በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰንበት

ሰንበት

ፍቺ:- ሰንበት ሻቫት ከተባለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ቃል ነው። ትርጉሙም “ማረፍ፣ ማቆም፣ መቆጠብ” ማለት ነው። በሙሴ ሕግ ውስጥ የተደነገገው የሰንበት ሥርዓት በየሳምንቱ የሚከበርን የሰንበት ቀን፣ በዓመቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የሚከበሩ የተወሰኑ ቀናትን፣ ሰባተኛውን ዓመትና ሃምሳኛውን ዓመት ይጨምራል። ሳምንታዊው የአይሁዳውያን ሰንበት ማለትም በእነርሱ አቆጣጠር መሠረት ሰባተኛው ቀን ዓርብ ፀሐይ ከጠለቀች ጀምሮ ቅዳሜ ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ ያለው ጊዜ ነው። ብዙ ክርስቲያን ነን ባዮች እሑድን የሥርዓተ አምልኮና የእረፍት ቀን አድርገውታል። ሌሎች ደግሞ በአይሁዳውያን ቀን መቁጠሪያ የተወሰነውን ሰንበት ይጠብቃሉ።

ክርስቲያኖች ሳምንታዊ ሰንበት የማክበር ግዴታ አለባቸውን?

ዘጸ. 31:16, 17:- “የእስራኤልም ልጆች ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ቃል ኪዳን በሰንበት ያርፉ ዘንድ ሰንበትን ይጠብቁ። . . . በእኔና በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘላለም ምልክት ነው።” (ሰንበትን ማክበር በይሖዋና በእስራኤላውያን መካከል ምልክት ሆኖ የተሰጠ መሆኑን ልብ በል። ሌሎች አሕዛብም ሰንበትን የማክበር ግዴታ ቢኖርባቸው ኖሮ በይሖዋና በእስራኤላውያን መካከል ምልክት ሊሆን አይችልም ነበር። “ዘላለም” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ኦህላም ነው። የዚህ ቃል መሠረታዊ ትርጉም ከአሁኑ ጊዜ አንጻር ሲታይ መጨረሻው የተሰወረ ወይም ያልታወቀ ረዘም ያለ ጊዜ ማለት ነው። ይህ ቃል ፍጻሜ የሌለውን ዘመን ሊያመለክት የሚችል ቢሆንም ሁልጊዜ ትርጉሙ ይኸው ነው ማለት አይደለም። በዘኁልቁ 25:13 ላይ ይህ የዕብራይስጥ ቃል የክህነቱን ሥርዓት በተመለከተ ተሠርቶበታል፤ በ⁠ዕብራውያን 7:12 መሠረት ይህ የክህነት ሥርዓት ከጊዜ በኋላ አቁሟል።)

ሮሜ 10:4 የ1980 ትርጉም:- “ሰው ሁሉ በእምነት እንዲጸድቅ፣ የሙሴ ሕግ በክርስቶስ አክትሞአል።” (ሰንበትን ማክበር የሕጉ ክፍል ነበር። አምላክ በክርስቶስ በመጠቀም ይህን ሕግ ወደ ፍጻሜ አምጥቶታል። በአምላክ ዘንድ የጽድቅ አቋም ማግኘታችን የተመካው በክርስቶስ በማመን እንጂ ሳምንታዊ ሰንበት በማክበር አይደለም።) (በተጨማሪም ገላትያ 4:9–11፤ ኤፌሶን 2:13–16)

ቆላ. 2:13–16:- “[አምላክ] በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፤ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንን በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ . . . እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ።” (አንድ ሰው በሙሴ ሕግ ሥር ቢሆንና ሰንበትን ያረከሰ መሆኑ ተረጋግጦ ከተፈረደበት መላው ጉባኤ በ⁠ዘጸአት 31:14ና በ⁠ዘኁልቁ 15:32–35 ላይ እንደተገለጸው በድንጋይ ወግሮ ይገድለዋል። ሰንበት መከበር አለበት የሚሉ ብዙ ሰዎች በሙሴ ሕግ ሥር ባለመሆናችን ሊደሰቱ ይገባቸዋል። በዚህ ጥቅስ ላይ እንደተመለከተው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አቋም ለማግኘት ሰንበትን ወይም ለእስራኤላውያን የተሰጡትን ሕግጋት ማክበር አስፈላጊ አይደለም።)

