በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሲኦል

ሲኦል

ፍቺ:- “ሲኦል” ወይም በእንግሊዝኛ “ሄል” የሚለው ቃል በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ይገኛል። አንዳንድ ትርጉሞች ለዕብራይስጡ እና ለግሪክኛው ቃላት “መቃብር”፣ “የሙታን ዓለም” ወዘተ የሚል ትርጉም ሰጥተዋቸዋል። ሌሎች ትርጉሞች ደግሞ አንዳንድ ጊዜ “ሲኦል” እየተባሉ የሚተረጐሙትን በመጀመሪያው ቋንቋ የሚገኙትን ቃሎች ሳይለውጡ እንዳሉ በመተው አሁን በምንጠቀምባቸው ፊደላት ጽፈዋቸዋል። እነዚህ ቃላት የትኞቹ ናቸው? የዕብራይስጡ ሺኦል እና የእርሱ አቻ የሆነው የግሪክኛው ሔድስ ናቸው። እነዚህ ቃላት አንድን የተለየ መቃብር ብቻ ሳይሆን የሞቱትን የሰው ልጆች የጋራ መቃብር ያመለክታሉ። እንዲሁም ለዘላለም ጥፋት ምሳሌ ሆኖ የሚያገለግለውን ጌኤና የተባለውን የግሪክኛ ቃል ሳይተረጉሙ አሁን በምንጠቀምባቸው ፊደላት በመጻፍ እንዳለ ትተውታል። ይሁን እንጂ ሕዝበ ክርስትናና ክርስቲያን ያልሆኑ ብዙ የሃይማኖት ክፍሎች ሲኦል አጋንንት የሚኖሩበትና ክፉዎች ከሞቱ በኋላ የሚቀጡበት ቦታ ነው በማለት ያስተምራሉ። (አንዳንዶች ቅጣቱ ከፍተኛ ሥቃይ መቀበልን እንደሚጨምር ያምናሉ።)

ሙታን እንደሚሰቃዩ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራልን?

መክ. 9:5, 10:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ . . . አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።” (ሙታን ምንም የማያውቁ ከሆነ ሥቃይ ሊሰማቸው አይችልም።) (“በሺኦልአስ፣ ሪስ፣ ኒኢ፣ ጀባ፤ “በመቃብር” ኪጄ፣ ኖክስ፤ “በሲኦል” ዱዌይ፤ “በሙታን ዓለም” ቱኢቨ፣ የ1980 ትርጉም)

መዝ. 146:4 አዓት:- “መንፈሱም ይወጣል፣ ወደ መሬቱም ይመለሳል፣ በዚያች ቀን ሐሳቡ ሁሉ ይጠፋል።” (“ሐሳቡ” ኪጄ፣ ዱዌይ 145:4፤ “ውጥኑ” ጀባ፤ “ዕቅዱ” ሪስ፣ ቱኢቨ፣ የ1980 ትርጉም፤ “ምክሩ” የ1954 ትርጉም)

መጽሐፍ ቅዱስ ሥጋ ከሞተ በኋላ ተነጥላ በሕይወት የምትኖር ነፍስ እንዳለች ይገልጻልን?

ሕዝ. 18:4:- “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።” (“ነፍስ” ኪጄ፣ ዱዌይ፣ ሪስ፣ ኒኢ፣ ኖክስ፤ “ሰው” ጀባ፤ “ሰውዬው” ቱኢቨ)

“በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ነፍስ’ ፍጹም መንፈሳዊ የሆነች፣ ረቂቅ አካል ‘ከሥጋ’ . . . ተለይታ የምትሄድ መሆኗን የሚያመለክት ሐሳብ አይገኝም።”—ላ ፓሮል ደ ዲዩ (የአምላክ ቃል) (ፓሪስ፣ 1960)፣ ዦርዥ አውዘ፣ የቅዱሳን ጽሑፎች ፕሮፌሰር፣ ሮውን የሃይማኖት ትምህርት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት፣ ፈረንሳይ፣ ገጽ 128

