላቸው።” (በተጨማሪ መዝሙር 13:3 (በ1954 ትርጉም ቁጥር 4⁠ን) ተመልከት።)

ሥጋ ሲሞት ተለይታ ለብቻዋ የምትኖር የሰው ክፍል አለችን?

ሕዝ. 18:4:- “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ [“ነፍስ” ሪስ፣ ኒኢ፣ ኪጄ፣ ዱዌይ፣ ኖክስ፤ “ሰው” ጀባ፣ ቱኢቨ ] እርስዋ ትሞታለች።”

ኢሳ. 53:12:- “ነፍሱን [“ነፍሱን” ሪስ፣ ኪጄ፣ ዱዌይ፤ “ሕይወቱን” ቱኢቨ፤ “ራሱን” ጀባ፣ ኖክስ፣ ኒአባ ] ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአል።” (ከማቴዎስ 26:38 ጋር አወዳድር።)

በተጨማሪም “ነፍስ” እና “መንፈስ” የሚሉትን ዋና ርዕሶች ተመልከት።

የሞቱ ሰዎች በሕይወት ያሉትን ሊረዱ ወይም ሊጐዱ ይችላሉን?

መክ. 9:6:- “ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፣ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም።”

ኢሳ. 26:14:- “እነርሱ ሞተዋል፣ በሕይወት አይኖሩም፤ ጠፍተዋል፣ አይነሡም።”

ሞቱ ከተባለ በኋላ ወደ ሕይወት እንደተመለሱና ሌላ ዓይነት ሕይወት ስለመኖሩ ተናገሩ ስለሚባልላቸው ሰዎችስ ምን ሊባል ይቻላል?

አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሰው መተንፈስና ልቡ መምታት ካቆመ በኋላ በሰውነቱ ሴሎች ውስጥ ያለው የሕይወት ኃይል ከጥቂት ደቂቃ በኋላ መክሰም ይጀምራል። ሰውነቱ ለከፍተኛ ቅዝቃዜ እንዲጋለጥ ከተደረገ በአካሉ ሴሎች ውስጥ ያለው የሕይወት ኃይል የሚሟሽሽበትን ጊዜ ማዘግየት ይቻላል። በዚህ ምክንያት የሞቱትን ሰዎች ልብና ሳንባ እንደገና በማንቀሳቀስ (ካርዲዮፕሉመናሪ ሪሰስቴሽን) እንዲነቁ ማድረግ የሚቻልበት ጊዜ አለ። እንዲህ በመሰለ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሰዎች አካላቸው በድን (በሕክምና አጠራር “ክሊኒካሊ ዴድ”) ቢሆንም የሰውነታቸው ሕዋሳት ወይም ሴሎች ግን ገና ሕያዋን ናቸው።

“ሞተዋል” (ክሊኒካሊ ዴድ) ከተባሉ በኋላ ሕይወት የዘሩ ብዙ ሰዎች ስለነበሩበት ሁኔታ ምንም ነገር አያስታውሱም። ሌሎች እንደ መንሳፈፍ ያለ ስሜት ተሰማን፣ በጣም ቆንጆ የሆኑ ነገሮችን ተመለከትን ሲሉ አንዳንዶቹ ደግሞ የነበሩበት ሁኔታ በጣም አስደንግጧቸው እንደነበረ ይናገራሉ።

እንደነዚህ ያሉት ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሙበት ምክንያት የሕክምና ማብራሪያ ሊገኝ ይችላልን?

ዘ አሪዞና ሪፓብሊክ ለተባለ መጽሔት የሕክምና ዓምድ አዘጋጅ የሆኑት እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ሰውነትን የመቆጣጠር ችሎታ ሐኪሞች በሚሰጡት ማደንዘዣ ወይም በሕመም ወይም በአደጋ የተነሣ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ጊዜ የሰውነትን ተግባሮች በደመ ነፍስ የመቆጣጠር ችሎታም ያንኑ ያህል ዝቅ ይላል። በመሆኑም የነርቭ ሥርዓት ክፍል የሆኑት ኒውሮሆርሞን እና ካቴኮላሚን ሆርሞኖች ከልክ በላይ በሰውነት ውስጥ ይረጫሉ። የዚህ ውጤት ከሚያስከትላቸው ነገሮች መካከል አንዱ በቅዠት ሁኔታ ውስጥ መሆንና ከነቁ በኋላም ሞተው ወደ ሕይወት እንደተመለሱ አድርጎ ማሰብ ነው።”—ግንቦት 28, 1977፣ ገጽ ሲ–1፤ በተጨማሪ ፎርትሽሪት ዴር ሜዲሲን የተባለው የጀርመን የሕክምና መጽሔት፣ ቁጥር 41፣ 1979፤ ሳይኮሎጂ ቱዴይ፤ ጥር 1981⁠ን መመልከት ይቻላል።

ከሞት የተመለሱ ሰዎች የሰጡት ምሥክርነት ከሞቱ በኋላ ለወዳጆቻቸውና ለዘመዶቻቸው ተገልጠው የተናገሩ ሰዎች በሰጡት መግለጫ ተረጋግጦ የለምን?