እሑድ ለአብዛኛው የሕዝበ ክርስትና ክፍል ዋነኛው የአምልኮ ቀን ሊሆን የበቃው እንዴት ነው?

ክርስቶስ ከሞት የተነሣው በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን (በአሁኑ ጊዜ እሑድ ተብሎ በሚጠራው ቀን ላይ) ቢሆንም ይህ ቀን ቅዱስ ሆኖ እንዲከበር መጽሐፍ ቅዱስ አያዝም።

“የጥንቱ ‘ዲየስ ሶሊስ’ የተባለ የአረመኔዎች ስያሜ ሳይለወጥ ለሳምንታዊው የክርስቲያኖች በዓል በእንግሊዝኛ ‘ሳንዴይ’ የሚባል ስያሜ የተሰጠው በአብዛኛው ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ [በ321 እዘአ ባወጣው አዋጅ] ተገዢዎቹ በሙሉ ክርስቲያን[ተብዬዎቹ]ም ሆኑ አረማውያን ‘ቅዱሱን የፀሐይ ቀን’ እንዲያከብሩ ባዘዘው መሠረት የአረመኔነትና የክርስትና መንፈስ የተቀላቀለበት ነው። . . . ይህን ያደረገው እርስ በርሳቸው የሚጋጩትን የግዛቱን ሃይማኖቶች በአንድ የጋራ አቋም ለማስተባበር ፈልጎ ነው።”—ሌክቸርስ ኦን ዘ ሂስተሪ ኦቭ ዘ ኢስተርን ቸርች (ስለ ምሥራቃዊት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የቀረበ ማብራሪያ) (ኒው ዮርክ፣ 1871)፣ ኤ ፒ ስታንሊ፣ ገጽ 291

የሰንበት ሕግ ለአዳም የተሰጠ በመሆኑ በሁሉም የአዳም ልጆች ላይ ተፈጻሚነት ያለው ሕግ ነውን?

ይሖዋ አምላክ ምድርን ለሰው ልጅ መኖሪያነት ካዘጋጀና ምድራዊ ፍጥረታቱን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ ማረፍ ጀመረ። ይህም በ⁠ዘፍጥረት 2:1–3 ላይ ተገልጿል። ይሁን እንጂ አዳም በየሳምንቱ ሰባተኛውን ቀን ሰንበት አድርጎ እንዲያከብር መታዘዙን የሚገልጽ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም።

ዘዳ. 5:15:- “አንተም [እስራኤላውያን ማለት ነው] በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ እግዚአብሔር አምላክህ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ ከዚያ አወጣህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ የሰንበትን ቀን ትጠብቅ ዘንድ አዘዘህ።” (እዚህ ላይ ይሖዋ የሰንበትን ሕግ መስጠቱን ያዛመደው እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ከመውጣታቸው ጋር እንጂ በኤደን ከተፈጸሙት ነገሮች ጋር አይደለም።)

ዘጸ. 16:1, 23–29:- “የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ከግብፅ አገር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን በኤሊምና በሲና መካከል ወዳለችው ወደ ሲን ምድረ በዳ መጡ። . . . [ሙሴም:-] እግዚአብሔር የተናገረው ይህ ነው:- ነገ ዕረፍት ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ሰንበት ነው፤ . . . ስድስት ቀን [መናውን] ልቀሙት፤ ሰባተኛው ቀን ግን ሰንበት ነው፤ በእርሱ አይገኝም አለ። . . . እግዚአብሔርም ሙሴን:- . . . እግዚአብሔር ሰንበትን እንደ ሰጣችሁ እዩ . . . አለው።” (ይህ ከመሆኑ በፊት ቀኖች እያንዳንዳቸው የሰባት ቀን ርዝመት ባላቸው ሳምንታት ይከፈሉ ነበር። ሰንበትን ስለማክበር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው ግን እዚህ ላይ ነው።)