“ምንም እንኳ ነፈሽ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል [በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ] ብዙ ጊዜ ‘ነፍስ’ ተብሎ ቢተረጐምም ለዚህ ቃል ግሪካዊ ትርጉም መስጠት ትክክል አይሆንም። ነፈሽ . . . ከሥጋ ተለይታ ትኖራለች የሚል ሐሳብ ከቶውንም አልነበረም። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ፕስሂ የሚለው የግሪክኛ ቃል ብዙውን ጊዜ ‘ነፍስ’ ተብሎ ተተርጉሟል፤ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የግሪክ ፈላስፎች ለቃሉ ይሰጡት የነበረው ዓይነት ትርጉም እንዳለው ተደርጎ አይታወቅም ነበር። ፕስሂ የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ ‘ሕይወት’ ወይም ‘ሕልውና’ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የገዛ ‘ራስ’ የሚል ትርጉም ነበረው።”—ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና (1977)፣ ጥራዝ 25፣ ገጽ 236

መጽሐፍ ቅዱስ ሲኦል ብሎ ወደሚጠራው ሥፍራ የሚሄዱት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?

መጽሐፍ ቅዱስ ክፉ ሰዎች ሲኦል ይገባሉ ብሎ ይናገራልን?

መዝ. 9:17:- “ኃጢአተኞች ወደ ሲኦል ይመለሳሉ፣ እግዚአብሔርን የሚረሱ አሕዛብም ሁሉ።” (“ሲኦል” 9:18 በዱዌይ፤ “ሞት” ቱኢቨ፤ “የሞት ስፍራ” ኖክስ፤ “ሺኦል” አስ፣ ሪስ፣ ኒኢ፣ ጀባ፣ አዓት )

መጽሐፍ ቅዱስ ቅን የሆኑትም ሰዎች ወደ ሲኦል ይሄዳሉ ይላልን?

ኢዮብ 14:13:- “[ኢዮብ እንዲህ በማለት ጸለየ:-] በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! ቁጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ! ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ!” (አምላክ ራሱ ኢዮብ “ነቀፋ የሌለበት፣ ትክክለኛ፣ አምላክን የሚፈራና ከመጥፎ ነገር የራቀ” ሰው ነው ብሏል።—ኢዮብ 1:8 አዓት ) (“በመቃብር” ኪጄ፤ “በሙታን ዓለም” ቱኢቨ፣ የ1980 ትርጉም፤ “ሺኦል” አስ፣ ሪስ፣ ኒኢ፣ ጀባ፣ አዓት )

ሥራ 2:25–27:- “ዳዊት ስለ እርሱ [ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ] እንዲህ ይላልና:- . . . ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፣ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም።” (አምላክ ኢየሱስን በሲኦል ውስጥ ‘አልተወውም’ መባሉ ኢየሱስ በሲኦል ወይም በሔድስ ውስጥ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን እንደነበረ አያሳይምን?) (“በሄል” ዱዌይ፤ “በሞት” ኒኢ፤ “በሞት ሥፍራ” ኖክስ፤ “በሙታን ዓለም” ቱኢቨ፣ የ1980 ትርጉም፤ “በሔድስ” አስ፣ ሪስ፣ ጀባ፣ አዓት )

አንድ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው ሲኦል መውጣት ይችላልን?

ራእይ 20:13, 14:- “ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፣ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፣ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ።” (እንግዲያውስ ሙታን ከሲኦል ይወጣሉ። በተጨማሪም ሲኦል ከእሳቱ ባሕር ጋር አንድ እንዳልሆነና ራሱ ሲኦል ወደ እሳት ባሕር የሚጣል መሆኑን አስተውል።) (“ሄል” ዱዌይ፣ ኖክስ፤ “የሙታን ዓለም” ቱኢቨ፤ “ሔድስ” ኒኢ፣ አስ፣ ሪስ፣ ጀባ፣ አዓት)

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሲኦል ምን እንደሚል ግራ መጋባት የተፈጠረው ለምንድን ነው?

