በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቁርባን

ቁርባን

ፍቺ:- የተቀደሰው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሥርዓተ አምልኮ ጉባኤ እንደ ገለጸው ሥርዓተ ቁርባን “የመስቀል መሥዋዕት ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግ መሥዋዕት፣ ‘ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት’ ላለው ጌታ ሞትና ትንሣኤ መታሰቢያ ነው። (ሉቃስ 22:19) የአምላክ ሕዝቦች የጌታን ሥጋና ደም በመቀበል የፋሲካ መሥዋዕት የሚያስገኘውን ጥቅም የሚካፈሉበት፣ አምላክ ለአንዴና ለዘላለም በክርስቶስ ደም አማካይነት ከሰው ልጆች ጋር የገባውን አዲስ ቃል ኪዳን የሚያድሱበት፣ በአብ መንግሥት የሚደረገውን የምጽአት ግብዣ በተስፋና በእምነት በመጠበቅ ‘ጌታ እስኪመጣ’ ድረስ ሞቱን የሚናገሩበት ቅዱስ ግብዣ ነው።” (ዩካሪስቲኩም ሚስቴሪዩም፣ ግንቦት 25, 1967) ይህ ሥርዓት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው ራት ላይ አድርጓል ብላ የምታምነውን የሚደግም ሥርዓት ነው።

ቂጣውና ወይኑ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደምነት ይለወጣልን?

ሊቀ ጳጳስ ጳውሎስ 6ኛ ሰኔ 30, 1968 ባወጡት “የእምነት መግለጫ” የሚከተለውን ብለው ነበር። “ጌታ በመጨረሻው ራት ላይ ባርኮ የቀደሰው ቂጣና ወይን ለእኛ ሲል በመስቀል ላይ ወደቀረበው የጌታ ሥጋና ደም እንደተለወጠ ሁሉ ቄሱም ባርኮ የሚቀድሰው ቂጣና ወይን በሰማይ በክብር ዙፋን ላይ ወደተቀመጠው የኢየሱስ ሥጋና ደም እንደሚለወጥ እናምናለን። በተጨማሪም ከቡራኬው በፊትም ሆነ በኋላ ለዓይናችን ያልተለወጠ መስሎ በሚታየው ቂጣና ወይን አማካኝነት የሚገለጠው ምሥጢራዊ የሆነ የጌታ መገኘት እውነተኛ፣ እርግጠኛና ገሃድ የሆነ መገኘት ነው። . . . ይህ ምሥጢራዊ መለወጥ በቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ቁርባን (ትራንሰብስታንሲያሽን ) ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው።” (ኦፊሻል ካቶሊክ ቲቺንግስክራይስት አወር ሎርድ፣ ዊልሚንግተን፣ ኖርዝ ካሮላይና፣ 1978፣ አማንዳ ጂ ዋትሊንግተን፣ ገጽ 411) ቅዱሳን መጻሕፍት ከዚህ እምነት ጋር ይስማማሉን?

ኢየሱስ ይህ ሥጋዬ ነው”፣ ይህ ደሜ ነውሲል ምን ማለቱ ነበር?

ማቴ. 26:26–29:- “ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና:- እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ:- ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ነገር ግን እላችኋለሁ፣ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም።”

“ይህ ሥጋዬ ነው”፣ “ይህ ደሜ ነው” ስለሚሉት አገላለጾች የሚከተለውን ልብ ማለት ይገባል። ሞፋት እንዲህ ይላል:- “ይህ ሥጋዬ ማለት ነው”፣ “ይህ ደሜ ማለት ነው።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) አዓት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። ለፈ “ይህ ሥጋዬን ይወክላል “ይህ ደሜን ይወክላል ” ይላል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ይህ አተረጓጎም በተለያዩ የካቶሊክ ትርጉሞች በቁጥር 29 ላይ ከተገለጸው ሐሳብ ጋር ይስማማል። ኖክስ እንዲህ በማለት ተርጉሞታል:- “በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር አዲስ ወይን እስከምጠጣ ድረስ ከዚህ የወይን ፍሬ ዳግመኛ አልጠጣም።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) በተጨማሪም ኮክ፣ ኒአባ እና ዱዌይ ኢየሱስ በጽዋው ውስጥ የነበረውን መጠጥ “የወይን ፍሬ” ብሎ እንደጠራ አመልክተዋል። ኢየሱስ ይህን የተናገረው “ይህ ደሜ ነው” ካለ በኋላ ነበር።

