በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቅዱሳን

ቅዱሳን

ፍቺ:- በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት መሠረት የሞቱና አሁን ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገኙ፣ በከፍተኛ ጽድቃቸውና ቅድስናቸው የቤተ ክርስቲያንን እውቅና ያገኙ ሰዎች ናቸው። በትሬንት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ የተላለፈው የእምነት መግለጫ ቅዱሳንን ከአምላክ ጋር እንዲያማልዱ መለማመንና የቅዱሳንን ምስሎችና የድሮ ዕቃዎች እንደ ቅዱስ አድርጎ ማክበር ተገቢ መሆኑን ይገልጻል። ሌሎች ሃይማኖቶችም የቅዱሳንን እርዳታ ለማግኘት ይጸልያሉ። አንዳንድ ሃይማኖቶች ደግሞ አባሎቻቸው በሙሉ ቅዱሳን እንደሆኑና ከኃጢአት የነጹ እንደሆኑ ያስተምራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች ስለ ቅዱሳን ይናገራል። በመንፈስ የተቀቡት 144,000ዎቹ የክርስቶስ ተከታዮችም ቅዱሳን እንደሆኑ ይናገራል።

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ቅዱስ ሆኖ ከመቆጠሩ በፊት ሰማያዊ ክብር ማግኘት እንደሚኖርበት ያስተምራልን?

መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ ስላሉ ቅዱሳን እንደሚናገር አይካድም። ይሖዋ “ቅዱስ [በግሪክኛ ሐጊዎን ]” እንደሆነ ተነግሯል። (1 ጴጥ. 1:15, 16፤ ዘሌዋውያን 11:45⁠ን ተመልከት።) ኢየሱስ ክርስቶስም በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ “የእግዚአብሔር ቅዱስ [ሐጊዎስ ]” እንደነበረና በሰማይም “ቅዱስ [ሐጊዎስ ]” እንደሆነ ተገልጿል። (ማር. 1:24፤ ራእይ 3:7) መላእክትም “ቅዱሳን” ናቸው። (ሥራ 10:22) ይኸው የጥንት የግሪክኛ ቃል በምድር ላይ ይኖሩ ለነበሩ በርካታ ሰዎችም አገልግሏል።

ሥራ 9:32, 36–41:- “ጴጥሮስም በየስፍራው ሁሉ ሲዞር በልዳ ወደሚኖሩ ቅዱሳን [ሐጊዎስ ] ደግሞ ወረደ። በኢዮጴም ጣቢታ የሚሉአት አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፣ [ሞተችም፤] . . . [ጴጥሮስ] ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ ጣቢታ ሆይ፣ ተነሺ አላት። እርስዋም ዓይኖቿን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች። እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና መበለቶችንም ጠራ ሕያውም ሆና በፊታቸው አቆማት።” (እነዚህ ቅዱሳን ገና ወደ ሰማይ የሄዱ እንዳልነበሩ ግልጽ ነው። በተጨማሪም ቅዱሳን ይባሉ የነበሩት እንደ ጴጥሮስ የመሰሉ ታዋቂ ግለሰቦች ብቻ አልነበሩም።)

2 ቆሮ. 1:1፤ 13:12:- “በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ወንድሙም ጢሞቴዎስ፣ በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን [ሐጊዎስ ] ሁሉ ጋር በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን።” “በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።” (እነዚህ በክርስቶስ ደም የነጹና የክርስቶስ ተባባሪ ወራሾች የመሆን ተስፋ ተሰጥቷቸው ለአምላክ አገልግሎት የተለዩ ክርስቲያኖች ቅዱሳን ተብለው ተጠርተዋል። ቅዱሳን ተብለው የተጠሩት ከሞቱ በኋላ አልነበረም።)

 “ቅዱሳን” ከአምላክ ጋር እንዲያማልዱን መጸለይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው ነውን?

ኢየሱስ ክርስቶስ:- “እናንተስ እንዲህ ጸልዩ:- በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ . . .” ብሏል። ስለዚህ ጸሎት የሚቀርበው ለአብ ነው። ኢየሱስም:- “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሏል። (ማቴ. 6:9፤ ዮሐ. 14:6, 14) ስለዚህ ኢየሱስ ከሱ በስተቀር ሌላ አማላጅ ሊኖር እንደማይችል ገልጿል። ሐዋርያው ጳውሎስም በመጨመር ስለ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል:- “የሞተው፣ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፣ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።” “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና።” (ሮሜ 8:34፤ ዕብ. 7:25) ጸሎታችን በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት እንዲያገኝ የምንፈልግ ከሆነ አምላክ ራሱ በቃሉ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ልንቀርበው አይገባንምን? (በተጨማሪም ገጽ 258 ላይ “ማርያም” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።)