“ብዙ ግራ መጋባትና መደናገር የተፈጠረው የጥንት የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ሺኦል የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል እንዲሁም ሔድስና ጌሄና የሚሉትን የግሪክኛ ቃላት በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ ለረጅም ጊዜ “ሄል” እያሉ በመተርጐማቸው ነው። በተሻሻሉት የመጽሐፍ ቅዱስ እትሞች ላይ ተርጓሚዎች እነዚህን ቃላት እንዳሉ ሳይተረጉሙ በጊዜው በሚሠራባቸው ፊደላት መጻፋቸው ብቻ ይህንን ውዥንብርና አለመግባባት ለማስወገድ በቂ አልሆነም።”—ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና (1942)፣ ጥራዝ 14፣ ገጽ 81

ተርጓሚዎች በኩረ ጽሑፎቹ ለተጠቀሙባቸው ቃላት አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም በመስጠት ፈንታ የግል እምነታቸው በትርጉም ሥራቸው ላይ እንዲንፀባረቅ አድርገዋል። ለምሳሌ (1) ኪንግ ጄምስ ቨርሽን ሺኦል ን “ሄል”፣ “መቃብር”፣ “ጉድጓድ”፤ ሔድስን ደግሞ “ሄል” እና “መቃብር” እንዲሁም ጌኤና ን “ሄል” በማለት ተርጉሟል። (2) ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን ሔድስ ን “ሔድስ” በማለት ሲያስቀምጠው ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ “ሄል” እና “የሙታን ዓለም” በማለት ተርጉሞታል። ከዚህ ሌላ “ሄል” የሚለውን ቃል ለሔድስ ብቻ ሳይሆን ጌኤና ለሚለው ቃልም ተጠቅሞበታል። (3) ዘ ጀሩሳሌም ባይብል ሔድስ ን ስድስት ጊዜ እንደዚያው እንዳለ ሔድስ ሲል ሌሎች ቦታዎች ላይ “ሄል” እና “ታችኛው ዓለም” በማለት ተርጉሞታል። ሔድስ ንም ሁለት ቦታ ላይ “ሄል” እያለ እንደተረጎመው ሁሉ ጌኤና የሚለውንም ቃል “ሄል” ብሎ ይተረጉመዋል። በዚህ መንገድ በጥንቱ ቋንቋ የተጻፉት ቃሎች ትክክለኛ ትርጉማቸው ሊደበቅ ቻለ።

ክፉዎች ለዘላለም ይቀጣሉን?

ማቴ. 25:46:- “እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፣ [“ተቆርጦ መጣል” ኢንተ፤ በግሪክኛ ኮላሲን ] ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።” (ዘ ኤምፋቲክ ዳያግሎት “ቅጣት” በማለት ፈንታ “ይቆረጣሉ” በማለት ተርጉሞታል። በአንድ የግርጌ ማስታወሻው ላይ እንዲህ ብሏል:- “ኮላሲን . . . የተገኘው ኮላዙ ከሚለው ቃል ሲሆን 1. መቁረጥን፤ የዛፍን ቅርንጫፍ መመልመልን፣ መግረዝን፣ መከርከምን 2. አንድን ነገር ከመሥራት ማገድን፣ በቁጥጥር ሥር ማድረግን . . . 3. መቅጣትን ያመለክታል በማለት ገልጿል። አንድን ግለሰብ ከሕይወት ወይም ከኅብረተሰብ መካከል መቁረጥ ወይም ማገድ እንደ ቅጣት ይቆጠር ነበር። ከዚህም የተነሣ ይህ ሦስተኛ ፈሊጣዊ አነጋገር ሊኖር ችሏል። የመጀመሪያው ፍቺ በዐረፍተ ነገሩ ውስጥ ከሚገኘው ከሌላ ቃል ጋር የበለጠ ስለሚስማማ ተመርጧል። እርሱንም በመውሰድ የተነጻጻሪ ሐሳቦች ኃይልና ውበት እንዳይጠፋ ተደርጓል። ጻድቃን ወደ ሕይወት ይሄዳሉ፤ ክፉዎች ግን ከሕይወት ይቆረጣሉ ወይም ይሞታሉ። 2 ተሰ. 1:9⁠ን ተመልከት።”)