“ይህ ሥጋዬ ነው”፣ “ይህ ደሜ ነው” የሚሉትን አገላለጾች በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከተሠራባቸው ሌሎች ምሳሌያዊ አነጋገሮች ጋር ማስተያየት ይገባል። ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ”፣ “እኔ የበጐች [ማደሪያ] በር ነኝ”፣ “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ” ብሏል። (ዮሐ. 8:12፤ 10:7፤ 15:1) ከእነዚህ አነጋገሮች አንዳቸውም እንኳን በተአምር መለወጥን አያመለክቱም።

ሐዋርያው ጳውሎስ በ⁠1 ቆሮንቶስ 11:25 (ጀባ ) ላይ ስለ መጨረሻው ራት ሲጽፍ ያንኑ ተመሳሳይ ሐሳብ ትንሽ ለየት ባሉ ቃላት ገልጾታል። ኢየሱስ ስለ ጽዋው “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ . . . የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” ያለውን በቀጥታ በመጥቀስ ፈንታ እንደሚከተለው ብሏል:- “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።” ይህ ማለት ጽዋው በተአምር ተለውጦ አዲስ ቃል ኪዳን ሆነ ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በጽዋው ውስጥ የነበረው አዲሱ ቃል ኪዳን የጸናበትን የኢየሱስ ደም ይወክል ነበር ብሎ መደምደም የበለጠ ምክንያታዊ አይሆንምን?

ኢየሱስ በዮሐንስ 6:53–57 ላይ ያለውን ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?

“ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፣ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፣ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል።”—ዮሐ. 6:53–57

ይህን አነጋገር ቃል በቃል የኢየሱስን ሥጋ መብላትና ደሙንም መጠጣት እንደሚገባቸው እንደሚገልጽ አድርገን መረዳት ይገባናልን? እንዲህ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ አምላክ በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ እንዲጣስ ይሰብክ ነበር ማለት ነው። ሕጉ ማናቸውም ደም እንዳይበላ ይከለክል ነበር። (ዘሌ. 17:10–12) ኢየሱስ ግን ማናቸውም የሕጉ ክፍል እንዳይጣስ አጥብቆ ያስተምር ስለነበር ደም እንዲጠጣ አላስተማረም። (ማቴ. 5:17–19) ስለዚህ ኢየሱስ የተናገረው ፍጹም በሆነው ሰብዓዊ መሥዋዕት በማመን በምሳሌያዊ ሁኔታ ደሙን እንዲጠጡ ነበር።—ከ⁠ዮሐንስ 3:16፤ 4:14⁠ና 6:35, 40 ጋር አወዳድር።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የሞቱን መታሰቢያ እንዲያከብሩ ሳይሆን መሥዋዕቱን የሚያድስ ሥነ ሥርዓት እንዲያከናውኑ ማዘዙ ነበርን?

ዘ ዶኩሜንትስ ኦቭ ቫቲካን 2 እንደሚለው ከሆነ:- “አዳኛችን አልፎ በተሰጠበት በመጨረሻው ራት ላይ የሥጋወደሙን የቁርባን መሥዋዕት አቋቋመ። ይህን ያደረገው የመስቀሉ መሥዋዕት በተደጋጋሚ እንዲቀርብ ሲል ነው። . . .”—(ኒው ዮርክ፣ 1966)፣ በደብልዩ ኤም አቦት የተዘጋጀ፣ ገጽ 154፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቁርባን ‘እውነተኛና ትክክለኛ መሥዋዕት’ የሚቀርብበት ሥርዓት እንደሆነ አድርጋ ትቆጥራለች። . . . ይሁን እንጂ የእኛ እምነት ዋና መሠረት ከጥንት ዘመናት ጀምሮ በሥርዓተ ቁርባን የሚቀርበው መሥዋዕት ትልቅ ዋጋ እንዳለው የሚያምነው ሃይማኖታዊ ወግ ነው።”—(1913)፣ ጥራዝ 10፣ ገጽ 6, 17

ኢየሱስ ራሱ:- “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሏል። (ሉቃስ 22:19፤ 1 ቆሮ. 11:24) ሉቃስ 22:19⁠ን ኖክስ፣ ዱዌይ እና ኒአባ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት ተርጉመውታል። ኢየሱስ በመጨረሻው ራት ላይ ያደረገው የእርሱ መሥዋዕት እንደሆነ ወይም ደቀ መዛሙርቱ መሥዋዕቱን በየጊዜው እንዲያድሱ አልተናገረም።

ዕብ. 9:25–28:- “[እንደ አይሁዶች] ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፣ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን . . . ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል። ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፣ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፣ . . . አንድ ጊዜ [ተሠዋ።]” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።)