የሙታንን ሁኔታ በተመለከተ ቀደም ብለው የተጠቀሱትን ጥቅሶች እንደገና አንብብ። የአምላክ የእውነት ቃል ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ምን ይነግረናል?

ሰዎች ከዚህ የተለየ ነገር እንዲያምኑ የሚፈልገው ማን ነው? ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አለመታዘዛቸው ሞት እንደሚያስከትልባቸው ካስጠነቀቃቸው በኋላ ይህንን በመቃረን አትሞቱም ያለው ማን ነው? “እባብም [ሰይጣን ተጠቅሞበት፣ ራእይ 12:9⁠ን ተመልከት] ለሴቲቱ አላት:- ሞትን አትሞቱም።” (ዘፍ. 3:4) በእርግጥ አዳምና ሔዋን ከጊዜ በኋላ ሞተዋል። እንግዲያው ነገሩን በምክንያታዊ አስተሳሰብ ስንመለከተው ሥጋ ከሞተ በኋላ በሕይወት የምትኖር መንፈሳዊ አካል አለች የሚለውን ሐሳብ የፈጠረው ማን መሆን አለበት? አስቀድመን እንደተመለከትነው የአምላክ ቃል እንደዚያ ብሎ አይናገርም። ለጥንቷ እስራኤል ተሰጥቶ የነበረው የአምላክ ሕግ ከሙታን ጋር መነጋገርን እንደ ‘ርኩስ’ እና “የተጠላ” ነገር በመቁጠር አውግዞታል። (ዘሌ. 19:31፤ ዘዳ. 18:10–12፤ ኢሳ. 8:19) በሕይወት ያሉት ሰዎች በሞት ከተለዩአቸው የሚወዷቸው ዘመዶቻቸው ጋር ለመነጋገር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ የፍቅር አምላክ ይህን ድርጊት ያወግዘው ነበርን? በሌላ በኩል ደግሞ አጋንንታዊ መናፍስት የሞቱትን ሰዎች መስለው በመቅረብ ቢያታልሉና በሰዎች አእምሮ ውስጥ ውሸት የሆነ ነገር እንዲቀረጽ ቢያደርጉ አገልጋዮቹ እንዲህ ከመሰለ ማታለል እንዲጠበቁ ቢያደርግ አምላክ ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየቱ አይሆንምን?—ኤፌ. 6:11, 12

የይሖዋ ምሥክሮች ለሙታን በሚደረገው ባሕላዊ የኀዘን ሥርዓት የማይካፈሉት ለምንድን ነው?

የሚወዱት ሰው በሞት ሲለይ ማዘንና ማልቀስ የተፈጥሮ ባሕርይ ነው፤ በተገቢው ሁኔታ ሊገለጽ ይችላል

የቅርብ ወዳጁ አልዓዛር ከሞተ በኋላ ‘ኢየሱስ እንባውን አፈሰሰ።’ (ዮሐ. 11:35) የአምላክ አገልጋዮች በሞት ምክንያት አምርረው ያዘኑባቸው ጊዜያት አሉ።—2 ሳሙ. 1:11, 12

ይሁንና የትንሣኤ ተስፋ በመኖሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ተብለው ተመክረዋል:- “ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፣ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን።”—1 ተሰ. 4:13

የይሖዋ አገልጋዮች የሚቃወሙት ከሞት ጋር የተያያዙትን ልማዶች በሙሉ አይደለም

ዘፍ. 50:2, 3 የ1980 ትርጉም:- “ዮሴፍ አገልጋዮቹ የሆኑትን መድኃኒት ቀማሚዎች የአባቱን ሬሳ መልካም መዓዛ ባለው ሽቱ እያሹ እንዲያደርቁት ትእዛዝ ሰጠ። . . . በሀገሩ ልማድ መሠረት ሬሳውን ለማድረቅ አርባ ቀን ፈጀባቸው።”—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

ዮሐ. 19:40:- “የኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት።”

አምላክን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች ከቃሉ ጋር ከሚቃረኑ ልማዶች ይርቃሉ

በአንዳንድ አገሮች ባሕል መሠረት አንድ ሰው በጣም ማዘኑን ለሰዎች ማሳየት አለበት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ:- “ስትጦሙም፣ [ከኀዘን የተነሣ] እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፣ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጦም፣ በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ፣ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።”—ማቴ. 6:16–18