የሙሴ ሕግ “የሥነ ሥርዓት” ሕግጋትና “የሥነ ምግባር” ሕግጋት በሚባሉ የተለያዩ ክፍሎች የተከፈለ ነውን? “የሥነ ምግባር” ሕግጋቱስ (አሥርቱ ትእዛዛት) በክርቲያኖች ላይ ተፈጻሚነት አላቸውን?

ኢየሱስ ስለሕጉ ሲናገር በሁለት ክፍሎች እንደሚከፈል አመልክ ቶአልን?

ማቴ. 5:17, 21, 23, 27, 31, 38:- “እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።” ኢየሱስ በሰጠው ተጨማሪ አስተያየት ላይ ምን እንዳለ አስተውል። “ለቀደሙት:- አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል። [ዘጸ. 20:13፤ ስድስተኛው ትእዛዝ] . . . እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ [ዘዳ. 16:16, 17፤ የአሥሩ ትእዛዛት ክፍል አይደለም] . . . አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል። [ዘጸ. 20:14፤ ሰባተኛው ትእዛዝ] ሚስቱን የሚፈታት ሁሉ የፍችዋን ጽሕፈት ይስጣት ተባለ። [ዘዳ. 24:1፤ የአሥሩ ትእዛዛት ክፍል አይደለም] ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። [ዘጸ. 21:23–25፤ የአሥሩ ትእዛዛት ክፍል አይደለም]” (ስለዚህ ኢየሱስ ስለ አሥርቱ ትእዛዛትና ስለ ሌሎቹ ሕጎች የሚገልጹ ጥቅሶችን አንድ ላይ ቀላቅሎ ጠቅሷል። በመካከላቸውም ምንም ዓይነት ልዩነት እንዳለ አላመለከተም። እኛስ ከዚህ የተለየ ነገር ማድረግ ይገባናልን?)

ኢየሱስ “መምህር ሆይ፣ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት?” ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ አሥርቱን ትእዛዛት ነጥሎ አውጥቷልን? ከዚያ ይልቅ እንዲህ ሲል መልሷል:- “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፣ እርስዋም ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።” (ማቴ. 22:35–40) አንዳንዶች አሥርቱ ትእዛዛት (ዘዳ. 5:6–21) በክርስቲያኖች ላይ ተፈጻሚነት አላቸው የቀሩት ግን ተፈጻሚነት የላቸውም ቢሉ ኢየሱስ (ዘዳ. 6:5፤ ዘሌ. 19:18⁠ን ጠቅሶ) ከሁሉ ስለሚበልጡት ትእዛዛት የተናገረውን ቃል አለመቀበላቸው አይሆንምን?

መጽሐፍ ቅዱስ የሙሴ ሕግ ስለመሻሩ ሲናገር ከተሻሩት ሕግጋት መካከል አሥርቱ ትእዛዛት እንደሚገኙበት በቀጥታ ይናገራልን?

ሮሜ 7:6, 7:- “አሁን ግን ለእርሱ ለታሰርንበት ስለ ሞትን፣ ከሕግ ተፈትተናል፣ . . . እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ኃጢአት ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ ባይሆን ኃጢአትን ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ:- አትመኝ ባላለ ምኞትን ባላወቅሁም ነበርና።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (እዚህ ላይ ጳውሎስ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ‘ከሕግ እንደተፈቱ’ ከተናገረ በኋላ ከሕግ የትኛውን ምሳሌ ጠቀሰ? አሥረኛውን ትእዛዝ ጠቅሷል። ይህም ትእዛዝ ነፃ ከወጡበት ሕግ ውስጥ እንደሚገኝ አመልክቷል።)