ኤፌ. 6:18, 19:- “ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤ ደግሞም የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (እዚህ ላይ የተሰጠው ምክር ስለ ቅዱሳን እንድንጸልይ እንጂ ቅዱሳን ወይም ቅዱሳን በኩል እንድንጸልይ አይደለም። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ፣ 1967፣ ጥራዝ 11፣ ገጽ 670 እንዲህ ይላል:- “በአዲስ ኪዳን ውስጥ ማንኛውም ጸሎት የግልም ሆነ ሕዝባዊ ምህላ ይቀርብ የነበረው በክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ነበር።”)

ሮሜ 15:30:- “ወንድሞች ሆይ፣ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር እየጸለያችሁ ከእኔ ጋር ትጋደሉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ፍቅር እለምናችኋለሁ።” (ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ ቅዱስ ሲሆን ቅዱሳን የሆኑት ክርስቲያን ባልንጀሮቹ እንዲጸልዩለት ጠይቋል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ የጸለየው ወደ እነዚህ ቅዱሳን ባልንጀሮቹ አልነበረም። እነርሱም ቢሆኑ ስለ ጳውሎስ የሚያቀርቡት ጸሎት ጳውሎስ ራሱ ከአብ ጋር በጸሎት አማካይነት ያደርግ ለነበረው የቅርብ ግንኙነት ምትክ አልሆነም። ከ⁠ኤፌሶን 3:11, 12, 14 ጋር አወዳድር።)

‘የቅዱሳንን’ ምስሎችና ድሮ ይጠቀሙባቸው ነበር የሚባልላቸውን ዕቃዎች ቅዱስ አድርጎ ስለማክበር እንዴት ያለ አመለካከት ሊኖር ይገባል?

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ ሐቁን በመቀበል እንዲህ ይላል:- “በብሉይ ኪዳን ውስጥ የቅዱሳንን የድሮ ዕቃዎች እንደ ቅዱስ ነገር ቆጥሮ ስለማክበር ድጋፍ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ከንቱ ነው። በአዲስ ኪዳንም ውስጥ ቢሆን የቅዱሳንን ጥንታውያን ዕቃዎች ስለማክበር የተሰጠ ምንም ዓይነት ሐሳብ የለም። . . . ኦሪገን የተባለው [የቤተ ክርስቲያን “አባት”] እንዲህ ያለውን አድራጎት አረማውያን ለቁሳዊ ነገሮች ከሚሰጡት አክብሮት ያልተለየ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተው ነበር።”—(1967)፣ ጥራዝ 12፣ ገጽ 234, 235

አምላክ ሙሴን እንደቀበረውና ማንም ሰው የተቀበረበትን ቦታ አግኝቶ እንደማያውቅ መገንዘብ ተገቢ ነው። (ዘዳ. 34:5, 6) ይሁን እንጂ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ስለ ሙሴ ሥጋ ከዲያብሎስ ጋር እንደተከራከረ ይሁዳ 9 ይገልጻል። የተከራከረው ለምን ነበር? አምላክ የሙሴን ሥጋ ማንም ሰው ሊያውቀው በማይችል መንገድ እንዲወገድ ያደረገበት ምክንያት ግልጽ ነው። ይህ ጠላት የሙሴ ሥጋ ለሰዎች በሚታይ ቦታ ተቀምጦ እንዲመለክ ፈልጎ ይሆንን?

“የቅዱሳንን” ምስል ስለማክበር “ምስሎች” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

የካቶሊክ “ቅዱሳን” አክሊለ ብርሃን ተደርጎላቸው የሚሳሉት ለምንድን ነው?

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ይላል:- “በሁሉም የቅዱሳን ሥዕል ላይ የሚታይ የጋራ ባሕርይ በቅዱሳኑ ራስ ዙሪያ ያለው በተወሰነ ቅርፅ የሚሳል ብርሃን ወይም ደመና ነው። ይህም የመጣው ከክርስትና ዘመን በፊት ይሳሉ ከነበሩ ሄለናዊ የአረመኔ ሥዕሎች ነው። በሞዛይኮችና በሳንቲም ገንዘቦች ላይ እንደታየው አክሊለ ብርሃን የሚሳለው እንደ ኔፕቱን፣ ጁፒተር፣ ባኩስ ባሉት አማልክትና በተለይ አፖሎ (የፀሐይ አምላክ) በተባለው አምላክ ራስ ዙሪያ ነው።”—(1967)፣ ጥራዝ 12፣ ገጽ 963

ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “በግሪካውያንና ሮማውያን ሥነ ጥበብ ሄሊዮስ በተባለው የፀሐይ አምላክና በሮማውያን ንጉሠ ነገሥቶች ራስ ላይ የብርሃን አክሊል ይሳል ነበር። ይህ ዓይነቱ አሳሳል ከአረመኔዎች የተገኘ በመሆኑ በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ሥዕሎች ላይ አይሳልም ነበር። ክርስቲያን ንጉሠ ነገሥቶች ግን በራሳቸው ዙሪያ ስስ ደመና እንዲሳል ማድረግ ጀመሩ። ከ4ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ አንስቶ ክርስቶስን በዚህ ንጉሣዊ አሳሳል መሳል ተጀመረ። . . . ድንግል ማርያምና ሌሎቹ ቅዱሳን በሥዕላቸው ላይ አክሊለ ብርሃን የተደረገው ከ6ኛው መቶ ዘመን በኋላ ነው።”—(1976)፣ ማይክሮፔድያ፣ ጥራዝ 4፣ ገጽ 864

ክርስትናን ከአረማዊ ምልክቶች ጋር መቀላቀል ተገቢ ነውን?

“ብርሃንም ከጨለማ ጋራ ምን ኅብረት አላው? ክርስቶስስ ከቤልሆር [ከቤላያል፤ ከሰይጣን] ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? . . . ስለዚህም ጌታ:- ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኩስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ:- እኔም እቀበላችኋለሁ፣ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል።”—2 ቆሮ. 6:14–18

የአንድ ሃይማኖታዊ ቡድን አባሎች በሙሉ ከኃጢአት የነፁ ቅዱሳን ሊሆኑ ይችላሉን?

የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ አባሎች በሙሉ ቅዱሳን የነበሩ መሆናቸው እውነት ነው። (1 ቆሮ. 14:33, 34፤ 2 ቆሮ. 1:1፤ 13:13) “የኃጢአት ሥርየት” የተደረገላቸውና አምላክ ‘የቀደሳቸው’ እንደሆኑ ተገልጿል። (ሥራ 26:18፤ 1 ቆሮ. 1:2) ይሁን እንጂ ከማንኛውም ኃጢአት የነፃን ነን የሚል አቋም አልነበራቸውም። የኃጢአተኛው አዳም ዘሮች ነበሩ። ይህ የኃጢአት ውርሻ ስለነበረባቸው ሐዋርያው ጳውሎስ በትሕትና ስለራሱ እንደተናገረው ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ በውስጣቸው ትግል ነበረባቸው። (ሮሜ 7:21–25) ሐዋርያው ዮሐንስም በማያሻማ መንገድ “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” ብሏል። (1 ዮሐ. 1:8) ስለዚህ ቅዱስ መሆን ቃሉ በክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ላይ ባለው ትርጉም መሠረት ከኃጢአት ሁሉ ነፃ መሆንን አያመለክትም።

ዛሬ ያሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉ የሰማያዊ ሕይወት ተስፋ ያላቸው ስለመሆናቸውና አለመሆናቸው ገጽ 164–168⁠ን ተመልከት።

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘በቅዱሳን ታምናለህ?’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘የትኞቹን ቅዱሳን ማለትዎ ነው?’ ሰውዬው ማርያምን ወይም ሐዋርያትን ከጠቀሰ የሚከተለውን ማለት ትችላለህ:- (1) ‘አዎ፣ እነሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰዋል። እኔ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ አምናለሁ። ይሁን እንጂ በይበልጥ የሚያሳስበኝ ነገር በአሁኑ ጊዜ ምን በማድረግ ላይ የሚገኙ መሆናቸውና ይህ በእኛ ላይ የሚኖረው ውጤት ነው። አይመስልዎትም? . . . ስለ እነዚህ ቅዱሳን በዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ጥሩ ነጥብ አግኝቻለሁ። ለእርስዎም ባካፍልዎት ደስ ይለኛል። (ራእይ 5:9, 10)’ [ማስታወሻ:- በእንግሊዝኛ በጥቅሱ አባባል ላይ ጥያቄ ከተነሣ ቀጥሎ ባለው ሐሳብ መጠቀም ይቻላል:- ጀባ “ዓለምን ይገዛሉ” ይላል። ኮክ “በምድር ላይ ይገዛሉ” ይላል። ኖክስ ደግሞ “በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ” ሲል ይገልጻል። ኒአባ እና ዱዌይ ግን “በምድር ላይ ሆነው ይገዛሉ” ይላሉ። በግሪክኛው ሰዋስው ላይ የተሰጠውን ሐሳብ “ሰማይ” በሚለው ሥር በገጽ 168 ላይ ተመልከት።] (2) ‘እንዲህ ባለው መስተዳድር ሥር ሕይወት ምን ይመስል ይሆን? (ራእይ 21:2–4)’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ (በፊት ካቶሊክ ከነበርክ):- ‘ለብዙ ዓመታት የቅዱሳንን በዓላት አከብርና ለእነርሱም እጸልይ ነበር። ግን በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አደርግ ስለነበረው ነገር እንድመረምር ያደረገኝ ጥቅስ አገኘሁ። እስቲ ላሳይዎት። ( ገጽ 352⁠ን ተመልከት።)’