አንዳንድ ባሕሎች ሰው ሥጋው ሲሞት በሕይወት የምትኖር የማትሞት ነፍስ ስላለችው በሕይወት ያሉት ምን እንደሚሠሩ ያያል የሚል እምነት ያንፀባርቃሉ። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን . . . አንዳች አያውቁም” ይላል። (መክ. 9:5) በተጨማሪ “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።”—ሕዝ. 18:4

ብዙ ልማዶች ሙታን በሕይወት ያሉት ሰዎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ከሚል ወይም ሙታንን ለመለማመጥ አንድ ነገር ካልተደረገላቸው በሕይወት ያሉትን ሊጐዱ ይችላሉ ከሚል ፍርሃት የመነጩ ናቸው። ነገር ግን ሙታን ሥቃይም ሆነ ደስታ ሊኖራቸው የማይችል መሆኑን የአምላክ ቃል ይናገራል። “መንፈሱ ይወጣል፤ ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ በዚያ ቀን ሐሳቡ ሁሉ ይጠፋል። ” (መዝ. 146:4 አዓት፤ በተጨማሪ 2 ሳሙኤል 12:22, 23⁠ን ተመልከት።) “ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፤ ከፀሐይ በታች በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲያ የላቸውም።”—መክ. 9:6

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ይህ ብዙዎች ያላቸው እምነት ነው። እኔ ግን አምላክ ስለዚህ ነገር ምን እንደሚል መመርመሩን ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘(ዘፍጥረት 2:17⁠ን አንብብ።) አንድ አባት ልጁን ይህን ብታደርግ ትሞታለህ ብሎ ቢያስጠነቅቀው ልጁ ያን እርሱ የከለከለውን ነገር እንዲያደርግ አባትዬው ይፈልጋል ለማለት ይቻላል?’ (2) ‘እንግዲያው አምላክ ለሰዎች ያለው ፈቃድ ምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ልጅንም አይቶ [ማለትም ኢየሱስ በእውነት የአምላክ ልጅ መሆኑን አስተውሎና ተቀብሎ] በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።” (ዮሐ. 6:40)’

‘ሞት ለዘላለም ይቀጥላል’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘እስከ ዘመናችን ድረስ በሰዎች ላይ ሲደርስ የቆየው ይህ ሁኔታ ነው።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘ይሁን እንጂ እስቲ በ⁠ራእይ 21:3, 4 ላይ (ወይም ኢሳይያስ 25:8) አምላክ የሰጠውን አስደናቂ ተስፋ ይመልከቱ።’

‘ቀንህ ከደረሰ ትሞታለህ’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ብዙ ሰዎች እርስዎ እንደሚሉት ይላሉ። ብዙዎቹ የጥንት ግሪካውያን ይህ ዓይነት አመለካከት እንደነበራቸው ያውቁ ነበር? እያንዳንዱ ሰው ምን ያህል ዕድሜ እንደሚኖረው የሚወስኑ ሦስት ሴት አማልክት አሉ ብለው ያምኑ ነበር። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወት የሚያቀርብልን አመለካካት ከዚህ በጣም የተለየ ነው።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘(መክብብ 9:11⁠ን አንብብ) ምሳሌ:- ከአንድ ሕንፃ ላይ አንድ ድንጋይ ተሸርፎ በአንድ መንገደኛ ላይ ወደቀ እንበል። ድንጋዩ በመንገደኛው ላይ እንዲወድቅ ያደረገው አምላክ ነው? ከሆነስ የሕንፃውን ባለቤት በቸልተኝነት ይህ አደጋ እንዲደርስ አደረገ ብሎ መክሰስ ትክክል ይሆናል? . . . መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ድንጋዩ በወደቀበት ጊዜ እግረኛው በዚያ ቦታ መገኘቱ ያልታሰበና ያልተጠበቀ አጋጣሚ ነበር።’ (2) ‘መጽሐፍ ቅዱስ መጥፎ አኗኗር ብናስወግድ ሕይወታችንን ልናተርፍ እንደምንችል ይነግረናል። (ምሳሌ 16:17) ወላጅ ከሆኑ ይህን መመሪያ ለልጆችዎ እንደሚጠቀሙበት እርግጠኛ ነኝ። ልጆችዎን እንዲህ ከመሰሉ ሕይወትን ሊያሳጡ ከሚችሉ ነገሮች እንዲርቁ ያስጠነቅቋቸዋል። ይሖዋም ዛሬ ለሰው ልጆች በማድረግ ላይ የሚገኘው ይህንኑ ነው።’ (3) ‘ይሖዋ ወደ ፊት ስለሚሆነው ነገር ያውቃል። በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የእርሱን ምክር ከማይቀበሉት ሰዎች የበለጠ ዕድሜ ለመኖር እንዴት እንደምንችል ይነግረናል። (ዮሐ. 17:3፤ ምሳሌ 12:28)’ (በተጨማሪ “ዕድል” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።)