2 ተሰ. 1:9 ሪስ:- የዘላለማዊ ጥፋት ቅጣት ይቀበላሉ፣ ይህም ከጌታና ከኃይሉ ክብር መራቅ ነው።” (“ዘላለማዊ ጥፋት” ኒአባ፣ ኒኢ፤ “ለዘላለም ይጠፋሉ” ጀባ፣ “ዘላለማዊ ቅጣት ይበየንባቸዋል” ኖክስ፣ “በመጥፋታቸው ዘላለማዊ ቅጣት ይደርስባቸዋል” ዱዌይ)

ይሁዳ 7:- “እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል።” (ሰዶምና ገሞራን ያጠፋው እሳት መንደዱን ካቆመ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት አልፈዋል። እሳቱ ያደረሰው ጉዳት ግን ዘላለማዊ ነበር። ከተሞቹ እስከ ዛሬ ድረስ ዳግመኛ አልተሠሩም። የአምላክ ፍርድ የወረደው በእነዚያ ከተሞች ላይ ብቻ ሳይሆን በከተሞቹ ይኖሩ በነበሩት ክፉ ሰዎችም ላይ ነው። በእነርሱ ላይ የደረሰው ነገር የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ሆኖ ያገለግላል። በሉቃስ 17:29 ላይ ኢየሱስ ሁሉንም “አጠፋ” በማለት ተናግሯል። ይሁዳ 7⁠ም ጥፋታቸው ዘላለማዊ መሆኑን ይገልጻል።)

በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው ‘የዘላለም ሥቃይ’ ትርጉም ምንድን ነው?

ራእይ 14:9–11፤ 20:10:- “ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ በግምባሩም ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር፣ እርሱ ደግሞ በቁጣው ጽዋ ሳይቀላቀል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር ቁጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፣ በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሣቀያል። የሥቃያቸውም ጢስ [በግሪክኛ ባሳኒስሙ ] ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል፣ ለአውሬውና ለምስሉም የሚሰግዱ፣ የስሙንም ምልክት የሚቀበል ሁሉ ቀንና ሌሊት እረፍት የላቸውም።” “ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፣ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ።”

በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የተጠቀሰው ሥቃይ ትርጉሙ ምንድን ነው? በ⁠ራእይ 11:10 ‘በምድር ላይ የሚኖሩትን ስለሚያሠቃዩ ነቢያት’ መገለጹን ልብ ማለት ይገባል። እንዲህ የመሰለው ሥቃይ ሊደርስ የቻለው ነቢያቱ የሚያጋልጥ መልእክት በማወጃቸው ነው። በ⁠ራእይ 14:9–11 ምሳሌያዊውን ‘አውሬና ምስሉን’ የሚያመልኩት “በእሳትና በዲን” እንደሚሠቃዩ ተገልጿል። ይህ ከሞቱ በኋላ እየሰሙ እንደሚሠቃዩ ሊያመለክት አይችልም ምክንያቱም “ሙታን . . . አንዳች አያውቁም።” (መክ. 9:5) እንግዲያው ገና በሕይወት እያሉ እንዲህ የመሰለ ሥቃይ የደረሰባቸው ለምንድን ነው? ‘አውሬውንና ምስሉን’ የሚያመልኩ ሰዎች “በእሳትና በዲን በሚቃጠል ባሕር” የተመሰለው ሁለተኛው ሞት እንደሚደርስባቸው የሚገልጸው የአምላክ አገልጋዮች ያስታወቁት መልእክት ነው። ከእሳታማ ጥፋታቸው ጋር የተያያዘው ጢስ ለዘላለም ወደ ላይ መውጣቱ ጥፋታቸው ዘላለማዊና የማይረሣ መሆኑን ያመለክታል። ራእይ 20:10 ዲያብሎስ ‘በእሳትና በዲን በሚቃጠለው ባሕር’ ‘ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሠቃያል’ ይላል። የዚህ አባባል ትርጉም ምንድን ነው? ራእይ 21:8 ይህ ‘በዲንና በእሳት የሚቃጠል ባሕር’ “ሁለተኛ ሞት ነው” በማለት በግልጽ ይናገራል። ስለዚህ ዲያብሎስ በዚያ ለዘላለም ‘ይሠቃያል’ ማለት እረፍት አይኖረውም፣ ለዘላለም በሞት ይታሠራል ማለት ነው። እዚህ ላይ ‘ማሠቃየት’ (በግሪክኛ ባሳኖስ ከተባለው ቃል የመጣ) ተብሎ የተተረጐመው ተመሳሳይ ቃል በ⁠ማቴዎስ 18:34 ‘የእስር ቤት ጠባቂን’ ለማመልከት እንደገባ ያስታውሰናል።— ሪስ፣ አት፣ ኤዳ፣ አዓት

ኢየሱስ የጠቀሰው ‘ገሃነመ እሳት’ ምንድን ነው?

ገሃነም የሚለው ቃል በግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ 12 ጊዜ ሲገኝ አምስት ጊዜ በቀጥታ ከእሳት ጋር ተዛምዶ ተገልጿል። ተርጓሚዎች ጌኤናን ቶው ፓይሮስ የሚለውን ግሪክኛ ሐረግ “የሲኦል እሳት” (ኪጄ፣ ዱዌይ፣ ኒኢ) “እሳታማ ጉድጓድ” (አት) እና “የገሃነም እሳት” (ኒአባ) በማለት ተርጉመውታል።

ታሪካዊ አመጣጡ:- የሄኖም ሸለቆ (ጌሄና) ከኢየሩሳሌም ቅጥር ውጭ ይገኝ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ጣዖት የሚመለክበትና ልጆች መሥዋዕት ሆነው የሚቀርቡበት ቦታ ነበር። በአንደኛው መቶ ዘመን ጌሄና የኢየሩሳሌም ቆሻሻ ማቃጠያ ሥፍራ ሆኖ ያገለግል ነበር። የእንስሳት በድን ወደዚህ ሸለቆ እየተጣለ ይቃጠልና እሳቱም እንዳይጠፋ ድኝ ይጨመርበት ነበር። እንዲሁም ሞት የተፈረደባቸውና አስከሬናቸው በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ መቀበር አይገባውም ተብለው የሚታሰቡ ወንጀለኞች አስከሬን ወደ ጌሄና ይጣል ነበር። ኢየሱስ በ⁠ማቴዎስ 5:29, 30 ላይ “ሙሉ ሰውነት” እንዳለ ወደ ጌሄና (ገሃነም እሳት) እንደሚጣል ተናግሯል። በዚህ ቦታ ወደሚገኘው ሳያቋርጥ የሚነድ እሳት የተጣለ አስከሬን ፈጽሞ ይቃጠል ነበር። ነገር ግን ከዚህ ጠባብ ሸለቆ ወደ ዳር ወጣ ብሎ የሚወድቅ ከሆነ በትሎች ይወረራል። (ማር. 9:47, 48) ሕያዋን ሰዎች ወደ ጌሄና አይጣሉም ነበር። ስለዚህ ጌሄና እየሰሙ የሚሰቃዩበት ቦታ አልነበረም።