 2 ቆሮ. 3:7–11 የ1980 ትርጉም:- “ሕግ የተቀረጸው በድንጋይ ጽላት በፊደል ነበር፤ ሕግ በተሰጠበትም ጊዜ የእግዚአብሔር ክብር በማንጸባረቅ ተገልጦአል፤ ምንም እንኳ በሙሴ ፊት ላይ ያንጸባርቅ የነበረው ብርሃን እየተወገደ የሚሄድ ቢሆንም እስራኤላውያን የሙሴን ፊት ትኩር ብለው ሊመለከቱ አልቻሉም፤ እንግዲህ ሞትን ያመጣ ሕግ በእንዲህ ዐይነት ክብር ከተገለጠ፣ ታዲያ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የሚገኘው አገልግሎት እንዴት የበለጠ ክብር ይኖረው! . . . ያ ጠፊ የነበረው ነገር ይህን ያህል ክብር ከነበረው ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው ነገርማ የበለጠ ክብር አለው ማለት ነው።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (እዚህ ላይ ‘በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ ሕግ’ ተጠቅሷል። በተጨማሪም ይህ ሕግ በተሰጠበት ጊዜ “የእስራኤል ልጆች ስለ ተሻረው ስለ ፊቱ ክብር የሙሴን ፊት ትኩር ብለው ሊመለከቱ” እንዳልቻሉ ተናግሯል። ይህ ጥቅስ የሚገልጸው ስለ ምን ነገር ነው? ዘጸአት 34:1, 28–30 እንደሚያመለክተው ስለ እሥርቱ ትእዛዛት መሰጠት የሚገልጽ ታሪክ ነው። በድንጋይ ላይ የተቀረጹት ሕግጋት አሥርቱ ትእዛዛት ናቸው። ቅዱስ ጽሑፉ “ጠፊ የነበረው” ብሎ ከጠቀሰው ሕግ ውስጥ አሥርቱ ትእዛዛት እንዳሉበት ግልጽ ነው።)

የሙሴ ሕግ አሥርቱ ትእዛዛትም ጭምር ከተሻረ ምንም ዓይነት የሥነ ምግባር ገደብ አይኖርም ማለት ነውን?

በፍጹም እንደዚያ ማለት አይደለም። በአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ ከተገለጹት የሥነ ምግባር ሕግጋት መካከል በመንፈስ አነሣሽነት በተጻፉት በግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በድጋሚ የሰፈሩ ብዙ ሕጎች አሉ። (የሰንበት ሕግ ግን ተደግሞ አልተገለጸም።) አንድ ሕግ ምንም ያህል ጥሩ ቢሆን የአንድን ሰው ፍላጎት የሚቆጣጠረው የኃጢአተኝነት ዝንባሌው እስከሆነ ድረስ ሕግ አፍራሽነት ይኖራል። ይሁን እንጂ በሕጉ ቃል ኪዳን ምትክ ስለ ተቋቋመው አዲስ ቃል ኪዳን ዕብራውያን 8:10 እንዲህ ይላል:- “ከዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና ይላል ጌታ፣ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፣ እኔም አምላክ እሆንላቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑልኛል።” እንደነዚህ ያሉት ሕግጋት በድንጋይ ጽላት ላይ ከተቀረጹ ሕግጋት የበለጠ ውጤት አላቸው።

ሮሜ 6:15–17:- “ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላይደለን ኃጢአትን እንሥራን? አይደለም። ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት፣ ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? ወይም ለሞት የኃጢአት ባሪዎች ወይም ለጽድቅ የመታዘዝ ባሪያዎች ናችሁ። ነገር ግን አስቀድማችሁ የኃጢአት ባሪያዎች ከሆናችሁ፣ ለተሰጣችሁለት ለትምህርት ዓይነት ከልባችሁ ስለ ታዘዛችሁ፣ ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለጽድቅ ስለ ተገዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።” (በተጨማሪም ገላትያ 5:18–24⁠ን ተመልከት።)

 ሳምንታዊው ሰንበት ለክርስቲያኖች ምን ትርጉም አለው?

