በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሪኢንካርኔሽን

ሪኢንካርኔሽን

ፍቺ:- አንድ ሰው አንድ ጊዜ ወይም ከአንድ ለበለጡ ተከታታይ ጊዜያት ሰው ወይም እንስሳ ሆኖ እንደገና ይወለዳል የሚል እምነት ነው። በሌላ አካል ውስጥ ገብታ ዳግም ትወለዳለች ተብሎ ብዙ ጊዜ የሚታሰበው ረቂቅ የሆነች “ነፍስ” ናት። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም።

ከዚህ በፊት የማናውቃቸውን ሰዎችና ቦታዎች እንደምናውቅ ሆኖ የሚሰማን መሆኑ ሪኢንካርኔሽን እውነት መሆኑን ያረጋግጣልን?

አንድ በሕይወት ያለ ሰው ወይም ሴት ሌላ በሕይወት ያለ ሰው ወይም ሴት መስሎህ በስህተት ተናግረህ ታውቃለህን? ብዙዎች እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ለምን እንዲህ ይሆናል? አንዳንድ ሰዎች ተመሳሳይ ባሕርይ ስላላቸው እንዲያውም አንዳንዶቹ መልካቸው በጣም ተመሳሳይ ስለሚሆን ነው። ስለዚህ ከዚህ በፊት አይተኸው የማታውቀው ሰው እንደምታውቀው ሆኖ ቢሰማህ በቀድሞው ሕይወትህ ስለምታውቀው መሆኑን አያረጋግጥም፤ ያረጋግጣል እንዴ?

አንድ ቤት ወይም አንድ ከተማ ከዚህ በፊት አይተኸው የማታውቅ ሆኖ ሳለ እንደምታውቀው ሆኖ የሚሰማህ ለምን ሊሆን ይችላል? በቀድሞው ሕይወትህ በዚህ ቦታ ትኖር ስለነበረ ነውን? ብዙ ቤቶች አንድ ዓይነት ዲዛይን አላቸው። በጣም ተራርቀው በሚገኙ ከተሞች ሰዎች የሚገለገሉባቸው ዕቃዎች አንድ ዓይነት አሠራር ሊኖራቸው ይችላል። በጣም ተራርቀው የሚገኙ ቦታዎች እንኳን አንድ ዓይነት መልክ ይኖራቸው የለምን? ስለዚህ ከዚህ በፊት አይተኸው የማታውቀውን ሰው ወይም ቦታ እንደምታውቀው ሆኖ ቢሰማህ የግድ በሪኢንካርኔሽን ምክንያት ነው ማለት አይደለም።

አፍዝዘው የሚያናግሩ ሰዎች (ሂፕኖቲስት ) አንድ ሰው በሌላ ቦታና ዘመን ያሳለፈውን ሕይወት ትዝታ ሊቀሰቀሱበት መቻላቸው ሪኢንካርኔሽን እውነት መሆኑን ያረጋግጣልን?