በ⁠ማቴዎስ 10:28 ኢየሱስ አድማጮቹን “ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ” በማለት አስጠንቅቋል። ይህ ምን ማለት ነው? እዚህ ላይ በገሃነም እሳት ውስጥ ስለ መሠቃየት የተገለጸ ነገር እንደሌለ ልብ በሉ። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የተናገረው ‘በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን ፍሩ’ ብሎ ነው። ኢየሱስ እዚህ ላይ “ነፍስን” ለይቶ የተናገረው አምላክ የአንድን ሰው የወደፊት የመኖር ዕድል ጨርሶ ሊያጠፋ የሚችል መሆኑን ለማጉላት ነበር። ይህም ማለት ለዚያ ሰው የትንሣኤ ተስፋ አይኖረውም ማለት ነው። ስለዚህ ‘ገሃነመ እሳት’ የተባለው በ⁠ራእይ 21:8 ላይ ‘የእሳት ባሕር’ ከተባለው ጋር አንድ ዓይነት ትርጉም አለው። ጥፋት ወይም “ሁለተኛ ሞት” ማለት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የኃጢአት ቅጣት ምንድን ነው ይላል?

ሮሜ 6:23:- “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው።”

አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ለሠራው ኃጢአት ሌላ ተጨማሪ ቅጣት ይቀበላልን?

ሮሜ 6:7 አዓት:- “የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ሆኗል።”

ክፉ የሠሩ ሰዎችን ለዘላለም ማሰቃየት ከአምላክ ባሕርይ ጋር ይስማማልን?

ኤር. 7:31:- “[ከሃዲ የይሁዳ ነዋሪዎች] እኔም ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን፣ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ያለችውን የቶፌትን መስገጃዎች ሠርተዋል።” (ሰዎችን ማቃጠል በአምላክ ልብ ውስጥ ከሌለ ሰዎች የሚቃጠሉበት ሠፊ ቦታ አይኖረውም።)

ምሳሌ:- አንድ ወላጅ ልጁ ስላጠፋ እጁን በእሳት ውስጥ አስገብቶ እያቃጠለ ቢቀጣው ስለዚህ ወላጅ ምን ይሰማችኋል? “እግዚአብሔር ፍቅር ነው።” (1 ዮሐ. 4:8) ትክክለኛ አእምሮ ያለው ወላጅ የማያደርገውን ነገር አምላክ ያደርጋልን? በፍጹም አያደርገውም!

ኢየሱስ ስለ ሀብታሙ ሰውና ስለ አልዓዛር ሲናገር ክፉዎች ከሞቱ በኋላ እንደሚሠቃዩ ማስተማሩ ነበርን?

በ⁠ሉቃስ 16:19–31 ላይ ያለው ዘገባ ቃል በቃል እንዳለ የሚወሰድ ነው ወይስ ስለሌላ ነገር የሚገልጽ ምሳሌ? ዘ ጀሩሳሌም ባይብል በግርጌ ማስታወሻው ላይ “በታሪክ የነበሩ ሰዎችን ለይቶ የማይጠቅስ በትረካ መልክ የቀረበ ምሳሌ ነው” በማለት ገልጿል። ቃል በቃል እንዳለ ከተወሰደ መለኮታዊ ሞገስ የሚያገኙት ሰዎች በሙሉ በአንዱ ሰው በአብርሃም እቅፍ ይሆናሉ፤ በአንድ ሰው ጣት ላይ ያለ የውኃ ጠብታ በሔድስ ነበልባል አይተንም፤ አንዲት ጠብታ ውኃ በዚያ የሚሠቃይን ሰው ታረካለች ማለት ይሆናል። ይህ ምክንያታዊ ሆኖ ይታይሃልን? ቃል በቃል የተነገረ ከሆነ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር ይጋጫል። መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ የሚጋጭ ከሆነ እውነትን የሚያፈቅር ሰው የእምነቱ መሠረት አድርጎ ሊጠቀምበት ይችላልን? መጽሐፍ ቅዱስ ግን እርስ በራሱ አይቃረንም።