ክርስቲያኖች በየቀኑ የሚያከብሩት “የሰንበት ዕረፍት” አላቸው

ዕብራውያን 4:4–11 እንዲህ ይላል:- “ስለ ሰባተኛው ቀን [አምላክ] በአንድ ስፍራ [በ⁠ዘፍጥረት 2:2]:- እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ ብሎአልና፤ በዚህ ስፍራም ደግሞ:- [መዝሙር 95:11] ወደ እረፍቴ አይገቡም። እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ ስለ ቀሩ፣ ቀድሞም የምሥራች የተሰበከላቸው ባለመታዘዝ ጠንቅ ስላልገቡ:- ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ በፊት እንደ ተባለ [በ⁠መዝሙር 95:7, 8] ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር:- ዛሬ ብሎ አንድ ቀን እንደገና ይቀጥራል። ኢያሱ አሳርፎአቸው ኖሮ ቢሆንስ፣ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር። እንግዲያውስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል። ወደ ዕረፍቱ የገባ፣ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፣ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና። እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ።”— ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

እዚህ ላይ ክርስቲያኖች የሚያርፉት ከምን ነገር ነው? ጥቅሱ ‘ከሥራቸው’ እንደሚያርፉ ይናገራል። እነዚህ ሥራዎች ምንድን ናቸው? ቀድሞ ራሳቸውን ለማጽደቅ ሲሉ ያደርጓቸው የነበሩ ሥራዎች ናቸው። አንዳንድ ሕጎችንና ሥርዓቶችን በመጠበቅ የአምላክን ሞገስና የዘላለም ሕይወትን የድካም ዋጋ ሆኖ ይከፈለናል ብለው ማመናቸውን ትተዋል። እምነተ ቢሶቹ አይሁዳውያን ‘ራሳቸውን ለአምላክ ጽድቅ ሳያስገዙ የራሳቸውን ጽድቅ ለማቆም ሲፈልጉ’ የሠሩት ስህተት ይህ ነበር። (ሮሜ 10:3) እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁላችንም ኃጢአተኞች ሆነን እንደተወለድንና ማንም ሰው በአምላክ ዘንድ የጽድቅ አቋም ሊያገኝ የሚችለው በክርስቶስ መሥዋዕት በማመን ብቻ እንደሆነ ይገነዘባሉ። የአምላክን ልጅ ትምህርቶች በሙሉ በልባቸው ውስጥ ለማኖርና በሥራ ላይ ለማዋል ይጥራሉ። ከአምላክ ቃል የሚሰጣቸውን ምክርና ተግሣጽ በትሕትና ይቀበላሉ። ይህ ማለት ግን እነዚህን ነገሮች በመፈጸም የአምላክ ሞገስ እንደ ድካማቸው ዋጋ ሆኖ ይከፈላቸዋል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሚሠሩት ሥራ የፍቅራቸውና የእምነታቸው መግለጫ ብቻ ነው። እንዲህ ያለውን አኗኗር በመከተል ከአይሁዳውያን የ“አለመታዘዝ ምሳሌ” ይርቃሉ።

በ⁠ዘፍጥረት 2:2 ላይ የተጠቀሰው “ሰባተኛ ቀን” የ24 ሰዓት ርዝመት ያለው ቀን አልነበረም። (ገጽ 87 ላይ “ፍጥረት” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።) በተመሳሳይም እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚያከብሩት “የሰንበት እረፍት” የ24 ሰዓት ርዝመት ባለው ቀን የተወሰነ አይደለም። በእምነትና የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በመታዘዝ በየቀኑ በተለይም በአምላክ አዲስ ሥርዓት ውስጥ በሰንበት እረፍት ለመደሰት ይችላሉ።