ሰዎችን በማፍዘዝ በአእምሮአቸው ውስጥ የተከማቸውን ብዙ መረጃ እንዲያወጡ የሚያደርጉ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሂፕኖቲስት የሚባሉ ሰዎች ሳናውቀው በአእምሮአችን ውስጥ የተከማቸውን እውቀት እንድናወጣ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ትውስታዎች ወደ አእምሮ እንዴት ሊገቡ ቻሉ? ምናልባት አንድ መጽሐፍ አንብበህ ይሆናል፣ ወይም አንድ ፊልም ተመልክተህ ወይም ስለሆኑ ሰዎች በቴሌቪዥን አይተህ ይሆናል። ራስህን በእነዚህ ሰዎች ቦታ አድርገህ ያን ትዕይንት ተመልክተህ ከነበረ በአእምሮህ ውስጥ ሲቀረጽ ራስህ ከዚያ ተሞክሮ በቀጥታ እንደተካፈልክ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ይህን ያደረግከው ከብዙ ጊዜ በፊት ይሆንና ጨርሰህ ረስተኸው ይሆናል። ይሁን እንጂ በምትፈዝበት (ሂፕኖሲስ) ጊዜ “በሌላ ሕይወት” ውስጥ እንደነበርክ ያህል ልታስታውሰው ትችላለህ። ግን ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ ሁሉ ሰው እንደነዚህ ያሉት ነገሮች ትዝ ሊሉት ይገባ አልነበረምን? ነገር ግን እንደነዚህ ዓይነት ትውስታዎች የሚያጋጥሙት ሁሉም ሰው አይደለም። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በማፍዘዝ የሚገኙ የምሥክርነት ቃሎችን የማይቀበሉ መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል። የሚኒሶታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ1980 የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቷል:- “በማፍዘዝ (ሂፕኖሲስ) የሚገኝ መረጃ ወይም የመረጃ ክፍል እውነት፣ ሐሰት ወይም ቅዠት መሆኑንና አለመሆኑን ሊያረጋግጥ የሚችል ባለሞያ የለም። እንደነዚህ ያሉት ወጤቶች ሳይንሳዊ ትክክለኛነታቸው አስተማማኝ አይደለም።” (ስቴት ቨርሰስ ማክ፣ 292 ኤን ደብልዩ 2ዲ 764) በሚገኙት መረጃዎች አስተማማኝ አለመሆን አስተዋጽዖ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ አፍዛዡ (ሂፕኖቲስቱ) የሚናገረው ቃል በሰውዬው ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ሪኢንካርኔሽን ይታመንበት እንደነበረ የሚያሳይ ማስረጃ አለውን?

ማቴዎስ 17:12, 13 በሪኢንካርኔሽን ማመንን ያንጸባርቃልን?

ማቴ. 17:12, 13:- “[ኢየሱስም:-] ኤልያስ ከዚህ በፊት መጣ፤ የወደዱትንም ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም፤ እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ከእነርሱ መከራ ይቀበል ዘንድ አለው አላቸው። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ስለ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው አስተዋሉ።”

ይህ ማለት መጥምቁ ዮሐንስ በሌላ አካል መልክ የመጣ ኤልያስ ነበረ ማለት ነውን? አይሁዳውያን ካህናት ዮሐንስን “ኤልያስ ነህን?” ብለው በጠየቁት ጊዜ “አይደለሁም” ብሏል። (ዮሐ. 1:21) ታዲያ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? የይሖዋ መልአክ አስቀድሞ እንደተናገረው ዮሐንስ ከይሖዋ መሲሕ በፊት “የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፣ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤሊያስ መንፈስና ኃይል” ወጥቷል። (ሉቃስ 1:17) ስለዚህ መጥምቁ ዮሐንስ የነቢዩ ኤልያስን የመሰለ ሥራ በማከናወን ትንቢቱን ፈጽሟል።—ሚል. 4:5, 6

በ⁠ዮሐንስ 9:1, 2 ላይ የሚገኘው ዘገባ ሪኢንካርኔሽንን ያመለክታልን?

ዮሐ. 9:1, 2:- “[ኢየሱስ] ሲያልፍም ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው አየ። ደቀ መዛሙርቱም:- መምህር ሆይ፣ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ ብለው ጠየቁት?”

እነዚህ ደቀ መዛሙርት “የጥሩ ሰዎች ነፍስ ወደ ሌላ አካላት ይዛወራል” በሚለው የአይሁድ ፈሪሣውያን እምነት አመለካከታቸው ተለውጦ ይሆን? (ዎርስ ኦቭ ዘ ጁውስ (የአይሁዶች ጦርነት)፣ ጆሴፈስ፣ 2ኛ መጽሐፍ፣ ምዕራፍ 8፣ አንቀጽ 14) ጥያቄአቸው ይህ ሰው ‘ጥሩ ሰው’ ነበር ብለው እንደማያምኑ ስለሚያመለክት እንደዚያ ሊሆን አይችልም። ከዚህ ይልቅ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናቸው መጠን በቅዱሳን ጽሑፎች ያምኑ ነበር። ነፍስ እንደምትሞትም ያውቁ ነበር። ሆኖም በማኅፀን ውስጥ ያለ ሕፃን እንኳ ሕይወት ስላለውና በኃጢአት የተፀነሰ ስለሆነ እንዲህ ያለው ገና ያልተወለደ ሕፃን በነበረበት ኃጢአት ምክንያት ዕውር ሆኖ ሊወለድ ችሎ እንደሆነ መጠየቃቸው ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ የሰጠው መልስ ሪኢንካርኔሽንም ሆነ በእናቱ ማኅፀን ያለ ሕፃን ከመወለዱ በፊት ኃጢአት ሊሠራ የሚችል መሆኑን አያረጋግጥም። ኢየሱስ ራሱ ሲመልስ “እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም” ብሏል። (ዮሐ. 9:3) የአዳም ልጆች በመሆናችን ሰብዓዊ ጉድለቶችንና አለፍጽምናዎችን እንደምንወርስ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ዕውሩን በመፈወስ ይህንን አጋጣሚ አምላክን ለማስከበር ተጠቅሞበታል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስና ስለ ሞት የሚሰጠው ትምህርት ለሪኢንካርኔሽን እምነት ቦታ ይሰጣልን?