የኢየሱስ ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው? “ሀብታሙ ሰው” ፈሪሳውያንን ያመለክታል። (ቁጥር 14⁠ን ተመልከት) ለማኙ አልዓዛር በፈሪሳውያን ዘንድ የተናቁትን ግን ንስሐ ገብተው የኢየሱስ ተከታዮች የሆኑትን ተራ አይሁዳውያን ያመለክታል። (ሉቃስ 18:11፤ ዮሐንስ 7:49፤ ማቴዎስ 21:31, 32⁠ን ተመልከት።) ሞታቸውም ቢሆን ምሳሌያዊ ነበር። ሁኔታቸው የተለወጠ መሆኑን ያመለክታል። ቀድሞ ይናቁ የነበሩት መለኮታዊ ሞገስ አገኙ፣ ቀድሞ ሞገስ ያገኙ ይመስሉ የነበሩት በአምላክ ተጥለው ይንቋቸው የነበሩት ሰዎች በተናገሩት የፍርድ መልእክት ተሠቃዩ።—ሥራ 5:33፤ 7:54

የእሳታማ ሲኦል ትምህርት ምንጩ ምንድን ነው?

በጥንት የባቢሎናውያንና የአሦራውያን እምነት “የታችኛው ዓለም . . . አሰቃቂ ነገሮች የሞሉበት ትልቅ ጉልበትና ጭካኔ ያላቸው አማልክትና አጋንንት የሚገኙበት ቦታ ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር።” (ዘ ሪሊጅን ኦቭ ባቢሎንያ ኤንድ አሲርያ (የባቢሎንና የአሦር ሃይማኖት)፣ ቦስተን፣ 1898፣ ጁንየር ሞሪስ ጃስትሮው፣ ገጽ 581) የሕዝበ ክርስትና የእሳታማ ሲኦል እምነት በጥንቱ የግብፅ ሃይማኖት ውስጥ እንደነበረ የሚያሳይ የቆየ መረጃ ተገኝቷል። (ዘ ቡክ ኦቭ ዘ ዴድ (የሙታን መጽሐፍ)፣ ኒው ሃይድ ፓርክ፣ ኒው ዮርክ፣ 1960፣ መግቢያው በኢ ኤ ዋሊስ ባጅ የተዘጋጀ፣ ገጽ 144, 149, 151, 153, 161) በ6ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ብቅ ያለው የቡድሃ ሃይማኖት ከጊዜ በኋላ የሚያቃጥልና የሚቀዘቅዝ ሲኦል እንዳለ ማስተማር ጀመረ። (ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና፣ 1977፣ ጥራዝ 14፣ ገጽ 68) በኢጣልያ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ሲኦልን ለመግለጽ የተሳሉት ሥዕሎች ከኢትሩስካውያን የተገኙ መሆናቸው ተደርሶበታል።—ላ ቺቪልታ ኢትሩስካ (ሚላን፣ 1979)፣ ወርነር ኬለር፣ ገጽ 389

ይሁን እንጂ የዚህ አምላክን የሚያዋርድ ትምህርት መነሻ ሥር ከዚህም የበለጠ ርቆ ይሄዳል። ሥቃይ ካለበት ሲኦል ጋር የተያያዘው አጋንንታዊ ፅንሰ ሐሳብ የአምላክን ስም የሚያጠፋና ኢየሱስ ክርስቶስ “የሐሰት አባት” ብሎ ከጠራውና የአምላክን ስም ከሚያጠፋው ዋነኛ ስም አጥፊ (ዲያብሎስ ትርጉሙ “ስም አጥፊ” ማለት ነው) የመነጨ ነው።—ዮሐ. 8:44