ከፊታችን ለሰው ልጆች የተጠበቀ የሺህ ዓመት “ሰንበት” አለ

ማር. 2:27, 28:- “[ኢየሱስ] ደግሞ ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም፤ እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው አላቸው።”

ኢየሱስ ሰንበት በአምላክና በእስራኤላውያን መካከል ምልክት ሆኖ እንዲያገለግል የተቋቋመ ሥርዓት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ይህም ሥርዓት የተደረገላቸው ከድካማቸው እረፍት እንዲያገኙ ተብሎ ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ የሙሴ ሕግ በራሱ ስለሚፈጸም የራሱ ሞት ለሙሴ ሕግ መሻር ምክንያት እንደሆነ ተገንዝቧል። የሰንበት ሕግ የሚገኝበት የሙሴ ሕግ ‘ለሚመጡ መልካም ነገሮች ጥላ እንደሚሆን’ ተገንዝቧል። (ዕብ. 10:1፤ ቆላ. 2:16, 17) ከእነዚህ ‘መልካም ነገሮች’ መካከል ወደፊት የሚመጣው “ሰንበት” ይገኛል። ኢየሱስ የዚህ ሰንበት ጌታ ነው።

ክርስቶስ የጌቶች ጌታ ሆኖ መላዋን ምድር ለሺህ ዓመት ይገዛል። (ራእይ 19:16፤ 20:6፤ መዝ. 2:6–8) በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በሰንበት ቀናት በጣም አስደናቂ የሆኑ የፈውስ ተአምራት ሠርቶአል። ይህም በሺህ ዓመቱ ግዛት ውስጥ ከብሔራት ሁሉ ለመጡ ሰዎች የሚሰጠውን ታላቅ እረፍትና እፎይታ ያመለክታል። (ሉቃስ 13:10–13፤ ዮሐ. 5:5–9፤ 9:1–14) ትክክለኛውን የሰንበት ትርጉም የሚገነዘቡ ሁሉ ከዚህ “የሰንበት” እረፍት የመጠቀም አጋጣሚ ያገኛሉ።

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘ክርስቲያኖች ሰንበትን ማክበር አለባቸው’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ለምን እንዲህ እንደተሰማዎት ብጠይቅዎትስ?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘በዚህ ጉዳይ ላይ ያለን አስተሳሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እንዲኖረው ያስፈልጋል። አይመስልዎትም? . . . በዚህ ጉዳይ ላይ ጠቃሚ ሐሳብ ሊሰጡ ይችላሉ ብዬ የማስባቸው አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። እስቲ አብረን እንያቸው። (ከዚያ በኋላ ቀደም ባሉት ገጾች ላይ ከቀረቡት ሐሳቦች በአንዳንዶቹ መጠቀም ይቻላል።)’

‘ሰንበትን የማታከብሩት ለምንድን ነው?’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘እርስዎ የሚናገሩት ስለየትኛው ሰንበት ነው? የምሰጥዎት መልስ በዚህ ላይ የተመካ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርለት ሰንበት አንድ ብቻ እንዳልሆነ ያውቁ ነበር? . . . አምላክ ለአይሁዳውያን የሰንበትን ሕግ ሰጥቶ ነበረ። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ሊያከብሩ ስለሚገባቸው የተለየ ዓይነት ሰንበት እንደሚናገር ያውቃሉ?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘መጽሐፍ ቅዱስ በሳምንት አንድ ቀን የሚውለውን ሰንበት ማክበር ‘እንደሚሻር’ ስለተናገረ ከሳምንቱ ቀናት አንዱን ሰንበት አድርገን አናከብርም። (2 ቆሮ. 3:7–11፤ ይህን በሚመለከት  በገጽ 347, 348 ላይ የሰፈረውን ሐሳብ ተመልከት።)’ (2) ‘ይሁን እንጂ ሁልጊዜ የምናከብረው ሰንበት አለን። (ዕብ. 4:4–11 ገጽ 348, 349⁠ን ተመልከት።)’