“ነገሩ ለመረዳት የማይቻል ጥልቅ ምሥጢርነውን?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መለኮታዊ ምሥጢሮች ወይም ቅዱስ ምሥጢሮች ይናገራል። ነገር ግን ከእነዚህ መካከል አንዱም እንኳ ቢሆን በግልጽ ከቀረቡት ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች ጋር የሚጋጭ አይደለም። ከቅዱሳን መጻሕፍት ይልቅ ወጎቻቸውን አስበልጠው ይከተሉ ስለነበሩት ሰዎች ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “እናንተ ግብዞች፣ ኢሳይያስ ስለ እናንተ:- ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፣ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ።”—ማቴ. 15:7–9

ኢየሱስ ይህ መታሰቢያ በየቀኑ ወይም በየሳምንቱ እንዲከበር አስቦ ነበርን?

ቤዚክ ካቴኪዝም የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ካቶሊክ ክርስቲያኖች በየሳምንቱ እሑድና በበዓል ቀናት በሚፈጸመው ሥርዓተ ቁርባን ላይ የመገኘት ግዳጅ አለባቸው።” (ቦስተን፣ 1980፣ ገጽ 21) “ታማኝ ምዕመናን ሁሉ እንዲያስቆርቡና አዘውትረው እንዲያውም በየቀኑም እንኳ ቢሆን ሥጋወደሙን እንዲቀበሉ እናበረታታለን።”—ዘ ቲቺንግ ኦቭ ክራይስትኤ ካቶሊክ ካቴኪዝም ፎር አደልትስ፣ በአጭሩ የተዘጋጀ (ሁንቲንግ፣ ኢንዲያና፣ 1979)፣ ገጽ 281

በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ‘እንጀራ ስለመቁረስ’ የሚናገሩት ጥቅሶች በሙሉ ስለ ክርስቶስ ሞት መከበር የሚገልጹ ናቸውን? (ሥራ 2:42, 46፤ 20:7) ኢየሱስ ከመጨረሻው ራት በፊት እንኳ ምግብ በሚቀርብበት ጊዜ ‘እንጀራን ቆርሶ’ ይሰጥ ነበር። (ማር. 6:41፤ 8:6) አይሁዳውያን በዚያን ጊዜ ይበሉት የነበረው እንጀራ ዛሬ በብዙ ሰዎች ዘንድ የታወቀው ዓይነት አይደለም። ብዙውን ጊዜ ምግብ በሚበሉበት ወቅት እንጀራ ወይም ደረቅ ያለ ስስ ቂጣ እየቆረሱ ይበሉ ነበር።

ኢየሱስ የሞቱ መታሰቢያ ምን ያህል ጊዜ መከበር እንዳለበት ገልጾ አልተናገረም። ይሁን እንጂ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ያቋቋመው የአይሁዳውያን የማለፍ በዓል በሚከበርበት ቀን ላይ ነው። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ይህን የአይሁዳውያን የማለፍ በዓል በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ተክተዋል። የማለፍ በዓል የሚከበረው በየዓመቱ ኒሳን 14 ቀን ነበር። በተመሳሳይም የአይሁድ የቂጣ በዓል፣ የሣምንታት (የጰንጠቆስጤ) በዓል፣ የዳስ በዓል እና የሥርየት ቀን ይከበሩ የነበሩት በዓመት አንድ ጊዜ ነበር።

የቁርባን ሥርዓት በሚከናወንበት ጊዜ የሚቀርበው ጸሎት በመንጽሔ ያሉትን ነፍሳት ነፃ ያወጣቸዋልን?

ዘ ቲቺንግ ኦቭ ክራይስትኤ ካቶሊክ ካቴኪዝም ፎር አደልትስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “‘መንጽሔ’ የሚለው ቃልም ሆነ ትምህርቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። . . . የአበው መጻሕፍት ግን መንጽሔ መኖሩን ብቻ ሳይሆን በመንጽሔ ውስጥ ያሉ ምዕመናን ሕያዋን በሚያቀርቡት ጸሎትና በተለይም በቁርባን መሥዋዕት ሊረዱ እንደሚችሉ ይገልጻሉ።”—ገጽ 347, 348

ሙታን የሚገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲህ ይላሉ:- “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉ፣ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም።” (መክ. 9:5) “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ [“ነፍስ” ኖክስ፤ “ሰው” ጀባ ] እርስዋ ትሞታለች።” (ሕዝ. 18:4) (በተጨማሪ በገጽ 99–101 ላይ “ሞት” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።)