ዘፍጥረት 2:7 አዓት እንዲህ ይላል:- “ይሖዋ አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፣ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፣ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።” ሰው ራሱ ነፍስ መሆኑን አስተውል። ነፍስ ረቂቅ የሆነች ከአካል የተለየች ነገር አይደለችም። “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።” (ሕዝ. 18:4, 20) የሞተ ሰው “የሞተ ነፍስ” እንደሆነ ተገልጿል። (ዘኁ. 6:6 አዓት ) ሰው በሚሞትበት ጊዜ “መንፈሱ ይወጣል ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ በዚያ ቀን ሐሳቡ ሁሉ ይጠፋል።” (መዝ. 146:4 አዓት) ስለዚህ አንድ ሰው ሲሞት ሁለመናው ስለሚሞት ከእርሱ ተለይታ የምትኖርና ወደ ሌላ አካል የምትዘዋወር ነገር የለችም። (ለተጨማሪ ማብራሪያ “ነፍስ” እና “ሞት” የሚሉትን ዋና ዋና ርዕሶች ተመልከት።)

መክ. 3:19:- “የሰው ልጆችና የእንስሳ እድል ፈንታ አንድ ነው፤ ድርሻቸውም ትክክል ነው። አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል።” (ሰውም ሆነ እንስሳ ሲሞት ከእርሱ ተለይቶ በሕይወት የሚኖር ምንም ነገር የለም። ወደ ሌላ አካል ገብቶ ዳግመኛ የሚወለድ ነገር አይኖርም።)

መክ. 9:10:- “አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።” (ሙታን የሚሄዱት ወደ ሌላ አካል ሳይሆን የሰው ልጆች የጋራ መቃብር ወደሆነው ወደ ሲኦል ነው።)

 በሪኢንካርኔሽንና መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ተስፋ መካከል ምን ያህል ልዩነት አለ?

ሪኢንካርኔሽን:- በዚህ እምነት መሠረት አንድ ሰው ጥሩና ትክክለኛ ሕይወት ኖሮ ከነበረ በሚሞትበት ጊዜ ነፍሱ ማለትም ‘እውነተኛው ማንነቱ’ ወደ ተሻለ ሕልውና፤ መጥፎ ነገር ሲያደርግ የኖረ ከሆነ ደግሞ ወደ እንስሳነት ትዛወራለች። ግለሰቡ እንደገና በተወለደ ቁጥር ወደዚሁ የነገሮች ሥርዓት እንደሚመለስ ይታመናል። በዚህም ሥርዓት ኖሮ ተጨማሪ መከራ ከተቀበለ በኋላ በመጨረሻው ይሞታል። የመወለዱ ድግግሞሽ ፍጻሜ የሌለው እንደሆነ ይታሰባል። ታዲያ አንተም የሚጠብቅህ ዕድል ይኸው ነውን? አንዳንዶች ከዚህ ለማምለጥ የሚቻለው የስሜት ሕዋሳትን ለሚያስደስቱ ነገሮች ያለንን ፍላጎት ፈጽሞ በማጥፋት እንደሆነ ያምናሉ። የሚያመልጡት ወዴት ነው? ምንም ሳይሰሙ በሕይወት ወደሚኖሩበት ሁኔታ ሲሄዱ ነው ይባላል።

መጽሐፍ ቅዱስ:- በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት መላው ሰው ነፍስ ነው። አንድ ሰው ከዚህ በፊት ክፉ ነገሮችን ሲያደርግ የኖረ ቢሆንም ንስሐ ቢገባና መንገዱን ቢለውጥ ይሖዋ አምላክ ይቅር ይለዋል። (መዝ. 103:12, 13) አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ከሱ ተለይቶ በሕይወት የሚኖር ነገር የለውም። ሞት ምንም ዓይነት ሕልም የሌለበት ከባድ እንቅልፍ ነው። ሙታን ይነሣሉ። ይህ ሪኢንካርኔሽን አይደለም። ሰውዬው ራሱ ከነባሕርያቱ የሚመለስበት ትንሣኤ ነው። (ሥራ 24:15) አብዛኞቹ ሰዎች የሚነሡት በምድር ላይ ለመኖር ነው። ይህም የሚሆነው አምላክ የአሁኑን ክፉ ሥርዓት ካጠፋ በኋላ ነው። በሽታ፣ መከራ፣ እና የሞት ግዳጅ እንኳን የቀሩ የቀድሞ ነገሮች ይሆናሉ። (ዳን. 2:44፤ ራእይ 21:3, 4) እንዲህ ዓይነቱ ተስፋ የበለጠ እንድታውቅና ለዚህም ተስፋ እርግጠኛ እንድትሆን የሚስችሉትን ምክንያቶች እንድትመረምር የሚያነሳሳህ ነውን?

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘እኔ በሪኢንካርኔሽን አምናለሁ’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ውሎ አድሮ ይህ ሪኢንካርኔሽን የተሻለ ሕይወት እንደሚያስገኝልዎት ተስፋ ያደርጋሉ፤ አይደለም? . . . እስቲ ይንገሩኝ በ⁠ራእይ 21:1–5 የተገለጸውን በሚመስል ዓለም ውስጥ ለመኖር አይፈልጉም?’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ይህን ስለነገሩኝ በጣም ደስ ብሎኛል። ግን ይህ እምነት ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበረዎት ነውን? . . . የቀድሞ እምነትዎን እንዲተዉ ያደረገዎት ነገር ምንድን ነው?’ (ከዚያም  በገጽ 319 ላይ ባለው ርዕስ ሥር የተገለጸውን ተጠቀም።)

ሌላ አማራጭ:- ‘እንዲህ ዓይነት እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር ጥሩ ውይይት አድርጌአለሁ። ግን ሪኢንካርኔሽን አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማዎት ለምንድን ነው?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘ከዚህ በፊት ኖሬባቸዋለሁ ብለው የሚያምኗቸው ሕይወቶች እንዴት ያሉ እንደነበሩ አንድ በአንድ ያስታውሷቸዋል? . . . ግን አንድ ሰው የቀድሞ ስህተቱን እንዲያሻሻል ከተፈለገ ቀድሞ ያሳለፈውን ሕይወት በዝርዝር ማስታወስ ይኖርበታል። አይመስልዎትም?’ (2) ሰውዬው ለማስታወስ አለመቻላችን ጥሩ እንደሆነ ከተናገረ እንዲህ ብለህ ልትጠይቅ ትችላለህ:- ‘አንድ ሰው በየዕለቱ የሚያጋጥሙትን ነገሮች የሚረሳ ቢሆን የሚጠቀም ይመስልዎታል? በየ70 ዓመት የተማርነውንና ያወቅነውን ነገር ሁሉ ረስተን በአዲስ ሁኔታ ብንጀምር የወደፊቱ ሕይወታችን የተሻለ የሚሆን ይመስልዎታል?’ (3) ሰውዬው ዳግመኛ ሰው ሆነው የሚወለዱት ደህና ሰዎች ብቻ ናቸው የሚል ከሆነ እንዲህ ብለህ ልትጠይቅ ትችላለህ:- ‘ታዲያ የዓለም ሁኔታ ይህን ያህል የከፋው ለምንድን ነው? . . . በዘመናችን እንዴት የተሻለ ሁኔታ እንደሚገኝ መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። (ዳን. 2:44)’